Monday, December 10, 2012

ሦስቱ ባዶ ወንበሮች (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ ወንበር እና ዙፋን ብዙ መገለጫ አለው። ወንበር ሲባል ሁላችን ራሳችንን የምናሳርፍበት ማንኛውም መቀመጫ ማለት መሆኑ እንዳለ ሆኖ “ወንበር” ብዙ አንድምታ እንዳለው እናውቃለን።

ለምሳሌ ፍርድ ቤት ገብተን “የግራ ወንበር፤ የቀኝ ወንበር” ሲባል ብንሰማ ትርጉሙ “የግራ ዳኛ፣ የቀኝ ዳኛ” መሆኑ ይከሰትልናል። ምናልባት ወደ አብነት ት/ቤት (ቆሎ ት/ቤት) ጎራ ብለን “ወንበር ተዘርግቷል፤ ወንበር ታጥፏል” ሲባል ብንሰማ “ትምህርት ተጀምሯል፣ ትምህርቱ ተጠናቋል” ማለት ነው። “እገሌ ወንበር ተከለ” ከተባለ ደግሞ “መምህር ሆነ፣ አንድ የትምህርት ዘረፍ ለማስተማር ጀመረ” ማለት ይሆናል። ሥልጣን ባለበት አካባቢ “እገሌ የእገሌን ወንበር ይፈልጋል” ከተባለ …. ያው … ሥልጣንም ከሆነች፣ ኃላፊነትም ከሆነች … ሊቀማ የተዘጋጀ አለ ማለት ነው።

አንድ ታሪክ

እዚህ በአሜሪካ የምርጫ ፉክክር ሰሞን ሁለት ታላላቅ የፓርቲዎቹ ጉባዔያት ተካሂደው ነበር። የሁለቱም ፓርቲዎች ዓመታዊና ፕሬዚዳንታዊ እጩዎቻቸውን የሚያጸድቁባቸው ወሳኝ ጉባዔዎች። ታዲያ፣ ከሁለቱ በአንዱ፣ በሪፐብሊካን ዓመታዊ ጉባዔ ላይ “ራምኒን ለማስተዋወቅ፣ ተመራጭ ለማድረግ” የቀረቡት ዝነኛው የሆሊውድ ኮከብ ክሊንት ኢስትዉድ (Clint Eastwood) ንግግራቸውን ሆሊዉዳዊ ድራማ አስመስለው ቀርበዋል። ሰውየው በንግግራቸው ጣልቃ፣ ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር ክርክር ቢጤ ያደረጉበት ትዕይንት አስደማሚ ነው። በርግጥ ኦባማ በቦታው አልነበሩም። እርሳቸውን እንዲተካ የተደረገው ገጸባሕርይ “ባዶ ወንበር” ነበር። ኢስትዉድ ሲያወሩ ወደ ወንበሩ እየዞሩ “እንደ ሰው” እያናገሩት ነበር። እናም በትዕይንቱ የተሳለቁ ሰዎች “Obamachair” የሚል ቃል ፈጥረው (ObamaCare የሚለውን ለውጠው) ሲዘባበቱባቸው ሰንብተዋል። “ካረጁ አይበጁ” እያሉም አሹፈውባቸዋል። ወደ ኢንተርኔት ገባ ብላችሁ “ኦባማቼር” ብትሉ ጉዱን ታዩታላችሁ።

