Thursday, June 28, 2012

የእግር ኳስ ነገር


(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- በዚህ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ሰሞን ስለዚህ ታላቅ ስፖርት አለመጨዋወት ትክክል ስላልመሰለኝ “ነገረ ኳስ”ን የዚህ ጽሑፌ ርዕሰ ጉዳይ ለማድረግ አሰብኩ። እግር ኳስ ብዙም በማይታወቅበት በአሜሪካ ሆኖ ስለ እግር ኳስ ማውራት ብዙም ባይመችም በዓይነ ኅሊናዬ የልጅነት የኳስ ፍቅራችንን እያሰብኩ አንዲቱን የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ገጽ የምትሞላ ትውስታ ለመቆፈር ወደድኩ።

ሰሞኑን በእኩለ ቀን የአውሮፓን እግር ኳስ ብቻዬን እኮመኩማለኹ። የሰዓት ልዩነቱ እነርሱ ጋር መሸትሸት ሲል እኛ ዘንድ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል አካባቢ ይሆናል፤ ያን ጊዜ እንጀምራለን። ኳስ በቀን ማየት ይደብረኛል። ቲቪ ለማየት መሸት ሲል ነው ደስ የሚለው። ቀን ለሥራ ነው የሚመቸው። ደግሞም እግር ኳስና የደቦ ሥራ ከሰው ጋር ሲሆኑ እንጂ ለብቻ አይሄድም። ቢሆንም እግር ኳስ፣ ያውም የአውሮፓ ዋንጫ ነውና ምን ይደረጋል። ብቻዬን ያውም በእኩለ ቀን አየዋለኹ።

እንዲያው “እግር ኳስን እግር ኳስ ያነሣዋልና” (ነገርን ነገር ያነሣዋልና እንዲሉ ጋዜጠኞች) የአውሮፓ ዋንጫን መቼ ማየት እንደጀመርኩ ባላስታውስም የዓለም ዋንጫን ግን በቡና ቤት መስኮት እየተንጠለጠልን ለማየት ስንሞክር ትዝ ይለኛል። ሕጻናቱን ማን ከሰው ቆጥሮ ያስገባናል? ደግሞስ ያን ጊዜ ቴሌቪዥን ቡና ቤት ላላቸው ሰዎች እንጂ ለግለሰቦች የሚፈቀድ አይመስለኝም ነበር። ኋላ ኋላ ቀበሌው ሁሉ ቲቪ በቲቪ ሆነና አገሩን አሳረፈው። አሁን ደግሞ ዘመን ተለውጦ ባለ ሳተላይቱ ጣቢያ ገባና ሰው ሁሉ እግር ኳስ ወዳድ ሆነ። እንዲያውም ወደ አሜሪካ ብቅ ያለ ወዳጄ ስለ እግር ኳስ ሲያወራ ሰምቼው “አንተም? ከመቼ ወዲህ?” ብለው “እንዲህ ሆንኩ እኮ፤ ማንቼ፣ አርሴናል፣ ሜሲ፣ ሆኛለሁ” ብሎ አሳቀኝ። እርሱ ወዳጄ ኳስ ከወደደ መቼም አገሩ ሁሉ ኳስ ማየት ጀምሯል ማየት ነው ብዬ ደመደምኩ። ድሮ “አንድ ኳስ ብቻ ከሚያባርሩ ለምን ሌላም አይጨመርላቸውም?” የሚል ዓይነት ልጅ ነበረ።

