Friday, August 31, 2012

ስለ “ግለሰብ እና ሕዝብ፤ ታሪክ እና ያለፈ ጉዳይ”ከዚህ በታች ያለው ጽሑፍ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሰጥተውት በነበረ ቃለ ምልልስ ላይ ተመርኩዞ  Sunday, March 20, 2011 (Part 1) Saturday, March 26, 2011 (Part 2) ላይ በዚሁ የጡመራ መድረክ ላይ የወጣ ነበር። ያላነበቡ ወዳጆቼ እንዲያዩት በሚል በድጋሚ በአንድ ላይ ተዘጋጅቷል። (READ IN PDF)
(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com Sunday, March 20, 2011 Saturday, March 26, 2011):- ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰፊ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ተመልከቼ ነበር። በተለይም በሊቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ እንዲሁም በጅማ እና አካባቢው ያለውን የሃይማኖት ግጭት በተመለከተ ምን እንዳሉ በስፋት ለመስማት ፈልጌ ነበር። በዩ-ቲዩብ ተቆራረጦ ከተቀመጠው የጠ/ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ ጥያቄና መልስ መካከል ባሰብኩት መልኩ ባይሆንም የ“ቁምነገር” መጽሔት ጋዜጠኛ ያነሣቸው ጥያቄዎች እና አቶ መለስ የሰጧቸው መልሶች ይህንን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ምክንያት ሆኑኝ።

