Monday, November 26, 2012

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 2012 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ልክ እንደ ዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ “ልብ አንጠልጣይ” ሆኖ አለፈ። ከአንድ ዓመት በላይ ሲካሄድ የነበረው “የምረጡኝ ዘመቻ”ም ዕልባት አገኘ። ግማሽ አሜሪካ (50%) ፕሬዚዳንት ኦባማን በድጋሚ መረጠች። ግማሽ አሜሪካ (48%) ደግሞ ሚት ራምኒ እንዲመራት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ። በቃላት ሲጠዛጠዙ የከረሙት ተወዳዳሪዎችም በመጨረሻ ተመሰጋገኑ። ራምኒም ለኦባማ መልካም ዕድል ተመኙ። እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ሊጸልዩም ቃል ገቡ።

ዳሰሳ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የአንድ አገር መሪ ሳይሆን የዓለም መሪ እንደመምረጥ ያለ አጓጊ ትዕይንት ነው። ዕለተ ማክሰኞ ኖቬምበር 6/2012 በአሜሪካውያን ዘንድ በጉጉት እንደመጠበቁ በሌሎች አገሮች ዜጎችም ዘንድ በአትኩሮት ሲታይ ነበር። አሜሪካውያንና በአሜሪካ የምንኖር ሌሎች ዜጎች “ማን ይመረጥ ይሆን?” በሚለው ጥያቄ ስንጠበብና ስንጨነቅ እንደዋልነው ሁሉ በሌሎች ዓለማት ያሉ ዜጎችም እንዲሁ ሲጠበቡ እንደዋሉ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።

ከአውሮፓ እስከ ሩቅ ምሥራቅ፣ ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ሁሉም እንደየ አጀንዳው እና ፍላጎቱ የምርጫውን ውጤት በጉጉት ሲጠብቅ ቆይቷል። በርግጥ የዓለም ሕዝብ ለአሜሪካ መሪ እንዲመር ዕድል ቢያገኝ ያለ ምንም ጥርጥር ሰፊውን ድምጽ የሚያገኘው የዲሞክራቲክ ፓርቲው ተወዳዳሪ ነው። በአሁኑ - ኦባማ- ማለት ነው።

ሪፐብሊካን መሪዎች አውሮፓ ብዙም አይጥሟትም። የሪፐብሊካኖች አጠቃላይ የፖለቲካ ፍልስፍናም እንዲሁ። ለዜጎች ኃዘኔታ የለውም የሚሉት የሪፐብሊካን “ብላ-ተባላ” ኢኮኖሚ መርሖ “ዜጎችን በመደጎም” ላይ ለተመሠረተው እና ከሀብታሞች ላይ ከፍ ያለ ታክስ ለሚጥለው የአውሮፓ ፍልስፍና ባዕድ ነው። ከዚያ ይልቅ ዲሞክራቲክ ፓርቲ የሚያራምደው ፖለቲካ ለአውሮፓ ይቀርባታል። በዚህ የሁለቱ ፓርቲዎች ፍልስፍና ምክንያት አውሮፓውያን ከሪፐብሊካኖች ይልቅ ዲሞክራቶችን ሲደግፉ ኖረዋል። ከራምኒ/ቡሽ ይልቅ ኦባማ/ክሊንተንን ይመርጣሉ።

ሪፐብሊካን-አሜሪካውያን ኦባማንና ፓርቲውን ይከሱ የነበሩት “አገራችንን እንደ አውሮፓውያን የመጦሪያ ኢኮኖሚ” ወይም ሶሻሊስት ሊያደርገው ነው እያሉ ነው። በራሳቸው ጥረት ጥሪት ካፈሩ ሀብታሞች ላይ በመዝረፍ “ለሰነፍ ድሆች” ለማከፋፈል ይፈልጋል ሲሉ ከርመዋል። ሪፐብሊካን-አሜሪካውያን የአውሮፓን “ዌልፌር ሲስተም” አጥብቀው ይኮንናሉ። የበረታ ሀብት ያካብት፣ ያልቻለ “እንደ ፍጥርጥሩ” ዓይነት ጨከን ያለ ፍልስፍና ይከተላሉ። ይህንንም አሜሪካን ለዚህ ኃያልነት ያበቃት” ነው ባዮች ናቸው።

