Wednesday, May 7, 2014

ጉዱ ካሳ እና “ሰበነክ-ሊቃውንት”(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ እንግሊዛዊ ሆኖ “ሼኪስፒርን የማያውቅ፣ ሥራዎቹንም ያላነበበ፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሀዲስ ዓለማየሁን የማያውቅ ‘ፍቅር እስከ መቃብርን’ም ያላነበበ” ቢኖር እጅግ የሚደንቅ ይሆናል። እንዲያውም ጥያቄው ‘ስንት ጊዜ አነበብከው?’ እንጂ ‘አንብበኸዋል እንዴ?’ አይሆንም የሚል ግምት ነበረኝ። ከዕለታት በአንዱ ቀን በድሮ የትምህርት ቤት መጽሐፎቻችን ውስጥ ስላሉ ታሪካዊ ጽሑፎች ስናወጋ በመካከሉ አብዲሳ አጋን አስታወስን። “ስንተኛ ክፍል መጽሐፍ ውስጥ ነበር ጃል?” እያልን ስንጠያየቅ አጠገባችን የነበረ አዕምሮው ብሩህ የሆነ ልጅ እግር የዩኒቨርሲቲ መምህር “ማነው አብዲሳ አጋ?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። በመጀመሪያ እንደ ቀልድም ወሰድነው። ቀጥሎ እንደ መገረምም አደረገን። ከዚያ በኋላ ግን በርግጥ ሐሳብ ውስጥ ከተተን። “እንዴት ነው ነገሩ?” አሰኘን። በዚያ ሁሉ ብሩህ አዕምሮው ውስጥ አብዲሳ አጋን ሳያውቅ ያለፈበት አጋጣሚ ወይ ከእርሱ ስንፍና ነው ወይንስ ከመማሪያ መጽሐፉ ውስጥ አልነበረም? እየተባባልን መልካም ወግ ፈጠርን።

ለጥያቄያችን መልስ ሳናገኝ ስለ አብዲሳ አጋ፣ ስለ ዘርዓይ ደረስ፣ ስለ አሉላ አባ ነጋ ገና በልጅነታችን በጀግንነት እንድናውቃቸው በለጋ ልቡናችን ላይ የተቀረፁትን ኢትዮጵያውያን እያስታወስን ብዙ ተጨዋወትን። ያንን ወጣት መምህር “ይህንን አለማወቅህ ያሳዝናል” በሚል ራስን የመካብና “እኛ ነን አዋቂዎቹ” በሚል መንፈስ ሳንጠርበው ያለፍን አይመስለኝም።  ከስንቱ የዕውቀት ጎተራ አንድ “አብዲሳ”ን አለማወቁ “ማይም” እንደማያሰኘው ብናውቅም “እኮ እንዴት ያንን ጀግና ላታውቅ ቻልክ” ሳንለው ግን አልቀረንም። ይኸው መነሻ ሆኖኝ “ፍቅር እስከ መቃብር”ንም ሆነ ሀዲስ ዓለማየሁን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ቢኖር እንዳይደንቀኝ ተዘጋጅቻለኹ።

“ፍቅር እስከ መቃብር” መጀመሪያ ከታተመበት ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ ከሰባት ጊዜያት ላላነሰ ለመታተም የበቃ፣ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ጥናት ውስጥ ምሁራኑ እጅግ ከፍ ባለ ዓምደ ወርቅ ላይ የሚያስቀምጡት ታላቅ ሥራ ነው። አብዛኛው ዜጋዋ ማንበብና መጻፍ በማይችለው በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በኢትዮጵያ ራዲዮ የእሑድ ምሽት “ከመጻሕፍት ዓለም” ተደጋግሞ በመተረኩ ትልቅ ዕውቅናን በሚያነበውም በማያነበውም ዘንድ ያተረፈ፣ ፈረንጆቹ “የቤት ውስጥ ቃል”፣ ‘household name’ እንደሚሉት ለመሆን የበቃ መጽሐፍ ነው። ደራሲው ሀዲስ፣ “ተራኪ ወጋየሁ ንጋቱ” ነዋ። ሀዲስ ዓለማየሁ በአንድ ወቅት  “እኔ መጽሐፉን ጻፍኩ፣ ወጋየሁ ደግሞ ሕይወትና ሙቀት ያለው ነፍስ” ሰጠው እንዳሉት (ጥቅሱ ከማስታውሰው ነው፤ ቃል በቃል አይደለም)።

