Friday, September 14, 2012

በመስከረም ትዝ ከሚሉኝ ነገሮች


እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ


(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ READ IN PDF)፦ እንዲህ እንደ አሁኑ ዓመታት አልፈው፣ አገር ቤቱም እንደ ጨረቃ ርቆ፣ ትዝታም የሕልም ያህል ቀጥኖ፣ ልቡና ዛሬን ሳይሆን ትናንትን፣ የዛሬን አዋቂነት ሳይሆን የትናንትን ልጅነት ሲናፍቅ … መስከረም እና አዲስ ዘመን በትዝታ መስኮት መምጣቱ አይቀርም። ያው አዲስ ዓመት። እንቁጣጣሽ። ሰማይ ምድሩ የሚለወጥበት። ገና ከቤታችን ወጣ ስንል ኳስ የምንጫወትባቸው ሜዳዎች፣ የትምህርት ቤታችን ግቢ፣ በሩቁ የሚታየን የተራራ ገመገም ሳይቀር ቢጫ ይለብሳል። በአደይ አበባ ይሸፈናል። የት/ቤታችን ሣር የእኛን ቁመት በልጦ፣ በውስጡ እየተሽሎከሎኩን ስንሮጥ፣ ስንወድቅ ስንነሳ፣ አዲስ ዓመትን ከአዲስ የትምህርት ዘመንም ከፍንደቃም ጋር እናያይዘዋለን።

የኔ ትውልድ፣ የልጅነታችን ወራት ያለፈው፣ መስከረም አንድንም መስከረም ሁለትንም እንደ “ርዕሰ ዐውደ ዓመት” እያከበርነው ነው። እንቁጣጣሽ ከዘመን መለወጫነቱ ይልቅ የመስከረም ሁለት ዋዜማ መሆኑ የታወቀ እስኪመስል ድረስ በልጅነት አዕምሯችን የተሳለው ዐቢዩ በዓል የቅ/ዮሐንስ ማግስት ነበር ማለት ይቻላል። የአብዮት ዘመን ልጅ መሆን ዕዳው ይኸው ነው።

