Tuesday, December 18, 2012

የሚያስታርቁ ብፁዓን ከሆኑ - የሚታረቁትስ? (ኤፍሬም እሸቴ - PDF)፦ የተረጋጋ ባሕር። ማዕበል የሌለበት። እንዋኝህ ቢሉበት፣ በጀልባ ቢንሸራሸሩበት፣ አሣ ቢያሰግሩበት፣ ቢዝናኑበት … የሚመች …። እንደ ስምጥ ሸለቆ ኃይቆቻችን ያለ … የሰፋ፣ የሰከነ፣ የተረጋጋ፣ የተንጣለለ ውኃ። የረጋ ሕይወት፣ የተረጋጋ ማኅበረሰብ እንደዚያ ነው። …

በጥንታውያን ገዳማውያን አበው ታሪክ ከተጻፉ ታዋቂ ምሳሌዎች አንዱ በረጋ ውኃ ተመስሎ ይነገራል። ከዕለታት በአንዱ ቀን፣ አንዱ ወጣኒ ገዳማዊ (ጀማሪና ተማሪ የገዳም ሰው) ምክር ፍለጋ ወደ አንዱ አረጋዊ አባት ዘንድ ሄደ። የተማሪው ጥያቄ “ውስጤ ተረጋግቶ በገዳም መኖር የምችለው፣ በጎውንና ክፉውን መለየት የምችለው እንዴት ነው?” የሚል ነበር። አረጋዊው መምህር መልሱን በተግባር  ሊያሳዩት ፈለጉ። እናም ውኃ የተቀመጠበት ሰፊ ሳፋ መሳይ ነገር አቅርበው ራሱን ውኃው ውስጥ እንዲመለከት አዘዙት። ነገር ግን ሳፋውን በጃቸው እየናጡ ውኃውን ያነቃንቁት ነበር። ጀማሪው ገዳማዊ በጠራው ውኃ ውስጥ የተሰባበረ የራሱን ፊት ተመለከተ።

ቀጥሎም የሳፋውን ውኃ እንዲረጋ ካደረጉ በኋላ ራሱን እንዲመለከት አደረጉት። አሁን ግን ኩልል ባለው ውኃ ውስጥ የጠራ የራሱን ፊትና ገጽ ተመለከተ። ጥያቄውንም በዚሁ መልስ ሰጡት። ጥርት ያለ ሐሳብ እንዲኖርህ ብትሻ ውስጥህን መጀመሪያ አረጋጋ፤ ከሁካታ፣ ከቱማታው ተለይተህ ለራስህ ጸጥታን አስለምድ። ከዚያ የራስህን ማንነትና ስህተትህንም አጥርተህ መመልከት ይቻልኻል። ንውጽውጽታ በበዛበት ኅሊና የጠራ ሐሳብ ማግኘት አይቻልም። እንዴት ተደርጎ?

አንድ ግለሰብ በውሳጣዊ ማንነቱ በሚነሣ ሐሳብ ምክንያት አጥርቶ ማየት፣ አስተውሎ መጓዝ፣ ሰክኖ መኖር እንደሚሣነው ሁሉ አንድ ማኅበረሰብም በውሳጣዊ ሁኔታው ምክንያት አጥርቶ ማየት፣ አስተውሎ መጓዝ፣ ሰክኖ መኖር ሊሳነው ይችላል። ከራሱ ያልታረቀ ሰው ራሱን ጎድቶ ለሌላው እንደማይረባው ሁሉ ማኅበረሰብም ጤናማነቱ ካልተጠበቀ “ከመ እንስሳ” ከመኖር ያለፈ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል።

