Wednesday, July 25, 2012

የበጋ ዋዕይ


 (ኤፍሬም እሸቴ/ adebabay.com/ PDF):- በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ አሁን የበጋ ወራት ነው። አሜሪካ ከዳር እስከ ዳር በከፍተኛ ዋዕይ መቃጠል ይዛለች። የአገሪቱ ሜትሮሎጂ የአየር ተንታኞች በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የሚያሳዩት ካርታ ቀይ እና ወይን ጠጅ የመሰለ ቀለም ነው። ሙቀቱን ለማመልከት። በዚህ ጨርቅ የሚያስጥል ሙቀት ውስጥ የሚጥለው ዝናብ ደግሞ ዛፍ ገንዳሽ፣ የኤሌክትሪክ ገመድ በጣሽ ነው። በሙቀቱ ላይ መብራቱ ሲጠፋ በየቤቱ ያለው ማቀዝቀዣ ድርግም ይላል፡፡ ፍሪጁ ጥፍት። ምግቡ ብልሽት። ሰዉ ላበት በላበት። (ላብ በላብ እንዲል)።

ኢትዮጵያ ውስጥም ሙቀት አይቻለኹ። “የዛሬዋ ፀሐይ፤ እህቶቿ ከአሰብ ከጂቡቲ መጥተዋል መሰለኝ” እያልን ስንቀልድ አስታውሳለኹ። አሰብንም ጂቡቲንም አላውቃቸውም። ጋምቤላን ግን ከነሙቀቱ አይቼዋለኹ። ለመጀመሪያ ጊዜ ካናቴራዬን ብቻ ሳይሆን ቢቻል ቆዳዬንም አውልቄ ቀዝቀዝ ማለት የፈለኩት ያን ጊዜ ነው። ብል ብል በምትል ካናቴራ መንገድ ለመንገድ የሄድኩበትን ጊዜ ከዚያ ውጪ አላስታውስም።
ከዚያን ቀጥሎ ድሬዳዋ ስሔድ ተመሳሳይ ሙቀት አይቻለኹ። ሰዉ ሁሉ ጀለቢያ አድርጎ በላይም በታችም ለምን ነፋስ ማስገባት እንደሚፈልግ የተረዳኹት ያኔ ነው። እያንዳንዷ የንፋስ ሽውታ ዋጋ አላት ኖሯል። መሐል አገር ለሚኖር ሰው ይኼ ብዙም አይገባውም።
መሐል አገርም ቢሆን የግንቦት ፀሐይ አናት በጥርቃ ነው የምትገባው። ኦዞን እንደተቀደደ ለመረዳት በግንቦት ወር ምሳ ሰዓት ላይ አራት ኪሎ መንገድ ላይ መገኘት በቂ ነው። ፀሐዩዋ ከሰዉ ቂም ያላት ነው የምትመስለው። በጨረር ሳይሆን በማይታይ መዶሻ አናት አናታችንን ስትወቅረን ቶሎ ብለን ታክሲ ውስጥ መግባት ወይም አንዱ ኬክ ቤት መሸጎጥ አለብን። ሴቶቹ እንኳን በሴትነት መብታቸው ተጠቅመው ጃንጥላ ይዘረጋሉ። ይህንን መብት ለእነርሱ ብቻ ነጥሎ ያጎናጸፋቸው ማን እንደሆነ “የወንዶች መብት አስከባሪዎች” ሲነሡ ያስረዱናል ብዬ እስከዛሬ እየጠበቅኹ ነው። እስካሁን የኛን መብት የሚያስከብርም አልተነሣ፣ አናት የሚበሳ ጠራራ ፀሐይ ሲወጣ ጃንጥላ ይዞ በመዞር አርአያ የሆነም “ወንድ” አልተገኘ።
ደግነቱ የኢትዮጵያ ፀሐይ እና የኢትዮጵያ ሙቀት ጥላ ሥር በመግባት ወይም አንዳች የሚያክል የአዲስ ዘመን ጋዜጣ በመጋረድ ከቃጠሎው መዳን ይቻላል፡: (እንዴ፤ አዲስ ዘመን ለዚህ እንኳን ያገልግል እንጂ። ድሮ ድሮ የቤታችንን ግድግዳ በማስዋብ የዋለውን ውለታ አልዘነጋውም።) አንዱ ዛፍ ሥርም በመከለል ሙቀቱን ማሳለፍ ይቻላል።
