Monday, December 24, 2012

የዛሬ አበባዎች (ኤፍሬም እሸቴ/PDF)፦ ልጅነት የንጽሕና እና የንፁህ ልብ ዕድሜ ዘመን እንደሆነ በሁሉም ሰው፣ በሁሉም ባህልና እምነት ይታመናል። ይህ እውነት መሆኑን ወላጅ የሆነ ሰው ወይም ለሕጻናት ቅርበት ያለው ሰው  ጥናትም ባያደርግ ይረዳዋል። ሁላችንም በልጅነት ዕድሜ ስላለፍን በርግጥም እኛም ምስክሮች ነን። በዚህ የማርነት፣ የጣፋጭነት፣ የረዳት የለሽነት ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ችግር ሲገጥማቸው ታዲያ አንጀት ይበላሉ። ሳቃቸው በለቅሶ፣ ፈገግታቸው በዕንባ ሲተካ ማየት የሰውን አንጀት ይበላል። ሰሞኑን በአሜሪካ የተፈጸመው የሕጻናት የጅምላ ጭፍጨፋ ዓይነት ሲከሰትማ ከኅሊና በላይ ይሆናል። “ምን ባጠፉ፣ በምን በደላቸው?” ያሰኛል። ሌላም ብዙ ጥያቄ እንድንጠይቅ ያደርገናል። ስለራሳችን፣ ስለ አገራችንም እንድናስብ ያደርገናል።

አንድ - አሜሪካ

ነገሩ፣ ሁላችሁም እንደሰማችሁት፣ “Sandy Hook Elementary School” በተባለ ት/ቤት ላይ አንድ የ20 ዓመት ወጠምሻ ጎረምሳ በከፈተው ተኩስ 20 ሕጻናትን እና 6 አዋቂዎችን መጨፍጨፉ ነው። ስለ ነገሩ በዋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት መግለጫ የሰጡት ፕሬዚዳንት ኦባማ ሐዘን ፈንቅሏቸው ንግግራቸውን ደግመው ደግመው ሲያቋርጡ፣ ጎንበስ ብለው ዕንባቸውን ሲያብሱ በቴሌቪዥን መስኮት አይተናቸዋል። እንደ አባት እንጂ እንደ ፕሬዚዳንት አይደለም የምናገረው ሲሉም ተደምጠዋል።

 

ፕሬዚዳንቱ ብቻ ሳይሆኑ አሜሪካ በሙሉ በዚህ አስደንጋጭ ዜና ክፉኛ ደንግጣ ነው የሰነበተችው። ሐዘኑ ብዙዎችን አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ ተሰምቷቸዋል። ብዙ ጊዜ የማዳምጠው ተወዳጁ የ“National Public Radio/ ብሔራዊ የሕዝብ ሬዲዮ” ተከታታይ ዝግጅቶችን፣ የሕዝብ አስተያየቶችን፣ የጭፍጨፋው ሰለባዎችን ታሪኮችን በማቅረብ ላይ ይገኛል። በተለይም ተጎጂዎቹ ክፉና ደጉን የማያውቁ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ 20 ሕጻናት መሆናቸው የሁሉንም አንጀት በልቷል።

አሜሪካውያን እንዲህ ባለው አደጋ ሲጠቁ የመጀመሪያቸው ባይሆንም በቅርብ ጊዜ ከደረሱ የጅምላ ግድያዎች ይህኛው በሟቾች ቁጥር ብዛትና ዕድሜ የተለየ ሆኗል። እንደዚህ ዓይነት አደጋ ሲደርስ ስሜታቸውን፣ ንዴታቸውንና ቁጣቸውን በይፋ ለመግለጽ ወደ ኋላ የማይሉት አሜሪካውያን መሣሪያ የመያዝ መብትን ለማስከበር በሚሟገቱ ድርጅቶች ላይ እና አሣሪ ሕግ እንዳይወጣ በሚያደርጉ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ላይ ቁጣቸውን በማውረድ ላይ ናቸው። “በ3ኛው ዓለም እንኳን የማይደረግ ነገር እንዴት እዚህ ይደረጋል?” የሚለው የሕዝቡ ቁጣ “መሣሪያ መያዝ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው” የሚሉትን ሳይቀር አፋቸውን አስይዟቸዋል። ስለዚሁ መብት ጉዳይ የሚከራከረውን ተቋም ሳይቀር። እንደ አያያዙና እንደ ሕዝቡ ቁጣ ከሆነ ባራክ ኦባማ የሚያራምዱት በዚህ የመሣሪያ አያያዝ ጉዳይ ላይ ዕቀባ የማድረግ ሕግ ሊጸድቅ ይችላል።