መጽሐፉን ከማንበቤ በፊት ትረካውን ነው የሰማኹት። ከእሑድ እስከ እሑድ በጉጉት ተጠብቆ። እኔ ብቻም ሳልሆን መላው ቤተሰብ። ማንበብ የሚችለውም፤ የማይችለውም። ማታ ማታ መሠረተ ትምህርት ለመማር የሚሔደውም፣ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የገባው የቤተሰባችን አባል በጉጉት የሚያዳምጠው ዝግጅት ነበር። ዳንቴል የምትለብሰው ሬዲዮ ዙሪያ ከብበን። ሬዲዮ በዳንቴል አሸብርቃ።

ከዜናው ቀጥሎ ተስረቅራቂው ዋሺንት መንቆርቆር ሲጀምር እና ዋና አዘጋጁ ርዕሱን፣ ደራሲውን፣ ያለፈውን ሳምንት ሊያስተዋውቅ ሲጀምር ቤቱ የጸጥታ ድባብ ይነግስበታል። ምንም እንኳን መጽሐፉ ከተጻፈ ብዙ ዓመታት ያለፉት ቢሆንም ከቤተሰባችን ቀድሞ ያነበበው አልነበረም። “ሳይማር ካስተማረ” ቤተሰብ ለምንመጣ ኢትዮጵያውያን እኛ የየቤተሰቦቻችን የመጀመሪያ የትምህርት ዓለም አስኳላ ቀማሾች መሆናችንም አይደል?

በዚያ የወጋየሁ ንጋቱ መግነጢሳዊ ድምጽ ያዳመጥነው መጽሐፍ ምራቅ ውጠን፣ በሰከነ ልቡና ስናነበው ደግሞ ልዩ ጣዕም ይዞ ይመጣል። በቅርቡ አንድ ወዳጄ ያመጣልኝን የድምጽ ቅጂ ስችልና እና ከረዥም ጊዜ በኋላ ያንን ትረካ ድጋሚ ለማዳመጥ ዕድል  ሳገኝ ይኼንን ጽሑፍ ለመጻፍ ግድ አለኝ። በተለይም የካሳ ዳምጤን (የጉዱ ካሳን)፣ የአባ ሞገሴን፣ የባሪያይቱን የሀብትሽ ይመርን ታሪክ የሚያትተውን ክፍል ሳዳምጥ አሁንም ዘመኔን እንድቃኝ ያደርገኛል። በተለይም መገስጹ ጉዱ ካሳ።

‘ጉዱ ካሳ’ የፍቅር እስከ መቃብር ልቦለድ ምሶሶ ነው። ያውም ትንታግ መገስጽ። በደማቸውና በዘራቸው የሚንቀባረሩትን ፊታውራሪ መሸሻንና መሰሎቻቸውን፣ የእርሳቸውን ፊት ዓይተው የሚያድሩትን አባ ሞገሴን እና በጠቅላላው ሥርዓቱን የሚተችበት ቋንቋ በየዘመኑ ሕያውና ዘመነኛ ያደርገዋል። “የማኅበራችን አቁዋም የተሠራበት ሥራት፣ ልማዱ፣ ወጉ፣ እንደ ሕይወታዊ ሥራት ማኅበር ሳይሆን ሕይወት እንደ ሌለው የድንጋይ ካብ  አንዱ ባንዱ ላይ ተደራርቦ የታችኛው የላይኛውን ተሸክሞ እንዲኖር ሆኖ የተሠራ በመሆኑ ከጊዜ ብዛት የታችኛው ማፈንገጡ ስለማይቀርና ይህ ሲሆን ሕንጻው በሙሉ እንዳይፈርስ እንደገና ተሻሽሎ፣ ሰውን ከድንጋይ በተሻለ መልክ የሚያሳይ የሕያዋን አቁዋመ ማኅበር እንዲሠራ ያስፈልጋል” ይላሉ የሀዲስ ዓለማየሁ ገጸ ባሕርይ ጉዱ ካሳ።

