Monday, November 26, 2012

እናት ተፈጥሮ ስትቆጣ(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ “ሒዩሪኬን/Hurricane ሳንዲ” ጉዳችንን አፈላችው እኮ ጃል ሦስት ቀን በቤታችን ተዘግተን ከረምን። መውጣት የለ፤ መግባት የለ። ጥርቅምቅም ሆነ ነገሩ ሁሉ። በመስኮታችን ወደ ውጪ ስንመለከት ያለው የንፋስ ሽውታ እና የዝናብ ውሽንፍር ወደ ሲዖል መሔጃ መንገድ እንጂ የሰፈራችን ደጃፍ አይመስልም።

 

የቃላት እና ስያሜዎች ትርጓሜ

 Hurricane የሚለውን ቃል ለመተርጎም ፍቺ እንዲሰጠኝ የተመለከትኩት የዎልፍ ሌስላው “እንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት” እንዲያው በደፈናው “ዓውሎ ነፋስ” ይለዋል። ፈረንጆቹ ደግሞ ሒዩሪኬን ማለት ከውቅያኖስ የሚነሣ ንፋስ፣ ዝናብ እና መብረቅ የቀላቀለ በሰዓት ከ119 ኪሎ ሜትር በላይ ፍጥነት ያለው ጠንካራ፣ የሚሽከረከር ዓውሎ ነፋስ ነው” ብለውት አንብቤያለኹ። ንፋሱ ዝም ብሎ የሚነፍስ ሳይሆን ክብ እየሠራ (ድሮ ሰይጣን የምንለው የመንደራችንን አቧራ የሚያሽከረክር ነፋስ ትዝ አለኝ) ሰፊ አካባቢን ሸፍኖ የሚነጉድ ነው።

ከኢትዮጵያ ለምንመጣ ሰዎች በዚህ በምዕራቡ ዓለም ያለው “እብድ አየር” ምንነት እና ትርጉም ቶሎ አይረዳንም። ለምን ብሎ ለሚጠይቀኝ መልስ አለኝ። ለምሳሌ በዚህ በምንኖርበት አገር “ቅዝቃዜ” ሲባል “በኢትዮጵያ ቅዝቃዜ” አይተረጎምም። ሙቀትም ሲባል “በአዲስ አበባ ሙቀት” አይተረጎምም። ቃላት ተመሳሳይ ይሁኑ እንጂ ዝርዝራቸው እና መጠናቸው የትየለሌ ነው።

ስለዚህ ከአገር ቤት ወደ አሜሪካ የሚመጣ ሰው እልም ባለው ቀዝቃዛ አየር ኮትና ሱሪ አድርጎ፣ ያቺን አፍንጫዋ ቀጭን የሆነ አዲስ አበባ ዘናጭ ጫማ ተጫምቶ፣ ምናልባት አንገቱ ላይ አንዲት ስካርፕ ነገር ጣል አድርጎ ልታዩት ትችላላችሁ። ብርድ ስለተባለ “ስካርፕ” ጣል አድርጓል፣ ምናልባት ከውስጥ አንድ ሹራብ ደርቧል። ታዲያ፤ ብርዱ እስኪቆነድደው ትርጉም እንዳልገባው ግልጽ ነው። ሁለት ቀን ሲቆይ የጨርቅ ሱሪውም፣ ሹል ጫማውም መቀየሩ የግድ ነው። (ግን ለምንድነው የአዲስ አበባ ሰው ሹል ጫማ የሚወደው?)

“ጉንፋን” የሚለው ቃልም አንዱ ትክክለኛ ትርጉም የማይሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለኹ። ኢትዮጵያ ሆኜ “ጉንፋን ያዘኝ” ስል የነበርኩት አሁን እዚህ አሜሪካ መጥቼ “ጉንፋን ያዘኝ” ከምለው የተለየ ነው። ዝርዝሩን ለሐኪሞቹ ትቼ በማይም ትርጉም ያለውን ለማብራራት ነው የምሞክረው። የኢትዮጵያው ጉንፋን በሻይ፣ በሻይ ኮረንቲ፣ ሎሚ በሻይ በማድረግ ቶሎ ይጠፋል። የዚህ አገሩ ደግሞ አንድ ሳምንት የሚያስተኛ፣ ሆስፒታል የሚያስገባ ብሎም ለሞት የሚያደርስ ሲሆን ቃሉ ብቻውን በትክክል ሐሳባችንን እንደማይዝ እረዳለኹ።

