Tuesday, February 19, 2013

ነገረ ቫቲካን(ኤፍሬም እሸቴ - READ IN PDF)፦ ከሰሞኑ የመገናኛ ብዙኃን አርዕስተ ጉዳዮች መካከል የሮማው ፓፓ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ የመወሰናቸውና ይፋ ማድረጋቸው ዋነኛው ነው። ግዙፏ ቫቲካን በ600 ዘመኗ አይታው የማታውቀው አስገራሚ ዜና። ነገሩን እንደሰማኹ እኔም በጉዳዩ ግር ተሰኝቼ “እነርሱም ዘንድ በፖፕ ላይ ፖፕ የሚባል ነገር አለ እንዴ?” የሚል ገሚስ ቀልድ ገሚስ ኩሸት ያዘለ ሐሳብ ወደልቤ መጥቶ ነበር። (“በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ” እንደሚለው የቤተ ክህነት መጽሐፈ ንትርክ ወፖለቲካ)። በአገራችን “ማይንድ ሴት/mindset” ላለ ሰው ቶሎ ወደ ልቡ የሚመጣው ይኼ ቢሆን አይገርምም።

 

“Mindset” ስል እንዲያው አንድ ነገር አስታወሰኝ። ከዚህ በፊት በአንድ ጽሑፌ ላይ መጥቀሴን አስታውሳለኹ። እዚህስ ብደግመው ምን ይለኛል? አንዱ የአገራችን ሰው በጀርመን የገጠመው እውነተኛ ገጠመኝ ነው። ገና ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ሳለ አገር የሚያስጎበኘው አንድ ጀርመኔ (ከወሎ የመጣው ወሎዬ፣ የጎንደሩ ጎንደሬ ከተባለ የጀርመኑን ‘ጀርመኔ’ አልኩት) ተመድቦለት በባቡር ይዞት ሲሔድ ምድር ለምድር የሚነጉደው ባቡር በምን እንደሚንቀሳቀስ ማወቅ የፈለገው አበሼ “ባቡሩ በምን ኃይል ነው የሚንቀሳቀሰው?” ይለዋል። መላሹ ጀርመኔም “በኤሌክትሪክ ኃይል” ይለዋል። አበሼውም “መብራት ሲጠፋስ?” አለው። ጀርመኔ ቶሎ መልስ አልመጣለትም።

 

በመጨረሻ ጀርመኔው ሲመልስ ግን እንዲህ አለ፦ “አንተ! እንዴት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ መጣልህ? በጣም ጨለምተኛ ሰው ነህ፤ you are a pessimist person”። እርሱ መብራት መጥፋት የሚባለው “mindset” ውስጥ አይደለማ። የኛው ሰውዬ “መብራት ጠፋች፣ ውኃ ሔደች፣ ታክሲ ጠፋ፣ ስኳር ጠፋ” ሲል ስለኖረ (ስለሚኖር) በዚያው ስሌት ነው የባቡሩንም ሁኔታ የጠየቀው። ሰው ኑሮውን ይመስላል። ትምህርት ቤት ካስተማረው ኑሮ ያስተማረው … ይባል የለ? እንዲያ ነው።

 

ወደ ነገረ-ሮም ስንመለስ፤ የሮማው ፖፕ (Pope) እንዲህ ያለ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው በስፋት እየተተነተነ ነው። የካቶሊክ ቴሌቪዥን ጣቢያ “EWTN” የተለያዩ የአሜሪካ ግዛት ጳጳሶቻቸውን፣ የካቶሊክ ቲዎሎጂ ሊቃውንትን እና አማኞቻቸውን እየጠየቀ ስለነገሩ ምን እንደተሰማቸው ሲያወያይ ነበር። ብዙዎቹ የፖፑን ውሳኔ እያደነቁ “መንፈስ ቅዱስ አዲስ አባት በመንበረ ጴጥሮስ ያስቀምጥልናል” እያሉ ይናገሩ ነበር። በነገራችን ላይ ከ4 አሜሪካውያን አንዱ ካቶሊካዊ ነው።

 