ጉዱ ካሳዎች የኅብረተሰባቸው ጉድፍ ነቃሾች፣ ዓይናፋርነትን የገደፉ የክፉ ነገር ጸሮች ናቸውና በእጅጉ ይናፈቃሉ። በሚኖሩበት ዘመን ግን ይጠላሉ። በተለይም ያረጁና የገረጀፉ፣ ውስጣቸው የነቀዘ ሥርዓቶች አንደኛውኑ ተገንድሰው ራሳቸውም ጠፍተው ሌላውንም እንዳያጠፉ ጉዱ-ካሳዎች መድኅን ናቸው።

“ጉዱ ካሳዎች” እንዲህ በቀላሉ እንዲኖሩ አይቻላቸውም። የራሳቸውን ነጻነት ለማግኘት “ጉድ” መባል እና ያንን “ጉድነታቸውን” ወይም በቀላል አባባል “ዕብድ” መሰኘታቸውን የተቀበሉ መሆን አለባቸው። ሰካራምና ዕብድ የልቡን ይናገራል እንደሚባለው ማኅበረሰባችን እንዲህ ግልጥ በግልጥ የሚናገሩ ሰዎችን መጀመሪያ ይፈራቸዋል፣ ቀጥሎ ከጀርባቸው አንድ ነገር ቢኖራቸው ነው ብሎ ይጠረጥራቸዋል፣ ሁሉንም ሲያጣ ደግሞ “ዕብዶች ቢሆኑ ነው” ብሎ የዕብድነትን ማዕረግ ያስታቅፋቸዋል።

ይህ በብዙዎች ዕብዶች መካከል ጤነኝነቱን ፈልጎ ያገኘው “ጉድ” (በሀዲስ ዓለማየሁ ፈጠራ “ጉዱ ካሳ”) የመጽሐፍ ቅዱሱን ሎጥን ያስታውሰኛል። ድፍን አገር በእግዚአብሔር ላይ አምጾ ኃጢአቱን እንደ ጽድቅ ሲቆጥር ብቻውን ጻድቅ ሆኖ (ከእነርሱ በመለየቱ ዕብድ መስሎ፣ እንደ ዕብድ ተቆጥሮ) የኖረው ሎጥ በዓለማዊ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ቢገለጽ “የዘመኑ ጉዱ ካሳ ነበር” ማለት ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም ስለ እርሱ ሲናገር (2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፥7-8) ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበር” ይላል። በወቅቱ እንደ ዕብድ ቢቆጠር እና “ጻድቅ ነፍሱን ቢያስጨንቅም” የኋላ ኋላ ግን ጻድቅነቱ ማለት እውነተኛነቱ ተመስክሮለታል። ጉዱ ካሳዎችም እንዲሁ።

ሎጥ ጻድቅ ነፍሱን እንዳስጨነቀ እነዚህ የየዘመናቸው ሎጦችም ነፍሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሥጋቸውንም በብዙ መከራ ለማስጨነቅ ይገደዳሉ። ከኤርትራ የበረሃ እስር ማሰቃያ ወኅኒዎች እስከ አዲስ አበባ ማዕከላዊ እሥር ቤቶች ብዙ ሎጦች እና ጉዱ ካሳዎች መከራቸውን አይተዋል። ከቻይና መንግሥታዊ ነፍሰ ገዳዮች ጀምሮ የሜክሲኮ አደንዛዥ ዕጽ አመላላሽ ነጋዴዎች እስከሚያሰማሯቸው ሽፍቶች ድረስ ብዙ እውነተኛ ሰዎች ሕይወታቸው ተቀጥፏል። ነገር ግን ታሪክ ዘወትር ይዘክራቸዋል። በጠራራ ፀሐይ ኩራዝ አብርተው ሰው ሲፈልጉ መቆየታቸው ውሎ አድሮ ትርጉም ያገኝላቸዋል።

