Sunday, March 10, 2013

ሮም: እንደጎበኘዃት


(ኤፍሬም እሸቴ - PDF)፦ከዚህ በታች የምታነቧቸው ሁለት ጽሑፎች በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጡ፣ ስለ ሮም ካየኹት የጻፍኳቸው የግል ጉብኝቴ ትውስታዎች ናቸው። የመጀመሪያው ጽሑፍ ሮም ስለነበረው የአክሱም ሐውልትና ስለ ኮሎሲየም የሚናገር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሁሌም ስለሚገርኝ የሮማ ዋሻ ካታኮምቤ ያትታል። መልካም ንባብ።

አክሱም ሐውልትና ኮሎሲየም

 ባለፈው “ነገረ ቫቲካንን” አንስተን መጠነኛ ሐሳብ መለዋወጣችን ይታወሳል። እንግዲያው የፖፑ ነገር ስቦኝ ቫቲካን ካደረሰኝ እግረ መንገዴን ጣሊያን በሄድኩበት ወቅት ያየኹትን ባካፍላችሁ ብዬ አሰብኹ። ሮምን ከቫቲካን እንዴት ይለዩታል? ይኸው ከሰሞኑ እንኳን የግራዚያኒ ሐውልት ሲመረቅ ሁለቱ መቼ ተለያዩና? ኢትዮጵያን ሊወር የመጣው የሮማ ወታደር መድፉ በቫቲካን “እየተባረከ” እንደመጣስ መቼ ይረሳል? ስለ ፋሺስቶቹም ባናወራ ስለ ሮም ግን ብዙ የሚነገር ነገር ይኖራል። እነሆ እንዲህ ይቀጥላል።

 

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሮም ስሔድ አኩሱም ሐውልት ወደ አገሩ ለመመለስ ዝግጅት ላይ ነበር። ከነግርማ ሞገሱ፣ ደረቱን ለጥልያን ፀሐይ ሰጥቶ፣ በኢትዮጵያዊ ኩራት ሲጎማሸር ብዙ ዓመታት ቆይቷል። በዚያ ቦታ። እኔ የደረስኩ ጊዜ ወደ እናት አገሩ ሊመለስ ዐለት-ሰውነቱን በአንዳች ላስቲክ መሰል ነገር ከላይ እስከ ታች ግጥም ተደርጎ ተገንዞ ተጠርዞ ነበር። እንደ ደጋ አገር ገበሬ ከአፍ ጢሙ እስከ እግር ጥፍሩ ቢከናነብም የኛው አክሱም መሆኑ ብቻ የጠፋ ዘመዴን ያገኘኹ ያህል ደስታ አጭሮብኛል።

ሐውልቱ ከዓለም የምግብ ድርጅት (FAO) ቢሮ ፊት ለፊት ነበር የተተከለው። አካባቢው የጥንቷ ሮም ሳትሆን ዘመናዊቱ ሮም ባየለችበት አካባቢ ያለ እንደመሆኑ የኛው ሐውልት ያለ ተቀናቃኝ ከዓይን ውስጥ ለመግባት ችሎ ነበር። የጥንቷ ሮም ያልኩት ከተማይቱ የታሪክ መዝገብ እና የብዙ ሐውልቶች እና ጥንታዊ ኪነ ሕንጻዎች ባለቤት በመሆኗ ነው። የሰው ልጅ ድንጋይ ያሾረበት ከተማ ቢፈለግ መቸም እንደሮም የሚሆን ያለም አይመስለኝ። ግሪክን መቼ አየኸውና የሚል ብቻ ያሸንፈኝ ይሆናል። በታሪክ እንደሰማኹት፣ ፎቶዎችም እንዳየኹት ግሪክም እንዲሁ የድንጋይ ጠራቢዎች አገር ነበረች። ድንጋይ አለዝበው የሚገዙ ሰዎች አገር።

 

ጣሊያኖች ከአክሱም ሐውልቶች ሁለተኛውን ትልቁን ነበር ቆራርጠው ወደ አገራቸው የወሰዱት። ምናልባት የድል አድራጊነታቸው ምልክት ለማድረግ አስበው ይሆናል። በራሱ በሞሶሎኒ ትዕዛዝ የተደረገ እንደመሆኑ ከታሪክና ከቅርስነት አንጻር ያለውን ዋጋ ከመመልከት ይልቅ ለ40 ዓመታት ለብቀላ ሲዘጋጁላት የነበረችውን ኢትዮጵያን የማስገበራቸው አርማ ለማድረግ ሽቶ መሆን አለበት።