በዚያን ዘመን፣ የ“ግብታዊው አብዮት” በዓል የሚከበርበት መስከረም ሁለት ከመጀመሩ ወራት አስቀድሞ ዝግጅቱ እንኳን ለአዋቂዎቹ ለእኛም ለልጆቹ ይተርፈን ነበር። ክረምቱ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ሕጻን ወጣቱ፣ በተለይም የከተማ ልጆች፣ “ሥራ የሚፈቱበት” ወቅት ስለሆነ ቀበሌዎቹ ወጣቱን በአ... (አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር)፣ ሕጻናቱን በሕጻናት፣ ሴቶቹን በአኢሴማ ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር)፣ ገበሬውን በገበሬዎች ማኅበር ጠምደው ዝግጅቱ ይጀመራል። ከሁሉም ዝግጅት ትዝ የሚለኝ “ሰልፍ እርገጥ” የሚባልበት ወታደራዊ ሥልጠና የመሰለ ዝግጅት ነው። ከዚህ የሚያመልጥ ማንም የለም። እናቶቻችን ራሳቸው በየዓመቱ ሰልፍ ሲማሩ፣ ከዚያም መሠረተ ትምህርት ሲማሩ፣ ትዝ ይለኛል። በመሠረተ ትምህርቱ ፊደል ለይተውበታል፣ የሰልፍ ሥልጠናው ግን አረማመዳቸውን የለወጠው አይመስለኝም።
ይኼ ሰልፍ-ሥልጠና እኛንም ሕጻናቱን አያልፈንም። ብዙ ጊዜ ከሰፈር ወጥተን ለመራገጡ ዕድል ስለሚሰጠን ብዙም አንጠላውም። ችግሩ የሚመጣው ሰልፍ ሥልጠናውን እንዳንቀር ከቡሄ ጭፈራ፣ ከእንጨት ሰበራ፣ ከኳስ ጨዋታ ሊከለክሉን ሲሞክሩ ነው። በተለይ አንድ ዓመት ላይ  ጅራፍ እያጮህን፣ ሆያ ሆዬ መጨፈራችንን እንድንተው የደብረ ታቦር ዋዜማ፣ ቡሄ በምንጨፍርበት ቀን፣ እስከ ማታ ድረስ ሕጻናቱን ቀበሌ አጉረው አስመሽተውናል። ዋናው የቡሄ ሰዓታችን ሲያልፍ ሁላችንንም ወደቤታችን ለቀቁን። መቸም ያዘንነው ዘን አይነገር። በተረፈችው ሰዓት ጓደኞቻችንን ሰፈር ለሰፈር ፈልገን የዓመት ጥማታችንን ለመወጣት ሞከርን።
ያን ጊዜ ቡሄ የምንጨፍረው ፀሐይ ከጠለቀችበት ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት፣ ከዚያም በበነጋው ጠዋት ተነስተን ደግሞ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ ነበር። ሲነጋ ማታ የተሸለምነውን ሙልሙል እና ሳንቲም ቁጭ ብለን እንከፋፈልና ዳቦ እያረጥን ስንገምጥ እንውላለን። ሳንቲሙ እስከዚህ ባይሆንም ከረሜላ ለመግዛት እና ሌላ ጊዜ ብዙም የማናገኘውን ለስላሳ ለመጠጣት ያስችለናል። ኋላ ኋላ ሰዉ ሙልሙል ከመስጠት ይልቅ የሳንቲም ድቃቂ መለገሱ ላይ እየበረታ ሲመጣ እኛም የምንገዛው ነገር ዓይነት ጨመር ማለት ጀምሮ ነበር። ቀበሌዎቹ ከዚህች ዓመታዊ ፌሽታን ሲያስተጓጉሉን ንዴታችን ወሰን ያጣል።
ከዚያ ግማሹን ሕጻን በኪነት፣ ግማሹን ሕጻን በሰልፍ ያሰማሩታል። ኪነት የሚገቡት ልክ እንደ ትልልቆቹ የአብዮት መዝሙሮችን አጥንተው በዕለቱ በአብዮት አደባባይ ጢም ብሎ ለሚሰበሰበው ሕዝብ እንዲዘምሩ ለማድረግ ነው። ሌሎቻችን ደግሞ እግረኛ ሰልፉን ሰልጥነን በተካነ ሁኔታ “በክቡር ትሪቡኑ” ፊት ለፊት እናልፋለን። ግማሾቻችን በባዶ እግራችን፣ ግማሾች በሸራችን፣ ግማሾች በበረባሷችን መሬቱን በትንሽ እግራችን እየደለቅን፣ እንደ ወታደርም እያደረገን።