የጉዱ ካሳን ያህል የሚደንቁኝ ደግሞ የየዘመኑ “አባ ሞገሴዎች” ናቸው። የሰው ፊት ዓይተው የሚያድሩ፣ የገዢዎቻቸውን ሐሳብ ለማጽደቅ፣ ሰማያዊ ትርጉም ለመስጠት፣ አቦ አቦ ለማለት ብቻ የሚተጉ እምነት ለበስ አጎንባሾች። የክፉ ነገር አጽዳቂዎች። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በየቤተ እምነቱ ነበሩ፤ አሁንም አሉ። በየቤተ እምነቱ ብቻ ሳሆን በየትምህርት ተቋማቱ አሉ፤ በሊቅነት፣ በፕሮፌሰርነት፣ በዶክተርነት፣ በታዋቂ ጋዜጠኝነት፣ ደራሲነት፣ ዘፋኝነት፣ በአገር ሽማግሌነት፣ በአዋቂነት ወንበር የተቀመጡ የየሥርዓታቸው አፎች፣ አንደበቶች፣ ምላሶች። George Ayittey/ ጆርጅ አዪቴይ “ሰበነክ ምሑራንIntellectual Prostitutes ያላቸው “ንጉሥ ፈጣሪዎች”። ከሚያነግሷቸው ባልተናነሰ የክፋታቸው አጋሮች።

እንደዚህ ዓይነት አዋቂ ሰዎች ባላቸው ችሎታ በአገር ላይ ትልቅ የአድርባይነት አዚም በማስፈን ትውልድ ሊገድሉ ይችላሉ። ሰበነክ-ደራሲዎቹ የሚደርሱትን፣ ሰበነክ-ዘፋኞቹ እያንጎራጎሩ፣ ሰበነክ-ምሑራኑ ማጣቀሻ ታሪካዊ ዳራ እየቆፈሩ፣ ሰበነክ-የእምነት መሪዎቹ መለኮታዊ ገጽ እየሳሉ ተርታውን ሕዝብ በተለይም ሕጻናቱን፣ ወጣቶቹን እና ሕጻናተ አዕምሮዎቹን በጸጥታ እና በዝምታ እንዲኖሩ በማድረግ ለጌቶቻቸው ወታደር እንኳን ሊፈጽመው የማይቻለውን “ጸጥ ረጭ” የማድረግ ተጋድሎ ይፈጽማሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ “ሰበነክ-ሊቃውንት” በየዘመኑ ነበሩ። ነገር ግን ለዕውቀታቸው የማይገባ ኅሊና-ቢስ ተግባራትን ፈጽመው አልፈዋልና በየሙያቸው ባላቸው ዕውቀት እና ችሎታ አንቱ የተባሉ ቢሆኑም በሕዝባቸው ላይ ያውም ዘመን ከሚያመጣቸው ዲክቴተሮች ጋር በማበር የሚፈጽሙት ወንጀል በሌላው ሙያዊ አገልግሎታቸው በጎነት የሚካካስ ሳይሆን ይቀራል።

ወደ መነሻዬ ተመልሼ ለማጠቃለል ልሞክር። ስለ አብዲሳ አጋ አላውቅም ያለውን ወጣት መምህር “የታሪክ ዕውቀት እጥረት” የሚባል በሽታ እንዳለበት በወዳጃዊ ተግሳጽ ሸንቁጠነው፣ ስለዚህ ጀግና ለማንበብ ቃል ገብቶ ተለያየን። ምናልባት አንድ ቀን “የታሪክ ዕውቀት እጥረት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና ውጤቱም እንዴት እንደሚከፋ ይጽፍልን ይሆናል። ለአገር ብዙ ተግባር የሠሩ ሰዎችን ማወቁ ቢያንስ ቢያንስ “ሰበነክ-ምሑር” ከመሆን ያድነዋል።

ይሰውረን!!!

    
© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::

21 comments:

ድርሻዬ said...

