Friday, November 8, 2013

ዜግነት ዋጋ ሲያጣ

(PDF):- ዜጋህ እንደ ወንጀለኛ በየመንገዱ እየታፈሰ ሲታሰር፣ ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ሁኔታ ደግሞ አንዱ የአገርህ ልጅ በአረብ ፖሊስ ጥይት ተመትቶ ዋዕዩ በሚነድደው አስፓልት ላይ ደሙ ረግቶ ስትመለከት ምን ይሰማኻል? ይህ ሁሉ በሳዑዲ ምድር ላይ በየቀኑ እተፈጸመ መሆኑን ስትረዳ ውስጥህ ምን ይልኻል? ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከሌላ ዜግነት በቅጡ አን ይሆን?

Saturday, October 19, 2013

ያማርኛ ስልት

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ “መዝገበ ፊደል፤ የግእዝና ያማርኛ ቋንቋ መክፈቻ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ስለ አማርኛ ቋንቋ የሚከተለውን ብለው ነበር።

ያማርኛ ስልት እንደ ሕዝቡ አራት ክፍል ነው። አንደኛው የቤተ ክህነት፣ ኹለተኛው የቤተ መንግሥት፤ ሦስተኛው የነጋዴ፤ አራተኛው የባላገር። የቤተ ክህነት ዐማርኛ በሰዋስው ተመሥርቶ ባገባብ የታነጠ፣ በትርጓሜ የተቀረጠ፤ በግእዝ አባ የተጌጠ ነው። ከግእዝ በቀር ሌላ ባዕድ ቋንቋ አይገባበትም። የቤተ መንግሥት ዐማርኛ የግእዝ ትምርት ስላለበትና ሠራተኞቹ የካህናት ወገን ስለ ኾኑ እጅግ ስብቅል ነው፤ ቃላትን ኹሉ ‘እግዜር’ እንደ ማለት በማሳጠርና በማሳመር በማከናወን ይነገራል።

Friday, October 18, 2013

“እግዚአብሔር”

የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ፀሐፊ አለቃ ዘነብ “መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ” በተባለው መጽሐፋቸው ስለ እግዚአብሔር ሲገልጡ እንዲህ አሉ። እስቲ ተመልከቱት። ከሁሉ የበለጠ የወደዳችሁትን ሐረግ ድጋሚ በመጻፍ ኮሜንት አድርጉ። እንማማር።
 “እግዚአብሔር”
እግዚአብሔር ዕሩቅ ነው በጥበቡ አይታይምና፤
እግዚአብሔር መኮንን ነው ቶሎ ይፈርዳልና፤
እግዚአብሔር እንግዳ ነው ቶሎ ወሬ ይሰማልና፤
እግዚአብሔር ትሑት ነው ሰውን አይንቅምና፤
እግዚአብሔር መሀሪ ነው ቶሎ ይቅር ይላልና ሩኅሩኅ ነውና፤
እግዚአብሔር ሐኪም ነው፣ ሁሉን በጥበብ አድርጓልና፤
እግዚአብሔር ምስጉን ነው ፀሐይን ጨረቃን ፈጥሯልና፤
እግዚአብሔር ክቡር ነው ሰማይና ምድር የርሱ ናቸውና፤
እግዚአብሔር ባለጸጋ ነው ለሁሉ ይመግባልና፤