ጥያቄው ለአጼ ኃ/ሥላሴ ሐውልት እንዲቆምላቸው ይደረግ ወይም አይደረግ እንደሆነ የሚያነሣ ሲሆን በመልሳቸው አቶ መለስ ስለ ሐውልት፣ ስለ ሕዝብ እና ግለሰብዕ በሰፊው አትተዋል። ሐውልት ማቆም ላይ የግሌ አስተያየት በተቻለ መጠን የግለሰቦችን ተክለ ሰውነት በሚያሳይ መልኩ ወይም ያንን በሚያጠናክር መልኩ ባይሆን ይመረጣል” የሚሉት አቶ መለስ ግለሰቦች አይደሉም ታሪክ የሚሠሩት ሕዝብ ነው ታሪክ የሚሠራው። ስለዚህ የግለሰቦች ሐውልት፣ አንድ ለየት ያለ መልዕክት ለማስተላለፍ ካልሆነ በስተቀር ያንን ግለሰብ በተምሳሌት በመውሰድ ለሕብረተሰቡ አንድ ለየት ያለ መልዕክት ማስተላለፍ የሚችል ካልሆነ በስተቀር የሚመረጥ ጉዳይ አይደለም ብዬ ነው የማምነው” ሲሉ ያትታሉ።
በዚህ አጭር አነጋገር ብዙ ጉዳይ አንሥተዋል፤ ወይም እንዳነሡ ተሰምቶኛል። መቼም ስለ ሐውልት አሁን ለመነጋገር ጊዜው አይደለም። ባይሆን ቅዱስነታቸው ሐውልታቸውን ያቆሙ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይህንን ብለው ቢሆን ኖሮ የሐውልቱን መገንባት የምንቃወምበት አንድ ተጨማሪ “ነጥብ” ይሰጡን ነበር። በትምህርተ-ተዋሕዶ መሠረት የተነገራቸውን እና አልቀበለው ያሉትን፣ ቅ/ሲኖዶስ ከወሰነውም በኋላ አልፈጽመው ያሉትን ውሳኔ “ኧረ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አይቀበሉትም፣ እባክዎ ቅዱስ አባታችን” ብለን ይሉኝታ ውስጥ እናስገባቸው ነበር። ግን ሳይሆን ቀረ።
በጠ/ሚኒስትሩ አመለካከት ግለሰቦች ሐውልት እንዲቀረጽላቸው ብዙም ፍላጎት የላቸውም። በጣም የተለየ እና “በሐውልት እና በሐውልት ብቻ” ካልሆነ በስተቀር በሌላ መልኩ ሊተላለፍ የማይችል መልእክት ያዘለ ካልሆነ በስተቀር። በሌላ ነገር የማይገለጽ፣ ሐውልት በመቅረጽ ብቻ የሚገለጽ ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ለጊዜው አልመጣልኝም።
በዚሁ አጋጣሚ ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ “ግለሰቦች አይደሉም ታሪክ የሚሠሩት ሕዝብ ነው ታሪክ የሚሠራው” ሲሉ ትልቅ ጉዳይ አነሡና አስደመሙኝ። ቃለ ምልልሱን ገታ አድርጌ ከራሴ ጋር ትንሽ ተወያየሁ። ይህንን አባባላቸውን በሌላ አማርኛ ከዚህ በፊትም ሰምቼው አውቃለኹ። ያኔም አልተቀበልኩትም ነበር። ቀላል ሒሳብ ነገር ነው ልበል? “አንድ” የብዙ “ቅንጣት” ነው። ብዙ አንዳንድ-ቅንጣቶች ደግሞ ብዙ መሆናቸው እርግጥ ነው። አንድ ከሌለ ብዙ ከየት ይመጣል? አንድ ሰው ከሌሎች አንድ ሰዎች ጋር ሲደመር ሲደማመር ብዙ አንዶች ይሆናል። ያንን ብዙ ሰዎች ሕዝብ እንበለው። እና ከግለሰብ ወደ ሕዝብ ደረስን ማለትም አይደል? “የምን ፍልስምና ነው?” ለሚለኝ ጥንት ሳይገባኝ ባለፈው “ፊሎዞፊ 101” እኔም የራሴን መሞከሬ ተደርጎ ይወሰድልኝ። ከዚህ በታች ያለውን ሐሳብ ግን በቅጡ ማቅረብ እችላለኹ።
ግለ ሰብዕ ከሌለ ሕዝብ የሚባል ነገር የለም። እኛ ግለሰቦች ነን ሕዝብ የምንሆነው። ግለሰቦች ታሪክ ስንሠራ ሕዝብ ታሪክ ሠራ ሊባል ይችል ይሆናል። ሕዝብ ብቻውን እንኳን ታሪክ ሊሠራ ህልውናም የለው። እኛ ግለሰቦች ነን ለራሳችን የጋራ ስም ስንፈጥር ራሳችንን ሕዝብ ያልነው። ምናልባት በምሥራቁ እና በምዕራቡ ካምፕ የተነሡ የተለያዩ ሊቃውንት “ሕዝብ ይበልጣል፣ ግለሰብ ይበልጣል፤ ሕዝብ ነው ቅድሚያ ማግኘት ያለበት፣ ግለሰብዕ ነው ቅድሚያ ማግኘት” ሲሉ የተከራከሩበት ብዙ ዶሴ ይኖር ይሆናል። ሙያዬም ንባቤም እዚያ ስላላደረሰኝ ያንን መጥቀስ አልቻልኩም። የማንንም “ማርክስ”፣ የማንንም “ሌኒን”፣ የማንንም “ማርቲን ሉተር ኪንግ” ሳልጠቅስ ለባዊት ነፍሴ የነገረችኝንና እኔም ትርጉም የሰጠኝን “እንደወረደ” እጽፋለኹ።
