Tuesday, April 9, 2013

አፈወርቆች(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)፦ ከሰሞኑ “ፋኖስና ብርጭቆ” የምትባለውን የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤልን ግጥም በፌስቡክ ገጼ ላይ ለጥፌ ነበር። “ስንቶቻችሁ ይህንን የክቡር / ከበደ ሚካኤልን ግጥም ታስታውሣላችሁ? በልጅነቱ ይህንን በቃሉ ይወጣ የነበረ አሁንም ያልረሣ ካለ እነሆ ካንገቴ ዝቅ ብዬ አክብሮቴን ልግለጽ” ከሚል ማስታወሻ ጋር። ለራሴ በገረመኝ መልኩ ብዙ ወጣት ፌስቡከሮች ግጥሙን በቃላቸው አሁን ድረስ እንደሚያውቁት በመግለጽ ትዝታቸውን አስፍረው ተመለከትኩ። ከእነርሱ መካከል ደግሞ ሁለቱ ስለ ግጥሙ ከማንሣት ባሻገር፣ ግጥሙን ደግም ክፉም ሳይሉ፣ ይልቁን ከበደ ሚካኤል ባንዳ እንደነበሩ አንስተው አለፉ። ነገሩ ገብቶኛል። “ግጥማቸው ምን ሸጋ ቢሆን፣ ያው የጠላት አገግጋይ ናቸው” የሚል አንድምታ አለው።

 

እርሳቸው በጠላት ወረራ ዘመን ምን ሲያደርጉ እንደነበር ምንም የማውቀው ነገር ስላልነበረ ሐሳብ ቢሰጠኝ ብዬ ፍተሻ ገባኹ። ስለ እርሳቸው አጭር ሐተታ ያቀረበው “ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ” ከበደ የተወለዱበት ዓመት እ.ኤ.አ 1914 ወይም 1915 (1907 ወይም 1908 ዓ.ም) እንደሚሆን ይጠቅሳል። ጣሊያኖች በእ.ኤ.አ 1936 (1928 ዓ.ም) ሲመጡ እርሳቸው 20 ዓመት አካባቢ የሚሆናቸው ወጣት ነበሩ ማለት ነው። ለጣሊያኖቹም በሬዲዮ ባለሙያነት ማገልገላቸውን አንሥቶ ምን እና እንዴት እንዳገለገሉ ብዙ መረጃ አይሰጥም።

 

ጣሊያን ከተሸነፈ፣ ነጻነት ከተመለሰ እና ባንዲራችን ወድቆ ከተነሣ በኋላ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ሞገስ እንዳገኙት እንደማንኛቸውም ባንዳዎች ሁሉ ከበደም በከፍተኛ የሥልጣን ወንበሮች ላይ ተቀምጠው አገልግለዋል። በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በትምህርት ሚኒስትር፣ ብሔራዊ ሙዚየም፣ ፖስታ ድርጅት ወዘተ ሠርተዋል።
 
ከበደ ሚካኤል አሁን ድረስ የሚታወሱትና የመወያያ ርዕስ የሆኑት በባለሥልጣንነታቸው ወይም ጣሊያንን በማገልገል-ባለማገልገላቸው ሳይሆን በጻፏቸው መጻሕፍትና ለትውልድ ባበረከቱት ሰፊ ዕውቀት ነው። ከጻፏቸው መጻሕፍትና ድርሰቶች መካከል “ብርሃነ ኅሊና፣ ታሪክና ምሳሌ፣ የትንቢት ቀጠሮ፣ ኢትዮጵያና ምዕራባዊ ሥልጣኔ፣ ከይቅርታ በላይ፣ ሮሜዎና ዡልየት፣ ጃፓን እንደምን ሰለጠነች፣ ታላላቅ ሰዎች፣ ትልቁ እስክንድር፣ የዓለም ታሪክ፣ አቶ በላይነህ ወይም የቅጣት ማዕበል፣ ግርማዊነታቸው በአሜሪካ አገር፣ የቅኔ አዝመራ፣ ዓጼ ካሌብ፣ ዓጼ ካሌብ፣ አክዓብ የሚሉት ይገኙበታል።
 