ሌሎቹ ሚዲያዎች ደግሞ ከአሁኑ ቀጣዩ ፖፕ ማን ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ማን ሊሆን እንደሚገባ መላምታቸውን እያቀረቡ ነው። “ዋሺንግተን ፖስት” እና ሌሎቹ ጋዜጦች የፊት ገጽ ሽፋናቸው በዚሁ ዜና ተሞልቷል። ዋሺንግተን ፖስት በበኩሉ አውሮፓዊ ያልሆነ ፖፕ ሊመረጥ የሚችልበት አጋጣሚ መፈጠሩን አትቶ፣ እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከአርጀንቲና፣ ከጋና፣ ከፊሊፒንስ  ካርዲናሎችን ጠቅሶ አስፍሯል።

 

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ አላት። ይህንን ሁሉ የሚመሩት ቫቲካን የሚቀመጡት ፖፕ ናቸው። በየትም አገር ያለ ካቶሊክ ፓፑን ተቀብሎ እና አክብሮ ይኖራል። በዚህ የማይስማሙ፣ ከእምነታቸው ውስጥ አዳዲስ ነገር እንዲጨመር የሚፈልጉ ብዙ ካቶሊካውያን ቢኖሩም ይኼንን ያህል ተደማጭነት ማግኘት አልቻሉም። ለምሳሌ በአሜሪካ ያሉ ካቶሊካውያን የግብረ ሰዶማውያን ጋብቻ እንዲፈቀድላቸው፣ የሴት ካህናት እንዲሾሙላቸው፣ ያገቡ ሰዎች ቄስ መሆን እንዲችሉ (በካቶሊክ ቄሶች በሙሉ መነኮሳት መሆን ስላለባቸው) ቢወተውቱም የቀደሙት ፖፕ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛም ሆኑ የአሁኑ ቤኔዲክት 16ኛ ነገሩን ሳይቀበሉት ቆይተዋል። በዚህም “ወግ አጥባቂዎች ናቸው” እየተባሉ ይተቻሉ።

 

ቫቲካን በመላው ዓለም ተደማጭነት ካላቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ዋነኛዋ ትመስለኛለች። ቤኔዲክት 16ኛ “በቃኝ፣ ሥልጣኔን አስረክቤያለኹ” ከማለታቸው ፕሬዚዳንት ኦባማ ከአድናቆት ጋር ያለፉትን ዓመታት “አብረው ስለመሥራታቸው” አሞግሰው መግለጫ ያወጡላቸው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ቫቲካንን የመጎብኘት ዕድል ያጋጠማችሁ አንባብያን ይህንን የበለጠ ትገነዙባታላችሁ።

 

ቫቲካን በጣሊያን አገር ሮማ ከተማ ውስጥ ያለ ራሱን የቻለ ነጻ አስተዳደር ነው። በአንድ አገር ውስጥ ያለ ሌላ አገር ማለት ነው።  ሮምን ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ጎብኝቻታለኹ። ዕድሜ በሮማ ለሚገኙት ወዳጆቼ የትራንስፖርት ድምቡሎ ሳልከፍል የቱሪስት መዳረሻ የሆኑትን ቫቲካንንና ሌሎች ጥንታዊና ድንቅ ሥፍራዎቿችን በሙሉ የመመልከት ዕድል አጋጥሞኛል። በስዊዘርላንድ የክብር ዘቦች (Swiss Guards) የሚጠበቀው ቫቲካን ቤተ መንግሥትነትን ከቤተ ክርስቲያንንነት አጣምሮ የያዘ ትልቅ ባለ ግርማ ሞገስ አካባቢ ነው።

 

የቫቲካን ትልቁ መታወቂያ የሆነው የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን አካባቢው በትልቅ የሰረገላ ቁልፍ ቅርጽ የተከበበ ሰፊ አደባባይ ያለው ነው። ቁልፉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥተ ሰማያትን ቁልፍ ለጴጥሮስ እንደሰጠው ለማጠየቅ የተደረገ ነው። ወደዚህ የቁልፍ ቅርጽ ክልል ለመግባት ሁሉም ሰው በጥብቅ የፍተሻ በሮች ያልፋል። ወደ ትልቁ የቅ/ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ለመግባት ረዥም ሰልፍ መሰለፍ የተለመደ ነው።

