Monday, November 26, 2012

የእርቅና የሰላም አየር - በሰሜን አሜሪካ(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሕይወት ውስጥ የተለየ ሥፍራ ይዞ የመጣ ዓመት ነው። ላለፉት 20 ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቱን በፓትርያርክነት ሲመሩ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አርፈው መንበሩ ባዶ መሆኑን ተከትሎ ብዙ ጥያቄዎች መነሣት ጀምረዋል። ከነዚህ ጥያቄዎች አንዱ ደግሞ በተለይም በዚህ በምኖርበት በሰሜን አሜሪካ ያሉትን አራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን የጨመረ “እርቅ እና ሰላም” የሚደረግበት ሁኔታ ነው። ይህ ጽሑፍ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያጠነጥን ስለሆነ “ቤተ ክርስቲያን” የሚለው በዚህ ማዕቀፍ ብቻ እንዲታይ በማስታወስ ልቀጥል።

አጠቃላይ ዳራ

ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ልዩነት ከገጠማት ጊዜ ጀምሮ በዳያስጶራ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ በተለያዩ የተሳሳቡ ጫፎች ላይ የቆመ ነው። በሃይማኖቱ በኩል ያለው መካረር ከፖለቲካው መሳሳብ ባልተናነሠ መልኩ የከረረ ሆኖ ዘልቋል። ፖለቲካው በመንግሥት ደጋፊና ተቃዋሚ፤ በተለያየ ብሔረሰባዊ ማንነት የተለያየ እና የሚጓተት መሆኑ ሳይበቃ “ቤተ እግዚአብሔሩም” እንዲሁ በፖለቲካዊ አቋም፣ በብሔረሰባዊ፣ በዘር እና በቋንቋ ማንነት የሚበየን ሆኗል።

በአሜሪካ እና ዳያስጶራው በብዛት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ያለው የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ቢያንስ በሦስት ዋና ዋና ቡድኖች የተከፈለ ነው። 1ኛ. “አገር ቤት ባለው ጠቅላይ ቤተ ክህነት (በእናት ቤተ ክርስቲያን) ሥር”  ያሉ አብያተ ክርስቲያናት፣ 2ኛ. በአሜሪካ ባለው ሲኖዶስ (ስደተኛው) ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት እና 3ኛ. ከሁለቱም ሥር የለንም የሚሉና በተለምዶ “ገለልተኛ” የሚባሉ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

ሦስቱም ክፍሎች አንድነት ያላቸው ቢመስሉም እያንዳንዳቸው በየራሳቸው ሲታዩ ግን ብዙ ልዩነት አላቸው። ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባው ቤተ ክህነት ሥር ናቸው የሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸው በብዙ ልዩነት የተያዙ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ካላቸው ታማኝነት ይልቅ ለቀድሞው ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ባላቸው ታማኝነት ይታወቃሉ።

በውጪው ሲኖዶስ ሥር ያሉትም ቢሆኑ አፍአዊ እንጂ ሥር የሰደደ አንድነት አላቸው ተብለው የሚነገርላቸው አይደሉም። እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዚህ በፊት ያልነበረ የውስጥ ለውስጥ አለመግባባት እየናጣቸው ነው። በአገር ልጅነት እና በዘር እንዲሁም ለፖለቲካው ባላቸው ቀረቤታ ይታማሉ።

“ገለልተኛ” የሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት “ከምኑም ውስጥ የለንም፣ ከነገሩ ጦም እደሩ” የሚሉ ሲሆኑ ገሚሶቹ ከአገር ቤት ጋር ገሚሶቹ ደግሞ ከውጪው ጋር የተሻለ ቅርርብ ያላቸው ናቸው። “ገለልተኛ” የሚያስብላቸው ካላቸው “መሐል ሰፋሪ” የመሆን ዝንባሌ ይልቅ የበላይ ካለመፈለግ የመነጨ ስሜት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። አዛዥ-ናዛዥ አለመፈለግ፣ በራሳቸው ጀማሪ-ፈጣሚ የመሆን ፍላጎት ነው ይሏቸዋል።

