Wednesday, April 3, 2013

“አይቴ ብሔሩ ለአማራ . . . የአማራ አገሩ ወዴት ነው?” ኢትዮጵያ አይደለምን?(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)፦ በንግግርም ይሁን በጽሑፍ ለማንሣትም ሆነ ለመጥቀስ፣ ለመወያየትም ሆነ ለመከራከር ከማይመቹኝ (discomfort እንዲል ፈረንጅ) የኢትዮጵያ ርዕሰ ጉዳዮች ሁሉ ዘርን፣ ብሔረሰብን የተመለከተው ዋነኛውና አንዱ ነው ጉዳዩ በዕለት ተዕለት የአገራችን ሕይወት ውስጥ ወሳኙ እና በሁነኛ መልክ ማኅበረሰባዊ ማንነታችንን እየበየነ እንዳለ እያወቅኹም እንዲህ እንደ አሁኑ በአደባባይ ለመውጣት ግን ብዙም አይቀለኝም። ምክንያቱ ሌላ ምንም ሳይሆን ጉዳዩ ያለው ስሱነት (sensitivity) ነው። አሁን ግን ላልፈው አልቻልኩም። አይገባምም። ለምን?

 

መነሻ

ከአማራ ክልል ወደ ቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ ተጉዘው የከተሙ በርካታ ሰዎች በወረዳው ባለሥልጣናትና ፖሊሶች፤ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የሚያትት ዜና የሰሞኑ ኢትዮጵያውያን ድረ ገጾች/መገናኛዎች ዋነኛ ትኩረት ነው። ስለዚሁ ጉዳይ ዜና ያስነበበው “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ጉዳዩን በተመለከተ የሚከተሉትን ቁም ነገሮች አስፍሯል።
  • በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ቦታ በማጣታቸውና የተሻለ ሥራ ፍለጋ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ መሔዳቸውን፣
·         “ከሌላ ቦታ እየመጣችሁና እየሠራችሁ የአካባቢውን ተወላጅ ሰነፍ አደረጋችሁት” በሚል ምክያት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ሳይሰበስቡ ከክልሉ እንዲወጡ መደረጋቸውን
  • አንዳንዶቹ በያሶ ወረዳ ውስጥ የከተማ ነዋሪነትና የንግድ ፈቃድ በማውጣት ላለፉት ሰባት ዓመታት በሥራ ላይ መቆየታቸውን፣ ገሚሶቹ ደግሞ ከ1997 ጀምሮ የቀበሌው ነዋሪ በመሆን ከክልሉ ተወላጆች ጋር በስምምነት መሬት የእኩል እያረሱ የራሳቸውንም የባለመሬቱንም ሕይወት መቀየራቸውን

·         በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይ ዞን በያሶ ወረዳ ውስጥ በሀሎ ትክሻ፣ ሆኒ፣ ሊጐ፣ ባብርኮ፣ ሻብቲ፣ ድልድል፣ ቲኒጆ መጢና በመሰል ቀበሌዎች በግምት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ ከአማራ ክልል የመጡ ሰዎች እንደሚገኙበት፣

  • “የክልሉ ነዋሪ ወዶንና ተቀብሎን በሰላም ነበር የምንኖረው” ማለታቸውን፣
  • ጐጐታ በተባለ ቀበሌ ከአማራ ክልል የመጡ 43 ሰዎች እንዲሁም በሀሎ ሙከአርባ ቀበሌ የ25 ሰዎች መታወቂያ ተቀዳዶ ሲጣል መመልከታቸውን፣

·         “እስከአሁን በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ከታሠሩት በርካታ ሰዎች በተጨማሪ በመኪና ተጭነው ነቀምትና ጊንቢ የተወሰዱት ሰዎች” መኖራቸውን፤ ስንቅ ሊያቀብሉ የሔዱ ሰዎችም መታሰራቸውን፤

·         ወደመጡበት እንዲመለሱ የተወሰነው፤ በብአዴን፣ ኦህዴድ እና የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ በኾነው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ ፓርቲ (ቤጉብዴፓ) በጋራ ተወያይተው በደረሱበት ውሳኔ መኾኑን ሥራው የወረዳው ብቻ ሳይሆን ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በትስስር እየተሠራ መኾኑን የያሶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ሻምበል ዳኛ መግለጻቸውን ዘግቧል።

 

ይህንን ዜና ከሌላ ተመሳሳይ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጋር ካመሳከርነው ከደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ ወረዳ ከተፈናቀሉት/ እየተፈናቀሉ ካሉት ሌሎች ዜጎች ጉዳይ ጋር ልናነጻጽረው እንችላለን። ሁለቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ አማርኛ ተናጋሪዎች (አማሮች) መሆናቸው ነው።

ሊወገዝ የሚገባው ተግባር
መነሻው ምንም ይሁን ምን፣ የክልሉ ፓርቲ ከማንም ጋር ይስማማ አይስማማ በነዚህ ዜጎች ላይ የተደረገው ተገቢነት የሌለው ነገር ነው። የዜጎች በአገራቸው ውስጥ የመዘዋወር፣ የመኖር መብት እንዲህ በጥቂት የፓርቲ ሹመኞች መወሰኑ የሚያስጨንቅም የሚያስደነግጥም ምልክት ነው። ከጉራ ፈርዳም ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉት ሰዎች “አማሮች” መሆናቸው ደግሞ አጋጣሚ ነው ለማለት በጣም የዋህ (ሲገፋም ጅል) መሆን ይጠይቃል።

በቋንቋ ማንነት ላይ ብቻ በተመረኮዘው የአገራችን ፖለቲካ “አማራ” የሚባል ለብዙዎቹ “ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” ጠላት የሆነ አካል እንዳለ በጓዳም በአደባባይም ሲነገር ብዙ ጊዜ ሰምተናል። ይህ ‘ፖለቲካ ያባውን - መፈናቀል ቢያወጣው’ (ሆድ ያባውን … እንደሚባለው) ምንጩ የማይታወቅ የማይሆነውም ለዚህ ነው።

ከደቡብም ከቤንሻንጉልም ለመፈናቀል “አማራነቱ” ምክንያት የሚሆንበት ከሆነ “አይቴ ብሔሩ ለአማራ? … የአማራ አገሩ የት ነው?” የትስ ሔዶ ይኑር? ኢትዮጵያ አገሩ አይደለምን?” ለማለት ያስገድደኛል። ደግሞስ አንድ ሰው አማርኛ ስለተናገረ የግድ ወደ አማራ ክልል መሔድ አለበት? ሁሉም ወደየክልሉ የሚለውን አዋጅ ያወጣውስ ማን ነው? አማርኛ የሚናገሩ ነገር ግን “የአማራ ክልል አገራቸው ያልሆኑ” ኢትዮጵያውያን የነገ ዕጣ ፈንታ ምንድር ነው?

የመታወቂያ ነገር
ለረዥም ጊዜ የቀበሌ መታወቂያ ሳይኖረኝ እኖር ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን የግድ የቀበሌ መታወቂያ ማውጣት የሚያስፈልገኝ ጊዜ ደረሰና እኖርበት ወደነበረው ቀበሌ ሔድኩ። ፎርም ሞላኹ። ከዚያም መታወቂያው ላይ መስፈር ያለበት የብሔረሰብ (እነርሱ እንኳን ብሔር ነው ያሉት) ነገር ተነሣ። መናገር አልፈለኩም። ቀበልዬው ካልተናገርኩ እንደማይሰጠኝ እርግጥ አደረገው። መሞላት አለበት። የዘር ማንዘሬን “ደም” ሁሉ እስኪሰለቸው ደረደርኩለት። በምን ፎርሙላ እንደሆነ ባላውቅም እርሱ ደስ ያለውን አንዱን ቋንቋ ብቻ መርጦ ብሔሬን ሞላው። በመታወቂያዬ መሠረት ቀብልዬው የሞላው ክልልና ብሔር አባል ሆንኩ። መታወቂያ እየታየ ሰልፍ መያዝ ሲጀመር እኔም አቶ ቀበልዬው በሞላው ተርታ የግዴን ልገባ ነው ማለት ነው።

ማንነትን በማወቅ ሰበብ ማንነትን ማጣት
ማንነትን ማወቅ፣ ባህልን መጠንቀቅ፣ ቋንቋን ጠብቆ መቆየት የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን መብትም ነው። ነገር ግን አሁን ባለው መንገድ ድንበር እያጠሩ ሰውን ያለ ፍላጎቱ “ሰልፍህ በየት በኩል ነው?” የሚያስብል ብሔረሰባዊ አሰላለፍ ግን ጤናማ ካለመሆኑም በላይ አገር ብለን በጋራ የምንኖርባትን ጎጆ የሚያፈርስ ከፋፋይ አስተሳሰብ ነው። በተለይ እዚህ አሜሪካን አገር ከመጣኹ በኋላ ያየሁት እና እንኳን ቋንቋን ቀለምን ማለትም ነጭ፣ ጥቁር፣ እስያዊ፣ ሂስፓኒክ የሚለውን እንኳን ፎርም ላይ ለመሙላት የሰውየው ብቸኛ ፍላጎት መሆኑን ማወቄ በግዳቸው “ብሔረሰብ እንዲመርጡ” ለሚደረጉ ኢትዮጵያውያን እንዳዝንም፣ እንድቆጭም፣ እንድበሳጭም ያደርገኛል።

ዛሬ አማራ ተብለው እንዲወጡ የተደረጉት ዜጎች ሌላው ሰው “አማራ” ይላቸው ካልሆነ ምናልባት ራሳቸውን በቀበሌያቸውና በትውልድ ቀዬያቸው ከመጥራት የዘለለ ነገር የሚኖራቸው አይመስለኝም። እንዳሁኑ “አማራ ናችሁ” የሚለው አንድ ቃል ሳይጫንባቸው በፊት “አገራችን ጎጃም ነው” ወይም “መንዝ ነው” ይሉ ይሆናል። ኦሮሞውም “ሜታ ነኝ” ወይም “ቦረና ነኝ፣ ወለጋ ነኝ” ይል እንደሁ እንጂ እንደአሁኑ “ኦሮሞነት” አልተጫነበትም ነበር። ሌላውም ሌላውም። ማንነትህን እወቅ በማለት ሰበብ የተጫነበት የቋንቋ ቀንበር ከጎረቤቱ የሚለየውና አርሶ ከሚያድርበት ቀዬ የሚያፈናቅለው ከሆነ ማንነቱ እንደ ዕዳ ተቆጥሮበታል ማለት ነው።

