Monday, August 13, 2012

ዕውቀትና መረጃ - ከማን ወደ ማን?


(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)ዕውቀት ምንድነው? መረጃስ? የሚል ሰፊ ሐተታ የሚፈልግ ዓምድ የሆነ ጥያቄ አለ። በተለያዩ ዘመኖች የዕውቀት እና የመረጃ ማዕከል እና ምንጭ ተደርገው የሚቆጠሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ነበሩ። ግለሰቦች እና ተቋማትም ብቻ ሳይሆኑ መረጃና ዕውቀት ተቀባዩም ክፍል ተለይቶ ይታወቃል፤ ማድረግ ያለበትም ነገር እንዲሁ። ዘመናት ባለፉ ቁጥር ግን ተቋማቱም ሆኑ ግለሰቦቹ፣ ምናልባትም እነዚሁ ተቋማት ያፈሯቸው ሰዎች፣ ምንጭነታቸው እና ተጠያቂነታቸው “ጥያቄ” ውስጥ ሲገባ ለውጥ ይጀመራል። ወይም ለውጡ ዕውቀትን ሳይሆን ጭካኔን በተላበሰ መልኩ ሊዳፈን ይችላል።

በራሴ ግምገማ ስመለከተው ለረዥም ዘመናት የዕውቀት እና የመረጃ ምንጭ ሆነው ሲያገለግሉ የኖሩት ሁለት ዐበይት አካላት መንግሥት እና ቤተ እምነቶች ሲሆኑ መዘውሮቹም በነዚሁ ተቋማት ላይ የተቀመጡ ወይም ተቋማቱ ያፈሯቸው ሰዎች ናቸው። ተቋማቱ ምንም እንኳን ሁለት ቢሆኑም በብዙ የታሪክ አንጓዎች ደግሞ አንድ የሚሆኑበት አጋጣሚ ከመኖሩም በላይ አንዱ የአንዱን ህልውና ሲጠብቁ፣ አንዱ የሌላውን ሕጋዊነት ሲያጸድቁ ይገኛሉ።
ከምሥራቃውያን ባለ ብዙ አማልክቶች እስከ ምዕራባውያን ባለ “አንድ አምላክ” ተከታዮች፣ ከጣዖት አምላኪዎች እስከ ክርስትና እና እስልምና እምነት አራማጆች ድረስ ይህ ምንታዌነት ሲንጸባረቅ ኖሯል። “የእምነት እና መንግሥት” ፍልስፍና አቀንቃኞች ራሳቸውም መሠረተ ሐሳቡን ለማራመድ ሲነሡ የሁለቱን ተቋማት ጋብቻ ተረድተው፣ ፍቺውን ሕጋዊ ለማድረግ ሽተው፣ ሕጋዊነቱንም ለማጽናት የጣሩ መሆኑ እሙን ነው።
እነዚህ ሁለት ተቋማት የመረጃ እና የዕውቀት ምንጭ መሆናቸው ማንኛውንም መረጃ እና ዕውቀት የማጽደቅ መብትም ይዘው መሆኑ ግልጽ ነው። በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ይህንን ‘አረጋጋጭነታቸውን’ የሚጋፋ ማንኛውንም ለውጥ በአዎንታዊነት አልተመለከቱትም፤ አለመመልከትም ብቻ ሳይሆን “ስታትስኮው” እንዲጠበቅ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ። አድርገውማል።
ዛሬ ዓለም የዕውቀትም ሆነ የመረጃ ምንጮቹ ሁለቱ ተቋማት ብቻ አይደሉም። የኑሮ ፍልስፍናው፣ የቀን ተቀን ሕይወቱ ዘዋሪዎች በነዚህ ሁለት ተቋማት ላይ የተቀመጡ ወይም ሁለቱ ተቋማት ብቻ ያፈሯቸው ልሒቃን አይደሉም። ዕውቀትና መረጃ የሚሸመትባቸው የተለያዩ የዕውቀት መስኮቶች ከመስፋታቸው አንጻር እንደ ጥንቱ ዕውቀትም ሆነ መረጃ ቆንጥሮ በመስጠት የራስን ወንበር ማደላደል ከማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል።
ዕውቀትን ለተጠቃሚዎች በመርፌ ቀዳዳ በማንጠባጠብ የዕውቀት ጥማት ላለበት ሕዝብ የዕለት ጥማቱን በማስታገስ፣ ዘላቂ ርካታውን በመቆጣጠር ያልረካ - ነገር ግን - ያልተጠማ አዕምሮ በመፍጠር በልሒቅነት መኖር የማይቻልበት ዘመን ነው። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የሰዎች የአስተሳሰብ መለወጥ ብቻ ሳይሆን ዘመኑ የፈጠረው የቴክኖሎጂ ዕድገት ያመጣው የማይገዳደሩት ለውጥ ነው።