በብዙ ዕብዶች መካከል ጤነኝነቱን ፈልጎ ያገኘ። እውነት ብለሃል። ይህን ጽሁፍ ሳነብ ግዜ መጽሃፉን ካስቀመትኩበት ፍለጋ ገባሁ። ቆንጆ ጥፍት ያለች ጥሁፍ ነች።

Anonymous said...

እንደ ሁል ጊዜው መልካም እይታ ነው ዲ/ን ኤፍሬም! በዘመናችንም እንደ ጉዱ ካሣ በጥብዓትም ባይሆን በፍርሃት በምትንቀጠቀት ብዕር ጫፍ ጥቂት ለመተንፈስ የምትሞክሩትን ምሁራን ባለማጣታችን ዕድለኞች ነን። በዚህ ረገድ የምሥጋናው እፍታ የሚገባው በሃገር ቤት እየኖሩ የሚያምኑትን በድፍረት የሚናገሩትና የሚጽፉ ጋዜጠኞችና ምሁራን ናቸው። እናንተ ዕብዶቹ እውነትን ከመናገር/ከመመስከር አትቦዝኑ፤ እኛም በፍርሃትና በጥንቃቄ እየኖርን ጤናማነታችን እናስመሰክራለን። የዕብዶቹ እንጂ የጤናማዎቹ ታሪክ ማንንም ሰለማይጥቅም ታሪካችሁ ከመቃብር በላይም ቢሆን መጻፉ አይቀርም።

Anonymous said...

Let say I had no radio and I did not speak amharic either in your happy times. Ready your self not to be excited, many of Ethiopians are like me and do not know who"gudu kassa" is. We are much many and diversified. Ethiopia is too different from What you have always tried to tell us in your bunch of manipulated stories. So what's the big deal dude? Are you going to erase our citizenship? Deacon, please be in your mind and do not judge. Rather, our church needs your help we have many issues to be raised and stay away from politics.

Anonymous said...

You know what I wonder, all all of us passed through the same line. I believe by the time of the narration, all the family used to be quiet. It could have all over the country. Lol . I love it. U know we never had the chance to get books to reed. If one book is around then the line itself takes longer than the time we need to finish the book. I wonder we had the interest. And there was no resource. So this program was one of our favorite program that helps us listen the books that we couldn't find and get some enjoyment to our life. I also can say that it brings the family together and brings common issue to discuss. It is one of my biggest nice childhood memory. Thanks for bringing the issue to the table Ababaye.

Hiwot

Anonymous said...

ዲ.ን ኤፍሬም ፍቅር እስከመቃብርን አለማንበብ ለምን ሊደንቅ እንደሚችል አልገባኝም:: አንተ ብቻ አይደለህም ከዚህ በፊት አንድ ጓደኛዬ ይህን ልብ ወለድ አለማንበቤን ስነግረው በጣም እጅግ በጣም ገርሞታል:: አብዲሳ አጋን በሚገባ አውቀዋለሁ:: ፍቅር እስከመቃብርን ግን አላነበብኩትም:: ካልተሳሳትኩ በሬድዮ እሁድ ማታ 3 ሰአት አካባቢ ይተረክ እንደነበር አስታውሳለሁ (በናንተ ጊዜ ሳይሆን እኛ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እያለን መሰለኝ በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ):: በርግጥ በጥራዝ ነጠቅ ከሬድዮ ትረካው አድምጫለሁ:: እነ ጉዱ ካሳን: ሰብለወንጌልን ወዘት የሚባሉ ሰዎች እንዳሉበት በጥራዝ ነጠቅ ሰምቻለሁ:: ስራዬ ብዬ ግን አልተከታተልኩም አልጨረስኩትምም:: ፍቅር እስከመቃብርን አለማንበብ ይህን ያክል ሊደንቅ የሚችልበት ጉዳይ ግን አሁንም አልገባኝም:: በርግጥ አማርኛ መምህራኖቻችን ከዚያ እንደሚጠቅሱና የተወሰነ ምእራፉን አንብበን እንድንመጣም የቤት ስራ ይሰጡን እንደነበርም አስታውሳለሁ:: የተባልኩትን ምእራፍ ወይም ገጽ ብቻም አንብቤ እመጣ ነበር:: አንተም ጓደኛዬም ግን በአንድ አይነት አገላለጽ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ፍቅር እስከመቃብርን አንብቦታል ወይም ከሬድዮ አድምጦታል የሚል ድምዳሜ ደረሳቹ:: የበለጠ የሚገርምህም ከሆነ እንግዲህ ከ1ኛ ክፍል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) በሀገራችን የትምህርት ስርአት አስኬጃለሁ ከወራት በኋላ ሶስተኛ ዲግሪዬን (PhD)በኢትዮጵያ ስርአትም እንኳን ባይሆን በአውሮፓውያኑ የትምህርት ስርአት እጨርሳለሁ ፍቅር እስከመቃብርን ግን እስከዛሬ ድረስ አላነብብኩም:: ፍቅር እስከመቃብርን ባለማንበቤ አንድም ቀን የጎደለብኝ ነገር እንዳለ ተሰምቶኝ አያውቅም ስራዎቼም ላይ እንቅፋት ፈጥሮብኝ አያውቅም:: አሁን ግን ያንተና የጓደኛዬ መገረማችሁ ምናልባትም ልብወለዱን ያነበቡት ሁሉ የሚገረሙ ስለሆነ ፍቅር እስከመቃብር ምን እንዳለው ለማንበብ ተገደድኩ ስለሆነም አሁኑኑ ፈልጌ ልጀምረው አሰብኩ:: ግን በአለም ላይ ካለው የተለየ ነገር የማገኝበት አይመስለኝም ግን እስኪ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማንበብ አለበት ስለተባልን እንጀምረው:: ምንም የተለየ ነገር ከሌለው ግን ኢትዮጵያዊ ሆኖ ይህን ልብወለድ ባለማንበቡ እንድተገረማችሁ ሁሉ ያላነበቡና በናንተ ግፊት ያነበብን ሰዎች በናንተ መገረም እንገረማለን::

Anonymous said...

ድ.ን ኤፍሬም, ከላይ ፍቅር እስከመቃብር አለማንበቤን የጻፍኩት እኔ ነኝ:: የረሳሁት ነገር ስላለ ነው ይኸውም ለኔ የሚገርመኝ ደግሞ ፍቅር እስከመቃብርን ያላነበበ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ፊደል ቆጥሮ በይስማእከ ወርቁ የተደረሰውን ዴርቶጋዳን ያላነበበ ኢትዮጵያዊ ነው::

Ephrem Eshete G. said...

ጥሩ ሐሳብ አንስተኻል። እኔም እንዳልኩት “ፍቅር እስከ መቃብርን” ባለማንበባችሁ የአዕምሮ እና የዕውቀታችሁን መጠን መቸም አናሳንሰውም። እንዲያው ለነገሩ እኔም የበኩሌን ከመናገሬ በፊት እስቲ ሌላ አንባቢ የሚለው ካለ ልጠብቅ። ምን ይመስልኻል?

Ephrem Eshete G. said...

For the one who asked me to refrain from "politics", you must be kidding. I know exactly how Ethiopia is multifaceted and diversified. I see you write a nice English. Will that not be weird not knowing your very country's African time-old alphabet? I see you care for the Church. This Church's heritage is beautified with Her Ethiopic alphabet. I recommend you to read Dr. Ayele Bekerie's book (Ethiopic, an African Writing System:
Its History and Principles). http://bit.ly/TxudWD

Anonymous said...

ዲ.ን ኤፍሬም
መልካም! እንዳልከውም እስኪ ሌላ አንባቢ የሚለው ካለ እንስስማ::

Anonymous said...