ግብታዊው አብዮት ሲፈነዳ ያላቸውን ቤት ንብረት በሙሉ አጥተው በድህነት ሕይወታቸውን ገፍተዋል። ባለቀ ዘመናቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር የዶክትሬት ዲግሪ ከማግኘታቸው በስተቀር በተለይ በዘመነ ወታደራዊ ደርግ ስማቸው ሳይጠራ ኖረዋል። በግጥሞቻቸው የብዙ ሕጻናትን የዕውቀት ዓይን እንዳልከፈቱ ድህነት ዕጣ ፈንታ ሆኗቸው አልፈዋል። በ1991 ዓ.ም ወደማይቀረው ዓለም እስኪሔዱ ድረስ።
+ + +
በተያያዘ ዜና (አለ ጋዜጠኛ) አገራችን ካፈራቻቸው ታዋቂ ፀሐፊ፣ ዲፕሎማት እና ባለሥልጣን መካከል አንዱ የሆኑት አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስም ባንዳነታቸው እና ሌላው ችሎታቸው መሳ ለመሳ እየመጣ ችሎታቸውን የሚያነሣ ባንዳነታቸው፣ ባንዳነታቸውን የሚያነሣ ችሎታቸውን ሳይጠቅስ የማያልፋቸው ሰው ነበሩ።
 
አፈወርቅ በቤተ ክህነት ትምህርት የሰለጠኑ ነበሩ። ከዚያም አልፎ ከፍተኛ የሥዕል ችሎታ ስለነበራቸው ያንን ችሎታቸው ለማጠናከር ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ስዊዘርላንድ ብሎም ወደ ጣሊያን ለመሔድ የቻሉ፣ በጣሊያን አገር አማርኛ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያስተማሩ፣ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የመጀመሪያ ረዥም ልቦለድ ነው የሚባለውን “ልቦለድ” መጽሐፍን የጻፉ፣ ከዚያም ባሻገር “ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” እና “የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ” የተሰኙ መጻሕፍት ያዘጋጁ ብሩህ አዕምሮ የነበራቸው ሰው ነበሩ።
 
ይሁን እንጂ ጣሊያን አገራችንን በወረረባቸው በነዚያ ክፉ ዘመናት ከጣሊያን ጋር በማበር እና ግንባር ቀደም የፕሮፓጋንዳ ማሺን በመሆን አገራችንን እና አርበኞችን በማዋረድ ሥራ ላይ ተሠማርተው ቆይተዋል። አፈወርቅ “የቄሳር መንግሥት መልዕክተኛ” በሚባለው ጋዜጣ ላይ እንዲህ አሉ፦
 
“የኢጣሊያ ሠራዊት ከዚህ ሲደርስ ጥቂቶች በጣም ጥቂቶች ብቻ ወደዱር ተሰማሩ። … ስለምን፣ እንኳንስ እነሱ ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ሲያሰኝ የነበረው ንጉሥ አንበሳነቱ ቀርቶ ጥንቸል ሆኖ ፈርጥጦ መሄዱን ያውቃሉ። እነዚህ የዱር ትሎች መሸፈታቸው የደሃውን የአማኙን በሬ እየሰነደቡ ለመብላት ብቻ ነው፤ ሌላ ትርጉም የለውም”። (መስከረም 13/1929 ዓ.ም)
 
አፈወርቅ በዚህ መርዛማ ብዕራቸው “ትሎች” ያሏቸው በዱር በገደሉ የሚጋደሉትን አርበኞች እንደሆነ ልብ ይሏል።
+ + +
 
እንደ አፈወርቅ ሁሉ ከፍ ያለ ስም ያላቸው እና ለጣሊያኖች ገባርነት የገቡት ሌላው ሰው ደግሞ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ናቸው። የሚገርመው ነገር ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ አርበኞችን ለጀግንነት የሚያነሳሱና እናት አገራቸውን እንዲከላከሉ የሚያደርጉ ዘፈኖችን በመድረስ ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ቢሆንም ጦርነቱ ሲጀመር ግን አቋማቸውን ከአሸናፊው ጋር አስተካክለው የጣሊያኖቹ አገልጋይ ሆነዋል።
+ + +
 
እንደ ምሁራኑ ሁሉ በተለያየ የሥልጣንና የሹመት ወንበር ላይ ያሉ ባለሥልጣናት በየራሳቸው ሚዛን ይጠቅመናል ባሉት ምክንያት ባንድነቱን ተቀላቅለዋል። ለፋሺስቶቹ ወረራ እና አገዛዝ ዕውቅና በመስጠት፣ በየዱሩ በየበረሃው ያለውን አርበኛ ዓላማ ስሑት መሆን በመስበክ፣ በስደትና በዝርወት የነበረውን ኢትዮጵያዊ በማራከስ፣ በአገር ውስጥ ያለው ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ብዙ ጥረዋል።
+ + +
 