ሌላው የሚያስጨንቀው ጉዳይ ምንነትን በማጠር ሰበብ ክፉ የፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱ ቡድኖች መኖራቸው ነው። የዚህ ጨዋታ ግንባር ቀደሙ ደግሞ ኢሕአዴግ ራሱ መሆኑን መናገር አገራዊ ግዴታ እየሆነ ነው። ፓርቲው ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም አገርን የሚያክል ትልቅ ቤት የሚያፈርስ ቁማር ውስጥ ነው ያለው። የሌሎች ብሔረሰቦችን ድጋፍ ለማግኘት አማራውን የመስዋዕት በግ አድርጎ የማቅረብ ቁማር። ዞሮ ተመልሶ ወደራስ ሊተኮስ (Backfire ሊያደርግ) የሚችል መድፍ መጫወቻ ማድረግ።

መረጫጨት ተጀመረ?
አንድ ሰሞን ዝነኛ የነበረች ቀልድ “መረጫጨት ተጀመረ” ትል ነበር። የንስሐ አባት ጸበል ሲረጩ ለጨዋታ የመሰለው ትንሽ ነካ ያደረገው ሰው “መረጫጨት ተጀመረ?” ብሎ ውኃ ያነሳበት ታሪክ። በዚህ ዓይነቱ ከባድ ርዕስ ላይ ይኼ ቀልድ ስላቅ ሆኖ በውስጤ ብቅ አለ። ዛሬ ያባረሩ ሰዎች በሌላው ዘንድ “መረጫጨት ተጀመረ?” እንደማያሰኝባቸው ማወቅ ተስኗቸው ነውን? ምናልባትም ይህ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው ማን ያውቃል። እንደመንደር ጎረምሳ “ሰፈሬ ለምን መጣህ?” ሲሉ ሌላው በተራው እነርሱን “ሰፈሬ ለምን መጣችሁ?” እንዲላቸው ፈልገዋል ማለት ነው? ከዚያስ? ተጠቃሚው ማን ሊሆን? ወይስ ካርዱን የሚጫወተው ዋናው ሰውዬ ከኋላ ሆኖ እንዲስቅ? ኢትዮጵያችን እንደማትጠቀም በርግጠኝነት መናገር እችላለኹ።

ለጊዜው
በእኔ ትንሽ ግምገማ ኢትዮጵያውያን በመታወቂያቸው እና በስማቸው እየተገማመቱ እንዲደባደቡ ትልቅ ፍላጎት አለ። እስካሁን ፍላጎቱ ያልተሳካው በኢትዮጵያውያን አርቆ አሳቢነት ነው። ይህንን የኢትዮጵያውያን አርቆ አሳቢነት በሕይወቱ ያልተረዳ እና በዚህ የዘር ፖለቲካ የተጠመቀ ትውልድ አገሪቱን እየተረከበ ሲመጣ እንዴት እንደምንሆን ግን እግዜር ይወቀው። ባለ ራእዩ ሰውዬ “አንተርሐሙዌ” (Interahamwe) ብለው ያሟረቱት ነገር ላለመድረሱ ማረጋገጫ የሚሰጥ ባገኘኹ በተደሰትኩ።

የቤንሻንጉል ክልል ሰዎችም ሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለዚህ ዕብደት አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት አለባቸው። በዚህ ነገር መጠየቅ ሲመጣ ማዕከላዊው መንግሥትም “አልነበርኩበትም፣ የክልሉ ጉዳይ ነው” ማለት አይችልም። መሬት ለሕንዶች በነጻ በማከፋፈሉ ላይ እጁን የሚያስገባው የቤተ መንግሥት አካል ድሃ ገበሬዎች ሲፈናቀሉ የለኹበትም ሊለን አይችልም። የሚሰማውም አያገኝ።

መቼም የእምነት መሪዎቻችን ራሳቸውን ችለው ቆመው “ተዉ” ይላሉ ብለን አንጠብቃቸውም። እንዲህ ዓይነቱ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲገታ መጠየቅ የሚገባቸው እነርሱ ቢሆኑም - በቅድሚያ። እነርሱ ባይናገሩም ሥልጣን ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ሐሳባቸውን መግለጽ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ነገሩ ወንጀል መሆኑን መናገር አለባቸው። “ትክክል አይደለም” ለማለት የግድ የአማራነት ቆብ መድፋት አያስፈልገንም። ሰብዓዊነት የሚሰማው በሙሉ ግድ ይለዋል። ለታሪክም ቢሆን። ከጊዜያዊ የፖለቲካ ወገንተኝነት ውጪ ማሰብ የሚያስፈልገው በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ነው። የገዢው ፓርቲ ደጋፊና መሪ የሆኑትም ቢሆኑ ይህንን መቃወም ኢሕአዴግን መቃወም አድርገው መቁጠር አይገባቸውም። እንዲያውም ያስመሰግናቸዋል። ለኅሊናችንና ለልጅ ልጆቻችን ስለምናስረክባት ኢትዮጵያ ስንል “ኧረ በሕግ አምላክ፣ ኧረ በባንዲራው” እንበል።     

 

ይቆየን - ያቆየን

(ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ በሚታተሙ አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ እንዲወጣ የተዘጋጀ ነው።)

*** ባይተዋር ***

መጥባት እስኪያቆሙ፣ የ'ናት ጡቱዋ ነጥፎ፤
ፀሐይ እስክትወጣ፣ ጨለማዋ ገፎ፤
ተደፍቶ መማረር፤
ተገፍቶ መባረር፤
ከራስ ቤት መሰደድ፤
ባይተዋርነትን፣ እስከጊዜው መልመድ።

/ትዕግስት ዓለምነህ/
መጋቢት 2005 ዓ.ም.
 