አገር የሚለውጥ፣ የታሪክ ሒደት የሚቀይረው ግለሰብዕ ነው። ዓለማችን በዚህ በኩል ሊጠቀሱ የሚችሉ ብዙ አብነቶች ስላሏት ብዙም የሚያስቸግር አይሆንም። ጥያቄው ሰዎቹ በዚያ በፈፀሙት ድርጊት ውስጥ ያላቸው ቦታ ነው። ለምሳሌ አጼ ቴዎድሮስን እናንሣ። ለእርሳቸው እዚያ መድረስ የጓደኞቻቸው እና የወታደሮቻቸው አስተዋጽዖ የሚካድ ባይሆንም ካሣ ባይነሡ ኖሮ ቴዎድሮስ የሚባል ንጉሥ ይኖር ነበር? በካሣ ቴዎድሮስነት ውስጥ የካሣ የብቻቸው ድርሻ ምን ያህል ፐርሰንት ነው? አጼ ምኒልክ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ሲነሱ የእርሳቸው በዚያች የታሪክ አጋጣሚ ንጉሥ መሆን ለድሉ አስተዋጽዖ ነበረው ወይስ አልነበረውም? ንጉሡ ማንም ይሁን ማን “ሕዝቡ” እስካለ ድረስ ጣሊያን በአድዋ ድል መሆኑ አይቀሬ ነበር? አስተዋዩዋ ጣይቱ ባይኖሩ የሚቀየር የታሪክ ውጤት አይኖርም ነበር? ሌላውን ሁሉ ብንተወው ኢሕአዴግ ያለ መለስ ዜናዊ አሁን ያለውን ኢሕአዴግ ይሆን ነበር? ከላይ ላነሣኋቸው ጥያቄዎች ሁሉ መልሴ አይሆንም ነው።
  ካሣ ኃይሉ ራሱን አጼ ቴዎድሮስ አድርጓል። ምኒልክ እና ጣይቱ ባይኖሩ አድዋ አሁን እንደምንኮራበት ላይሆን ይችል ነበር። መለስም ባይኖሩ ኖሮ ኢሕአዴግ አሁን ባለው መልኩ ላናገኘው እንችል ነበር። ያለ መንግሥቱ ኃ/ማርያም “ደርግ” ከኮሚቴነቱ አልፎ ለ17 ዓመታት የዘለቀ መንግሥት መሆን አይችልም ነበር።
ይህ የምኖርበት የምዕራቡ ዓለም የአስተሳሰባቸው እና የዕድገታቸው መሠረቱ ግለሰባዊ የማሰብ ነጻነታቸው እና የግለሰቦች ከፍ ያለ የፈጠራ ምንጭ መሆኑን እንድረዳ አድርጎኛል። የጥንቱን የፍልስፍና እና የቴክኖሎጂ ዓለም እና ግለሰቦች ያመጡትን ለውጥ መጥቀስ እንኳን ብንተው ባለፉት 10 ዓመታት የዓለምን የቴክኖሎጂ አስተሳሰብ የለወጡትን ግኝቶች ብንመለከት ለውጦቹ የመጡት በጥቂት ግለሰቦች ፈጠራ መሆኑን እንረዳለን።
ማይክሮሶፍት የተመሠረተው በኮሚቴ አይደለም። የ“ኮሎጅ ድሮፕ አውቱ” (የኮሌጅ ትምህርቱን ያቋረጠው) የቢል ጌትስ አዕምሮ ማይክሮሶፍትን ፈጠረ። ጓደኛው ስቲቭ ጃብስ (Steven Paul Jobs) አፕል/ Apple ኩባንያን እና ዓለምን ያስደነቁትን የአይፎን/ አይ.ፓድ ውጤቶች አመጣ። ለግላጋው ወጣት ማርክ ሱከርበርግ ፌስቡክን አስገኘ፣ ጓደኛሞቹ ሰርጌይ ብሪን እና ላሪ ፔጅ (Sergey Brin and Larry Page) ጉግልን ፈጠሩ። ሁሉም የግለሰቦች ውጤት እንጂ ሕዝብ የምንለው ነገር ውጤት አይደሉም።
የምዕራቡን ዓለም ትተን ወዳገራችን አስተምህሮ ብንመጣ እና የጥንታዊቱን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በወፍ በረር ብንመለከት የቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርት እና የፍልስፍና መዋቅር በግለሰቦች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኖ እናገኘዋለን። ጥንታዊው የኢትዮጵያ ትምህርት በመምህራኑ ማንነት ላይ የተመሠረተ ነው። መምህሩ ባሉበት ትምህርት ቤቱ አለ። መምህሩ በምንም ምክንያት ይሁን በዚያ አካባቢ ሊኖሩ የማይችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ተማሪዎቹ እና ት/ቤቱም አይኖሩም። “ወንበሩ” በመምህሩ ማንነት ላይ የተመሠረተ ነው።