ከዓለማውያኑ ምሁራንም ውጪ የጣሊያኖችን ወረራ በጽንዓት የምትቃወመውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አከርካሪ ለመስበርና አርበኝነቱን እንዳታግዝ ለማድረግ ፋሺስት ጣሊያን ብዙ ካህናትን፣ ገዳማውያንንና መናንያንን ከመፍጀቷም በላይ የሥልጣን ጥማት ያላቸው የተለያዩ የቤተ ክህነት ምሁራንን በመያዝ ተጠቅማባቸዋለች። ሰማዕታቱ እነ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል የሕይወት መስዋዕትነት እንደከፈሉት ሁሉ የእነርሱን ተግባር የሚያራክሱ ሌሎች ባንዳ ሊቃውንትም ተነስተው ነበር።
+ + +
 
ለጊዜው ባንዳ የሚለውን “ግብረ በላ” በሚለው እንያዘው። ፍላጎቴ የተለያዩ ባንዳዎችን ሥራና ማንነት ለመዘርዘር ሳይሆን አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ለመጠየቅ ነው። እነዚህ ብሩኅ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች፣ ከዚህ ሁሉ የዕውቀት ሀብት ጀርባ የክፉዎች ተባባሪ ለመሆን እንዴት ቻሉ? ዕውቀታቸው ኅሊና ያላተረፈላቸው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ሳገኝ በየዘመኑ ለሚነሱት ግብረ-በላዎች ጠባይና ግብረ በላዊ ሕይወት መልስ አገኛለኹ ብዬ እገምታለኹ።
 
አማራጭ ከማጣትና የዕውቀትና የችሎታቸውን አናሣነት ከኃይለኞች ጋር በመጠጋት ለማካካስ የሚሞክሩ እንዳሉ ቢታወቅም (ከአፈወርቅ ገ/ኢየሱስ ጀምሮ ብንመለከት) ኅሊናቸውን በጨርቅ ጠቅጥቀው ከክፉ ጋር በግብረ በላነት የሚቆሙ ሰዎች የችሎታ ችግር የለባቸውም። ብዙዎቹም በያዙት ሙያ ላቅ ያለ ዕውቀት ያካበቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ናቸውም። እነርሱ ካለፉ በኋላ ይህንን ግብረ በላነታቸውን ለመኮነን የሚሹ ሁሉ ሰዎቹ የነበራቸውን ችሎታ ሲመለከቱ ወደ ኋላ ለማለት ይዳዳቸዋል።
+ + +
 
በየዘመኑ ከሚነሡ ክፉ አገዛዞች ጋር እንዲህ ዓይነት ኅሊና ቢስ ግብረ በላዎች አብረው መነሣታቸውን ለመገንዘብ የነአፈወርቅን ታሪክ ዞር ብሎ መመልከቱ ይጠቅማል። እነዚህ ጎበዝ ግብረ በላዎች የሚታወሱት አንድም ችሎታቸውን ተጠቅመው ክፉዎችን የጠቀሙበት መጠን ከፍ ስለሚል ነው። አፈወርቅን በምናስታውስበት መጠን ለአልፎ ሒያጅ ሹምባሽ ግጥም ያወረደውን አዝማሪ ሁሉ አናስታውሰውም። የአፈወርቅ ተግባር ከአዝማሪው በእጅጉ እንደሚልቅ ስለምንረዳ። 
+ + +
 
ላቅ ያለ ሙያ ባለቤት መሆን ሰውየው ለሚያደርገው ቀጣይ ስሕተት ማካካሻ ሊሆን አይችልም። አይገባምም። እንዲያውም ቅዱስ መጽሐፍ (“ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።” (ሉቃስ ወንጌል 12፤48) እንደሚለው ለአዋቂው ጥፋት ፍርዱም የከበደ ይሆናል።  
 