+++

የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች ተመፅዋች ሆኑ

 (Addis Admas):-“ከእነ ቤተሠቤ እዚህ ለመድረስ ያየሁትን ፈተና ፈጣሪ ያውቀዋል፡፡ ቤተሰቤ ከቁጥር ሳይጐድል ለአገሬ መሬት በቅቻለሁና ከእንግዲህ የፈለገው ይሁን” አሉኝ፤ ከቤኒሻንጉል ክልል ያሶ ወረዳ ተፈናቅለው በፍኖተ ሰላም ድንጋያማ መጠለያ ውስጥ ያገኘኋቸው አዛውንት፡፡ በአማራ ክልል የከሠላ ወረዳ ተወላጅ የኾኑት አዛውንት፤ ኑሮ አልቃና ቢላቸው በ1997 ዓ.ም ሦስት ልጆቻቸውን ከትዳር አጋራቸው ጋር ይዘው፣የትውልድ ቀያቸውን ለቀው የተሻለ ሥራ ይገኝበታል ወደ ተባሉበት ቤንሻንጉል ክልል ያቀናሉ፡፡ ኑሮአቸውንም በቤኒሻንጉል ክልል ካደረጉ በኋላ ተጨማሪ አራት ልጆችን አፍርተው የቤተሠባቸውን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ ያደርጋሉ፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት ቀን ከሌት እየሠሩም ኑሮአቸውን መምራት ይቀጥላሉ፡፡ ለዓመታት ከኖሩበት መንደር በድንገት እንዲለቁ ሲገደዱ ግራ የተጋቡት አዛውንት የስምንት ልጆች አባት በመኾናቸው ሲፈናቀሉ ከፍተኛ ውጣ ውስጥ ከተታቸው፡፡
በቀላሉ የሚሳካላቸው አልኾነም፡፡ ‹‹ ከያሶ ወረዳ ውጡ ተብለን ድብደባና እንግልት ሲደርስብን እንደ ሌሎቹ እመር ብዬ መሸሽ አልኾን አለኝ፡፡ ልጆቼንና ባለቤቴን እንዴት ላድርጋቸው? ከአንድ ቤት ዘጠኝ ሰው የትስ ነው መውደቂያችን? ስል ጭንቀት ገባኝ›› የአዛውንቱ ዐይኖች እንባ አቀረሩ፡፡ አሁን አዛውንቱ ብዙ ስቃይ አልፈው በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም ከተማ ከሌሎች 3500 ተፈናቃዮች ጋር ከእነ ቤተሠባቸው በችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ቦታ ባለማግኘታቸው የተሻለ ሥራ ፍለጋ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ኑሮአቸውን ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያዛወሩ የአማራ ተወላጆች ካለፉት ሦስት ሣምንታት ጀምሮ በወረዳው ባለሥልጣናትና ፖሊሶች ከቀያቸው ተፈናቅለው በምስራቅ ጎጃም በጀቢጠናን ወረዳ ፍኖተ ሰላም ከተማ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ በደረሰን ጥቆማ መሰረት ወደዚያው አመራን፡፡
ከመጠለያው ወዲህ ከንፈሯ ክው ብሎ ደርቋል በጥቁር መናኛ ሻሽ እራሷን ጠፍንጋ አስራዋለች፡፡ የለበሠችው ቀሚስ ዳር ዳሩ ተተልትሏል፣ የተጫማችው ላስቲክ ጫማ ብዙ ቦታ ተበሣስቷል፡፡ በጠይም መልኳ ላይ ድካምና ተስፋ መቁረጥ ይነበብባታል- በፍኖተ ሰላም ከዳሞት ሆቴል ጀርባ ከአውቶብስ መናህሪያ ዝቅ ብሎ ባለው ‹‹ፍቶተ ሠላም›› ክሊኒክ መግቢያ በር ላይ ያገኘኋት የ27 ዓመቷ ወጣት የአራት ወር ነፍሰ ጡር ናት፡፡ በጉዞዋ በደረሰባት እንግልት በመታመሟ ከመጠለያው ለህክምና ወደ ክሊኒኩ እንደመጣች ነገረችኝ፡፡ “ራሴን ያዞረኛል፣ ሰውነቴን በጠቅላላ ይቆረጥመኛል፣ ያስለኛል፣ በተለይ ሌሊት ሌሊት እንቅልፍ የለኝም” የምትለው ነፍሠ ጡሯ፤ ባደረገችው ምርመራ ደም ማነስ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማት ተነግሯታል፡፡
ባለቤቷም የታዘዘላትን መድሀኒት ሊገዛ ሄዷል፡፡ “ቀን ፀሀዩ፤ ማታ ብርዱ በዚያ ላይ ያለ ምንጣፍ ጠጠር ላይ እየተኛሁ ነው ለበሽታ የተጋለጥኩት፡፡ ከዚህ ቦታስ በሕይወት የምገኝ አይመስለኝም” አለች፡፡ ባለቤቷ ተመልሶ ሲመጣ ጨዋታው አላማረውም፡፡ ማንነቴን ጠይቆኝ ከተረዳ በኋላ፤ “እዚህ ያሉ የከተማው አስተዳደሮችና የክልሉ ኃላፊዎች አሁን ያለው ችግር እስኪፈታ ለማንም አትናገሩ ብለውናል” አለኝ፡፡ ‹‹አንዳንድ ጋዜጦች ከመካከላችሁ ያልሆነ መረጃ እየወሠዱና እየጻፉ ጋዜጣ ማሻሻጫ አድርገዋችኋል፤ ስለዚህ ዝም በሉ ተብለናል” የሚል ምላሽ ሠጠኝ፡፡ ችግሩን እንዲነግረኝ ለማግባባት ሞከርኩ፤ “ዋ! ለሠው ቢያወሩት መፍትሄ ካልመጣ ምን መላ አለው እህቴ?” በማለት መልሶ ጠየቀኝ፡፡ በእግራችን እየተጓዝን መጠለያው አካባቢ ደርሰን ነበርና ባለቤቱን ወደመጠለያው አስገብቶ አቧራማው ሜዳ ላይ ተቀምጠን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ገባን፡፡
የ31 ዓመቱ ወጣት አዲስ አበባ ውስጥ ለ12 ዓመታት በሎተሪ አዟሪነት ሠርቷል፡፡ ቤተ መንግሥት አካባቢ በሚገኘው ግቢ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ኢትዮጵያ አንድነት ት/ቤት ጐን ከአራት ጓደኞቹ ጋር ቤት ተከራይቶ ይኖር ነበር ፡፡ “አሥራ ሁለት ዓመት አዲስ አበባ ስኖር ለውጥ አጣሁ፡፡ ስለዚህ አገሬ ገብቼ ሚስት አግብቼ ወገኖቼ እንደሆኑት እሆናለሁ ብዬ ጐጃም ገባሁ” የሚለው ተፈናቃይ፤ አገሩ ከገባም በኋላ ተስፋ የሚሠጥ ነገር አልተመለከተም፡፡ ሆኖም ቤተሠቦቹ ልቡ እንዲረጋ በሚል አስቀድሜ ክሊኒክ በር ላይ ያገኘኋትን ጠይም ቆንጆ ልጅ ዳሩለት፡፡ የሙሽርነት ወጉን በአግባቡ ሳይጨርስ ሚስቱን አሣምኖ ይዟት ቤኒሻንጉል ያሶ ወረዳ ጥቅሻ ቀበሌ እንደገባ አጫወተኝ፡ ይህ የሆነው በ1999 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ነበር፡፡ ቀበሌዋ እጇን ዘርግታ እንደተቀበለችው ይናገራል፡፡ እንደ ሌሎች ያገሩ ልጆች እርሱም ከጉሙዝ ባለ መሬት ጋር ተስማምቶ ግብርናውን ቀጠለ፡፡ ባለ መሬቱ በሠጠው ቦታ ላይ ጥሩ ቤትም ሠራ፡፡
ህይወት ከአዲሶቹ ሙሽሮች ቤት በፈገግታ ገባች፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት በጥሩ ሁኔታ ከተደላደለ በኋላ ልጅ ለመውለድ ከባለቤቱ ጋር ተመካክሮ ሚስት ፀነሠች፡፡ የአራት ወሩ ፅንስ ግን ዕድለኛ አልኾነም፤ መፈናቀል ተከሠተ፡፡ “አንተ ታመልጣለህ እኔ አቅመ ደካማ ነኝ፤ ከኅብረተሠቡ ጋር ልሣፈርና ልሂድ›› በማለት ባለቤቱ ቀድማው ወደ ፍኖተ ሠላም ትመጣለች፡፡ እርሱ እንዴት የለፋሁበት በቆሎና ሠሊጥ መና ይቀራል በሚል ብቻውን ጫካ ይገባል፡፡ ወደ እህሉ ክምር ሲመጣ፣ ባለ መሬቱ አሠሪው ሌሊቱን ሲወቃ አድሮ በማዳበሪያ ከቶ ያገኘዋል፡፡ “አሠሪዬ መኪና አምጥቶ የራሱ አስመስሎ የኔንም ጫነልኝ፡፡ 40 ኩንታል በቆሎ በ200 ብር ሂሣብ ሸጬ፣ ስንቄን ይዤ ድብደባና እንግልት ከበዛበት ቀበሌ ለማምለጥ ጥሻ ጥሻውን ስመጣ ሊገድሉኝ ለጥቂት አመለጥኩ›› ነበር ያለኝ፡፡
በፍኖተ ሰላም ባከል መንደር ስድስት ወይም በተለምዶ “ቄራ ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለድንጋይ መጥረቢያነት ሲያገለግል የቆየ ኮረት ድንጋይ የፈሰሰበት ሰፊ ሜዳ ለጠራቢዎቹ ፀሐይ መከላከያ በሚል በተሠራው አምስት ቦታ ላይ ተፈናቃዮቹ ሰፍረዋል፡፡ ወደ መጠለያው ስጠጋ ለእርዳታ ሥራ እንደመጣች የገመትኳት ዩናይትድ ኔሽን ‹‹UN›› የሚል ሰሌዳ የለጠፈች ላንድ ክሩዘር መኪና በመጠለያዎቹ ቦታዎች መሐል ለመሐል ቆማለች፡፡ አምስተኛው መጠለያ አካባቢ ሁለትና ሦስት ፖሊሶች ተመለከትኩና መጠለያው እየተጠበቀ እንደኾነ ገምቼ ራሴን ደበቅ አደረኩ፡፡ ግድግዳ አልባ መጠለያ መጠለያዎቹ በወጣቶች፣ በእናቶች፣ በህፃናትና በአዛውንቶች ተሞልተዋል፡፡ አጠቃላይ ቁጥራቸው ወደ 3500 ይገመታል፡፡ ለመኝታ አይደለም ለመቀመጫ በማይመቸው ድንጋያማ ግርግዳ አልባ ባለ ቆርቆሮ ጣሪያ መጠለያ ውስጥ ደቀቅ ያሉትን ጠጣሮች ደልድለው ጎናቸውን አሳርፈዋል፡፡ ጠንከር ያለ አቅም ያላቸው ደግሞ ራቅ ብለው በመሄድ የባህር ዛፍ ቅጠል መልምለው ለማረፊያቸው ጉዝጓዝ አመቻችተው፣ ቢያንስ ካገጠጡት ጠጠሮች ጉርባጤ ራሳቸውን ይከላከላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት አብዛኞቹ ግን መሬቱ ላይ ተኝተዋል፡፡ የሸራ ምንጣፍ ያነጠፉ አንዳንድ ሰዎችንም አስተውያለሁ፡፡
የቆርቆሮ ጣሪያ ብቻ ያላቸው ‹‹መጠለያ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አምስቱ ቦታዎች በመሙላታቸው ሲመሽ ሜዳው ላይ የሚተኛው ተፈናቃይ ቁጥር እንደሚጨምር ነገሩኝ፡፡ መጠለያውን በዐይኔ ቃኘሁት፡፡ አራስ ሕፃናት ያቀፉ እናቶች፤ ልጆቻቸውን ከንፋስና አቧራ ለመከላከል ይታገላሉ፡፡ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በደረቅ ሜዳ ተሰጥተው ንፋስና ፀሐይ ሲፈራረቅባቸው ማየቱ መንፈስን ይረብሻል፡፡መብራት የሌለውና እና ለዛ ሁሉ ተፈናቃይ ሁለት የውሃ ቧንቧ ብቻ ባለው መጠለያ፤ እናቶች ባዶ የፕላስቲክ ውሃ መያዣዎችን አንጠልጥለው ውሃ ፍለጋ ወደ ከተማው መሀል ይሄዳሉ፡፡ ተፈናቃዮች በውሃ ችግር የተነሳ በከተማዋ መግቢያ ላይ ወደሚኘው “ላህ” የተባለ ወንዝ እየሄዱ ይታጠባሉ፡፡ ጠዋት እና ማምሻውን ከምግብ ዋስትና የሚቀርብላቸው በነፍስ ወከፍ አንድ እንጀራ በአንድ ጭልፋ ወጥ 11 ሰዓት ላይ ተበልቶ መጠናቀቅ አለበት፡፡
ከዚያ ካለፈ መብራት ስለሌለ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ያውም ምሳ መመገብ የለም፡፡ ፍኖተ ሠላም አቅራቢያ በምትገኘው ማንኩሳ አካባቢ በአንዲት የገጠር መንደር የተወለደ የ25 ዓመት ወጣት ነው፡፡ የነተበ ቲሸርት ለብሷል፡፡ ቁምጣው ጉልበቱን ሳይነካ ታፋው ላይ ቀርቷል፡፡ የቀኑ ፀሀይና የማታው ንፋስ መፈራረቅ ሰውነቱን ከመሬቱ አፈር ጋር አመሣስሎታል፡፡ የቤተሠቡ መሬት ተሸንሽኖ ለታላላቅ ወንድሞች ሲሠጥ ዕድሜው ገና በመሆኑ ከቤተሠቡ ጉያ አልወጣም ነበር፡፡ “መሬት ጠበበ ደካማ ቤተሠቦቼ ላይ ሸክም አልሆንም ጉልበትና ጤና እያለኝ ሊርበኝ አይገባም፤ በዚያ ላይ ዕድሜዬ ለአቅመ አዳም እየደረሠ ነው ብዬ ነበር፤ በ2000 ዓ.ም ወደ ቤኒሻንጉል የሄድኩት›› የሚለው ወጣቱ፤ በያሶ ወረዳ በብርኮ ቀበሌ ኑሮውን ካደረገ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከጉሙዝ ገበሬ የእኩል እያረሠ ሠሊጥ እና በቆሎ እያመረተ በመሸጥ ከራሱ አልፎ ደካማ ቤተሠቦቹን መርዳትም ጀምሮ ነበር፡፡ ወጣቱ እንደሚለው የቋጠረውን ጥሪት ለመሠብሠብ እንኳን ጊዜ ያልሠጠው “የአገራችንን ለቃችሁ ውጡ” ወከባ ባዶ እጁን ፍኖተ ሠላም እንዲመጣ አስገድዶታል፡፡
“በጣም ተስፋ የቆረጥኩት እዛው እያለኹ ነው፡፡ አንድ የክልሉ ፖሊስ ስድስት ሠዓት ላይ አግኝቶኝ ከሁለት ሠዓት በኋላ ስመለስ ባገኝህ በነፍስህ ፍረድ ካለኝ በኋላ ነው›› የሚለው ወጣቱ፤ “ከምሞት ነፍሴን ይዤ ላምልጥ በሚል የምቀይረው ልብስ ሳልይዝ 350 ብር ከፍዬ ወደ ፍኖተ ሠላም መጥቼ መሠሎቼን ተቀላቅያለኹ፡፡ እኔ ጉልበት ኖሮኝ አመለጥኩ፤ እዛው የቀሩት ናቸው የሚያሳዝኑኝ” ይላል፡፡ ተፈናቃዩ ጨርቄን ማቄን ያለ፣ ንብረት እና ቤተሰቡን ለመሠብሠብ የተፍጨረጨረ በድብደባ ለስብራትና ለቁስለት መዳረጉን ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እናቶች የመውለጃ ወራቸው ከመግባቱ ቀደም ብሎ እንደየ አቅምና ፍላጐታቸው የገንፎ፣የአጥሚት እህሉ፣ የህፃኑ ልብስና መታቀፊያ ይዘጋጃል፡፡ እናት ምጥ ስትያዝ በቤተሰብ በወዳጅ ዘመድ ትከበባለች፡፡ ሁሉም ጭንቀቷን ይጋራል፡፡ ተፈናቃዮቹ እናቶች ግን ይህ ዕድል ተነፍጓቸው በጠጠራማውና ገመናን በማይሸፍነው ሜዳ ላይ በስቃይ ልጅ እየተገላገሉ ነው፡፡ በዚህ ዐሥር ቀናት ውስጥ እንኳን አራት እናቶች በመጠለያው መውለዳቸው ተነገረኝ፡፡ አንጀት የሚጠግን ምግብ፣ ጐን የሚያሞቅ የረባ ልብስ ለማግኘት አልታደሉም፡፡ እነዚህን አራስ እናቶች ከ3500 ተፈናቃይ መካከል ለመለየት ብቸገርም የዐይን እማኞች ጠቁመውኛል፡፡
