Saturday, April 13, 2013

ቼሪ በዲሲ፣ ባሕር ዛፍ - በሸገር


(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)፦ ቅዳሜ ኤፕሪል 13/ሚያዚያ 5 በዲሲ ከተማ ታላቅ የአደባባይ ክብረ በዓል ቀን ነው። በየዓመቱ በዚህ ቀን አይደለም የሚከበረው። የኢትዮጵያ ሊቃውንት እንደሚሉት “ኢይዐርግ - ኢይወርድ” ኖሮበት ሳይሆን ከአየሩ ሁናቴ ጋር የሚወጣ እና የሚወርድ በመሆኑ ነው። ስለ በዓሉ ጥቂት ላጫውታችሁ። በዚህ ሰሞን የሚከበረው ዓመታዊ የዲሲ የአደባባይ በዓል “የቼሪ ዛፍ ማበቢያ” (Cherry Blossom Festival) በዓል ሲሆን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎችና ከአገር ውስጥም የሚሰበሰቡ ቱሪስቶች የሚያደምቁት በዓል ነው። “ቼሪ” የጃፓኖች ዛፍ ስትሆን ወደ አሜሪካ ከመጣችና ከጸደቀች አንድ መቶ ዓመት ሊሆናት ነው። ታሪኩ እንደዚህ ነው።

ታሪክ

ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ቀደም ብሎ ጀምሮ ወደ ጃፓን ይጓዙ የነበሩ አሜሪካውያን በጃፓን ዝነኛ በሆነችው የቼሪ ዛፍ እና አበባዋ ይመሰጣሉ። ወደ አገራቸው ሲመለሱም ዛፉን በብዛት ለማስመጣት እና ለመትከል ፍላጎት ያድርባቸዋል። አንዳንዶቹም በግላቸው ዛፏን ያጸድቃሉ። ነገር ግን በግላቸው ማጽደቃቸው ብቻ እንደ ጃፓኖቹ አምሮና ደምቆ ስላልታያቸው በዋና ከተማቸው በዋሺንግተን ዲሲ ለመትከል ይፈልጋሉ። ፍላጎታቸው ሲንከባለል ቆይቶ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አሥርት ጀምሮ መሳካት ይጀምራል።

 

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ የመጡት ዛፎች 2000 ሲሆኑ ዘመኑም እ.አ.አ 1910 ነበር። ቀጥሎም በቀዳማዊት እመቤት ሔለን ታፍት ትብብርና ፈቃድ እንዲመጡ የተደረጉ 3000 የቼሪ ዛፎች ይተከላሉ። ከዚያ በኋላ ባሉ ዓመታትም ዛፎቹን የማስመጣት እና መትከል ሥራ በግብርና መሥሪያ ቤቱ አማካይነት መከናወኑ ይቀጥላል። ዛፎቹ አድገው፣ አብበውና ከተማውን አሳምረው ሲታዩም እነርሱ በሚያብቡበት በዚህ ወራት ዝግጅት ማድረግና ማክበር እየተለመደ ይመጣል። ለዚህም ቀዳማውያት እመቤቶች ድርሻ ከፍ ማለት ይይዛል። እነሆ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ጃፓኖችና አሜሪካኖች የአበባ ዛፎች የመለዋወጥ ሰፊ ልምድ አዳብረዋል። ሁነኛዋ መታወቂያ ግን የቼሪ ዛፍ ናት።

 

ቼሪ በጃፓንና በሌላው ዓለም

 

ጃፓኖች “ሐናሚ” የሚባል በአበቡ የቼሪ ዛፎች (ሳኩራ) ሥር የመንሸራሸር ባህል አላቸው። ከ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተለይም ጃፓኖቹ ዘመነ-ሐያን በሚባለው (ከ8ኛው-12ኛው መቶ/ክ ዘመን የዘለቀ) ሥርዓት የተጠናከረ ነው። ልማዱ አስቀድሞ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ዘንድ ብቻ ሲዘወተር የቆየ ቢሆንም በዘመን ብዛት ግን የሌላው ተርታ ጃፓናዊ ባህል ሊሆን በቅቷል።

 