 

ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ ሮም ብዙ ሐውልቶች፣ የሐውልት ፍራሾች፣ ኪነ ሕንጻዎችና ጥንታውያን የጥበበ ዕድ ሥራዎች ያሉባት ከተማ ናት። የሮም ሐውልት እዚያ መቆሙ እኛን ያጎድለናል እንጂ ለእነርሱ ብዙም የሚጨምርላቸው ነገር አልነበረም።

 

“ሰው ባገሩ - ሰው ምድሩ፤ ቢበላ ሣር - ቢበላ መቅመቆ፤

ይከበር የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ”

እንዲሉ ሐውልቱም እንዲያ ያለኝ መሰለኝ። እውነት ነው። በአጠገቡ ከሚመላለሰው ወጪ ወራጅ ስንቱ ሰው በርግጥ ያ ባለ ታሪኩ የኢትዮጵያውያን ሐውልት መሆኑን ያውቅ ይሆን? ባይተዋርነቱ ከዓለት ገላው ተርፎ ለእኔም ተሰምቶኛል።

 

በሰው አገር ባይተዋርነቱ፣ እንዲያ ከሰለጠነው ዓለም ገብቶ ከመሐል አደባባያቸው ቢገተርም፣ ያ ዓለት-ገላው ጥንት እንደነበረው እንደ አፍሪካዊነቱ እርቃኑን ሳይሆን ላስቲክ ቢጤ መሸፈኑ ውበት አልሆንህ ብሎት፣ የአገሩን ራቁትነት፣ ዘመዶቹን፣ ወዳጆቹን እየናፈቀ የቆመ መሰለኝ። ብቸኛው አክሱም በደበበ ሰይፉ “ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ” (1967 ዓ.ም) ግጥም፦

እኔና ወንድሞቼ ሁላችን … ሁላችን፣

ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን

ይህ ነው አንድነታችን

ይህ ነው ባህላችን።” ያለኝ መሰለኝ።

 

እኔ ካየኹት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ያንን ላስቲክ ገላውን አውልቆ፣ አካሉን ከሦስት ቦታ አስመትሮ፣ በትልቅ ጢያራ እየተርገፈገፈ አክሱም እትብቱ ከተቀበረበት ገብቷል። አንዱ ወንድሙን እንደቆመ፣ ሌላኛውንም በተኛበት ሰላም ብሎ እርሱም ከቤተሰቦቹ ሐውልቶች ተቀላቅሏል።

 

አክሱምን ሐውልት አግታ የኖረችው ሮም ብዙ ድንቅ ድንቅ ኪነ ሕንጻዎች ስላሏት አገር ማየት የሚሻ ሮምን ከልቡ ቢጥፋት ደስተኛ ነኝ። ካሏት የታሪካዊ ኪነ ሕንጸዎች መካከል “ኮሎሲየም”/Colosseum የሚባለው ጥንታዊ ስቴዲየም ወይም አምፊቴያትር በመሐል ከተማ አለ። ቬስፓሲያን በተባለው ንጉሠ ነገሥት ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ 72 ዓ.ም  የተጀመረውና በ80 ዓ.ም በቲቶ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመው ይህ 50ሺህ ተመልካች የሚይዝ ግዙፍ አምፊቴያትር ድንቅ የሮማውያን ኪነጥበብ ውጤት ነው። ዕድሜ ጠገብ መሆኑና አሁን በአገልግሎት ላይ የሚገኝ ካለመሆኑ በስተቀር አሠራሩም ሆነ ዓላማው የዘመናችን ምርጥ ስታዲየሞች ዓይነት ነው። እዚያ ቦታ እግሩ የረገጠ ጎብኚ በአግራሞት ተደምሞ ፈዝዞ ቢቀር አይፈረድበትም።

 

የኮሎሲየም መገንባት ዓላማው መዝናኛ ዝግጅቶችን ለመመልከት ነው። እንደ ዘመናችን እግር ኳስን የመሳሰሉ ሌሎች ስፖርቶች ባልነበረበት ዘመን ሰዎችን ከሰዎች ጋር የሚያታግሉበት፣ ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚያመጧቸውን አውሬዎች አደን የሚያሳዩበት፣ ነጻ ትግልን የሚያካሒዱበት፣ ኋላም ክርስትና እየተስፋፋ ሲመጣም “አዲሱን እምነት” የሚከተሉትን ለአውሬዎች የሚጥሉበትና ትግሉን ሕዝቡ የሚመለከትበት አደባባይ ነበር ይባላል።