ከቤኒሻንጉል ሲባረሩ አራስ የነበሩ ወላጆችም በመጠለያው ይገኛሉ፡፡ ለነፍስ ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ክርስትና ያልተነሱ ሕፃናትን ለይተው ክርስትና ሲያስነሱና ሲያጽናኗቸው እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ በ17 ዓመት ወጣት ጀርባ ላይ የታዘለው በዐይን ግምት ሁለት ዓመት የሚኾነው ሕፃን አፍንጫው ተገባብጦ ቆስሏል፡፡ ወንድሜ ነው ያለችኝን ሕፃኑን ያዘለችውን ወጣት ምን ኾኖ አፍንጫው እንደቆሰለ ጠየቅኳት “የምንተኛበት መሬት ደንጊያ ስለሚበዛው ሲንፈራገጥ ልጦት ነው” አለችኝ፡፡ ድንጋዩ እንኳን ለሕፃን ለዐዋቂም እንደሚያስቸግር አስተውያለሁ፡፡ ከዛሬ ስምንትና ዘጠኝ ዓመታት በፊት ከአማራ ክልል ከተለያዩ ቦታዎች የተሻለ ሕይወት ለመኖር እና እየተባባሠ በመጣው የእርሻ መሬት እጦት የተነሳ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይዞን ያሶ ወረዳ ሀሎ ጥቅሻ፣ ሆኒ፣ ሊጐ፣ ባብርኮ፣ ሻብቲ፣ ድልድል፣ ቲኒጆ መጢና ሌሎችም ቀበሌዎች ኑሯቸውን አደረጉ፡፡ አብዛኛዎቹ በአካባቢው ካሉ የጉሙዝ ተወላጆች ጋር በመስማማትና መሬታቸውን የእኩል በማረስ ጥሪት መቋጠርና የጉሙዝ ተወላጆችንም ሕይወት መቀየራቸውን በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡
ጥቂቶች ደግሞ በያሶ ከተማ ንግድ ፈቃድ በማውጣት የንግድ ሥራ ማንቀሣቀስና በሕጋዊ መንገድ ለመንግሥት ግብር እየከፈሉ መኖራቸው ቀጥለው ነበር፡፡ በየዓመቱ በአካባቢው ባለሥልጣናት ውጡ እየተባሉ በስጋት ሲናጡ ይቆዩና ተመልሠው መሥራት እንደሚጀምሩ የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፤ አብዛኛው ገበሬ ከጉሙዝ ተወላጆች ጋር ተዋዶና ተስማምቶ፣ ጥሪት አፍርቶ ወልዶና ከብዶ ይኖር ነበር፡፡ የዘንድሮው የ “ውጡሉን” ጥያቄ ግን በጥያቄ ብቻ አላበቃም፡፡ እንደ ተፈናቃዮቹ ገለፃ ያለ ማስጠንቀቂያ ንብረትና ቤተሠብ ሳይሠበስቡ እየተደበደቡና እየተንገላቱ አካባቢውን እንደለቀቁ ይናገራሉ፡፡ ከአካባቢው ጉልበት ያለው እየሮጠ፣ አቅመ ደካማው እየተደበደበ፤ እየወደቀና እየተነሳ መውጣት የቻለው ወጥቷል፡፡ የወረዳው አመራሮች መኪኖች እየጫኑ እዲያደርሷቸው ለሹፌሮች ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ፣ ሹፌሮችም አጋጣሚውን በመጠቀም በ300 ብር የሚሔደውን መንገድ ከ350 እስከ 400 ብር እያስከፈሉ፣ የሕዝቡን እንግልት ቢያባብሱትም ዕድለኛ የሚባሉት ነፍሳቸውን ይዘው በፍኖተ ሠላም ከተማ በአንድ የደረቀ መሬት ላይ በብርድና በፀሀይ እየተቆሉ ይገኛሉ፡፡
ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት፤ ከባህርዳርና ከየወረዳቸው ኃላፊዎች መጥተው ስብሰባ እና ፍሬአልባ ውይይት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡ “በየጐጣችን ያሉ የወረዳው ኃላፊዎች ለችግሩ መፍትሔ እስኪገኝ ወደየቤተሰባችን እንድንገባ ይነግሩናል” ያሉት ተፈናቃዮቹ፤ “እኛ ቤተሰብ አፍርተን እንዴት ደካማ ቤተሰቦቻችን ላይ ሄደን ሸክም እንሆናለን” የሚል ጥያቄ ለኃላፊዎች ሲያነሱ “እኛ ከክልሉ ታዘን እንጂ እንኳን እናንተን አንድ በሽተኛ የሚያስጠጋ እንኳን ቦታ የለንም” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን በመጠለያው ያሉት ተፈናቃዮች ይገልጻሉ፡፡
በድንጋጤና በወከባ ምንም ሳይዙ በመፈናቀላቸው ወደየትውልድ ቀያቸው ቢመለሱ የሚልሱት የሚቀምሱት እንደሌለ በስብሰባው ላይ ለኃላፊዎቹ ሲናገሩ “እንደምንም ተጠጋግታችሁ ተቀመጡ፤ ምንም ልንረዳችሁ አንችልም” ይሉናል፤ በዚህ አይነት ባዶ ሜዳ ላይ ከሚወድቁ እዚሁ ሜዳ ላይ መንግሥት የፈለገውን ያድርገን በሚል ወዴትም የመሄድ ፍላጐት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ “እኛ ከቤኒሻንጉል ስንባረር የክልሉ ተወላጅ ባለመሬቶች ስብሰባ እየተቀመጡ ከወረዳው ባለስልጣናት ጋር ሲሟገቱልን ከርመዋል” የሚለው አንድ ተፈናቃይ፤ “እኛ ምን መብላት እንዳለብንና እንደሌለብን እንድንለይ ያደረጉን እነዚህ ገበሬዎች ናቸው አርሰውና አምርተው ከሚሰጡን ምርት ሚስቶቻችንን ከእንብርክክ የድንጋይ ወፍጮ አውጥተን ዘመናዊ ወፍጮ እስከመትከል እና ባለሀብት እንድንሆን አድርገውናል” ብለው ለያሶ ወረዳ ኃላፊዎች ይነግሩላቸው እንደነበር ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ፡፡
የጉምዝ ገበሬዎችን ሰብስበው “እነዚህ ስደተኞች መጀመሪያ ሲገቡ አባባ ይሏችሁ ነበር፣ ከዚያ አቶ እገሌ ማለት ቀጠሉ፣ አሁን ስማችሁን ብቻ ነው የሚጠሩት፣ ነገ ደብድበውና መሬታችሁን ቀምተው፣ ክብራችሁን አዋርደው የቀን ሠራተኛ ያደርጓችኋል፡፡ እነሱ ከመጡ ብዙ ሃብትና ንብረት አፍርተዋል፣ እናንተን እያሰነፉ ራሣቸው ሃብታም እየሆኑ ነው፤ ስለዚህ በአፋጣኝ መውጣት አለባቸው” እያሉ ሊያሳምኗቸው ቢሞክሩም የጉሙዝ ገበሬዎች ከእኛ መነጠሉን አልወደዱትም፤ እየተደበደብን ንብረታችን የትም ተበትኖ ሲቀር እያለቀሱ ሽኝተውናል” ነበር ያለኝ አንዱ ተፈናቃይ፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደ ፍኖተ ሠላም ከገቡ ወደ ሦስት ሳምንት እየተጠጋቸው ሲሆን ገና እንደመጡ ያሳረፏቸው ሌላ ቦታ ነበር ፡፡
በዚህም የከተማው ሰውና የሚመለከተው አካል የማያያቸው ቦታ በመሆኑ ከተፈናቃዮቹ ወጣት ወጣቶችና በትምህርታቸው ትንሽ የገፉት ስደተኞችን በማስተባበር መጀመሪያ ካሉበት ቦታ ዋናውን አስፋልት መሃል ለመሃል ይዘው ግር ብለው ወደ አደባባዩ ሲወጡ የከተማው ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ወጣ፡፡ ከዚያም የከተማው ኃላፊዎች አሁን ያሉበትን ቦታ እንደሰጧቸውና፣ አሁን ያሉበት ቦታ በፊት ከነበሩበት የሚሻለው ከተማው ውስጥ በመሆኑ የአካባቢው ሰው ለህፃናቱ ውሃም ዳቦም እንዲያቀብላቸው ረድቷቸዋል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደር ወደ 15 ኩንታል የሚጠጋ በቆሎ ከማቀጣጠያ እንጨት ጋር ይዞ በመምጣት እየቆላ እንዲመገባቸው ይናገራሉ፡፡ በቄስ መሪነትም ወደ 200 የሚጠጋ እንጀራ ይዘው የደከሙትን እንዲመገቡላቸው ይገልፃሉ፡፡ እንደ ተፈናቃዮቹ ገለፃ በየዕለቱ ለስብሰባ ነው፡፡ መፍትሔ ግን የለም፡፡ ሰው በችጋርና በህመም እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ቀይ መስቀል አልፎ አልፎ ህክምና ቢሰጥም በቂ አለመሆኑን ነግረውኛል፡፡ አንዲት እናት “በቀን ሁለት ጊዜ ለሚሰጡን ብናኝ እንጀራ 50 ዐይነት ካሜራ እተየደቀነ እንቀረጣለን” ብለው አማረዋል፡፡
እኔ በስፍራው በደረስኩበት ዕለት ከአምስቱ በአንዱ መጠለያ ባለው ሜዳ ላይ ሕዝቡ ጨረቃ መስሎ ተሰብስቦ ነበር፡፡ ነፍሰጡሯ እንደነገረችኝ፤ ከቤኒሻንጉል በመጡት ስደኞች ሰበብ በየቦታው ስደት ሄደው የነበሩ ሁሉ ከእነሱ ጋር ያሰፍሩናል በሚል እየተቀላቀሉ በመሆናቸው፤ አሁን የየወረዳውና የክልል ሃላፊዎች እንለያለን በሚል መታወቂያ እየሰበሰቡ እንደነበር አጫውታኛለች፡፡ መንግሥትን ፍለጋ ተፈናቃዮቹ ከመጡ ሁለት ሳምንት አልፎ ሦስተኛውን ጀምረዋል፡፡ በየጊዜው የየወረዳውና የየ ክልሉ “በአማራ ሰንዲ ወንበርማ በተባለ አካባቢ ቤንሻንጉሎች ሰፍረው በሰላም እየኖሩ ነው፡፡ የእነርሱ ክልል ሃላፊዎች እኛን ጠልተው በግፍ ካባረሩን እነሱ ይውጡና ቦታውን እኛ እንስፈርበት የሚል ጥያቄ ለሃላፊዎቹ አንስተን ነበር” የሚለው አንድ ተፈናቃይ፤ “ይሄ የብሔር ግጭት ስለሚያመጣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ አይደለም፤ በድጋሚም እንዳታነሱ” በሚል እንዳስጠነቀቋቸው፤ ይገልፃል፡፡
አያይዞም ከዚህ በኋላ የተሻለ መፍትሔ ለማግኘት እስከ 12ኛ ክፍል የተማሩና የተሻለ ብቃት አላቸው ያሏቸውን በመምረጥ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን ይናገራል፡፡ በኮሚቴው አማካኝነት ከተፈናቃዩ በነፍስ ወከፍ አምስት ብር ተዋጥቶ ሃያ ሺህ ብር እንደተሰበሰበ የሚናገረው የኮሚቴው አንድ አባል፤ ይህ ሃያ ሺህ ብር በተፈናቃዩ ለተወከሉ ሰዎች ተሰጥቶ መብታቸውን ለማስከበር ለሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴ ሥራ ማስኬጃ ይሆናል ሲል ነበር ያጫወተኝ፡፡ “ ጉዳያችን በየወረዳችን እና በክልሉ መንግሥት እልባት ስላላገኘ፣ የመጀመሪያ ሥራችን ተፈናቃዩን ወክለን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ጽ/ቤት ለመሄድ ዝግጅት ጨርሰናል” ይላል ወጣቱ ተፈናቃይ፡፡ ሃያ ሺህ ብሩም ለዚሁ እንቅስቃሴ የሚውል ነው፡፡ ከመጠለያው ወጥቼ ኳስ ሜዳውን መሃል ለመሀል ሰንጥቄ ወደመጣሁበት ስመለስ አንድ መልከ መልካም ጐልማሣ ከበረዶ የነጣ ጋቢያቸውን ደርበው፣ ከአንድ ወጣት ጋር ሜዳው ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ጥሩ ወዘና ያላቸው በመሆኑ ተፈናቃይ አይመስሉም፡፡ ግምቴም ትክክል ነበር፡፡ ሠላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ስለ ስደተኞቹ አንስቼ መጨዋወት ጀመርን፡፡ “እኔ 58 ዓመት ሙሉ ስኖር የሰው ልጅ እንዲህ ያለ ፈተና ሲቀበል ሳይ የ”በኸሬ” ነው (በአካባቢው አነጋገር የበኸሬ ማለት የመጀመሪያዬ እንደማለት ነው) አሉኝ የአካባቢው ነዋሪ፡፡ “ሰሞኑን አራት ሴቶች እዚህ የምታይው ሜዳ ላይ (መጠለያውን ማለታቸው ነው) ሲወልዱ ስመለከት መፈጠሬን ጠላሁ” በማለት የችግሩን አስከፊነት አስረዱኝ፡፡ ወገን ሲንገላታ ማየት ምን ያህል እንደሚከብድ የተናገሩት የዛው መንደር (የባከል) ነዋሪው ጐልማሳ፤ የተፈናቃዮቹን ችግር ለመስማት “ላህ” የተባለ ወንዝ ሲሄዱ አብረው ሄደው ችግሮቻቸውን እንደሚያዳምጡም አጫውተውኛል፡፡
ምንም እንኳ የእኚህ ሰው ቤት ከመጠለያው ፊት ለፊት ኳስ ሜዳው እንዳለቀ የሚገኝ ቢሆንም ወደ መጠለያው ለመግባት አይደፍሩም፡፡ “ጆሮ ጠቢውና አዋሻኪው ማንና የት እንደሆነ አይታወቅም፤ ከእነሱ ጋር ለመጨዋወት ላህ ወንዝ ነው የምሄደው” በማለት ስጋታቸውን ነግረውኛል፡፡ በዛን ሰዓት ሜዳ ላይ ለምን እንደተቀመጡም ጠይቄያቸው ነበር፡፡ “ይሄ ሁሉ ሰው ሜዳ ላይ እንደጥሬ ፈሶ እንዴት በጊዜ እቤቴ እገባለሁ” የሚሉት እኚሁ የመንደሩ ነዋሪ፤ ሁኔታውን ለመቃኘትና የሰዎችን ሁኔታ ለመታዘብ ሁሌም በዚያ ሰዓት እዛ ቦታ እንደሚቀመጡ ነገሩኝ፡፡ በመጨረሻም “ለመሆኑ አንቺስ ከተፈናቃዮቹ ወገን ነሽ” የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡ ለአካባቢው እንግዳ መሆኔን ነግሬያቸው ተሰናበትኳቸው፡፡