ጀፓኖች የቼሪ ዛፍ ማበቢያ ወቅት የሆነውን የማርች ወር መጨረሻ እና የኤፕሪል ወር መግቢያ በልዩ ስሜት ይጠብቁታል። ቀዝቃዛው ወራት እየተጠናቀቀ ሙቀቱ ሲመጣ፣ አየሩ እንደሚቀየርበት ጊዜ ሁናቴ በተለያዩ የጃፓን ከተሞች ዛፉም እንዲሁ በተለያዩ ጊዜያት ያብባል። ይህንን ወቅትም ለማክበር ዐውደ ዓመት ሆኖ ይቆያል። ጃፓናውያኑም የሚደሰቱበትና የሚዝናኑበት ወቅት ይሆንላቸዋል።

 

ከመዝናናቱም ጋር “ቼሪ” ያላት አገራዊ ተምሳሌት ብዙ ነው። በብርዱና በቅዝቃዜው ተዳፍኖ የነበረው አገር በሙቀቱና በሚፈነዳው አበባ ውበት እንደሚያሸበርቀው ሁሉ ቼሪም የትንሣኤና የሕይወት ምልክት ሆና ትታያለች። ምናልባት ከአገራችን የአደይ አበባ፣ የመስከረም ወር ስሜት፣ ከአዲስ ዓመት ሁናቴ ጋር ይመሳሰላል።

 

ከጃፓንም ውጪ ጃፓናውያን በሔዱባቸው አገሮች ዛፉን የመትከልና የማጽደቅ ልማድ አላቸው።   በብራዚል የሚኖሩ ጃፓናውያን ዛፉን በዋና ከተማዋ በሳዎፓውሎ በስፋት በመትከላቸው ይታወቃሉ። በአውትራሊያ፣ በቫንኩቨር ካናዳ፣ በሐምቡርግ ጀርመን፣ በኔዘርላንድስ፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በስታፎርድሻየር እንግሊዝ እና በቱርክ የቼሪ ዛፍ አበባና ባህሉ እንዲለመድ ተደርጓል።

 

ባሕር ዛፍ

የቼሪ ዛፍ ወደ አሜሪካ እንዲመጣ ሙከራ በተጀመረበት ሰሞን በአገራችን ደግሞ ባህር ዛፍ እየገባ ነበር። ቀይ ባሕር ዛፍ፣ ነጭ ባሕር ዛፍ፣ ሳሊኛ ባሕር ዛፍ፣ ሽቶ ባሕር ዛፍ በየዓይነቱ ከአዲስ አበባ ጀምሮ እየተተከለ ከከተማነት መስፋፋት ጋር የገጠመው የማገዶ እንጨት ችግር እንዲቀረፍ በዳግማዊ ምኒሊክ ግንባር ቀደም መሪነት በመተግበር ላይ ነበር።

 

አሜሪካውያኑ ለአንክሮ-ለተዘክሮ ማለት ለውበት ቼሪን ሲያስገቡ እኛ ደግሞ እንጀራ ለማብሰያ፣ ጎጆ ቤታችንን ለማቆሚያ የሚጠቅመንን ባሕር ዛፍ እናስገባ ነበር። እንዲያው ነገሩን ሳየው የዛሬ 100 ዓመት ለማገዶ እንጨት እንዳልተቸገርን ዛሬም ማገዶ ፍለጋው ላይ ነን። ያኔም እናበስልበት የነበረው መንገድ ዛሬም ያው ፈቅ አላለም።

 

አጅሬ ባሕር ዛፍ የዕለት ችግራችንን ለመቅረፍ በቶሎ ቢደርስም እግረ መንገዱን ግን ዘላቂ የሆነ ችግር እንደፈጠረ ባለሙያዎቹ ሲናገሩ እንሰማለን። ከሳር አቅም እንኳን እያደረቀ መሬቱን ባዶ አድርጎ የጎርፍ ሲሳይ እያደረገ።

 

ቼሪ ከውበት እና ከቁንጅና ጋር እንደሚያያዘው፣ ባሕር ዛፍ ደግሞ የዕለት ተዕለት ኑሮ መደጎሚያ ነው። የባሕር ዛፍ ፍላጎቱ ያልተሟላለት ሰው ቼሪ ፍለጋ ሊሔድ አይችልም የሚል ፍልስፍና ቢጤ መጣብኝ። “ባሕር ዛፍ የለው ቼሪ ይንቃል” ተብሎ ያልተተረተው ቼሪ አገራችን ስላልገባ ነው።

 