ባደጉትና ባላደግነው አገሮች መካከል ያለው አንደኛው ልዩነት ይህ ይመስለኛል። የተረጋጋ ማኅበረሰብ “ለነገ”፣ ለመጪው ትውልድ ብሎ ማሰብ ይችላል። ከአንድ ወር በኋላ የምትደርሰውን ጎመን ብቻ ሳይሆን ከዓመታት በኋላ የሚያፈራውንም ተክል ይተክላል። ዛሬ እንብላ እንጠጣ፣ ነገ ለምታልፍ ዓለም፣ ነገ ለምንሞተው (“ንብላዕ ወንስተይ ጌሰመ ንመውት”) ብቻ ሳይሆን ለነገ፣ ለከነገ ወዲያ፣ ለጡረታ ዘመኔ፣ ለልጅ ልጆቼ ቅርስ የሚል ውሎ የሚያድር ሐሳብ ያመነጫል።

ለሀብት-ለሀብት ከሆነ ወርቅ ተንተርሰው፣ አልማዝ ላይ ተቀምጠው፣ ድፍድፍ ነዳጅ ከጓሯቸው ተቀብሮ የሚኖሩ ብዙ አገሮች አሉ። ከኮንጎ እስከ ሴራሊዮን፣ ከሶማሊያ እስከ ካሜሩን ችግሩ የተፈጥሮ ሀብት አይደለም። በየዕለቱ ቦንብ እንደ እንጉዳይ የሚፈላባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ቢያንስ በነዳጅ ሀብት አይታሙም። በከርሰ ምድር ሀብት ይህ ቀረሽ የማትባለው ሩሲያ፣ የአፍሪካ ትልቋ ናይጄሪያ ወይም ደቡብ ሱዳን ገንዘብ ሊቸግራቸው የሚችሉ አገሮች አይደሉም። ነገር ግን የተነዋወጹ ባሕሮች፣ ያልተረጋጉ ሕዝቦች፣ ባለህበት እርግጥ ከማለት ያለፈ ሊዘልቁ የማይችሉ አገሮች መሆናቸው ነው የማዕበሉ ንውጽውጽታ በምን ይርጋ?

በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ለዚያ አገር ሕዝብ ሰላማዊ አንድነት በጎ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ብዙ አካላት አሉ። ከነዚህም መካከል ሃይማኖታዊ እና ማኅበረሰባዊ ተቋማት (ሲቪክ ተቋማት) ዋነኞቹ ናቸው። መንግሥታት በፖሊስና በወታደር ኃይሎቻቸው ከሚያመጡት ሰላምና መረጋጋት ይልቅ ሃይማኖታዊና ሲቪክ ተቋማት የሚያሰፍኑት ሰላም የተሻለ፣ ተዓማኒና ዘላቂ ነው። ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ጥንታዊ አገሮች ከመንግሥት መዋቅሮች ይልቅ እነዚህ ሃይማኖታዊና ማኅበረሰባዊ ተቋማት የተሻለ ተደራሽነትና ታማኝነት ነበራቸው። ይህ ተደራሽነት በበጎ ጎኑ ብዙ አዎንታዊ ፋይዳዎችን ሊያበረክት የሚችል የጤናማ ማኅበረሰብ ጥሩ ሀብት ነው። በዚህ መሠረት ላይ ማነጽ ከተቻለ በዳበረ ባህላዊ ሀብቱ የሚኮራና ራሱን የቻለ ኅብረሰተብ መፍጠር ይቻላል። የሕዝብ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ማንነቱ መነካት የሌለበት አንድም ለዚህ ነው። መብቱም ነው። የማንነቱ መገለጫ።

“ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ” እንደሚባለው “በአገርህ ያለውን የሃይማኖታዊና ሲቪክ ተቋሞች አያያዝ ንገረኝና የአገርህን ሁኔታ ልንገርህ” ማለት ይቻላል። እነዚህ ተቋማት በነጻነት፣ በስፋት እና ሁሉን ባገናዘበ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ሊያገኛቸው የማይችላቸውን ዘርፈ ብዙ ጥቆሞች ሊሰጡት ይችላሉ። ኅብረተሰቡም የሰከነ ኑሮ ይኖራል። ተቋማቱ ነጻነት ከሌላቸውና ማነቆ የሚበዛባቸው ከሆኑ ደግሞ የዚያ ሕዝብ የአንድነቱ አያያዥ ባህላዊ ገመድ ዕለት ወደ ዕለት እየሳሳና እየተበጠሰ ይሄዳል። ውሎ አድሮ በብዙ ገንዘብ ሊገኝ የማይችል አገራዊ ሀብት ይከስማል። በተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል፣ በድንበርተኞች መካከል፣ የሚታየው አለመግባባትና ጦር መማዘዝ እየሰፋ ከመሔዱም በላይ የአገር አንድነት የሚባለው ትልቅ ቁም ነገር ጥያቄ ላይ ይወድቃል።