ሌላ ታሪክ

እንዲህ በዐቢይና ታላቅ ጉባኤ ላይ በክብር የሚቀመጥ “ባዶ ወንበር” የማውቀው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅ/ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ነው። ጉባዔው በፓትርያርኩ መሪነት የሚስተናበር ቢሆንም መሪውና ወሳኙ መንፈስ ቅዱስ ነው ከሚለው አስተምሮ በመነሣት በጉባዔው ውስጥ በመጎናጸፊያ የከበረ አንድ ባዶ “ዙፋን” እንደሚቀመጥ አባቶች ይናገራሉ። ወንበሩ ከርዕሰ ጉባኤው፣ ከባዔው ሊቀ መንበር፣ ከፓትርያርኩ ጀርባ ይቀመጣል። ማንም ሰው አይቀመጥበትም። መንፈስ ቅዱስ የጉባዔው አካልና መሪ መሆኑን ያጠይቃል። “ባዶው ወንበር” ተምሳሌታዊ ብቻ ሳይሆን አማናዊ ትርጉም ያለው ሐሳብ ነው። በሌሎቹ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትም ይሁን ሲኖዶሳውያን በሆኑ ካቶሊክን በመሳሰሉ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህ ትውፊት ይኑር አይኑር አላወቅኹም።

የአቶ ኢስትዉድ ባዶ ወንበር እና ሃይማኖታዊ ትርጓሜ ያለው የቤተ ክርስቲያን “ባዶ ዙፋን” በይዘትም፣ በተምሳሌትም ይለያያሉ። የመጀመሪያው “ወንበር” ለጊዜው በዚያ ቦታ ያልተገኘ ሰውን ወክሎ እንዲጫወት የተደረገ ገጸ ባሕርይ ሲሆን ሁለተኛው ግን በርግጥም “እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን አለ፤ ይመራናል” ብሎ በማመን የሚደረግ ነው።

ሦስተኛ ታሪክ

ታዲያ የባዶ ወንበር ነገር ለሦስተኛ ጊዜ ራሴን “ቂው” ያደረገኝ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ም/ቤት ተገኝተው መልስ ሲሰጡ የተቀመጡበትን ቦታ ባየኹ ጊዜ ነው። “ምናልባት አቀራረጹ ይሆን?” ብዬ አተኩሬ ለማየት ሞከርኩ። በርግጥም አቶ ኃ/ማርያም የተቀመጡበት ቦታ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በሚቀመጡበት ቦታ አልነበረም። የአቶ መለስ “ወንበር” (ሁለተኛው ተርታ ቁጥር አንድ) ባዶዋን ቁጭ ብላለች። ደርሶ ተቺ፣ ደርሶ ነቃፊ ላለመሆን ለራሴ ሁሉንም ሎጂካዊ አመክንዮዎች ለማየት ሞከርኩ። በዚህም ብል በዚያ ያቺ “ወንበር” ባዶ የሆነችበት ምክንያት ግልጽ አልሆነልኝም። መቸም እንደ አቶ ኢስትዉድም፣ እንደ ቅ/ሲኖዶሱም እንዳልሆነ እናውቀዋለን። ታዲያ ለምን ባዶ አደረጓት?

በየትኛውም የሥልጣን ወንበር ላይ ለሚቀመጥ ሰው፣ እርሱ በሚያልፍበት ጊዜ ተተኪው በርሱ ቦታ እንደሚቀመጥ፣ እንኳን ዛሬ “ዲሞክራሲያውያን” ነን ብለን ቀርቶ በነገሥታቱም የተለመደ ነው። “ተቀመጥ በወንበሬ፣ ተናገር በከንፈሬ” እንዲል “መተካካቱ” ሲመጣ ከነሙሉ ክብሩና ግዴታው ሁሉ እንጂ በግማሹ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር የመተካት ልምድ የሌላት አገራችን እርሟን ከዚያ ሰዓት ስትደርስ የትኛውን ጥላ የትኛውን እንደምታንጠለጥል የቸገራት ይመስላል። በሌሎች ጉዳዮች ሲሆን “በሕንድ እንዲህ ሲደርግ ዓይተን ነው፣ ጎረቤታችን ኬኒያ እንኳን እንዲህ ነው የምታደርገው፣ ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ስዊዘርላንድ እንዲህ ናት” እንደሚባለው በዚህ ጉዳይ ማጣቀሻ ለመፈለግ የተሞከረ አይመስልም።