እውነት ነው ኤፍሬም፡፡ የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ እያንዳንዱ ቤት ባይገባ የሚደንቅ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ትረካውን የሰማሁት በልብወለድ መጽሐፍት አንባቢነቷ ከቤታችን ወደር የሌላት ከእህቴ ( ለቤታችን ሦስተኛ ልጅ) ነው፡፡ በዛ የብረት አልጋ ላይ ከሷ በታች የሆነው አራት ልጆች ( ሶስት ወንዶች አንድ ሴት) ተደራርበን አፋችንን ከፍተን ነበር የምንሰማት፡፡ ድምጿን እንደ ገጸ ባህርያቱ እየቀያየረች ስተርክልን በዛ የልጅነት እድሜያችን እንዴት ይጣፍጠን እንደነበር አሁን ላይ ሆኜ ሳስታውሰው ይደንቀኛል፡፡ ከዛም በሬዲዮም ትረካውን ሰምቻለሁ፡፡ መጽሐፉንም አንብቤዋለሁ፡፡ ከዚህ ጋር በማገናኘት ያስነበብከን የጽሑፍህም መልዕክት እጅግ መስጦኛል አመሰግናለሁ፡፡

Anonymous said...

እውነት ነው ኤፍሬም፡፡ የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ እያንዳንዱ ቤት ባይገባ የሚደንቅ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ትረካውን የሰማሁት በልብወለድ መጽሐፍት አንባቢነቷ ከቤታችን ወደር የሌላት ከእህቴ ( ለቤታችን ሦስተኛ ልጅ) ነው፡፡ በዛ የብረት አልጋ ላይ ከሷ በታች የሆነው አራት ልጆች ( ሶስት ወንዶች አንድ ሴት) ተደራርበን አፋችንን ከፍተን ነበር የምንሰማት፡፡ ድምጿን እንደ ገጸ ባህርያቱ እየቀያየረች ስተርክልን በዛ የልጅነት እድሜያችን እንዴት ይጣፍጠን እንደነበር አሁን ላይ ሆኜ ሳስታውሰው ይደንቀኛል፡፡ ከዛም በሬዲዮም ትረካውን ሰምቻለሁ፡፡ መጽሐፉንም አንብቤዋለሁ፡፡ ከዚህ ጋር በማገናኘት ያስነበብከን የጽሑፍህም መልዕክት እጅግ መስጦኛል አመሰግናለሁ፡፡

Anonymous said...

እውነት ነው ኤፍሬም፡፡ የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ እያንዳንዱ ቤት ባይገባ የሚደንቅ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ትረካውን የሰማሁት በልብወለድ መጽሐፍት አንባቢነቷ ከቤታችን ወደር የሌላት ከእህቴ ( ለቤታችን ሦስተኛ ልጅ) ነው፡፡ በዛ የብረት አልጋ ላይ ከሷ በታች የሆነው አራት ልጆች ( ሶስት ወንዶች አንድ ሴት) ተደራርበን አፋችንን ከፍተን ነበር የምንሰማት፡፡ ድምጿን እንደ ገጸ ባህርያቱ እየቀያየረች ስተርክልን በዛ የልጅነት እድሜያችን እንዴት ይጣፍጠን እንደነበር አሁን ላይ ሆኜ ሳስታውሰው ይደንቀኛል፡፡ ከዛም በሬዲዮም ትረካውን ሰምቻለሁ፡፡ መጽሐፉንም አንብቤዋለሁ፡፡ ከዚህ ጋር በማገናኘት ያስነበብከን የጽሑፍህም መልዕክት እጅግ መስጦኛል አመሰግናለሁ፡፡

Anonymous said...

እኔ እስከሚገባኝ የነ ኤፍሬም ኢትዮጵያና የልጅ እግሩ የዩኒቨርሲቲ መምህር ኢትዮጵያ የተለያዩ ናቸው። ዩኒቨርሲቲ ሲባልም እንደ አ/አ ዩኒቨርሲቲ ያለ ትዝ የሚለው ካለ ትልቅ ስህተት ይመስለኛል ። ሶማልያ ክልል ተወልዶ ጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ እዚያው መምህር ቢሆን ፍቅር እስከመቃብርን ይቅርና የፊደል ገበታን የሚያነብ አይመስለኝም። በአማርኛ ከትምህርት ሚኒስቴር የተላከን ደብዳቤ የማያነብ የዩኒቨርሲቲ መምህር ጓደኛ አለኝ።ዲን ኤፍሬምም ለንጽጽር/ለማጉላት/ ተጠቀመው እንጂ ሲጀመር አብዛኛው የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ህዝብ የማንበብም ሆነ በሬድዮ የመስማት እድል ስለሌለው ዜግነቱ ይሻር ማለቱ አይመስለኝም። ዋናው ጭብጡ ጉዱ ካሳነትና አባ ሞገሴነት ይመስለኛል።

Anonymous said...

