Wednesday, August 29, 2012

ከ“ዜግነታዊ ጋዜጠኝነት” አንዱ “ጡመራ”


(ኤፍሬም እሸቴ/ www.adebabay.com/ PDF)ባለፈው ስለ ዕውቀት ምንነት እና ስለመረጃ” በተለያዩ ዘመኖች የዕውቀት እና የመረጃ ማዕከል እና ምንጭ ተደርገው የሚቆጠሩ ግለሰቦች እና ተቋማት እንዲሁም ስለ መረጃና ዕውቀት ተቀባዩም ክፍል መጠነኛ ሐሳቦች ለማካፈል መሞከሬን፣ እያንዳንዳችን የዕውቀት እና የመረጃ ምንጮች መሆናችንን፣ ዜጎች ይህንን ችሎታቸውን ከተረዱ በእጃቸው ከሚይዙት ስልክ ጀምሮ ታሪክ ሊሠሩበት የሚችሉት ብዙ መሣሪያ እንዳላቸው እንደሚረዱ፣ ዘመኑ የመረጃ መሆኑን መጠቆሜን ለማሳየት መሞከሬን፣ ጋዜጠኝነትን ባልተማሩ ነገር ግን መረጃን በሚያሰራጩ ሰዎች ላይ የተመሠረተን ጋዜጠኝነት ብዙዎች citizen journalism”/ “ዜግነታዊ ጋዜጠኝነት” እንደሚሉት በማስታወስ ልጀምር።