ሪፐብሊካውያን ሥራ ለሌላቸው ድጎማን፣ ለአረጋውያን ቀላል ሕክምናን፣ ለተማሪዎች በትንሽ ብድር መማርን፣ ለውጪ ዜጎች (ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ ለገቡትና ለሚገቡት) ዕድል መስጠትን አበክረው ይቃወማሉ። አገራችንን የሰነፎች፣ የውጪ ዜጎችና የሶሻሊስት አስተሳሰቦች መናኸሪ ያደርጋል ባይ ናቸው። ዲሞክራቶች ከዚህ ይለያሉ።

ዲሞክራቶች ሥራ ለሌላቸው ድጎማን፣ ለአረጋውያን ቀላል ሕክምናን፣ ለተማሪዎች በትንሽ ብድር መማርን፣ ለውጪ ዜጎች (ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ ለገቡትና ለሚገቡት) ዕድል መስጠትን ጨምሮ ለግብረ ሰዶማያውያን መብት በመከራከራቸው ይታወቃሉ። በዚህም ምክንያት እምነታቸውን ጠበቅ በሚያደርጉ እና የውጪ ዜጎችን በአገራቸው መርመስመስ በዓይናቸው እንትን ለሚመለከቱ ሰዎች አይስማሙም። ሀብታሞችም በገቢያቸው ላይ ጫን ያለ ታክስ መጣሉን አይሹትም።

እስያውያን እና አፍሪካውያን በየአገሮቻቸው ያለውን ዓምባገነናዊ  አስተዳደር በመጠኑ ሊገዳደርላቸው የሚችል መሪ ፍለጋ ሲባክኑ ኖረዋል። ሪፐብሊካኖች “የራሳቸውን ጥቅም አሳዳጆች” ተደርገው ስለተሳሉ የተሻለ ነገር የሚጠብቁት ከዲሞክራቶች ነው። የቻይናን ኢኮኖሚ ያሳደጉት የአሜሪካ ኩባንያዎች በአገራቸው ያለውን ፋብሪካ እየዘጉ በቻይና የሚከፍቱት እና በዚህም በታክስ ገቢ የሚበለጽጉት ለቻይናውያን ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደማይቆሙ ያውቁታል። እነዚህ ባለጸጎች ደግሞ የሪፐብሊካን ፓርቲን ፍልስፍና የሚደግፉ ናቸው። እስያውያን ይህንን ያውቃሉ።

በአፍሪካም ቢሆን ያው ነው። ኦባማ አፍሪካዊ ዝርያ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን ከእምነታቸውም በመነሣት “ይረናል” የሚል ልቅ ግምት ነበር። ነገር ግን እንደተጠበቀው ሳሆን ሲቀር ከእናት አገራቸው ከኬንያ ጀምሮ ብዙው አፍሪካዊ አፍንጫውን ነፍቶባቸዋል፣ ፊቱን አዙሮባቸዋል። ነገር ግን ራምኒ ከሚመረ ኦባማ ቢቀመ ይሻሉ። ደስታቸውም ከዚህ የመነጨ ነው።

ኢትዮጵያውያን-አሜሪካውያን፣ ልክ እንደ ሁሉም አፍሪካዊ ሁሉ፣ በኦባማ ትልቅ ተስፋ ነበራቸው። ተስፋው ኦባማ በአሜሪካ በሚሠሩት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የኢትዮጵያውያንን ድምጽ ይሰማሉ ከሚል የመነጨ ነበር። ይሁን እንጂ ኦባማ ይህንን አላደረጉም። እንዲያውም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት እየጠነከረ በመሔዱ ብዙ ኢትዮጵያውያን በእጅጉ ከፍቷቸዋል። (ሱዛን ራይስ በአቶ መለስ ቀብር ላይ ያደረጉት ንግግር ኢትዮጵያውያን በኦባማ ላይ ለያዙት ቁርሾ ማጠናከሪያ ሆነ።) በዚህ ዙሪያ የተደረጉ የተለያዩ ውይይቶች ላይ እንደተገለጸው ኢትዮጵያውያን-አሜሪካውያን ኦባማን በድምጻቸው ለመቅጣት አልፈለጉም። ከራምኒ ኦባማ ይሻሏቸዋል

