Wednesday, March 13, 2013

የጥቁሮች-ታሪክ ወር

(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)፦ በአሜሪካ የታሪክ ግጻዌ ውስጥ፣ ፌብሩዋሪ የተባለው ሁለተኛው ወራቸው “የጥቁሮች አፍሪካውያን-አሜሪካውያን ታሪክ ወር”/ Black History Month ተብሎ ይታወቃል። በጥቁር አሜሪካውያን የተፈጸሙ በጎ ተግባራት የሚታወሱበት፣ ለአገራቸው ጠቃሚ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ጥቁር አሜሪካውያንም የሚዘከሩበት፣ ባህላቸው፣ ልማዳቸው የሚወሳበት ወር ነው። ሥልጣኔ ማማ ላይ ቆማ ነገር ግን የጥቁር-ነጭ ልዩነት፣ በጥርጣሬ መተያየት እና የእኩልነት ነገር እልባት ባላገኘባት አሜሪካ አሁንም የማንነት ጉዳይ ትልቅ ጥያቄ ነው።


የወሩ አከባበር ጥንተ ታሪክ
የጥቁሮች ታሪክ ወር አከባበር ታሪክ መነሻ የሚያደርገው እ.ኤ.አ 1915 ሲሆን ወቅቱ “ባርነት” በሕግ ከተከለከለ እና “Thirteenth Amendment” የሚባለው ታሪካዊ ሕግ ከጸደቀ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ያለውን ጊዜ ነው። በዚያን ዓመት የመስከረም ወር፣ የሀርቫርድ የታሪክ ክፍለ ትምህርት ምሩቅ የሆነው ካርተር ጂ. ዉድሰን እና ጄሴ ኢ. ሙርላንድ በጋራ አንድ ድርጅት አቋቋሙ። የጥቁሮች ሕይወት እና ታሪክ ማጥኛ ማኅበር የተባለ። ድርጅቱ ዛሬም በዚሁ ስም (ASNLH) ይታወቃል።

ማኅበሩ በወቅቱ የጥቁሮችን ታሪክ የሚያዘክር ሳምንታዊ ዝግጅት በፌብሩዋሪ ወር ሁለተኛ ሳምንት ላይ ስፖንሰር አድርጎ አዘጋጀ። ሳምንቱ የታዋቂው ፀረ-ባርነት አቀንቃኝ ፕሬዚዳንት የአብርሃም ሊንከን እና የታዋቂው አፍሪካዊ አሜሪካ ፀሐፊና ንግግር አዋቂ የፍሬዲሪክ ዳግላስ የትውልድ ሳምንት ነው። ሳምንቱ የተመረጠው ሆን ተብሎ ነበር። ከዝግጅቱ በኋላ በየት/ቤቶቹና በየማኅበረሰቡ ክፍሎች ትልቅ መነቃቃት ፈጠረ። የታሪክ ክበቦች፣ የኅብረተሰቡ የተለያዩ ክፍሎች የሚገናኙባቸው ዝግጅቶች ተቀታጠሉ። ከዚያ ቀጥሎ በመጡት አስር ዓመታት አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎች ሳምንቱን በአዋጅ መቀበላቸውን ያስታውቁ ገቡ።

በዚሁ መልክ ሳምንቱ በወር ደረጃ መከበር ጀምሮ ቀጥሎ በመጨረሻም በ1976፣ በዘመነ ፕሬዚዳንት ጄራርድ ፎርድ፣ ፌብሩዋሪ “የጥቁሮች ታሪክ ወር” ተብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ተወሰነ። ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ እንዳሉት አጋጣሚው “በታሪካችን ውስጥ ብዙ ጊዜ ተዘንግተው የቆዩ ሁሉን አቀፍ የአፍሪካውያን አሜሪካውያን አስተዋጽዖዎች ለማክበር” ዕድል ይፈጥራል ብለው ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ፕሬዚዳንቶች በሙሉ ለወሩ የሚስማማ የተለየ ርዕሰ ጉዳይ በማንሳት ወቅቱን ሲዘክሩት ቆይተዋል። ለምሳሌ የ2013 መሪ ቃል “በነጻነት እና በእኩልነት መስቀልያ መንገድ ላይ” የሚል ሲሆን በአሜሪካ የርስበረስ ጦርነት ዘመን ፕሬዚዳንት ሊንከን ያስተላለፉትን ፀረ ባርነት መግለጫ 150ኛ ዓመት እና 200 ሺህ ጥቁር አሜሪካውያን በዋሺንግተን ዲሲ ሰልፍ ያደረጉበትን 50ኛ ዓመት በዓል የሚያዘክር ነው።

