Monday, October 8, 2012

ይህ ሁሉ ለአንድ ሰው(ኤፍሬም እሸቴ/ ARTICLE IN PDF)፦ ባለፈው ዓመት በአንዱ እሑድ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኔ አንድ የክርስትና ዝግጅት ነበር። በአካባቢያችን ከሚኖሩት ክርስቲያኖች አንዷ ልጃውን ለማስጠመቅ መጥተው ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ካህናቱ ከቅዳሴው አስቀድመው ለሕጻኑ መደረግ ያለበትን ሥርዓተ ጸሎት ያደርሱ ገቡ። ሙሉ ሥርዓቱ ከተከናወነ በኋላ ካህኑ ሕጻኑን በውኃው ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያደረጉ “አጠምቀከ በስመ አብ፣ አጠምቀከ በስመ ወልድ፣ አጠምቀከ በስመ መንፈስ ቅዱስ ይን ስምከ …፤ በአብ ስም አጠምቅኻለኹ፣ በወልድ ስም አጠምቅኻለኹ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠምቅኻለኹ፣ ስምህ … ይሁን” እያሉ የክርስትና ስሙን እየሰየሙና እየተናገሩ ያጠምቁታል።

ሕጻኑ ከተጠመቀ በኋላ ቅብዐ ሜሮን ተቀብቶ፣ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ በንፍሐት እንዲያድርበት ካህኑ እፍፍፍፍ አሉበት። ማተብ አሠሩለት። ወደ ክርስትና አባቱ ዞረው “ይህንን ልጅ በሃይማኖት ኮትኩተህ የማሳደግ ኃላፊነት አለብህ” እያሉ አደራውን አስረከቡት። አዲሱ ክርስትና አባትም አንገቱን ደፍቶ “እሺ፣ እሺ” እያለ ቁልቁል ሕጻኑን ይመለከተዋል።

መቸም ጥምቀተ ሕጻናት ወይም ክርስትና ሲኖር ቤተሰብን ተከትለው የሚመጡ “አቋቋሚዎች” ይኖራሉ። በዕለቱ ከነበሩት ብዙ ሰዎች አንዱ በዚያ በጠዋት የመነሣት ልምዱ ያላቸው አይመስሉም። አንድ ሕጻን ለማጥመቅ ያ ሁሉ ጸሎት እና ሥርዓት እንዲሁም ክብር መኖሩ ደንቋቸዋል። “ይኼ ሁሉ ጸሎት ለአንድ ሕጻን?” ሲሉ መጠየቃቸው ፈገግ አሰኝቶኝ በየጨዋታው የምናነሣው ጉዳይ ሆነ።

በሌሎቹ እምነቶች በኩል ያለውን የዚህ መጽሔት ዓምደኞች በሃይማኖት ዓምዳቸው ሊያብራሩልን እንደሚችሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አንጻር ያለውን እና በመግቢያዬ የተነሣኹበትን ምሳሌ ትንሽ ለማስፋፋት ልሞክር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፈጣሪዋ የምታገኘውን ጸጋ እና በረከት ለመንፈስ ቅዱስ ልጇቿ የምታስተላልፈው እያንዳንዳቸውን በምታውቃቸው በየስማቸው እየጠራች፣ በግላቸው ነው። ሲወለዱ ክርስትና ታነሣለች፣ ታቆርባለች፣ ማግባት ሲፈልጉ ጸሎት አድርጋ (ምሥጢረ ተክሊል ፈጽማ) ታጋባለች፣ ሲታመሙ (በምሥጢረ ቀንዲል) በጸሎቷ - በጠበሏ ትፈውሳለች፣ ሲሞቱ ጸሎት (ፍትሐት) አድርጋ ትሸኛቸዋለች። ይህ ሁሉ አገልግሎቷ በግለሰብ ላይ የተመሠረተ ነው።

