Monday, October 29, 2012

እውነታ - ማንጠር (Fact Checking)(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ አሜሪካ አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ደፋ ቀና እያለች ነው። ሁለቱ እጩዎች ማለትም ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና የማሳቹሴትስ ገዢ የነበሩት ሚት ራምኒ እረፍት የላቸውም። ከደጋፊዎቻቸው ያሰባሰቡት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በተለይም ወሳኝ በሚባሉ ግዛቶች ከፍ ላለ የማስታወቂያ ክፍያ በዋል ላይ ይገኛሉ። ከማስታወቂያውም ባሻገር ራሳቸው ተወዳዳሪዎቹም በመላው አገሪቱ በመዞር የምረጡኝ ዘመቻ በማካሔድ ላይ ናቸው።

እያንዳንዱ ወሳኝ ቲቪ እና ሬዲዮ ጣቢያ ዋነኛ የፖለቲካ ዓምድ ይኸው ምርጫ ነው። በአገሪቱ ታዋቂ የሆኑ “ቶክ ሾዎች” (ማለቴ ፖለቲካ ቀመስ ቶክ ሾዎች) በዚሁ ምርጫ ዙሪያ ሰፊ ትንተና ያቀርባሉ፤ ይከራከራሉ። ያለኹበትን አካባቢ ለመጥቀስ ሞከርኩ እንጂ እያንዳንዱ ከተማ እና አካባቢ ባሉት ኤፍ.ኤም ሬዲዮኖች የሚያቀርቡትን በሙሉ መስማት አልችልም። ለመገመት ግን ይቻላል።

የዚህ ሁሉ የቲቪና ሬዲዮ እንዲሁም የጋዜጣ ትንተና እና ውይይት መድረሻና መዳረሻ “እውነታን ማንጠር”፣ ሐሳብን እና አመለካከትን መሞረድ፣ ወይም ገለባን ከምርቱ እንደማንጠርጠር፣ በሰፌድ በወንፊት እንደማጣራት ዓይነት ነው። በዚህ ውይይት የሚንጠረጠረውና የሚጣራው እውነታው ከሐሰቱ፣ ጠቃሚው ከማይጠቅመው ነው። ይኸው የአንዱ መስመር ከሌላው የሚለይበት የሐሳብ ማንጠርጠሪያ ገበታ በሌላ አነጋገር “ነጻ ሚዲያ” ልንለው እንችላለን።

ከ“ነጻ ሚዲያው” መካከል ዜናውንና ሐተታውን ከማቅረብ ባሻገር በሁሉም መስክ የሚባለው፣ የሚነገረው፣ የሚጻፈው፣ የሚተነተነው ጉዳይ ትክክል መሆን አለመሆኑን ቀድመው በማረጋገጥና ለዚህም ከፍተኛ ግምት በመስጠታቸው የሚታወቁ ጥቂት የዓለም ሚዲያዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ የጀርመኑን ሳምንታዊ መጽሔት “ዴር ሽፒግል”ን (Der Spiegel) የሚያክል የለም። (“ኒውዮርክ ታይምስ”ን የመሳሰሉት ጭምር።)

መጽሔቱ (እ.አ.አ) ከ1940ዎቹ መጨረሻ  ጀምሮ ለብዙ አሠርት ዓመታት በዚህ ጉዳይ ልምድ በማካበቱ ይታወቃል። “ዴር ሽፒገል” ለሚጽፋቸው ነገሮች ያለው ጥንቃቄ እና የጉዳዩን እርግጠኝነት የሚያጣሩለት “እውነታ አንጣሪዎች” ብዛት አላቸው፤ ለብቻቸው በአንድ መምሪያ ደረጃም የተዋቀሩ ናቸው። በየዓምዱ፣ እንደየሙያው የሚጻፈውን ነገር እርግጠኝነት ያጣራሉ። እውነታውን ያነጥራሉ።

ታዲያ ይህ “እውነታ ማንጠር” በዚህ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሰሞን ተደጋግሞ የሚነሣ ሐሳብ ነው። ከፍ ብዬ እንዳልኩት፣ ሁለቱ ተወዳዳሪዎች፣ በማስታወቂያውም በምረጡኝ-ዘመቻውም ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ናቸው። ሚዲያዎቹ ደግሞ እጩዎቹ የሚናገሯቸውን ንግግሮች በመውሰድ “እገሌ ያለው ትክክል ነው ወይስ አይደለም?” እያሉ ይተነትኑታል። በተለይም አንዱ ተወዳዳሪ ስለሌላኛው የሚናገረውን እንዲህ በቀላል አያልፉትም። እያንዳንዷን ሐሳብ እና ንግግር ይሰነጣጥቋታል፤ ያበጃጇታል። እውነታ-ማንጠር ያልኩት ፈረንጆቹ Fact Checking የሚሉትን ሐሳብ ነው።