“የኔ ይገርምኻል እንዴ? እንዲያውም የአርሴና፣ ማንቼ (የማንቸስተር ዩናይትድ) ደጋፊ እየተባባሉ ይደባደባሉ” ሲለኝ “የኛ ነገር፤ መቸም ሁል ጊዜ ዋናውን ቁም ነገር ሳይሆን ጦርነት ያለበትን ክፍል ኮፒ ማድረግ ይቀናናል” ብዬ አሳቅኹት። አሁን ካልጠፋ ነገር ጥበባቸውን ኮፒ ማድረግ ሲቻል ድብድባቸውን ፈልጎ መቆንጠር ምን ይባላል? አሁን አሁን እንግሊዞቹ ራሳቸው “ተደባደቡ” ሲባል አልሰማኹም። “ፉትቦል ሁሊጋኒዝም” ጣራ ነክቶ የነበረበት ጊዜ አልፎ አሁን ለጥቁር ተጫዋች ሙዝ መወርወር የጀመሩት በቅርቡ ከኮሚኒዝም “እስር ቤት” የወጡት እንደ ራሺያ ያሉ ነጻነትን በቅጡ ያልተለማመዱ አገሮች ናቸው እንጂ እንግሊዞቹ አይደሉም። እንደ እባብ ጭንቅል-ጭንቅላታቸውን ከሚቀጠቅጥ መንግሥት ተላቀው የራሳቸውን ነጻነት አስከብረው የሰውንም አክብረው መኖር ስላልለመዱ ጥቁር ሁሉ ዝንጀሮ ይመስላቸዋል። አለማወቅ።

Ian Rush

የእንግሊዝ ፉትቦል ማየት ስጀመር ሊቨርፑል ዝነኛ ክለብ ነበር። (ዕድሜ መቁጠር እናቁማ!!) የሊቨርፑሎቹ ኢያን ራሽ እና ጆን ባርነስ (Ian Rush እና John Barnes) ሲጫወቱ ልክ እንደ ራሺያ ፊልሞች “ፊክሽን” እንጂ የእውነት ተጫዋቾች አይመስሉኝም ነበር። በየሳምንቱ ቅዳሜ ወደ ማታ ላይ ሽማግሌ እንግሊዛዊ የስፖርት አቅራቢ በቄንጠኛ አቀማመጡ ቁጭ ብሎ ያለፉ ጨዋታዎችን ሲተርክ እና በየመካከሉ ጨዋታዎቹን ብቅ ሲያደርግ የልጅ ልባችን ጥፍት ….. ትል ነበር። በተለይም ከጀማይካ ቤተሰቦች ተወልዶ ኳስን በነጮቹ እንግሊዞች መካከል የሚያሽሞነሙናት ባለ ግራ እግሩ ባርነስ ጨዋታው አሁንም አይረሳኝም።

በነጋታው እኛም የቤት ካልሲ፣ የሰፈር ላስቲክ አይተርፈንም። የጨርቅ ኳሳችንን ሰርተን ሜዳ ነን። ጠዋት የወጣን ምሳም ትዝ ሳይለን የሚገላግለን ወይ ዝናብ ወይ ጨለማ ነው። ደግመን በጠዋት ልንገናኝ። ደግነቱ የሜዳ ችግር አልነበረብንም። እንዳሁኑ የሰው መላጣ ሳይቀር ፎቅ ካልሠራንበት በማይባልበት ጊዜ ሜዳው ሁሉ የኛ ስታዲየም ነበር። ልጅ ሆኖ ሜዳ የሚቸግረው ያለ አይመስለኝም ነበር።

በዚያ የኳስ ፍቅራችን በስንት ጊዜ አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ቡድን ይጫወታል ተብሎ በራዲዮ የሚተላለፈው እንደነ ሊቨርፑል ዋንጫ በዋንጫ ስለማይሆን የሕጻን ቆሽታችን እርር ድብን ትላለች። ቆይቶ ቆይቶ የምሥራቅና መካከለኛውን አፍሪካ ዋንጫ “ገብርኤል በዕለተ ቀኑ” (እናቴ እንዳለችው) ከዚምባቡዌ ጉድ አውጥቶ ዋንጫ ሲሰጠን መቸም ደስታችን ወደር አጣ። ደምሴ ዳምጤ “ዳኙ ገላግሌ …” ሲል። ቢሆንም ከአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከወጣን 30 ዓመት ሆነን።

እንዲህ ያለው የአውሮፓ ዋንጫ ሰሞን በሰው አገር ያለነውን ከልጅነት የኳስ ፍቅራችን አንስቶ ያለውን ትዝታ እየጎተተ መምጣቱ አይቀርም። ጭል ጭል በምትል ቲቪ ከአንድ ቀበሌ ሕዝብ ጋር እናየው የነበረውን ጨዋታ ትልቅ መስኮት በሚያክል “HD” (ሃይ ዴፊኒሽን) ቲቪ እያዩትም ጣዕሙ እንደ ድሮው አይሆንም ልበል?