 

በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በእሳትና በሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የተለያዩ ጉዳቶች የደረሰበት አምፊቴያትሩ አሁንም ለታሪክ ምስክርነት ከፊል ደህና ጎኑን ይዞ አለ። የሮማ ሥርዓተ መንግሥት ምልክት ነውና በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ ትንቢቶችም ሲነገሩለት ቆይተዋል። በ8ኛው መቶ ክ/ዘመን የተነገረ ነው የሚባለው “ኮሎሲየም ከፈረሰ፣ ሮም ትፈርሳለች፤ ሮም ከፈረሰች ደግሞ ዓለም ይፈርሳል” የሚለው ሮምን የዓለም እንብርት የሚያደርጋት አባባል ከሁሉም ቀልቤን ስቦታል። ምናልባት አባባሉ ቀልቤን የሳበው በዘመናችን የተለመደው “እንዲህ እንዲህ ካልሆነ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ ትበታተናለች” የሚለው ትንቢት መሰል አነጋገር ሊሆን ይችላል። በርግጥ ኮሊሰየምም ፈረሰ፣ የሮማ መንግሥትም ፈረሰ፣ ዓለም ግን ይኸው አለች።

 

ሮምን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ዋነኛ መስህብ “ኮሎሲየም” ነው። አይበዛበትም። 2000 ዘመን የዘለቀው ስቴዲየም 50 ሺህ ሰው መያዙ ብቻ ሳይሆን በውስጡ የያዛቸው ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎች የምህንድስና ጥበባቸውን እንድናደንቅ ያደርገባል። የእንስሳት (አውሬዎች) ማስቀመጫዎች፣ የመሬት ስር መመላለሻዎችና የተለያዩ ክፍሎች አሉት። ዛሬ ሙሉ አካሉ ባይኖርም ጥንት ምን ይመስል እንደነበር ለመገመት ብዙም አያስቸግርም። የሆሊዉድ የኪነጥበብ ውጤቶች የሆኑት “ግላዲዬተር”ን የመሳሰሉ ፊልሞች ስትመለከቱ በርግጥም ኮሎሲየም ያንን ሊመስል እንደሚችል ከምትስሉት የምናብ ቅርጽ ጋር ይመሳሰልላችኋል።

 

ሮም ከሃይማኖታዊነትም ከታሪካዊነትም አንጻር ልቡናን የሚመስጡ ብዙ ሥፍራዎች አሏት።

   ታኮምቤ (ግበበ ምድር)

(ኤፍሬም እሸቴ - www.adebabay.com)፦ ሮምን የጎበኘ ሰው አንድም ቫቲካንንና ኮሎሲየምን አንድም ካታኮምቤን (በእንግሊዝኛው ደግሞ Catacomb) ሳይጎበኝ አይመለስም መመለስም የለበትም። ካታኮምቤ የሚለውን ስም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ግበበ-ምድር ይሉታል (ግበበ የሚለው ሁለተኛውን ‘በ’ በማጥበቅ ይነበባል)። በምድር ውስጥ የተቆፈረ ሥፍራ፣ ፍልፍል መሬት፣ የመሬት ውስጥ ለውስጥ መመላለሻ እንደማለት ነው። ስለ ቦታው ጥቂት ላጫውታችሁ።

 

ካታኮምቤ በሮምና በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ ጉድጓዶች ናቸው። ጉድጓድ ሲባል በእኛ አገር ውኃ ለመቅጃ ወይም እንደ ዘመነኛው ነዳጅ ፈላጊ ወደታች የሚቆፈር ጥልቅ ጉድጓድ ሳይሆን ምድር ለምድ እንደሚምዘገዘግ የከተማ ባቡር መመላለሻ ያለ ነው። ግበበ ምድሩ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው ጥናት ያደረጉ አርኪዎሎጂስቶች ያትታሉ። አገልግሎቱ ደግሞ በዋነኝነት ለመቃብር ሥፍራነት ነበር።

 