 በሌላ ምሳሌ ቅ/ያሬድ ባይኖር አሁን የምናውቀው ጥንታዊ የኢትዮጵያ ዜማ አይኖርም። የአቡነ ተ/ሃይማኖት መነሣት ባይኖር ክርስትና በመካከለኛው እና በደቡብ ኢትዮጵያ አሁን ባለው መልክ ላይገኝ ይችል ነበር። በመካከለኛው ዘመን ያለውን ታሪካችንን ስንቃኝ እንኳን “አህመድ ኢብን ኢብራሒም አል ጋዚ” ወይም በተለምዶ እንደምናውቀው አህመድ ግራኝ ባይነሣ ኖሮ አሁን በምሥራቅ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ያለው ዓይነት የእምነቶች ሚዛን አይፈጠርም ነበር።

ጓደኛሞቹ ሰርጌይ ብሪን እና ላሪ ፔጅ

አገር እንዲያድግ ከተፈለገ ሰዎች በግላቸው ያላቸው የማሰብ፣ የመፍጠር እና ራሳቸውን የመሆን ነጻነታቸው ሊጠበቅላቸው እና ሊከበርላቸው ይገባል። ሕዝብ በሚባለው ግዑዝ ፍጥረት ስም ግለሰብዕነት ከተጨፈለቀ ራሱ ሕዝብ የሚባለው ነገር ይጨፈለቃል። የምሥራቁ የኮሚኒስት ዓለም ለመፈረካከሱ የተለያዩ ሙያዊ አንድምታዎች እና የአሜሪካ እና የምዕራቡ ዓለም ሴራ ቢሰጡምና ቢጠቀሱም ዋናው ምክንያቱ ግን ኢ-ተፈጥሯዊ የሆነው “ግለሰብዕነትን” የመጨፍለቅ መመሪያው ይመስለኛል።
ሁሉንም ነገር ልክ እንደ ጠጅ ብርሌ፣ እንደ አህያ ልጅ መልክ የማመሳሰል ፍልስፍናው አልተሳካለትም። በአገራችንም ከልብስ አቅም እንኳን የተለያየ ልብስ መልበስ ቁምነገር ሆኖ ሁሉ ካኪ ካልለበሰ በሚለው አባዜ ብዙ ችግር ተፈጥሮ ነበር። ሁሉ እንደ “ሃይ ስኩል” ተማሪ አንድ ዓይነት ካኪ ለብሶ ሲቸገር ማየት አስቂኝ አጋጣሚ ነበር። ይህ ሁሉ ግለሰባዊ ማንነትን ያለመቀበል ነገር ነው።
ይሁን እንጂ ሥነ ተፈጥሮ የሚያስተምረን ከዚህ ተቃራኒ ነው። አንድ አዳም አስቀድሞ ተፈጠረ፤ ከዚያም ብዙ አዳሞች መጡ። የአዳሞችን መብት ለማክበር ቀላሉ መንገድ አዳምን ማክበር ነው። ለአዳሞች (ለአዳሜ) ተብሎ የአንዱ የአዳም ፍላጎት መጨፍለቅ የለበትም። ለዚህ ነው ጠ/ሚኒስትሩ “ታሪክ ሰሪው ሕዝብ እንጂ ግለሰብ አይደለም” ሲሉ የማልቀበላቸው። ይህ አስተያየታቸው በማያሻ መልኩ ስሑት መሆኑ የታየው የምሥራቁ ካምፕ አስተሳሰብ ቅጣይ ነው።
(ይቀጥላል)
ስለግለሰብ እና ሕዝብ፤ ታሪክ እና ያለፈ ጉዳይ” (ካለፈው የቀጠለ)
ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የፖለቲካ ውዝግብ የሚፈጥር ነገር የሚመረጥ አይደለም። በመጪ ጉዳዮች ላይ ብንወዛገብ አንድ ጉዳይ ነው፤ አገራችን እንዴት እናልማ፣ በየት አቅጣጫ እንምራ በሚለው ጉዳይ ላይ ብንከራከር ብንወዛገብ አንድ ጉዳይ ነው። በተወሰነ ደረጃ ገንቢ ገጽታ አለው። ተወያይተን ተመካክረን አንድ የጋራ አቋም ልንይዝ እንችላለን። ባለፈ ጉዳይ ላይ ብንነታረክ ግን ይኼን ያህል ገንቢ ጉዳይ የለውም። ያለፈ ጉዳይ ነው። ሲሉ ያስታወሱኝን አስተሳሰብ ደግሞ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ ባልኩት መሠረት እነሆ የጫርኩትን።
አቶ መለስ “ያለፈ ጉዳይ” ያሉት ስለ አጼ ኃ/ሥላሴ ከመንበረ ሥልጣን መውረድ፣ አሟሟት እና አቀባበር እና ተያያዥ ጉዳዮች መሆኑ ነው። እርሳቸው ለአንድ ታሪካዊ እውነታ እና ታሪካዊ ሰው የጠቀሷት ትንሽ መልስ ብዙ ጓዝ አስታወሰችኝ። አቶ መለስ “ያለፈ ጉዳይ” ያሉት ምንድር ልበለው ብዬ ሳስብ “ታሪክ” ከሚለው ቃል ውጪ ሌላ መልስ ላገኝለት አልቻልኩም። በዚህ ዘመን እና ሁኔታ በተለይም ኢትዮጵያ ልትታረቅበት እና ልታስታርቀው የሚገባት ጉዳይ “መጪው” ብቻ ሳይሆን “ያለፈውም ጉዳይ” ይመስለኛል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከራሳችንም እርስበርሳችንም አላግባባን ያለው የትናንቱ፣ የትናንት በስቲያው ጉዳያችን ነው። በያንዳንዱ የታሪክ አንጓ ላይ የምንሰጠው የታሪክ ትርጉም እና አንድምታ አራምባ እና ቆቦ በመሆኑ ምክንያት እንደ አገር እና ዜጋ፤ እንደ “ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች”፤ እርስበርሳችን ያለን መተማመን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ማንኛውም ጤናማ አገር ጤናማነቱ “ስላለፈው ጉዳይ” ባለው “ጤናማ” ብሔራዊ መግባባት (National Consensus?) ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ጤናማ ብሔራዊ መግባባት ደንቃራ ከገጠመው  ያ አገር ምን ያህል የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረው፣ ምን ያህል የተማረ ዜጋ ቢኖረው፣ ምን ያህል ሰፊ አገር ቢኖረው፣ እንዲሁም ምን ያህል ጠንካራ መንግሥት ቢኖረው ከችግሩ እና ከችጋሩ ይላቀቃል ብዬ አልገምትም። ያም አገር እና የዕድገት አቅጣጫው አደጋ ላይ ይወድቃል ብዬ አስባለኹ።