Saturday, October 12, 2013

ኳስ ብቻ ነው አትበለኝ

እግር ኳስ ወደድክም አልወደደክም፣ የሰሞኑን የኢትዮጵያን ሁኔታ ሳትመለከት ልታልፍ አትችልም። ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ አገሮች ድረስ ኢትዮጵያውያን ያሉበት አንድ ዓይነት ነው። ሬዲዮኖች፣ ድረ ገጾች እና የማኅበራዊ ድረ ገጾች በሙሉ በአገር ስሜት እንደሚናጡ ይታያል። ግን ይኼ ብቻ ኳስ ነው አትበለኝ። አንዲት ኳስ አገር ምድሩን እንዲህ አደረገችው አትበለኝ። ስፖርት ብቻ ነው አትበለኝ። ዕንባው በሙሉ የኳስ ፍቅር ብቻ ነው አትበለኝ። ከሕጻን እስከ አዛውንቱ ልቡን በፍቅር ሰቅዞ አገሬ ያሰኘው ኳስ ብቻ ነው አትበለኝ። ግዴለህም ይህ ፍቅር ከውስጥ ከአጥንት መቅኔ ፈልቆ የሚወጣ፣ ከልብ ልብ ውስጥ የሚፈልቅ የፍቅር ጠበል ዝም ብሎ የኳስ ነገር ነው አትበለኝ። ይህ የአገር ፍቅር ነው።  

Wednesday, September 25, 2013

Monday, September 23, 2013

ባንዴራ


Do you know the term ባንዲራ meaning "Flag" is a Spanish term "Bandera/"ባንዴራ? We use it in Amharic to say "Sendeq Alama/ ሰንደቅ ዓላማ". There are many other Spanish terms we use in our day to day Amharic. Eg. "Baño" = ባኞ Bath. Spaniards never came to Ethiopia or had a war with us. How did their words take foot in our vocabularies? Dear Linguists, please enlighten us on this.  ዛሬ IN ETHIOPIA የባንዲራ ቀን ተብሎ መከበሩን በማስታወስ::

Sunday, September 22, 2013

በመስቀል ሰሞን የመስቀል ወሬ

(PDF):- ሰሞኑን የተመለከትኩት አንድ ትንሽ ቪዲዮ በሰማይ ላይ የተመሳቀሉ እና የመስቀል ምልክት የሠሩ ደመናዎችን እያሳየ “መስቀል በሰማይ ተገለጠ”፤ ተአምር ነው እያለ ያትታል። ቪዲዮው በእጅ ስልክ ወይም በግለሰብ አማተር ካሜራ የተቀረጸ ነው። ቦታው የትና መቼ እንደሆነ ባይጠቁምም ፈረንጆች የተሰበሰቡበት መስክ ነገር ነው። አውሮፕላን ሰማዩን በየደቂቃው እየሰነጠቀ በሚበርበት በዲሲና አካባቢው ለሚኖር ሰው ጭሳቸውን በመስመር ለቅቀው ያለፉ የሁለት አውሮፕላኖች መስመር (መም) ነው ብሎ መገመት ቀላሉ ግምት ይሆናል። ቪዲዮውን “ሼር” ያደረጉን ሰዎች ግን ድንቅ ነገር እንደተከሰተ እንድንቀበል በብርቱ ፈልገዋል።

Sunday, September 15, 2013

ከሦስቱ አካኼዶች አንዱን

ይህቺ ግጥም ከዓመታት በፊት የሞነጫጨርዃት ነች። ዛሬ ድንገት ትዝ ስትለኝ ድጋሚ ጻፍኳት። ግጥሟን በመጀመሪያ የጻፍኳት እንዲህ ብዬ ነበር።
++
ምድር የእግዜር ምጣድ፣
ሰማይ ወስከምቢያዋ፤
እኔ እግዜር እንጀራ፣
የተሰፋሁ ከመሐልዋ።

·         የቃላት መፍቻ፦ ጠላ ይጠመቃል፣ ጠጅ ይጣላል፤ ክራር ይከረከራል፣ በገና ይደረደራል፣ እንጀራ ይሰፋል፤ ማስፋት - መጋገር።

Saturday, September 14, 2013

አንድ ሐሙስ የቀራቸው . . .