የጥንት ሮማውያን ሙታኖቻቸውን የማቃጠል ባህል ነበራቸው። እንደ ሕንዶቹ። በቀደመው ዘመን በሮም ግዛት አስከሬን የሚቀብሩት በግዛቱ የሚኖሩ አይሁድ ነበሩ። አይሁዳውያን (እስራኤላውያን) በአገራቸው እንዳለው ልማድ ጉድጓድ እየማሱ ይቀብሩ ነበር። ኋላ ክርስትና ሲነሣ ክርስቲያኖች እንደ ሮማውያን አስከሬናቸውን ማቃጠል ሳይሆን እንደ አይሁዶቹ ይቀብሩ ጀመር።

ቲቶ (ጥጦስ) የተባለው ሮማዊ ንጉሥ በ70 ዓመተ-እግዚእ ኢየሩሳሌምን እስካወደመበት ጊዜ ድረስ በሮማውያን ዘንድ ክርስትና የይሁዲነት ቅርንጫፍ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበር ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የተመለሱ አይሁዳውያንም እንደሌሎቹ አይሁድ ዘመዶቻቸው ሁሉ አስከሬኖቻቸውን ይቀብሩ እንደነበር ማስረጃዎች ተገኝተዋል። ከአሕዛብነት የተመለሱት ክርስቲያኖች ግን ይቅበሩ ወይም ያቃጥሉ አይታወቅም።

የክርስቲያኖች መቃብር የሆነው ግበበ ምድር የተስፋፋው ከ2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ ነው። ይህም የሆነው ሮማውያን በከተማው የሚደረገውን ቀብር በመከልከላቸው የተነሣ ነው። እነርሱ አስከሬን ማቃጠል እንጂ መቅበር ስለማያውቁ ክልከላው በአይሁዶቹ እና በክርስቲያኖቹ ላይ የተጣለ ይመስላል። ክርስቲያኖቹና አይሁዶቹ በኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ ከሚባለው ሕብረተሰብ የሚመደቡ ባሮችና ድሆች መሆናቸው በከተማዋ የቀብር ሥፍራ ለመግዛትና በባለቤትነት ለመያዝ አላስቻላቸውም። ስለዚህም ከከተማው ውጪ ለስላሳ የእሳተ ገሞራ አፈር ያለበትን ክፍል በመማስና በመቆፈር የቀብር ሥፍራቸውን ማዘጋጀት ያዙ።

 

ጉድጓዶቹ ከመሬት ወደ ታች ከ7-20 ሜትር ጠልቀው ይቆፈራሉ። መተላለፊያዎቹ ደግሞ 2.5 ሜትር በአንድ ሜትር ናቸው። አስከሬኖቹን ከመተላለፊያዎቹ ግራና ቀኝ እንደ መጻሕፍት በመደርደሪያ ላይ እንደሚቀመጠው ባለ ደርብ ላይ እንዲያርፉ ያደርጋሉ። ሌሎቹ የግድግዳው ክፍሎች ሥዕሎች እና ጽሑፎች ተጽፈውበታል።

 

ሮማውያን ክርስትና ሃይማኖት ላይ ሰፊ ጭፍጨፋ ማድረግ ሲጀምሩ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች እነዚህን የምድር ውስጥ ጉድጓዶች የመኖሪያና የመሸሸጊያ ሥፍራ አድርገዋቸው ነበር። ክርስትና የሮማ ኤምፓየር እምነት እስከሆነበት እስከ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ማሳደዱና ሰማዕትነቱ ቀጥሏል።

 

ክርስትና በሮማ ከታወጀ በኋላም ቢሆን ብዙዎቹ ክርስቲያኖች በግበበ ምድር መቀበሩን ይመርጡ ነበር። ምክንያታቸውም ከእነርሱ በፊት በሰማዕትነት ያረፉ ወገኖቻቸው በረከት ተካፋይ ለመሆን ነው። በኢትዮጵያ በደብረ ሊባኖስና በሌሎች ቅዱሳት መካናት ለመቀበር እንደሚሳሉ ሰዎች ያለ ነው። 

 