 

33 comments:

Anonymous said...

Girum Akerareb new. Gin man astewale? mans lib ale? Yihew be'araya Selassie Yetefeterewun kibur Yesewu lij meda lay eyebetenut new. Yefeterewun yemayresa Amlake Kidusan Egziabiher Yidresilin enji lela min enilalen.

Bewketu Teshale Bekele said...

የቤንሻንጉል ክልል ሰዎችም ሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለዚህ ዕብደት አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት አለባቸው። በዚህ ነገር መጠየቅ ሲመጣ ማዕከላዊው መንግሥትም “አልነበርኩበትም፣ የክልሉ ጉዳይ ነው” ማለት አይችልም። መሬት ለሕንዶች በነጻ በማከፋፈሉ ላይ እጁን የሚያስገባው የቤተ መንግሥት አካል ድሃ ገበሬዎች ሲፈናቀሉ የለኹበትም ሊለን አይችልም። የሚሰማውም አያገኝ።

Thanks Ephrem, for me it looks like a revenge by the government officials. I admit that there are some wrong doings by some past Ethiopian leaders. But two wrongs can not make things right, the government has to re-think its agenda. I don't want to say this, but there is no reason not see backfire again by the future generation.

Let us reconcile and prosper in the entire Ethiopia. Let us not always lag by two or three or even four decades from the rest of the world by everything. Such as racial attitude, technology. Sometimes in my head I believe that say in 30 or 40 years this will be a history like it is now a history in USA, South Africa (black and whites). But why wait for that day? especially while Ethiopia is not benefiting from it.

People let us be rational and play our role in changing this.

Anonymous said...

yehanen neger bemanebeba dasetegna negn yehan yalekut selasawochu mesedad ayedalem endih gelets aderegah bemetsafeh new enan hulam yamiyasechanekagn neger yeha selahona enam yederasabegn ena yetegodhut neger selale new yebalet maweka demo malekam new bezu endana ayenat sewoch negeru yasasebachew endalu lemawek eradetognal amesagenalehu

Anonymous said...

Interahamwe is invitable?

Gere said...

Nice one...but we need solution. We all know the truth. We need some1 to lead us. There are a lot of volunteers to sacrifice their lives for freedom.

tesfamariam said...

mechereshachin min yihone ,eskemech dires new ewokilew alehu yemilewun hizib asalifo yemiset /zonbe/the so called Amhara National DEMOCRATIC Movement eyale hizbune lesekoka and le engilit yemidarig amerar tebiyewoch .yeken jiboch ,Medhanialem yiylachew .GOD bless ETHIOPIA

Anonymous said...

sile ager tekorkureh motehal wishetam!

Anonymous said...