ይህ ዘመን ዕውቀትም ሆነ መረጃ ከተወሰነ ተቋም ወይም ግለሰብ ወጥቶ፣ በተወሰነ ተቋም ወይም ግለሰብ ጸድቆ፣ ከተወሰኑ ተቋማት ወይም ግለሰቦች ብቻ እንዲደርስ ተመጥኖ የሚላክበት ዘመን አይደለም። ዕውቀት ከየትም እየመነጨ፣ የማንንም “ይሁንታ” ሳይጠብቅ ከማይታሰብበት ቦታ ሳይቀር የሚደርስበት የዕውቀትና የመረጃ ምልዓት የሰፈነበት ዘመን ነው። መንግሥታትም፣ ቤተ እምነቶችም፣ የትምህርት ተቋማትም ከዘመኑ ጋር ይራመዱ ካልሆኑ በስተቀር ዘመኑን መግታት አይቻላቸውም።
 እንኳን እነዚህ ተቋማት፣ የመረጃን ሥራ በመቀበል፣ በማቀናበር እና ለሕዝብ በማድረስ ሙያ ላይ የተሠማሩ ሚዲያዎች ሳይቀሩ በዚህ የመረጃ ለውጥ ፍሰት ተነዋውጸዋል። ብዙዎቹም ሥራቸውን ከዘመኑ ጋር ለማጣጣም ሰፊ ለውጥ ለማድረግ ተገድደዋል። በዚህም ሕዝቡ እነርሱን እንዲጠብቅ፣ አሁንም እነርሱን እንዲከታተል፣ ከሌላ ምንጭ የሚያገኘውን መረጃ ከእነርሱ ጋር እንዲያመሳክር ለማድረግ እና አስፈላጊነታቸውን ለማጠየቅ እየደከሙ ነው።
ዘመኑ “የመረጃ ሞኖፖሊ”ን ሁነኛ በሆነ መንገድ እየለወጠው ነው። አንድን እውነት ለማረጋገጥ እንደ ጥንቱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሰዓት ጠብቆ መክፈት፣ ሰዓት ጠብቆ መዝጋት እየቀረ ነው። መረጃ እጃችን ላይ ይዘነው በምንዞረው ተንቀሳቃሽ (ሞባይል) ስልክ፣ በኮምፒውተራችን፣ አይ.ፓድን በመሳሰሉ ታብሌቶች (ጽሌዎች፤ Tablet ታብሌት የሚለውን ጽሌ ብለውስ?) በሙሉ ይፈሳል። እንደ ጥንቱ “የዜና ሰዓት ደረሰ፤ የዜና ሰዓት አመለጠኝ” የሚባል ነገር የለም። ዜና አያመልጥም። ሁሌም የዜና ጊዜ ነው።
 መረጃውና ዕውቀቱ እንዲህ የትየለሌ ሲሆን ተቋማዊ ቁጥጥሩ ይፈታል። ክፉውም በጎውም መረጃ እና ዕውቀት በየመስመሩ ይናኛል። የመረጃው ቴክኖሎጂ ሌላ ዘመን ላይ በብዙ ኢንሳይክሎፒዲያ ውስጥ የተደበቁ፣ በመጻሕፍት ገጾች ውስጥ የተወሸቁ እውነቶችን በአንድ “ክሊክ” ርቀት ላይ እንዲገኙ አስችሏቸዋል። ለመካከለኛው ምሥራቅ ወጣቶች ቦንብ በየቤቱ እንዴት እንደሚሠራ ከሚያስተምሩት የአሸባሪዎች ድረ ገጾች ጀምሮ በኦንላይን የነጻ ትምህርት መስጠት እስከጀመሩት ሐርቫርድን እስከመሳሰሉት ድርጅቶች ድረስ ዓለም እና ዕውቀት፣ ዕውቀትና መረጃ ተቀራርበዋል።
መረጃዎችን እና ዕውቀቶችን እንዲገበይ የሚጠበቀውም ሕዝብ በፈንታው የዕውቀትና የመረጃ ምንጭ ሆኗል። በየአካባቢው ስለሚደረጉ ተግባራት ሪፖርት ለማድረግ እና ከመላው ዓለም ለማዳረስ የጋዜጠኝነት ትምህርት ያቀላጠፈ ምሩቅ ጋዜጠኛ መሆን ግድ አይደለም። በብዙ ሺህ ብር የሚገዛ ፎቶ ማንሻ ወይም ቪዲዮ መቅረጫም መያዝ አያስፈልግም። በእጅ ስልክ፣ በትንሽ የፎቶ/ቪዲዮ ካሜራ የሚቀረጹ ፎቶዎች፣ ምስሎች እና ድርጊቶች ታላላቆቹን የሚዲያ ተቋማት ቀልብ የሚስቡ ዜናዎች ይወጣቸዋል።
ሌላውን እንኳን ብንተወው፣ አሁን ሦሪያን በማመስ ላይ ያለውን የእርስበርስ ጦርነት እና የአሳድ መንግሥት ፍጅት ዕለት ተዕለት እየተቀረጹ ያሉት ሥራቸውን ጋዜጠኝነት ባደረጉ ባለሙያዎች ሳይሆን ባገኙት መሣሪያ ፎቶዎችን እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች በመቅረጽ ዘመኑ በፈቀዳቸው የቴክኖሎጂ መንገዶች (በኢንተርኔት) ዩ-ቲዩብን በመሳሰሉ ድረ ገጾች አማካይነት ለዓለም በሚያሰራጩ ዜጎች ነው። ጋዜጠኝነትን ባልተማሩ ነገር ግን መረጃን በሚያሰራጩ ሰዎች ላይ የተመሠረተውን ጋዜጠኝነት ነው ብዙዎች citizen journalism”/ “ዜግነታዊ ጋዜጠኝነት” የሚሉት።
