Wednesday, May 15, 2013

የማትረሣዋ የ1983 ዓ.ም ግንቦት ልደታ


ቅድመ ታሪክ
ከዕለታት በአንዱ ዓመት (ለነገሩ በ1983 ዓ.ም ነው)፣ ኮሌጅ ከመበጠሳችን በፊት፣ እንዳሁኑ አዲስ መንግሥት ሳይመጣ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የተባለ ሁሉ ወታደር ካልሆነ ተባለ። ከዚያም ክተት ታወጀና ብላቴ ከሚባል የጦር መንደር ገባን። ቱታ ከሸራ ጫማ፣ ትንሽ ቁምጣ ከነ ብርድ ልብስና አንሶላ ተሰጠን። ሌሊት 11 ሰዓት ሲሆን ስፖርት ተባለና ከመኝታችን በግድ እየረቀሰቀስን መሮጥ ያዝን።


ከዚያ መሣሪያ መግጠምና መፍታት፣ ኢላማ ላይ አነጣጥሮ መተኮስ ተማሩ ተባለ። አዲስ መንግሥት ለመሆን አዲስ አበባ አፍንጫ ሥር የደረሱት ጸጉረ ልውጦች ደግሞ “እንግሊዝኛ ተናጋሪ ወታደሮች መጡ” እያለ ተሳለቀብን። እኛ ደግሞ ገና ኮሌጅ በመግባታችን ከወታደሩ የተለየን ልሒቃን መሆናችንን ለማሳየት “እኛ ምሁራን” እያልን በየስብሰባው መናገር ጀመርን። አሰልጣኝ ወታደሮቹንም በጣም ናቅናቸው። (ይኼ ሁሉ የራሱ ታሪክ ስላለው እሱ ውስጥ አልገባም።) የዛሬው ወግ በዚያ የወታደር ማሰልጠኛ በረሃ ውስጥ ስላከበርነው የግንቦት ልደታ በዓል ብቻ የምትተርክ ትሁን።

ልደታ ለማርያም
የግንቦት ልደታ በዓል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደት በዓል ብቻ ሳይሆን ባህላዊ አከባበሩም ብዙ ትውስታ ያለው ከመሆኑ አንጻር ቤተ ክርስቲያን የማያዘወትሩ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ሊሳተፉበት የሚችሉት ነው። ከቤት ውጪ መሰብሰቡ፣ ንፍሮ መቀቀሉ፣ የሚታረድ በግም ሆነ ፍየል ካለ ያንን እየጠባበሱ መቋደሱ (የአበሻ ባርቢኪው)፣ ጎረቤታማቾች ተሰብስበው ቡና እያፈሉ ወይም አባ ወራዎቹ ተኮስ የሚያደርግ አልኮል እየተጎነጩ መጫወቱ፤ ሕጻናቱም “ጅብ መጣባችሁ፣ ጭራቅ መጣባችሁ” በሚባሉበት ጨለማ አጠገባቸው ባሉት ቤተሰቦቻቸው ተመክተው በጨለማ መጫወቱ የራሱ የሚጥም የልጅነት ትዝታ አለው።

ብላቴ በነበርንበት ወቅት በነዚያ ወራት ያገኘናቸውን በዓላት በሙሉ እያሟጠጥን አብረን ለማክበር ሞክረናል። እንደ ወራት ቅደም ተከተል ሆኖ በዚያን ጊዜ የሚከበሩትን የሆሳዕናን፣ የትንሣዔንና ግንቦት ልደታን በሕብረት አክብረናል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ባለው ሥፍራ ግንቦት ልደታ ከትንሣዔ የበለጠም ባይሆን በብላቴ ባገኘው አከባበር ግን ግንቦት ልደታ ዕድለኛ ነበረ። ምክንያቱ እንዲህ ነው።

ብላቴ የገባነው ለትንሣዔ አንድ ሳምንት ሲቀረው ነበር። ገና ዙሪያ ገባውን፣ መውጫ መግቢያን ሳናውቀው ሕማማቱ አለቀ። ከዚያ በኋላ ግን ተዋውቀን፣ አገሩን ለምደን፣ የምንጸልይበት ሥፍራ አግኝተን፣ ከተደላደልን በኋላ እንኳን በዓል ተገኝቶ ቀርቶ እያንዳንዱንም ቀን በጸሎት፣ በመዝሙርና በትምህርት ማክበር ያዝን። ከዚያ ግንቦት ልደታ መጣ።