መስከረም ሁለት ስልችት የሚለኝ የንግግሩ ብዛት ነበር። ወደ ቤት እንዳንሄድ የከተማችን አብዮት አደባባ በር ግጥም ተደርጎ ተዘግቶ መግባት እንጂ መውጣት የለ። ወደቤትስ ብንሄድ ማንን እናገኛለን? ቤተሰቡ በሙሉ እዚያው አደባባዩ ነው ያለው። እንጀራ ከሌማት ቆርሶ የሚሰጥ ሰው እንኳን ቤት ሳይቀር ሁሉም እንዲሄድ ግዴታ ነው። የቀረ ወዮለት። ደግሞ ልክ እንደ ቅዳሴ ሌሊት 11 ሰዓት (5ኤ.ኤም) የወጣን ቤታችን የምንመለሰው እኩለ ቀን ካለፈ በኋላ ነው። የልጅነት ሆዳችን በረሃብ ተጨራምቶ፣ በውሃ ጥም አፋችን ደርቆ። ቤት የሚቀሩት የታመሙ ወይም አረጋውያን ብቻ ናቸው
ፕሮግራሙ ሲጀመር መድረክ መሪዎቹ በሚያንባርቅ ድምጻቸው የዕለቱን መርሐ ግብር ይዘረዝራሉ። አብዛኛው መቼም ንግግር ነው። የወጣቶች ተወካይ (አኢወማ)፣ የአኢሴማ (አብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር ማለት ነውአዲሱ ትውልድ) ተወካይ፣ የአኢገማ (ገ=ገበሬዎች)፣ የአኢሰማ (ሰ=ሰራተኞች) ተወካይ፣ ከዚያ የዕለቱ ዋነኛ እንግዳ ንግግር ያደርጋሉ። ፍሬ ሐሳቡ አብዮታችን ከድል ወደ ድል መሸጋገሩን ማብሰር፣ ለወደፊቱም ከፊቱ የሚመጣውን ፈተና ሁሉ እየበጣጠሰ እንደሚያልፍ መተንበይ፣ የአብዮቱ ጠላቶች የሚባሉትን ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጀምሮ “መርገም” እና በመጨረሻም “ከቆራጡ፣ ከታላቁ፣ ከሊቁ፣ ከመጢቁ …. መሪያችን ጋር ወደፊት!!!! ማለት ነው (ይቺ ታላቁ መሪያችን የምትባል ነገር ዞራ መጣች ዘንድሮም)። ይኸው ንግግር ነው በተለያዩ ሰዎች አንደበት ተመልሶ ተመልሶ የሚነገረው። ንግግር የማያደርገው ምንም “አ.ኢ” የሌለን (“አኢሕማ = አብዮታዊት ኢትዮጵያ ሕጻናት ማኅበር” ያልተባልነው) የእኛ የሕጻናት ተወካይ ብቻ ነው።  
በንግግሮች እና በፕሮግራሞች መካከል መርሐ ግር አስተናባሪው “ጓዶች፣ አንድ ጊዜ አብራችሁኝ መፈክር እንድትሉ እጠይቃለኹ” ይልና ለደቂቃዎች ያህል የመፈክር ዓይነት ያዥጎደጉዳል። ከሁሉም ትዝ የሚለኝ “ከሁሉም በላይ አብዮቱ!!” የምትለው ናት (አንዱ የቤተ ክህነት ሰው ከሁሉም በላይ አብ-ሕይወቱ እያለ ለራሱ ይቀይረው ነበር አሉ)። ታዲያ እያንዳንዱ መፈክር ቢያንስ ሦስት ጊዜ ይባላል። አንዳንዱ ደግሞ መልሱ ለየት ያለ ነው። ለምሳሌ መፈክር አስባዩ (አስፈካሪው ልበለው?) “እናሸንፋለን” ሲል እኛ ተቀባዮቹ “አንጠራጠርም!!” ብለን መመለስ አለብን። አንዳንዱ ደግሞ የመፈክሩን የመጨረሻ ቃል መድገም ሊሆን ይችላል። “ኢምፔሪያሊዝም ይውደም” ሲል ሕዝቡ ደግሞ “ይውደም!!” ይላል ማለት ነው። መፈክሩ የድጋፍ ከሆነ ግራ እጅ ወደላይ ሲነሣ፣ የተቃውሞ እና የእርግማን ከሆነ ደግሞ ያንኑ ግራ እጅ ወደታች ማድረግ ይገባል።
አንድ ቀልድ ትዝ አለኝ። እኚህ በየቀልዱ ልክ እንደ አለቃ ገብረ ሐና ስማቸው የሚነሣው የጎጃሙ ጓድ ኮምጫምባው ግራ እጃቸውን ሳይሆን ቀኝ እጃቸውን ሲያነሡ ያየ ሰው ጠጋ ብሎ “ጓድ ኮምጫምባው ይውደም ሲባል በግራ እጅ እንጂ በቀኝ እጅ አይደለም” ቢላቸው “ዞር በል በደንብ የሚያደቀውን እጅ እኔ መቼ አጣኹት” አሉ ይባላል። ታዲያ እኛም የሚያደቀውን ሳይሆን የማያደቀውን እያነሣን “ይውደም፣ ይውደም” ስንል አንድ-አስራ አምስት ደቂቃ ይሞላል። እኛ ሕጻናቱ “ይውደም!!” የሚባሉትም፣ “ወደፊት!!!” የሚባሉትም ሳይገቡን ሌላው እጁን ሲያነሣ ስናነሳ፣ ሲያወርድ ስናወርድ እንቆያለን። አሁን አሁን ሳስበው ግን እኛ ልጆቹ ብቻ ሳንሆን ብዙውም ትልልቅ ሰው እንደ እኛው ሳይሆን አልቀረም። አቤት የመፈክሩ ብዛት። ያኔ እንሰማናቸውና እንሰማናቸው መፈክሮች ብዛት እርግማናችን አሜሪካንን ጠራርጎ ወይ አትላንቲክ ወይ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ሳይጨምራት መቅረቱ።
በሌላው ፕሮግራም የየቀበሌው ሰልፈኛ እና ኪነት ሲያጠና የከረመውን ዘፈን (አብዮታዊ መዝሙር) ያቀርባል። ሁለት ወር ላላነሰ ጊዜ አገር ሥራ ፈትቶ እንደ ሰሜን ኮሪያና ቻይና ወይንም ሶቪየት ሕብረት የደመቀ ሰልፍ ለማሳየት መከራውን ሲበላ የከረመበትን ዝግጅት አሳይቶ ወደየቦታው ይመለሳል።  
በዚያን ዘመኑ የኪነት ሙዚቃ መድረክ ላይ ወጥተው እስካሁንም እንጀራቸው ሆኖ የዘለቀ አርቲስቶች አሉ። ስለ ዕድገት በሕብረት፣ ስለ መሠረተ ትምህርት፣ ስለ ዳር ድንበር፣ ስለ አገር አንድነት፣ ስለ ዕድገት … መቸም ያልተገጠመ ግጥም፣ ያልተሞከረ ድምጽ፣ ያልተፈተሸ ትከሻ የለም - ያኔ። ያን ጊዜ የተጀመረ ሰልፍ እስካሁን ይኸው አለ። ሰበብ ፈልጎ መሰለፍ ነው። ቀበሌ ሥራው ሰው ማሰለፍ ሳይመስለው አይቀርም።
በመስከረም ሁለቱ ክብረ በዓል ቀን ታዲያ ሰዓቱ እየገፋ ሲመጣ ሰዉም መዳከም፣ ሕጻናቱም መራብ፣ በዚያ ሽንት ቤት እንኳን በሌለበት ሁኔታ የውስጥም የውጪም ጥሪ ሲመጣ ሕዝቡ መቁነጥነጥ ይጀምራል። መቼ በሩ ተከፍቶለት እንደሚወጣ ይናፍቃል። ችግሩ በሩ ላይ የሚቆሙት አብዮት ጠባቂዎች “አይቻልም” እንጂ ሌላ ቃል የሚያውቁ አይመስሉም። ሰው ቢታመምም፣ ባይታመምም፣ ሕጻንም ቢሆን አረጋዊም ቢሆን ለሁሉም መልሳቸው “አይቻልም፣ ተመለስ” ብቻ ነው። ክፋቱ እኩለ ቀን ካለፈ ዝናብ አይጠፋውም። “ክቡር ትሪን” ላይ ለሚቀመጡት ሳይሆን በእግሩ ሰዓታት ተጉዞ ለሚመጣውና ለሚሄደው ጭንቅ ነው። ከገጠር የሚመጣው ሰልፈኛ ወንዝ ይሞላበታል፣ ይጨልምበታል፣ የክረምት ጉዞ አስቸጋሪ ነው። ደግሞ የክረምት ጭቃ።
በዚያ ወጥቶልኝ ነው መሰለኝ “ሰልፍ” የሚባል በቴሌቪዥን ሳይ፣ መፈክር የተሸከሙ ሰዎች “እንትንን ደግፈው፣ እንትንን አውግዘው” ሲባል ትዝ የሚለኝ የያኔው መስከረም ሁለት ነው። “ደግፈውታል” የተባለው ነገር እኔ ራሴም የምደግፈው ነገር ቢሆንም እንኳን ያ ሁሉ ሰው ደግፎት ወጣ ለማለት ይቸግረኛል። በሆነ ነገር ሳያስፈራሩት መቼም ሁሉም ሰው “እንደ አንድ ልብ መካሪ” ሆኖ ሰልፈኛ የሚሆንበት ነገር አይገባኝም። ወይም ለእኛ አገር ብቻ የተሰጠ ልዩ የቀበሌ ሥጦታ እንደሆነ እንጃ።
ሬዲዮኑ የሚያንቆረውረው “እንቁጣጣሽሽሽሽሽ…” የሚለው በተስረቅራቂ ድምጽ የሚንኮለኮል ሙዚቃ ገና መሰማት ከሚጀምርበት የነሐሴ የመጨረሻ ቀናት ጀምሮ ድባቡ ይለወጣል። መስከረም ….. ልዩ ወር። መስከረም ሲመጣ፣ ከሌላው ነገር ጋር ሁሉ ይኼ ትዝ ይለኛል። አየሩ ራሱም ትዝ ይለኛል። ለስለስ ያለ፣ ቀለል ያለ ንፋስ። ፀሐይዋ ሯሷ የተሳለች እንጂ ተፈጥሮ የማትመስልበት። በተስፋ የተሞላ አዲስ ሕይወት። ደግሞም እርሱም ሊያረጅ። አሮጌ ዓመት ሊባል።