(PDF):- ብቻውን ከራሱ ጋር እየተነጋገረ፣ እየተሳሳቀ፣ እየተበሳጨም ይሁን እየተቆጣ የሚሄድ ሰው ምን ይባላል? ጨርቁን ጥሎ አልለየለትም፤ እግር-ተወርች በብረት በገመድ አልተታታም። ጽድት ያለ ይለብሳል። ምናልባትም ክሽን ያለ ገቢ ይኖረዋል። ቤተሰብ ያለው፣ ብዙ ሰው የሚያስተዳድር ብረት መዝጊያ የሚባልም ሊሆን ይችላል። ጭራሹን ካላበደ እና ሩብ ጉዳይ ከሆነ በአጭሩ ‘አንድ ሐሙስ የቀረው’ የሚለው ያስኬዳል።

Thursday, September 12, 2013

ኤርትራን በአቋራጭ

(PDF):- በሰሜን ምዕራቧ የአሜሪካ ከተማ በሲያትል ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የሚርመሰመሱበት አንድ ሰፈር አለ። ንግድ ቤቶቹ፣ ጋራዦቹ፣ ሬስቶራንቶቹ እና እዚያ አካባቢ የሚቆሙት መኪናዎች አብዛኛው የኛ ሰዎች ንብረት ናቸው። ከመንገዱ አንዱ ኮርነር ላይ “ስታርባክስ” ቡናመጠጫ ደረቱን ሰጥቶ መንገዱን ቁልቁል ይመለከታል። ወደ ውስጥ ሲገባ አንዱ ጥግ “የኢትዮጵያውያን ጥግ” ነው፤ ሌላው ደግሞ “የኤርትራውያን ጥግ”። አንድ ኢትዮጵያዊ ሲገባ እግሩ የሚመራው ወደራሱ አገር ጥግ ነው። መቀመጫ ባይኖርና በኤርትራው ጥግ በኩል ባዶ ቦታ ቢገኝ፣ ወደዚያ ለመሔድ አይሞክርም። ድንበር አይሻገርም። አንድ ኤርትራዊም እንዲሁ ወንበር ቢሞላበት ወደ ኢትዮጵያው ጥግ ለመሔድ አይሞክርም። ይህንን የሚነግረኝ ወዳጄ እየሳቀ ነው። ስታርባክሱ የባድመ ግንባር (ጦርነት የሌለበት፣ ነገር ግን ወታደሮቹ የተፋጠጡበት) አሊያም የአሰብ ቡሬ ግንባር መሰለኝ። ለመግባት አልፈለግኹም።

Monday, May 20, 2013

ሙስና የዘመናችን "የፍየል ወጠጤ ..." ናት?


ሕልምና የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተቃራኒው ይተረጎማል ...

(READ IN PDF):- የሰሞኑ ትልቁ አገርኛ ዜና (ቢያንስ በዳያስጶራው ዓይን) የመንግሥት ባለሥልጣናት በሙስና ምክንያት መያዝና መታሰር እንዲሁም የባሕር ዳሩ ሰላማዊ ሰዎች ግድያ ጉዳይ ነው። አገር ቤት የማይነበቡት ድረ ገጾችና የጡመራ መድረኮች (ብሎጎች)፣ የአካባቢ ሬዲዮኖችና ማኅበራዊ ድረ ገጾች (ለምሳሌ ፌስቡክና ትዊተር) የሚያወሩት ስለዚሁ ነው።

Wednesday, May 15, 2013

የማትረሣዋ የ1983 ዓ.ም ግንቦት ልደታ


ቅድመ ታሪክ
ከዕለታት በአንዱ ዓመት (ለነገሩ በ1983 ዓ.ም ነው)፣ ኮሌጅ ከመበጠሳችን በፊት፣ እንዳሁኑ አዲስ መንግሥት ሳይመጣ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የተባለ ሁሉ ወታደር ካልሆነ ተባለ። ከዚያም ክተት ታወጀና ብላቴ ከሚባል የጦር መንደር ገባን። ቱታ ከሸራ ጫማ፣ ትንሽ ቁምጣ ከነ ብርድ ልብስና አንሶላ ተሰጠን። ሌሊት 11 ሰዓት ሲሆን ስፖርት ተባለና ከመኝታችን በግድ እየረቀሰቀስን መሮጥ ያዝን።

Saturday, May 4, 2013

በሆሳዕና “ማክበር” - በቀራንዮ “መስቀል”