የዚህ የአሜሪካው ዋዕይ የተለየ ነው። ሙቀት ከሆነ ምንም ሥር ብትገባ ይሞቅኻል። ጥላ ብትዘረጋ፣ ጋዜጣ ብትጋርድ፣ በካናቴራ ብትሔድ፣ ትልቅ ዛፍ ሥር ብትከለል፣ እቤት ውስጥም ብትሆን ያው ነው። ብቸኛው መፍትሔ ማቀዝቀዣ ማግኘት ብቻ ነው። ቀንም ሌሊትም ያው ነው። ሌሊት ነው ብለህ መስኮትህን ብትከፍት የሚገባው ትኩስ አየር ነው።
ደግነቱ አገሩ አሜሪካ ነው። ቤት ውስጥ ማቀዝቀዣ አለ። መኪና ውስጥ ማቀዝቀዣ አለ። ቢሮ ውስጥ ማቀዝቀዣ አለ። አውራ-ጎዳና ላይ ብቻ ነው ማቀዝቀዣ የሌለው። ሰዉ ሙቀቱ ካየለበት አንዱ ሱፐር ማርኬት ይገባና ዕቃ የሚገዛ መስሎ ወተት፣ ዕንቁላል፣ ፍራፍሬ ምናምን ከሚደረደርበት ክፍት ፍሪጅ አጠገብ ዞር ዞር ይላል። ያን ጊዜ ከፍሪጁ የሚወጣው ቆዳ የሚኮረኩር ቅዝቃዜ ነፍሱን ይመልስለታል።
የዘንድሮው በጋ ግን ከዚህ በፊት ካየዃቸው የተለየ ሆኖብኛል። ሙቀቱ ብቻ ሳይሆን ዝናቡና ውሽንፍሩ። የዝናቡ አወራረድ ፍጥነት ይገርማል። ድንገት ይደርስና እንዲያው እንደ ሰነፍ ሠራተኛ ዝርግፍ ሲያደርገው ምድር ቀውጢ ትሆናለች። ያበደ ዝናብ። በዚያ ላይ ደግሞ መብረቁ። ብልጭልጭ ብሎ ሰከንድ እንደቆየ ጆሮ የሚሰነጥቅ ድምጽ ድብልቅልቁን ያወጣዋል። ከዚያ በየቦታው የተሰቀለው የመብራት ማስተላለፊያ እንደ ብራቅ ይፈነዳል። ከዚያ የመብራት ዘር ድርግምግም ይላል።
አሜሪካ እንዲህ ሠልጥና ሳለ የመብራት መስመሮቿን መሬት ውስጥ አለመቅበሯ ይገርመኛል። የመብራት ገመዶች በሙሉ መሬት ውስጥ የተከተቱበት የአሜሪካ ከተማ ያየኹት ላስ ቬጋስ ብቻ ነው። አዲስ ከተማ ስለሆነ ይመስለኛል። አውሮፓን እንደማስታውሰው አንድም የመብራት ገመድ በአየር ላይ ተዘርግቶ አላየኹም። የመብራት ገመድ ተዘርግቶ ካያችሁ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች፣ ትራሞች ወይም ሌሎች ባቡሮች የሚጠቀሙበት መሆን አለበት። አሜሪካ ስገባ መጀመሪያ የደነቀኝ እንደ ዳንቴል የተጠላለፈው የክር መዓት ነበር። ዝናብና ንፋስ ሲመጣ በአንዴው ጨለማ ውስጥ የሚጥለን ይኼው ነው።
እናም ባለፉት ሳምንታት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች መብራት አልነበራቸውም። ዛፉ ከሥሩ ንቅል እያለ በየመንገዱ ላይ ያለውን መኪናውንም፣ መብራቱንም፣ ቤቱንም አተረማመሰው። ያንን የሚያካክል ዛፍ እንዲህ በቀላሉ እየተነቀለ መውደቁ ግርም ይላል። ዛፎቹ ሥርም የላቸው እንዴ? ደግሞ አንዳንዱ ከወገቡ ላይ ቅምጥል ይልና አጠገቡ ያለውን ነገር ይደፈጥጠዋል። በዚያን ጊዜ ዛፍ አካባቢ መገኘት በራስ ላይ ሞት ማወጅ ነው።