ብሔሩሰ ለአማራ፣ ብሔረ አማራ ውዕቱ፣ ዛቲ ይዕቲ እንተ ውስቴታ ኢትዮጵያ።
የኦሮሞ አገሩ ኦሮሚያ፣ የትግሬም ትግራይ፣...ወዘተ እንደሆነ እናውቃለን። ኢትዮጵያ ደግሞ የሁላችንም የጋራ አገር ናት። እርግጥ ነው፣ የኦሮሞ ልጅ በአማራ፣ የትግሬ ልጅ በደቡብ፣... እንድህ ተደባልቀን ነው የምንኖረው። ይህ ግን በሽዎች የሚቆጠር ህዝብ ከክልሉ ወጥቶ በሌላ ክልል እንዲሰፍር ምክንያት/መሠረት አይሆንም። መዘዋወር ህገ-መንግስታዊ መብት ነው ብለናል፤ የአማራ ተወላጅ(ወይም ሌላ) የሆነ ማንም ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ በፈለገበት የመኖር መብት አለው። ይህ ካልተቻለ የዚያኔ ኢትዮጵያ የለችም ማለት ነው። ነገር ግን በብዙ ሺዎች የሚቆጠር የአማራ(ወይም ሌላ) ህዝብ መሬቱ አልተመቸኝም ብሎ የተሻለ ነው ባለው ሌላ ክልል ላይ በራሱ መንገድ ደን መንጥሮ የመስፈር መብት የለውም፣ ህገወጥ ተግባርም ነው። የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና እስከ ጦርነት ሊያደርስ የሚችል ጉዳይ እኮ ነው። ሆኖም፣ ብዙዎችን አገዳድሎም ሰምተናል፣ እናውቃለን።
በሰፈረው ህዝብ እየፈረድኩ አይደለም። እነሱማ ተቸግረው እንጂ ከትውልድ ትውልድ ተጠብቆ ከቆየው ቀዬአቸው ባልፈለሱም ነበር። ለችግራቸው የሚደርስላቸው ቢያጡ መፍትሄ ያሉትን እርምጃ ወሰዱ። እዝህ ላይ የተዘነጋው የቤንሻንጉሉ ህዝብ ፍላጎትና መብት ነው፤ ማንም ያለፈቃዱ መጥቶ በገዛ መሬቱ ሊሰፍር አይችልምና! በክልሉ ስምምነት ቀደም ባለ ጊዜ የሠፈሩትማ(የአማራና ሌሎችም ህዝቦች) በሰላም እየኖሩ መሰለኝ።
ችግሩን በሚገባ አጥርቶ እርሱን መታገል እንጂ በሆነ ባልሆነው የአማራውን ህዝብ ሆድማስባስና በሌላው ላይ ቂም እንድይዝ ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም።
ጉዳዩን የአማራና የትግሬ(ወያኔ) የዘር ጨዋታ፣ አስጠሊታ የፖለቲካ ጨዋታ ሳናደርገው በንጹህ መንፈስ በሰዎቹ ላይ የደረሰባቸውን ኢሰብአዊ ድርጊት(መንገላታት፣ ንብረት መነጠቅ፣ ያለ በቂ ህጋዊ 'process' መፈናቀል...ወዘተ) ብቻ መቃወምና ማውገዝ አይቻልም ይሆን?

Anonymous said...

ህም! ኣይ ፖለቲካ! ቃላት የሉኝም። ያን ኣካባቢ ኣውቀዋለሁ። ዞኑ ግን "ከማይ" ሳይሆን "ካማሽ" ተብሎ ይስተካከል።

ብርሀኔ ግርማይ said...

እግዚአብሔር ይስጥልኝ ወንድሜ ኤፍሬም:: ለኔ መንፈሳዊነት የሚገባኝ አንደዚህ ነው:: አንዳንድ ያለገባቸው ሌሎች ሲበደሉ መናገርን ፖለቲካ ያደርጉታል:: በርታ!

Anonymous said...

Yih budn eskaltewogede dires belelochum hizboch yemiketil yihonal. Chuhetachin le amara
Bicha sayhon beandinet, begara yih budin endiwoged new metagel yalebin.

Anonymous said...

ኧረ በህግ አምላክ … ኧረ በባንዲራው የሚባለው ለማነው?? ወይ ፍረድ ወይ ውረድ አለ የጨነቀው፡፡

Anonymous said...

አማሮችን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲፈናቀሉና እንዲባረሩ ማድርግ አሁን ላለዉ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያስገኝለት ፖለቲካዊ ትርፍ ምን ይሆን ? ትርፉስ ምን ያህል አዋጭና ዘላቂነት ያለው ይሆን? የዚህ አይነት ፖለቲካዊ ስሌትና ቀመር ማጥንጠኛ ሳይንሳዊ ዉሉ ምን ይሆን?

ለማንኛዉም ኤፍሬም እሸቴ ግሩም ጥያቄ አንስተሃል:- “አይቴ ብሔሩ ለአማራ . . . የአማራ አገሩ ወዴት ነው?” ኢትዮጵያ አይደለምን?"

Shenkut Ayele

Anonymous said...

በጣም ጥሩ ጽሑፍ ነው ኤፍሬም። አንተ የድርሻህን ተወጥተሃል። በእውነቱ ይህን የመሰለ ወንጀል በሀገር እና በወገን ላይ ሲፈጸም በዝምታ የምንመለከት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ወደድንም ጠላንም በተባባሪነት በታሪክ እና በእግዚአብሔር ፊት እንጠየቃለን። ማናቸውን ዓይነት ኢሰብአዊ ተግባር ሲፈጸም እያየን ዝም ማለት በራሱ ወንጀል ነውና። ከዚያም በላይ ወገኖቻችን በሀገራቸው የደረሰባቸውን ስደት ከሰብዓዊነት አንጻር እንኳ ለመርዳት የሚነሳ መጥፋቱ የደረስንበትን የሞራል ዝቅጠት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። እነዚህ ወገኖች እየተጠቁ ያሉት ምንም አቅም የሌላቸው በመሆኑ ነው የሚል አቋም አለኝ። ለወገኖቻችን አቅም መሆን ያለመቻላችን በጣም የሚያሳዝን ነው። ምነዋ የሃይማኖት ሰዎች ነን የምንል ለወገኖቻችን መድረስ ተሳነን? ለሰው ልጅ መሠረታዊ መብት ለመከራከር እና ለተጠቁት ለመቆም ”የእገሌ” ዲሞክራሲያዊ/አብዮታዊ ድርጅት/ግንባር አባል/ ደጋፊ መሆን ሳያስፈልግ ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነበር እኮ! ሁሉም ነገር እኮ ፖለቲካ አይደለም። ሌላው ወያኔ በታወቀና በተረዳ የማጋጨት ዓላማ ባጠመደው በዚህ ወጥመድ ሌሎች ፖለቲከኞች ሲጠመዱበት ማየቱ በራሱ የሚያስገርም ነው። ይህ ተግባር በማንም የሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይገባው ሁሉም በአንድነት ተነስቶ ሊቃወመው የሚገባ የሰበአዊ መብት ጥሰት ነው የሚለው አመለካከት ጤነኛ ነው የሚል እምነት አለኝ። ለጉዳዩ ‘የአማራ’ ታቤላ መለጠፉ (ወያኔ የሚወደው ያለ ይመስል) ለወያኔ የተመቸ አካሄድ ነው። ሀገራችን ውስጥ የየትኛውም ግለሰብ/ቡድን መብት ሲጣስ ዝም ማለታችን አንተም እንደዘረዘርከው ገና ብዙ ጣጣ የሚያመጣብን ነው የሚል እምነት አለኝ። ተቃዋሚ ነን የሚሉት የወያኔ ‘የእጅ አዙር ደጋፊዎችም’ ወያኔ በቀደደው ቦይ እየፈሰሱ ይህን አጋጣሚ ለራሳቸውም እንኳ ግልጽ ላልሆነ ዓላማቸው ሊጠቀሙበት ከሚሞክሩ ከምር እነዚህን ወገኖች በመርዳት ላይ ቢያተኩሩ ይሻል ነበር። ፖለቲካን እንደ ኤሌክትሪክ የምንፈራ የተቀረነው ወገኖች እነዚህን ወገኖቻችንን በማቋቋም እና በመርዳት በጎ ምግባር ከመስራት የሚከለክለን ማን ይሆን? በአጠቃላይ ተግባራዊ ምላሽ ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።

Anonymous said...

ወይ የክፋታችን ልክ ብዛቱ፥ ውርስ (Legacy) ሲሉ አለማፈራቸው::

Anonymous said...

ወይ የክፋታችን ልክ ብዛቱ፥ ውርስ (Legacy) ሲሉ አለማፈራቸው::

Anonymous said...

arif new berta.ewnetan mesaf yaskebral engi ayaserem ,sle gelebaw lemawrat emengest gazyta ale

Anonymous said...