ይህ የጥቁሮች ታሪክ ወር ከአሜሪካ ውጪ በካናዳ እና በታላቋ ብሪታንያ መከበር ጀምሯል። በብሪታኒያ ከ1987 ጀምሮ፣ በካናዳ ደግሞ ከ1995 ጀምሮ በመከበር ላይ ይገኛል።
የወሩ ተቃዋሚዎች
ወሩ በዚህ መልክ በታላቅ ሁኔታ በመከበር ላይ ቢሆንም ለጥቁሮች የተለየ ወር መሰጠቱን የሚቃወሙ ብዙ አሜሪካውያን አሉ። ከነዚህም መካከል ታዋቂ ጥቁር አሜሪካውያን ይገኙበታል። የተለየ ወር ለአንድ ወገን ብቻ መሰጠቱን በመንቀፍ የጥቁሮች ታሪክ የመላው አሜሪካ ታሪክ ነው፤ የተለየ ጊዜ ለምን የሚሉ ተግሳጾች ይሰማሉ፡፤ ከዚህ ሐሳብ አራማጆች መካከል ታዋቂው የፊልም አክተር ሞርጋን ፍሪማን (Morgane Freeman) ይገኝበታል።  

ጥቁር ማነው?
ማነው ጥቁር የሚል ጥያቄ ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የሚል ቢኖር ተገቢ ነው እላለኹ። በአሜሪካ ደረጃ አፍሪካውያን አሜሪካውያን የሚባሉት ጥቁሮች በየሌላው አገር ተወልደን ከመጣነው ከመጤዎቹ በቀለም ባይለዩም በታሪክ ተዛምዶ እና ባሳለፉት አሰቃቂ የባርነት ሕይወት ምክንያት የተለዩ ናቸው። ከሌላው ክፍለ ዓለም የመጣነው ጥቁሮች ለጥቁርነታችን አንድና ሁለት ባይኖረውም “አፍሪካውያን አሜሪካውያን” በሚለው ስያሜ ውስጥ  እንጠቃለላለን ብዬ አልገምትም። የየመጡበትን አገር እያስቀደሙ አሜሪካዊነትን የሚያክሉበት ለዚያ ነው። ናይጄሪያውያን-አሜሪካውያን፣ ሶማሌ--አሜሪካውያን፣ ፊሊፒኖ--አሜሪካውያን፣ ሓይቲ-አሜሪካውያን፣ ኢትዮጵያውየን-አሜሪካውያን፣ ቻይና/ሕንድ-አሜሪካውያን ወዘተ።

ጥቁር ኢትዮጵያውያን?
በአሜሪካን አገር ተወልደው የሚያድጉ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በወላጆቻቸው አማካይነት ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ባይካድም ብዙዎቹ በሥነ ልቡናቸው ከኢትዮጵያዊነት ይልው አፍሪካዊ አሜሪካዊነታቸው ያይላል። እኛ የምንኮራባቸው፣ ራሳችንን ቀና አድርገን የምንሔድባቸው ማንነቶቻችን በልቡናቸው ዘልቆ ላይገባ ይችላል። ስለዚህም ቆዳቸው የእኛ ውሳጣሚ ማንነታቸው ግን የሌላ ይሆናል።

እኛ ኢትዮጵያውያኑ፣ ልክ እንደ ፈረንጆቹ፣ አፍሪካውያን አሜሪካውያኑን “እነዚህ ጥቁሮች” እያልን ነው የምንጠራቸው። ለስድብ የምንጠቀምበት ባይሆንም አባባላችንን ለሚሰማ ግን የምንሳደብ ነው የምንመስለው። እንዲያውም ነገራችን ሁሉ የአብዬ መንግሥቱ ለማን “ባሻ አሸብር ከልካይ በአሜሪካ” ግጥም ያስታውሰኛል። ግጥሙ እንደሚያትተው ራሳቸውን የተለየ ዘር አድርገው ይቆጥሩ የነበሩት ባሻ በአሜሪካ ያው ጥቁር እንጂ ምንም እንዳልሆኑ መገንዘባቸውን በሚያስፈግግ፣ በሚያስደምም የአብዬ መንግሥቱ ስላቃዊ ስንኞች እናዳምጣቸዋለን።