ሦስቱም ክፍሎች እንደየማንነታቸው ለኢትዮጵያው ፖለቲካ ያላቸው ደጋፊነት እና ተቃዋሚነት የተገለጸ ነው። በአገር ቤት አስተዳደር ሥር ያሉት ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን ከፖለቲካ ለማራቅ የሚሞክሩ ቢሆኑም መደገፍ በሚያስፈልግበት ወቅት በግልጽ ለመደገፍ የሚደፍሩት የኢትዮጵያን መንግሥትና መሪ ፓርቲውን ሲሆን በተቻለ መጠን ግን ወደዚህ ደረጃ ላለመድረስ ይሞክራሉ።

ውጪ አገር ባለው ሲኖዶስ ሥር ያሉት ደግሞ በፖለቲካ አቋማቸው “አጽራረ መንግሥት” መሆናቸውን ይናገራሉ፣ ተቃዋሚዎችን ይደግፋሉ፣ በየጊዜው ለሚነሱ ፖለቲካዊ ትኩሳቶችም ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ። የሲኖዶሱ አባላትም ሆኑ ጳጳሳት በየጊዜው በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫዎች ይሰጣሉ፣ በስብሰባዎችና በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ሲገኙ ይታያሉ። በውግዘት ለመለያየት ምክንያት በሆነው አዳዲስ ጳጳሳት ሹመት ወቅት ከተሾሙት የስደተኛው ሲኖዶስ ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት “አቡነ መቃርዮስ” ኤርትራ ድረስ በመዝለቅ የኢትዮጵያን መንግሥት በነፍጥ ከገጠሙት ተቃዋሚዎች ጋር መነጋገራቸውን በአካባቢያችን ሚዲያዎች ሰምተናል፣ ፎቶዎቻቸውንም አይተናል።

ሦስተኛዎቹ ማለትም “ገለልተኛ” የሚባሉት ደግሞ በፖለቲካዊ አቋማቸው በግልጽ ለመደገፍ የሚደፍሩት ተቃዋሚዎችን ሲሆን ምርጫ 97 በመሳሰሉት አጋጣሚዎች የከረረ ጸረ መንግሥት አቋም አራምደዋል። ይሁን እንጂ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት፣ ሀብት ለማደርጀት እና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመሥራት በሚኖራቸው ፍላጎት ጠንካራ ተቃዋሚ መሆንን ብዙም አይፈልጉትም።    

ጉዳዩ በዚህ ዓይነት ውጥንቅጥ ውስጥ ሲሆን ምእመኑ ግን በአብዛኛው የልዩነቱ ተጠቂ እንጂ ደጋፊም ነቃፊም አይደለም። ወርሃዊ በዓላትን እየጠበቀ፣ የልዩነት ድንበሩ ሳይከልለው ወደ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የመሔድ ልማድ አለው። ይህ “የልዩነትን ድንበር አልፎ መሔድ” የሌለው በካህናቱ እና በአገልጋዮቹ ዘንድ ነው። በርግጥም ለእነርሱ አስቸጋሪ ነው።

አሁን

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ላለው መከፋፈል በዐቢይ ምክንያትነት የሚጠቀሰውን በውግዘት የመለያየት ችግር ለመቅረፍ ይበል የሚያሰኝ ጥረት በመካሔድ ላይ ነው። ከሁሉም ወገኖች ያሉ ግለሰቦች የተሰባሰቡበት የአስታራቂው ቡድን ጥረቱ በሁለቱም ሲኖዶሶች ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ ተደራዳሪዎችን ለማገናኘት መቻሉ ይታወሳል። ይኸው ጥረት አሁን መሠረት በመያዝ በምእመናን ደረጃ ዋነኛ አጀንዳ በመሆን ላይ ይገኛል። የቤተ ክህነቶች “አጀንዳ” የነበረው ጉዳይ ምእመኑም የራሱ አጀንዳ እያደረገው እና በመነጋገሪያነቱም “መወያያ” እየሆነ ነው።

በዚህ ረገድ እና በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ በሰሜን አሜሪካ የማኅበረ ቅዱሳን ማዕከል ያዘጋጀው “ቴሌኮንፈረንስ” ሰፋ ያለ ትኩረት አግኝቷል። ካህናት አባቶች፣ ሊቃንት፣ ምሁራን እና አጠቃላይ ምእመናን የተሳተፉበት እና በአቋማቸው በተግባር የተገለጸውን አስተዳደራዊ ክፍፍል የሚያንጸባርቅ ሐሳብ ያራምዱ የነበሩ ተናጋሪዎች አስተያየታቸውን በሰጡበት ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው ከሆነ “ሕዝቡ ክፍፍሉ አንገሽግሾታል”።