በርግጥም እውነት ነው። ሰው ከዕለት ፍላጎቱ የተረፈ ነገር ማሰብ የሚችለው ያቺው ውሎ ማደሪያው ስትሟላለት ብቻ ነው። እንዲያውም “ሕዝባችን መጽሐፍ ማንበብ አይወድም፣ አርት አያፈቅርም” ምናምን ለሚሉ ሰዎች “ያንን ማድረግ የሚችሉ የዕለት እንጀራቸው የተሰጣቸው ብቻ ናቸው” የሚል መልስ ይከሰትልኛል። ለዚህ ደጋፊ ብዙ ተረቶች ማምጣት ይቻላል። “የደላው ሙቅ ያኝካል፣ ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት፣ አላንድ የላት ጥርስ በዘነዘና ትነቀስ፣ ዓባይ ማደሪያ የለው - ግንድ ይዞ ይዞራል (ቦንድ ይዞ ይዞራል አላልኩም)” ወዘተ።

 

ታዲያ ይኼ ባሕር ዛፍ ብቻ የመፈለግ ልምድ ከጥንትም ጀምሮ ሲከታተለን ቆይቶ ውጪ አገር ሄደንም ቼሪ ለማድነቅ ስንቸገር እንገኛለን። ባሕር ዛፍ እና ቼሪ የሚሉትን በደረቁ አትተርጉሙብኝ። ከፍ ብዬ በጠቀስኩት አግባብ ይወሰድልኝ። በዲሲ አካባቢ እየኖርን ይኼንን በዓል ለመመልከት የምንወጣ ኢትዮጵያውያን ጥቂት ብንሆን ብዙም አይደንቅም። ነገርየው ባሕር ዛፍ አይደለማ።

 

ዲሲ ከሚገኙ ሙዚየሞች በአንዱ የምትሠራ ኢትዮጵያዊት ስለ ሙዚየሙ እየነገረችኝ ነበር -  በያ ሰሞን። መግቢያው በነጻ ነው። ነገር ግን ሔጄ አይቼው አላውቅም። ለራሴ ውስጤን እየወቀስኩ “ሌሎችስ ኢትዮጵያውያን ይመጣሉ?” አልኳት። “በጭራሽ” - መለሰችልኝ። በየምግብ ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ ተኮልኩለን እናመሻለን እንጂ ሙዚየም የመሔድ ልማድ የለንም። “የባሕር ዛፍ ሲንድሮም” ልትሉት ትችላላችሁ።

 

ባሕር ዛፍ ለጊዜያዊ ችግራችን ማባረሪያ ብለን አስገብተነው የአገር ውስጡን ነገር በሙሉ ተክቶና አጥፍቶ መቀመጡን ስታስተውሉ አንዴ ከምዕራብ አገሮች፣ አንዴ ከምሥራቅ አገሮች፣ ለጊዜያዊ ችግራችን ብለን የምናስገባቸውን ፍልስፍናዎች፣ አሠራሮች፣ መመሪያዎች፣ ፖሊሲዎች አያስተውሳችሁም?

 

የጥንቱን እንኳን ብንተወው፣ በዘመናዊቱ ኢትዮጵያ ያለው አሠራራችን አንድ ሰሞን የፈረንሳይ ነበር። ባቡሩም ምኑም ምኑም። ከዚያ ከእንግሊዞቹ ጋር ፍቅር ወደቅንና የመኪና መሪያችን ሳይቀር በግራ ሆነ። ከዚያ ደግሞ አሜሪካኖቹ ሲመጡ እንግሊዝን ትተን አሜሪካ ጉያ ገባን።

የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው፣

በ’ንግሊዝ አናግሪያቸው” ብለን ዘፈንን። (አሁን ደግሞ በት/ቤቶቻችን “አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ያስቀጣል” እንላለን አሉ።)

 

ከአሜሪካኖቹ ቀጥሎ አብዮት ፈነዳና ራሺያ ጠቅልላ ወሰደችን። አሁን ደግሞ የቻይና የግል ንብረት ሆነናል። ነገ ደግሞ ብራዚልና ሕንድ ሲጠነክሩ ይጠቀልሉን ይሆናል። ሕንድ እንኳን መሬታችንን “በሰፊው እያለማ” ጀምሮናል።

 

ስንደሰት፣ ስናዝን … ስንስቅና ስንለብስ … የኑሮ መጠናችንን ስንለካ ሁሉም በውጪ መለኪያ ነው። “ይህንን ነገር በተመለከተ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በእንትን፣ በ ….. እና በ… የታየና የተመሰከረለት ነው” ብለን ማረጋገጫ ካልሰጠን የሠራነውን ማንም እውነት ብሎ አይቀበለውም። በንግግራችን መካከል አንድ ለየት ያለ የውጪ አገር ሰው ስም ካልተጠቀሰ ምሁርነታችን ሚዛን አይደፋም። በራሴ ጽሑፍ ውስጥ ስንት የእንግሊዝኛ ቃል እንደማስገባ ሳየው … ‘አይ ባሕር ዛፍ’ …. ብዬ በራሴ እስቃለሁ።

 

ነገረ ቼሪ ወባሕር ዛፍ በዚህ ቢፈጸምስ … ለጊዜው?   ይቆየን - ያቆየን

(ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው።)

4 comments:

Tedy said...

ዺን ኤፍሬም ስለ መሳጩ መጣጥፍህ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ። ማለፊያ ነው። እኔም የተወሰነ ለማለት የሎሎች አገራት ቴክኖሎጅን መጠቀሙስ ባልከፋ ነበር። ችግሩ ግን አጠቃቀሙ ላይ ነው። ብዙውን ጊዜ “የቆጡን አወርድ ብላ፣ የብብቷን ጣለችው” አይነት አባዜ ነው ያለብን። ሁሉንም ነገር እንደ ወረደ ለመጠቀም እንሞክራለን። ለምን፣ እንዴት፣የት የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ማንሳት አንፈልግም። ለምሳሌ ባህር-ዛፍን ብንጠቅስ፤ ብዙ ባለውለታችን ነው። ባለሙያዎቹ ግን ችግር አለበት ሲሉ፤ ለምን እንደተከሰተና ሊወሰድ የሚገባውን መፍትሔ አይጠቁሙም። እንዲያውም ችግር አለበት ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የጻፈልንም ያው የውጭ ዜጋ ነው። የእኛዎቹም ተቀብለው አስተጋቡት።በዚህ የተነሳም ሕዝቡን ግራ አጋቡት፤ አንዳንዶቹም ባህር ዛፍ ላይ ጽንፈኛ አቋም ያዙ። እሱን የተመለከተ ጽሑፎቹን በተኑ፤ ማስታወቂያም አስነገሩ። “ችግር” ካሉት ውስጥ አንዱ አሁን ባንተ ጽሑፍ ያየሁት አመለካከት ነው “ከሳር አቅም እንኳን እያደረቀ መሬቱን ባዶ አድርጎ የጎርፍ ሲሳይ እያደረገ።” ለምን ሳር ከስሩ ጠፋ? የውጭ ስለሆነ ይሆን? ሳር ከውስጡ እንዳይበቅል የሚያደርጉ አገር በቀል ዛፎች የሉንምን? ለእኔ የችግሩ መንስኤ፤ ከባህር ዛፉ ሳይሆን ከእኛው ነው። እሱማ ባይኖር ኑሮ፤ አገራችን አንደ ስንዴው የማገዶና የቤት መስሪያ እንጨት ተመጽዋች ትሆን ነበር። ገበሬውንም ከእህል እጥረት በተጨማሪ የጎኑ ማረፊያ፤ የብርድ መከላከያና ያገኛትን ማብሰያ ያጣ ነበር። አዲስ አበባ ውስጥ በባህርዛፍ ማገዶ ሽያጭ የሚተዳደሩ ከ15 ሽህ ያላነሱ ዜጎቻችን ምን ይውጣቸው ነበር? ሌሎችን መጥቀስም ይቻላል። ይሄን ባለውለታ እንዲህ እንዲወቀስ ያደረገው ፤ በወቅቱ ወዳገራችን ሲገባ፤ አብረው መደረግ ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ስላላሰብንባቸው ነው። ያገኙትን መጉረስ ጣጣው ብዙ ነው። ስናስፋፋው የት ቦታ የሚለውን አላሰብንበትም። ባሕር ዛፍ ውሃ አጠር ከሆነ አካባቢ ከተተከለ-አዎ በስሩ ሌሎች ነገሮች እንዲ በቅሉ አያደርግም። ይሄም ከእድገቱ ጋር የተያያዘ ነው። በፍጥነት ለምርት ለምድረስ፤ ብዙ ውሃ ይጠቀማል። ስለዚህም ሌሎቹ ከባህር ዛፍ ጋር ሊወዳደሩ ስለማይችሉ፤ ይደርቃሉ ወይም ሳይበቅሉ ይቀራሉ። በዚህ የተነሳም አጼ ምንሊክን ሊወቅሱና ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞክሮ ወገኖች ብቅ ብለዋል። እኔ ግን እጅግ በጣም አከብራቸዋለሁ። አርቆ አስተዋይ መሪያችን እንደነበሩ አንዱ ማሳያም ነው። በተለይ በወቅቱ የነበረው አማካሪ ታላቁን ቦታ ይይዛል። መንግስታቸውን ለጊዜው በማገዶ ችግር ምክንያት ከቦታው እንዳይነሳ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፤ ለአካባቢው ተስማሚ የሆነ፣ ይሄን ዘመን ተሻጋሪ ድንቅ ዛፍ እንዲያስገቡ መምከሩ ነው። በምክሩ መሰረትም ይኸው የእንጦጦ ተራራን ታደገው። ከተራቆተበት ተመለሰ። እንደ ወሎና ሃረር አካባቢ እንዳሉት፤ ያገጠጡ ተራራ ከመሆን ዳነ። ባህርዛፍም ትክክለኛውን ቦታ ስላገኘ፤ የሚጠበቅበትን አገልግሎት በወቅቱ ለነበረው ሕብረተሰብ ሰጠ። ለአካባቢ ጥበቃም እንዲሁ። በጫና ብዛት ጠፍተው የነበሩ አገር በቀል ዛፍች፤ ፍሬአቸው በወፍና በንፋስ ከሌላ አካባቢ ሲመጣ፤ ጥላ ከለላ ሆኖ ተቀበላቸው ፤ አሳደጋቸውም። እንጦጦን የሚያውቅ የባህርዛፍና የአበሻ ጽድን አብሮ መኖር በቀላሉ ማየት ይችላል። ሳሩም እንዲሁ እንደ ጉድ ነው። ቦታውን ካገኘ-የማይሆነው የለም። ካለቦታው ከገባ ደግሞ ለሃሜተኞች እራት ይሆናል፤ “ባጎረስሁ ተነከስሁ” እነዲሉ ፤ ይቆረጥ፤ ይጥፋ የሚል መግለጫና አቋም ይያዝበታል። ይሄው ነው የእኛ ኢትዮጵያውያን ስራ። ራሳችን ከተሳሳተ ቦታ ወስደን፤ ይሄው ይሄ እኮ! እያልን ጣታችንን መቀሰር። ሌሎችንም ቴክኖሎጂዎች እንዲሁ ነው። መኪና ባይገባልን ኑሮ፤ ያው በቅሎና እንትን ላይ ተጣብቀን እንቀር ነበር። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ብዙ ንገሮች አሉን። ሌሎቹ የራሳቸው የሆነውን ምግብ፤ በቀላሉ ለመስራት ስንት የማቀነባበሪያ ማሽን አላቸው!? ድንችን ወይም ስንዴን በስንት ማሽን ውስጥ እንደሚያሰማምሩት ልብ እንበል። ወደ እኛዋ ጤፍ እንምጣ! ያው በምጣድ፤ በመቅቢያ (ቅሉ-ወደ ፈረንጅ ፕላስቲክ)፤ እዚያ እንዳለ ነው። አሁን ፈረንጆች ጥቅሙን ስላወቁ፤ ማሽን ስራው ላይ እንቅልፍ አጠዋል። እናም የእኛን ትቶ የፈረንጅን የመቀበል አባዜ ብቻ ሳይሆን ያለብን፤ የእኛውንም ለማሻሻል ጊዜ ወስዶ ማሰብ ያቆምን ይመስለኛል። ሳስበው፣ ሳስበው አባቶቻችን በወጠኑልን ቴክኒክ እየተጠቀምን፤ በውጩ ፓለቲካ የተሳከርን ይመስለኛል። ስለዚህ-ወደ ራሳችን ብንመለከት፤ የሌሎቹንም ቴክኖሎጅዎች ስንናስገባ ከእነ መሰረታዊ መረጃቸው ቢሆን ምንኛ ባማረ!
Anonymous said...

Thanks, very nice view- learned a lot.

Anonymous said...

selam dn ephrem endet aleh?eski ebakihn kechalk sele whight house corospondant diner and neger belen ene kezih befit semichew alawukim neber tinish eski abrarteh beza mesach metatifih asnebiben ameseginalew!

Anonymous said...

Aygebachehum libel? Bahir zaf yegebaw eko bedenb tetentobet Ethiopian endet enadrkat teblo eko new. Bizuwochachehu "conspiracy" yemilew word ke wordnet besteker astewlachu atawkum. Silezih bahirzaf is the part of the conspiracy. Beka hagerachinin lematfat kewesenut andu menged new. D/N Ephremin chemro most of habesha blogers scare to talk about conspiracy, why? Tell the truth die real.