ግብረ በላነት የገቡ ሊቃውንት ዋነኛ ተግባራቸው መተርጉማን እና ዕውቅና ሰጪዎች መሆን ነው። መተርጉማን ወይም ተርጓሚዎች ማለት ክፉዎቹ የሚፈጽሙትን ተግባር፣ ዓላማቸውን እና ግባቸውን ለሕዝቡ በሚረዳ መልክ ቀምመው የሚያቀርቡትና የሕዝቡን ልብ የሚያደነዝዙት እንዲህ ዓይነት ሰዎች ናቸው። የአፈወርቅ አርበኞችን የሚያዋርድ ብዕር ከአንድ የጣሊያን ወታደር ጥይት ያነሠ ኃይል አለው? ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ የሚጽፉት ጽሑፍ እና የሚያስተላልፉት ፕሮፓጋንዳ ከአንድ የጣሊያን ጄኔራል ተግባር በምን ይተናነሣል?
+ + +
 
እንዳልኩት ዕውቅና ለመስጠት ትልቅ ችሎታ ያስፈልጋል። የጣሊያኖች ኢትዮጵያን መውረርን ሕዝቡን ከማሰልጠን እና አገሪቱን ከመጥቀም አንጻር እየተመለከቱ ይናገሩ የነበሩ አንደበቶች ትልቅ ለውጥ የማምጣት ኃይል ነበራቸው። (ምነው ጣሊያን አንድ-ሃያ መት በገዛን ኖሮ የሚሉ ዛሬም አሉ)።
 
ከአገራችን ወጣ ብለን ብንመለከት እንኳን ናዚዎችም ሆኑ የሩሲያ ኮሚኒስቶች ታዋቂ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የሶሲዮሎጂ፣ የኪነ ጥበብ፣ የሃይማኖት ሊቃውንትን ይጠቀሙ የነበረው አስተሳሰባቸው ሳይንሳዊና ሥነ ልቡናዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ለማድረግ ነበር።
  
በአገራችን የፈነዱት ሁለቱ የደርግና የኢሕአዴግ አብዮቶች በተመሳሳይ መልኩ ዕውቅና የሚሰጧቸውን የተለያዩ ሊቃውንት ለመጠቀም ሲሞክሩ እናያለን፣ ዓይተናል። “ኪነት ለአብዮቱ” ከሚለው የወታደራዊው መንግሥት ዘመን አሠራር ጀምሮ በዚህም ዘመን “ልማታዊ” መምህራን፣ የጋዜጠኝነት፣ የኪነ ጥበብ፣ የትምህርት ተቋማት ተመስርተዋል፤  አንድ ለአምስት የሚሰኙ ቡድኖች መዋቅራቸውን ዘርግተዋል።
 
ሁሉም መዋቅሮች በሕዝቡ መካከል ለገዢዎች ዕውቅና ለማስገኘት የሚጥሩ፣ የመንግሥታቱን ተግባራት፣ ዓላማዎችና ግቦች በተርታው ሕዝብ ቋንቋ ለማቅረብ የሚሞክሩ እንዲሁም የሕዝቡን ጥቂት በጥቂት እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ናቸው። ከታላላቅ መዋቅሮች ባልተናነሰ ደግሞ ግለሰቦች ሰፊ ዕውቅና ሰጪዎች የሚሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው። እነ አፈወርቅ ብቻቸውን እንደ ድርጅት እንዳገለገሉት ሁሉ ዛሬም በሰዉ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖራቸው ይችላል የሚባሉ ሰዎች ገዢዎችን በመርዳት በኩል ብዙ አገልግሎት ይሰጣሉ።
+ + +
 
ከጥቂት ወራት በፊት ደብረ ዘይት የሚገኘውን የአየር ኃይል የተለያዩ ተቋማት ለመጎብኘት የሄዱ የኪነ ጥበብ ሰዎችን ጉብኝት ኢቲቪ ሲያቀርብ ተመልክቼ ነበር። ግለሰቦቹ ሕዝቡ ሁሉ የሚያውቃቸው የኪነ ጥበብ ሰዎች ቢሆኑም ስለ አየር ኃይል ሳይንስ ሊጠየቁ የሚበቁ ሊቃውንት እንዳልሆኑ እገምታለኹ። ነገር ግን በጉብኝታቸው የተሰማቸውን ደስታ እየገለጹ፣ ምኑን ከምን አነጻጽረውት እንደሆነ ባላውቅም አየር ኃይሉ የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ ሲያበስሩ ተደምጠዋል። ከጉብኝታቸው ሲመለሱም በሙያቸው አየር ኃይሉን እንደሚደግፉ ቃል ሲገቡ ነበር። በሙያቸው መደገፍ የተባለው ሌላ ምንም ሳይሆን እነ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ የተጫወቱትን ሚና ለመጫወት መሞከር ይመስለኛል። ለገዢዎች ተግባራትና ዓላማዎች “ዕውቅና” መስጠት። ይህ የገዢዎቻችን ዓላማና ተግባር አዲስ ስም የወጣለት ሲሆን እርሱም “የመለስ ራዕይ” ይባላል።
+ + +
 
በከበደ ሚካኤል መነሻነት እዚህ ሁሉ ውስጥ ገባን። (አሁንም ገና የከበደ ሚካኤልን ትክክለኛ የን ጊዜ አቋም መልስ አላገኘኹለትም።) ሊቃውንት ከገዢዎች ጋር መስመሩን ያለፈ ወዳጅነት ውስጥ ሲገቡ እንዲህ ዓይነት ምስቅልቅል መፈጠሩ አይቀሬ ነው። አዋቂዎች ነጻ ኅሊናቸውን ከሚያቆሽሹ ተግባራት በተለይም ከአድርባይነት እና ከግብረ በላነት ካልራቁና የሞራል የበላይነትን ካላሳዩ ችሎታቸውና ጥበባቸው የክፉ አገልጋይ ይሆናል። እነርሱም አቡነ ጴጥሮሶች ሳይሆን አፈወርቆች ይሆናሉ። በዚህ ዘመንማ ስንቱን አፈወርቅ አየነው፣ ታዘብነው።     
   
ይቆየን - ያቆየን
 
ማስታወሻ፦ ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ የወጣ ነው።
 

9 comments:

Anonymous said...

I love this Ababaye. U asked the right question. And I believe everybody should ask himself the same question. all of us could be
"አፈወርቆች" in some way I guess. U make me think about myself. Thank you Ababaye. May God bless u.

Anonymous said...

Great View Ababaye. I Actually did saved the pic from your page. I love the idea of "አፈወርቆች" which I believe is inside all of us.

Anonymous said...

d.n eprem tkeklega ena betkekel eytsera yale neger new here sentu yebetkrstyan sew new be gebre belanet betkrstyanune ena tarkun yeshete here sentu ye haymanot abate new gedamatu sefersu betekrstiyanu sekatelu eyaye zem yalew?yehe geze yalfal lmene lemele teyake hulume alafi newna here ebakachune bemiyalfe neger yemayalfewne semayawe kebrachune atlewtu almawewes byaderge bezume lygerm yechlal menfesawiyanu siyadergute gene beamaniywiyanume zend hone befetari zend yasteykal yehe endete yersal 20 wey 30 amete lemymola edmie here lbe engza abatoch ebakachune?

Anonymous said...

Very weak analogy! Negadras Afework is blamed for serving the fascist invaders, i.e. foriegn power that tried to colonize Ethiopia; but currently, our atists or any body is both entitled and obligated to serve his country whether the one group in power is from this or that ethnic group (for that matter EPRDF is an Ethiopian regime, not an invading force!). Be it a supporter or opponent of EPRDF, every Ethiopian has an obligation to serve his country. Trying to portray Ethiopians of our generation, who serve their country, as "lolie" or banda" is an idiotic remark. By the way,I would like to thank Ephrem Eshete for revealing that Mahbere Kidusan is a political grouping with the aim of overthrowing the Ethiopian government, at least by smearing campaigns.

Anonymous said...

ጽሁፉ በጣም ደስ ይላል። ጥሩ ጥሩ ነጥቦች ተነስተውበታል። ነገር ግን የጽሁፉን ርዕስ አልወደድኩትም። አፈወርቅ እንዲሁ ሳይሆን ከመልካም ግብራቸው አንጻር እንደመጠሪያ ስምነት የተሰጣቸው ሰዎች ነበሩና ፤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ይጠቅሷል።

Adebabay A said...

ትክክል ብለዋል አንባቢዬ። ዮሐንስ አፈወርቅን የመሳሰሉ ሰዎች መኖራቸውን አውቃለኹ። ነገር ግን ሌሎች "አፈወርቆች" መነሣታቸው የቀድሞዎቹንም ሆነ ከዚህ በኋላ የሚመጡትን ደጋግ አፈወርቆች የሚያሳጣ/የሚያዋርድ አይደለም። ጌታን የካደውን ይሁዳን ሁልጊዜም እንወቅሰዋል። "ወልዱ ... ይደምሰስ" እንላለን። ነገር ግን ሌላው ጻድቁ ሐዋርያ ይሁዳ መኖሩን መቼም አይረሳም። (የይሁዳ መልእክትን ማንበብ ነው። ስለዚህ ርዕሱ አላስደሰተኝም ማለቱ ብዙ የሚያሳምን አይመስለኝም።

Anonymous said...