ይህ እውነታ-ማንጠር በተለይ ጎልቶ የሚታየው ሁለቱ እጩዎች ፊት-ለፊት፣ መሳ-ለመሳ በሚያደርጉት ክርክር እሰጥ-አገባ ወቅት ነው። እጩዎቹ ኦባማ እና ራምኒ ሦስት ጊዜ ተገናኝተው የተከራከሩ ሲሆን “እውነታ አንጣሪ” (ፋክት ቼከርስ) ባለሙያዎቹ ደግሞ የያንዳንዱን ንግግር ብልት በብልት እያነሱ “እገሌ ያሉት ሙሉ እውነታ አለው፣ ግማሽ እውነታ አለው ወይም ስሐተት ነው” እያሉ ይተቻሉ።

ክርክሮቹ እንዳበቁ፣ ዋናዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለምሳሌ ሲ.ኤን.ኤን፣ ኤም.ኤስ.ኤን.ቢ.ሲ እና ፎክስ የየራሳቸው “እውነታ አንጣሪዎችን” አቁመው የየራሳቸውን ዳታ በማቅረብ ክርክሮቹን ይተቻሉ። ጋዜጦቹ እና መጽሔቶቹ እንዲሁም ይህንኑ ጉዳይ የሚከታተሉ ድረ ገጾችም “ፋክት ቼኪንጉን” ይቀጥላሉ። በድረ ገጽ ደረጃ እውነት-አንጣሪዎች ምን እንደሚመስሉ በምሳሌ ለማጎላመስ www.politifact.com እና www.factcheck.org መመልከት ጥሩ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ እውነት የሆነውን እና የተሳሳተውን ነገር እየለየ እና እየፈተሸ የሚያቀርብ ነጻ ሚዲያ እና ተቋም መኖር ሕዝብ የትኛውን መውሰድ እንዳለበት እንዲረዳ ያግዘዋል። በአንድ ግለሰብ ደረጃ ሊታወቁ እና ሊመረመሩ የማይችሉ ነገሮች በዚህ መልኩ ተበጥረው እና ተንጠርጥረው ሲቀርቡ ለሦስተኛ ወገን ብቻ ሳይሆን በዚህ “ምርመራ” ውስጥ ለሚያልፈውም አካል ቢሆን እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። በግምት፣ በይሆናል፣ በስማበለው እና በጥርጣሬ ላይ ተመስርቶ ርምጃ ከመውሰድ ያግዳል።

የምዕራቡ ዓለም የተጣራ እና ጥንቅቅ ያለ ነው ባይባልም እንዲህ እውነቱን ለማወቅ የሚፈልግና የሚሞክር ነጻ ሚዲያ እና ተቋም አለ። በነዚህ ነጻ ሚዲያዎች እና ነጻ ተቋማት የማይፈተሽ ሐሳብም ሆነ አመለካከት የለም። ለማሰብ ገደብ የለም። ስለዚህ በአመዛኙ የሕዝባቸውን ይሁንታ የሚፈልጉ፣ የሕዝባቸውን ድምጽ የሚያዳምጡ መንግሥታት፣ ተቋማት እና አሠራሮች ተፈጥረዋል።

በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነቱ የነገሮች፣ የአመለካከቶች እና የሐሳቦች እውነታ ማንጠሪያ እና ማበጠሪያ ተቋም እና ባህል በሌላቸው አገሮች በነጻነት ማሰብ የተገደበ ነው፤ ቢፈቀድም ‘የተወሰኑ ነገሮችን ሳይነካ’ ነው። አይነኬ የሆኑት ሐሳቦች ዞረው ዞረው “ተፈቀደ” የተባለውን ነጻነት የሚገድቡ ሲሆኑ እናገኛቸዋለን። እነዚህ አገሮች ዞሮ ዞሮ ዓምባ ገነኖች የሚመሯቸው ናቸው።

እንዲህ ዓይነቱን ነጻ አሠራር የሚመለከት ማንኛውም ሰው በራሱ አገር ላይ ሲተገበር ቢያየው ይደሰታል። ኢትዮጵያዊው በኢትዮጵያ አገሩ እንደማለት ነው። በአገራችን በዚህ መልክ ልንፈትሻቸው የሚገቡ ብዙ ወሳኝ ጥያቄዎች አሉን። በሁሉም የሕይወት መስኮች ላይ የሚገኙ።

በሌላውም ዓለም እንደሚደረገው የመጀመሪያው ጥያቄ የሚመለከተው አገሪቱን የሚያስተዳድረውን መንግሥት ነው። ፖሊሲዎቹ፣ አሠራሮቹ፣ አመራሮቹ እና ርዕዮቹ በሙሉ በገለልተኛ ሚዛን እንዲታዩ ማድረግ ማለት ነው። በአገራችን የተለመደው ራሱ መንግሥት ስለ ራሱ ጠንካራ እና ደካማ ጎን እውነታውን ለማንጠር (ግምገማ) የሚፈልገው በር ዘግቶ በራሱ ዘዴ እና በራሱ ሰዎች ስለሆነ “እውነት ማንጠሩ” ገለልተኛ አይሆንም፤ ማጠቃለያው ትክክልም እንኳን ቢሆን በሌሎች ዘንድ የሚኖረው ተቀባይነት አናሳ ይሆናል።

ዜጎች መንግሥቶቻቸውን የማያምኑት ከዚህ የተነሣም ነው። ይፈሯቸዋል እንጂ አያምኗቸውም። ያከብሯቸዋል እንጂ አይወዷቸውም። ያሞግሷቸዋል እንጂ ከልባቸው አይቀበሏቸውም። ያሉትን አይቃወሙም እንጂ ከልባቸው አያደርጉትም። ይሰሟቸዋል እንጂ አያዳምጧቸውም።

እንዲ ሲሆን ደግሞ ሕዝቡ “ጮኽነ ጮኽነ፤ እንዳልጮኽነ ኾነ” እንዳለችው ውሻ ወይም “እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” እያለ ዝምታን ይመርጣል። ወይም አልቅስ ሲሉት ያለቅሳል፣ ዝፈን ሲሉት ይዘፍናል፣ ተራገም ሲሉት ይራገማል። እቤቱ ሲገባ ግን ሁሉንም ረስቶ በራሱ ሕይወት ይኖራል።

መንግሥት የእውነታ ማንጠሪያውን የመገንባት ግዴታ አለበት። ነጻ ሚዲያውን፣ ነጻ ተቋማቱን። ነጻ ሚዲያና ተቋም የሚጠላ መንግሥት ክፉ ቀንም ሆነ በጎ ቀን መምጣቱትን የሚናገሩ ነቢያቱን እንደሚገድል ሰው ነው። መንገድ ጠራጊዎቹን አስቀድሞ ስለሚያጠፋ መች ወድቆ እንደሚሰበር፣ ተሰብሮም እንደሚቀር ሳያውቀው ይቀራል። ነገሩ ሁሉ ነቢዩ ዳዊት እንዳለው “እንደ ሊባኖስ ዛፍም ረዝሞ አየኹት፣ ብመለስ ግን አጣኹት፤ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም።” (መዝሙረ ዳዊት 36/37፥36) ይሆናል። ጋዜጠኞችን በሙሉ እየሰበሰቡ እያጎሩ “ሁለት ባርኔጣ አርገው አገኘዃቸው፣ ቀይ መስመር አለፉ፣  አሸበሩኝ” ማለት ጠቢብነት አይደለም።

www.politifact.com የተባለው ድረ ገጽ የፕሬዚዳንት ኦባማን ፖሊሲዎች እና የገቧቸውን ተስፋዎች የሚገመግምበትን ዓምድ “Obameter/ ኦባሜትር” (ቴርሞ ሜትር፣ ባሮ ሜትር እንደሚባለው) እንዳለው “ኢሕአዲሜትር” -ለኢሕአዴግ፣ ለጠ/ሚ ኃ/ማርያምም “ኃይሌሜትር” ያስፈልጋል። በየጓዳችን የምናማቸውን በአደባባይ፣ በግልጽነት እንድንመዝናቸው። የወደድነውን ወደነዋል፣ የጠላነውን አያሳየን እንድንል።

መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትነት ራሳቸውን የሚያጩ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች በሙሉ በእውነታ ማንጠሪያ ሚዛን ሊፈተሹ ይገባል። በስመ ተቃዋሚ ምን እንደሚያምኑ፣ ምን መልካም ሐሳብ እንዳላቸው የማይታወቁ፣ ነገር ግን መንግሥትን መቃወምን ብቻ እንጀራቸው ያደረጉ ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች ካሉ በዚሁ መልክ ቢታዩ ለራሳቸውም ለአገርም መልካም ይሆናል።

በሌሎች ምሳሌዎች፦

በአገራችን በደፈናው የሚነገሩ ነገር ግን እውነት ይሁኑ አይሁኑ የማናውቃቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ከቅርቡ ለመጀመር አክራሪነትን የሚያራምዱ ወገኖችን እየተከታተለ መሆኑን መንግሥት ይናገራል። ከመናገርም አልፎ ርምጃዎች እየወሰድኩ ነው ብሏል። አክራሪዎች አይደለንም ነገር ግን ጥያቄ አለን የሚሉት ዜጎች ደግሞ ሐሳባቸውን ለመግለጽ ሙከራ ሲያደርጉ እየተመለከትን ነው። በአገሪቱ እምነቶች መካከል መሳሳብ እና ሊፈነዳ የሚችል ጠላትነት እንዳለ የሚሰብኩ እንዳሉት ሁሉ አገር ሰላም ነው የሚሉም ብዙዎች ናቸው። በ“ብሔረሰቦች፣ ብሔሮች፣ ሕዝቦች” ግንኙነት እና ጥያቄ ዙሪያ እንዲሁ ብዙ የተተበተበ ነገር አለ። ወዳጅነቱ እንዳለ ነው የሚሉ ያሉትን ያህል፣ ጠላትነት እየተጠነሰሰ ነው የሚሉም አሉ።

የዕውቀት መገብያ የነበሩ፣ እውነታ ማንጠሪያ ዘዴዎችን ሊቀስሙ የተሰበሰቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በዘርና በቋንቋ ተቧድነው ድንጋይ ሲወራወሩ ከማየት የበለጠ ልብን የሚያደማ ነገር ከወዴት ይመጣል?

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከዚህ ሁሉ የሐሳብ ትብትብ ውስጥ የእውነታውን ውል (እንደ ክር) ፈልጎ ለማግኘትና ትብትቡን ለመፍታት የሚቻለው እንዴት ነው? ሁሉም ትንሽ እውነታ ብዙ ሐሰት እየያዘ የራሱን መንገድ ከሄደ መመለሻው የት ነው? ለነጻ ሚዲያውና ለነጻ ተቋማት በሙሉ ጥብቅና መቆም የሚገባው አንድም ለዚህ ነው።

አገሪቱ ፖለቲካዊ ስብከት በዝቶባታል። እያንዳንዱ ጉዳይ በፖለቲካዊ ስብከት እየታጀበ ስለሚመጣ እውነታው ነጥሮ አይወጣም። ልክ እንደ ሃይማኖት “አሜን ወአሜን” ብቻ ሆኗል። እግር ኳስን የመሰለ ፖለቲካ የማይስማማው ነገር እንኳን ፖለቲካ-ፖለቲካ ሲል ስናይ “ከዕለት ተዕለት ኑሯችን ውስጥ የፖለቲካው ቫት” እንዲቀነስና ሕይወታችንን እንደወረደ እንድንኖር እንመኛለን። እውነታ ይንጠርና ይውጣ።

ይቆየን-ያቆየን።

 

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ.የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ማተም አይገባም::

 


 

6 comments:

Anonymous said...

Good article and good correlation.

Anonymous said...

Good article and excellent comparison
with Eth. media.

Adugna said...