በዚህ ረገድ ካየነው ኢትዮጵያውያን የእምነት ተቋማትና ሲቪክ ተቋማት በዘመናችን እንደሚገባቸውና እንደሚጠበቅባቸው የተረጋጉ እንዳልሆኑ እንመለከታለንኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት አሥርት የዘለቀ አስተዳደራዊ ቀውስ ውስጥ ስትዳክር ቆይታለች። በእስልምና እምነት ውስጥም እንዲሁ የዘለቀ ችግር ቢኖርም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተነሣው ነውጥ ብዙዎች ለእስር ዳርጓል፣ የእምነቱ ተከታዮች በየአርቡ ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ። በሲቪክ ተቋማት በኩል ይህ ነው የሚባል በነጻነት የሚንቀሳቀስ አገራዊ ተቋም አለ ማለት ያስቸግራል። ነጻ ሚዲያው ከዓመት ዓመት እየተዳከመና እየመነመነ ብልጭ ድርግም ማለት ይዟል። ጋዜጠኞችን በእስር በማጎር ትልቅ “ዝና” ካላቸው የዓለም አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ወዘተ ወዘተ

 በሃይማኖቱ በኩል የጠቀስነውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በአብነት ስንመለከት በውስጥ ያለው መከፋፈል ሥር ከመስደዱ የተነሣ ሁለት “ሲኖዶስ” እስከማቋቋም መደረሱ ይታወቃል። ይኸው ችግር ይፈታ ዘንድ ለረዥም ጊዜ የተደረጉ ሙከራዎች ፍሬ ሳያፈሩ ቆይተው አሁን ግን የተሰነጠቀውን ለመጠገን ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ታይቷል። ከኅዳር 26-30/2005 ዓ.ም ድረስ በዳላስ ቴክሳስ በተደረገ የዕርቅና የሰላም ጉባዔ ለ20 ዓመታት ላለመተያየት ሲገዘቱና ሲገዛዘቱ የነበሩ አባቶች ፊት ለፊት ተገናኝተው ተወያይተዋል። አብረውም ጸልየዋል። በዳላስ በጉባኤው የተገኘው ሕዝብም ደስታውን በይፋ ሲገልጽ ሰንብቷል።

በዚህ ጉባዔ ላይ ተወያዮቹ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ቢነጋገሩም ዋነኛ የሆነው ጉዳይ ግን በስደት የሚገኙት የአራተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ጉዳይ ነበር። የጋራ መግለጫቸው ላይ እንደተጠቀሰው የቀድሞው ፓትርያርክ ወደ አገራቸው ስለሚመለሱበት ሁኔታ የሚያስማማ ሐሳብ ላይ መድረስ አልቻሉም። ከአገር ቤት የመጡት ልዑካን “ሙሉ ክብራቸውና ጥቅማጥቅማቸው እንደተሟላላቸው በሚፈልጉት ቦታ ይቀመጡ” ሲሉ በውጪ አገር የሚገኙት አባቶች ደግሞ “ወደ መንበረ ፕትርክናቸው ተመልሰው እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው በፓትርያርክነት ይምሩ” የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