በተፈጥሮ ሀብቷ እዚህ ግቢ የማትባለው ጃፓን የሥልጣኔ ጫፍ ደርሳ ሁሉ የሞላቸው ኮንጎዎች ለምን የዕለት እንጀራ ናፋቂዎች ሆኑ? የበሬ ግንባር የሚያክሉ የአውሮፓ አገሮች ለሰው ክብር የሚገባውን ኑሮ ሲኖሩ እና ለሰው ልጅ የሚገባውን ኑሮ ሲኖሩ ለምን አረቦቹ ነዳጅ ላይ ተቀምጠው ያክካሉ፣ አፍሪካውያንስ ከአልማዝና ዕንቁ እስከ ተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ይዘው ለምን ለስደት ሲወጡ የባሕር ራት ይሆናሉ?
ኢትዮጵያ እርስ በእርሷ የተለያየችው፣ አንዱን ከአንዱ የሚያናቁረው፣ እርስ በርሳችን የሚያናጨን “ላለፈ ጉዳይ” የምንሰጠው መልስ አይደለምን? ባለፉት 40 ዓመታት የተነሡት አብዮታውያን የኢትዮጵያ ልጆች ሊመልሱት የሞከሩትና አሁንም የሚሞክሩት “ያለፈ ጉዳያችን” አይደለምን? ላለፈው ጉዳያችን የሰጡትና በመስጠት ላይ የሚገኙት መልስ ከብሔር ፖለቲካ እስከ ሊበራሊዝም፣ ከ “ትገንጠል፣ አትገንጠል” እስከ “የራስን ዕድል በራስ እስከመወሰን”፣ የራስን ቋንቋ ከመጠቀም እስከ የላቲን ፊደል መጠቀም ጓዝ ይዞ አልመጣምን?
አቶ መለስ የሚመሩት አብዮት የሚታወቀው “ላለፈ ጉዳያችን” በሚሰጣቸው ደፋር መልሶች ነው። በዚህ በኩል ደግሞ ግንባር ቀደሙ ራሳቸው አቶ መለስ ናቸው። እርሳቸውና የእርሳቸው ትውልድ ለአገርኛው ታሪክ፣ ትምህርት እና ዕውቀት ያለው እና የነበረው ግንዛቤ እና ቅርበት ምን ያህል ጥልቀት እንደነበረው ሁል ጊዜም ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ነበር፣ ነውም። በዚህም ምክንያት “ላለፉ ጉዳዮቻችን” የሰጧቸውና የሚሰጧቸው መልሶች አሁን ላለንበት ጥሩም ሆነ መጥፎ ደረጃ አድርሰውናል። አሁን ያለንበትን ሁኔታ ገሚሶቻችን ኢትዮጵያውያን “መንግሥተ ሰማይ ነው” ስንለው፣ ሌሎቻችን ኢትዮጵያውያን ደግሞ “ዋነኛው ሲዖል ከዚህ በምን ይበልጣል” ብለን እንከራከራለን።
እነአቶ መለስ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ጉዳይ በራሳቸው ታሪካዊ ትንታኔ ፈቱት እንጂ “ያለፈ ጉዳይ” ብለው አልተዉትም። ግማሹ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊውን ፊደል ሳያውቅ እያደገ ያለውና መሠረቱን ላቲን ባደረገው በአውሮፓዊው ፊደል እየተጠቀመ ያለው ሳይንሳዊ በሆነ ጥናት ሳይሆን “ኢትዮጵያዊው ፊደል በግድ የተጫነብን ነው” በሚለው “ታሪክን ያጣቀሰ ላለፈ ጉዳይ” በተሰጠ መልስ አይደለምን? ሌላው ቢቀር ከኤርትራ ጋር ጦርነት ገጥመን 70 እና 80 ሺህ ወጣቶቻችንን የገበርነው “ድንበራችን እዚህ ነው፣ እዚያ ነው” እያልን ታሪክ እየጠቀስን አይደለምን?
ላለፉት ከ40 ላላነሡ ዓመታት አብዮተኛ ኢትዮጵያውን ሲያንከባልሉት የነበረው የኢትዮጵያን ታሪክ የመከለስ እና ድጋሚ የመጻፍ ጉዳይ አሁን ወደ ቤተ ሃይማኖቶች እና ወደ ምዕመኖቻቸው በመዝለቁ በዋነኞቹ ቤተ እምነቶች ማለትም በክርስትና እና በእስልምና መካከል ሁነኛ መጓተትን እና መቆራቆስን በመፍጠር እየተገለጠ አይደለምን? ችግሩ ከቤተ-ፖለቲካ እየወጣ ወደ ቤተ-እምነት እየዘለቀ እና መሠረቱን እያጸና ነው ማለትስ አይደለምን?
በአጠቃላይ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ የዘለለ፣ አገራችንን በትክክል የሚገልጽ፣ እኛነታችንን የሚረዳና የሚያስረዳ፣ “ያለፈ ጉዳያችንን” የሚተነትን መግባባት ያስፈልገናል። እንደ አገርም እንደ ሕዝብም ወደፊት መራመድ ያቃተን ያልቋጨነው የኋላ ጉዳይ፣ ያለፈ ጉዳይ ስላለን ነው። ከየት እንደመጣን ሳንግባባ ወደየት እንደምንሄድ በምን እንግባባለን። ኋላችንን አላወቅን፣ ወደፊታችንን በምን እንተልመዋለን? ግማሾቻችን አንድ ሕዝብ እና አንድ አገር ነን እያልን፣ ሌሎቻችን ምንም አንድ የሚያደርገን ነገር የለም እያልን፣ ገሚሶችም አንድ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ጠላቶች ነን እያልን እንዴት “ያለፈው ጉዳይ” አያስፈልገንም? በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ጉዳያችንን እና ዕዳችንን ማወራረድ፣ ወደፊታችንን መተለም ይኖርብናል። አለበለዚያ “አባቱን አያውቅ፣ልጅ ልጁን ይናፍቅ” ያስብለናል።