ሁለት - ቻይና

እንዲሁ ከሕጻናት ጋር በተያያዘ ጉዳይ፣ ቻይና ውስጥ፣ 23 የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን በጅምላ በጩቤ ሲወጋ የነበረ ሰው የመያዙን ዜና ተሰምቷል። አምናም ሌላ ቻይናዊ በተመሳሳይ መልኩ ብዙ ተማሪዎችን በጩቤ ወግቷል። ምክንያቱ - ቻይና ውስጥ ያለው የኑሮ ለውጥ ያመጣው ቀውስ ነው የሚሉም አሉ፣ አይደለም “የማያ ዘመን አቆጣጠር” ዕለተ ምጽዓት ደርሷል በማለቱ ቀልቡን ነሥቶት ነው የሚሉም አሉ። የቻይና የሕጻናት ቀበኞቹ ጩቤ እንጂ መትረየስ ባለማግኘታቸው ሕጻናቱን በቀላሉ ሳይፈጇቸው ቀርተዋል።

ሦስት - ኢትዮጵያ

አገራችን ኢትዮጵያ ልጆችን በጉዲፈቻ ወደ ውጪ አገር በመላክ ኮኮብ ሆናልናለች። እውነትነቱን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሜሪካ የሚበሩ ሰዎች በግርምት አፋቸውን እየያዙ የሚደነግጡበትን ማየት በቂ ነው። ወደ አውሮፓ የሚወሰዱት ቁጥርም ቀላል እንደማይሆን እገምታለኹ። አሳዳጊዎቻቸው ካመጧቸው በኋላ ሕጻናቱ እየደረሰባቸው ስላለው ነገር ሰፊ ዘገባ ማግኘት ቀላል ባይሆንም ወንጀል እየተፈጸመባቸው ሕይወታቸውን፣ አካላቸውን ስለሚያጡት ጉዳይ ብዙ ዘገባዎች በመውጣት ላይ ናቸው።

  ከሕጻናቱ ከፍ ስንል የአገራችን ወጣቶች በእግራቸውም በመኪናም፣ በጀልባም አገራቸውን እየተዉ ለመሰደድ በሚያደርጉት ጥረት ካሰቡት ሳይደርሱ ደመ-ከልብ ሆነው የሚቀሩትን በተመለከተ መስማት የየዕለት ዜና ነው። ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት እንኳን ከሶማሊያ ወደብ ወደ የመን ለመሻገር በጀልባ የተሳፈሩ ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን (ዜናው ኦሮሞዎች ብሎ አስቀምጦታል) ሰጥመው መሞታቸውን ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ እየሰማኹ ነው። ሌላም ብዙ ብዙ ነገር ማውሳት እንችላለን።

በአሜሪካ 20 ሕጻናት ተገደሉ የሚባል ነገር ስንሰማ ብዙዎቻችን “እንዴት ያለ ያበደ አገር፣ ያበዱ ሰዎች” ብለን ስንፎክር እንሰማለን። በራሳችን አገርና ባህል እንኮራለን። የምናምንቴ ፈረንጆችን ባህልና አዘኔታ የለሽነት እንወቅሳለን። በአገራችን ዓይን ላይ ያለውን ትልቅ ምሶሶ ሳናወጣ በሌላው አገር ዓይን ላይ ያለውን ጉድፍ እንመለከታለን።

