Saturday, July 7, 2012

አንድ-ትልቅ ወይስ ብዙ-ትንንሾች? (ክፍል አንድ)

(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- በኢኮኖሚያቸው አድገዋል የሚባሉ አገሮችን ማየት ከጀመርኩባቸው ዓመታት ጀምሮ ከተገነዘብኳቸው ነገሮች አንዱ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ብትኖር፣ ከተማም ሆነ ገጠር፣ ግዙፍ ከተማም ሆነ ትንሽ የአካባቢ ከተማ … መሠረታዊ ነገሮች በተመሳሳይ መልኩ ተሟልተውላቸዋል። አውሮፓ በነበርኩበት ጊዜ ትልቅ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ወዳጆችም፣ ትንሽ መንደር ውስጥ የሚኖሩም ነበሩኝና ሁለቱም ዘንድ ለመሔድ ዕድል ገጥሞኝ ነበር። የሕዝብም ሆነ የቤቶች መብዛትና ማነሥ፣ የሱቆች መስፋትና አለመስፋት፣ የመንገዶች መብዛትና አለመብዛት ካልሆነ በስተቀር በትልቅ ከተማ የሚኖረውን በትንሽ ከተማ ካለው እንዲበልጥ የሚያደርገው ምንም ነገር አላየኹም።