በመጀመሪያ። የጠ/ሚኒስትሩ ቤተሰቦች ቤተ መንግሥቱን ለአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ላለማስረከብ “ግብግብ” መግጠማቸውን “ጠላት የሚባለው ዳያስጶራው” ብቻ ሳይሆን “የታመኑ የውጪ አገር ፈረንጅ ጋዜጠኞች” ሳይቀሩ ሲተቹ ሰንብተዋል። እንደ መንግሥት ሳይሆን እንደ ግለሰብ ሳስበው እንኳን 20 ዓመት 2 ዓመት ከምኖርበት አፓርታማ ስቀይር እንዴት እንደሚከብድ አውቀዋለኹ። “ይኼ ሁሉ ዕቃ መቼ የሰበሰብኩት ነው?” ማለት የተለመደ ነው “ልሸክፍህ” ሲሉት። የሆነው ሆኖ የቤት ርክክቡ “ሰላማዊ” በሆነ መንገድ መጠናቀቁ ተገቢም፣ የሚጠበቅም ነው።

ቤቱ ይለቀቅ እንጂ፣ እንደማንኛውም የመሪ ቤት “የሚነቃነቁ” እና “የማይነቃነቁ” ነገሮች መኖራቸው ይታወቃል። መተካካት ስለተባለ ብቻ ኋላ የመጣው የፊተኛውን ጫማና ኮት አድርግ አይባልም። የፊተኛው ሲጠቀምባቸው ከነበሩት ዕቃዎች መካከል ለመታሰቢያነት በሙዚየም ሊቀመጡ የሚገባቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። አገሪቱን 20 ዓመት ያስተዳደሩት ጠ/ሚኒስትር (እንደተባለው በስማቸው ሙዚየም የሚቆም ከሆነ) ይጠቀሙባቸው የነበሩት የቢሮ ዕቃዎች ወዘተ ወዘተ መሰብሰባቸው አይቀር ይሆናል።

ይሁን እንጂ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር መንግሥታዊ ኃላፊነትን በሚረከቡበት ወቅት ከነሙሉ ክብሩ እንጂ በጎዶሎነት መሆን አይገባውም። በፓርቲ ሥርዓታቸው ለቀድሞ የፓርቲ ሊቀመንበራቸው ክብር ሲሉ የፓርቲያቸውን “ወንበ ባዶ” ማድረግ ይችላሉ። የመንግሥት ሥልጣን ግን አገራዊ እንደመሆኑ ለግለሰቡ የሚሰጠው ክብር የሰውየውን ማንነት ከግምት ውስጥ ሳያስገባ መሆን አለበት።

እውነቱን ለመናገር የፓርላማው ባዶ ወንበር ከቀጥተኛ ትርጉሙ ይልቅ ተምሳሌታዊነቱ (Symbolism) የበለጠ ትርጉም ይሰጠኛል። አቶ ኃ/ማርያም በመለስ ወንበር አለመቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን ያልተረከቡት ሌላም ብዙ ነገር እንዳለ ማሳያ ይመስላል። ቢሯቸውስ “ግዴለም የድሮው ቢሮዬ ሆኜ እሠራለዅ” ወይም “አንዲት ወንበር በጎን በኩል አስቀምጡልኝ” ብለው በደባልነት ገብተው ይሆን?