ልደታን የማክበሩ ሐሳብ ከማን እንደመጣ ትዝ አይለኝም። ምናልባት ታደሰ የሚባል ሰው ፊት መናገር የማይወድ ጎበዝ ልጅ ያመጣው ይመስለኛል። መቸም እንዲህ አዲስ ነገር በመፍጠር የተካነ ነበር። መድረክ ላይ ውጣ አትበሉት እንጂ ከጀርባ በሚሠሩ ሥራዎች ጥሩ መሐንዲስ ነው። ለማክበር ወስነን እንቅስቃሴ ከጀመርንም በኋላ እንዳየኹት በዓሉ ግሩም ሆኖ እንዲከበር ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረገው ታደሰ ነበር።

በዓሉ እንዲከበር ከተወሰነ በኋላ ሁሉም ሰው ኃላፊነት ተሰጠው። በጊዜው ያስፈልጋሉ ያልናቸው መዝሙር (ያሬዳዊ ወረብ) ማዘጋጀት፣ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች እና ልንጋብዛቸው ላሰብናቸው አሰልጣኞቻችን የሚሆን ንፍሮ መቀቀል፣ ያንን ሁሉ ወፈ ሰማይ ሕዝብ ሊይዝ የሚችል ቦታ ማዘጋጀት፣ ለዚያ ሁሉ ዕድምተኛ የሚሆነውን ንፍሮ መቀቀያ ዕንጨት መልቀም፣ ለንፍሮው የሚሆን እህል ከገበያ መግዛት፣ ለሚገዙ ነገሮች ከተማሪው ገንዘብ መሰብሰብ ወዘተ።

መዝሙር እና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚያስተባብሩት እነ ዲያቆን አልአዛር (አሁን ቀሲስ) እና ዲ/ን ንዋይ (አሁን ዶ/ር) ሲሆኑ መምህራቸው ደግሞ ቀኝጌታ ይቻለዋል (አሁን መሪጌታ) ነበር። በየዕለቱ ማታ፣ ከጸሎት እና ትምህርት በኋላ መዘምራኑ ወረቡን ጥሩ አድርገው ሲለማመዱት ያመሹ ነበር። መቋሚያ እና ጸናጽል በአካባቢው ከሚገኙ ነገሮች ተሠርቷል። መሥራት ያልተቻለው ከበሮ ብቻ ነበር። እርሱንም ቢሆን ቢያንስ ቀደም ብለን እንዳከበርነው እንደ ትንሣዔው ዕለት “ጀሪካን” እየመታንም ቢሆን እንጠቀማለን የሚል ሐሳብ ነበረን። (በዕለቱ ከበሮ በአካባቢው ከሚገኘው ከቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተውሰናል)

የመዝሙሩ በዚህ ከተያዘ በኋላ ንፍሮ ለመቀቀል (እንደ ባህሉ) እህሉን መግዣ ተማሪው ካለችው ላይ አዋጣ። ከዚያም ከማሰልጠኛው ሰባት ኪሎሜትር በላይ ርቆ ከሚገኘው ከጨርቾ መንደር ለመግዛት ሦስት ተማሪዎች ተላክን። ስንሄድ በእግራችን ያለ ምንም ችግር ሰተት ብለን መንገድ መንገዱን ይዘን ደረስን። ችግሩ ስንመለስ ነው። እህሉን ተሸክመን፣ ሰባቱን ኪሎ ሜትር እንዴት አድርገን ልንወጣው ነው። በዚያ ላይ ሙቀቱ። ነገር ግን ከመሔድ አልታቀብንም።

ለንፍሮ የሚሆነውን እህል እንዲያው በአቦ-ሰጠኝ ከሽንብራውም፣ ከስንዴም ግማሽ ግማሽ አድርገን ገዛን። ከዚያም በትከሻችንም በጀርባችንም እያፈራረቅን ተሸክመን ጉዞ እንደጀመርን ወደ ካምፑ የሚሔድ መኪና ስላገኘን “ሊፍት” ሰጥተው አንከብክበው አደረሱን። ትልቅ ሸክም ተቃለለ። እህሉም ወደ መቀቀያ ቦታው በሰላም ደረሰ። የሚቀጥለው ንፍሮ መቀቀያ እንጨት ለቀማ ይሆናል።

በብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ባሕል መሠረት የማገዶ እንጨት የሚለቅመው ራሱ ሰልጣኝ ወታደሩ ነው። በሌላው ጊዜ በየሳምንቱ አርብ እንጨት እንለቅማለን - ለምግባችን። ታዲያ በግድ ነው እንጂ በመልቀማችን አንድም ቀን ደስ ብሎን አያውቅም። ግንቦት ልደታ መከበር ካለባት እና ንፍሮም መቀቀል ካለብን ተማሪውን እንጨት እንዲለቅም ልንጠየቀው ነው ማለት ነው። የማይወደውን ነገር። አማራጭ የለምና ጠየቅነው። ማንም ተማሪ አላንገራገረም። . . .

እንጨት በምንለቅምበት በአንዱ ቀን፣ ከሥልጠና በኋላ፣ እንጨታችንን ስንለቅም ቆይተን ተሸክመን ወደ ካምፓችን ጉዞ ስንጀምር አህያ የማይችለው ዝናብ መጣል ጀመረ። እንዳጋጣሚ ሆኖ ሥልጠናችንን ፈጽመን የምንመለሰው በሴቶች ብርጌድ፣ በሦስተኛ ብርጌድ፣ በኩል ነበር። ጭራሯችንን ተሸክመን ስንንከላወስ ዝናቡ የሕጻን ልጅ ጭንቅላት የሚያክለውን ነጠብጣብ ያወርደው ጀመር። እንጨት ውኃ ሲነካው እንዴት ወገብ እንደሚያጎብጥ ልጅ ሆኜም አውቀዋለኹ። በልጅነቴ እንጨት የምንለቅም ቀን ዝናቡ ሳይመጣ ወደቤታችን ለመመለስ የምናደርገው ፍጥነት ትዝ ይለኛል። . . .

የብላቴ ዝናብ መቸም የሚገርም ዕብድ ዝናብ ነው። የበረሃ ዝናብ ሁሉ እንደዚያ ይሁን አይሁን አላውቅም። ዝናቡ “ስብጥር ተኩስ” የሚለውን የአሰልጣኞቻችን ቃል ያስታውሰኛል። ስብጥር ተኩስ ማለት እልም-ድርግም ባለ ጨለማ ውስጥ፣ ጠላት ከየት አቅጣጭ እንደሚመጣ በማይታወቅበት ጊዜ፣ ምሽግ ይዞ ወደ ግራም ወደ ቀኝም እያሉ የሚተኮስ ውሽንፍር ዓይነት ተኩስ ማለት ነው። ዝናቡ እንደዚያ ነው። አንዴ ከግራ፣ አንዴ ከቀኝ ይመጣል። ፊት ይገርፋል።

የብላቴው ዝናብ ሲመጣ በመጀመሪያ ንፋሱ አሸዋውን አንስቶ ይከልስብሃል። ከዚያ ዝናቡ መዝነብ ሲጀምር ከአቧራው ጋር እየተቀላቀለ የጭቃ ሐውልት ያደርግሃል። ያጨናብስሃል። እንዲያ ባለ ዝናብ ላይ ነው ተማሪው እንጨት እንዲለቅም ያደረግነው። በዕብድ ዝናብ ላይ የልደታን እንጨት ጨመርንበት ማለት ነው

ሦስተኛ ብርጌድ ያሉት ሴቶች እንጨቱ እንደ ወትሮው ለማብሰያ የለቀምነው መስሏቸው በዚያ ቀጫጭን ድምጻቸው “ጣሉት ጣሉት” ሲሉ ይሰማኛል። የጣለ ግን አልነበረም። የማርያምን እንጨት ማን ይጥላል። እየተጨናበስንም፣ እየተንገዳገድንም ከቦታችን አድርሰን ከመርነው። ተማሪው አንዲትም እንጨት አለመጣሉን ያወቅኹት ብዛቱን ሳየው ነው። በሌላ ጊዜ፣ በቀን። . . .