(PDF):- ታላቁ የክርስቲያኖች ጾም፣ ዐቢይ ጾም እነሆ የመጨረሻው “ሰሙነ ሕማማት”/ስቅለት ላይ ደረሰ። ለእምነቱ ተከታዮች የአጽዋማት ሁሉ በኩር እና ዋነኛ (ዐቢይ) እንደመሆኑ ከምንም በዓል በላይ በታላቅ መንፈሳዊ ስሜት የሚከበር ነው። የእምነቱ ተከታይ ላልሆነውም ወገን ቢሆን የሚኖረው ባህላዊ አንድምታ ከፍ ያለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ታሪኩን በደረቅ ንባብ ለሚመለከተውም ቢሆን ከዕለት-ተዕለት ሕይወቱ ጋር ሊያስነጻጽረው የሚችለው ብዙ ቁም ነገር እንደሚያገኝበት ጥርጥር የለኝም።

ፋሲካ፦ “ሥጋዊ ወመንፈሳዊ”(ኤፍሬም እሸቴ - ኢትዮጵያዊ/ READ IN PDF) በኢትዮጵያውያን ዘንድ በታላቅ ሁኔታ ከሚከበሩት በዓላት መካከል ትንሣኤ ወይም ፋሲካ አንዱና ዋነኛው ነው። ሃይማኖታዊ ትርጓሜው እና ምንነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ባህላዊ አከባበሩ እና ምንነቱም ከኢትዮጵያውያን ባህላዊ ማንነት ጋር በጥልቅ የተያያዘ ነው። እንኳን በአገር ቤት ያለው በሰው አገር ያለነውም እንኳን ብንሆን እንደ አቅሚቲ የአገር ቤቱን መንፈስ በያዘ ሁኔታ እናከብራለን። ስለዚህ ፋሲካው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሥጋዊ/ ባህላዊ አንድምታው ከፍ ያለ ነው ማለት ነው።

Saturday, April 13, 2013

ቼሪ በዲሲ፣ ባሕር ዛፍ - በሸገር


(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)፦ ቅዳሜ ኤፕሪል 13/ሚያዚያ 5 በዲሲ ከተማ ታላቅ የአደባባይ ክብረ በዓል ቀን ነው። በየዓመቱ በዚህ ቀን አይደለም የሚከበረው። የኢትዮጵያ ሊቃውንት እንደሚሉት “ኢይዐርግ - ኢይወርድ” ኖሮበት ሳይሆን ከአየሩ ሁናቴ ጋር የሚወጣ እና የሚወርድ በመሆኑ ነው። ስለ በዓሉ ጥቂት ላጫውታችሁ። በዚህ ሰሞን የሚከበረው ዓመታዊ የዲሲ የአደባባይ በዓል “የቼሪ ዛፍ ማበቢያ” (Cherry Blossom Festival) በዓል ሲሆን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎችና ከአገር ውስጥም የሚሰበሰቡ ቱሪስቶች የሚያደምቁት በዓል ነው። “ቼሪ” የጃፓኖች ዛፍ ስትሆን ወደ አሜሪካ ከመጣችና ከጸደቀች አንድ መቶ ዓመት ሊሆናት ነው። ታሪኩ እንደዚህ ነው።

Tuesday, April 9, 2013

አፈወርቆች(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)፦ ከሰሞኑ “ፋኖስና ብርጭቆ” የምትባለውን የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤልን ግጥም በፌስቡክ ገጼ ላይ ለጥፌ ነበር። “ስንቶቻችሁ ይህንን የክቡር / ከበደ ሚካኤልን ግጥም ታስታውሣላችሁ? በልጅነቱ ይህንን በቃሉ ይወጣ የነበረ አሁንም ያልረሣ ካለ እነሆ ካንገቴ ዝቅ ብዬ አክብሮቴን ልግለጽ” ከሚል ማስታወሻ ጋር። ለራሴ በገረመኝ መልኩ ብዙ ወጣት ፌስቡከሮች ግጥሙን በቃላቸው አሁን ድረስ እንደሚያውቁት በመግለጽ ትዝታቸውን አስፍረው ተመለከትኩ። ከእነርሱ መካከል ደግሞ ሁለቱ ስለ ግጥሙ ከማንሣት ባሻገር፣ ግጥሙን ደግም ክፉም ሳይሉ፣ ይልቁን ከበደ ሚካኤል ባንዳ እንደነበሩ አንስተው አለፉ። ነገሩ ገብቶኛል። “ግጥማቸው ምን ሸጋ ቢሆን፣ ያው የጠላት አገግጋይ ናቸው” የሚል አንድምታ አለው።