ይህ ዜጎች ሐሳባቸውን እና እይታቸውን፣ መረጃቸውን እና ዕውቀታቸውን ለማካፈል ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል ብሎጊንግ ወይም ጡመራ (መ ይጠብቃል) አንዱ ነው። በግለሰባዊ አስተሳሰብ እና ተሞክሮ ላይ የተመሠረተ፣ እጅግ በጣም ረቂቅ እና ምጡቅ የሆነ የግዘጣ (የጋዜጠኝነት) ሙያን ወይም ልሒቃዊ አካዳማዊነትን የማይጠይቅ በአንዲት በተመረጠች ጉዳይ ላይ የግል እሳቤን በማካፈል ላይ የተመረኮዘ ዘመን-ወለድ፣ ዘመን ያስገኘው መድረክ ነው። 
የኢንተርኔትን ውልደት እና ዕድገት ወደ ኋላ ሄዶ መተንተን ሳያስፈልግ በግሌ የግል ኢ-ሜይል ፈጥሬ፣ ኢንተርኔት መክፈት ችዬ በኮምፒውተር መስኮት ከምሥራቅ አፍሪካ ከተማዬ ተቀምጬ ዓለምን መመልከት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ወቅት ብቻ እንኳን ስቃኘው ኢንተርኔቱ ዓለም ያሳየው ዕድገት በ10 ዓመት ውስጥ ይመጣል ተብሎ የማይጠበቅ ይሆንብኛል። አንድ ኮምፒውተር መግዛት መኪና እንደ መግዛት ዓይነት ትልቅ “ኢንቨስትመንት” ከነበረበት ዘመን፣ አሁን በየግለሰቡ እጅ አንድ ላፕቶፕ መኖር ከማይደንቅበት ጊዜ ላይ ተደርሷል።
ዜጎች ኮምፒውተርን የሚያክል መሣሪያ ሲያገኙ፣ ከዓለም የሚቀላቅላቸው የሕዋው መረብ ኢንተርኔት ሲፈጠርላቸው፣ ይህንን ሐሳባቸውን በነጻ የሚያስተናግዱ “ነጻ ሰሌዳዎች” በነጻ ሲበረከትላቸው፣ እጃቸውን ከብዕር ጋር እያገናኙ መጻፍ፣ የጻፉትንም በኢንተርኔት መልቀቅ ጀመሩ። ይህም አዛዥ፣ ናዛዥ የሌለበት የዕውቀት ገበያን “የጡመራ መድረክን” (ብሎግን) አስገኘ። ስለዚህም በዕድገት ከገለጸገው እስከ ታዳጊው አገር ዜጋ፣ ፀሐይ አውቆት አገር አውቆት ከሚጽፈው፣ በድብቅ ማንነቱን ሰውሮ “በስም የለሽነት/anonymously” እስከሚኖረው፣ ስለ ጡመራው ገንዘብ ከሚያገኝበት በመጦመሩ ወደ ወሕኒ እስከሚወረወረው ያለውን የጦማሪ ዓይነት አፈራ።
የሳንቲም ስባሪ ሳያወጡ ነገር ግን ጊዜን በመሰዋት ብቻ ሐሳብን በአንድ ጊዜ ለመላው ዓለም ማዳረስ የሚቻልበት ዘፊ ዕድል ተከፍቷል። ጋዜጣና መጽሔት በማሳተም፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በማቋቋም ወይም መጻሕፍትን በመጻፍ ብቻ ሊሠራጩ ይችሉ የነበሩ አስተሳሰቦች፣ ዕውቀቶችና መረጃዎች ምንም ዓይነት ድርጅት ሳይኖር በግል ጦማሪዎች ብቻ የሚፈጠሩበት ዘመን ተወልዷል። የቴክኖሎጂው ዓይነት እና ቅሩብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ፣ እየቀለለ፣ ዘመናዊ እየሆነ መጥቷል።
ወደ ጡመራው ዓለም ከተቀላቀልኩበት ከኤ.አ ከ2006 ጀምሮ ባሉት ጥቂት ዓመታት እንደተመለከትኩት የሌላውን ዓለም ትተን በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩና በኢትዮጵያውያን የሚዘጋጁ ድረ ገጾች የመኖራቸውን ያህል ጡመራ ግን ብዙም የተለመደ አልነበረም። በአማርኛ የሚጦምሩ ፀሐፍያን (ጦማርያን) አልነበሩም። በየድረ ገጹ የሚጽፉት ጥቂት ፀሐፍትም ቢሆኑ መግባቢያቸው በዋነኝነት እንግሊዝኛው ነበር። በአማርኛ ላለመጻፍ ምክንያት የሚመስሉኝ የአማርኛው ሶፍትዌር እንደሌሎቹ ቋንቋዎች በቀላሉ አለመገኘቱ፣ ኮምፒውተርና ሶፍትዌር አምራቾች (ዛሬም ድረስ እንደሚያደርጉት) ብዙም ትርፍ ለማያገኙበት ለድሃው ዓለም ትኩረት አለመስጠታቸው፣ በዚህም አማርኛን የመሳሰሉ ቋንቋዎች በኢንተርኔቱ ዓለም ያላቸው ተደራሽነት ጥቂት ወይም ከባድ መሆኑ ነው።
 በአማርኛ ቋንቋ መጦመርን እንደ ብቸኛ መጠቀሚያ ቋንቋ በማድረግ በኩል ሃይማኖታዊ ጦማሪዎች ይቀድማሉ ብዬ እገምታለኹ። ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የሚዘጋጀው ደጀ ሰላም (http://www.dejeselam.org/) ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአማርኛ ብቻ ሲጦምር የቆየ ሲሆን ከዚያ ተከትሎ ያለ እንግሊዝኛ ረዳትነት ሐሳባቸውን በነጻነት መግለጽ የሚችሉ ብዙ የጡመራ መድረኮች ተፈጥረዋል። ጉዳዩን የሚያጠኑ ባለሙያዎች የበለጠ የሚያስፋፉት ቢሆንም በወፍ በረር ካየሁት ተነሥቼ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ብዙ በካር-ጦማርያን (amateur bloggers) ወደዚሁ ቴክኖሎጂ ወለድ የብዕር ገበታ ተቀላቅለዋል። ገና አንድም ሁለትም ዓመት የሞላቸውን እንኳን ብተው የፍትሕ ጋዜጣ ፀሐፊ የነበረውና አሁን በውጪው ዓለም ላለነው በተለይ በጡመራው ጽሑፎቹን የሚያስኮመኩመን “አቤ ቶኪቻው/ አበበ ቶላ” (http://www.abetokichaw.com) የአዳዲሶቹ የአማርኛ ጦማርያን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
