Tuesday, August 7, 2012

ትዝታ ዘኦሎምፒክ


 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)ለመጀመሪያ ጊዜ በወረዳዎች መካከል የሚደረግ የገበሬ ማኅበራት የሩጫ ውድድር ሆሎታ ላይ ሲካሔድ ግንባሩን በነጭ ጨርቅ ግጥም አድርጎ አሥሮ በባዶ እግሩ ሲሮጥ በልጅነቴ ያየሁትን አትሌት አልረሳውም።  ጥቂት ቆይቶ ለመናገሻ አውራጃ፣ ቀጥሎም ለሸዋ ክፍለ አገር መሮጥ ጀመረ። ከዚያ በኋላ ወደ አገሩ የተመለሰ አይመስለኝም። በየሬዲዮኑ የምንሰማው ዝነኛ አትሌት ሆነ። በባዶ እግር ለወረዳ ገበሬ ማኅበር ከመሮጥ ተነሥቶ ዓይኔ እያየው ዓለማቀፋዊ የትራክ ንጉሥ የሆነው አበበ መኮንን። እንደ ዕድል ሆኖ እርሱ ከፍተኛ ችሎታ ላይ በነበረባቸው ወቅቶች የነበሩት ሁለቱ አትሌቲክሶች የደቡብ ኮሪያው እና የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒኮች በፖለቲካ ምክንያት ኢትዮጵያ ባለመካፈሏ ስሙን በኦሎምፒክ የታሪክ መዝገብ ላይ የተመዘገ ሳይሆን ቀርቷል።