የዜግነታዊ ጋዜጠኝነት የመረጃ ምንጭ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ መንገዶች ከሚዲያዎችም ሆነ ከመንግሥታት ወይም ከሌሎች አካላት የሚሠራጩ መረጃዎች ትክክል መሆን አለመሆናቸውን ከሕዝቡ ማረጋገጫ የሚገኝባቸው ጥሩ ማረሚያዎች በመሆን ላይ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የለንደን ኦሎምፒክን በአሜሪካ ለማሠራጨት ሙሉ ኮንትራነቱን በሞኖፖል የያዘው ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤን.ቢ.ሲ ውድድሮቹን በቀጥታ ከማስተላለተፍ ይልቅ እየቀዳ ፊልሞቹን እሱ በፈቀደው ሰዓት በማስተላለፉ የተበሳጩ ብዙ ተመልካቾች ይህንን ብስጭታቸውን በድረ ገጾች አማካይነት (ለምሳሌ በትዊተር) በግልጽ ሲያስተጋቡ ሰንብተዋል።
ኤን.ቢ.ሲ ይህንን ማድረጉን “ሕዝቡ እንደወደደው አድርጎ ሲያቀርብ የነበረውን ዘገባ ባዶ ያስቀረበት ይህ የተመልካቹ አስተያየት ያለምንም ሳንሱር በትዊተር አማካይነት መቅረቡ የቴሌቪዥን ጣቢያውን “እውነት” ለማረቅ እና የሕዝቡ ስሜት ሌላ መሆኑን ለማሳየት ረድቷል። ኤን.ቢ.ሲ ግን በዚህ ደስተኛ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይባስ ብሎ በጉዳዩ ላይ በተደጋጋሚ የሚጽፍን አንድ ጋዜጠኛ “ትዊተር ገጽ” እንዳይነበብ ለማገድ ሞክረውም ነበር። ጉዳዩ ሲታወቅና ጋዜጠኞች ከየአቅጣጫው ሲንጫጩ ጣቢያው በጠበቆቹ አማካይነት ይቅርታ ጠይቆ ስህተቱን ለማረም ሲሞክር ሰንብቷል።
ዜጎች ሙያቸው ባይሆንም ወደ ግዘጣው ሥራ የሚገቡት በአካባቢያቸው ያለው የመረጃ አያያዝና አሰረጫጨት ሁኔታ ትክክል አይደለም ብለው ሲያምኑ እንደሆነ ከብዙዎች መነሻ መመልከት ይቻላል። ለዚህም ደግሞ ዘመኑ የፈጠረው የብሎጊንግ (የጡመራ፣ blogging) እና ማኅበራዊ ድረ ገጽ (social media) ቴክኖሎጂ ትልቅ ዕድል ፈጣሪ ለመሆን ችሏል።ነጻነት ባለባቸው አገሮች እነዚህ ዜጎች በግልጽ ማንነታቸውን እና አድራሻቸውን ሳይደብቁ ሲጽፉና ሐሳባቸውን ሲገልጹ፣ ነጻነት በሌለባቸው እና አደጋ በሚያሰጋቸው አካካባቢዎች ያሉቱ ደግሞ በ“ስም-የለሽነት/ anonymously” መጻፍን ይመርጣሉ።
አሜሪካውያን ሳዳም ሁሴን/ ኢራቅ ላይ የማያዳግመው ጦርነት ሲያውጁ የዕለት ተዕለት መረጃዎችን በጡመራው እየጻፈ ለዓለም ጋዜጠኞች የመረጃ መስኮት የነበረው አንድ ሰው ጋዜጠኛ አልነበረም። የአረቦቹን ተከታታይ ሕዝባዊ ነውጦች በየዕለቱ ይፋ ያደርጉ የነበሩት ተራ ዜጎች ናቸው። በሎስ አንጀለስ የአንድ ጥቁር አሜሪካዊን በአሰቃቂ ሁኔታ በፖሊስ መደብደብ በቪዲዮዋቸው ቀርጸው ይፋ ያደረጉት ተርታ ግለሰቦች/ዜጎች ናቸው። ሌላው ቢቀር ኮሞሮስ ላይ ተጠልፎ ባሕር ላይ የወደቀውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተዓምራታዊ ትንግርት የቀረጹት በመዝናናት ላይ የነበሩ ቱሪስቶች አይደሉምን?
እያንዳንዳችን የዕውቀት እና የመረጃ ምንጮች ነን። ዜጎች ይህንን ችሎታቸውን ከተረዱ በእጃቸው ከሚይዙት ስልክ ጀምሮ ታሪክ ሊሠሩበት የሚችሉት ብዙ መሣሪያ እንዳላቸው ይረዳሉ። ዘመኑ የመረጃ ነው!!!      
    


© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::
     
  

6 comments:

Tihitina Beyene said...

Ejeg betam konjo temhert new lentekemebet yegebale balen neger ye Eweket balebatoch mehon enchelalen ejihe yebarekelen

Anonymous said...

ይህን ያልተረዱ በስም እውቀትን ተሸክመው ትንሿን ብቻ ይዘውአዋቂዎች እኛ ብቻ ነን የሚሉትን የእውቀት የግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶችን ወይም niet work siyet ይዘጉ እያሉ ያሉትን ምንእበላቸው

Anonymous said...

Good Analysis!!!

Anonymous said...

It Initiates me to practice "citizen journalism"! Thank you!Keep on writing!

Abel said...

ወንድማችን፣ ድገመ-ድገመን-ድገምን ብያለሁ። እጅግ ውብ፣ማራኪና አስተማሪ መጣጥፍ። በተለይ ለእኛ ለአብዛኛዎቹ ኢትዬጵያዉያን፣ እንዲህ ሆነ አሉ የምትለዋን መረጃ የምንወድ። መረጃ አመንጭ ሳንሆን ተቀባይ፤ ስንቀበልም ጨው ጨመር አርገን የምናስተላልፍ የዘመኑ መሳለቂያዎች ስንቶቻችን እንሆን? ምን ላቅርብ፤ ምን ልስራ ሳይሆን ምን ተባለ ለሚለው ጊዜአችንን የሰዋን ጥሩ አስተማሪ ናት። ጣቶችህ ይባረኩ።

Anonymous said...

Add me!

Blog Archive