እንደ ሥርዓቱ ከሆነ ሰውየው ድሃም ሆነ ባለ ጸጋ፣ ከየትኛውም ዘር ይገኝ - ከየትኛውም አካባቢ ይምጣ ከዚህ ሰማያዊ ጸጋ የመካፈል መብቱ የተጠበቀ ነው። ቤተ ክርስቲያንም “በነጻ የተቀበልሽውን በነጻ ስጪ” ተብላለችና የእምነቱ ተከታይ የሆነ ማንም ሰው ከነዚህ ሀብታት በነጻ የመካፈል ነጻነት አለው። ከሰማይ የሚገኘውን ሰማያዊ ሀብት በነጻ መካፈል ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው ማንነቱ በተለየ ሁኔታ ታውቆ የዚህ ጸጋ ተካፋይ መሆኑ፣ “ይህ ሁሉ ለአንድ ሰው” መደረጉ ለውስጤ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል።

ለአንድ ሰው የሚደረግ መልካም ነገር ለብዙ ሰው እንደሚደረግ መልካም ነገር መቆጠር ይችላል። በተነጻጻሪ በአንድ ሰው ላይ የሚደረግ ክፉ ነገር፣ በብዙዎች ላይ እንደተደረገ ክፉ ነገር ሊቆጠር ይገባዋል። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው “ለራስህ የምትጠላውን ለማንም አታድርግ” (ጦቢት 4፡15)፤ እንዲሁም “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱት እንዲሁ እናንተ አድርጉላቸው” (ሉቃስ 6፡31፤ (ማቴዎስ 7፡12)፤ የሚለው ሁሉ በራሳችን እንዲደርስ የማንፈልገው ማንኛውም ነገር በሌላ በማንም ግለሰብ ላይ እንዳይደርስ ማሰብን ያጠይቃል።

ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በዘመነ ናዚ ጀርመን የነበረን አንድ ጀርመናዊ ቄስ የጸጸት ንግግር ያስታውሰኛል። ጀርመናዊው ቄስ ማርቲን ኔውሞለር (1892-1984) ናዚ ጀርመኖች በገነኑበት እና አይሁዶችን ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጨፈጨፉበት ዘመን ዕብደቱ ሲጀምር ጀምሮ ዝምታን መርጠው፣ ራሳቸውን ለማትረፍ ሽተው ነገር ግን ሌላውንም ሳያተርፉ ራሳቸውም ሳይድኑ በእሳቱ ለተገረፉ ዝምተኛ ምሑራን የተናገረው እንደሆነ ይጠቀሳል። በአጭሩ እንዲህ ይላል “መጀመሪያ ኮሚኒስቶቹን ሊወስዱ መጡ፣ ኮሚኒስት ስላልሆንኩ ምንም አልተናገርኩም፤ ቀጥሎ የሠራተኛ ማኅበራቱን ሊወስዱ መጡ፣ ምንም አልተናገርኩም ምክንያቱም የሠራተኛ ማኅበር (አባል) አይደለኹም፤ ቀጥሎ ወደ አይሁዳውያኑ መጡ፣ ምንም አልተናገርኩም ምክንያቱም አይሁዳዊ አይደለኹም፤ ቀጥሎ ወደ እኔ መጡ፣ እና ለእኔ ለመናገር (ለመቆም) የሚችል የተረፈ ማንም ሰው አልነበረም”።

ናዚዎቹ “ወደ አንዱ ሰው ሲመጡ” የሚናገር ሰው ቢኖር ከዚያ በኋላ ለተወሰዱት ለሚሊዮኖች መትረፍ ምክንያት ይሆን ነበር ብለን ማሰብ እንችላለን። የመጀመሪያው ሰው ሲወሰድ ያልተናገረ አንድ ሚሊዮነኛው ሰው ሲወሰድ ለመናገር ብርታቱም፣ ብቃቱም አይኖረውም። አንዱን ሰው ማትረፍ ብዙውን ሰው ማትረፍ ነው። አንዱን ሰው መጉዳት ዞሮ ዞሮ ሌሎች ብዙዎችን መጉዳት ነው።

