Saturday, September 14, 2013

አንድ ሐሙስ የቀራቸው . . .

(PDF):- ብቻውን ከራሱ ጋር እየተነጋገረ፣ እየተሳሳቀ፣ እየተበሳጨም ይሁን እየተቆጣ የሚሄድ ሰው ምን ይባላል? ጨርቁን ጥሎ አልለየለትም፤ እግር-ተወርች በብረት በገመድ አልተታታም። ጽድት ያለ ይለብሳል። ምናልባትም ክሽን ያለ ገቢ ይኖረዋል። ቤተሰብ ያለው፣ ብዙ ሰው የሚያስተዳድር ብረት መዝጊያ የሚባልም ሊሆን ይችላል። ጭራሹን ካላበደ እና ሩብ ጉዳይ ከሆነ በአጭሩ ‘አንድ ሐሙስ የቀረው’ የሚለው ያስኬዳል።


እውነተኛ ታሪክ እነሆ። ቀልድ ይመስላል አሁን ሲሰሙት። ሰውየው ከአገር ቤት ከወጣ ቆይቷል። ኑሮው አውሮፓ ነው። የአውሮፓ ስደት ደግሞ አስቸጋሪ ነው።  በቋንቋ እንኳን የሚግባባው ብዙ ሰው ከሌለበት ከአንዱ ትንሽ የገጠር መንደር ያስቀምጡታል። ጠዋት ማታ ያው ነው። መሥራት የለም። መማር የለም። ብቻ መብላት፣ መጠጣት፣ መውጣት፣ መግባት፣ መተኛት፣ መነሣት። ሲውል ሲያድር፣ ሲከራርም፤ ጭንቅላቱን ነካ ያደርገዋል። ከዛ የመኖሪያ ፈቃዱን ይሰጡታል። ከገጠሯ መንደር ወጥቶ ወደ ትልቅ ከተማ ይገባል። ሥራም መሥራት ይጀምራል። እነዚህ ሰዎች ሰው ጭንቅላቱን ነካ ካላደረገው ፈቃድ መስጠት አይወዱም ልበል? እንደዚያ ናቸው።

ሰውየው ጭንቅላቱ መነካቱ እየባሰ፣ እየገፋ ሄዶ ምንም ሥራ መሥራት ከማይችልበት ደረጃ ይደርሳል። ሰው እንዲህ ሲሆን ምን ይደረጋል? ወዳጅ ዘመድ ወዳለበት ይላካል። ውጪ አገር ያለን ሰዎች ያለምንም ማንገራገር ከምንረዳዳባቸው ነገሮች መካከል ሰው ሲሞት አስከሬኑን ወደ አገር ቤት ለመላክ ገንዘብ ማዋጣት እና ጽኑዕ በሽታ ሲይዘው እንዲሁ ገንዘብ ማዋጣት የሚሉት ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው። በዚሁ ሥርዓታችን መሠረት ጭንቅላቱን ነካ ያደረገው ሰው በወዳጅ ዘመዶቹ ገንዘብ ተዋጥቶ ጸበል እንዲጠመቅ ወደ አገር ቤት ይላካል። ወደ ቤተሰቦቹ።

አረጋውያን ቤተሰቦቹ ለረዥም ዘመን የተለያቸው ልጃቸው በሰላም ከአገሩ ወጥቶ እንዲህ አንጎሉ ታውኮ መመመለሱ የወላጅ ልባቸውን ሰብሮት ኖሮ ገንዘብ አዋጥተው የላኩትን ጓደኞቹን “ምነው ገና ሲጀምረው ብትልኩት ኖሮ?” ሲሉ የጸጸት ሐሳብ ያቀርባሉ። ጓደኞቹም ልባቸው በሐዘን እንደተጎዳ “አዬዬ፣ ገና ሲጀምረው የሚላክ ከሆነማ ማንኛችንም አንተርፍም ነበር። ሁላችንም ወደ አገር ቤት ልንላክ ነዋ” ሲሉ ይመልሳሉ። እነሆም ዛሬ ድረስ “አንድ ሐሙስ የቀረው ሁሉ ወደ አገር ቤት ከተላከ ውጪ አገር ማን ይተርፋል አሉ” እየተባለ ይተረታል።

በተለያዩ አረብ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያት እህቶች በዜና ሽፋን ላይ ከሚገለጹባቸው ነገሮች አንዱ በተለያየ የአዕምሮ መታወክ የሚጎዱ መኖራቸው፣ በዚያም ሰበብ አንዳንዶቹ ራሳቸውን ወደማጥፋት አንዳንዶቹም ችግር ላይ የጣሏቸውን ሰዎች ለመጉዳት ወንጀል ወደ መፈጸም ይገባሉ ይባላል።

