Tuesday, July 31, 2012

“እናንተ በመናገር - እኛ በዝምታ እናምናለን”


 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF):- ዝምታ በተለይ ከሃይማኖት አንጻር ሰፊና ጥልቅ ትርጉም አለው። በክርስትናው ዓለም ዝምታና አርምሞ ትልቅ ዋጋ ይሰጣቸዋል። ሥጋን ፍፁም ከኃጢአት ነጻ ከማድረግ ደረጃ የደረሱ ሰዎች ከሚሰጣቸው ማዕረግ አንዱ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ “ጽማዌ” የሚባለው “ዝም፣ ጸጥ ማለት፤ መናገርን እና የማያስፈልግ ንግግርን መተው” ነው። አባ አጋቶን የተባለ ጻድቅ ክፉ ላለመናገር ድንጋይ በአፉ ይዞ ይኖር ነበር። የሰይጣንም ፈተናው ያንን ድንጋዩን ከአፉ እንዲያወጣና የማይገባ ንግግር እንዲናገር ማታለል ነበር።

በሙስሊም ሱፊዎች፣ በቡዲስቶች እና በሒንዱ እምነት ተከታዮች እንዲሁም በሌሎቹም እምነቶች፣ ደረጃው ይለያይ እንጂ፣ ዝምታ በሁሉም ዘንድ ዋጋ የሚያሰጥ አንድ ችሎታ ተደርጎ ይቆጠራል። አይሁዳውያን “ዝምታ የዕውቀት መጠበቂያ አጥር/ ግንብ ነው” እንደሚሉ ማንበቤን አስታውሳለኹ። ዝምታ በአብዛኛውም ከውስጣዊ መረጋጋት ጋር ይገናኛል። ውስጣዊ መረጋጋትን ለማመልከት ብቻም ሳይሆን “ክብር ለመስጠት” በሚልም “የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት” እየተባለ ወይም ጽኑዕ ዝምታ (Moment of silence) የሚደረግበት ጊዜ  አለ። ለምሳሌ ሙታንን ለማሰብ።
ስለ ዝምታ ወርቅነት ብዙ ብዙ ተብሏል። “ዝምታ ወርቅ ነው” ብቻ ሳይሆን “ዝም አይነቅዝም” እና “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም” የሚሉ “ዝ”ዎች ያሉባቸው ብዙ ተረቶች አሉን። ዝም የሚሉ ሰዎችም እንደ መልካም ሰዎች፣ አስተዋዮች ይታያሉ። ወጣት ዝምተኞች እንደ ጨዋዎች ይቆጠራሉ። በተለይም ሴቶች ከሆኑ ዝምታ እጅግ የሚያስከብራቸው ሀብት ሆኖ ይቀርባል።
ከዚሁ ጋር አብሮ ደግሞ ዝምታ የማያስፈልግበት ጊዜ እንዳለ የሚያሳዩ ተረቶችም አሉ። “ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል”፤ “ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም”፣ “ዝምታ ለበግም አልበጃት፣ አስራ ሁለት ሆና አንድ ነብር ፈጃት” የሚሉት ዓይነት። እንግዲህ “ዝምታ ወርቅ” ከሆነ፣ እንደገናም “ዝም ማለት ደጃዝማችነትን የሚያስቀር” ከሆነ መቼ ዝም ማለት እንደሚገባ እና በፈንታው መቼ መናገር እንደሚገባ መወሰን ጥበብ ይሆናል ማለት ነው።
በባህል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በትምህርታችንም ቢሆን “ዝም በል” እንጂ “ተናገር” የሚባል ትምህርት የለንም። ስለ መናገር፣ ራስን ስለመግለጽ፣ ለራስ አቋምና አመለካከት ጥብቅና ስለመቆም አልተማርንም። እንኳን የማናውቀውን የምናውቀውንም መናገር ይከብደናል። ስለዚህም ከመናገር አለመናገርን እንመርጣለን።
በቅርቡ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስናወጋ ይኸው የመናገር እና ያለመናገር ጉዳይ የጨዋታችን ርዕስ ሆነ። እዚህ አሜሪካን አገር በዞረባቸው ቦታዎች ሁሉ ያገኛቸው ጓደኞቹ “ተናጋሪዎች” ሆነውበት ኖሮ ነገሩ ግር እንዳሰኘው አልደበቀኝም። በግል ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ አገራዊ እና ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ በዚህ በዳያስጶራ የሚያገኘው ሰው “ተከራካሪ” መሆኑ ብዙም አላስደሰተውም።