ሒዩሩኬንና ዓይነቶቹ
ሒዩሪኬን መታን ስል በአማርኛ “ዓውሎ ነፋስ ነፈሰብን” ከሚለው ጋር በሐሳብም በይዘትም አንድ እንዳልሆነ ለማስረዳት የፈለግኹት ግልጽ ነው ብዬ አምናለኹ። ሑዩሪኬኖች በሙሉ አንድ ዓይነት አይደሉም። ደረጃ ደረጃ አላቸው። ደረጃ አንድ ሒዩሪኬን ብሎ ይጀምርና እስከ አምስት ይዘልቃል። ደረጃ አንድ አነስተኛው ሲሆን ደረጃ አምስት ሒዩሪኬን ደግሞ ከፍተኛው ነው። ደረጃ አንድ ሒዩሪኬን ትንሽ ነው ሲባል ግን ጥፋቱ ትንሽ ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም አንዳንዴ ትልቅ ከሚባለው ይልቅ ትንሽ የሚባለው የበለጠ ጉዳት የሚያደርስበት ጊዜ ይኖራል። ለምን ቢባል ሒዩሪኬኑ እየተሽከረከረ በሚጓዝበት ወቅት በመንገዱ ላይ እንደሚያገኘው ነገር ይወሰናል። ትንሽ ሆኖ በመንገዱ ከተማ ሊያጋጥመው ይችላል፤ ትልቅ ሆኖ ከሰው መኖሪያ ርቆ በማለፍ ጉዳት ላያስከትል ይችላል።

የሒዩሪኬኖች ስያሜ
ሒዩሪኬኖች ስያሜ ስያሜ አላቸው። ሰሞኑን መከራችንን ያበላችን ሱፐር-ሒዩሪኬን “ሳንዲ” ናት። በየጊዜው የሚነሱት በሙሉ የየራሳቸው ስያሜ አላቸው። ስያሜ የሚሰጣቸው ሀ ብለው ከተጠነሰሱበት ጊዜ ጀምሮ ኃይላቸው “በሰዓት 39 ማይል/ 63 ኪሎ ሜትር” ፍጥነት ላይ ሲደርሱ መሆኑን Hurricane.com ያትታል።

ሑሪኬኖች የየራሳቸው ስያሜ ነበራቸው። ከመቶ ዓመታት ጀምሮ የነበሩ በካሪቢያን ደሴቶች ያሉ ሕዝቦች ሒዩሪኬኑ በተነሳበት ቀን ያለውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “ቅዱስ” ስም የመስጠት የቆየ ልማድ ነበራቸው። በተለያየ ዓመት የተነሡት ሁለት ሒዩሪኬኖች በአንድ ቀን ላይ ቢውሉ ሁለቱን ለመለየት “ሒዩሪኬን ቅዱስ እገሌ አንደኛ” እና “ሒዩሪኬን ቅዱስ እገሌ ሁለተኛ” ይሏቸው ነበር።

በቀደመው ዘመን አሜሪካኖች ለሒዩሪኬኖች ስያሜ የሚሰጡት ሒዩሪኬኑ በተነሣበት “ሎንጊቲውድ/ላቲቲውድ” ላይ ተመርኩዘው ነበር። ነገር ግን ስያሜው በቀለላሉ የሚያዝ እና ለማስታወስ፣ ለመግባባትም ከባድ ሆነ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ግን ወታደሮች በአሁኑ ዘመን እንደሚደረገው ሒዩሪኬኖቹን በሴት ስም መጥራት ጀመሩ። ይኸው የወታደሮቹ አሰያየም ቀላልና ለማስታወስም ቀላል ሆኖ በመገኘቱ “National Hurricane Center” በ1953 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ በዚሁ መልክ መጥራቱን ጀመረ። ኅብረተሰቡም በቀላሉ መረዳትና መግባባት ቻለ። እ.ኤ.አ ከ1978 ጀምሮም የወንዶችንም ስም መጠቀም ተጀመረ።

ይህንን የአሰያየም መመሰቃቀል መልክ ለመስጠት ከ1979 ጀምሮ በየዓመቱ በአትላንቲክ ውቅያኖች ላይ ለሚነሱ ሒዩሪኬኖች አስቀድሞ 21 ስያሜዎችን ማውጣት ተጀመረ። ለስድስት ዓመታት የሚያገለግሉ ስሞችን አስቀድሞ ማውጣት ማለት ነው። ከA-Z ካሉት ፊደሎች ከ-Q,U,X,Y,Z በስተቀር በተቀሩት በያንዳነዳቸው ስም ይሰየማል። (በዚያ ዓመት ድንገት ከ21 በላይ ሒዩሪካኖች በሚነሱ ጊዜ ስያሜዎችን ከግሪክ ፊደል ስም ይሰጣቸዋል።)  ከአትላንቲክ ውጪ ባሉ አካባቢዎች የሚነሱ ሒዩሪኮኖችም የየራሳቸው ስያሜ እና አሰያየም ያላቸው ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ለማየት የሞከርኩት በ2012 በ “S” ተርታ የተሰየመችው እና አገር ምድሩን ያገለባበጠችው “ሳንዲ”/Sandy ያለችበትን የአትላንቲክ ሒዩሪኬን ብቻ ነው። ከ2012-2017 ያሉትን የአትላንቲክ ሒዩሪኬኖች ዝርዝር እዚህ ላይ (http://www.nhc.noaa.gov/aboutnames.shtml#atl)  መመልከት ይቻላል።

ከሒዩሪኬን ይሰውራችሁ
ሒዩሪኬን ሳንዲ ከመነሣቷ አስቀድሞ ጀምሮ መንግሥትም ሚዲያውም ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ሰንብተዋል። በተለይም አደጋው በከፋ ሁኔታ በተከሰተበት በኒውዮርክ ከተማ እና በውኃ ዳሮች በሚገኙ ከተሞች እና መንደሮች ቀደም ብሎ ጀምሮም ከፍ ያለ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቷል። የአሸዋ ክምሮችን መከመር፤ በሮችን እና መስኮቶችን በጣውላዎች ማሸግ፣ መንግሥት ለቃችሁ ውጡ ካለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ለቆ በመውጣት ወደተዘጋጁ መጠለያ ሥፍራዎች መግባት ዋነኞቹ ቢሆኑም እኔ የምኖርበትን አካባቢ ጨምሮ ባሉ ከውኃ ራቅ ባሉ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ቀድመው እንዲሸምቱ፣ ሻማ እና ኩራዝ እንዲያዘጋጁ፣ ስልካቸውን ባትሪ እንዲሞሉ፣ በባትሪ ድንጋይ የሚሠሩ ሬዲዮኖች እንዲያዘጋጁ ወዘተ ወዘተ ሲወተወት ተሰንብቷል።

እንደተባለውም ሳንዲ በተቀጠረው ቀን ስትመጣ እና በዝናብ፣ በነፋስ፣ በጎርፍ ስታጥለቀልቅ ዓለም ተደባለቀ። ኒውዮርክ እና ሌሎች በውኃ አካባቢ ያሉ ከተሞች በጨለማ ተዋጡ። በተለይ ኒውዮርክ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። እንደ ፀሐይ የሚያበራው ከተማ ጽልመት ወድቆበታል። የምድር ውስጥ ባቡሮች መሔጃ መንገዶች ለመጀመሪያ ጊዜ በውኃ ተጥለቅልቀዋል። ሁሉም ባይሆኑም። በእኛ አካባቢም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ መብራት አጥቷል። ዛፎች እየወደቁ ብዙ ጉዳት አድርሰዋል። የሰልክ መስመሮች፣ ቴሌቪዥኖቸ እና ኢንተርኔት ግንኙነቶች ተቆራርጠዋል።

ሒዩሪኬኑ እንዳለፈና “ሰላም ነው” ከተባለ በኋላ እስኪ ጉዱን ልየው ብዬ ካሜራዬን ይዤ ወጥቼ ወደ ዲሲ አቀናኹ። ከአንድ መንገድ ዳር የቆመ መኪና ትልቅ ዛፍ ተገንድሶበት ተጨፍልቆ አገኘኹ። ሰው ቢኖርበት በኩል እንዴት ያደርጋቸው እንደነበር ለመገመት ይዘገንናል። ለታሪክ በካሜራዬ ቀጭ ቀጭ አድርጌ ጉዞዬን ቀጠልኩ። መንገዱ በሙሉ በዛፎች ቅጠል ተሸፍኗል። ቅጠሎቹ ዝናብ ሲዘንብባቸው ደገሞ ከአስፓልቱ ጋር ይጣበቃሉ። ከዚያ መኪና ሲሔድባቸው የሙዝ ልጣጭ እንደረገጠ ሰው ይዘው ገደል ይገባሉ። ዋና ዋና መንገዱ ቶሎ ስልተጠረገ አደጋው ቀንሷል። ውስጥ ለውስጥ አሉነ መንገዶች ግን ገና ስላልተጠረጉ አደገኞች ናቸው። ሬዲዮኖቹ ይህንን ደጋግመው አስጠነቅቃሉ “እባካችሁ በዚህ በዚህ መንገድ አትሒዱ” ይላሉ። ሬዲዮ ለዚህ ካልሆነ ለምን ሊሆን ነው ታዲያ? ዝም ብሎ የፈረንጅ ሙዚቃ ማስኮምኮምና የአውሮፓ እግር ኳስ መተንተን ብቻ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ አያሰኝም።

እንዳልኳችሁ፣ ሳንዲ የ29 ሰው ሕይወት ቀጥፋ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት አውድማ፣ ብዙዎችን ያለ መኖሪያና ንብረት አስቀርታ አልፋለች። ቢሆንም “ተመስገን ነው፤ ከዚህ በላይ ልትጎዳ ትችል ነበር” እያሉ በየመገናኛ ብዙኃኑ እያወሩ ነው። ወሬው ሁሉ የፈረሰውን ስለመገንባት ነው። ኒውዮርክን የሚያክል ከተማ መብራት በመጥፋቱ፣ እሳት በመነሣቱ እና ጎርፍ በማጥለቅለቁ ምክንያት ሕይወት ወደ “ኖርማሉ” ለመመለስ ጥቂት ቀናት ይፈጁበታል። በዚህ አጋጣሚ ከቅድስት አገር ኢትዮጵያ በመደወልም፣ በመጻፍም ስለ ደኅንነታችን የተጨነቃችሁትን ሁሉ በማመስገን ላጠቃልል።

ይቆየን-ያቆየን።

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ.የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ማተም አይገባም::

No comments: