Monday, November 26, 2012

የጋዜጠኛ ዋጋው ስንት ነው?

  • መታሰቢያነቱ፦ ለታላቁ ጋዜጠኛ ለደምሴ ዳምጤ

(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ ሬዲዮ የብዙ ኢትዮጵያውያን ባለውለታ ነው። ምንም ይሰማበት ምን፣ የትኛውም ጣቢያ ይሰማበት የትኛው፣ ከየትንንሽ መንደሮቻችን እና ከተሞቻችን፣ ጎጆዎቻችን እና ሕንጻዎቻችን አውጥተው ወዳላየነው እና ወደማናውቀው አዲስ ዓለም እና አዲስ ሐሳብ በምናብ የሚያደርሱን የልቡናዎቻችን አክናፋት ሬዲዮኖች ናቸው። በዚያም ውስጥ ዕውቀታቸውን በዘባነ-ድምጽ (በድምጽ ትከሻ) ጭነው፣ በሬዲዮ ቧንቧ የሚያንቆረቁሩልን እና በድምጻቸው ብዕር ዕውቀት በልቡናችን የሚጽፉት ጋዜጠኞችም እንዲሁ ትልቅ ባለውለታዎቻችን ናቸው። ከጣት ጣት ይበልጣል እንዲል ተረታችን፣ “ኮከብ እምኮከብ ይኼይስ ክብሩ፤ ከአንዱ ኮከብ ክብር የአንዱ ኮከብ ክብር ይበልጣል” እንዳለው ቅዱስ መጽሐፍ ከአንዱ የሬዲዮ ጣቢያ ሌላኛው፣ ከአንዱ ጋዜጠኛም ሌላኛው ጋዜጠኛ፣ ከአንዱ ደራሲም ሌላኛው በማይረሳ መልኩ ተለይቶና ልቆ ይወጣል።

በርሱ ሙያ እና ሥራ በዘመኑ ከነበሩት ከዋክብት ልቆ እና ጎልቶ የታየው የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ነበር። ልጅ ሆኜ በሕጻን አዕምሮ፣ ነፍስ አውቄም በአዋቂነት ልቡና ብመዝነው ደምሴ የማይፋቅ ታላቅነቱን በልቡናዬ ቀርጾ ያለፈ ጋዜጠኛ ነው። ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ስሰማ ከማዘን ባሻገር ብዙ ትዝታዎች መቀስቀሳቸው አልቀረም። የልጅነትም የአዋቂነትም። የኢትዮጵያ ሬዲዮ እያንዳንዱን የደምሴን ሥራዎች እያወጣ ሊያሰማን እና ሊያስታውሰን እንደሚችል ባውቅም በእኛ በአድማጮች ልቡና ያለውን ትዝታ እና ውለታ ግን ከእኛ ውጪ ማንም ሊዘክረው አይቻልም።

ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ ይጣፍጥም ይምረርም ሰው የየግሉን ሐሳብ ሲያንጸባርቅ፣ ውሎ አድሮ ከትልቁ የታሪክ ክምር ውስጥ አንዲት ሚጢጢ ቀዳዳ የምትደፍን ፍሬ ይገኝባታል። በየሕይወታችን እና በታሪካችን ውስጥ ቁም-ነገር የሠሩ ሰዎችን ስንዘክር ሥራቸው መሬት እንዳልወደቀ፣ እኛም ዘረ-ቆርጥም መሬት እንዳልሆንን ማሳያ ሆኖ ይሰማኛል። እንደ ደምሴ ዳምጤ ላለውና ብቻውን የዕውቀት እና የመረጃ ምንጭ (በአጭሩ የዕውቀት አባት) ለነበረ ሰው ከዚህ ውጪ በግል ምን ሊደረግለት ይቻላል?