አየህ፤ እናንተ ብዙ በመናገር ነው የምታምኑት። እኛ ደግሞ በዝምታ ነው የምናምነው” አለኝ እንደቀልድ። “እናንተ” ያለው በውጪ ያለነውን፤ “እኛ” ብሎ ራሱን የፈረጀው ደግሞ በአገር ቤት የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማለት ነው። “እኛ ዳያስጶራዎች” ሳይታወቀን ከምንኖርበት አገር የመናገርን ባህል ወርሰነው ኖሯል። ይህ መናገራችን ነው ባዕድ የሆነበት።
ወዳጄ፣ መናገር ታበዛላችሁ ያለው እርስበርሳችን ስላለን ወሬ እንዳልሆነ ገብቶኛል። ትንሹንም ትልቁንም ከአገራችን ጋር እያነጻጸርን በቁጭትም በ“ለምን አይሆንም”ም የምናሰማውን ሮሮ ነው። ወዳጄ ያልገባው አንድ ቁም ነገር ሰው ስለ ራሱ ጉዳይ፣ ስለ ራሱ መብት እንዲከራከር እና እንዲጠይቅ መንገድ ካገኘ ከዚያ በኋላ “ዝም በል” ቢባልም “ዝም” ለማለት እንደሚቸገር ነው። በምንኖርበት አገር ደግሞ ሁሉም መመሪያ “እንዲህ ከሆንክ እንዲህ በል፤ ይህ ባይደረግልህ ለዚህ አቤት በል፤” የሚል ሮሮ ማሰሚያ መንገዶችን በሙሉ የሚያሳይ አገር ነው።
“እናንተስ ለምን አትናገሩም? እኛን ዝም በሉ ከምትል እኛ ለምን አንናገርም አትልም?” ብዬ ጠየቅኹት። “ብትናገር ምን ታመጣለህ? እንዲያውም የምትወደውን እና የምትጠላውን፤ የምትደግፈውን እና የምትቃወመውን፤ ጠንካራውን እና ደካማ ጎንህን አሳየህ ማለት ነው። ከዚያ ሊያጠቃህ የሚፈልገው እንደፈለገ ያጠቃኻል። ዝም ካልክስ? ምን ትውደድ፣ ምን ትጥላ፣ ትደግፈው፣ ትቃወመው ጠላትህ ምንም አያውቅም። ዝም ስትል ትፈራለህ። ብትናገር ትደፈራለህ። ተናግረህ ከምታመጣው ለውጥ ዝም ብለህ የምታገኘው ይበልጣል።” ትንታኔውን አወረደው።
እውነቱን ለመናገር ትንታኔው ብዙ ቁም ነገር አዝሏል። በርግጥም ዝም ከሚል ይልቅ የሚናገር ይታወቃል። ለመርዳትም ለመጉዳትም የሚናገር ይሻላል። ጸጥ ብሎ ከተኛ ሐይቅ እና ከኩሬ ይልቅ ወራጅ ወንዝ ይሻላል። ከደፈረሰ ውኃ ይልቅ የጠራው ውስጡን ለማወቅ ይቀላል። ይህ ወዳጄ የሚናገረው ስለ ግለሰባዊ ዝምታ ሳይሆን ስለ አገር ዝምታ፣ ስለ ሕዝብ ዝምታ፣ ስለ ቡድኖች ዝምታ መሆኑን ሳስብ ግን ትንሽ ፍርሃት ፍርሃት አለኝ።
ሰው በግሉ ዝምተኛ ቢሆን ግድ የለም። አገር ዝም ብሎ እንዴት ይሆናል? አገር ዝም ካለስ አገሩ ላይ የተሾሙት አለቆች፣ የሚመሩት ሊቆች ምኑን አለቃ እና ሊቅ ይሆናሉ?
በጥንቱ ዘመን የነበረውን “እረኛ ምን ይላል?” ወይም “እረኛ ምን አለ?” ብሒል እና ትርጓሜ በቅጡ ከተመለከትነው ገዢዎች እና አስተዳዳሪዎች “ዝም” ካለ ሕዝብ ዝምታ ውስጥ ንግግሩን ፍለጋ እንደሚሞክሩ እንረዳለን። ሕዝብ ዝም ሊል አይችልም፤ ዝምም ሊል አይገባውም። ሕዝብ ሲናገር እንጂ ዝም ሲል አደጋ አለው። በእረኛው፣ በአዝማሪው፣ በአስለቃሿ፣ በሕጻናት ጨዋታ እና በተረት ውስጥ የሕዝብ ንግግር፣ ብሶት፣ እሪታ እና ስሞታ አለ።
ቀና ብዬ ሳየው ሰማዩ ቀለለኝ፣
እግዜሩን ሰፈራ ወሰዱት መሰለኝ” ነው ያለው አንዱ ሰፋሪ? ወይም ከዚህ ጋር የሚቀራረብ አሁንም በኅሊናዬ የቀረ የዘመነ ደርግ የገበሬ አባባል አለ። እኔ ዘመናዊ እረኛ ወይም ዘመነኛ ብሶተኛ ሰፋሪ ብሆን፦
አፈረሱት አሉ ጊርጊሮ አራት ኪሎን፣
አፈረሱት አሉ ጊዮርጊስ ሥጋ ቤቱን፣
ቁርጥ ሥጋ ጥብሱን የበላንበትን“ እላለሁ ማለት ነው።