ይህንን ጽሑፍ በምጽፍበት በዛሬው ዕለት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፍርድ ቤት ቀርቦ እየተከራከረ ነው። እስር ቤት የተወለደው ልጁ የአባቱን ዕጣ ፈንታ ለማመዛዘን ዕድሜው ባይፈቅድለትም ትንሽ ልቡ በአባት ፍቅር እንዴት ጠብ እርግፍ እንደምትል ለመገመት አይከብደኝም። ምናልባትም ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ እስክንድርን ንብረት እንዲወረስ ከፈረደ፣ ያ እንቦቃቅላ ሕጻን እስር ቤት መወለዱ ሳያንስ ካደገበት ቤት እንዲወጣ ይገደዳል ማለት ነው። ይህ አሳፋሪ ተግባር እየተፈጸመ ያለው በኢትዮጵያ ነው።

ሕጻናትን በየት/ቤታቸው በመሣሪያ የሚገድላቸው ወንጀለኛ በአገራችን አለመኖሩ ትልቅ ነገር ነው። ነገር ግን ልጆች በቀጥታ የጥቃት ሰለባ አለመሆናቸው ብቻ ትልቅ እፎይታ አይሰጥም። በምግብ እጦት ከት/ቤት ሰልፍ ላይ ራሳቸውን እየሳቱ ስለሚወድቁ ሕጻናት “አዲስ ጉዳይ” ሰፊ ዘገባ እንዳስነበበችን ይታወሳል። “ምን በልተን እንማር?” ማለታቸውንም እንዲሁ። እንደ አገር ልጆቻችንን መመገብ የማንችል ነን፤ ይህ እየሆነ ያለው በኢትዮጵያ ነው።

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች “በሕገ ወጥ መንገድ በያዙት የመንግሥት መሬት ላይ ሕገ ወጥ ቤት” በመሥራታቸው ቤቶቹ እንዲፈርሱ በመደረጉ ነዋሪዎቹ “መቸገራቸው” እየተሰማ ነው። ሕገ ወጥ በመባላቸው ቤቱ ቢፈርስባቸም፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው ደግሞ አደጋ ለሚደርስባቸው ዜጎች ከተፍ ብሎ ደርሶ የዕለት ጉርስ፣ የዕለት መጠለያ ማቅረብ የማንኛውም መንግሥት ግዴታ አይደለምን? ማፍረስ ብቻ እንጂ ለዜጎች ሕይወት አለመጨነቅ አሳፋሪ አይደለም? በአንድ ቀን ብዙ አባ/እማወራዎችን ከነልጆቻቸው ቤት አልባ አድርጎ ማደር በምንም መመዘኛ “ግዴታችንን ተወጣን፣ ሥራችንን ሠራን” የሚያሰኝ አይደለም። ይህ የሚደረገው በኢትዮጵያ ነው።

አራት - በጠቅላላው

የነዚህ አሜሪካ ሕጻናት የአንድ ጊዜ ፍጅት የሚያስደነግጠውን ያህል በየዕለቱና በየሰዓቱ የተለያየ ችግር የሚገጥማቸውን ብዙ ሕጻናት አለማሰብ ተገቢ አይደለም። ከቤታችን ጀምሮ ለየአንዳንዱ ልጅ ደኅንነት የምንጨነቅ ከሆነ ልጆቻችን ሁሉ ደኅና ይሆናሉ። ትንሽ ትንሽ፣ ጥቂት በጥቂት መጎዳትን መታገስ እና አንድ ጊዜ እንደ ናዳ የሚወርድ ጉዳትን እንደ መዓትና ቁጣ መቁጠር ከአጥንታችን የደረሰ ጠባያችን ነው። በየዕለቱ ጥቂት በጥቂት መሞትን ከቁም ነገር አንጥፈውም፣ ተያይዘን ስናልቅ ደግሞ “እግዚኦ እግዚኦ” እናበዛለን። “ዝምታ ለበግም አልበጃት፣ ሐምሳ ራሷን ሆና አንድ ነብር ፈጃት” እንዲሉ ሐምሳ ፍየል በአንዴ ሲያልቅ እንጂ አንድ-በአንድ ሲያልቅ ብዙም አይገደንም። የበደል እና የግፍ ትንሽ የለውም። በአንዱ የተደረገ በሁሉም ተደረገ፣ በአንዱ የደረሰ ግፍ በሁላችንም የደረሰ ነው። የአንድ ሰው መጎዳት የሁሉም መጎዳት ነው።