ኦሎምፒክ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅና አዋቂ የየአራት ዓመት አስደሳች ህልም ነው። ምናልባትም ከአበበ ቢቂላ እና ማሞ ወልዴ አንጸባራቂ ድሎች ጋር ሳይገናኝ የቀረ አይመስለኝም። እነርሱ በማራቶን የጀመሩት ድል እንደ ባህል ተቆጥሮ ማራቶን የኢትዮጵያውያን የባህል ሩጫ እስኪመስለን ድረስ “ማራቶን ማራቶን” ማለት የተለመደ ነበር። ኋላ በነምሩጽ ይፍጠር የሞስኮ ኦሎምፒክ ድል ጀምሮ፣ ቀጥሎም በነ ኃይሌ ገ/ ሥላሴና በነደራርቱ ድጋሚ ውልደት ያገኘው መካከለኛ ርቀት በተለይም ለአዲሱ ትውልድ “የኢትዮጵያ የባህል ሩጫ” መስሎ ይታያል።
ጆሮዬን ሬዲዮ ወደ መስማት ማቅናት በጀመርኩባቸው የልጅነት ወራት የሞስኮ ኦሎምፒክ በማርሽ ቀያሪው በምሩጽ ይፍጠር እና በሌሎቹ ዝነኛ አትሌቶች በነእሸቱ ቱራ፣ መሐመድ ከድር፣ …. ሌላ ማን ነበ …… ር፣ አ … ዎ የርምጃ ሩጫ ተወዳዳሪው ሁንዴ ጦሬ የአገራችን ባንዲራ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ፣ ሲዘመርላቸው እና ሲወደሱ አበበ ቢቂላ ድጋሚ የተወለደ ያህል ይሰማኝ ነበር። አትሌቶቹ ለልምምድ ሆለታ ገነት ጦር ት/ቤት መጥተው በነበረ ጊዜ በልጅነት ዓይናችን በጉጉት ስንመለከታቸውም አስታውሳለኹ።
የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በተለይም ለአትሌቶች የግል ሕይወት ብዙም ጠቃሚ የሆነ አይመስለኝም። (ሩጫቸውን ሲያቆሙ ሕይወታቸው እንዴት እንደቀጠለ፣ በምን እንደሚተዳደሩ ማለቴ ነው።) የሶሻሊስቶቹ ወደ ካፒታሊስቶቹ ከተሞች፣ የካፒታሊስቶቹም ወደ ሶሻሊስቶቹ ለመሔድ የፖለቲካው ሙቀትና ቅዝቃዜ ወሳኝ ነበር። ለምሳሌ ካፒታሊስቶቹ በሞስኮ ኦሎምፒክ አንሳተፍም አሉ። ሶሻሊስቶቹ ደግሞ በፈንታቸው የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክን አንሳተፍም አሉ።
ፕሬዚዳንት ካርተር ሶቪየቶች አፍጋኒስታንን መውረራቸውን በመቃወም ሞስኮ ኦሎምፒክ ላይ ማዕቀብ ጣሉ። ሞስኮም በበኩሏ ብድሯን ለመመለስ አራት ዓመት/ አንድ የኦሎምፒክ ዘመን ብቻ ነው የጠበቀችው። የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክ ሲመጣ እርሷም፣ ሌሎች 13 ደጋፊ አገሮችም አብረዋት ከኦሎምፒኩ ቀሩ። ኢትዮጵያም ሶቪየት ሕብረትን ደግፋ ሳትሳተፍ ቀረች። የሚያሳዝነው የሎስ አንጀለስ ብቻ ሳይሆን ሰሜን ኮርያን ለመደገፍ በሚል የደቡብ ኮሪያ ሴዉል ኦሎምፒክ ላይም አገራችን አለመሳተፏ ነው። በወቅቱ ትልቅ ችሎታ ላይ የነበሩት ብዙ አትሌቶች ስማቸውን በኦሎምፒክ ማኅደር ከነአበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ እሸቱ ቱራና መሐመድ ከድር … ጋር ለማስመዝገብ የነበራቸውን ዕድል አጡ። አበበ መኮንንን በመግቢያዬ ያነሣኹት ለዚያ ነው። ዕድል አልቀናችውም።
ኃይሌ ገ/ሥላሴ ዕድለኛ ነው። በዚህ ችሎታው “በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን”፣ ዓለም ምዕራብና ምሥራቅ ተብሎ በተከፈለበት ዘመን ላይ ሮጦ ቢሆን ኖሮ አሁን የምናውቀውን የወርቅ ብዛት ላያገኝ ይችል ነበር። ዕድለኛ ሆነና የበርሊን ግንብ ሲፈርስ እርሱም ወደ ሩጫው ዓለም ገባ። ዓለምም ችሎታውን ለማየት፣ ወደ ምዕራቡም ወደ ምስራቁም አገራት ለመዘዋወርና ለመሮጥ ቻለ። ብዙዎቹ የርሱ አንጋፋዎች ያላገኙት ዕድል ይመስለኛል። እነሆ እንደምናየውም ድንቅ የሆነ የሩጫ ዘመናትን አሳለፈ፤ በሕይወቱም ለሌሎቹ አትሌቶች አርአያ የሚሆን የደረጀ የገንዘብ አቅም ሊኖረው ቻለ።
ኢትዮጵያ በፖለቲካ ምክንያቶች ኦሎምፒክን ያክል ነገር ከመሳተፍ ታቅባ ድጋሚ ስትመለስ “የእንኳን ደህና መጣሽ” ወርቅ ያገኘቸው በደራርቱ ቱሉ መሆኑ አይረሳም። የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ባለ ወርቅ ሜዳሊያ አትሌት። ሳቂታ። ፍልቅልቅ። ሳቋ ብቻ ሳይሆን ጣፋጭ ንግግሯም የማይረሳ። በወቅቱ ፊጣ ባይሳ እና አዲስ አበበም ከሜዳሊያ ሰንጠረዥ ዝርዝር ውስጥ ለመግባት ችለው ነበር። ፊጣ በ5000 ነሐስ፣ አዲስ ደግሞ በ10000 ነሐስ።
እነርሱ በከፈቱት የድል በር የገቡት ኃይሌ እና ፋጡማ ሮባ በአትላንታው ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ የዘመነ አበበ ቢቂላን ትንሣኤ አሳዩን። ከዚያ በኋላማ አትሌቲክሱን ባህላዊ ስፖርታችን፣ ወርቁን የግል ንብረታችን አደረግነው። ስንቶቹን እናነሣለን። አሰፋ መዝገቡ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ተስፋዬ ቶላ፣ ስለሺ ስሒን፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽና እጅጋየሁ ዲባባ፣ መሠረት ደፋር፣ ጸጋዬ ከበደ ስማቸውን  በኦሎምፒክ ታሪካ በደማቁ ጻፉ።
በኦሎምፒክ ላይ የሚደረግ ውድድር እንደማንኛው ጊዜና ቦታ ውድድር አይደለም። ወርቁም እንደማንኛውም ወርቅ አይደለም። ሁለቱም የተለዩ ናቸው። ከሁሉም ውድድሮች ደግሞ የማይረሱ ልዩ ውድድሮች እና አጋጣሚዎችም አሉ። የደራርቱ የባርሴሎና ድል ለአፍሪካ የመጀመሪያው ታሪካዊ የኦሎምፒክ የሴት ወርቅ ስለሆነ በጭራሽ የሚዘነጋ አይደለም። ከውድድር በኋላ ባንዲራውን የለበሰችበትና እጇን ከፍ አድርጋ ስቴዲየሙን የዞረችበት ቄንጠኛ አሯሯጥ ልዩ ነበር። ዘመኑ ራሱም፣ የመንግሥት ለውጥ ሰሞን፣ ባንዲራን ከፍ ማድረግ ትልቅ ትርጉም በሚሰጥበት ወቅት መሆኑስ እንዴት ይረሳል?