ሁላችንም ወንዶች ስለሆንን ንፍሮ ሲቀቀል አይተን ይሆናል እንጂ ቀቅለን አናውቅም። ብንቀቅልስ ለዚያ ሁሉ ሺህ ሰው የሚሆን ንፍሮ መቀቀል የራሱ ጥበብ ያስፈልገዋል። ንፍሮውን ለመቀቀል የተመደቡት ልጆች ብዙ ችግር ውስጥ ገብተው ነበር። ትልልቅ ጎላ ብረት ድስት አይቸግረንም። ጨዉንም ከሜንሲ ቤት (የምግብ መመገቢያው) አግኝተናል። እሳቱን መጣድም አልተቸገርንም። የረሳነው ነገር የድስቱን ክዳን ገጥመን መቀቀል እንደነበረብን ነው። እኛ በክፍቱ አድርገን ስለቀቀልነው ነው መሰል ንፍሮው ከሰል የመሰለ ጥቁር ሆነ። ለምን እንደጠቆረ የተረዳነው በኋላ “አልከደናችሁትም አይደል?” ስንባል ነው። ጣዕሙ ግን … “ጣት ያስቆረጥማል”። ከምር።

ንፍሮው በዚህ ከተጠናቀቀ ዘንዳ በዕለቱ ጉባዔው ለወታደር ማደሪያነት በመሠራት ላይ በነበረ እጅግ ትልቅ የብረት ቤት ውስጥ ተዘጋጀ። እሑድ ከሰዓት በፊት። ቀኑ ግንቦት 4/1983 ዓ.ም። በዚያን ዕለት “ለእንግሊዝኛ ተናጋሪው ወታደር” ድራማ የሚያሳዩ ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ስለመጡና ሜዳ ላይ የሚታየው ድራማ ትንሽ ጨለም ባለ ብርሃን እንዲሆን ስለተፈለገ    መርሐ ግብሩ ከሰዓት በስቲያ እንዲሆን በመደረጉ ድራማውንና የተማሪውንም ሁኔታ ለመቅረጽ የመጡ የቲቪ እና የሬዲዮ ጋዜጠኞች ወደ ግንቦት ልደታው ዝግጅት እንዲጋበዙ ሆነ። የቴሌቪዥን ጋዜጠኞቹን ባላስታውስም የሬዲዮው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ያቀረበው ሪፖርት፣ የተሳሳታት የግዕዝ አነባበቡ፣ የድምጹ ቅላጼ ሁሉ አይዘነጋኝም። በርግጥ ግሩም በዓል ነበር። ግንቦት ልደታ በየመንደራችን ትከበር ካልሆነ እንዲህ በሺህ የሚቆጠር ሰው ተሰብስቦ ግን ሲያከብራት የመጀመሪያ ሳይሆን አይቀርም። በጠቆረ ንፍሮ፣ በተበጠበጠ የመርቲና የውሐ ቅልቅል (ብርዝ?)፣ እንዲሁም በወታደር አጀብ።

ተማሪው ያጠናው ያሬዳዊ ወረብ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ሀበ እግዚአብሔር፣ እንዘ ትብል ‘አምላኪየ ነጽረኒ ወአድኅነኒ እምኃይለ ጸላዒ ወጸር’… ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፣ አምላኬ ከሚጠሉኝ ከጠላቶቼ አድነኝ’ እያለች” እንደማለት ነው። ነጋሽ መሐመድ ይህንን በመቅረጸ ድምፁ አስቀርቶታል፣ በመረዋ ድምጹ አንብቦታል። የማይረሣ አድርጎታል። በየአገሩ ያለው የተማሪው ቤተሰብ ይህንን ሲሰማ ልቡ እንዴት እንደተሸበረ ሁሉ ነገር አልቆ፣ ጸጉረ ልውጦቹም የምኒልክን ቤተ መንግሥት ይዘው (አጥሩ ላይ ልብሳቸውን አጥበው ካሰጡበት በኋላ)፣ ወደየቤተሰቦቻችችን ስንመለስ ዘመዶቻችንና ዘመቻ ያልሔዱት ጓደኞቻችን ነግረውናል። ያቺን የግንቦት ልደታ የማትረሣ ያልኳት ለዚህ ነው። ንፍሮ ከዚያ ወዲህ ቀቅዬ አላውቅም፣ ብቀቅል ግን ብረት ድስቱን መክደን አልረሳም። ንፍሮው እንዳይጠቁር።

ይቆየን፣ ያቆየን

(ይህ ወግ “የብላቴ ትዝታዎች” በሚል ካዘጋጀኹት ያልታተመ መጽሐፍ ውስጥ የተቀነጨበ ነው። ስማቸው የተጠቀሰውን ወዳጆቼን ስላላስፈቀድኳቸው የአባታቸውን ስም ሆን ብዬ ዘልዬዋለኹ - ለጊዜው።)

14 comments:

Anonymous said...