“ከልት”/Cult መፍጠር

ሳስበው ሳስበው መለስን “ኢትዮጵያዊው ኪም ኤል ሱንግ” ለማድረግ እየተሠራ ይመስለኛል። ኪም ኤል-ሱንግ እ.ኤአ. ከ1948-1994 ድረስ የአገሪቱን አመራር ጨብጠው የዘለቁ መሪ ነበሩ። ከ1948-1972 ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከ1972-94 ደግሞ ፕሬዚዳንት ነበሩ። ርሳቸው በሥልጣን ላይ ብቻቸውን በተቀመጡባቸው ዓመታት አሜሪካ 10 ፕሬዚዳንቶችን፣ እንግሊዝ 14 ጠ/ሚኒስትሮችን፣ ሶቪየት ኅብረት ሰባት መሪዎችን፣ ጃፓን 21 ጠቅ/ሚኒስትሮችን፣ ጎረቤቷ ደ/ኮሪያ 6 ፕሬዚዳንቶችን አስተናግደዋል።

ሞት አይቀርምና ሲሞቱ ልጃቸውን ለልጃቸው አሸጋግረው አልፈዋል። እርሳቸው በበኩላቸው “ታላቁ መሪ"The Great Leader" (በኮሪያኛ Suryong) የሚል ቅጽል ተቀጽሎላቸዋል። ከዚያም ባሻገር በሕገ መንግሥት ደረጃ የተቀመጠ የአገሪቱ “ዘላለማዊ ፕሬዚዳንት” ተብለው ተሰይመዋል። የልደት ቀናቸውም ከዓመታዊ አገሪቱ በዓላት እንደ አንዱ በይፋ እንዲከበር ተሰይሟል።

በየአደባባዩ፣ በየታላላቅ ሕንጻዎች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በምክር ቤት ወዘተ ወዘተ ፎቶግራፋቸውን ከመደበኛ ይዘት እጅግ ከፍ ባለ መጠን እያሳተሙ መስቀል የገጽ ግንባታ ሳይሆን “ከልት”/Cult መፍጠር ነው። አሁን ባለው ይዘት መለስ ዜናዊን ኪም ኤል-ሱንግ ማድረግ ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለቤተሰባቸው ክብር አይሆንም።

“የመለስ ራእይ” ከሚለው ጀርባም የሚኖረው ይኸው “ዘላለማዊነት” የተመኙለት መሪ እና ኢትዮጵያዊ-ኪም አል ሱንግ የመፍጠር ሐሳብ ነው። ፓርቲው “ራእዩ” በትክክል የገባቸው እና ያልገባቸው፣ ራእዩን የተቀበሉና ያልተቀበሉ፣ የራእዩ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች በሚል ፍረጃ ውስጥ ለመግባት አፋፍ ላይ ይመስላል። ነገ ማንም ሰው ያለምንም አመክንዮ “ራእዩን ባለመደገፉ ብቻ” ወንጀለኛ ሊባል ይችላል። ኢሕአዴግ የታገለው የፓርቲ ዓላማ ነበረው። መለስም ያንን አይተው ነው የፓርቲው አባል የሆኑት። አሁን ግን መመሪያቸው የመለስ ራእይን መቀበል እና አለመቀበል “ማስቀጠልና አለማስቀጠል” ሆነ ማለት ነው?

በነገራችን ላይ “ማስቀጠል” የሚለው ቃል ሁሌም ያስፈግገኛል። ቋንቋ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል በሚለው የሥነ-ቋንቋ ሀ-ሁ እንዳምን ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱ እንዲህ ያሉት ቃላት ናቸው። “ማስቀጠል” የሚል ግስ ተፈጠረ ማለት ነው? ለነገሩ ሁሉም “አስቀጣይ” ከሆነ ማን “ቀጣይ” ሊሆን ነው? ቃሉን “መገደብ” በሚል ብትተረጉሙት ሁሉም “አስገዳቢ” ከሆነ ማን “ገዳቢ” ሊሆን ነው። ሁሉ ከሆነ ቃልቻ ማን ይሸከማል ስልቻ አለ ያገራችን ሰው።

 

ይቆየን - ያቆየን።

 


10 comments:

Anonymous said...

Amazing....I am so impressed with your explanation.May God help you to write us more..

Anonymous said...