የዘመናዊት አፍሪካ ዘመናዊ ገዢዎቻችን ወይ  ለ“እረኛው ምን አለ?” አይፈቅዱ ወይም ለ“ዘመናዊ የሕዝብ መገናኛ” መንገዶች በር አይከፍቱ፣ ከላይም ከታችም ሁሉን መተንፈሻ ደፍነው አህጉሩን ሊያበላሹት ነው። ያ ወዳጄ “እኛ በዝምታ ነው የምናምነው” ያለው ትልቅ አባባል ዋጋ የሚሰጠኝ ከዚህ ላይ ነው። በዝምታ እንድንኖር የተፈረደብን፣ በራሳችን ላይ የዝምታ አዋጅ ያወጅን ሕዝቦች ከሆንን በዝምታ እየኖርን ነው እንላለን እንጂ በዝምታ እየሞትን ነው ማለት ይቻላል። የሚያሳዝነው ግን ዝምታው ሕዝቡን ዝም እንዲል ለሚፈልገው አካል ራሱ የማይበጀው መሆኑ ነው።
የሰው ልጅ በተፈጥሮ የሚስማማው መናገር እንጂ ዝምታ አይደለም። እንኳን እኛ በፈጣሪ አርአያ እና አምሳል የተፈጠርንና የመናገሪያ አካል ያለን ፍጡራን ቀርቶ ማሰብ እና ማስተዋል የማይችሉ በደመ ነፍስ የሚኖሩ እንስሳት እንኳን ሳይቀሩ መግባቢያቸው ድምጽ ነው። እንስሳት ከፍ ያለ አደጋ ካልገጠማቸው በስተቀር ዝምታን አይመርጡም። ዝምታቸው ምልክት የሚሆንበት አጋጣሚ የአደጋ ምልክት መሆኑን እንዳነበብኩ አስታውሳለዅ። ይህ በዓለመ እንስሳት እንኳን የሌለ የጅምላ ዝምታ በአገር ላይ ከመጣ በርግጥም ያስፈራል። ወይ እረኛው፣ ወይ አዝማሪው ወይ ጋዜጠኛው ካልተናገረ  ታዲያ የሕዝብ ንግግሩና ድምጹ በምን ይታወቃል? የቀሩን አማራጮች “እብዶች” እና “ሰካራሞች” ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው። “እብድ እና ሰካራም የልቡን ያወራል” እንዲል ተረታችን። መቸም ቴሌቪዥናችንን እና ሬዲዮናችንን ማመን ከተውን ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ይህ የዝምታ አባዜ ከሕዝቡ ወደ ገዢው ሲሸጋገር ደግሞ አደጋው የበለጠ ይከፋል። ሌላው ቀርቶ የቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳይ እና ስለ ጉዳዩ እውነተኛ መልስ ለማግኘት ያለው ውጣ ውረድ “እንዴት ያለ አገር ነው?” ያሰኛል። ሕዝብን “አትናገር!” ማለት አንድ ነገር ነው። “እኔም አልናገርም” ማለት ከመጣ ተኮራርፎ አገርን አገር ማድረግ እንዴት ይቻላል? ነገሩ የተኮራረፉ ባልና ሚስት በዓይነ ሕሊናችሁ እንድትስሉ ያደርጋችኋል። ወይ አልተፋቱ ወይ አይነጋገሩ። በመካከል ልጆቻቸው እንዴት እንደሚሆኑ ማሰብ ነው።
ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጭር መልስ መስጠት የመንግሥትነት ተግባር መሆኑን እስከመዘንጋት የሚያስደርስ የዝምታ ልማድና ምሥጢረኝነት እንደተጠናወተን ግልጽ ነው። ጋና ፕሬዚዳንቷ በሞቱ በአምስት ሰዓታት ውስጥ ዜናውን አውጃ፣ ምክትሉን ወደ ዋናነት አውጥታ፣ አገር አረጋግታ በዓለም ፊት ስትከበር እኛ የአገሪቱ መሪ የት እንዳሉ፣ በምን ሁኔታ ላይ እንደሆኑ ለመናገር ስንቸገር ማየት “በእውነት ሁለታችንም አንድ ዘመን ላይ ነው ያለነው?” ያሰኛል።
ባልተናገርን መጠን፣ መተንፈሻ ቀዳዳዎችን በዘጋን መጠን ዝምታው ጆሮ ሊበጥስ ወደሚችል የድምጾች ነጎድጓድነት ለመቀየር ይከማቻል እንጂ እንደታፈነ እንደማይቀር ታሪክ ምስክር ነው። አንዱ ጋዜጣ “ጠ/ሚኒስትሩ አሁን በደህና ገቡ” ሲል፣ ሌላው “አሁን በደህና ወጡ” ሲል እኛ በፈንታችን የነጋድራስ ተሰማ እሸቴን ቅኔ እናስታውሳለን።
ደህና ከሆነማ የማይመጣ ምነው፣
አለ አልሞተም ማለት ላልጋ ክርክር ነው፡፡” (ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ)
    