 

ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ለመግባት ሲጠጉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሰውነታቸውን በሚያሳዩ ልብሶች (ቁምጣ፣ አጭር ቀሚስ፣ ጃፖኒ) መግባት እንደማይችሉ የሚያሳስብ በትልቁ የተለጠፈ ማስታወቂያ አለ። ድንገት ተራቁተው የሚመጡ ጎብኚዎች ሲገኙ አስጎብኚዎቹ ያዘጋጁትን የዝናብ ልብስ የመሰለ እስከ ቁርጭምጭሚት የሚደርስ የላስቲክ ልብስ ለመደረብ ይገደዳሉ። “ቱሪስት ስለሆነ እንደፈለገው ሆኖ ይግባ” የሚባል ነገር የለም። የውጪ አገር ሰው “ቱሪስት ንጉሥ ነው፣ እንደፈለገው ሆኖ ይግባ” የሚባለው የኢትዮጵያን ክቡር ሥፍራዎች ሲጎበኝ ብቻ ነው።

 

ቫቲካንን መጀመሪያ ያየኹት ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ከማረፋቸው፣ ቤኔዲክት 16ኛ ከመሾማቸው በፊት ነበር። ሹመቱ ሲካሔድ ቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ በሙሉ ሥርዓቱን በቀጥታ ስለሚያስተላልፉ ስለ ቫቲካን አስተዳደራዊ ሁኔታ የበለጠ ለመገንዘብ ዕድል ይሰጣል።

 

ቫቲካን እንደ ነጻ መንግሥት የምትቆጠር ስለሆነች በየአገሩ የሯሷ ኤምባሲዎች አሏት። አዲስ አበባን ጨምሮ። የአገሪቱ የበላይ ደግሞ ፖፑ መሆናቸው ነው። የሥራና የዕለት ተዕለት መግባቢያ ቋንቋቸው ጣሊያንኛ ቢሆንም በሕጋዊ ደብዳቤዎቻቸውና መግለጫዎቻቸው ላይ ላቲንን ይጠቀማሉ።

 

እንደ አገርነቷ ወታደርና ፖሊስም አላት። ወታደሩ ክፍል ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተቋቋመና በዋነኝነት በስዊዝ ወታደሮች የተሟላ ከነስሙም “የስዊዝ ዘብ” ተብሎ የሚጠራ ነው። ይሁን እንጂ ዋነኛ አገልግሎት ሥነ ሥርዓታዊ (በዓል አክባሪነት) ነው። አገሪቱን የመጠበቁ ዋነኛ ሥራ ዞሮ ዞሮ የጣሊያን ጦር ተግባር ነው።

 

ቫቲካን የሯሷ ገንዘብ የምታሳትም ብትሆንም ዋነኛ መገበያያዋ ዩሮ እንዲሆን ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ስምምነት አላት። የገቢ ምንጯም ከጎብኚዎች ጋር የተያያዘ ነው። ቴምብሮችን፣ እምነት መግለጫ የተለያዩ ቁሳቁሶችንና ሙዚየም መግቢያ ቲኬቶችን በመሸጥ ብዙ ገቢ ታገኛለች።

 

አገር እንደመሆኗ ዜግነት አብሮ ይመጣል። የቫቲካን ዜግነት አላቸው 1000 የማይሞሉ ሰዎች እንዳሉ ስለዚሁ ጉዳይ የሚያብራራ ጽሑፍ ያትታል። ዜግነቱ የሚሰጠው ለቫቲካን አገልግሎት ከመመደብ ጋር በተገናኘ ሲሆን ዜግነቱ የተሰጠው ሰው ዜግነቱን ቢተውና የሌላ የምንም አገር ዜጋ ባይሆን ደግሞ “ጣሊያናዊ” ተደርጎ እንደሚቆጠር ሕጋቸው ያዛል።    

 