I am really impressed with the issue you raised, Dn. Ephrem. Thank you very much. May God bless you. The topic is about those individuals who stand against their country/people in favor of invaders/insider-tyrants as did Afework G/yesus and other prominent personalities. So, it does not collide with the respected usage of "Afework" in our church.

Anonymous said...

There are so many 'Banda'Journalists,Merchants,students,teachers Farmers etc. What they lack is not knowledge but commitment to love Ethiopia.They want to be in the side of TEMPORARILY WINNERs.They don`t have history.They love their stomach.AFEWORKS are kawards...

Anonymous said...

ግሩም እይታ ነው ኤፍሬም። ከዚህ በላይ አንድ አስተያየት ሰጪ እርሳቸው የሚደግፉትን ሥርዓት አስተሳሰብ የተቃወመን ሁሉ “የሀገር ጠላት” የሚደግፈውን ደግሞ “የሀገር ወዳጅና ግዴታውን እየተወጣ ያለ”ለማለት የሞከሩ ይመስላል። የጽሁፉ አላማ የፖለቲካ ሥርዓትን በመደገፍ የሚሠራውን ”የምሁራን ስህተት“ ለመኮነን አይመስለኝም። ከሆነም ስህተት ነው። ርእዮተ ዓላም በየጊዜው የሚቀያየር እና በስሜት የሚደገፍ ስለሆነ ሰዎች በአንድ ወቅት የተሻለ ነው ብለው ለሚያምኑት መሥመር ምሁራዊ/ሙያዊ ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ።ይገባልም። የመማር ትርጉም ሆድን መሙላት ሳይሆን በኃሳብ ልዕልና ሀገርን መጥቀምና ሌላውንም መምራት ጭምር ነውና። ነገር ግን ምሁራን የድጋፋቸው ውጤት ሀገርን እና ዜጎችን እየጎዳ መሆኑን ሲረዱ ግን ለደገፉት አካል በሚገባ አስረድተው የመለየት (ባይችሉ/ቢፈሩ ደግሞ ድጋፋቸውን የመንፈግ) ግደታ አለባቸው። ከዚህ አንጻር ሲታይ በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ያሉ “ምሁራን” ለሥርዓቱ እየሰጡት ያለውን ”ስልታዊ“ እና ግልጽ ድጋፍ መመዘን ይቻላል። “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ለልማታችን ይበጃል ብለው ከልባቸው የሚያምኑ “ምሁራን“ ባይጠፉም በዚህ ርእዮተ ዓለም ምክንያት በንጹኃን ዚጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በግልጽ እየተቃወሙ (እየተሠራ ያለው ግፍ እንደ ዘመነ ደርግ በስውር ስላልሆነ)፣ ከግል ተጠቃሚነት ርቀው፣ ለሀገር የሚበጀውን ሃሳብ የሚደግፋት ስንቶች ናቸው?ጸሀፊውም ኅሊናቸው እያወቀ የሚሠራውን ግፍ የሚሸፋፍኑትን እንጂ ለሀገር ይበጃል ብለው “ስህተት እየሠሩ” ያሉትን “ባንዳ” ያለ አይመስለኝም። እውነቱን ለመናገር የእነዚህን “ምሁራን” ሆዳምነት የወያኔ ባለሥልጣናት እንኳ እንዴት እየታዘቧቸው እንደሆነ ሳሰበው ነው ድህነት ምን ያህል አዋራጅ እንደሆነ የምረዳው። ይህ ሁሉ የሚሠራው ለሦስት ምክንያት ብቻ ነውና ነውና 1ኛ/ ለገንዘብ 2ኛ/ለገነዘብ 3ኛ/ ለገንዘብ። ለሁሉም ሕሊናችን የማያምነበትን ከመሥራት እና በእኛ ላይ ሊፈጸም የማንሻውን ለላ ላይ ሲፈጸም ዝም ከሚያሰኝ ”ምሁርነት“ ይሰውረን።