ቸር ያገናኘን!!

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::
     


  

16 comments:

Anonymous said...

I was wondering where is the main point, and there it is at the last three paragraphs...

Tsegaye Girma said...

Well observed and written! Our utterances are conspicuous by their absence.

Anonymous said...

i like it sooooo!!!!!

Anonymous said...

እየጎዳን ያለው “መቼ መናገር መቼ ዝም ማለት እንዳለብን አለማወቅ” ነው። ይህ ጽሁፍ ለምሳሌ እንደ ብዙዎቻችን ሕይወት በመንፈሳዊ ቃላት ጀምሮ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተደመደመ። መንፈሳውያን ፖለቲካ ላይ መሳተፋቸው ባይከፋም ወይም ፖለቲከኛ መሆን የለባቸውም የሚል እምነት ባይኖረኝም- ጊዜ ሰጥተው እንደዚህ አይነት እረጅም ጽሁፍ መጻፍ ያለባቸው ግን፤ ትሪብያል ለሆኑ፣ ብናቀውም ባናውቀውም ምንም ለማናመጣው- የጠቅላይ ሚንስትሩ የጤና ጉዳይ መሆን ያለበት አይመስለኝም። ስለዚህ አላስፈላጊ በሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ “በዝምታ” እና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ “መበናገር” ብናምን መጽሃፍ ቅዱሱም ይደግፈናል

Anonymous said...

ውድ ወንድሜ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። ግራ አጋቢውን ገመናችንን-ግልጥልጥ አርገህ አሳይተኸናል። ነገሩ ፍራት ይሁን ሌላ ብቻ በዝምታ ድባብ ውስጥ ነው። የእኛዎቹ-ይሄን ቢያደርጉ አይደንቀኝም። የራሳቸውን አለም፤እውነት፤ሕዝም መስርተው በህልም ቅዥት ወስጥ ናቸው። ስለ ሕዝቡ መጨነቅ ካቆሙ ቆይተዋል። በእጅጉ የሚያስቆጨው ግን ወዲህ ነው። ምዕራባዎያኖቹ። የተመቻቸ ፈረስ ስለ ነበር፤ በደረሰበት አደጋ ዝምታን መርጠዋል። ምንም እንዳልሆነ፤ እንዳላዩ እያለፉት ነው። የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ መረጃ ሲያወጣ ነው፤ ቢቢሲ ተብዬውም ትንሽ የተነፈሰ-ለምን ዝም አላችሁ እንዳይባል። እስኪ ዞር አርገን እንዬው፤ መለስ ጠላታቸው ቢሆን ኑሮ፤ ልክ እንደነ ሳዳም። የዜና አይነት እናይ ነበር። ምን አልባት፤ በጣም ወደላይ የወጣና የጦዘ ወሬ ያቀብሉን ነበር። ጋዳፊ ላይ ይሄን ሲሰሩ አይተናል። ታላላቅ የዜና አውታሮች አይኖቻቸውና ሰራተኞቻቸው ጦርነት መሃል እየገቡ ሲዘግቡልን ነበር። በሕዝብ ቁጠር ብንለካው-ለ 6 ሚሊዩን መሪ ያን ያህል ሲጨነቁ የነበሩ፣ ዛሬ በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር 2ኛ የሆነች አገር፣ ከ 80 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያለች አገር፣ የአየር ንብት ለውጥ ችግርን መፍትሔ ለማፈላላግ መሬዋን የወከለች አገር፣ እነሱ በሚሉት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከጎናቸው ያለች አገር፣ ዛሬ መሬዋ ሲጠፋባት ለምን ምዕራባውያን ልሳናቸው ተዘጋ? በውኑ የት እንደሆነ አጠውት ይሆን? የኢትዬጵያን ሕዝብ መናቅ ይመስለኛል።
ለማንኛውም አምላክ የስራቸውን ይስጣቸው፣ እውነቱን በተሎ ይግልጥልን።

Anonymous said...

Great blog! Thanks for laying our cultural values around silence in an excellent way and its misappropriation, by the leaders in our country, to suppress our people.

Anonymous said...

Dear Epherem, as you said it the government should put out more info to the public,but i feel like even if they put out about the prime minister day to day event most oppostion party's and their supporters stil will talk like he is dead,In a diaspora that fantasize the death of a leader nothing will full fill it's wish.
Hopefully you may blog about what is wrong with us that we want a person to die?

Anonymous said...

ur right!!!

Anonymous said...

ይህ ከተፈቀደለት ኣካል በቀር ማለትም ከኢሕኣዴግ በቀር ሌላ ሊያውቀው ኣይፈቀድለትም
በተለይም እንደ ኤፍሬም እሸቴ የመሰሉ መንታ መንገድ ላይ የቆሙ ማለትም ሃይማኖታዊ ፖሎቲካ የሚያራምዱ ከቶ ሊያውቀው ኣይችልም
"ኣልቦ ዘየኣምራ ዘእንበለ ኣብ ባሕቲቱ" እንዲል መጽሓፍ

Anonymous said...

This is it what I expected from you last time, nice article..!!
I Amsterdam.

Anonymous said...

so u mean, ETV to talk the truth need to drink a lot ?

Ephrem Eshete G. said...

ሰደብከኝ ወይስ አስተያየት ሰጠህ ነው የሚባለው? ቁምነገሩን ብትናገር ለኔም ለአንባቢውም ትጠቅማለህ። ስትሳደብ የራስህን ፍላጎት ታረካለህ በሌላው ዘንድ ትቀላለህ።

Anonymous said...

No No No! እንደሱ ማለት አይደለም ወዳጄ፡፡ ኢቲቪ ቢጠጣም ባይጠጣም ለውጥ የለውም፡፡ ኢቲቪ በመጀመሪያ ለ17ዓመታት የአረንጓዴውን የምርት እድገት ሲያናፋ ቀጥሎም ለ21ዓመታት ምትሃተኛውን የአሥራ ምናምን እድገትና ትሩፋት ሲናኝ እውነት በሌለበት ለ38ዓመታት በውሽት ጠባይ (character) "ተቀጥቶ፣ተቆንጥጦ" ያደገ ተቋም ነው፡፡ 38ዓመት ሙሉ በውሽት መረጃ ራሱን ያሳበጠ ተቋም እንኳንስ ዛሬ ነገም ደግ ቀን ቢመጣ (የፕሬስ ነጻት ተግባራዊ ቢሆን)የተዋቀረበትን የማንነት ምህዋር ርግፍ አድርጎ ይተዋል ማለት እይቻልም ለማለት ነው፡፡ "ምን ለማለት ፈነጌ ነው ወድሜ የተናገረውን በመደገፍ ለመናገር ፈልጌ ነው" የሚለውን ከ"ትኩስ ድንች" ቀልድ ተመልከት፡፡ ቀልድ አልኩህ እንጂ አንጓ ያለው የሚጨበት እውነታ መሆኑን እዚያው ያረዳሃል፡፡

Anonymous said...