 የቀድሞዎቹ ድረ ገጾች እንደሚያደርጉት በእንግሊዝኛ የሚጦምሩ ኢትዮጵያውያን ብዙ ቢሆኑም በአማርኛ ወይም በሌላ አገርኛ ቋንቋ የሚጽፉትን የበለጠ አበረታታለኹ። ለቋንቋዎቹ ዕድገት የሚጠቅመውና ለአንባቢው ሥነ ልቡናም ቅርብ የሆነው አገርኛው ቋንቋ ነው ብዬ አምናለኹ። ቋንቋውን በማያውቁ ሰዎች ዘንድ ለውን ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ እና ዓለማቀፋዊ ተነባቢነትን ለመጨመር ለሚሹ በእንግሊዝኛ ወይም በሌላ ሰፊ ተናጋሪ ቁጥር ባላቸው ቋንቋዎች መጻፉ አሌ የማይባል ነው። በአገርኛ ቋንቋም ይሁን በውጪው ተጦመረ ዋናው ጉዳይ ግን መጦመሩ እና ለአንባቢ መድረሱ ነው።
ወደ ጡመራው ዓለም የሚቀላቀል ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ቢነሣም መጻፉ ግን ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል። በቅርቡ ያነበብኩት ጄፍ ቡላስ (“Jeff Bullas”) የተባለ ጦማሪ የዘረዘራቸው፣ እኔም በግሌ የማውቃቸውን የተወሰኑ ሐሳቦች እንመልከት። በመጀመሪያ ለመጦመር የሚታትር በካር-ጦማሪ እግረ መንገዱን በሁለት እግሩ የሚቆም ፀሐፊ ለመሆን ይረዳዋል። ውኃ ውስጥ ሳይገቡ ዋናተኛ፣ ሳይሮጡ ማራቶነኛ መሆን አይቻልም። ከብዙ ስሕተቶች በኋላ ስሕተቶቹን እያረመ፣ ጠንካራዎቹን እያጎለመሰ ጥሩ ፀሐፊ ይወጣዋል።
በሁለተኛ ደረጃ “ጡመራ” በራሱ መማሪያ ነው። ለመጦመር ሲባል፣ ማንበብ፣ ማገናዘብ፣ አንዱን መረጃ ከሌላው ጋር ማስተያየት ስለሚጠይቅ ያለውድ በግድ፣ ትምህርት ቤት ሳይገቡ መማር ይሆናል። ስቴፋን ኪንግ የተባለው የዘመናዊ ልቦለዶች ታዋቂ ደራሲ እንዳለው “ደራሲ መሆን ከፈለግህ ሁለት ነገሮችን ከሌላው ነገር ሁሉ አብልጠህ አድርግ። ብዙ አንብብ፤ ብዙ ጻፍ።” እኔም ለራሴ እንዲህ ልበላ!! “ውድ ኤፍሬም፦ ጥሩ ጦማሪ ለመሆን ከፈለግህ፣ ሁለት ነገሮች ከሁሉ አብልጠህ አዘውትር። ብዙ አንብብ፤ ብዙ ጻፍ” 
ከዚህም በላይ፣ በተለይ በውጪው ዓለም ያሉ ጦማርያን፣ በመጦመራቸው ምክንያት ታዋቂነትን ያተርፉበታል፣ መጻሕፍትን ለማሳተም እና በዚህም በገንዘብ ደረጃ ራሳቸውን ለመጥቀም ብሎም በኤክስፐርትነት ለመታወቅ እና ዝነኛ ሆነው በየሚዲያው ለመቅረብ ያስችላቸዋል። ይህ ሁሉም ቢቀር ለመጻፍ የሚታትር ሰው ለሰው አደርሳለሁ ብሎ በሚሞክረው የንባብና የምርምር ሙከራ ራሱን መጥቀሙ አይቀሬ ይሆናል።
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች ደግሞ ጡመራ እጅግ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለኹ። አገሪቱ አፈራቸው ሚዲያ እና ባለሙያ በብዛት እና በነጻነት ሁሉንም ነገር ለሁሉ አንባቢ ማድረስ ስለማይችል የግል ጦማርያን ክፍተቱን ለመሙላት ይችላሉ። መደበኛው ባለሙያ ጋዜጠኛ እንደ አነስተኛ ነገር ብዙም ሳይመለከት የሚያልፋቸውን ጥቃቅን ጉዳዮች ጦማሪው ብርሃን ሊፈነጥቅባቸው ይችላል።
ከውጭ አገር ሆኖ የአገሩን ሁኔታ በጉጉት እንደሚከታተል ሰው በተለይም ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በክፍለ አገር ያሉ እና ስለ አካባቢያቸው ሁኔታ የሚጽፉ ጦማርያን ቢኖሩ ምኞቴ ነው። ስለ አካባቢው ሕዝብ፣ ስለ አኗኗሩ፣ ስለ አመጋገቡ፣ ስለ ወጣቱ-ሴቱ-አዛውንቱ ወዘተ ወዘተ … የሚጽፉ ቢገኙ። ያንን ደግሞ መጽሐፍ አድርገው ለትውልድ የሚያቆዩ። በየዩኒቨርሲቲው፣ በየከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቱ የሚገኙ መምህራንና ሌሎችም ባለሙያዎች ብዕራቸውን ቢያነሱ እንዴት ደስ ይል ነበር።
የመንግሥት ጋዜጠኞችም ቢሆኑ በዕለት ተዕለት ሥራቸው ከሚያጋጥማቸው ውስጥ ለሚዲያዎቻቸው ፍጆታ የማይሆን፣ ነገር ግን በተባ ብዕራቸው ለአንባብያን ሊያደርሱት የሚችሉት ብዙ ቁም ነገር የማግኘት ዕድል አላቸው። ያንን በግል የጡመራ መድረካቸው ላይ ቢያወጡት ትልቅ ቁም ነገር ይሆናል።
የግል ጡመራ ሲባል የተለየ እና ከባድ ይመስላል እንጂ ብዙው ሰው ሳያውቀው ብዙ ነገር ሲጽፍና ሲአበረክት ይውላል። በተለይም “በሶሻል ሚዲያዎች” (ማኅበራዊ ድረ ገጾች) ላይ አስተያታቸውን የሚሰጡ ብዙዎች ናቸው። ያንን መልክ አስይዘውና በመጠኑ ሰፋ አድርገው ቢያቀርቡት ጦማርያን እንላቸው ነበር። ከመዝናናቱ ጋር ዕውቀት ቢያካፍሉን ዜግነታዊ ጋዜጠኝነትን እያካሄዱ ነው ማለት ነው።
ይቆየንና ያቆየን።

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::
     
  

No comments:

Blog Archive