ከዚህ ሌላ የማይረሳኝ የኦሎምፒክ አጋጣሚ የኃይሌ ገ/ሥላሴና የኬኒያዊው የፖል ቴርጋት የስድኒ የ10 ሺህ የመጨረሻ ትንቅንቅ ነበር።
ደግነቱ የልብ ድካም የሌብኝም እንጂ ያቺን ቀን ማለፌን እጠራጠራለሁ። የትራክ-ተአምር ማለት እችላለሁ። ቴርጋት የተፈተለከበት ፍጥነት፣ በአንዱ አትሌት ጀርባ ተደብቆ የወጣበት ዘዴ፣ ኃይሌ በእግሩም በጥርሱም በሐሞቱም ሮጦ የደረሰበት ፍጥነት፣ የቀደመበት ትንግርት …. ልዩ ነበር። በ“ካናል ፍራንስ” የሚያስተላልፈው ድምጸ ሸጋ አፍሪካዊ ጋዜጠኛ ለጆሮ በማይቆረቅር ጩኸት “ሄደ፣ ቀደመው፣ ያዘው፣ ለቀቀው” ሲል ቆይቶ ኃይሌ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ወርቁን ሲነጥቅ “ገብረ ሥላሴ ሀዝ ቢትን ቴርጋት ኤጌይን” አለበት ድምጽ ራሱ የተለየ ነበር። በግሌ ቁጥር አንድ ውድድር ብዬዋለኹ።
ከዚህ ልብ ሰቃይ ሩጫ ጋር የሚስተካከል እስካሁን አላየሁም። በግርማ ሞገስ ደረጃ ደግሞ ቀነሲሳና ስለሺ ስሕን ተከታትለው የገቡበት፣ ኃይሌን በዓይናቸው ወደ ኋላቸው የፈለጉበት፣ ቴዲ አፍሮም “አንበሳ ቀነኒሳ”ን የደረሰበት ሩጫ ፈረንጆቹ “ማጄስቲክ” የሚሉት፣ ባለ ግርማ ሞገስ ውድድር ነበር። በድንገተኝነት በኩል ሚሊዮን ወልዴ በ5 ሺህ ወርቅ የወሰደበት ውድድር በድንገተኛ አስደሳችነቱ፣ በ10 ሺህ ሴቶች አንዲት ቻይናዊት ወርቁን ከእጃችን “የሰረቀችበት” እና ጥሩነሽ ከዚያን ሁሉ ችሎታዋ ጋር በሩን ያገኘችበት ደግሞ በአናዳጅነቱ ወደር ያለው አይመስለኝም። “እነዚህ ቻይናዎች እንደ ጫማቸው አቃጠሉን” የምትለው ቀልድ ያንን ሰሞን የተፈጠረች ይመስለኛል።
እነሆ አሁን ደግሞ ሎንዶንን ኦሎምፒክ በአገረ አሜሪካ እየተከታተልኩ ነው። ኤን.ቢ.ሲ 24 ሰዓት እየደጋገመ እያሳየ ነው። እውነቱን ለመናገር የትራኩ ውድድር ካልተጀመረ በስተቀር ኦሎምፒኩ የተጀመረ-የተጀመረም አይመስልም። ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ እንጂ ለሌሎቹ አገሮች የደመቀ ውድድር በመካሄድ ላይ ነው። ወርቁንም እያፈሱት ነው። የኢትዮጵያውያን የግል ውድድር የሚመስለው የመካከለኛና የረዝም ርቀት ሩጫ እስኪመጣ ድረስ ግን ብዙም ደማችን አይሞቅም።
ኦሎምፒክ የአሜሪካውያንም የቤተሰብ ስፖርት ተደርጎ እንደሚቆጠር ሚዲያዎቻቸው እየተናገሩ ነው። ልክ እንደ ክሪስማስና ታንክስጊቪንግ በዓሎቻቸው፣ ከሕጻን እስከ አሮጊት ተሰብስበው እንደሚያዩት፣ ይህም ለብዙ ዓመታት የነበረ የስፖርት ባህላቸው መሆኑን ሰሞኑን የሚቀርቡት ዝግጅቶች ሲያትቱ ተመልክቻለኹ። በልቤ “የኛን ባያችሁ፤ ለአቦ ለሥላሴ እየተሳልን በዕንባ ስንከታተል” እላለኹ። “ቀላል?” አሉ የአራዳ ልጆች። ኦሎምፒክ እኮ ነው!!!!!! ትዝታ ዘኦሎምፒክ በዚህ ተፈጸመ።   