    ደምሴን ባሰብኩ ቁጥር ቀድሞ በኅሊናዬ የሚመጣው የ1970ዎቹ እና 80ዎቹ የዓለም ዋንጫዎች፣ ኦሎምፒኮች እና የኢትዮጵያ የራሷ እግር ኳስ ውድድሮች ናቸው። የዓለም ዋንጫን ካነሣን ችሎታው በደምሴ ልብ አንጠልጣይ ድምጽ ይተነተን የነበረውን የወጣቱን ማራዶናን ችሎታ፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ከዋክብትን ጥበብ፣ የየቡድኖቹን ውጣ ውረድ ያቀርብ የነበረበትን መንገድ እናነሣለን።

በተለይም 1986 እ.ኤአ. (1978 ዓ.ም) የተደረገውን የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ በአንድ እግሯ ቆማ ስትመለከት ከጨዋታው እና ከነማራዶና ችሎታ ይልቅ ቴሌቪዥን ማግኘት የማይችለውን ሚሊዮን እና ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ የደምሴ ትረካ ዓይን ሆኖት ነበር ማለት እላለኹ። ይህ 13ኛው የዓለም ዋንጫ ከሰባት ሰዓት በላይ የሰዓት ልዩነት ባለን በሜክሲኮ በመደረጉ ጨዋታው በቀጥታ በሚተላለፍበት ሰዓት አገራችን እኩለ ሌሊት ነው። በዚያ በሌሊት የተደረገውን ጨዋታ ውጤት እና ሁናቴ በበነጋው ልክ በዓይናችን እንዳየን አድርጎ የሚስልብን የደምሴ ሪፖርት ነበር።

ደምሴ የዓለም ዋንጫን ተመልክቶ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለዛ ባለው መንገድ የሕዝቡንም አስተያየት እየቃረመ ያቀርብ የነበረበት መንገድ ትዝ ይለኛል። ማራዶና የሚለው ስም እንዲያ በገነነበት በዚያ የዓለም ዋንጫ አዝማሪውም ግጥሙን ከጨዋታው ጋር አስተካክሎ ይዘፍን እንደነበር በፈገግታ በታጀበ ቅላጼ የሚያስረዳው ደምሴ ነበር። በየመሸታ ቤቱ ያሉ አዝማሪዎች “በሸዋ ላይ ደሴ ታቹን በቦረና፣ ና … ና ማራዶና” እያሉ እንደሚዘፍኑ እየሳቀና እያዋዛ ሲያቀርብስ እንዴት ይዘነጋል። ታዲያ ሰኞ ማታ ሬዲዮ በእጅጉ የሚናፈቀው አንድም ለደምሴ ሲባል ነው።

ከዓለም ዋንጫ ባሻገር ኦሎምፒክንም እንዲሁ ልብ አንጣልጣይ በሆነ መልኩ ተርኮልናል። ቴሌቪዥን ብርቅ በነበረበት ዘመን የኢትዮጵያን ስፖርት በዓይነ ሥጋ እንዳየን ሁሉ በዕዝነ ኅሊናችን እንድንመለከተው አድርጓል። ከስፖርቱ በተለይም ከእግር ኳሱ ደካማ መሆን ጋር የርሱን የመንፈስ መንገላታት ስንመለከት ስፖርት ለደምሴ ሥራ ሳይሆን የኑሮው አካል እንደነበር እንታዘባለን። ሙያን እንዲህ ከነፍስና ከሥጋ ጋር አቆራኝቶ መሥራት በብዙዎች ዘንድ የሚታይ ሥጦታ አይደለም።

እንደራሴ ግምገማ ከሆነ ደምሴ ዳምጤ ለኢትዮጵያ ስፖርት የተጫወተው ድርሻ ከማንም የማይተናነስ እንደመሆኑ ውለታው እንደዋዛ እንዳይረሳ ያስፈልጋል። የሰውን ውለታ በመርሳት በኩል ደግሞ የተካበተ ልምድ ያለን አገር ስለሆንን ደምሴንም በዚያው በተለመደው የመርሳት መዝገብ ከተጻፉት እንዳንደምረው እሰጋለኹ። በተለያዩ ሙያዎች የተሰለፉ የሌሎቹን ባለውለታዎቻችንን እንኳን ባንጠቅስ በስፖርቱ ሙያ የአፍሪካ እግር ኳስ አባት የሆኑትን የአቶ ይድነቃቸው ተሰማን ጉዳይ መጥቀስ እንችላለን።