የዛሬ 10 ዓመት ዲሲ እና አካባቢዋን በሽብር ያናወጣት ተከታታይ የግድያ ወንጀል ተፈጽሞ ነበር። ያንን ወንጀል የፈጸሙት ሁለት ሰዎች በቅጽል ስማቸው “የዲሲው አነጣጥሮ ተኳሽ/ The DC Sniper” ተብለው ይታወቃሉ። ሰዎቹ በተለያዩ የዲሲና አካባቢ መንደሮች በመዘዋወር፣ መኪናቸው ውስጥ ባዘጋጁት የመተኮሻ ቀዳዳ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ለመፈጸም የሚጣደፉ ዜጎችን እያነጣጠሩ ይገድሉ ነበር። ሰዎቹ ከተያዙና ከተፈረደባቸው የቆየ ቢሆንም 10ኛ ዓመቱን አስመልክቶ ከሁለቱ አንዱ ሰሞኑን በሰጠው ቃል በጉዳዩ መጸጸቱን ተናግሮ በተለይ ከገደላቸው ሰዎች ጀርባ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን እያነሣ ሲናገር ተደምጧል። ከገደለው አንድ ሰው ጀርባ ስንት ሰዎች ነበሩ? የአንዱ ሰው ሕይወት መቀጠፍ የስንቱ ሕይወት ላይ ጥላውን አጥልቷል?

“አንድ” የምትባለው ቁጥር በሌሎች ነገሮች ስትመዘን ትንሽ ብትሆንም በ-‘ሰው’-ነት ከተቆጠረች ግን “አንድ” ጥቂት ሳትሆን ብዙ ናት። አንድ ሰው በምንም መመዘኛ ከአንድ ሕንጻ፣ ከአንድ ግድብ፣ ከአንድ እርሻ ወይም ከአንድ መኪና ጋር ሊነጻጸር አይገባውም። ሰው ክቡር ነው ሲባል ከአንዱ ሰው ጀምሮ እንጂ ሰዎች ለመከበር እና የሚፈልጉት ነገር እንዲሟላላቸው “ብዙ ሰው-ዎች” መሆን አይጠበቅባቸውም። ለአንዱ የተደረገው ለሁሉ የተደረገ ነው። በቅዱስ መጽሐፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው “ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት፤ ለአንዱ ያላደረጋችሁት ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ነው” (ማቴዎስ 25፡40-45)። በርግጥም እያንዳንዱ ሰው ጤነኛ ከሆነ ሁላችን ጤናማ ነን። ግለሰብነትን የሚድጡ እና ጅምላነትን (ሕዝብነትን) ብቻ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ አመለካከቶች እና አስተምህሮዎች የማይስማሙኝ ለዚህ ነው።

ሕዝብ የሰዎች አንድነት ነው። ሰዎች ደግሞ በጋራ አንድ ሆድ፣ አንድ ጭንቅላት፣ አንድ መራመጃ፣ አንድ ዓይን የላቸውም። ሕዝብ መብቱ የሚከበርለት ሕዝብን ሕዝብ ያደረጉት እያንዳንዳቸው ቅንጣት ሰዎች በየራሳቸው ማንነታቸው ሲታወቅ፣ ሲከበር ነው። ሕዝብ የሚባለው ነገር የጋራ ሆድ እንደሌለው ሁሉ የጋራ ጭንቅላትም የለውም። የሕዝብ ጭንቅላቶች ዜጎች/ ግለሰቦች ናቸው። ሕዝብን የሚወድ - ቅንጣት ሰዎችን ሊወድ ይገባዋል።

በተቋም ደረጃ ብቻ ሳይሆን በባህልም ደረጃ ስንመለከተው ኢትዮጵያውያን አንዳችን ለአንዳችን ያለን ክብር እና መጠንቀቅ በጉራ እንደምናወራው ይኼን ያህል የሚያኮራ ነው ብዬ አላምንም። እርስበርሳችን አንዳችን የሌላችንን መብት ስንጥስ ውለን ስንጥስ የምናድረው ለሰውነት ያለን ክብር ችግር ስላለው ይመስለኛል። በግላችንም ይሁን በተሰጠን ኃላፊነት የምንሠራው ሥራ ሌላ ሰው መጥቀም ቢያቅተው እንኳን እንደማይጎዳ ግን እርግጠኛ መሆን አለብን።  ለምሳሌ በየሠፈሩ የምናስቆፍራቸው ጉድጓዶች የስንቱን ሰው እግር እንደሚሰብሩ፣ በስንቱ ሰው ላይ አካላዊ ጉዳት እንደሚያደርሱ ሲሰማ በርግጥ “ጥቂት ጥንቃቄ ማድረግ ይኼን ያህል ከባድ ነበር?” ያሰኛል። ችግሩ ከተግባሩ ሳይሆን ሰው ለሚባለው ፍጥረት ከምንሰጠው ቦታ ነው።