“ደረቴ ላይ ያለው ያገሬ ባንዲራ፣
ያምራል ተባለ እንጂ ከብሮም አልተፈራ፣
….
አውቃለኹ ከጥንቱ ነጭና ሻንቅላ፣
በቁም እንደኖረ ሲባላ ሲጣላ፣
እኔ ግን አበሻው ምን ወገን ልለይ፣
በማያገባኝ ጉዳይ ለምን ልሰቃይ፣”
ወዘተ …

ግጥሙን በአለፍ ገደም በቃሌ ካስታወስኩት የጠቀስኩት ነው። ሙሉውን አግኝቶ ማንበብ ይጠይቃል። ፍሬ ነገሩ፣ ኢትዮጵያዊ እንጂ ጥቁር አይደለኹም ያሉት ባሻ አሸብር የማታ ማታ ጥቁር መሆናቸውን እንዳረጋገጡ፣ እናም የትኛውም ዓይነት ጥቁር ይሁን፣ ጠይም ሆነ የቀይ ዳማ ጥቁር መሆኑን ማንገራገር እንደማይገባው፣ በባዶ ቂ** ጉራ ከምንም እንደማያደርስ የተማሩበትን የሚመሰክሩበት ነው።
“…
ይመስገነው ገባኝ ከጊዜ በኋላ፣
ስልቻ ቀንቀሎ ቀንቀሎ ስልቻ
ስልቻ ስልቻ ስልቻ ስልቻ።”

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ብዙ ባሻ አሸብሮች አሁንም በአሜሪካ አሉ። ይኖራሉ። ልጆቻቸው ስልቻ ቀንቀሎ መሆኑን ተገንዝበው ብዙ መንገድ ርቀዋል እነርሱ ግን “እኔ ግን አበሻው ምን ወገን ልለይ፤ በማያገባኝ ጉዳይ ለምን ልሰቃይ፣” የምትለዋ ስንኝ ላይ ናቸው። ከዚያ አላለፉም።

ከ2 ዓመት በፊት በተካሔደው የአሜሪካ ሕዝብ ቆጠራ ላይም ሆነ በማንኛውም በሚሞላ ፎርም ላይ እኛ ኢትዮጵያውያንን የሚያካትት መግለጫ ማግኘት ከባድ ነው። “ስፓኒሽ ነህ? ጥቁር አሜሪካዊ ነህ? እስያዊ ነህ?” ይላል እንጂ “ኢትዮጵያዊ ነህ” የሚል የለውም። አንዳንዶቻችን ጥቁር የሚለው አፍሪካዊ አሜሪካዊ አጠራር በርግጥም ስለማይገልጠን ሌላ የምንለው እያጣን ባዶ መተዉን እንመርጣለን። ወይም ምንም የሌለበት ቦታ ላይ “ኢትዮጵያዊ” የሚለውን እናስገባለን።

ለዚህም ይመስለኛል ብዙ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሳይቀር የእኛ ቁጥር በስታቲሰቲክስ ሲጠቀስ የማይሰማው። በዲሲ አካባቢ፣ በአትላንታና በካሊፎርኒያ ቁጥራችን የትየለሌ ሆኖ ሳለ እንደ ቁጥራችን መኖራችንን በሚያሳይ መልክ ማስቀመጥ አልቻልንም። ልጆቻችን ደግሞ አፍሪካዊ አሜሪካዊ የሚለውን ለመሙላት አይቸገሩም። ተለያይተናል። አንዲት ባለሙያ በሬዲዮ ሲናገሩ እንደሰማኹት “ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊ” የሚለውን ነገር በሕጋዊ ደረጃ ለማስገባት ብዙ ሥራ ያስፈልገዋል። ለልጆቻችንም እነርሱ ዛሬ የሚዝናኑበትን የጥቁሮች እኩልነት ለማስገኘት የተከፈለውን መስዋዕትነት መንገር ካልቻልን “ከሁለት ያጣ ጎመን” እናደርጋቸዋለን።