በአካል ባላየውም በቴሌቭዥን ስመለከት ሁሉም የፓርላማ ወንበሮች አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ የአንዱ ከአንዱ አይበልጥም፣ አያንስም፣ መቱን የተደረደሩ ይመስለኛል፡፡ ነገር ቆፋሪ ካልሆንክ በቀር ይህን የወንበር ልዩነት ብዙም ትኩረት የሚያሰጠው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አገራችን ዙፋናዊ ሥርዓት ብትከተል ኖሮ የአልጋ ወራሽ /የዙፋን ወራሽ/ በሚል ትኩረት ይስብ ነበር፡፡ ሌላው ባለ ራዕዩ መለስ እንደሌሎቹ መንግሥታት እነሆ በመንግሥቴ ይድላኝ ያላለ የዓለማችን ምርጥ ብቸኛ መሪ ነው፡፡ ይህ በየመንገዱ በየአደባባዩ የሚሰቀሉት ምስሎቹ ጊዜያዊ ናቸው በፀሐይና በዝናብ አርጅተው በራሳቸው ጊዜ ይነሳሉ ወይም ይወድቃሉ፡፡ በዛ ላይ ሕዝቡ የራሱን ኢንተረስት (ፍቅር) ለመግለጽ ይመስለኛል ይህን ያደረገው፡፡ ሌላው አስደንጋጭ ሃሳብህ ““የመለስ ራእይ” ከሚለው ጀርባም የሚኖረው ይኸው “ዘላለማዊነት” የተመኙለት መሪ እና ኢትዮጵያዊ-ኪም አል ሱንግ የመፍጠር ሐሳብ ነው።” በጣም የሚገርም ሃሳብ ነው ያለህ፡፡ በኢትዮጵያችን የመለስን ዓይነት አስተሳሰብ፣ አመራር፣ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ በፖለቲካ፣ በሶሻል፣ በኢኮኖሚ፣ በፌደራል ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ የሚተካከለው መሪ በኢትዮጵያ በታሪክ ተጽፎ አንብቤም ሆነ በዘመኔም አይቼ አላውቅም፡፡ በአገራችን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በማንነታቸው ተሸማቀው ይኖሩ የነበሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእኩልነት የፓርላማ ወንበር ያገኙበት፣ የአንድ ብሔርና እምነት የበላይነት የከሰመበት፣ በታሪክ የተዘነጉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንነታቸው የኮሩበት፣ በቋንቋቸው የተዳኙበት፣ ባሕላቸውን ማንነታቸውን ለዓለም ያሳዩበት፣ እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ ለካ ያሉበት ሁኔታ የተፈጠረበት ሥርዓት ኢትዮጵያችን መቼም መቼም አስተናግዳ አታውቅም፡፡ ታዲያ ለምርጡ ኢትዮጵያዊ መሪ ለዘለዓለም ሲታወሱ ቢኖሩ ምንድነው ችግሩ፡፡ ለአንተ ላይገባህ ይችላል ግን የመለስ ሞት እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በብዛት አሉ፡፡ ምናልባትም የሕዝባችንን ¾ የሚሆኑ፡፡ አበቃሁ፡፡

Anonymous said...

አታስቀኝ ባክህ ወዳጄ።

Anonymous said...

Sew ybelesh wechi kemasaye alu! Yelushin besemash--------!!!
Demissie

Anonymous said...

ግሩም ድንቅ ዕይታ ነው። ለእኔ። በእርግጥ ጥሩ አልሠሩም፣ ለአገሪቱ ዕድገት አልደከሙም አንልም። በአንጻሩ ኢትዮጵያችንን እንደ አሜባ ሴል ከፋፋፍለው ሕዝቡን በቋንቋና በዘረኝነት ወጥመድ ተብትበው የማንተዋወቅ እስኪያስመስለን ድረስ ማድረሳቸው ... በአንድነት ለኖሩ ሕዝቦች እንደ ረመጥ እሳት የፈጃቸዋል። ምን ይደረጋል! ታዲያ አንዴ፣ ሁለቴ ሦስቴ ... ተለቅሶላቸው በክብር አርፈዋል። ዝንተ ዓለም እያነሱ እንዲህ ነበሩ እንዲህ ሊያደርጉ አስበው ነበር እንዲህ እንዲህ እየተባለላቸው ስማቸው የትየለሌ መድረሱ በእውነት ትዝብት ነው! ኧረ ይበቃል! እርግጠኛ ነኝ ጸሐፊው እንዳሉት የወንበሩ ባዶ መሆን ሌላ አንድምታ ሳይኖረው አይቀርም። በረታ አለቃዬ