Monday, April 8, 2013

አገርን ፍለጋ(ዮሴፍ ዘካናዳ 06/04/2013/ ወደአገራችሁሂዱ ለተባሉት ህፃናት መታሰቢያ ትሁን/ PDF)

የጨርቋን ጫፍ ጥለት
በአቧራ ነትቦ ባንዲራ ያለበት
ጭምድ አርጎ ይዞ ህፃኑ ጠየቀ
ግራ ቀኝ እያየ እየተሳቀቀ
አገራችሁ ሂዱሰዎቹ የሚሉን
የት ነው አገራችን?
ጥለትሽ ላይ ያለው ያገርሽ መለያ
የት ናት ኢትዮጲያ?
የት ጋር ተጀምራ የት ጋር ነው ምታልቀው?
አፈርና ወንዙ ባህል ሐይማኖቱ ይት ጋር ነው ሚለየው?

Thursday, April 4, 2013

ድሀ ከሆኑ አይቀርስ - ልክ እንደ አቶ መለስ(ኤፍሬም እሸቴ/PDF)፦ ሰሞኑን በተካሔደው የኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ያደረጉትና በኢቲቪ የዜና ዕወጃ ላይ የቀረበው ንግግራቸው የማኅበራዊ ድረ ገጾች የመወያያም የመሳሳቂያም የመሳለቂያም ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር። “#SomeoneTellAzebMesfin” በሚል “ሐሽ ታግ/ #Hashtag” (ቅምር-ቃል ልበለው?) በትዊተር ላይ ኢትዮጵያውያን የግል ሐሳባቸውን ሲሰጡበት የቆዩት የወይዘሮዋ ንግግር ያተኮረው በአቶ መለስ ደሞዝና ድህነት ላይ ነበር።

Wednesday, April 3, 2013

“አይቴ ብሔሩ ለአማራ . . . የአማራ አገሩ ወዴት ነው?” ኢትዮጵያ አይደለምን?(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)፦ በንግግርም ይሁን በጽሑፍ ለማንሣትም ሆነ ለመጥቀስ፣ ለመወያየትም ሆነ ለመከራከር ከማይመቹኝ (discomfort እንዲል ፈረንጅ) የኢትዮጵያ ርዕሰ ጉዳዮች ሁሉ ዘርን፣ ብሔረሰብን የተመለከተው ዋነኛውና አንዱ ነው ጉዳዩ በዕለት ተዕለት የአገራችን ሕይወት ውስጥ ወሳኙ እና በሁነኛ መልክ ማኅበረሰባዊ ማንነታችንን እየበየነ እንዳለ እያወቅኹም እንዲህ እንደ አሁኑ በአደባባይ ለመውጣት ግን ብዙም አይቀለኝም። ምክንያቱ ሌላ ምንም ሳይሆን ጉዳዩ ያለው ስሱነት (sensitivity) ነው። አሁን ግን ላልፈው አልቻልኩም። አይገባምም። ለምን?