ቫቲካን በከተማ ውስጥ ያለ ሌላ ከተማ፣ በመንግሥት ውስጥ ያለ ራሱን የቻለ ሌላ መንግሥት እንደመሆኑ በድንበር ተለይቶ ራስን ከመቻልና ነጻ ከመሆንም በላይ ያለው ውስጣዊ ነጻነት ለአገራችን ቤተ እምነቶች ትልቅ ትምህርት አለው። በተለይ 6ኛ ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ላለችው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሁነኛ አብነት ሊሆን ይችላል።

 

ተደጋግሞ እንደተነገረው የአገራችን የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ነጻነት ለመቀዳጀት ልቻሉ፣ በመግሥት ቀጥተኛ ወይም እጅ አዙር አስተዳደር ሥር ያሉ እንደመሆናቸው ይህንን ከመሰለው የሌላ አገር ሃይማኖታዊ ተቋም ብዙ ሙያ ሊቀስሙ ይገባቸዋል። የአገራችን ሰው “ሙያ ከጎረቤት” ያለውን ልብ ይሏል። የእምነት ተመሳስሎ እንደሌለ በታወቀና በተረዳ ማስረጃ ግልጽ ነው። እንዲቀስሙት የሚፈለገውም ትምህርት እርሱ አይደለም። ካቶሊካውያን አንድ ቢሊዮን ሕዝብ እያስተዳደሩ እኛ ግን የራሳችንን በንጽጽር ሲታይ ጥቂት ቁጥር ያለው አማኝ በቅጡ ማስተዳደር ያልቻልነው፣ የተከበረ አስተዳደራዊ ነጻነት ያላገኘነው በምን ምክንያት ነው?” ብለው ሊጠይቁ ይገባል።

 

እንደ ቫቲካን በድንበር የተከለለ ልዩ መብት የሚጠየቅበት ዘመን ላይ አይደለንም። ውስጣዊ ነጻነትን ማረጋገጥ ግን ያስፈልጋል። አሁን ያለው ራስን ያዋረደ እና ሙሉ ለሙሉ የመንግሥት ተላላኪነትን ያነገበ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚመጥን አይደለም። በዚህ ምስቅልቅል ውስጥ እየዳከሩና የምእመናቸውን ጥሪ ሁሉ አልሰማ እያሉ አዲስ መሪ (ፓትርያርክ) ለመምረጥ መነሣት ማንአለብኝነት ካልሆነ ሃይማኖታዊ አያሰኝም። ሃይማኖት ፈቃደኝነት ነው። ምእመኑን አልሰማ የሚል አስተዳደር አንሰማህም እንደሚባል ማወቅ አለበት። በጸብና በእምቢተኝነት የተወሰነን 6ኛ ፓትርያርክ የመምረጥ ውሳኔ ለማስፈጸም “ጸሎት አውጀናል” ማለትስ ከግብዝነት ሌላ ምን ስም ይገኝለታል? አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ” (ማቴ ፭፥፳፬) የሚለው ቤተ ክህነቶቹን አይመለከታቸውም?

 

ይቆየን - ያቆየን     

16 comments:

Anonymous said...

Dn Ephrem - Kale hiwot yasemalin! I have followed the news about the Catholic pope. But I have learnt a lot from your well articulated blog. Especially, I like the way you suggested about what could possibly be learnt to avoid the current administrative issue in our Church. Keep the good work up!

gabrieltbs2a2012blog said...

እናስ oriental orthodox ለምን በኣንድ ፓትርያረክ ኣንመራም?

Anonymous said...

very interesting


yeshi

Anonymous said...

yeraswa eyarerebat yesew tamaselalche malet le endate aynetu new.....

Tekalign Mengesha said...

1,“ቱሪስት ስለሆነ እንደፈለገው ሆኖ ይግባ” የሚባል ነገር የለም። የውጪ አገር ሰው “ቱሪስት ንጉሥ ነው፣ እንደፈለገው ሆኖ ይግባ” የሚባለው የኢትዮጵያን ክቡር ሥፍራዎች ሲጎበኝ ብቻ ነው።
2,የስጋን ፍላጎት ከመንፈሳዊዉ ማስበለጥና ለይቅርታ ቦታ አለመስጠት ከ፪ቱም ወገን የሚታይ ነገር ነው።

Anonymous said...