እኔ ምለው ይህ ሁሉ የሰሞኑ ጋጋታ የበዛበት ወሬ ምርር ብሎኛል!! ለመሆኑ እስከዛሬ የት ሰንብቶ ነው ሰው? መንጫጫት መንጫጫት ሊያውም ተደብቆ በፌስቡክ፣በብሎግ ምናምን ... ወገኔ ይህ የእኔ የግሌ አስተያየት ነው ምናልባት ከዚህ በመቀጠል የምነግርህን ካልሰማህ ከመንግስት ተርታ ልታሰልፈኝ ትችላለህ ስለዚህ ስማ፣ አንብብ፣ የተፈጥሮ ጭንቅላትህን ተጠቀም ከዛም የገባህን በተግባር ለመተግበር ጣር ወይም ያልገባውን አስረዳ ። ካልገባህ ደግሞ ደጋግመህ አንብብ! ታዲያ የመንግስት የበላይ ...የበታች..የጎን ምናምን አካል ከሆንክ ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድልህ። ከስተትህ የምትማርበትን መንገድ ይግለጽልህ ...መቼም አልተማርክምና ትምህርትህን ይግለጥልህ እንዳልል ለፈጣሪም ስራ ማብዛት ነው!! ነገሩ ምን ይሳነዋል ... እኔም ምኔ ይጎልብኛል? ትምህርትህን ይግለጽልህ! .... አንብብ ...
1ኛ. “የአማራ ብሔር ተወላጅ” የሚል ቃል እየደጋገምክ የኢትዮጵያዊነት መብታቸውን በፍላጎትህ አትቀይር። ቃሉ እንደመዥገር ከምላስህ የማይለቅ ወይም ደግሞ እንደ መንግስት በግድ ያንሰራፋብህ ከሆነ፥ ከመናገርህ በፊት ምን ያህል የሌላ ብሔር ተወላጆች አብረው እንዳሉበት አጥና
2ኛ. እንደው ሃገራዊ ስሜት ይሰማኛል የምትል ከሆነ ደግሞ በእምዬ ኢትዮጵያ መሬት ላይ መጥተህ ከወገንህ እኩል ችግርን ተጋፍጠህ የተደራጀና የተስተካከለ የአመለካከት ብቃት ካለው ወንድምህና እህቶችህ ጋር በመሆን ይህን የማይረባ አስተዳደር ለውጥ።
3ኛ. “ባለሁበት በሃሳብና በገንዘብ እረዳለሁ እደግፋለሁ” ካልክ እውነቱን ልንገርህ በጣም ውሸታም ነህ!! ደግሞም የእምዬ ጉዳይ አንተን አይመለከትም። ምክንያቱም ድርሻህ ከነጮቹ እኩል “በገንዘብና በሃሳብ” መርዳት ነዋ
4ኛ. “አይ ተቃውሜ በኤርትራ፣ በሱዳን፣ በኬንያ... መሬት ላይ ታጥቄ ፣ ተዋግቼ ፣ ደምቼና ቆስዬ የወገኔን ችግር እፈታለሁ” የሚል ሐሳብ ካለህ እምዬ ኢትዮጵያ ትፋረድህ! እምዬ እንዳንተ ያለ ውሸታም አትፈልግም።
የምርህንም መሮህ ጫካ ከወጣህ አንተንም ከ60ዎቹ ጎረምሳዎች ማለትም ካሁኑ ጠብደል መሃይም መሪዎች ለይቼ አላይህም ሃገሬ ኢትዮጵያ የእር በእርስ እልቂትን አትፈልግማ!!
5ኛ. “ባለስልጣኑ መንግስት በመሳሪያ ካልሆነ በሰላማዊ ትግል አይለቅም” ካልክ መች ሞከርክና? የፈረደበት 97 እንዳትለኝ! 97 ብልጥ፣ ጠንካራ አልነበርክማ! ንቃ!!!! 97ን እንደ ትምህርት ውሰድ ካልበቃህ የግብጽንና የሊቢያን ተሞክሮ ቃኝ። ሃይማኖት፣ ጾታ፣ ብሔር ወዘተ ቅራቅንቦ በማለት ሳትለያይ አንድ አቋም ያዝ። ነገ አዲሱ ጠ/ሚ ሞተ ስትባል ጥቁር ለብሰህ ቤተመንግስትን ለማየት አትሯሯጥ! እውነቴን ልንገርህ? አቋም ካለህ ነገ በወታደር ፣በአጥር በውሻና በምትሃት የማይከለል የራስህ ድምጽ የሚወሰንበት ቤተ መንግስት ይኖርሃል። በኢትዬጵያዊነትህም የበለጠ ትጀነናለህ። በአረብ ሃገር የምትንገላታው እህትህም የአረብ መጫወቻ ከመሆን ትድናለች ያለጥርጥርም ሃገሯ ላይ አምሮባት ታያታለህ። ያኔ ጠንክረህና ተዋደህ ከሰራህ የእምዬ ኢትዮጵያንም ስም ከአለም የድህነት መዝገብ ላይ በላብህ ውጤት ትፍቃታለህ።
እናም ወገኔ ጨቀጨከኝ እንዳትል። የእምዬ ጉዳይ ነው ደግሞም በብሄር ሃሳብ ከተሞላ ሁለት መስመር ይልቅ የፍቅር ያለህ፣ አቋም ይኑረን፣ የሚገነባ እንጂ የሚያፈርስ ያሁኑን መንግስት አይነት አመለካከት አይኑረን ፣ የሚል አንድ ጆንያ ብታነብ ይሻልሃል። በል ስጀምር እንደነገርኩህ ይህ የግል አመለካከቴ ነው ከጣመህ አስተላልፍ ካልሆነም ደግመህ አንብበው ምክንያቱም ይህ የእምዬ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነውና።

Anonymous said...

Demissie,
Ewnetun edezih asmreh bemtsafeh Egziabher yelbhen meshat yifetsm kemalet wechi lela kal yelegnem. Thanks sooooo much!

ድርሻዬ said...

ኤፍሬም እንደ እኔ እንደ እኔ ጥፋቱ መንግስት ተብዬው ላይ ብቻ አይደለም፤ የእነሱን የታመመ እግር እና እጅ የሌለንው የሙት ፍልስፍና ተቀብሎ አብሮ የሚታመመውን ገራገር ህዝቤም ጭምር እንጂ። ትዕዛዙ ከላይ ከምንሊክ ቤተ መንግስት እንደሚመጣ ጥያቄ አያስፈልገውም። በሞግዚት የሚተዳደር ክልል እንደሆነ ሲያወሩ ሰምተናል፤ አንተ እንዳልከው መሬት ለመቸብቸብ ብቻ ከሆነ ግን ለእዚህ ኢሰብዓዊነት ትዕዛዝ ሰጭዎችም ሆኑ ትዕዛዝ ፈፃሚዎች ነገን እንዲይስቡ አቅሉን ያድላቸው። ለነገሩ እንደሰውኛው ሳስበው የዚያች ሃገር ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ነው እግዚዓብሔርን በተስፋ መጠበቅ ግን አማራጭ የለውም።

Anonymous said...

Dear Dn. Ephrem,
I am happy that you voiced this very frustrating issue. However, what can we do to our people to help them live with liberity. As immigrants living in the free world there is no word to express this human right abuse. At least, people who have access to this information should join and be the voice for the voiceless that is humanity, that is spirituality if we are religious.! We know the government will have a deaf ear to this but people should struggle until there is a solution.
Egziabiher Ethiopian Hizbuan Yitebikiliin!

Anonymous said...

እኔ በማውቀው የትውልድ ቁጥር ለአማራ የሚጠጋ ዘር የለኝም፡፡ ከእናቴ በስተቀር ሁላችንም አማርኛን "ከአማሮቹ" ባላይ አቀላጥፈን እንናገራለን፡፡ አሁን ኦሮምኛ ባለመናገሬ ውጣ ብባል አገሬ የት ይሆን?

አይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባለራእዩ ተቆራርጦ 4000 ምናምን ስትበላ የነበርከው ደስ ይበልህ ራእይህ አሁን በግልጥ ርግጥ ሆነ፡፡

ባለፈው ስለጉራ ፈርዳ በፓርላማ ስትናገር ደን ስለጨፈጨፉ ነው፣ ሕገወጥ ሠፋሪዎች ስለሆኑ ነው፤ ጉራ ፈርዳ ምሥራቅ ጎጃም ስለሆነ ነው ብለህ ቀለድህ፡፡

ለመሆኑ ስንት መቶ ሺህ የትግራይ ወገኖቻችን ናቸው በመላ ኢትዮጵያ ከዘመናት በላይ እየኖሩ ያሉት? ይህን ታውቀዋለህ?

አይ ህወሃት/ኢሕአዴግ

Anonymous said...

d.n efrem ante yedershen tewtehal yeblaglge lega yeh eko wengel new sew yetmarwen besera meglete yasfelgal yewndmhe gudat yante gudate newna. ene gen yemteykew abatochenena yewengel astemarwcen new menew zem alacehu here egziabher yeferdbenal kalu yeferdbenal men belne new wengelune yemnastmerwe here lebe enbel begedamatu laye mekeraw sederse zeme!be hezbu lay mekera siderse zeme!meche new yemnenagerw wengel eko yehe new here lbe belu? deyakon epreme kelbe new yemnagerwe dershhen tewtahe ayzohe berta egziabher kante gare yehune.egziabhere etyopiyanena hezbuane yetbkelene chere wezei yasemane!

Anonymous said...

በኢትዮጵያችን ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ተስማምተውና ተፈቃቅደው የሚኖሩባት አገር ነች፡፡ በደርጉ ጊዜ እንዲሁም በኢህአዴግ የአንደኛው ክልል በድርቅ እና በመሳሰሉት በተጠቃ ጊዜ ወደ ተሻለው /ለምነት/ ወዳለው አገር ማጓጓዙ /ማፈናቀሉ/ “ሠፈራ” የተለመደ አሠራር ነበር፡፡ በጊዜው ምንም እንኳን አዋጪ ሥራ የተሠራ ቢሆንም በተቃዋሚዎች ትችትን ያስነሳ ጉዳይ ነበር፡፡ እንደውም “ሕዝቡ ተወልዶ ካደገበት ቀዬ አፈናቀለ” እየተባለ ሁላ ሲነቀፍ የምንሰማው ጉዳይ ነበር፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ጥቂት በድርቅ የተጎዱ በሠፈራ መልክ የተወሰዱትን አይተው ኑሯቸው ከበፊቱ የተሻለ መሆኑን ያዩ በሺዎች የሚቆጠሩ፡ አካባቢያቸው በድርቅ ያልተጎዱባቸው ሰዎች /አማራዎች/ በማን አለብኝነት ስደታቸውን በቤኒሻንጉል ጉምዝ አድርገው፣ ደን መንጥረው፣ የሰዉ አጥር ደፍረው ሰፈራቸውን መሠረቱ፡፡ ይህ የቤኒሻንጉልን ሕዝብ መናቅ አይደለም? ምን ያመጣሉ? ብለው አይደለም በዚህ ኑሮዎቸውን የመሠረቱት:: እርግጥ ነው እነዚህ ሰዎች ከአጼ ሚኒሊክ ጀምሮ እስከ ኃ/ሥላሴ ድረስ እንደሰው እንደማይቆጠሩ እሙን ነው፡፡ ግን ቢሆንም አሁን ደግሞ በተገላቢጦሽ ሁሉም ነገር ተቀይሮ እድገት የሚታይበት አካባቢ ሆኗል፡፡ ዞሮ ዞሮ ምን ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ ልክ ሌሎቹ በሰፈራ መልክ የሄዱት ሕዝቦች ይሁንታ አግኝተው በሰላም እየኖሩ ባለበት ሁኔታ እነዚህም ጥቂቶቹ አማሮች ከቤኒሻንጉል መንግሥት ይሁንታን ማግኘት አለባቸው:: ምክንያቱም ሁሉም በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ አሁንም ምንም ሳያካብዱ “ከስደት ወደ ሀገርህ ተመለስ እና እዚያው በቀዬህ አልምተህ ኑር አሁን ጊዜው የተመቻቸ ነው” በሚባልበት ጊዜም እንዲሁ ኡኡኡ ታውን አቁሞ ወደ ሀገሩ እልል እያለ ተመልሶ ቀዬውን ቢያለማ እና ቢጠቀም የተሻለ ነው እላለሀ፡፡ ለእግዚሩም ለመንግሥትም አልመች ማለት ጥቅም የለውም፡፡

Anonymous said...