Anonymous said...

Addisu
እዉነት ለመናገር የጠ/ሚኒስትር መለስን ሰብዕና የተረዳነዉ ከሞቱ በኃላ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ አሁን አሁን የማይመች እየሆነ የመጣዉ ነገር በተገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ መለስን ማንሳት ነዉ፡፡ አሁን ያሉት ሰዎች ስራ የላቸዉም ወይስ ….. ከትላልቅ ባላስልጣናት ጀምሮ ታች እስካሉት ካድሬዎች (ገብቶዋቸዉም ይሁን ሳይገባቸዉ) “የመለስን ሌጋሲ ማስቀጠል” የሚሉት አሰልቺ አባባል አላቸዉ፡፡ እባካችሁን ባላስልጣናትና ካድሬዎች መለስን መዉደዳችሁን በወሬ ወይም ፎቶ በመስቀል ሳይሆን በስራ አሳዩ፡፡ መለስ ለራሱ ሳይኖር የሞተ መሪ ነዉ በቃ! ለቁንጫዉም ለቅማሉም የመለስን ስም ጠርቶ ይቻላል እንዴ? ስላለፈዉ ትታችሁ ስለሚቀጥለዉ አስቡ፡፡ እንደዉ ብቻ ሌጋሲ ሌጋሲ በማለት መደንፋት ለነገዋ ኢትዮጲያ ምንም ጥቅም የለዉም፡፡

Anonymous said...

very nice article , i love it.
Thank you. D. epherm.

ብርሃኔ ግርማይ said...

Please try to arrange a reply form. Some of the comments need to be replied. ከዚያም:-

ውድ ወዳጄ ጥሩ ብለሀል:: በርታልን:: አሁን በአገራችን የሚታየው ሁሉ በሌሎች ጭፍን ኮሚኒስት አገሮች ሲደረግ የነበረው ነው::የእነ ሌኒን;ስታሊን;ሂትለር;ጋዳፊ... በየቦታው መመለከም ምክንያት ይህው ይመስለኛል::በነገራችን ላይ ኢዲያሚን ዳዳን ከማምለክ ባልተናነስ የሚውዱት ስዎች ዩጋንዳ የሄድኩ ጊዜ አጋጥመውኛል::ዕድሜውን ሙሉ አንድ አይነት ነገር ብቻ ሲስማና ሲመለከት የኖረ ደጋፊ እንደ መለስ ዓይነቱን አረመኔ ቢያመልክ አይፈረድበትም:: ለዚህም ነው የአንዳንድ ጭፍን ደጋፊዎች አስተያየት ከሰውዬው ማንነትና ከእውንታው ርቆ የሚታየው::አምናለሁ አንድ ቀን የነበረው እንዳልነበር ይሆናል:: እየገነቡት ያለው የውሸት ተራራ ሁሉ ይደረመሳል::

Addis Bezuwork said...

betam girum eyeta!!!

Anonymous said...