14 comments:

Anonymous said...

Interesting Article!!!!!

ድርሻዬ said...

ኤፍሬም ትዝታን በትዝታ ዓይን ማለት ይህ ነው። ሆዴን ባር ባር አስባልክብኝ። ለማንኛውም ጥልቅ የትዝታ ቅኝታ ነው።

Anonymous said...

A very interesting article
10Q

ZeKrstos Ts. said...

Efrem I'm from that place & I remind a little

Anonymous said...

እስኪ ይህን ስላስነበብከን እግዚአብሔርን በማመስገን ልጀምር።

እፍሬም በዛ በ”አብዮት” ዘመን ጎዳናዎች እኮ አንሸራሸርከን። በእውነት የእብደት ዘመን ነበር። እብደቱ እየጨመረ መጣ እንጂ አልቀነሰም። “አብዮቱ” ሲፈነዳ የመጀመርያ ደረጃ ትምሀርት ቤት ጨርሸ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበርኩ። ከአብዮቱ በፊት ምን እንመስል እንደነበር ትዝ ይለኛል። እኔ ደግሞ እስኪ ትንሽ በነዛ ጎዳናዎች ላንሸራሽርህ።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ (ሙስሊምም ቢሆን) መጀመሪያ ትምህርት የሚጀምረው በቄስ ትምህርት ቤት ነበር። አንድ ኢትዮጵያዊ መጀመሪያ የትምህርት አፉን የሚከፍተው “አባታችን ሆይ በስማይ የምትኖር” በሚለው ጸሎት በመሆኑ የአራትና የአምስት አመት ልጆች ተሰብስበን በአንድ ላይ በስድ ንባብ ሳይሆን በቤተክርስቲያን ዜማ “አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር። ስምህ ይቀደስ ….” እያልን እንጸልያለን። ከዛ ሀ ሁ መቁጠር እንጀምራለን። ይህን የምንማረው “ሀ” ግዕዝ፣ “ሁ” ካሊብ፣ “ሂ” ሳልስ” ፣ “ሃ” ራብዕ ወዘተ .. እያልን ነበር። ከዛ አቡጊዳ፣ መልእክተ ዮኃንስ፣ ወንጌል፣ ዳዊት እያለ ይቀጥላል።

ከቄስ ትምህርት ቤት በኋላ ዘመን አመጣሹ ትምህርት ቤት ወይም አስኳላ ትምህርት ቤት (école, school) እንገባለን። አስኳላ ትምህርት ቤት ጧት በሰልፍ ይጀመራል። አስኳላ ትምህርት ቤት እንደመጣ የአባታችን ሆይ ጸሎት ወዲያውኑ አልቀረም። እስከኛ ጊዜ ድረስ ጧት በሰልፍ ላይ እንዳለን አባታችን ሆይ እንል ነበር። ከዛ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር እየተዘመረ ሰንደቅ አላማ ይሰቀላል። የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙርም ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ የሚለው ነበር።