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::
     
  

6 comments:

Anonymous said...

ይመችህ ወንድማችን ኤፍሬም! በጣም የተመቸኝ ወኔ ቀስቃሽ ጽሑፍ ነው! በርታልን!

Aweqe said...

qale hiywet yasemalin wendime Dn. Ephrem.
Good thoughts

Anonymous said...

Thank you, EFR!! The article is good. Why you forget Ibrahim Jailah, the fantastic runner?

Gebre Z Cape said...

Thanks Ephrem, that is great piece reminding our athletics history.

All the best for the rest of London Olympics. Lela 2 Gold Jeba bilun min alebet.

Anonymous said...

ወይ ጉድ የአትሌቶቻችንን ድል በጉጉት እኮ ነው የምንጠብቀው እኔ በጣም ነው የሚገርመኝ ሲሸነፉ እንዴት እንደማዝን ሲያሸንፉ ወርቁን ነሐሱን ሲያገኙ እንዴት ደስ እንደሚለኝ ለመግለጽ ያስቸግራል
አይ ኢትዮጵያዊነት

Anonymous said...

ሀምሌ 27/2004 ዓ.ም
ህብረት ነው ድላችን
ጥሩነሽ ዲባባ ወርቅ ልታመጣ ስትሮጥ በወኔ'
ተስፈንጥራ ወጥታ እንደ አቦሸማኔ'
ፈር ቀዳጅ ነበረች ወርቅነሽ ኪዳኔ::
ሶስት ሆነው በተርታ ከፊትም ከኋላ'
አዳክመው አድክመው ዙር ሲከር ሲላላ'
አይበገሬ ናቸው በህብረት በጋራ ዘይደዋል መላ ::
አንዳንዱም ሲጀመር ተወርውሮ ወጥቶ'
በመጨረሻው ላይ ቀረ ተጎትቶ::
ሙያ በልብ እንጅ አይደለም በወሬ'
ቀድሞ አይፎከርም ነውር ነው በሀገሬ::
በተግባር ሲገለጽ የድሉ ምስራች'
ያገሬ ባንዲራ በለንደን ኦሎምፒክ በጥሩዬ ምክንያት ከፍ ብላ ታየች::
ኢትዮጵያ ሀገሬ ምንጊዜም ያልሆነች የወላድ መካን'
ጥሩዬ አመጣችው ዛሬም እንደጥንቱ ወርቁን በለንደን::
ባሯሯጥዋ ማማር አለም ሲደነቅ'
ተውባ ብቅ አለች ባንዲራዋን ለብሳ አድምቃው በሳቅ::
ምክንያቱ ምንድንነው? ብሎ ለሚጠይቅ የድሏን ሚስጢር'
ብዙም አያስጨ”ቅ አይሻም ምርምር::
ታሪኩ ሲፈተሽ ሲቃኝ ወደ ኋላ'
እኛ ኢትዮጵያውያን ድላችን ህብረት ነው ህብረትም ድላችን አይምስላችሁ ሌላ::
ከአራት አመት በፊት የቤጅንግ ኦሎምፒክ ሲቃኝ በትዝታ'
ምን ተወስቶ ነበር በጥሩየ ዙሪያ እስኪ አናንሳው ላፍታ::


ነሀሴ 09/2000 ዓ.ም
እናት ስም አውቃለች
እምየ ጥሩነሽ ያገሬ ልጅ ወርቋ'
በኦሎምፒክ መንደር ባይን ያለማለቋ::
ሁሉ ሲያስተውላት በቤጅንግ ኦሎምፒክ'
ተገርሞ ተደንቆ በዓሯሯጥ ስልቷ በጣም በመማረክ::
በቴሌቭዢን መስኮት አስተያየት ሰጪው::
“ጥሩነሽ ናት እኮ በጥሩ ሁኔታ” ይላታል ደጋግሞ'
ልቡ በማወቁ ድሏን አስቀድሞ::
ወርቁን አመጣችው ለናት ኢትዮጵያ'
ሪከርዱን ሰብራ ከኋላ አስከትላ የኛ ባለሙያ::
እናት ስም አውቃለች ለአንች ስታወጣ'
“ጥሩነሽ” አለችሽ ከሁሉ አስበልጣ::
ሩጫው ሲጀመር በጣም ተጨንቄ'
አየሩ ከባድ ነው ተብሎ ሲነገር ቀድሞ በማወቄ'
እስዋን ምን በግሯት ድል አርጋ ብቅ አለች አጅሪት ጠንቃቄ::
እንኳን በአየር ንብረት ሙቀት ቅዝቃዜ'
ከመውደቅ ተነስታ አሸንፋ የለ ባለፈውስ ጊዜ::
ጥሩየ አኮራሽን በኦሎምፒኩ መንደር'
ሌላው ድካም ይዞት ወደ ኋላ ሲቀር::
ከፊትሽ ላይ ዕንኳን ድካም ሳይታብሽ'
ተንጎራደድሽ እኮ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ይዘሽ::
በሱስ መች በቃና- በድል ተደስቶ ያገር ልጅ ሲደውል'
መልሱን ሰጥተሸዋል ሞባይልሽን ይዘሽ ብለሽ ነኝ ባለ ድል::

ስለዚህ ጥሩየ ኑሪልን ለኛማ '
ዐርኪያችን ነሽና ድልን ስንጠማ::


ለአስተያየቶቻችሁ፡- አበባየሁ ዘበነ ተኮላ
ባህር ዳር
ሥልክ:-0920512048 (ሞባይል)
e-mail:-abebayehuzebene@ymail.com
ማሳሰቢያ:-
የመጀመሪያው ግጥም የለንደን ኦሎምፒክ የጥሩነሽ ድልን አስመልክቶ የተጻፈ ሲሆን በሁለተኛ ርእስ እናት ስም አውቃለች በሚል የቀረበው የቤጅንግ ኦሎምፒክ የጥሩነሽን ድል በተመለከተ የተጻፈና በወቅቱም በአማራ ብዙሃን መገናኛ በሬዲዮ በቀጥታ ስርጭት የተላለፈ ነው::

Blog Archive