Anonymous said...
yeraswa eyarerebat yesew tamaselalche malet le endate aynetu new.....
February 20, 2013 at 7:43 AM

አገላለጽህ ጥሩ ነው ግን ያገላበጥከው መሰለኝ፡፡ ምናልባት እንዲህ ለማለት ፈልገህ እንደሆነ፣

1. "ኢትዮጵያ እያረረባት ለአፍሪካ ታማስላለች"
2. "ኢሕአዴግ እያረረባት በ11 በመቶ አብስየዋለሁ ትላለች"
3. "የክስ ማስረጃ ሲያጥራት በድራማ ታጣጣዋለች"

መጨመር ይቻላል፤ ግሽበቱ እንዳይጎዳን ይቅርብኝ

Anonymous said...

ዲ/ን ኤፍሬም

ስለ ቫቲካን አጠር አድርገህ ያቀረብክልን ዘገባ በጣም ጥሩ ግንዛቤ ስለሚያስጨብጥ ወድጄዋለሁ። ሁለት ትናንሽ አስተያየቶች ላንሳ።

1.ጀርመኔ የሚለው ቃል አወጣጥ አመጣጥህ ትክክለኛ አይመስለኝም። ኢትዮጵዬ አንልም ኢትዮጵያዊ እንጂ፣

2.የኛ አባቶች የ50 አመት የአስተዳደር ተሞክሮ ከቫቲከን ረጅም የአስተዳደር ልምድጋር በእኩል መታየት የሚችል አይመስለኝም። እኛ እኮ ገና ዳዴ እያልን ነው። ምናልባትም ቫቲካን በመጀመርያዎቹ የአስተዳደር ዘመንዋ ምናልባትም አውሮፓም የዲሞክራሲ የመንግስት አስተዳደር ባልሰፈነበት ወቅት ከነበራት ጊዜ ጋር ልናወዳድራት እንችል ይሆናል። ቫቲከንም እኮ በአንድ ወቅት የነበራት የተበላሸ አስተዳደር ለሉተራን እንቅስቃሴ መነሻ አንዱ ምክንያት እንደነረ መዘንጋት የለብንም።

Anonymous said...

i know u have ur own agenda on Ethiopia and on EOTC. U lost your track. you better be back to the track and live in desence.

Anonymous said...

1. "የእምነት ተመሳስሎ እንደሌለ በታወቀና በተረዳ ማስረጃ ግልጽ ነው። እንዲቀስሙት የሚፈለገውም ትምህርት እርሱ አይደለም።"

What do you mean by this? What is your difference with them?2. የጨው ገደል ሲናድ ሞኝ ይልሳል ብልጥ ያለቅሳል፡፡ Whether you like it or not the world is closing up on you Christians. You better wake up.

Adebabay A said...

"የተለየ አጀንዳ/i know u have ur own agenda on Ethiopia and on EOTC አለህ" ላልከኝ፤ እንዲየያው እንዲህ ጭፍን ያለ አስተያየት አልሰለቸህም? ወይ ተናገረው ወይ ተወው። ምሥጢር ያለ ስላስመሰልከው ሰው ማሳመን የምትችል መስሎህ ከሆነ ድብቅነትን ከዕውቀትና ከሊቅነት ከሚቆጥሩት ወገን አይደለኹም።

Anonymous said...