I didn't read 'fikir eske mekabir'. Now I am tempted to read it, we will see if I can do it.
I found the following link for the scanned version of the book:
http://good-amharic-books.com/onebook.php?bookID=683

Ephrem Eshete G. said...

Thank you friends. For the last Annonymous, if you are in Ethiopia, I recommend you to read the hard copy if you can.

Anonymous said...

ዳ/ን: ፍቅር እስክ መቃብርን ሙሉ ታሪኩን ያነበብኩት በቅርቡ ነው:፡ በዚያ ዘመን እንደዚህ ያለ ግሩም ልብ-ወለድ ጽሑፍ መጻፍ የሚያስደንቅ ነው:: በየዘመኑ ያለውን የመንግስት አወቃቀር ስርዓት፣ የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ፣ብሶትና ስርዓቱን ለማስወገድ ያለውን ቁርጠኛነት በግልጽ የሚተች እና ያለ ፍርሃት የሚያጋልጥ: እንደ ሀዲስ ዓለማየሁ ያለ ደራሲ ያስፈልገናል:ዛሬም::

Anonymous said...

ሁልጌዜም ቢሆን ፍቅር እስከ መቃብር ባለማንበቤ ቅር ይለኛል ምንም በትረካ ማለትም በሬድዮ ትረካ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ተከታትየ በልጅነት አምእሮየ አዳምጨዋለሁ ስለዚህም አሁን ከፊት ከነበረኝ ሃሳብ በተለየ መልኩ ለማንበብ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ እግዚያብሄር ይባርክህ አመሰግናለሁ! ንጉስ ከ ደ/ታቦር

Anonymous said...

ሁልጌዜም ቢሆን ፍቅር እስከ መቃብር ባለማንበቤ ቅር ይለኛል ምንም በትረካ ማለትም በሬድዮ ትረካ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ተከታትየ በልጅነት አምእሮየ አዳምጨዋለሁ ስለዚህም አሁን ከፊት ከነበረኝ ሃሳብ በተለየ መልኩ ለማንበብ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ እግዚያብሄር ይባርክህ አመሰግናለሁ! ንጉስ ከ ደ/ታቦር

Anonymous said...

እኔ ሰው የተረከልኝን ነገር ማንበብ አልወድም ፍቅር እስከ መቃብርን እናቴ ተርካልኛለች ደርቶጋዳን ጓደኞቼ ተርከውልኛል የተተረከ ነገር ማንበብ ለምን የታየ ፊልም እንደመድገም ነው...በነገራችን ላይ የሰርቅ.ዳ...ን ቆንጆዎቹ_ ያነበበ አለ?መጽሃፉ ስለቁንጅና አይደለም ስለ ኢትዮጵያዊነት ደግሞም አፍሪካዊ ራእይ ነው ..ይልቅ ኦሮማይን ጀመሮ የሚቆም ሰው ሊያስገርም ይችላል ፍቅር እስከ መቃብር ግን የመጀማሪዎች ገጾች ደባሪዎች ናቼው ጠቃ ጠቆውን ሳንጨመር!

Anonymous said...

yihuna min yibalal

Getahun Seifu said...

What a perspective! It's provocative to think about what is happening right now in the country. I liked the term "intellectual prostitutes". It brought one problem I usually think about. I am referring to those big names we know in Ethiopia who helped the TPLF design their divisive policies. Such guys/professors/doctors/intellectuals include the likes of prof Andreas Eshete, Kifle Wodajo, Negaso Godada, Berhanu Nega, etc who came with TPLF and assisted them do what is devastating Ethiopia right now. Though later, some fell out. If they were not selfish and advised the illiterate TPLFs and affiliates correctly, things could have been different now. I am sure Ephrem can put these in beautiful language one day. Thanks again for eliciting the weaknesses of the current teachings in the country, which is also a byproduct of what I said above.