በቲቪ ሲታይ ደስ ከሚለኝ ነገር አንዱ የሕዝብ መዝሙር ሲዘመር ያለው የተጫዋቹም የተመልካቹም ስሜት እና የባንዲራ ብዛት ነው። “አገር” የሚባለው ነገር ምን ዓይነት ምትሐታዊ ስሜት እንዳለው እና እንደሚፈጥር ማሳያ ነው። በተለይም ጥንታውያን የሆኑ አገሮች አርበኝነታቸው በሕዝብ መዝሙራቸው ወቅት ግልጽ ብሎ ይታያል። ጣሊያኖቹ (Il Canto degliItaliani The Song of the Italians) እና እንግሊዞቹ “God Save the Queen” ሲሉ ማየት ራሱ አንድ ትርዒት ነው። ጀርመኖቹ ነበሩ (Das Deutschlandlied (Song of Germany)) ሲባል ለብዙ ጊዜ ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት የሚቸገሩት። ነገሩ የገባኝ ደግሞ እነርሱ አገር ስኖር ነው።

የጀርመኖች አገር ፍቅር ብዙ ጊዜ ግድቡን እየጣሰ የሌላ አገር መብላት ልማዱ ነበር። ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ከእነርሱ ጋር የተገናኙ ከመሆናቸውም በላይ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች እና የሌሎች አገር ዜጎች የተጨፈጨፉት ከጀመርን በተነሡት ናዚዎች መሆኑ የጀመርኖችን እዩኝ እዩኝ የሚል የአርበኝነት ስሜት ሌላው ዓለም በበጎ አይመለከትላቸውም። እነርሱም ብዙም አያሳዩም። በዚያ ከብረት በጠነከረ ገጻቸው አፍነው ያስቀሩታል።

የ2006 የዓለም ዋንጫ በጀርመን ሲዘጋጅ እዚያው ነበርኩኝ። አሰልጣኙ የርገን ክሊንስማን (Jurgen Klinsmann) የቡድኑን አጨዋወት ብቻ ሳይሆን አጠቃላዩን የአርበኝነት ስሜታቸውን ጤናማ በሆነ መልኩ እንደቀየረው ሲናገሩ ሰምቻለኹ። ወጣቶቹ “ጀርመን ጀርመን” ማለትን “ናዚ ናዚ” ከማለት ለይተው “ጀርመን ጀርመን” ማለታቸውንም ሌላው “ናዚ ናዚ” ከማለት ጋር ያነጻጽርብናል ማለትንም በድፍረት አልፈው የወጡበት ጊዜ ነበር። ምናልባትም በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀርመንን የእግር ኳስ ቡድን የደገፍኩት ያን ጊዜ ነው። ንፁህ እግር ኳስ፣ ማራኪ ጨዋታ ሲያሳዩ። ጣዕም በሌለው ጨዋታ የዓለም ዋንጫን ከሚበሉ በዚያ ግሩም ጥበብ ሦስተኛ ሲወጡ ሕዝባቸው ቅር ያለው አይመስልም ነበር።