ነገሩ በዚሁ ሳይቋጭና ሳይወሰንበት ቢቆይም የሐሳብ ልዩነቱ እንደከዚህ በፊቱ ተጣልተው እንዲለያዩ አላደረጋቸውም። “ፈግጠው - ፈግጪው” አለመባባላቸው ብቻ ሳይሆን ለየምልዓተ ጉባዔዎቻቸው አቅርበው ውሳኔ ለመጠየቅና በድጋሚ ከአንድ ወር በኋላ በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ለመገናኘት ወስነዋል። በብዙዎች አንድምታም “ተስፋ ሰጪ” ጉባዔ እንደነበር ተወስቷል። በሁለቱም በኩል ያሉት “ምልዓተ ጉባዔዎች” ውይይቱ በቀና  መልኩ እንዲቀጥል ማድረግ ከቻሉ የዘመናችንን አንድ ወሳኝ የልዩነት በር ይዘጋሉ ማለት ነው።

ይህንን የሰላም ውይይት በድጋሚ ማንሣት ያስፈለገው ጉዳዩ ከሃይማኖታዊ አጀንዳነትም የዘለቀ ብዙ አገራዊ አንድምታ ስላለው ነው። ከፍ ብለን እንደጠቀስነው ቤተ ክርስቲያኒቱ የአገሪቱን አንድነት ከሚጠብቁ ዋልታዎች አንዷ ናት። መዳከሟና ማኅበረሰባዊ ፋይዳዋ መቀነሱ የሚጎዳው እምነቱን ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና በጎ ኅሊና ያላቸውን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ነው። ከዚህ አንጻር የእምነቱ ተከታይም ሆነ ሌላው ኢትዮጵያዊ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ጉዳይ ከቁምነገር ሊጥፈውና ሊከታተለው ይገባል። የእምነቱ ተከታይ ምእመንም ነገሩን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ለተቀመጡ ጥቂት እምነቱ መሪዎች ብቻ መተው አይገባም። እንደ መሪነታቸው የሚሉትን መስማትና መከተል ቢገባም አንድነትን የሚያክል ቁምነገር መፈጸም ሲያቅታቸው ግን ምእመኑ መጠየቅ ይኖርበታል።

“እንትንን በእንትን ላይ ማነሣሣት” ካልተባለብኝ በስተቀር በሰሜን አሜሪካ ባሉ ካህናትና ምእመን በኩል ያለው “አንድ የመሆን” ፍላጎት በአገር ቤት ባሉት አባቶችና ምእመናን ዘንድም እንዲንጸባረቅ ይጠበቃል። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው “የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው”፤ የሚታረቁትም እንዲሁ። እስከዛሬ ስለሚያስታርቁት ብጽዕና ስናነብ ኖረናል፤ ለሚታረቁት ብጽዕና መስማት ያለብን አሁን ነው። የሚያስታርቁ ብፁዓን መሆናቸውን ዕድሜያቸውን በሙሉ ሲያስተምሩ የኖሩ አባቶች፣ አሁን ደግሞ እነርሱም በመታረቅ “ብጽዕናን” በተግባር ያሳዩ። የሚታረቁ ብፁዓን ናቸው።

ይቆየን -  ያቆየን።

 

 


© ይህ ጽሑፍ ተቀንጭቦ በሮዝ አሳታሚ ኃ.የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ማተም አይገባም::


 

 

 

 

8 comments:

ብርሃኔ ግርማይ said...

"መንግሥታት በፖሊስና በወታደር ኃይሎቻቸው ከሚያመጡት ሰላምና መረጋጋት ይልቅ ሃይማኖታዊና ሲቪክ ተቋማት የሚያሰፍኑት ሰላም የተሻለ፣ ተዓማኒና ዘላቂ ነው" ጥሩ አባባል:: አገር ቤት ያሉትን አባቶቻችንን አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸው ችግሮች ያሉ ይመስለኛል::
፩.በሁሉም ነገር ውስጥ እጁ ከሌለበት እንቅልፍ የማይዘው የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና
፪.የራሳችው የአባቶቻችን ትልቅ ፍርሀት
፫.በውጭ ያሉትንም አባቶች ግትርነት ሳንረሳው ማለት ነው::
የቅዱሳን አምላክ ይርዳን::

Tsegaye Girma said...