ጊዜ እያለፈ ሲሔድ የካታኮምቦቹ የቀደመ አገልግሎት እየቀነሰና እየቀዘቀዘ መጣ። ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ሰማዕታትን ለማሰቢያ የተለየ መንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ይካሄድባቸው ነበር። 10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ግበበ ምድሮቹ ሙሉ በሙሉ ተዘነጉ። አስቀድሞ ሮምን በተለያየ ጊዜ ባጠቁና አደጋ ባደረሱ ሌሎች ሕዝቦች ከተመዘበሩትና ከተጎዱት ቅርሶች መካከል እነዚህ የመቃብር ሥፍራዎችም ስለሚገኙበት እየቆየ ዋነኛ ትዝታቸው እየተሸረሸረ መጥቷል። ድጋሚ መታወስ የጀመሩት ከ16ኛው መቶ በኋላ ነው። በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የግበበ ምድሮቹ የክርስትናው ክፍል በቫቲካን የአርኪዎሎጂ ጥናት የገንዘብ ድጎማ ቁፋሮዎች እና እንዳይጠፉ መከላከል እየተደረገ ነው። ጥናቶቹም በዚያው መልክ ቀጥለዋል። ሌሎቹ ከክርስትና ጋር ሙሉ ግንኙነት የሌላቸው ግበበ ምድሮችም እንዲሁ ለቱሪስት መስሕብነት ያገለግላሉ።

 

በነዚህ ጉድጓዶች ውስጥ የሚያልፍና ታሪካቸውን የሚሰማ ማንም ሰው በስሜት መያዙ አይቀርም። በተለይም በክርስትና ሃይማኖታቸው ምክንያት በምድር ላይ ለመኖር ተከልክለው እንደ ዓይጥ መሬት ውስጥ የተሸሸጉትን የዚያን ዘመኖቹን ክርስቲያኖች ማሰብ ልቡናን በአንዳች መንፈሳዊ ስሜት ያሞቃል።

 

እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ በጎበኘኹበት ወቅት የተጓዝነው በቡድን ነበር። ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል ባዘጋጀው ጉዞ ከተለያዩ የአውሮፓ ግዛቶች የመጡ ተጓዦችን የያዘ ነበር። አስጎብኚዋ በጣሊያንኛ ቅላጼ በተጌጠ እንግሊዝኛ ስታስረዳን ቆይታ የውስጥ ለውስጥ ጉዞው ፍጻሜ ላይ ጎብኚዎች ጸሎት የሚያደርጉበት አንድ የሥዕል ቤት የመሰለ ክፍል ጋር ደረሰን። አንድም አረፍ ለማለትና የጉዞውን ትርክት ለማጠቃለል፣ ጉልበት ለመሰብሰብ፣ ጸሎት ለማድረግ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ሥፍራ ነው። እኛም በአንድነት ጸሎታችንን አድርሰን፣ ከነዚያ ከሰማዕታቱ ረድዔትና በረከት እንዲከፍለን ተማጽነን ስንወጣ ተጓዦቹ “ዓይኖቼ ማዳኑን አይተዋልና፣ ይገባዋል ክብርና ምሥጋና” የሚል መዝሙር ይዘምሩ ጀመር።

 

ካታኮምቤ ውስጥ የተፈጸመው ታሪክ በክርስትናው ዓለም የተከሰተው መከፋፈል ከመፈጠሩ አስቀድሞ የሆነ ታሪክ በመሆኑ በየትኛውም የክርስትና ስም ለሚጠሩ የዓለም ሕዝቦች የራሳቸው አድርገው እንዲመለከቱት ያስችላል። እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ስሜት ሊያሳድር የሚችለው ቅዱስ ሥፍራ ኢየሩሳሌም ይመስለኛል። ክርስቶስ የተወለደበት፣ የተጠመቀበት፣ የጸለየበት፣ የተሰቀለበት ቦታ በየትኛውም ክርስቲያን ዓይን “የእኔን እምነት አይወክልም” የሚያሰኝ አይሆንም። ካታኮምቤም በካቶሊካዊቷ አገር የሚገኝ ቢሆንም ሰማዕትነት የተቀበሉት የጥንት ክርስቲያኖች እና በነዚያ ዘመናት የተነሱት ቅዱሳን በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት ስላላቸው ለሃይማኖት ጉዞ ለሚሔድ ሰው ተገቢ ቦታዎች ናቸው። ነገረ ሃይማኖት ብዙም አይገደኝም ለሚል ጎብኚም ቢሆን ታሪኩና የሚታየው ነገር ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።

 