U better publish it very soon ababaye. U know we love to hear it.

Anonymous said...

plese dn epherame publish is quickely........lemegezate maneme ayekedemegneme....pls...pls...pls

Anonymous said...

Thank u,I`m eager to read your book.

Anonymous said...

I Can't wait for the book! Thank you bro, keep it up.
May God bless you

Demissie Brile said...

Arif twsta new. Yehen zena yesemahut yebetekrstiyanachin astedadari Ferensay Eyesus ke'qdase behola awdemhretu lay hunew "Ayachu semachu aydel ye'university temare lejochachen Egziabhiren seyamesegnu" silu neber. TV keyet meto enyachu!!!

ephrem amente said...

በጣም ደስ የሚል ትውስታ ነው ንፍሮው ግን አሁንም አልተከደነም
ማለት ንፍሮው ሲከደን መጽሃፉ በእጃችን ገባ ማለት ነው
የብላቴን ሙቀት ግን እንዳትረሳው
በመቀጠል በውታደር ቤት ያሬዳዊ ዜማ እንዴት ደስ ያሰኛል
“ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ሀበ እግዚአብሔር፣ እንዘ ትብል ‘አምላኪየ ነጽረኒ ወአድኅነኒ እምኃይለ ጸላዒ ወጸር’…

ephrem amente said...

በጣም ደስ የሚል ትውስታ ነው ንፍሮው ግን አሁንም አልተከደነም
ማለት ንፍሮው ሲከደን መጽሃፉ በእጃችን ገባ ማለት ነው
የብላቴን ሙቀት ግን እንዳትረሳው
በመቀጠል በውታደር ቤት ያሬዳዊ ዜማ እንዴት ደስ ያሰኛል
“ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ሀበ እግዚአብሔር፣ እንዘ ትብል ‘አምላኪየ ነጽረኒ ወአድኅነኒ እምኃይለ ጸላዒ ወጸር’…

Anonymous said...

Ye Belate Neger Betam Des Yelal....

mulugeta said...

dn.eprem betame teru yemayresa tewsta new lehulachenem mekenyatume ye mahebere kedusan tarekeme selhone tolo yelekena methafun enanbebew berta egzeabher yagzehe.mulugeta

Anonymous said...

I was there,too but I read it as if I were not there-you are describing it in depth and attractive way! I am so eager to read your book!
Ke 5gna bergide 3gna shaleka 3gna shamble 1gna yemeto:)!!

Anonymous said...

ሰላም ዲያቆን ኤፍሬም;
ታሪኩን በመጽሐፍ ለመፃፍ ማሰብህ መልካም ነገር ነው። ይህ ራሱ ከኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አንዱ ምዕራፍ ነው። አሁንም “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ሀበ እግዚአብሔር፣ እንዘ ትብል ‘አምላኪየ ነጽረኒ ወአድኅነኒ እምኃይለ ጸላዒ ወጸር’" እያልኩ እዘምራለው።

Anonymous said...

ዳያቆን ኤፍሪም እግዚአብሄር በበረከት ይጎብኝህ ድንቅ እይታ ነዉ።ለእኛ ቤት ግንቦት ልደታ ልዩ ቀን ናት በተለይ የብላቴዋ ምክነያቱም ታላቅ ወንዲሜን ወደቤተክርስቲያን የጠራች ቀን ሰለሆነች ያን ቀን አስታዉሳለሁ ካአባቴ እግር ስረ ቁች ብይ ነበር ያዳመጥኩት የነጋሽ መሀመድ ዘገባ ሰለብላቴ ግንቦት ልደታ አከባበር

Anonymous said...

ebakihin cherisew

Anonymous said...

“ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ሀበ እግዚአብሔር፣ እንዘ ትብል ‘አምላኪየ ነጽረኒ ወአድኅነኒ እምኃይለ ጸላዒ ወጸር’… ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፣ አምላኬ ከሚጠሉኝ ከጠላቶቼ አድነኝ’ እያለች” ይህም ደግሞ ትንቢት መሆኑ ነው፡፡ በትንሹም ቢሆን ከደርግ የተሻለ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ እንስያለ አንጻራዊ እጂ ማንሳት አደረገች ማለት ነው፡፡ ይገርማል፡፡
ጸሐፌ ሆይ በረታ!