Wednesday, November 7, 2012

አንድ ማስታወሻ ለጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ (መስፍን ነጋሽ/ለ - adebabay.com/ PDF)፦ በእኔ እድሜ የደምሴን ያህል አገራዊ የስፖርት ስሜትን፣ በተለይ እግር ኳስን ወደ ልባችን ያቀረበ ጋዜጠኛ አልነበረም። እንደዛሬው ኢንተርኔት መገልበጥ ማእረግ በማያሰጥበት ዘመን። በሳምንት ሁለትና ሦስት ቀን ስታዲየም በምገባበት፣ ሁለቱን ሙሉጌታዎች፣ እነሚሊዮን በጋሻውን፣ እነቸርኬን (ጊዮርጊስ) እነሙሉዓለም እጅጉን (ጦሩ) እነአብዲን (ድን) እነአፈወርቅን (እርሻ) ደሞ የአየር ኀይሉ አጥቂ ማን ነበር? ... ረሳሁት ማለት ነው? (ይልቅ ተከላካያቸው መሰለ፣ ጆን ቴሪን ቁጭ ነበር) ከዛ ደሞ ... ይህ ሁሉ ሲሆን ብቸኛው የስፖርት መረጃ ምንጫችን ደምሴ ነበር፤ እርግጥ ሌሎችም ጋዜጠኞች ነበሩ በተለይ እነ ... ማነው ... ይንበርበሩ መሰለኝ። ቢሆንም ደምሴ የተለየ መስህብ ነበረው።

ከሁሉም የማልረሳው የደምሴ ገጠመኝ 1980 የምስራቅና መከካለኛው አፍሪካን ዋንጫን ያሸንፍን (የበላን) ጊዜ የሆነው ነው። ብዙ ሰው የሚያስታውሰው ጨዋታው በፍጹም ቅጣት ምት ማለቁንና ዳኛቸው ደምሴ (ደምሴ "ዳኙ" እያለ ያቆላመጠው፣ አመለ ሸጋው ተጫዋች) የመጨረሻውን ምት አስቆጥሮ ማሸነፋችንን ነው። ለፍጹም ቅጣት ምት የደረስነው ግን 1 0 ስንመራ ቆይተን ባለቀ ሰዓት ባገባነው ጎል ነበር። ታዲያ ብዙ ተመልካች በመበሳጨቱ ጨዋታው ሳይጠናቀቅ መውጣት ጀምሮ ነበር። ለዋንጫ መድረሳችን የፈጠረው ስሜት ከመናሩ የተነሣ፣ በገዛ ሜዳችን ሌላ ሲሸለም አናይም ብለው ነው። ቀኑ ገብርኤል ነበር፤ ብዙ ሰው ተስሎ እንደነበርም አስታውሳለሁ። 

እኔ መጨረሻውን ሳናይ አንሄድም ካሉት ወገን ሆኜ ቆየሁ፤ ጥቂት ጓደኞቼ ግን ለመውጣት ጉዞ ጀመሩ፤ አንዳንዶቹም ከወጡ ቆዩ። በመጨረሻ (በትክክል አስታውሼው ከሆነ) "ሙሉዓለም ያሻማትን፣ /መድኅን ኀይሌ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አዋሃዳት" የምትለዋ ዝነኛዋ የደምሴ የምስራች መጣች። መቼም በዚያ ደቂቃ በስታዲየሙ የተሰማውን ድምጽ መቼም አልረሳውም፤ እስከዛሬም አቻ ወይም መግለጫ አላገኘሁለትም። "ተመልካቹ ጮኸ" ማለት ተርታ ንግግር ነው፤ ቋንቋ ከስሜት ጠቦ የሚገኝበት። 

ለማንኛውም ጎሉ ገብቶ፣ እኩል ሆነን፣ ለፍጹም ቅጣት ምት በቅተን፣ አሸነፍን። መንጌም ደስ ብሏቸው ዋንጫውን ለአገራቸው ልጆች ሰጡ፤ የተሸናፊዎቹ "አባት" አገር በኋላ መጠጊያ እንደሚሰጡዋቸው እንዴት ይጠርጥሩ። (እኛ ሰፍር ስታዲየም ሊሰራ ቃል የተገባውም ያን ጊዜ ነበር መሰለኝ።) ታዲያ ጨዋታው ሳያልቅ የወጣው አንዱ የት/ቤት ጓደኛችን ጎሉን የሰማው ታክሲ ውስጥ እንደገባ ኖሯል። ግን በደንብ አልሰማም። ከዚያ "የውይይቱን" ወያላ ይጠይቀዋል፤ "ማን አገባ በናትህ?" ወያላው መለሰ "ደምሴ ዳምጤ" እሱ /መድኅንን የት ያውቀዋል፤ ደምሴ ዳምጤን እንጂ።
60 ዓመት መሞት እኩለ ቀን አለፍ እንዳለ እንደመሞት ነው። እርግጥ ደምሴ አመሻሽ ላይ 90 ቢሞትም ኖሮ ማዘናችን አይቀርም ነበር። ለማንኛውም፣ ድሃዋ አገር ከሰጠችው ያላነሰ፣ መልሶ ሰጥቷት ስለሞተ ሕይወቱ የባከነ አልነበረም።
ደምሴ፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን እንደጦር በሚፈሩ ሁለቱ አምባገነኖች ዘመን በስፖርት ጋዜጠኝነት ሰርቷል። ምን አጋጥሞት ይሆን? የጫረው ነገር ይኖር ይሆን? ደምሴ ያቺ የገ/መድኅን ጎል ምንጊዜም ያንተ መዘከሪያ ናት፤ የታክሲ ረዳቱ ያጸደቀልህን ጎል አጽድቄ አስታውሳለሁ፤ ከልጅነት የኳስና የስታዲየም ጓደኞቼ ጋራ

 

 

6 comments:

Anonymous said...

Wendim Ephrem;
metsnanatin lantem le igir kuwas afqari leityopya hizibm imegnalehu.
Ine yedemise gib bicha sayhon ye beregnew ye Tekabe Zewde mengomalel new iskahun be ayane yemimelalesew.
Ye Kanadaw wedajih

Anonymous said...

...Quasuan yashamaw Amanuel neber.Destachen Asmera yegeletnew ye welajochu bet bemehed neber..yemayresa tarikawi elet neber.

Anonymous said...

አንድ ማረሚያ ብቻ፡ ኳሱን ያቀበለው ሙሉጌታ የቡናው ነው። ጎሉን በጭንቅላት ያገባው ሙሉጌታ የጊዮርጊሱ ነው። ጎሉ ግን እንዳልከው ለብዙዎቻችን የደምሴ ዳምጤ ነው።

The Architect said...

መስፍኔ አንጀቴን አራስከው፡፡ ትዝ ይልህ እንደሆነ የዛን እለት ምሽት የከተማ አውቶቡሶች በነጻ ከተማዋን ነዋሪዎች ሲያሳፍሩ ነበር፡፡ (ዋጋው 15 ሳንቲም መሆኑንም ሳልዘነጋ) ታዲያ ምድሪቱ ጠብባን ባንዲራ ለብሰን፣ ባንዲራ ጎርሰን፣ ባነዲራ ሆነን (የዛኔው ባንዲራችን መሃሉ ላይ አንባሻ አልነበረውም) ስንቦርቅ !... የዚህን ሁሉ ፈንጠዚያ አብሳሪ ደምሴን የእኔ ትውልድ እንዴት ሊረሳው ይችላል! ወይኔ ወይኔ.. ወይኔ… ዳኙ…. እነኳንም ያኔ ኖርን !መስፍኔ አንጀቴን አራስከው፡፡ ትዝ ይልህ እንደሆነ የዛን እለት ምሽት የከተማ አውቶቡሶች በነጻ ከተማዋን ነዋሪዎች ሲያሳፍሩ ነበር፡፡ (ዋጋው 15 ሳንቲም መሆኑንም ሳልዘነጋ) ታዲያ ምድሪቱ ጠብባን ባንዲራ ለብሰን፣ ባንዲራ ጎርሰን፣ ባነዲራ ሆነን (የዛኔው ባንዲራችን መሃሉ ላይ አንባሻ አልነበረውም) ስንቦርቅ !... የዚህን ሁሉ ፈንጠዚያ አብሳሪ ደምሴን የእኔ ትውልድ እንዴት ሊረሳው ይችላል! ወይኔ ወይኔ.. ወይኔ… ዳኙ…. እነኳንም ያኔ ኖርን !

ምስጋናው said...

በየ እግር ኳስ ሜዳው ሩጣ ስትሰለች
የዳምሴ ነፍሱ እረፍትን ጠየቀች
የእስፖርት ዜና አፍቃሪ በይ ደህና ሰንብች::

Anonymous said...

CORRECTION-2

THAT DAY WAS NOT ST.GABREAL'S FEAST BUT ONE DAY BEFORE THE FEAST. 18TH OF TAHISAS1980E.C