ፕሬዚዳንት ኦባማ የዚህ ዓመት የፓርቲያቸው ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር አንድ ዐቢይ ቁምነገር ሲጠቅሱ ሰማዃቸው። እንዲህ አሉ፦ “ዜግነት በሚባለው ቁምነገር እናምናለን፤ የአገራዊ መሠረታችን አስኳል፣ የዲሞክራሲያችንም ቅመም ነው። ይህች አገር ሕያው ሆና የምትሠራው አንድኛችን ለአንድኛችን ሲገደን፣ (አንድናችን ለአንድኛችን) እና ለመጪውም ትውልድ ኃላፊነት ሲሰማን ነው። … አንድ የመኪና ፋብሪካ ኃላፊ ሠራተኞቹ የሚሠሩትን መኪና መግዛት እንዲችሉ ሲያደርግ ጠቅላላ ድርጅቱ ውጤታማ/አትራፊ እንደሚሆን እናምናለን። አንድ ቤተሰብ መክፈል ከማይችለው የቤት ግዢ ዕዳ ውስጥ በማጭበርበር እንዲገባ ካልተደረገ ቤተሰቡ ከችግር ይድናል፣ ያ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ቤተሰቦች እሴቶችም ከጉዳት ይድናሉ፣ በጠቅላላው ኢኮኖሚያችም ይድናል …”።

በዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገን ትልቅ ሀብት ቢኖር ይህ እርስ-በርስ ያለን መተሳሰብ፣ መተዛዘን፣ መከባበር እና የኃላፊነት ስሜት ነው። አገራችንንም መድኅን የሚሆናት እርሱ ነው። እንደ ቃየል “እኔ የወንድሜ ጠባቂ አይደለኹም” ማለት አያዋጣንም። ከዘርና ጎሳ በላይ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት እና ድርጅታዊ ታማኝነት በላይ፣ ከጊዜያዊ ርካሽ ጥቅም እና ስግብግብነት በላይ “ሰው” ያውም ዜጋችን ለሆነው የራሳችን ሰው የምንቆምበት ዘመን አሁን ነው። በርግጥም ይህ ሁሉ ነገር “ለአንድ ሰው ያስፈልገዋል፤ ይገባዋልም”።

ይቆየን - ያቆየን።   

  

 

 

 

 

  

 © ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም::

 

5 comments:

Anonymous said...

እግዚአብሔር ይስጥልኝ ቅልብጭ ጥፍጥ ስላለች ጡመራህ፡፡

Anonymous said...

God bless you! Nice article. Helping & loving each other is the best thing that we should follow.

The Architect said...

ከጽሑፍህ መንፈስ እንደተረዳሁት (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ) ለግለሰብ መብት እውቅና እና ቅድሚያ ሳንሰጥ ስለ ቡድን ወይንም ብዙኃን መብት ጥበቃ መከራከር ትክክለኛ ሃሳብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች የግል ምርጫቸው (የሌሎችን መብት እስካለተጋፉ ድረስ) ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ ፈቃዳቸው ካልሆነም ብሄር፣ መንደር፣ ሠፈር… ተብለው በጅምላ መፈረጅ የለባቸውም፡

The Architect said...

ከጽሑፍህ መንፈስ እንደተረዳሁት (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ) ለግለሰብ መብት እውቅና እና ቅድሚያ ሳንሰጥ ስለ ቡድን ወይንም ብዙኃን መብት ጥበቃ መከራከር ትክክለኛ ሃሳብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች የግል ምርጫቸው (የሌሎችን መብት እስካለተጋፉ ድረስ) ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ ፈቃዳቸው ካልሆነም ብሄር፣ መንደር፣ ሠፈር… ተብለው በጅምላ መፈረጅ የለባቸውም፡፡

The Architect said...

ከጽሑፍህ መንፈስ እንደተረዳሁት (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ) ለግለሰብ መብት እውቅና እና ቅድሚያ ሳንሰጥ ስለ ቡድን ወይንም ብዙኃን መብት ጥበቃ መከራከር ትክክለኛ ሃሳብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች የግል ምርጫቸው (የሌሎችን መብት እስካለተጋፉ ድረስ) ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ ፈቃዳቸው ካልሆነም ብሄር፣ መንደር፣ ሠፈር… ተብለው በጅምላ መፈረጅ የለባቸውም፡፡