እናም እግር ኳስና አርበኝነት አብረው ይሄዳሉ የምለው ለዚህ ነው። ስፖርት መገንባት እግረ መንገዱን አገራዊ ስሜትን (አርበኝነትን) መገንባት፣ ጤናማ ትውልድን መፍጠር ነው። ስፖርት የሚጠላ መሪ፣ በቆሎ በመዝራት ብቻ የሚያምን መንግሥት አገር ያጠፋል። ትውልድ ይገድላል። ለምሳሌ ኢትዮጵያን ብንመለከት በኦሎምፒክ ባንዲራችን ሲውለበለብ የሚፈጠሩ ስሜቶች ብዙ ወጣት ትውልድ ኢትዮጵያዊነቱን በጽኑዕ መሠረት ላይ እንዲያቆም ይረዳዋል። ስፖርተኞቹ ለአገራቸው የዋሉት ውለታ ታላቅ የሚሆነው ከዚህም አንጻር ስለሚታይ ነው። ስፖርተኞች ብዙ ፖለቲከኞች የሚያበላሹትን ጥፋት የሚያስተካክሉ አራሚዎች ናቸው። አላዋቂ ፖለቲከኛ በሕዝብ መካከል የሚቀብረውን መርዝ ስፖርተኞች እና ጥሩ መምህራን ናቸው የሚፈውሱት - የሚመስለኝ። የኃይሌ እና የደራርቱ ዕንባዎች።

ሉሲዎቹ

ባለፈው እሑድ ኢትዮጵያ ቡድን ከቤኒን አቻው ጋር ሲጫወት በኮምፒውተር መስኮት ስመለከተው ይህንን ሐሳብ በድጋሚ አጫረብኝ። የሴቶቹ ቡድን ከአገሩ ወጥቶ፣ በሌላ አገር ተጫውቶ ማሸነፉ በስፖርቱም ብቻ ሳይሆን በሌላውም ሕብረተሰባዊ ግንኙነት ኢትዮጵያውያን በራስ መተማመናችን እንዲያድግ ያደርገዋል ብዬ አስባለኹ። ከራሳችን ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ጋር መወዳደርን፣ ማሸነፍን፣ ስማችንን ማደስን የምንጀርው በዚህ በዚህ ነው። ዋልያዎቹም፣ ሉሲዎቹም በርቱ!!!

የኳስ ነገር ለዛሬ በዚህ ተፈጸመ።

 

  

 

 

 

 

 

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::
    

12 comments:

Anonymous said...

የኳስ ነገር ለዛሬ በዚህ ተፈጸመ።
Regular time playing foot ball 90 Min
Regular time for American President 4 year
Regular time for Ethiopia Government!!!!!!Unlimited …Why!!!! High Definition Government playing to destroy Ethiopia!!!!! ሃይ ዴፊኒሽን) ቲቪ “Government “ እያዩትም ጣዕሙ እንደ ድሮው አይሆንም ልበል?
የኢትዮጵያ ነገረ!!!!!!
Long man the Minnesota

Anonymous said...

you brought back may childhood memories.it was a wonderful article!!may God bless you

Anonymous said...

you brought back my childhood memories back.i really appreciate the way you wrote the article !!

Anonymous said...

You brought back my childhood memories.it was such a nice article!God bless you!

Anonymous said...

THATS GOOD AND LET US RETRIVE OUR MEMORIES
THANK YOU EF

Anonymous said...

ስፖርት መገንባት እግረ መንገዱን አገራዊ ስሜትን (አርበኝነትን) መገንባት፣ ጤናማ ትውልድን መፍጠር ነው። ስፖርት የሚጠላ መሪ፣ በቆሎ በመዝራት ብቻ የሚያምን መንግሥት አገር ያጠፋል። ትውልድ ይገድላል።

Anonymous said...

d ephrem tiru nebab new!thankyou i was expect you are going to say about ethiopian sport federation in usa.the just devided by two..any way

Anonymous said...

እንዳሁኑ የሰው መላጣ ሳይቀር ፎቅ ካልሠራንበት በማይባልበት ጊዜ ሜዳው ሁሉ የኛ ስታዲየም ነበር።..lol

Anonymous said...