ሕጻናት በሕጻንነታቸው ለዕድሜያቸው በሚመጥን መልኩ እንዲኖሩ እንጂ ገና በዚያች ጨቅላነታቸው “ምን ልብላ? ምን ልጠጣ፣ ምን ልልበስ? በምን እስክሪብቶ ልጻፍ?” የሚል ጭንቀት ውስጥ ሊገቡ አይገባም። በርግጥ ብዙዎቻችን ያደግንበትን ሁኔታ ስንመለከተውና በሌላው ዓለም ልጅ ምን ያህል ዕድል እንደሚያገኝ ስንገነዘብ ቁጭት መፈጠሩ ግድ ይላል። “ዝም ብለህ የኛን ከምዕራባውያኑ የማነጻጸር አባዜ ተጸናውቶሃል” ለሚለኝ አዎ ከኛ ካነሱት ጋር በማነጻጸር ባለችን ድህነት መጽናናት አይስማማኝም እለዋለኹ። ከኬኒያ እንበልጣለን፣ ከሰሃራ በታች ካሉት አገሮች እንሻላለን፣ ከኤርትራ በጣም እንልቃለን እያሉ ራስን በማሞኘት አላምንም። ሰው ሊኖርበት ከሚገባው ደረጃ ጋር ማነጻጸር እንጂ በችግር ውስጥ ካሉትና የኑሮ ማጥ ውስጥ ከተዘፈቁት ጋር ራስን ማነጻጸር ለምንም ዕድገት የሚያበቃ አይሆንም። የዛሬ አበባዎች የምንላቸው ልጆች እንደ አባባ ተስፋዬ ተስፋ ገንቢ አባባል “የነገ ፍሬዎች” እንዲሆኑልን እንጂ በአበብነታቸው እንዲጠወልጉ፣ እንዲረግፉ የማንም ወላጅ አንጀት አይፈቅድም። ከግማሽ በላይ ዜጋዋ ሕጻን፣ ወጣት፣ ሴት ለሆነባት አገር ልጆች ትልቅ አጀንዳ ሊሆኑ ይገባል።

 

 

    

© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ.የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ማተም አይገባም::

 

 

 

 

6 comments:

Anonymous said...

The Article combined with the speech of Mr. President is touching. I wonder that more or less the same period of the time the children has been killed and before so many years Herods has done the same thing to find the little baby who was born in his city, the devil who worked at that time still continue to destroy the innocent one even in our days. I think the killer is a product of the society and I believe that we whereever we are need to contribute to change the society and try to have good products of human being as far as behaviour is concerned. Let the soul of all rest in peace.

Anonymous said...

"ሕጻናትን በየት/ቤታቸው በመሣሪያ የሚገድላቸው ወንጀለኛ በአገራችን አለመኖሩ ትልቅ ነገር ነው። ነገር ግን ልጆች በቀጥታ የጥቃት ሰለባ አለመሆናቸው ብቻ ትልቅ እፎይታ አይሰጥም። በምግብ እጦት ከት/ቤት ሰልፍ ላይ ራሳቸውን እየሳቱ ስለሚወድቁ ሕጻናት “አዲስ ጉዳይ” ሰፊ ዘገባ እንዳስነበበችን ይታወሳል። “ምን በልተን እንማር?” ማለታቸውንም እንዲሁ። እንደ አገር ልጆቻችንን መመገብ የማንችል ነን፤ ይህ እየሆነ ያለው በኢትዮጵያ ነው።" Thanks ... nice view and interesting article.

Anonymous said...

you write about the children of USA, because they get the medias coverage after what happened there.It is known Media has a great influence on things. I know children are Innocent and do not deserve this type of things. I always wish it doesn't happen. But why you do not say any thing about children of Syria, Palestine, Afghanistan and others? Are they different when they bombed from the sky? Please, be rational with things we have to do and let us raise our voice for the neglected one.

Anonymous said...

Obama Replied with tear What If this question was asked for our ex prime Mese Zeawi or Ethiopia Government ….He will say … the Government has made sever research on this issue then we understood the kid with gun was not normal he has brain problem …. Obame speech was as father … as family Good Quality

Anonymous said...

PPLEASE WRITE ABOUT THE eot CHURCH.dON`T BE SILENT!

set said...

efrem minew tefah ,tsafilin anbabian eyetebekin new