ከካታኮምቤ ሌላ፣ ቅዱስ ጳውሎስ አንገቱን ተከልሎ (ተቆርጦ) በሰማዕትነት ያረፈበት ቦታ መታየት ካለባቸው ሥፍራዎች አንዱ ነው። ቦታው በካቶሊክ ይዞታነት ያለ ሲሆን አንገቱን በተሰየፈ ጊዜ ጭንቅላቱ የነጠረባቸው ሦስት ቦታዎች ጸበል መፍለቁን አስጎብኚያችን አስረድተውናል። አንገቱን ለመሰየፍ ጭንቅላቱን ያስጎነበሱበት ትልቅ ጥርብ ድንጊያ አሁንም በቦታው ተቀምጦ ይጎበኛል።

ከዚያ ሌላ ጳውሎስና ሲላስ የታሰሩበትና መልአከ እግዚአብሔር የእስር ቤቱን በር በተአምር ከፍቶ፣ ሰንሰለታቸውን ትሎ ነጻ ያወጣቸው ቦታም ለጉብኝት ተቀምጧል። ጊዜ አድርሶኝ ልመለከተው አልቻልኩም። ቦታውን ብቻ ከውጪ ተመልክቼዋለኹ።

ቅዱስ ጴጥሮስን በተመለከተ በሮማ ከተማ የሚደርስበትን መከራ ተሰቅቆ፣ ከከተማዋ ወትቶ ሲሸሽ ክርስቶስ በራእኢ ተገልጾ የታየው ሥፍራም ከሚጎበኙት መካናት አንዱ ነው። ሁለቱም ቆመው የተነጋገሩበትን ቦታ የእግሮቻቸውን ቅርጽ በእብነ በረድ ሰርተው ጎብኚ እንዲመለከታቸው ያደርጋሉ።

ከክርስትና ሃይማኖት ጋር ከተያያዙት ታሪካዊ ሥፍራዎችም ውጪ ረዥም ታሪክ አላት ሮማ በየዘመናቱ ካለፈችበት ታሪክ ጋር የተያያዙ አያሌ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ሕንጻዎች፣ ሐውልቶች መኖራቸው ከተማይቱ የሚሔድ ሰው ከተማ ሳይሆን የከተማ ሙዚየም እንደሚያይ እርግጠኛ ሊሆን ይችላል።

ሮማን ዞሬ ስመለከት ከድካሙ ውጪ በደስታ ተምልቼ ነበር። ፋሺስቱ ሙሶሎኒ ናዚዎችን ደግፎ መቆሙን በማወጅ ንግግር ያደረገባትን (ኢትዮጵያን እንደሚወርር ወዘተ ወዘተ) የሚፎክርባትን የ Palazzo Venezia መስኮት እስካይ ድረስ። ያ ሁሉ ወፈ ሰማይ ጥልያን የተሰበሰበበት አደባባይ። ሕንጻውም፣ አደባባዩም ሁሉም እንዳለ ነው። በዘመነ ሞሶሎኒ የነበረውን አሁን ካለው ለማነጻጸር የሚሻ ዩ-ቲዩብ ገብቶ ፊልሙን ሲመለከተው ያገኘዋል።

ታሪክ እየቆረቆረም፣ እያናደደም ያው እውነቱን ብቻ እያሳየ ይዘልቃልና ቢያናድድም በዚያ አደባባይ መቆሙ “ታሪክን የኃሊት” እንደሚባለው ነው። በነገራችን ላይ ከሞሶሎኒ ንግግር መካከል “ነጻ አገር ወደ ባህር መውጪያ በሩ ከተዘጋበት ምኑን ነጻ ሆነው” የምትለዋን ሐረግ ስትሰሙ ከባህር 60 ኪሎ ሜትር ላይ ተቀምጣ ወደብ የሌላትን ኢትዮጵያን ያስታውሳችኋል። የርሱ አባባል በጸረ ናዚያ ምዕራቦች ጣሊያን ተከባለች ለማለት ያስቀመጠበት ቢሆንም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚሠራ አባባል ሆኗል። “ፊቱን ጸፍቶ፣ አፉን ከፍቶ አናገረው” እንዲሉ አበው። ነገረ ጣሊያን በዚህ ተፈጸመ።      

ይቆየን - ያቆየን     

 

2 comments:

Anonymous said...

Dn Efrem Thank you!

Anonymous said...

Dear D/N Efreme
Kale hiywote yasemalen
I was one of the luckiest to be there with the brothers and sisters of MK it was very spiritual and historical visite of my life i never forget it.
thank you!!
God bless you
menebere mariame