ሃዘኔ በዛ ስላንቺ
መቅነሽ ሲፈስ ስትደክሚ ስትረችቺ
አንቺ እናቴ እንዲያዉ በከንቱ ደከምሽ
ወጣሽ ወረድሽ ላይሳካ ላይሰምርልሽ
እደግልኝ ልጄ ብለሽ ደግፈሽዉ
በሌለ አቅምሽ ተቸግረሽ አድልበሽዉ
ዉለታሽን ረሳ በደነ ዞሮ ባንቺ ላይ ደገነ
ካጥፊዎችሽ ጋር አብሮ ጥፋትሽን አፋጠነ
ሁሉም ሆኑ እንደ ባዳ አንዱ እንኳ ያንቺ አልሆነ
ደብር ዓባይ ዙርአምባ ዜማ አስቀፅለሽዎ
ገለዓድ ዋሸራ ቅኔ አስመስጥረሽዉ
ጎንደር እስከ ሸዋ አንዴም ሳትሰለቺ
አንድምታና ዚቁን በፍቅር መግበሽዉ
በጎችሽ ላይ ብትሾሚዉ በትረ ሙሴ ብትሸልሚዉ
እሱቴ ምን ተዳዉ ድካም ፍቅርሽ መቼ ታየዉ
ተልእኮሽን መች የኔ አለዉ
ቀድሞ የተዘራበት እንክርዳድ ንፁህ ዘርሽን አመከነዉ
ጭንጫ ልቡ ድካምሽን መና አስቀረዉ
እናም እናታለም ላንቺማ ይታዘን ይለቀስ ባያሌዉ
ዘርተሸ መራራ ለለቀምሽዉ
ገዳይሽን ለታቀፍሽዉ
እረጉሙንም ለመረቅሽዉ
የዉር መሪ አበጅትሽ
በተስፋ ቢስ ተስፋ ጥለሽ
ሁሉም ጠፋ ገደል ገባ
ወገን የደም እንባ አነባ
ለከት ያጣዉ ኃጢአታችን ካምላክ ጸጋ ቢለያየን
ቅፅራችን ፈረሰ አዉሬም ተራኮተን
ጭላንጭሉ ብርሃን ጠፋ ጨለማዉ ወረረን
ከትናንቱ የዛሬዉ ከዛሬም የነገዉ አስፈራን
ሰላማችን ቢርቅ ቢከሽፍ ርእያችን
የያሪኮን ፍሬ ሙጥኝ ባሉ ከንቱ …ቻችን

Anonymous said...

I read Some of the comment, Like “ I know you have ur own Agend “ Which is nonsense for me He does not have any agenda All he wants to say is Before the pop election we need come up one point or some point (two synod) Reconciling…….Let he write whatever he likes May God Bless You and your Family Dn Ephrem keep writing We love you !! Good Example !!!!your are on the the track!!!!! Good Luck !!!!!

Anonymous said...

thanks Dn efrem

Anonymous said...

“ በዚህ ምስቅልቅል ውስጥ እየዳከሩና የምእመናቸውን ጥሪ ሁሉ አልሰማ እያሉ አዲስ መሪ (ፓትርያርክ) ለመምረጥ መነሣት ማንአለብኝነት ካልሆነ ሃይማኖታዊ አያሰኝም። ሃይማኖት ፈቃደኝነት ነው። ምእመኑን አልሰማ የሚል አስተዳደር አንሰማህም እንደሚባል ማወቅ አለበት። ” (Ephrem Eshete)

ይህን ቃል የተናገርከው ራስህንና ጥቂት የተቃዋሚ ቡድን ምዕመናንን ወክለህ እንደሆነ ልታውቅ ይገባሃል፡፡ በአጠቃላይ ምዕመኑን ወክለህ መናገር አትችልም፡፡ ምክንያቱ እኛ በኢትዮጵያ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ብቻ ነን ይህንንም ሆነ ሌላ ማለት የምንችለው፡፡ ዜግነቱን የለወጠ ስደተኛ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ በኛ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ሊበጠብጠን አይገባውም፡፡