ልዩነትን ማክበርና በልዩነት አለመለያየት
በአሜሪካ የቀለም ልዩነት እንደመጣያና እንደመቧቀሻ እንዳይታይ ይልቁንም በመከባበር አብሮ ለመኖር ሙከራ የሚደረገውን ያህል አንድ ቀለምና ዘር ያለን እና ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በቋንቋ ያለንን ልዩነት እንደ ትልቅ ገደል እየቆጠርነው የማይሽር ጠባሳ በመሳል ላይ እንገኛለን። አለፉት 40 ዓመታት እና በዚህ መካከል የመታው ትውልድ በዘርና በጎሳ ላይ የተመሠረተ ማንነትን ብቸኛ መገለጫው በማድረግ ከጎረቤቱ ያለውን ልዩነት እጅግ እያሰፋው በመምጣቱ በርግጥ የአንድ አገር ልጆች ነን ወይስ ከተለያዩ ፕላኔቶች የመጣን ወደሚያሰኝ አሳዛኛ መሳሳብ እየተጓተትን ነው። በተለይም ልዩነቱ በባህል አጥር ባልታጠረበት በዳያስጶራው ቤተ እምነቶች ሳይቀሩ በአገር ልጅነትና በወንዝ ተገድበው ሲቀመጡ እያስተዋልን ነው።

በአገር ቤት ያለው እውነታም ግልጽ ነው። የዕውቀት ማማ በሚባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ዘንድ ያለውን በየቋንቋቸው የመቧደንና የመጠላላት ጉዳይ ስንመለከተው የቋንቋ ልዩነታችንን የወሰድንበት እመቀመቃት ጥልቀት ፍንትው ብሎ ይታየናል።

አገራችን በቋንቋ ልዩነት ላይ በተመሰረቱ ክልሎች ከተከፋፈለችበት ካለፈው 20 ዓመት ወዲህ ያለውን ተጨባጭ ሁናቴ ስንመለከተው በልዩነታችን በመከባበር መኖርን ለመድን ወይንስ ልዩነታችንን እያጎላን አንድነታችንን እያፈረስን ነው የሚለው መጠየቅ አለበት። እዚህ አሜሪካን አገር የተለመደው “Are we better off than ...” የሚለው ጥያቄ መጠየቅ ያለበት ጊዜ አሁን ነው። በአገራችን ያለው ቋንቋን ብቻ መሠረት ያደረገ (የውሸትም ሆነ የእውነት) ፌዴራሊዝም የተገነባበት መሠረቱ አሸዋ ነው ወይንስ ዐለት? ዘመን ይሻገራል ወይንስ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ነው? ጥያቄ መጠየቃችን እንደቀጠለ፣ እኔ ግን በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ቃለ ምዕዳን እንዲህ ብንል ያዋጣናል እላለኹ።

“አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ”

ይቆየን - ያቆየን

8 comments:

Anonymous said...

This is really a nice perspective. your writing is always simple but has meaningful value. I admired it a lot.

Anonymous said...

Thank U Ephrem

Anonymous said...

ደስ የሚል ንብባብ አነበብኩ፡፡ እግዜር ይስጥልኝ፡፡

Anonymous said...

ደስ የሚል ንብባብ አነበብኩ፡፡ እግዜር ይስጥልኝ፡፡

Mahlet Mesfin said...

it is an informative piece. Was an interesting reading for me. really! What a beautiful writing, the flow, analysis, content,.......
thank you.

Anonymous said...

አሁንም የጥቁሮች ወር ላይ ነን? ስንት ጊዜ ነው የሚቆየው ይሄ የጥቁሮች ወር?

Anonymous said...

What happened to u please update ur blog

አግናቲዎስ ዘጋስጫ said...

ካደጉበት ስፍራ ከወንዝ ከቀያቸው
ተሰደው.....ተባረው ግፍ የበዛባቸው
እኒህ አማራዎች የትነው ሀገራቸው?
በሰሜን በደቡብ በምስራቅ በምዕራብ
በሁሉም አቅጣጫ መኖር ያለገደብ
መብቱ መሆኑ የእያንዳንዱ ዜጋ
በታሪክ አፍራሾች ምነው ተዘነጋ
ኧረ ያገር ያለህ አረ በባንድራው
እንድ ይባል ወያኔ ምንአልባት ቢገባው

4/9/13
አግናቲዎስ ዘጋስጫ