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የደረሰበትን ጭቆና፣ ጦርነት፣ ጠኔና ድህነት ስንመለከት በመለስ ዜናዊ መሪነት ወደ አዲስ ከፍተኛ ተስፋና ዕድል ከፋች የታሪክ ምዕራፍ መሸጋገራችን ይታያል፡፡ ያም ሆኖ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለብልጽግና በኢትዮጵያ የተጀመረው ትግል ገና ከሁሉም አያሌ ጥረት እንደሚጠይቅ አያከራክርም፡፡ በነባርና በበለፀጉ ዲሞክራሲያዊ አገሮችም ሆነ በቅርቡ አስደናቂ እድገት ባስመሰከሩ (ለምሳሌ ቻይናና ሕነድ) የነጻነትና የእኩልነት ጥያቄዎች አጠጋቢ መልስ አላገኙም፡፡
በመለስ መሪነት ፈር ለያዘው ለፌዴራሊዝም ሥርዓት ምስጋና ይግባውና፣ በፊት በተወለዱበት ቀዬ መብቶቻቸውን ተነፍገው አሌ የተባሉ ወገኖች፣ ኢትዮጵያን አሌ በማለት ፈንታ አንድ ላይ በመሆን እሙን የሆነና በሰላማዊነት የተቃኘ ፖለቲካዊ ሥርዓትን በመተባበር ለመዘርጋት የተዘጋጁ ሆነዋል፡፡ ፌዴራሊዝምን የሚቃወሙና ያለፈውን “ ደግ ዘመን ” በቅሬታ የሚናፍቁ ወገኖች አልጠፉም፡፡ እንዲህ ላሉት አንዳንድ ወገኖች፣ ፌዴራሊዝም የቆየውን የኢትየጵያዊነት መለዮ ያቀጨጨ መስሎ ይታያቸዋል፤ በእነሱ አስተሳሰብ የቆየው የኢትዮጵያዊነት ሞገስ በክልላዊነት ወይም በጎጣዊነት ፈሊጥ ከጥንተ ርስቱ ተነቅሏል፡፡ እንዲህ ያሉ ወገኖች የሚዘነጉት ግን፣ ንጉሣዊው አገዛዝ የራሱን ትልቅነትና ሞገስ ከፍ አድርጎ ለማሳየት ሲጠቀምባቸው የቆዩት ድርሳኖችና ትእምርቶች ወይም ምስሎች ለሌሎች ብዙ ወገኖች ባዕድ መሆናቸውን ነው፡፡
ብሔራዊና ባሕላዊ ስብጥርን እንደተደምሳሽ ኋላቀር ቅርስ ወይም የአንዱ ክብር፤ የሌላው ውርደት አድርጎ ከመመልከት ተገላግለን፤ ዘላቂ የጋራ ፀጋ መሆኑን እነሆ ሁላችንም እየተመለከትን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህነት ለመላቀቅ አሁን ያለው መልካም ተስፋ በገጠሬው ሀብትና ጉልበት የተመሠረተ ነው፡፡ ይህንን መሠረት በፍጥነት ለማሳደግና ለማስፋፋት ከዚያም ወደ ኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የገጠሬው ሀብትና ጉልበት በዘመናዊ ጥበብና ቴክኖሎጂ መታገዝ ይኖርበታል፡፡ የዘመናዊ ጥበብና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዋናው ድልድይ ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ ታዳጊ ኢንዱስትሪውም የሚጠይቀው ይህንኑ ወጣት ትውልድ ነው፡፡ ስለዚህም አዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ ብልጽግናን ዕውን ለማድረግና በዚያውም አገሩንና ሕዝቡን ከድህነት ጨለማና ውርደት ለማዳን እጅግ ሰፊና የሚያጓጓ፤ የትኛውም የቀድሞ የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ያላገኘው፤ ታሪካዊ ዕድል አለው፡፡ ይህ ተስፋ ሰጭ ጅምር ሥራዎችን በድፍረት ያስጀመሩት ብልሁ መሪ መለስ ዜናዊ በወጣቱ፣ በሕጻናቱ፣ በሴቶቹ፣ በገበሬው፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ለዘላለም ሲታወሱ ቢኖሩ ሲያንሳቸው ነው እንጂ አይበዛባቸውም፡፡