ኳስ በሰፈራችን ድም ሲል ምሳዪን ከመብላት አቋርጨ የወጣሁትን አስታወሰኝ
ለካስ ፍራሽ እያራገፉ ነበር

mamit said...

በነጋታው እኛም የቤት ካልሲ፣ የሰፈር ላስቲክ አይተርፈንም። የጨርቅ ኳሳችንን ሰርተን ሜዳ ነን። ጠዋት የወጣን ምሳም ትዝ ሳይለን የሚገላግለን ወይ ዝናብ ወይ ጨለማ ነው። ደግመን በጠዋት ልንገናኝ። ደግነቱ የሜዳ ችግር አልነበረብንም። እንዳሁኑ የሰው መላጣ ሳይቀር ፎቅ ካልሠራንበት በማይባልበት ጊዜ ሜዳው ሁሉ የኛ ስታዲየም ነበር። ልጅ ሆኖ ሜዳ የሚቸግረው ያለ አይመስለኝም ነበር።

mamit said...

በነጋታው እኛም የቤት ካልሲ፣ የሰፈር ላስቲክ አይተርፈንም። የጨርቅ ኳሳችንን ሰርተን ሜዳ ነን። ጠዋት የወጣን ምሳም ትዝ ሳይለን የሚገላግለን ወይ ዝናብ ወይ ጨለማ ነው። ደግመን በጠዋት ልንገናኝ። ደግነቱ የሜዳ ችግር አልነበረብንም። እንዳሁኑ የሰው መላጣ ሳይቀር ፎቅ ካልሠራንበት በማይባልበት ጊዜ ሜዳው ሁሉ የኛ ስታዲየም ነበር። ልጅ ሆኖ ሜዳ የሚቸግረው ያለ አይመስለኝም ነበር።

Anonymous said...

እንኳንም የሊቨርፑልን እግር ኳስ ጨዋታ እያየህ አደክ፡፡ያንን ቡድን አይተህ ዛሬ ላይ ያለዉን ቡድን ስታይ ያ ጥንካሬዉ የት ገባ ልትል እንደምትችል እገምታለሁኝ፡፡እኔ ሊቨርፑል በዱሮ ዘመን ምን አይነት ክለብ እንደነበር መመስከር ባልችልም ደጋፊዎቹ/ስታዲየም ዉስጥ ገብተዉ የሚደግፉት/ የሚያስተምሩኝ ነገር ስላለ ዛሬ በዘመኔ ጨዋታዎቹን እከታተላለሁ፡፡ደጋፊዎቹ መንፈሰ ጠንካራ ናቸዉ፤እያንዳንዷ ደቂቃ እና ሴኮንድ ለእነርሱ ዋጋ አላት፡፡በእነርሱ አገር የጊዜ እጥረት ለክለባቸዉ ሲሉ ደጋፊዎቹ ሙሉ 90 ደቂቃ፤ጨዋታዉም ካላለቀ ከዚያ በላይ ስታዲየሙን በጩኸት ያናጉታል፡፡ሊቨርፑል ጎል ካገባ እሰየዉ ደጋፊዎቹ ይጮሃሉ፤ካላገባም እንዲያገባ ይጮሃሉ እንጂ እንደሌላዉ ክለብ ደጋፊ ስታዲየሙን ለቀዉ አይወጡም፡፡ከሊቨርፑል ደጋፊዎች ታማኝነትን፤ ጽናትን፤ ተስፋን፤ መተባበርን----ትመለከትበታለህ፡፡ዋንጫ ካነሳ/የፕሪሚየር ሊጉን/20 ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም ደጋፊዎቹ አንድ ቀን ክለባቸዉ ያንን እንደሚያሳካዉ በመተማመን ዘወትር ተጫዋቾቹን አይዞአችሁ ከጎናችሁ ነን/you never walk alone/እያሉ ያበረታቱዋቸዋል፡፡የኮፕሶች ደጋፊም ሆነ አድናቂ መሆን ትልቅ ኩራት ነዉ፡፡(ዉብሸት)