ይድነቃቸው  ተሰማ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ እግር ኳስም ታላቅ ባለውለታ እንደመሆናቸው አገራቸው ኢትዮጵያ ለስማቸው መጠሪያ አንዲት ድንጋይ አለማቆሟ፣ አንድም አደባባይ አለመሰየሟ፣ አንድም ት/ቤት አለመገንባቷ ሲታይ ውለታ በመዘንጋት ረገድ ወደር እንደማይገኝላት ያሳያል። አረባዊቷ የሰሜን አፍሪካ አገር ሞሮኮ ለእርሳቸው መታሰቢያ በካዛብላንካ የሚገኘውን ስታዲየሟን “ተሰማ ስቴዲየም” (Stade Tessema) ብላ ስትጠራ ኢትዮጵያ ጭራሽ መዘንጋቷ ዘረ-ቆርጥም ያሰኛታል።

ደምሴ ዕድሜ ዘመኑን የደከመው ለኢትዮጵያ ስፖርት እንደመሆኑ ዝክረ ስሙ እንዳይጠፋ መጠሪያ የሚሆነው አገራዊ ሽልማት ያስፈልገዋል። ከፍ ብዬ ለጋሽ ይድነቃቸው እንደጠቀስኩት መዘከሪያ ሐውልት ሊቆምለት፣ አደባባይ ሊሰየምለት፣ ት/ቤት ሊከፈትለት፣ ፋውንዴሽን ሊቋቋምለት ይገባል። በአገሪቱ ካሉት የጋዜጠኝነት ማስተማሪያ ኮሌጆች አንዱን “ደምሴ ዳምጤ የጋዜጠኝነት ማስተማሪያ ኮሌጅ” የሚል ዩኒቨርሲቲ ቢገኝ ታሪክን በመዘከሩ ዩኒቨርሲቲውም ይከበራል።

እንዲህ ያሉ ታላላቅ ሰዎችን ስማቸውን ከመቃብር በላይ ልናቆም የምንችለው አንድም “ፋውንዴሽኖችን” በማቋቋም እና የነርሱን አሰረ-ፍኖት መከተል ለሚፈልጉ ወጣት ጋዜጠኞች የዕውቀት በር በመክፈት ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በአገራችን ያሉ የስፖርት ጋዜጠኞች፣ አሰልጣኖች፣ የደምሴ ወዳጆች እና አጋሮች ቅድሚያውን ቢወስዱ ያስመሰግናቸዋል። የስፖርት “ቶክ-ሾው” አዘጋጆች ለአውሮፓው ስፖርት ከሚሰጡት ጊዜ ጥቂቱን እንዲህ ባለው ጉዳይ ላይ ቢያውሉስ?

የደምሴ እናት ድርጅት የሆነው “የኢትዮጵያ ሬዲዮ” (ኢ.ሬ.ቴ.ድ?) ይህንን ታላቅ ባለሙያውን የሚዘክርበት ብዙ መንገድ አለው። ቢያንስ ቢያንስ የደምሴና ቃለ ምልልሶች፣ ዋና ዋና ዝግጅቶች በመሰብሰብ እና ለተጠቃሚ/ለአድማጭ በሚመች መልክ “ዶኩመንት” በማድረግ፤ እንደዘመኑ ከሆነ ደግሞ በኢንተርኔት ለተጠቃሚ ማድረስ ይችላል። ምናልባትም ቋሚ ዐውደ ርዕዮች ካሉት ወይም በማዘጋጀት ደምሴን የመሳሰሉ ዐበይት ጋዜጠኞቹን ፎቶዎች፣ ቃለ ምልልሶች፣ ዝግጅቶች ማሳየት ይችላል፤ ይገባዋልም። አንዳንዴ ከካድሬነቱ ስብከት ቀነስ አድርጎ እንዲህ ዓይነት ሙያዊ ሥራ መሥራትም ያስፈልጋል።