ትምህርት ቤት ውስጥ ቁጥር ወይም ሂሳብ፣ ሃይጂን፣ ግብረገብነት እና አጻጻፍ እንማራለን። እስፖርት (ኳስ ጨዋታ እና ሩጫም አለ)። ከትምህርት በኋላ አብዛኛውን ጊዜ የምናሳልፈው ሩጫ፣ ድብብቆሽ፣ ኳስ፣ ብይ፣ ቆርኪ፣ በመጫወት ነበር;። ከበዓላት ውስጥ ትልልቆቹ ገና፣ ጥምቀት፣ መስቀል፣ ቅዱስ ዮኃንስ አንዳንዶቹ ናቸው። እንቁጣጣሽ፣ ቡሄ፣ ሆያ ሆየ፣ እና ሌሎችም ባህላዊ ጨዋታወች ነበሩ። ባህላዊ ይባሉ እንጂ ሁሉም ከክርስትና ጋር የተያያዙ ነበሩ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ግብር እና በየቦታው ይመሰገን ነበር። ህጻን ልጅ እግዚአብሔርን በማመስገን አንደበቱን ይክፍታል። እያንዳንዱ ሰው በጧት ተነስቶ ቸር አውለኝ በማለት ቀኑን ከእግዚአብሔር እጅ ይጠይቃል። አንድ ሰው ለመንገድም ሲነሳ ቸር መንገድ አድርግልኝ ብሎ መንገዱን ከእግዚአብሔር እጅ ይጠይቃል። በመንገድም ሰው ሲያጋጥመው ካጋጠመው ሰው ጋር እንደምን ዋልክ እንደምን ዋልሽ ይባባልና ሁሉም እግዚአብሔር ይመስገን ብለው ይመልሳሉ። በሰላምታ እግዚአብሔርን ማመስገን የኢትዮጵያዊ ባህል ነበር። አንድ ሰው እርዳታ ሲያደርግ ወይም ስጦታ ሲሰጥ እግዚአብሒር ይስጥልኝ እንል ነበር (አመሰግናለሁ ብሎ እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰጪውን ሰው ማመስገን የመጣው ከአብዮቱ ወዲህ ነው)። እግዚአብሔር ከእርሻ ሥራ በፊት እና በኋላ ይመሰገናል፣ እህል ሲዘራ በመስቀልኛ አዘራር ይመሰገናል፣ ሲታጨድ ይመሰገናል፣ ሲወቃ ይመሰገናል፣ ከጎተራ ሲገባ ይመሰገናል። እያንዳንዱን ቀን በቅዱሳን ስም መሰየም የኢትዮጵያ ባህል ነበር። ቅዱሳን የሚመሰገኑት ስለ እግዚአብሔር ነበር። ንጉሥም የሚከበረው ስለ እግዚአብሔር ነበር። ደሃም የሚረዳው ስለ እግዚአብሄር ነበር። ባጭሩ ኢትዮጵያ ራሷ እንደ አንድ ቤተክርስቲያን ነበረች። ቀስ በቀስ ግን የአስኳላ ትምህርት መጀመሪያ አቅራቢያዋን፣ ከዛ ቅጥር ግቢዋን፣ ከዛ ምእመናኗን፣ ከዛም ካህናቶቿን፣ ከዛም መቅደሷን እየለወጠውና እያረከሰው መጣና አንተ የተረክህልን ዘመን ተከተለ። እነሆ በዚህም እጅ እጅ በሚል የ”አብዮት” ዘመን አርባ አመት ተጓዝን። አሁን ጥያቄው ኢትዮጵያ ወደ ነበርችበት ወርቃማ ዘመን እንድትመለስ ምን እናድርግ ነው?

Anonymous said...

አሽሙርህ ትመቼኛለች፡፡ ለምን ልብ ወለድ አትጽፍም?

Anonymous said...

Thanks Ephrem. You took us back to those old memories.

Anonymous said...

Lij Ephrem;
beyegizew yemitsfiachewn tsihufoc anebalehu:: igzer yistilign ilalehu::
ye kanadaw wedajih

Anonymous said...

I think it is better go forward. No way to go back ward. That past days are the foolish century.

endixs mamo said...

I realy like it tnx. E/R yabertah

endalekachew Senkea said...

I realy love it. tnxs E/R yabertah

endalekachew Senkea said...

i love it tnxs

Tsiyon Eshetu said...

ወደ ኋላ ዞር ብዬ እንድመለከትና ብዙ ነገሮችን እንዳስታውስ ያደረገኝ ርዕስ ነው፡፡ እኔንም በልጅነቴ ከመስከረም ሁለት የተራረፉ የግንቦት 20 ሰልፎች ደርሰውኛል፡፡ በትምህርት ቤት ከነ ዩኒፎርማችን መፈክር እያስተጋባን በየአውራ ጎዳናው ስንሰለፍ፡፡
የእንቁጣጣሹ ነገር ይምጣብኝ፡፡ እስከዛሬ ድረስ የሚያስቀኝ ሌሊቱ አልነጋልሽ ብሎኝ ተነስቼ የተገዛልኝን አዲስ ልብስ ለብሼ ተመልሼ የተኛሁት፡፡
መልካም ርዕስ መርጠሐል ውዱ ወንድማችን፡፡


Tsiyon Eshetu said...

ወደ ኋላ ዞር ብዬ እንድመለከትና ብዙ ነገሮችን እንዳስታውስ ያደረገኝ ርዕስ ነው፡፡ እኔንም በልጅነቴ ከመስከረም ሁለት የተራረፉ የግንቦት 20 ሰልፎች ደርሰውኛል፡፡ በትምህርት ቤት ከነ ዩኒፎርማችን መፈክር እያስተጋባን በየአውራ ጎዳናው ስንሰለፍ፡፡
የእንቁጣጣሹ ነገር ይምጣብኝ፡፡ እስከዛሬ ድረስ የሚያስቀኝ ሌሊቱ አልነጋልሽ ብሎኝ ተነስቼ የተገዛልኝን አዲስ ልብስ ለብሼ ተመልሼ የተኛሁት፡፡
መልካም ርዕስ መርጠሐል ውዱ ወንድማችን፡፡