ከአንድ ወዳጄ ጋር ስለዛፎቹ አቅመ ቢስነት ስናነሣ አንድ መላምት አጫወተኝ። እንዲህ ሲል። “የዚህ አገር ዛፎች ሥር የሌላቸው ምግብም ይሁን ውኃ ለማግኘት ብዙ መንገድ መሔድ ስለሌለባቸው ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ውኃ አጠር አካባቢዎች የሚገኙ ዛፎች ውኃ ፍለጋ ሥራቸው ወደ ታች ወይም ወደ ጎን ብዙ መንገድ መሔድ አለበት። ስለዚህ ንፋስም ሆነ ሌላ የሚገፋ ነገር በቀላሉ አይጥላቸውም”። የጥቅሱ መጨረሻ።
ከሳይንሱ አንጻር እንዴት እንደሆነ እንጃ እንጂ ለእኔ ግን አሳምኖኛል። እንደዚያ ባይሆን ይህንን የሚያካክሉ ዛፎች እንዲህ በቀላሉ ከሥራቸው እየተነቀሉ በየሰዉ ቤት ላይ የሚወድቁበት ምክንያት ምን አለ? ሌላም ትርጉም ይሰጣል የወዳጄ ማብራሪያ። የዚህ አገር ሰዉም ራሱ እንደ ዛፎቹ ነው። መከራ አይችልም። ችግር አይችልም። ውኃ ጥም አይችልም። ትንሽ ችግር ከመጣ እርስ በርሱ ሊባላ ምንም አይቀረውም።
ለምሳሌ በእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ሰሞን ሱፐርማርኬቶች ይጨናነቃሉ። ዳግም ምጽዓት የመጣ እንጂ መብራት የጠፋ አይመስልም። ሁሉም ነገር አርቴፊሻል ነው። የመብራት መጥፋት ብቻውን የሰዉን ኑሮ ሙሉ በሙሉ ያቃውሳል። ምግቡ ወዲያው ይበላሻል። ነዳጅ ማደያው በአንዴ ይጨናነቃል። ማብሰያው ኤሌክትሪክ የሆነባቸው ቤቶች ምግም ለማብሰል ይቸገራሉ። ሙቀቱ ወይንም ክረምት ከሆነ ብርዱ ቀንም ሌሊትም ስለሚበረታ ብዙ ቤተሰቦች መብራት ያላቸው ወዳጆቻቸው ዘንድ ወይም ሆቴል መሔድ ይመርጣሉ።
ሥራ የሚበዛባቸው አደጋ ጊዜ ተከላካዮችና ሚዲያዎች ናቸው። አደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቀንም ሌሊትም እንደሚተጉት ሁሉ ሚዲያዎቹም ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ፣ ማድረግ ስላለበት ነገር ለማስረዳት “ቢዚ” ናቸው። ሙቀቱ ሲበዛ ከሰውነታችን ውስጥ አለው የውኃ መጠን እንዳይቀንስ እና እንዳንጎዳ “ውኃ ጠጡ፣ በዚህ ውጡ፣ በዚያ ግቡ” የማይሉት የለም። ሰዉም ያሉትን በሙሉ ይከተላል።
በርግጥም ሙቀቱ እንዲህ ቀላል ስላልሆነ በተለይ ሕጻናቱን እና አረጋውያኑን ብዙ ፈሳሽ እንዲወስዱ ማድረግ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ብዙዎቹ ከተኙበት ሳይነሱ ይቀራሉ። ደግነቱ ሕጻናቱ በትምህርት ቤትም ስለሚነገራቸው ውኃ መጠጣት ለምደዋል። ከኢትዮጵያ የመጣ እንግዳ ካለ ነው የሚያስቸግረው።
·         ብዙ ውኃ ጠጣ፣
·         አልጠማኝም።
·         ባይጠማህም ጠጣ፤
·         ለምን ሳይጠማኝ እጠጣለኹ።
·         ግዴለም አትከራከረኝ ጠጣ።
·         እኔ ብዙ ውኃ መጠጣት አልለመድኩም።
·         ቢሆንም አሁን ልመድ