13 comments:

Gebre Z Cape said...

Thanks Ephrem, we really need national consensus. I wish I could see the time in my life to forgive and forget situation in Ethiopia (like the South African's).

GOD help us, allah help us.

Anonymous said...

thank you brother; please go ahead

Anonymous said...


thank u bro

Anonymous said...

it is a nice view Ephrem!

Anonymous said...

Pls PDF

Anonymous said...

PDF pls

Anonymous said...

kalehiwot yasemalin

Anonymous said...

thank u very much Ephrem ! this is the real analysis about our country story?
may God bless you

endixs mamo said...

እግዚያብሄር ያበርታህ;፡ የውስጤን ነው የነገርከን አሁንም እግዚያብሄር ይሰጥህ

Berhanu z usa said...

ውድ ኤፍሬም እሸቴ፤
በጣም ቆንጆና ጥንቃቄ የተሞላበት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ትምህርታዊ ስነ ጽሁፍ ነው። ጽሁፎች ህ ሁል ጊዜም ያስደስቱኛል፤ በጣምም ትምህታዊ ናቸው። እግዚአብሔር ይስጥልን።

Anonymous said...

Hi Ephrem
why don't you write your opinion based on your view. ሰው ያለውን ተንተርሰህ መጻፍ ለምን አስፈለገህ ?.....የራስህን ሃሳብ አደንቃለሁ የሄድክበት መንገድ ግን እኔ ብቻ አዋቂ ነኝ ለማለት ያስመስልብሃል.....

Anonymous said...

wow really am satisfied on this article .thank you.

Oskar Glauber said...


Thanks , I've recently been searching for information about this subject for a long time and yours is the best I have found out till now. However, what concerning the conclusion? Are you positive in regards to the supply? gmail sign in

Blog Archive