አብዛኛው ኮሌጅ ጨርሶ የወጣ ኢትዮጵያዊ የብዙዎች ሕልም ለተወሰኑ ዓመታት ከአዲስ አበባ ውጪ ሠርቶ በመጨረሻ ግን መኖሪያና መጦሪያውን አዲስ አበባ ለማድረግ የሚያስብ ነው። እኔ ራሴም እንኳን ከአዲስ አበባ ወጥቼ ትንሽ ጊዜ ከቆየኹ ይጨንቀኝ ነበር። ትንሽ ከተማ እፍን ያደርገኛል። እንቅ። አየር የሚያሳጣ እፈና ዓይነት ነገር። አዲስ አበባ አየርም መተንፈሻም ማስተንፈሻም አላት። ፊልምም ለመግባት፣ ቲያትር ለማየት፣ ቦታም ለመቀየር ቢሆን አዲስ አበባ ምቹ ናት። ሆስፒታል ቢባል ማንኛውም መንግሥታዊ አገልግሎት አዲስ አበባ ሲኾን ይሻላል። ኡኡ ቢባል እንኳን ለመሰማት አዲስ አበባ ይሻላል።
እነዚህ ምዕራባውያኑ ያላቸው አኗኗር ከዚያ ፍፁም ይለያል። ምናልባት አንድ የተለየ ነገር ላይ “ስፔሻላይዝ” ያደረጉ አካባቢዎች ከመኖራቸው በስተቀር መሠረታዊ የኑሮ ጉዳዮችን በተመለከተ ሁሉም ከተማ እና ክልል፣ አካባቢ እና ቀበሌ ያው ነው። በተለይም ለምግብ መጠጥ፣ ለሆስፒታል፣ ለትምህርት ቤት፣ ለፖሊስ ማለቴ ነው።
አሜሪካን በመሳሰሉት አገሮች ደግሞ ከተሞች ከሙያ አንጻርም የተከፋፈሉ ይመስላሉ። ዋና ዋናዎቹ ቴሌቪዥኖች እና መዝናኛ ፕሮግራም (ሾው) አቅራቢዎች መቀመጫቸው ኒውዮርክ ነው። ሞዴሊንግ፣ ፋሺን ነክ ሥራዎች የሚሠሩ ሰዎች የመጨረሻ ግባቸው ኒውዮርክን መቆጣጠር መሆኑ ግልጽ ነው። የአሜሪካ አክሲዮን ገበያ ማዕከል እና ገበያውን አንዴ ወደላይ አንዴ ወደታች እያደረጉ አንድ ቦታ ሆነው ገንዘብ የሚያፍሱት ባንከሮች ከኒውዮርክ ውጪ የት ሊሆኑ ይችላሉ? የኛም አበሻው ደግሞ ኒውዮርክ ገብቶ ታክሲውን ያጧጡፈዋል። አሜሪካ የመጣ ሰው ኒውዮርክን ሳያይ ቢሄድ አሜሪካ መጣ አልለውም።
መቸም ፊልም ለሚወድ ሰው እና ፊልምን ሙያው ለማድረግ ላቀዱ ሰዎች በሙሉ ሕልማቸው ሎስ አንጀለስ ነው። አክተሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ ደራሲዎች ወዘተ ወዘተ ሆሊውድ “መንግሥተ ሰማያቸው” ናት። በሆሊዉድ ፊልም የምናውቃቸው ነገር ግን ሎስ አንጀለስ የሌሉ ሰዎች ማግኘት ከባድ ይመስለኛል። አንድኛውን በጡረታ አንዱ ውቅያኖስ ዳር ቤት ቀልሰው፣ አንዲት ደሴት ለብቻቸው ገዝተው ለመኖር ወስነው ካልወጡ በስተቀር።
የመኪና ፋብሪካዎች መዲና “ዲትሮይት” ነው። የአሜሪካ ኢኮኖሚ ወገቡን ብሎ ካስቀመጠው በኋላ በፕሬዚዳንት ኦባማ ፖሊሲ ድጋሚ አገግሞ ከሞት የተረፈ አገር ነው። የከተማው ነዋሪ ዋነኛ የሠራተኛውን ደሞዝ የሚከፍሉለት እነዚሁ መኪና ፋብሪካዎች ናቸው። ስለዚህ “ፊልም” ተብሎ “ሆሊዉድ ሎስ አንጀለስ” ከተባለ፣ “መኪና/ ፎርድ” ከተባለ ደግሞ ዲትሮይት መባሉ አይቀርም።
በዓለማችን ላይ የምናገኛቸው ታላላቆቹ የቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽኖች መቀመጫ በሳንፍራንሲስኮ አካባቢ በሚገኘው በሲሊኮን ቫሊ Silicon Valley ነው። ብዙ ሰው ከሚያውቃቸው መካከል አዶቤ ሲስተምስ፣ አፕል፣ ሲስኮ፣ ጉግል፣ ኤች.ፒ፣ ኦራክል፣ ያሁ ወዘተ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል። ምናልባት ከነዚህ ሁሉ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል ያልተኘው እና ብቸኛ መቀመጫውን ከተወለደበት ከሲያትል ያደረገው ማይክሮሶፍት ብቻ ነው። ሌሎቹ ገና  ሥራ ስጀምሩ ጀምሮ ቤታቸው ሲልኮን ቫሊ ነው።
አንዳንዴ ሳስበው “ብልህ ሰው እንቁላሉን ሁሉ በአንድ ቅርጫት አያስቀምጥም” የተባለውን ተከትለው ነው እንዲህ ያደረጉት ያስብላል። ክፋቱ ግን የአካባቢው ነዋሪ በሙሉ በአንድ ሙአ ላይ ባለ ገበያ ላይ ኑሮውን ስለሚመሠርት በዚያ ሙያ አካባቢ የገበያ ችግር ሲመጣ የሰዉም ኑሮ ይናጋል። ለምሳሌ የመኪና ገበያ ችግር በገጠመው ጊዜ አብዛኛው የዲትሮይት ነዋሪ ሥራ አጥ እንደሆነው ዓይነት ማለት ነው።
ይህንን በጎ ያልሆነ ነገር ለጊዜው ብናቆየውና ሌላውን በቅጡ ብንመለከተው እያንዳንዱ ከተማ እና አካባቢ የየራሱን የሥራ መስክ የፈጠረ ይመስላል። ከተሞች ራሳቸው “ራሳቸውን ፈልገው አግኝተዋል” ያስብላል። ከእኛ አገሩ የከተሞች እና የኢኮኖሚ አወቃቀር ጋር ስነጻጸር መሠረታዊ የፍልስፍና ልዩነት እንዳለ ይሰማኛል።
እኛ “አንድ፣ ትልቅ” ነገር ስንፈልግ እነርሱ ደግሞ “ብዙ፣ ትንንሾች” ይፈልጋሉ። በርግጥ እነርሱ “ትንንሽ” ብለው የጀመሯቸው ነገሮች እና “ትልቅ” ከምንለው በብዙው ይበልጣል። ለጊዜው ግን “ፍልስፍናው” ላይ እንወያይ። ፍልስፍና የሚባለው ካልገዘፈበት በስተቀር። ለእኔ ግን ፍልስፍና ነገር ታይቶኛል። አንድ ትልቅ ወይስ ብዙ ትንንሾች?
ዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር ከተጀመረባቸው ዘመናት ወዲህ ያለውን አካሄድ ስንመለከተ “መጠቅለል፣ በአንድ አስተዳደር ሥር መምራት፣ ትንንሾቹን ሁሉ ጨፍልቆ አንድ ትልቅ መፍጠር” ላይ ያተኮረ መሆኑን ለመገንዘብ የግድ የመንግሥት አስተዳደር ፕሮፌሰር መሆን አልጠየቀኝም። እስካሁን ያለኝ ንባብ ያሳየኝ ይኼንን ነው። የከተሞቹንም ዕድገት በዚያ አንጻር ካየናቸው አዲስ አበባ እየሰፋች እና እያደገች ሌሎቹ ግን ከገጠር መንደርነት እንዳልወጡ እንመለከታለን።
በወፍ በረር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በካርታ ላይ ብናስቀምጠው ገንዘቡ ሁሉ ተሰብስቦ አዲስ አበባ ላይ የሚገኝ ይመስለኛል። ድሮ ድሮ ከአዲስ አበባ ወጣ ስንል የቤት መኪና ማየት ብርቅ እንደነበር ትዝ ይለኛል። አልፎ ሒያጅ የዕቃ ጫኝ ተሳቢ፣ የክፍለ ሀገር አውቶቡስ፣ ሎንቺና ወይም ከከተማው አስፓልት የሚሰፋ የኤን.ጂ.ኦ ላንድክሩዘር ወይም ትልቅ የአካባቢው ካድሬ የጓድ እንትና መንቀባረሪያ ካልሆነ የአንድ ተርታ ነዋሪ ዜጋ መኪና ማየት በርግጥም ብርቅ ነበር። መኪናዎቹ ሁሉ ተሰብስበው አዲስ አበባ ናቸው ያሉት።
ሳስበው ሌላው ዜጋ አዲስ አበባ ያሉት ሰዎች አኗኗሪ (ሲኖሩ የሚመለከት) ነው። አሯሯጭ እንደሚባለው በአትሌቲክሱ። ሩጫውን ቀድመው የሚሮጡ ነገር ግን ወርቅም ሆነ መዳብ ወይም ነሐስ የማይፈልጉ አሯሯጮች፣ ላባቸውን አፍሳሾች።
አትሌቲክሱም ራሱ የዚህ “ብዙ ትንንሽ ወይም አንድ ትልቅ” ፍልስፍና ጥሩ ማሳያ ነው። ብዙ ጊዜ የእኛ አትሌቲክስ በየዘመኑ አንድ ታላቅ እና ትልቅ ሯጭ ይኖረናል እንጂ እንደ ኬንያውያን ብዙ/ ትንንሽ ጎበዞች የሉንም። አንድ ምርጥ ካፈራን በኋላ ሌላው ከቁጥር የማይገባ ይሆናል። አንዱ ትልቁ ላይ እንጂ ብዙዎቹ ትንንሾች ላይ ስለማናተኩርና ስለማንሠራ አንድ ምርጥ ሯጭ ይኖረናል፤ ከዚያ ግን ምንም።
ኃይሌ ገ/ሥላሴና ደራርቱ ተነሡ ዓለምን አስደመሙ። እነሆ አሁንም ድረስ ያስደምሙናል፤ ያስደንቁናል። ከነርሱ አስቀድሞ ምሩጽ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ እና አበበ ቢቂላ ነበሩ። በቅርቡ ደግሞ ቀነኒሳ በቀለ፣ መሠረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ። ከነዚህ በዓለም አትሌቲክስ ውስጥ የስኬትን ጣራ ከነኩት ጎን ለጎን የነርሱን ግማሽ የስኬት መሰላል መውጣት የቻሉ ለመፍጠር ሥራ መሥራት ያለበት አካል ባለመሥራቱ የባንዲራችን ነገር በነዚሁ ብቸኛ ሰዎች ትከሻ ላይ የወደቀ ይሆናል። 
እግር ኳሱ ራሱ አልሳካልን ብሎ የቆየው ብዙ ትንንሾች እና እኩያዎች የማፍራት ችግር ስላለብን ነው። እንደሩጫዉ ቢሆን አንድ ምርጥ አፍርተን በእርሱ ላብ እንደሰት ነበር። እግር ኳስ ግን አንድ ሜሲ፣ አንድ ሮናልዶ፣ አንድ ድሮግባ ሳይሆን ብዙ ሜሲዎች፣ ብዙ ሮናልዶ፣ ብዙ ድሮግባዎች ስለሚፈልግ በሕብረት የሚሠራ ነገር ላይ ትንሽ መጓዝ ዳገት ሆኖብናል። አሁን በስም እንኳን አንድኛቸውንም የማላውቃቸው ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋቾች መጥተው በየዜናው መመልከት ያስደስታል።
ከአንድ ትልቅ ብዙ ትንንሾች!!!!
(ይቀጥላል)
                

6 comments:

DESALEW said...

it is nice veiew!! NURilin Ababa!!!

Alemnew Sheferaw said...

ግሩም ድንቅ የሆነ እይታ ነው።
.... ሳስበው ሌላው ዜጋ አዲስ አበባ ያሉት ሰዎች አኗኗሪ (ሲኖሩ የሚመለከት) ነው። አሯሯጭ እንደሚባለው በአትሌቲክሱ።....

ቀጣዩን ክፍል በቅርብ እንጠብቃለን!

መልካም እለተ ሰንበት።

Anonymous said...

great article,,looking forward to the next part

Anonymous said...

ትልቅ "ወይስ"ብዙ-ትንንሾች !!! ትልቅ + ብዙ-ትንንሾ Great view

Anonymous said...

አንዳንዴ ሳስበው “ብልህ ሰው እንቁላሉን ሁሉ በአንድ ቅርጫት አያስቀምጥም” የተባለውን ተከትለው ነው እንዲህ ያደረጉት ያስብላል።

Gebre Z Cape said...

እንደሩጫዉ ቢሆን አንድ ምርጥ አፍርተን በእርሱ ላብ እንደሰት ነበር። እግር ኳስ ግን አንድ ሜሲ፣ አንድ ሮናልዶ፣ አንድ ድሮግባ ሳይሆን ብዙ ሜሲዎች፣ ብዙ ሮናልዶ፣ ብዙ ድሮግባዎች ስለሚፈልግ በሕብረት የሚሠራ ነገር ላይ ትንሽ መጓዝ ዳገት ሆኖብናል።

Thanks Ephrem