ተናጋሪዎቹም ቢሆኑ በአሁኑ ወቅት ያለው “ክፍፍል” ሥር የሰደደ ሳይሆን ቀላል እና በጊዜ መፍትሔ ከተወሰደበት ያለ ምንም ጠባሳ ሊቀረፍ የሚችል መሆኑን አጽንዖት ሰጥተውበታል። ችግሩ መኖሩን ቀደም ብሎም ሲነገር የቆየ ቢሆንም ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት በካህናቱና በምእመናኑ ዘንድ አንድ ዓይነት እና ጠንካራ ፍላጎት በማሳየቱ ግን አሁኑን ፍላጎት የተለየ ያደርገዋል።

አንዳንድ ነጥቦች

በብዙዎቹ ተሳታፊዎች ዘንድ እንደተገለጸው ከሆነ በአባቶች መካከል ለሁለት ዐሥርት ለዘለቀው ክፍፍል መፍትሔ መፈለግ ከምንም ነገር መቅደም እንዳለበት መግባባቱ አለ። ከምንም ነገር ማስቀደም ያስፈልጋል ሲባል ደግሞ በዋነኝነት ለጊዜው ባዶ ስለሆነው “መንበረ ፕትርክና” ወይም የፓትርያርክነት መንበር እና ፓትርያርክነት ነው። በሁሉም ክፍሎች ያሉ ተናጋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ “ፓትርያርክ መሰየም” ከእርቁ በኋላ ሊመጣ የሚገባው ዋነኛ ነገር ነው።

       ሲጀመርም “ፕትርክናው” የሁሉም ነገር እና የመለያየቱ መለያ ድንበር እና ምልክት ነበር። ለወደፊቱም ለእርቁም ሆነ ለጸቡ በምልክትነት የሚቀርበው ይኸው “የፓትርያርክነቱ ወንበር/መንበር” ነው። ስለ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዕውቀት ከሌላቸው ሰዎች ጀምሮ እስከ ሊቃውንቱ ድረስ በአንድ ዓይነት መልኩ የሚያነሱት ቃል “በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ መሾም” የምትለው ሳትሆን አትቀርም። በዚህ ዙሪያ ያለውን ችግር መፍታት ከተቻለ በተለይም በሰሜን አሜሪካ ላለው አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ እንቅስቃሴ ትልቅ ርምጃ ይሆናል። የኢትዮጵያዊውን ማኅበረሰብ የርስ በርስ ግንኙነትም ጤናማ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያው ማኅበረሰብ በሃይማኖት በኩልም ሆነ በ40 ዓመቱ ፖለቲካችን ውስጥ በገጠመው ጫፍ እና ጫፍ የመቆም (የፖላራይዜሽን) ችግር በአሜሪካ ውስጥ ተሰሚነት ያለው ትልቅ ኮሚዉኒቲ ለመሆን ሳይችል ቀርቷል የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ። ከሌሎች መጤ-ማኅበረሰቦች ጋር ሲነጻጸር የእኛው ብዙም ዕድገት ካላሳየባቸው ምክንያቶች አንዱ ይኸው ልዩነቱ ነው።

ሌሎች መጤ-ማኅበረሰቦች ለምሳሌ ግሪኮች፣ ቪየትናሞች፣ ግብጾች፣ ሕንዶች እና የደቡብ እስያ ሕዝቦች ያላቸው ተቀራራቢነት እና ተሰሚነት ከእኛ የበለጠው ልዩነቶቻቸውን ለማቻቻል በመቻላቸው መሆኑን ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ይስማሙበታል። ለዚህ መቻቻል እና መስማማት በድልድይነት ልታገለግል የምትችለው ቤተ ክርስቲያን የልዩነቱ ቦታ እና ምልክት መሆኗ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኗል። የእርቁን ስሜት ብዙዎች በተስፋ የተመለከቱት ከዚህም አንጻር ሊሆን ይችላል።