ይህንን በምሳሌነት አነሣን እንጂ ድርጀቱ ለብዙ አሥርት ዓመታት ያከማቸውን የድምጽ ወምስል ሀብት ጥቅም ላይ ሊያውል የሚገባው ዘርፈ ብዙ ሀብት አለው። በሌላው ዓለም እንደሚደረገው እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ቢጠቀም ለራሱም ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ይፈጥራል። የቆዩ ዝግጅቶችን በአንድ በመሰብሰብ “በኮሌክሽን” መልክ ማሳተም የተለመደ ነው። የቆዩ “የእሑድ መዝናኛ” ዝግጅቶችን የመሳሰሉ ተወዳጅ የነበሩ ዝግጅቶች በዲ.ቪዲዎች ቢዘጋጁ ለታሪክ ለማስቀመጥም ቢሆን ለመግዛት የሚፈልጉ ብዙ አድማጮች እንደሚኖሩ ጥርጥር የለኝም።

ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው ግን እንደ አገርም፣ እንደ መንግሥትም ለጋዜጠኞች እና ለጋዜጠኝነት የምንሰጠው ትርጉም እና ቦታ ቁም ነገር ያለው ሲሆን ነው። እስካሁን ባለን “ሪከርድ” ጋዜጠኞች አንድም ባሮች አንድም ጠላቶች ተደርገው ስለሚቆጠሩ በሁለቱም ጠርዝ ተጎጂዎች ናቸው። ጋዜጠኛው የሚፈለው “ካድሬ” እንዲሆን እንጂ ኅሊና ያለው እና እውነት-አንጣሪ (fact checker) እና ሚዛን የሚደፋ ሐሳብ አቅራቢ እንዲሆን አይደለም። ስለዚህም የተከበረው ሙያ በእኛ አገር አንድም ወደ ወህኒ የሚያስወረውር አንድም ኅሊናን የሚያስሸጥ እና “እንጀራ ሆኖብኝ ነው” የሚያሰኝ ራስን የማዋረድ ሥራ ሆኗል።

የኢትዮጵያን ቴሌቪዥንን የሚመለከት ሰው “ምራቁን የዋጠ ጋዜጠኛ በዚህ አገር የለም እንዴ?” ያሰኛል። ዕውቀት ሁለት ጸጉር በማውጣት ይገለጣል የሚል ድምዳሜ ባይኖረኝም ጋዜጠኛው በመንግሥት ቲቪም ሆነ ሬዲዮ የሚሠራው ለጊዜው፣ ቀን እስኪወጣ፣ አጋጣሚ እስኪፈጠር፣ የተሻለ ቦታ እስኪያገኝ ብቻ ከሆነ የተሻለ ልምድ ያለው ባለሙያ አይኖርም። አማተርነት ብቻ የቤቱ መገለጫ ይሆናል። ዞሮ ዞሮ ጉዳቱ ለአገር ነው። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው ራሱ መንግሥት ነው። ደምሴን የመሳሰሉ ሙያና ተሞክሮ የተላበሱ ሰዎች በሞትም፣ በጡረታም፣ በካድሬ በመገፋትም ከአገራዊው ሚዲያ ላይ ሲጠፉ የሚያስቆጨን ለዚህ ነው። ደምሴ፦ ነፍስህን በደጋጎቹ ጻድቃን ዘንድ ያሳርፍልን፤ ለቤተሰብህም መጽናናቱን ይስጣቸው።

ይቆየን - ያቆየን።

 

1 comment:

Anonymous said...

Thanks Dn. Ephrem. Demise loves Ethiopia and Ethiopian Sport. His passion and attention was mainly on Ethiopian Sport: athletics, football... Junior journalistic should learn a lot from him. Especially our FM Sport journalists; they give attention to English premier league, Wayne Rooney, Van Percy, etc. I have never heard them trying to create our own football heroes and heroins. They are simply Google and TV dependent journalists. They do not want to go to the football pitch, where the athletes train...I think they need to work hard to reach the level of Demise. You are my Hero. RIP Demise.