ወዳጄ ኤፍሬም፡ መልካም ነገር ጽፈሃል፡፡ እውነታን ለማንጠር፤ እውነት መስማትንና እውነት መናገርን ባህል ማድረግ ግድ ይላል፡፡ እውነት መናገር ሙያዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊ ግዴታ ጭምር ነው፡፡ እውነት መናገርና እውነትን መመስከር በቅጽበት የሚመጣ ጠባይ ሳይሆን ከቤተሰብ ጀምሮ ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ መዳበር መቻል አለበት፡፡ መንግስትኮ ከማኅበረሰቡ የሚመነጭ አንድ አካል እንጂ ከሌላ ፕላኔት የሚመጣ አይደለም፡፡ የመንግስትም ይሁን የግል ጋዜጠኞች ከማኅበረሰባችን የወጡ ናቸው፡፡ መሰረቷ እውነት በሆነችው ቤተ-ክርስቲያን ስም በሚታተሙ አንዳንድ ጋዜጦች እንኳ ሳይቀር እውነቱና ሐሰቱ ተደበላልቆ ለህዝብ የሚቀርብበት ሁኔታ አለ፡፡ እርግጥ ነው በጣም ጥቂት ቢሆኑም ለአውነትና ለእውነት የቆሙ ጋዜጠኞችና ጸሐፊዎች ይኖራሉ፡፡ በአብዛኛው ግን እውነታውን ከማንጠር ይልቅ ጥላቻን የሚያንጸባርቅና እኔ ብቻ ትክክል የሚል ጭፍን አቋም የሚንጸባረቅበት፤ ለእውነት ሳይሆን በማጭበርበር ደጋፊ የሚሰበሰብበት ሥርአት ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ጋዜጠኞችም በዚህ ማዕበል ውስጥ የሰጠሙ ይመስለኛል፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የመንግስትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ሚዘናዊ መረጃ ለህዝቡ ያቀርባሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለምሳሌ የመንግስት ጋዜጣ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፖለቲካ አምድ ላይ የሚቀርበውን ጽሑፍ ሳነብ አንድም የሚገነባ ነገር አላገኝበትም፡፡ በጋዜጣው ላይ የሚወጡት የውጭ ዘገባዎች ምናልባት እውነት ላይ ሊያመዝኑ ይችላሉ፡፡ እነሱም ቢሆኑ ከቢቢሲና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ዜናዎች ቀጥታ የተቀዱ ናቸው፡፡ የመንግስትን ድክመቶች በግልጽ በማስቀመጥ ለህዝብ የሚያሳውቅ ጽሑፍ ሲቀርብ አይታይበትም፡፡ በአጠቃላይ አብዛኞች የመንግስት ጋዜጦች ሚዛናዊ መረጃ አያቀርቡም ማለት ይቻላል፡፡ የመንግስት ጋዜጦች በመንግስት በጀት ስለሚገዙ የገበያ ስጋት የለባቸውም፡፡ እነዚህ ጋዜጦች ህዝቡ የሚፈልገው መረጃ ደረሰ አልደረሰ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ቴሌቪዥኑም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
የግል ጋዜጦችም ቢሆኑ የመንግስት ግልባጭ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የግል ጋዜጦች አሉታዊ ወሬ ላይ እንጅ ለሀገር የሚጠቅምና የሚገነባ መረጃ ሲያቀርቡ አይታይም፡፡ መንግስት ያከናወናቸውን በጎ ሥራዎች ጥላሸት የሚቀቡና ከብርሃን ይልቅ ጨለማ የሚታያቸው ጋዜጠኞች የሚስተናገድበት ነው፡፡ ታሰረ የሚለውን እንጅ ተፈታ የሚለውን መስማት የማይፈልጉ ጋዜጦች ብዙ ናቸው፡፡ ህዝቡ ሁሉ ቢታሰር ደስታቸው ወደር ያለው አይመስለኝም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠፉት የታሰረ፣ የሞተ፣ የተደበደበ፣ የቆሰለ፣ ወዘተ ሰው ፍለጋ እንጅ ራሱን በሥራ የለወጠና ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ያከናወነ ሰው ፍለጋ አይደክሙም፡፡ ይህ የእነርሱ ጉዳይ አይመስላቸውም፤ የመንግስት እንጅ፡፡ እነሱ የሚታያቸው እውነት ሳይሆን ገንዘብ ነው፡፡ ወዳጄ ኤፍሬምም ብትሆን በአብዛኛው የመንግስትን ክፍተቶች እንጅ መቀጠል ያለባቸውን መልካም ጎኖች ስታንጸባርቅ አላየሁም፡፡ ሚዛናዊ መረጃ ማቅረብ የሚጀምረው ከራስ ነው፡፡ እኛ የማናደርገውን ሌላ እንዲያደርገው መጠበቅ የለብንም፡፡ በአጠቃላይ የተዛባ አመለካከት መያዝ ሚዛናዊ መረጃ ለህዝቡ በማድረስ ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፡፡

desalew said...

Nice article!! Eigih yibarek ababa !

Seme said...

Good point, logical and to the point. We really need fact checkers starting from private life to public life(government). We also need to all other institutions we have wether religious or secular institutions. That is a key factor in societal development and peace

Anonymous said...

ይህቺን ጽሑፍ ብቻ በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት በድጋሚ ብትታተም በተገባ ነበር::
ትምህርት ሰጭነቶ እጅግ የጎላ ስለሆነ ማለት ነው፨ እንዲያውም CC ሁሉ ያስፈልጋት ነበር
Demissie