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊ ይኖርበታል በሚባለው በዲሲ እና በአካባቢው አንድም የኢትዮጵያ ት/ቤት የለም። በዲሲ አማርኛ በከተማው እውቅና ከማግኘቱ ውጪ በቨርጂኒያም ሆነ በሜሪላንድ ለሚኖረው እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊ የተለየ ጥቅም የሚያስገኝ መንግሥታዊ መብት አላስገኘለትም። በጠቅላላው ከላይ በዘረዘርኳቸው በሦስቱም ቡድኖች ውስጥ ያሉና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስም የሚጠሩ ከ20 ያላነሱ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም አንድነት ስለሌላቸው ለማኅበረሰባቸው የጋራ የሆነ ተሰሚነትን ለመፍጠር ሳይቻላቸው ቀርቷል።

ሲጠቃለል

የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ከሃይማኖታዊው አንድምታው ባሻገር በሰሜን አሜሪካ ላለው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብም ሆነ ራቅ አድርገን ካሰብነው ለኢትዮጵያም የሚኖረው ጠቀሜታ ሰፊ ነው። ዎርልድ ባንክ የ2010-2011 ከውጪ ወደ አገር ቤት ያለውን የገንዘብ ፍሰት (Remittance flows to Ethiopia) ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን መጥቀሱ ይታወሳል። ያውም በይፋ የሚታወቀው። አንድነት እና ኅብረት ያለው ማኅበረሰብ ቢሆን ኖር ምን ያህል ታላቅ ለውት ሊያመጣ የሚችል እንደሆነ ለመገመት ጥሩ ማሳያ ነው።

እንግዲህ በቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ላይ የተቀመጡት አባቶች ትልቅ ታሪካዊ ወቅት ላይ ይገኛሉ። አሁን የሚወስኑት ውሳኔ ታሪካዊ ነው። የሚገጥማቸውን መሰናክል አልፈው የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ማስጠበቅ ከቻሉ ለቤተ ክርስቲያናቸውም ለአገራቸውም ትልቅ ውለታ ይውላሉ፤ በታሪክም በበጎ ሲወሱ ይኖራሉ።

ከዚህ አንጻር የተጀመረው የእርቅና ሰላም እንቅስቃሴ በጉጉት እየተጠበቀ ነው። ምእመኑ የእርቁ በጎ ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት ከማሳየትም በላይ የአቅሙን ለማድረግ ትረት ጀምሯል። በሁለቱም ሲኖዶሶች በኩል ያሉ አባቶች በጎ ምላሻቸው በዚሁ ከቀጠለ እና ከውጪ የሚመጣባቸውን ተጽዕኖ ያለ ፍርሃት እና ያለ ይሉኝታ መቋቋም ከቻሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እና ለአገሪቱ ጠቃሚ የሆነ ውጤት ያስገኛሉ። በዚህ ጉዳይ ውስጥ “ፍላጎት ያላቸው” ወገኖችም እጃቸውን በመሰብሰብ ለአንድነቱ ዕድል ቢሰጡ ዞሮ ዞሮ የጥቅሙ ተሳታፊ እንጂ ተጎጂ አይሆኑም። ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሰላም አየር እየነፈሰ ነው።

ይቆየን - ያቆየን።

 

3 comments:

አንድ አድርገን said...

ዎርልድ ባንክ የ2010-2011 ከውጪ ወደ አገር ቤት ያለውን የገንዘብ ፍሰት (Remittance flows to Ethiopia) ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን መጥቀሱ ይታወሳል። ያውም በይፋ የሚታወቀው። አንድነት እና ኅብረት ያለው ማኅበረሰብ ቢሆን ኖር ምን ያህል ታላቅ ለውት ሊያመጣ የሚችል እንደሆነ ለመገመት ጥሩ ማሳያ ነው።. ይህ ለእኛ ምናችን ነው… ከእርቀ ሰላሙ ጋር አብሮ ኤሄድም

Anonymous said...

God bless you. This is great article keep it up. Be neutral which is not stand on one side. We need peaceful message like this to be come as unity because all of us the children of eotc.

Anonymous said...

God bless you. This is great article keep it up. Be neutral which is not stand on one side. We need peaceful message like this to be come as unity because all of us the children of eotc.