ይህንን “ጨለማ የሆነ ርዕስ” በተመለከተ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር ተቀምጠን ስንወያይ፣ አበሾች በሚዝናኑባቸው ብዙ የቡና መሸጫዎች አካባቢ ወጣ ወረድ የሚሉ፣ በዓይን የምናውቃቸውን ሰዎች ማንሣት ጀመርን። ውይይቱ ገፋ ሲል ደግሞ በተለያየ መልኩ የምናውቃቸውንና የአዕምሮ ችግር የገጠማቸውን ሰዎች እያነሣን ሰፊ ዳሰሳ ያልተደረገበት “ጥናት” አካሔድን።
አንዳንዶቹ “ሲ.አይ.ኤ/ ኤፍ.ቢ.አይ ይከታተለኛል” የሚሉ ናቸው። አንዳንዶቹ “ዩፎዎች ይታዩኛል፤ ሊያጠፉኝ የሚፈልጉኝ ሰዎች አሉ” የሚሉ ናቸው። ራሳቸውን ቤተሰቦቻቸውን የሚጠራጠሩም አሉ። መንገድ ላይ የሚያዩት ፖሊስ በሙሉ በድብቅ የሚከታተላቸው ስለሚመስላቸው ፊት ለፊት ከመጋጨት ወደ ኋላ አይሉም። እኔ የማውቀው አንድ ወጣት ልጅ “ፖሊስ ለመምታት በመሞከሩ” ዘብጥያ ወርዶ ነበር። ሆን ብሎ ሳይሆን ባለበት የአዕምሮ ችግር መሆኑ ተረጋግጦ እስኪፈታ ስድስት ወራት ታሥሯል። ኋላ ጓደኞቹ ወደ አገሩ ላኩት፤ እንደተለመደው ገንዘብ አዋጥተው።

ከአገሩ የወጣ ሰው ሁለት ጉዳት ይጎዳል። የአገሩና የቤተሰቡ ናፍቆት እንዳለ ሆኖ የውስጡን ውጣውረድ የሚያሰክንለት ‘እህ ባይ’ ሰው ማጣት ውሎ አድሮ ሕይወቱን ያቃውሰዋል። በማይም ግምገማ እንዲህ ነው የምረዳው። ባለሙያዎቹ የራሳቸው ትንታኔ ይኖራቸዋል።

ባለፉት ዓመታት “የአዲስ ነገር” (ያኔ ‘ሮዝ’ መጽሔት) ዓምደኛ የነበረው ተድባበ ጥላሁን በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን የሚፈጽሟቸውን አንዳንድ ወንጀሎች ማስነበቡን አስታውሳለኹ (ምሳሌ፡ ሮዝ መስከረም/2003 ዓ.ም)። አሁንም በየድረ ገጾቹ ላይ አልፎ አልፎ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ አደጋዎች ሲዘገቡ ይታያል። ከወንጀሎቹ ጀርባ፣ የወንጀሎቹ ፈጻሚዎች ያሉበትን የአዕምሮ ሁናቴ ማየት ይቻላል። በሆነ ወቅት ላይ አንድ ሐሙስ የቀራቸው ነበሩ። ከዚያ …

አንዳንድ የእኛ ሰዎች ብዙ አገራቸው ሰው የሚበዛበት አካባቢ ሲገኙ፣ ለአፋቸውም ይሁን እንጃ ከልባቸው፣ “አበሻ የሚበዛበት ቦታ ይደብረኛል” ይላሉ። ልብ ብላችሁ ስትከታተሏቸው ግን “አበሻ ከሚበዛበት ቦታ” አይጠፉም። አበሻ የሚበዛበት ሕንጻ ላይ ይከራያሉ፣ አበሻ የሚበዛበት “ስትራብክስ ወይም ካሪቡ” ቡና ይጠጣሉ፣ ራት ምሳቸውን ቢያንስ በሳምንት ከአበሻ ሆቴል ገብተው ይበላሉ።

ምናልባት ኢትዮጵያዊው ‘አብሮ ለመኖር የሚከብድ፣ተለይቶ ለመኖርም የሚከብድ” ሆናባቸው ይሆናል። ጭራሹኑ ምንም የአገራቸውን ቋንቋ ከማይሰሙበት ሰፈር እንዳይኖሩ - ይከብዳቸዋል። ደግሞ ከራሳቸው ሰዎች ጋር እንዳይኖሩ - ይከብዳቸዋል። አለማስተዋል ነው እንጂ ከራሳቸው ሕዝብ ጋር እየተደሰቱም ይሁን እየተጣሉ መኖሩ (ስብሐት ገ/እግዚአብሔር እንዳለው) “ሶሻል ቴራፒ”/ መድኃኒት ነው። ምን ቢያናድድህ የራስህ ሰው ይሻልሃል። ከአንድ ሐሙስ ይሰውርሃል።

በተለይ ኑሮ ማለት አፈር ድሜ ግጦ ገንዘብ መቋጠር ብቻ አድርገን ለምንመለከተው ከዚህ ከዳያስጶራው ጽኑዕ የአዕምሮ ደዌ የሚታደገን ይኸው “ሶሻል ቴራፒ” ያለው የራሳችን ሰው ገጽና መልክ፣ ሽታና ጫጫታ ነው። አበሾች ወደሚኖሩባቸው አፓርትመንቶች ሲገባ አፍንጫን የሚሰነፍጠው የበርበሬ ሽታ ወይም ቁሌት ከማናደድ ይልቅ የሚያስደስተኝ ለዚያ መሰለኝ። የሰው ያለህ ከማለት ሰው ቢበዛ አይሻልም? “ሰው መጣ፣ ነገር መጣ” ቢባልም “ሰው ጠፋ፣ ልብ ጠፋ” ከመባል ይሻላል። አንድ ሐሙስ ለቀራቸው ሁሉ ምክሬ ይቺው ናት።


ይቆየን - ያቆየን

1 comment:

Anonymous said...

bizarre