ይህ ክርክር ለቀልድ የተፈጠረ አይደለም። የእውነት ከማውቀው ገጠመኝ የተቆነጠረ ነው። ብዙ ጊዜ ውጪ አገር የሚኖር አበሻ ውኃ መጠጫ ዕቃ ይዞ ሲዞር የሚታየው ከዚህ ልምድ በመነሣትም ነው። እንጂ ለጉራ ብቻ አይደለም። ለነገሩ ለጉራም፣ “ቀላል አልምሰላችኹ” ለማለትም የሚጠቀምበት አይጠፋም። የኛ ነገር ነገሮችን ከጥቅማቸው ይልቅ ለጉራነታቸው የምናውላቸው ይበዛል። መኪና ያላቸው ሰዎች ቁልፋቸውን በጣታቸው እንዴት እያሽከረከሩ ይሔዱ እንደነበረ አስታውሳለኹ። ሞባይል የገባ ሰሞን ያንን የጣሊያን የእጅ ቦንብ የሚያክል ኖኪያ ለአገሩ ሁሉ እያሳዩ በኩራት የሚራመዱ ሰዎች ትዝ ይሉኛል። ራሱን ሞባይሉን የፈጠረው ሰውዬም እንደዚያ የሚኮራና የሚጀነን አይመስለኝም።
በፌስቡክም ሆነ በጉግል ወይም በስካይፕ (ተከለከለ ይሆን እንዴ?) የማገኛቸው ወዳጆቼ አዲስ አበባ ብርዱ አላስቀምጥ አለን ብለውኛል። አላያችሁ!! “ብርድ” በርግጥ ምን እንደሚመስል፤ ሙቀትም እንዴት እንደሆነ እያልኩ እቀልድባቸዋለኹ። በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ያሉ ሰዎች ይህንን ቅጥ-አምባሩ የጠፋ አየር ተቋቁመው ለመኖር ፈልሳፊዎች እና ሳይንቲስቶች ቢሆኑ አይገርምም። የምድር ወገብ ላይ ያሉ ሕዝቦች ሰነፎች ናቸው፣ አላደጉም ከተባለ ላለማደጋቸው አንዱም ምክንያት የአየሩ ተስማሚነት መሆን አለበት። (በርግጥ የመጥፎ መሪዎቻችንን ድርሻ እና ሌሎች ጉዳዮችን ዘንግቼ አይደለም።) ለሙቀቱ ፍሪጅ፣ ለቅዝቃዜው ማሞቂያ ቢሠሩ የሚጠበቅ ነው። አለበለዚያ እንዴት መኖር ይቻል ነበር? ከዚህ ዓይነቱ ዋዕይ ይሰውራችሁ።   
  © ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::
   


  

7 comments:

Anonymous said...

It is a nice article but I was expecting you say something about Meles Zenawe. by the way here in Amsterdam today it is 27 c so everybody is out side. sorry for my pore witting because now I mix with Netherlands language. I AM STERDAM...

Anonymous said...

thankyou dn Ehrem1 yehew zare muketun eyayehew new[maryland]yehenen sheshiche sturbucks kuch beyelehalehu na buna enteta?[addis abeba resturant
fitlefit]

Anonymous said...

thankyou dn Ehrem1 yehew zare muketun eyayehew new[maryland]yehenen sheshicheCAFE kuch beyelehalehu na buna enteta?[addis abeba resturant
fitlefit]

Anonymous said...

Efooy...you made my day Ababaye
In addition to the strong message you made it is very entertaining!

Anonymous said...

Beautiful article!!! Thank you!

Anonymous said...

ምን ጊዜ ጥበብ መንፈሳዊ እና ጥበብ ሥጋዊ የምትመግበን ኢትዮጵያዊው ኤፍሬም ለአክብሮቴ ቃላቶች ከወዴት ላግኝ

Anonymous said...

Nice article