Well written!

asesbe said...

ትላለህ ብዬ የጠበኩት ሌላ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት አባቶችን ብጹአን ከማለት እስክንድር ነጋን ብጹእ ማለት ይቀለኛል። እነዚህ ጳጳሳት ተብዬዎች ገሚሶቹ ፈራን ብለው ምዕመን በትነው ይፈረጥጣሉ: ሌሎቹ ደግሞ ሚሊዮኖች የሚያወጡ ቪላዎች እየገነቡ አንድ ነገር ብል መንግስት አሸባሪ ብሎ ንብረቴን ይቀማኛል ብለው የሚፈሩ ሆድ አደሮች ናቸው። አንተና መሰሎችህም ከቤተክርስቲያን ይልቅ ለማኅበራችሁ ስለምትጨነቁ ያልበላንን ታካላችሁ። ዛሬንኳን የጻፍከውን መልስና አንብበው እስኪ ማለት የፈለግኽውን ሳትል ስንት አገር አዞርከን

ALEMAYEHU TENKIR said...

Betam des yilal. Thank you ABABAAAA

Anonymous said...

Asebe,
What were your expectation? Esti tenesh negeren.

Anonymous said...

Good view. I like ur & Daniel's writings.

Anonymous said...

የሃይማኖት አባት ለመባል መመዘኛው ምንድነው፣ መጠምጠም፣ እድሜ፣ ስልጣን ወይስ ሌላ ተመሳሳይ፡፡ በግሌ ሽማግሌ የረከሰበት፤ ሃይማኖትም የተዋረደበት፤ ቤተመቅደስም መሸቀጫ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ለትልቁም ለትንሹም ገንዘብ ያሳወረው፤ ግፍ የሚሰራ የማይወቀስበት ጭራሽ ተፈርቶ የሚከበርበት ነው፡፡ ሁሉንም ለእግዚአብሄር ብንሰጥየሃይማኖት አባት ለመባል መመዘኛው ምንድነው፣ መጠምጠም፣ እድሜ፣ ስልጣን ወይስ ሌላ ተመሳሳይ፡፡ በግሌ ሽማግሌ የረከሰበት፤ ሃይማኖትም የተዋረደበት፤ ቤተመቅደስም መሸቀጫ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ለትልቁም ለትንሹም ገንዘብ ያሳወረው፤ ግፍ የሚሰራ የማይወቀስበት ጭራሽ ተፈርቶ የሚከበርበት ነው፡፡ ሁሉንም ለእግዚአብሄር ብንሰጥ

Anonymous said...

የሃይማኖት አባት ለመባል መመዘኛው ምንድነው፣ መጠምጠም፣ እድሜ፣ ስልጣን ወይስ ሌላ ተመሳሳይ፡፡ በግሌ ሽማግሌ የረከሰበት፤ ሃይማኖትም የተዋረደበት፤ ቤተመቅደስም መሸቀጫ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ለትልቁም ለትንሹም ገንዘብ ያሳወረው፤ ግፍ የሚሰራ የማይወቀስበት ጭራሽ ተፈርቶ የሚከበርበት ነው፡፡ ሁሉንም ለእግዚአብሄር ብንሰጥየሃይማኖት አባት ለመባል መመዘኛው ምንድነው፣ መጠምጠም፣ እድሜ፣ ስልጣን ወይስ ሌላ ተመሳሳይ፡፡ በግሌ ሽማግሌ የረከሰበት፤ ሃይማኖትም የተዋረደበት፤ ቤተመቅደስም መሸቀጫ የሆነበት ዘመን ነው፡፡ ለትልቁም ለትንሹም ገንዘብ ያሳወረው፤ ግፍ የሚሰራ የማይወቀስበት ጭራሽ ተፈርቶ የሚከበርበት ነው፡፡ ሁሉንም ለእግዚአብሄር ብንሰጥ