ማክሰኞ ዕለት፣ ቴሌቪዥን ፊት ለፊት ተቀምጠን የምርጫውን ቁጥር ስንከታተል አንድም በጉጉት ስጠብቀው የነበረው የቨርጂኒያ ውጤት ነበር። ቨርጂኒያ እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው ግዛቶች አንዱና ዋነኛው ሲሆን ቆጠራው እንደተጀመረ ራምኒ ኦባማን መምራት ሲጀምሩ “ኢትዮጵያውያኑ በርግ ኦባማን አልመረጡም ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ አጭሮብኝ ነበር።

ዘግየት ብሎ፣ ብዙ የውጪ ዜጎች ይኖሩባቸዋል የሚባሉት የቨርጂኒያ ክፍለ ከተማዎች እና አውራጃዎች ድምጽ መግባት ሲጀም ኦባማ አንሠራሩ። ከዚያም አሸነፉ። በርግጥም ትውልደ-ዳያስጶራ የሆነው አብዛኛው አሜሪካዊ በኦባማ ቢከፋም ራምኒን እንዳልመረጠ ገባኝ። ኢትዮጵያውያንም አሜሪካ ከኢሕአዴግ መንግሥት ጋር የወደቀችው የቀለጠ ፍቅር ቢያንገበግባቸውም “መቸስ ምን ይደረግ?” በሚል መልኩ ድምጻቸውን ለኦባማ ሰጥተዋል።   

በርግጥ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን ለመስጠት አልሰነፉም። አይሰንፉምም። ብዙዎቹ በአገራቸው ይህንን የመሰለ ሥርዓት ባለመኖሩ የሚቆጩ እንደመሆናቸው አሜሪካዊ ዜግነት” ካገኙ በኋላ መምረን በአክብሮት ይመለከቱታል። አንድ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ የተባሉ የፌስቡክ ወዳጄ የምርጫው ዕለት (በ11/6/2012) “ድምጼ” በምትለው ግጥማቸው እንዳሉት ማለት ነው።
ዛሬ ተረዳሁ[]፤ ድም ዋጋ እንዳላት።
ከሀገሬ ስወጣ ወንዙን ሳሻግራት
ይህንኑ ነበር የተመኘሁላት

እንግዲህ የኦባማ ሁለተኛ-ዙር ፕሬዝዳንትነት ለኢትዮጵያውያን የተለየ ነገር እንደማያመጣ ቢታወቅም ለአሜሪካውያን ግን የተሻለ የኢኮኖሚ እና የሥራ ፈጠራ ዘመን እንደሚሆን በጉጉት እየተጠበቀ ነው። ኢትዮጵያውያንም በአሜሪካ ዜግነት እና በአሜሪካ ምርጫ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለየ ለውጥ ለማምጣት ድምጻቸውን እንዳልሰጡ ከተረዱት ዘንዳ እውነታውን እየመረራቸውም ለመቀበል ይገደዳሉ። ከኬንያዊ አባት የተገኙት ኦባማ ለአባታቸው ጎረቤት አገር የተለየ ውለታ እንማይውሉ ግልጽ ነው። ለኢትዮጵያ ለውጡን የሚያመጡት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው ።

ወደ ቀደመው የምርጫ ሁኔታ ስንመለስ፣ ኦባማ የ2012 ምርጫን ለማሸነፍ በብርቱ የረዷቸው ሴቶችና ወጣቶች መሆናቸውን እናገኛለን። ድምጻቸውን ከሰጡ ሴቶች መካከል 55% ኦባማን ሲመርጡ 44% ብቻ ራምኒን ደግፈዋል። ዕድሜያቸው ከ18-29 ዓመት ከሆኑት መራጮች 60% ኦባማን፣ 37% ራምኒን መርጠዋል። ወንዶች እና በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አሜሪካውያን አብዛኛ ድምጻቸውን የሰጡት ለራምኒ ነው።