ለጥያቄህ መልስ ይሆን ዘንድ፡፡ የአማራ አገሩ፡- ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ (መንዝ፣ አንኮበር፣ መራቤቴ፣ ቡልጋ፣ ምንጃር ወዘተ) ሸዋ በገሚሱ መሰለኝ፡፡ በምንም ተዓምር ቤኒሻንጉል ጉምዝ ሊሆን አይችልም፡፡

Anonymous said...

ዋው አንተ እንዴት አይነት አዋቂነህ ጃል። አቤት እውቀት። ኸረ ለኛም ይድረሰን። ስንት አይነት ሰው አለ?

Justice said...

Citizens in their own country have mobility right and freedom of settlement. People also have Moral and Ethical obligation of working hard to their abilities and feed themselves and taking care of others who needs it. In Ethiopia, doing so is declared as crime (only for one Ethnic group) and causing families to be homeless and some of them are punished to death.

Because of work, In 2005 I traveled to small cities of different Ethiopian regions. That time, my colleagues and I used to have a driver originally from Tigray region. You know what he was showing us in small town of Wolega ?, Several buildings used for business owned by people from Tigray. In his way of expression ( Yihegnaw hintsa, Yegna sew new, Yihegnawum Yegna sew new …….) . I am fine with Tigrian’s go to Wolega, Wollo, Gojjam and Gondar ….. They have a right to go and work anywhere that is their own country. However, from those Small Wolega towns, there was time Amhara people has been killed in ridicules way and Evicted, soon after replaced by Tigrians! What is this teaching us?

I listen to VOA, these newly Evicted people don’t even know what Ethiopian rulers call them. No Ethnicity thought is in their mind just natural and innocent people. One of the guy was saying ( Egnama Ethopia new yalew bilen nebere….) They are a kind of convinced as they crossed boarder outside of Ethiopia. God is watching these innocent people and I pray for his judge for injustice.

Peace for Ethiopia!

temesgen veto said...


ኧረ በህግ አምላክ … ኧረ በባንዲራው የሚባለው ለማነው?? ወይ ፍረድ ወይ ውረድ አለ የጨነቀው፡፡

temesgen veto said...


ኧረ በህግ አምላክ … ኧረ በባንዲራው የሚባለው ለማነው?? ወይ ፍረድ ወይ ውረድ አለ የጨነቀው፡፡

temesgen veto said...

ኧረ በህግ አምላክ … ኧረ በባንዲራው የሚባለው ለማነው?? ወይ ፍረድ ወይ ውረድ አለ የጨነቀው፡፡

temesgen veto said...

ኧረ በህግ አምላክ … ኧረ በባንዲራው የሚባለው ለማነው?? ወይ ፍረድ ወይ ውረድ አለ የጨነቀው፡፡

Anonymous said...

ኢትዮጵያ አሁን የማን አገር ናት?

Anonymous said...

አማራነት ኢትዮጵያዊነት ነው!
እውቅና ለሚገባው እውቅና ለመስጠትና ለማመስገን አንፍራ፡አንፈር ከኛ የተሻለ ለሰሩና ለደከሙ እወቅና መስጠትና ማበረታታተ የተሻለእንዲሰሩና አርአያ ሆነው እንዲቀጥሉ የደርጋል፡፡ለእኛም ቢሆን ጠንካራ ጎንን ማድነቅና ማበረታታት ለራሳችን ያለንን ግንዛቤም የሚያሳይ በመሆኑ ታላቅነትን ለማድነቅ ጭራ አነሁን፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ ከፊት የሚቀድመውና በጣም ጎልቶ የሚታየው አማርኛ ቋንቋችን ነው፡፡አማርኛ የራሳቸው ፊደልና መቁጠሪያ ካላቸው በጣም ጥቂት አገራት አንዱ ሲሆን ለአፍሪካም አንድ ለናቱ የሆነ የኢትዮጵያዊነት ቁንጮና ክብር ነው፡፡ ለዚህ ነው አማራነት ኢትዮጵያዊነት አንጂ ብሄረተኝነት አይደለም የሚባለው፡፡ዜግነት መለካት ያለበት በትንሽ የብሄርተኝነትና የጎጠኝነት መስፈሪያ ሳይሆን፤በራሱ በኢትዮጵያዊነት መሆንና መታየት ይገባዋል የሚባለውም ለዚያ ነው፡፡ከዚህ አንጻር እኔን ያልደገፈ ሁሉ ጠላቴ ነው ከሚል ፤ዜግነት እኔን የተከተለና የደገፈ ማለት ነው ከሚል የቂምና የጥላቻ ሰይጣናዊ መንገድ ወጥተን ዜጋ ነጻ ሆኖ መኖር የሚችልባት፡ዜጋ የሚጠቀመውም የሚጎዳውም በደጋፊነት ሳይሆን በስራውና በድካሙ ብቻ የሆነባት አገር፡ነጻ ሆኖ መኖር የፈለገ ሳይገለልና ሳይሸማቅ ከጠላትነት ሳይፈረጅ የሚኖርባት አባቶቻችን በመስዋእትነት ያወረሱንን የነጻነት አገር በነጻነት ልንኖርባት ይገባናል፡፡የዜግነት መስፈርቱ ራሱ ኢትዮጰያዊነት ብቻ እንጂ የመደገፍና የመቃወም ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚመጥነው ነጻ ሆኖ ማሰብና በነጻነት መኖር ነው፡ይህንንም ያቆዩንና ያወረሱንን ጀግኖች አባቶቻችንን ልናመሰግንና ልናከብራቸው ግድ ይለናል፡፡እነሱ፡- በልቶ መኖርን ብቻ ሳይሆን ታምኖ መሞትንም፡የናጻነት ትርጉም እስከምን ደረስ እንደሆነ ለአለም ያስተማሩ ጀግኖች፤በእምነትም በኩል በቁስና በታይታ ወደውጭ ከመኖር ባለፈ ቅጠል ቀንጥበው ጤዛ ልሰው አለምን በመናቅ ወደውስጥ እየኖሩ እምነትን ያቆዩን የእምነት አርበኞች ናቸው፡፡ ለእነሱ ሁሉም ነገር ከኢትዮጵያዊነት በመለስ ነው፡፡ኢትዮጵያዊነት ቀይ መስመር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማቆየት በጎራዴና ጋሻ ታንክና መትረየስን መክተዋል፤በህይወት መስዋእትነት የእሳት ላንቃ አጥፍተዋል፡፡
ስለዚህ በማንኛውም መንገድ ለሃገርና ለኢትዮጵያዊነት ለደከሙ እውቅና መስጠት ተገቢ ነገር ነው፡፡
በእነዚህኛዎቹ (በዘመነኞቹ)ግን፡-
-አጀንዳቸው በግለሰብ፡በአካባቢና በጎሳ ላይ ለተመሰረተ ስለሆነ የ30 እና የ50 አመት እቅድ የላቸውም፡አገርን በመሸጥ ከሚያገኙት ቢሊዮን ዶላር በመቀንጨብ እየሰሩ በማፍረስ ለሚጫወቱት ልማት ለሚሉት ነገር እንኳን የራሳቸው ስም መጠሪያና ማስታወቂያ ብቻ ነው
ብዙ አጠራጣሪና በታሪክም ፊት ምህረት የሌለው አጠያያቂና አሳፋሪ እውነታዎች በጉልህ እየታዩ ናቸው፡፡ኢትዮጵያዊነትን እንደጦር የሚፈሩ፤ህልውናቸው በኢትዮጵያዊነት ኪሳራ ላይ ብቻ የተመሰረተ፡መለያየትን፡ቂምና ጥላቻን ዘርተው በማጨድ በእንክርዳድ የሚበለጽጉ ህቡአን ናቸው፡፡
መገለጫቸው፡-
-ሁሉም ነገር የህልውናቸው መሰረት ነው፤ደጋፊ እንጂ መሃል ሰፋሪና ተቀነቃኝ የሚባል ነገር አይታወቅም፤ደጋፊ ያልሆነ ሁሉ ጠላት ስለሆነ በጥርጣሬና በአይነ ቁራኛ ከመታየት አያመልጥም፤ የህልውና ጥያቄ ስላለበት ሁሉ ነገር ስውር አጀንዳና አጠራጣሪ ነው፡በግድ የሚጫን እንጂ ተማምኖ መሄድ የሚባል ነገር የለም፤
-የኢትዮጵያዊነት ጥያቄን በማሳነስ ቢቻል በማጥፋት ልዩነትን ማጉላት :ልዩነቱንም ለመፍጠር ከግለሰብ እስከ ሃገር፡ከፖለቲካ እስከ ሃይማኖት ተቋማት ድረሰ ማስፋት ነው፡፡
-በመስዋእትነት ታፍራና ተከብራ የኖረችን አገር በመቆራረስ ለዚያም ለዚያም በማከፋፈል እንደጠላት ገንዘብ በማድፋፋት ባለቤቱን በድህነት እንዲኖር የማድረግ የበቀል ተግባር መፈፀም ነው፡፡
ለዚህ ነው አሁን አሁን አየተፃፉ ያሉ አንዳንድ የታሪክ መፃህፍት ነን ባዮች ምንጫቸው ከዚሁ ሰይጣናዊ መንፈስ የተቀዱ በመሆናቸው እናት ኢትዮጵያን በማሳነስና ዝቅ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ማንነትን አጥፍተው ፡እነሱ አገር ሸጠው ካገኙት እርጥባን ጠብ በማድረግ፡ ቀና ብሎ የማያይ ለእለት እንጀራው ሲል ብቻ የሚኖር ጥገኛ ዜጋ እና እንደፈለጉት የሚነዱትን ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተጉ ይገኛሉ፡፡
ስለዚህ ነገርን ከምንጩ፡ችግርን በእንጭጩ ነውና ኢትዮጵያዊነት የሚገደን ሁሉ ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው እላለሁ፡፡