እናንተ ጥቂቶቹ የደርግ ርዝራዥ የሆናችሁት ብቻ ናችሁ አራተኛው ፓትርያርክ እንዲመጡ የምትፈልጉት፡፡ ምክንያቱም ደርግ (መንግሥቱ ኃ/ማርያም) ጳጳሳቱን አስገድዶ አስፈርሞ አቡነ መርቆርዮስ እንዲመረጡ ማድረጉ ይህ ለማንም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ነው፡፡ እናንተም የያኔው ሥርዓት ፍልፍሎች ስለሆናችሁ ከሳቸው ውጭ ፓትርያርክ ለምኔ እያላችሁ ማቆሚያ የሌለው ጩኸት የምታሰሙት፡፡ እኛ በአገራችን ምድር የምንኖር ሕዝቦች አራተኛውን ወዲያ እዛው በፀበልህ ብለን 6ኛውን ፓትርያሪክ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ ጭራሽ ብላችሁ ብላችሁ ለአክራሪው እስላም ድጋፋችሁን እያደረጋችሁ ይችን ቅድስት ሀገር ልታረክሷት ላይ ታች ትላላችሁ፡፡ ምን ይህን መንግሥት ብትጠሉት ለእስላም አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ፡፡ በግራኝ መሐመድ ጊዜ የተቃጠለችው ቤተ ክርስቲያን አልበቃ ብሏት ነው ዛሬም ከግብጻዊ አክራሪ ጋር ተመሳጥራችሁ ልታጋዩዋት የተነሳችሁት፡፡ ወይ ነዶ ይላል ያገሬ ሰው፡፡

Anonymous said...

“ በዚህ ምስቅልቅል ውስጥ እየዳከሩና የምእመናቸውን ጥሪ ሁሉ አልሰማ እያሉ አዲስ መሪ (ፓትርያርክ) ለመምረጥ መነሣት ማንአለብኝነት ካልሆነ ሃይማኖታዊ አያሰኝም። ሃይማኖት ፈቃደኝነት ነው። ምእመኑን አልሰማ የሚል አስተዳደር አንሰማህም እንደሚባል ማወቅ አለበት። ” (Ephrem Eshete)

ይህን ቃል የተናገርከው ራስህንና ጥቂት የተቃዋሚ ቡድን ምዕመናንን ወክለህ እንደሆነ ልታውቅ ይገባሃል፡፡ በአጠቃላይ ምዕመኑን ወክለህ መናገር አትችልም፡፡ ምክንያቱ እኛ በኢትዮጵያ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ብቻ ነን ይህንንም ሆነ ሌላ ማለት የምንችለው፡፡ ዜግነቱን የለወጠ ስደተኛ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ በኛ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ሊበጠብጠን አይገባውም፡፡

እናንተ ጥቂቶቹ የደርግ ርዝራዥ የሆናችሁት ብቻ ናችሁ አራተኛው ፓትርያርክ እንዲመጡ የምትፈልጉት፡፡ ምክንያቱም ደርግ (መንግሥቱ ኃ/ማርያም) ጳጳሳቱን አስገድዶ አስፈርሞ አቡነ መርቆርዮስ እንዲመረጡ ማድረጉ ይህ ለማንም ኢትዮጵያዊ ግልጽ ነው፡፡ እናንተም የያኔው ሥርዓት ፍልፍሎች ስለሆናችሁ ከሳቸው ውጭ ፓትርያርክ ለምኔ እያላችሁ ማቆሚያ የሌለው ጩኸት የምታሰሙት፡፡ እኛ በአገራችን ምድር የምንኖር ሕዝቦች አራተኛውን ወዲያ እዛው በፀበልህ ብለን 6ኛውን ፓትርያሪክ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ ጭራሽ ብላችሁ ብላችሁ ለአክራሪው እስላም ድጋፋችሁን እያደረጋችሁ ይችን ቅድስት ሀገር ልታረክሷት ላይ ታች ትላላችሁ፡፡ ምን ይህን መንግሥት ብትጠሉት ለእስላም አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ፡፡ በግራኝ መሐመድ ጊዜ የተቃጠለችው ቤተ ክርስቲያን አልበቃ ብሏት ነው ዛሬም ከግብጻዊ አክራሪ ጋር ተመሳጥራችሁ ልታጋዩዋት የተነሳችሁት፡፡ ወይ ነዶ ይላል ያገሬ ሰው፡፡

ይህን ጽሑፍ የማታወጣው ከሆነ አንተም በፕሬስ ነጻነት የማታምን ሰው ነህ ማለት ነው፡፡

Anonymous said...

When are we going to learn to agree to disagree? When are we going to stop the name calling and stick to the facts and advance reasonable arguments? That is the only thing I can say after reading through some of the comments. If you have the time, please read Yilma Bekele's article on how low we have sunk as a society via the following link http://indepthafrica.com/debretsion-church-and-the-ethiopians/