ከወጣቶችና ሴቶች ድምጽ ጋር የትውልደ-ዳያስጶራው ድምጽ ሲካተት ኦባማ አሸናፊ ሆነው ወደ ኋይት ሐውስ እንዲመለሱ አስችሏቸዋል። ከትውልደ-ዳያስጶራ መካከል እጅግ ትልቁን ቁጥር የሚይዙት “ላቲኖዎች” (ስፓኒሽ ተናጋሪ አገሮች ዜጎች) በወሳኝ መልኩ ለኦባማ ድምጻቸውን ሰጥተዋል። እንዲያ ባይሆን ኖሮ፣ የወንዶቹን እና አብዛኛውን ነጭ አሜሪካዊ ድምጽ ያገኙት ራምኒ በቀላሉ ያሸንፉ ነበር። ከነጭ-ወንድ-አሜሪካውያን ይሁንታ ያላገኙት ኦባማ ፕሬዚዳንት ለመሆናቸው ባለውለታዎቻቸውን እንደማይዘነጉ፣ ለነርሱም ጥቅም እንደሚቆሙ ይጠበቃል።

ትውስታ

ይህንን የምርጫ ዕለት የቀጥታ ሥርጭት ልክ እንደ እግር ኳስ ውድድር ጫጫታ እና ከተቻለም የድጋፍ ዘፈን ካለበት ቦታ ሆኜ ለመከታተል ነበር ያቀድኩት። እናም ወደ አንዱ “የስፖርት ባር” ገብተን በአዳራሹ ከተገጠገጡት ብዙ ቴሌቪዥኖች መካከል ዋኛውና ትልቁ ከተዘረጋበት ፊት ለፊት ተቀመጥን። “ሻይ ቡናችንን” (መቸም ይገባችኋል) እየወሳሰድን ተከታተልን። የመጨረሻው “የሲ.ኤን.ኤን ፕሮጄክሽን” እስከታየባት ደቂቃ ድረስ ኦባማ ለማሸነፋቸው ምንም እርግጠኛ አልነበርኩም። ኦባማ እንዳሸነፉ ሲታወጅ እንዴት ሆኜ ከመቀመጫዬ እንደተነሣኹ አላውቀውም። እጃችንን በጭብጨባ አቅልጠን፣ ትከሻ ለትከሻ ተገጫጭተን፣ ሰከን ሲልልን ቁጭ አልን። በእውነቱ የዓለም ዋንጫ ያሸነፍን እንጂ ፕሬዚዳንት ሲመረጥ ያየን አይመስልም ነበር።

ትዝብት

የአሜሪካ የምርጫ ሥርዓት በብዙ ምስቅልቅሎች የተሞላ መሆኑ ብዙዎችን እያስገረመ ነው። አውሮፓውያን በቀላሉ የሚያከናውኑት ምርጫ አሜሪካ ላይ እጅግ በጣም ውስብስብ፣ አዳጋች፣ አሰልቺ እና ጊዜና ገንዘብ አባካኝ መሆኑን ሁሉም ይስማማበታል። ምናልባትም ሌሎች ጨቋኝ መንግሥታት ይህንን በምሳሌነት እየጠቀሱ የአገራቸውን ሕዝብ እንዳይበድሉበት ሥጋት አለኝ። “ምን ታማርራላችሁ በአሜሪካ የነበረውን ችግር አላያችሁም?” ማለታቸው አይቀርም። ኦባማም በንግግራቸው መግቢያ ላይ “ይህንን ነገር ማስተካከል አለብን” ብለው በጨረፍታ መናገራቸውን አስታውሱ። አሜሪካውያኑ ድምጽ ለመስጠት ከአራት ሰዓታት በላይ ለመሰለፍ ተገደዋል።