Wednesday, March 13, 2013

የጥቁሮች-ታሪክ ወር

(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)፦ በአሜሪካ የታሪክ ግጻዌ ውስጥ፣ ፌብሩዋሪ የተባለው ሁለተኛው ወራቸው “የጥቁሮች አፍሪካውያን-አሜሪካውያን ታሪክ ወር”/ Black History Month ተብሎ ይታወቃል። በጥቁር አሜሪካውያን የተፈጸሙ በጎ ተግባራት የሚታወሱበት፣ ለአገራቸው ጠቃሚ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ጥቁር አሜሪካውያንም የሚዘከሩበት፣ ባህላቸው፣ ልማዳቸው የሚወሳበት ወር ነው። ሥልጣኔ ማማ ላይ ቆማ ነገር ግን የጥቁር-ነጭ ልዩነት፣ በጥርጣሬ መተያየት እና የእኩልነት ነገር እልባት ባላገኘባት አሜሪካ አሁንም የማንነት ጉዳይ ትልቅ ጥያቄ ነው።

Sunday, March 10, 2013

ሮም: እንደጎበኘዃት


(ኤፍሬም እሸቴ - PDF)፦ከዚህ በታች የምታነቧቸው ሁለት ጽሑፎች በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጡ፣ ስለ ሮም ካየኹት የጻፍኳቸው የግል ጉብኝቴ ትውስታዎች ናቸው። የመጀመሪያው ጽሑፍ ሮም ስለነበረው የአክሱም ሐውልትና ስለ ኮሎሲየም የሚናገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሁሌም ስለሚገርኝ የሮማ ዋሻ ካታኮምቤ ያትታል። መልካም ንባብ።

አክሱም ሐውልትና ኮሎሲየም

 ባለፈው “ነገረ ቫቲካንን” አንስተን መጠነኛ ሐሳብ መለዋወጣችን ይታወሳል። እንግዲያው የፖፑ ነገር ስቦኝ ቫቲካን ካደረሰኝ እግረ መንገዴን ጣሊያን በሄድኩበት ወቅት ያየኹትን ባካፍላችሁ ብዬ አሰብኹ። ሮምን ከቫቲካን እንዴት ይለዩታል? ይኸው ከሰሞኑ እንኳን የግራዚያኒ ሐውልት ሲመረቅ ሁለቱ መቼ ተለያዩና? ኢትዮጵያን ሊወር የመጣው የሮማ ወታደር መድፉ በቫቲካን “እየተባረከ” እንደመጣስ መቼ ይረሳል? ስለ ፋሺስቶቹም ባናወራ ስለ ሮም ግን ብዙ የሚነገር ነገር ይኖራል። እነሆ እንዲህ ይቀጥላል።

Wednesday, March 6, 2013

For Bloggers: 10 Tips from Literature to Turn Your Blog into a Masterwork


10 Tips from Literature to Turn Your Blog into a Masterwork

(Written by Margaret Pincus)
There are three parts to a really great blog post. Thinking, writing and editing.

Thinking” is where you need to start if you want to write that article. Thinking abhors a vacuum. The inspiration has to come from reading journeys that stir the neurons and stimulate the emotions.

Tuesday, March 5, 2013

ሁለት እና አንድሁለት እና አንድ (PDF)
ከአንድ ሁለት ይሻላል
              ለመሸከም፣
ከሁለት አንድ ይሻላል
                ለመቆዘም።
አንድ ሁለት  ተሽሏል - ሲቦርቁ ሲደሰቱ፣
ሁለተኛው ከየት መጥቶ - ሲቸገሩ ሲንገላቱ።

(“ሁለትና አንድ”/ ኤፍሬም እሸቴ፤ ማርች 6/2013፤ የካቲት 27/2005 ዓ.ም፤ ሀገረ ማርያም ሜሪላንድ)

Monday, March 4, 2013

ክብሪት


(PDF)

ሞቷን በራሷ ተሸክማ
ሕይወቷን በሞቷ ቀምማ
እርሷ የኖረች ለታ
ብርሃኗን ለእኛ ሰጥታ
እርፍ ትለዋለች እስከዚያዉ
የክብሪት ሕይወት ይኼዉ።

(ዘለሰኛ ዘለክብሪት - ለሙከራ ፤ ኤፍሬም እሸቴ፤ 
ማርች 5/2013፤ የካቲት 26/2005 ዓ.ም፤ 
ሀገረ ማርያም ሜሪላንድ

Blog Archive