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዚህ ዓይነት ድንገተኛና እንደ ዜጋም ሆነ አንደ ሰብአዊ ፍጡር በሚያሳዝን መልኩ ዘመነ መንግሥታቸው ማክተሙ በጥቂቱም ቢሆን እንዳዝንላዠው አድርጎኛል፤ ሰው ነኝና፡፡

ከዚያ በተረፈ ግን አጋጣሚው ወያኔ መራሹን የኢሕአዴግ መንግሥት ውሳጣዊ ማንነት በአደባባይ እንዲጋለጥ ያደረገ ታሪካዊ ኩነት ነው፡፡

1. ሕግ መንግሥት
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደጋግመው እንደ ደሰኮሩት እንከንየለሽ አለመሆኑ ርቃኑ ወጥቶ የታየበት ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ተፍጨርጫሪዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለማሰለስ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች በርካታ ጉድለቶችና ክፍተቶች እንዳሉባቸው ያስገነዘቡት በቀደሙት ዓመታት ቢሆንም ጆሮ የሰጠ፣ ልክ ነው ያለ የለም፡፡ እናም ሕገ መንግሥታችን በቅጡ ከተፈተሸ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻም ሳይሆን ሌሎች አይነኬ የሚባሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሚኒስትሮች እንደ ፍትሕ፣ ውጪ ጉዳይ፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት፣ ኮሙኒኬሽን (የአቶ በረከቱን ድሪቶ ጽ/ቤት አይደለም)የመሳሰሉት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመነጩና ለእሳቸውና ከእርሳቸው ጋር ብቻ የሚኖረው ተጠሪነትና ግንኙነት ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ከሌለው በስተቀር ለ21 ዓመታት ያየነው ከመከና መሪም በቀለለ ሁኔታ እንደፈለጉ ማሾር የሚቀር አይሆንም፡፡

2.ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ...
ሕገ መንግሥቱም ሆነ ፌደራላዊ ተቋማዊ አደረጃጀት "ሙጃውን ፓርላማ" ጨምሮ በቅድመ ጥንቃቄና በጥሩ ዲዛይነር በመልክ በመልኩ እየተቀደደ ለወያኔ መራሹ መጨረሻ የሌሽ አገዛዝ ማስፈኛነት እንደተቋቋሙ ፍንትው ብሎ የታየ ሃቅ መሆኑ የአቶ መለስ መታመም ትልቁ ውጤት ነው፡፡ ዛሬ ፍትሕ፣ፕሬስ፣ መከላከያ፣ሚዲያ፣ ተዋጽኦውን የጠበቀ የሥልጣን ድልድል ከሁሉም በላይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የመጠበቅ፣ የማስጠበቅና በርእሱም የመመራት መርህ ተራ ዲስኩርና ማሽካካት እንጂ እውነት እንዳልነበር በእርግጡ የተረጋገጠበት ነው፡፡

እናም አቶ መለስ አይሙቱ ከሕመማቸው ወያኔ መራሹ ስብስብ ለምሕረት ያልሆነ ጥፋት፣ ለበረከት ያልሆነ መርገም በአገሪቱ ላይ ሲመርግ መቆየቱ ግልጥ ፍንትው ያለው ሃቅ ነው፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ፣ ይስማ፣ ይስማ፣

hanicho said...

“ዝምታ ወርቅ” ከሆነ፣ እንደገናም “ዝም ማለት ደጃዝማችነትን የሚያስቀር” ከሆነ መቼ ዝም ማለት እንደሚገባ እና በፈንታው መቼ መናገር እንደሚገባ መወሰን ጥበብ ይሆናል ማለት ነው።

tigist melaku said...

u r right, we Ethiopians dont know the right time to talk about something. sometimes we kept quiet a the time we should talk.sometimes we talk at the time when we dont have to talk.............