ሌላው ትዝብቴ አሜሪካውያን፣ በተለይም በየገጠሩ የሚኖሩት እና ዕድሜያቸው የገፋው፣ እንዴት ያለ የመረጃ እጥረት እንዳለባቸው ማየቴ ነው። ይህ ሁሉ የመረጃ ዝናም እየዘነመ ምንም የማያረጥባቸው፣ “ኦባማ አሜሪካዊ አይደሉም፣ ሙስሊም ናቸው፣ ሶሻሊስት ናቸው፣ አገራችንን ሊያጠፉ የተላኩ ናቸው” ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው። ይልቁንም “ለ47%ቱ ደሃ አሜሪካዊ አልጨነቅም፣ ዋናው 1% ሀብታሙ ነው” የሚሉትን ባለጸጋ ባለ ሁለት ምላስ ተወዳዳሪ ለመምረጥ መንገታገታቸው እጅጉን አስገርሞኛል። “እንዴት ያለ አገር ነው?” አሰኝቶኛል። የሆነው ሆኖ፣ የማታ ማታ፣ ኦባማ 50%፣ ራምኒ 48% አግኝተዋል፤ ኦባማም በድጋሚ ተመርጠዋል።

ክቡር ፕሬዲደንት ኦባማ “እግዚአብሔር ይርዳዎ”፤ መልካም ዘመን ይሁንልዎ። ቀጣዩ አራት ዓመት እንደከዚህ በፊቱ በአንድ አጀንዳ ላይ ሁለት ዓመት የማያጠፉበት፣ በየዓለም ዳሩ ያሉ ዲክቴተሮችን የማያቀማጥሉበት፣ ለአፍሪካ ትንሽ ዕድል የሚሰጡበት፣ ከቀረዎት ጥቂት ጥቁር ጸጉር ላይ ትንሹን የሚያተርፉበት ጊዜ እንዲሆንሎት እመኛለዅ። ትልቁ ምኞቴ ግን እንዲህ ያለ ሥርዓት በአገሬ በኢትዮጵያ ላይ ማየት ነው።

ይቆየን - ያቆየን።

 

1 comment:

ቁጭቱ said...

ይህችን ጽሑፍህን ሳነባት ትንሽ ፈገግ አልሁ። አንተም እንዳልከው የእግር ኳስ ደጋፊዎች ስለየሚደግፏቸው ቡድኖች የሚሰጡትን ማበራሪያ ነው የሚመስለው። እኔም ስለቡድኔ በመናገር እንዳላስቅህ ሰጋሁ። በዚህ ዘመን ሁለቱ ፓርቲዎች መከከል ያለው ልዩነት ለደሆች ከመቆምና በደሆች ላይ 'ከመጨከን' ጋር እየተያያዘ መቅረቡ በራሱ ፖለቲካዊ ነው። ለማንኛውም ነገሩን ከምር ብንመለከተው የፖለቲካ ነገር በየትኛውም(ዘመን እና ሀገር) ግለሰቦች የሚፈልጉትን በመንገርና ስሜታቸውን በመኮርኮር ላይ ያተኮረ አስጠሊታ ጫዋታ መሆኑን ነው፡፡

ለእኔ እጅጉን የሚያሳስበኝ (በተለይም ከኢትዮጵያዊያን አንጻ) ስሜታችንን ተከትለን ስንሄድ የሚጫኑብን የሊበራሊዝም አመለካከቶች በሃየማኖታዊና ማኅበረሰባዊ አመለካከታችን ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ነው። በዚህ በኩል ከስሜት በጸዳ ሁኔታ ወገኖቻችንን የምንጠቅምበት ሥራ መስራት ቢቻል የተሻለ ይሆናል የሚል አመለካከት አለኝ።

Simply out, Republicans believe that less government is better government. They believe, as corollaries to this seminal idea that people should keep and decide how to spend their own money rather than turning it over to the Government as taxes and that private industry should be deregulated. They believe that left to their own devices, they will do the right thing. They will make money and this money will 'trickle down' and create both good jobs and overall prosperity in our land.

The Democrats, on the other hand, believe that business needs to be regulated by government. They believe this because they don't think it likely that proprietary business, by definition, will appropriately self-regulate in a way that will benefit the populace at large. Democrats believe that greed destroys and that deregulation invites and nurtures it. Therefore, they feel that more money paid in taxes will allow the Government to provide for the needs of people and take care of the things in society that seem to need taking care of - like regulating big business.

http://voices.yahoo.com/the-real-difference-between-republicans-democrats-11067018.html?cat=9