Sunday, September 22, 2013

በመስቀል ሰሞን የመስቀል ወሬ

(PDF):- ሰሞኑን የተመለከትኩት አንድ ትንሽ ቪዲዮ በሰማይ ላይ የተመሳቀሉ እና የመስቀል ምልክት የሠሩ ደመናዎችን እያሳየ “መስቀል በሰማይ ተገለጠ”፤ ተአምር ነው እያለ ያትታል። ቪዲዮው በእጅ ስልክ ወይም በግለሰብ አማተር ካሜራ የተቀረጸ ነው። ቦታው የትና መቼ እንደሆነ ባይጠቁምም ፈረንጆች የተሰበሰቡበት መስክ ነገር ነው። አውሮፕላን ሰማዩን በየደቂቃው እየሰነጠቀ በሚበርበት በዲሲና አካባቢው ለሚኖር ሰው ጭሳቸውን በመስመር ለቅቀው ያለፉ የሁለት አውሮፕላኖች መስመር (መም) ነው ብሎ መገመት ቀላሉ ግምት ይሆናል። ቪዲዮውን “ሼር” ያደረጉን ሰዎች ግን ድንቅ ነገር እንደተከሰተ እንድንቀበል በብርቱ ፈልገዋል።


“ይህ በእንዲህ እንዳለ” እንዲል ጋዜጠኛ፣ ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ከሰሞኑ “ከሰማይ የወረደ መስቀል መገኘቱን” እያነበብን ነው። አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደጻፈው ከሆነ መስቀሉ ከሰማይ የወረደው “የዛሬ 5 መት የተቋቋመው [የቅዱስ] ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነሐሴ 23 ቀን የክርስቶስ ሰምራ በለ ንግ እየተከበረ እያለ ከሌሊቱ 9 ሰዓት” አካባቢ “በከባድ የፍንዳታ ድምጽ እና ቀስተ ደመና ቀለማትን ተላበሰ ብርሃን” ነው። ምስክርነቱ የተገኘው ከቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ ከመጋቤ ሐዲስ ተሾመ እንዲሁም መስቀሉን በእጁ ለመያዝ ሲሞክር አንዳች ነገር ወደ ላይ አስፈጥንሮ መሬት ላይ እንደጣለውበደረሰበት አደጋ ራሱን ስቶ ቆይቶ በ4ኛው ቀን መንቃቱንና በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ፣ “መስቀሉን ተመልክቶ ሊያነሳው እጁን ሲሰነዝር ከኋላው አንዳች ህፃን ልጅ የመሰለ ነገር ጐትቶ መሬት ላይ እንደጣለውና ከዚያ በኋላ የሆነውን እንደማያውቅ” ከተናገረ ወጣት ነው።
 ጉዳዩ የተገለጸላቸው በርካታ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሰኞ ነሐሴ 27/2005 ዓ.ም በቦታው ተገኝተው  መስቀሉ ከወደቀበት መሬት ተነ ወደተዘጋጀለት ሥፍራ ሲገባ የተሸከሙት አባት “እያቃጠለኝ ነው” ሲሉ እንደነበር  እናም ውሎ አድሮ ለአካባቢው ፀጥታ በማሰብ መስቀሉ በየለቱ ለምዕመናን እንዳይታይ ከቤተክህነት ትዕዛዝ እንደተላለፈ ጠቅሰው፤ መስከረም 19ቀን 2006 ዓ.ም በቤተክርስቲያኑ ቅር ግቢ መስቀሉን በይፋ ለይታ ለማብቃት ቀጠሮ መያዙን አዲስ አድማስ ዋቢውን መጋቤ ሐዲስ ተሾመን ጠቅሶ ጽፏል። መስቀሉ የሰው ራ እንዳይሆን የተጠራጠሩ ካህናት መኖራቸውንም ጋዜጣው ነግሮናል፣ ባያብራራውም።

ወራቱ የአዲስ ዘመን ብሎም የወርኃ መስቀል ነውና ተቀብሮና ከሰው ተሰውሮ የነበረው መስቀል የወጣበት ግብር በሚዘከርበት ሰሙን “መስቀል ከሰማይ ወረደ” መባሉ ስለሁናቴው እንድናነሣ ይጋብዛል። በሌላው ዓለምም ቢሆን እንዲህ ያለ ዜና የማንንም ጆሮና ዓይን መሳቡ አይቀርም። ጆሮ ገብ መሆኑ እና ለማየት የሚያጓጓ መሆኑ ብቻ ሳይሆን “በርግጥ ነገሩ እውነት ነው?” የሚል ጥያቄም ያሥነሣል።

በተለያየ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ እንደሚነገረውና እንደተጻፈው እንዲህ ያለ ለሰው ኅሊና የሚከብድ ነገር ሲከሰት አበው ድርጊቱን ማረጋገጫ ተግባራት አሏቸው፤ ነበሯቸው። በየዓመቱ ከምናከብረው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መቀበርና መገኘት ጋር ያለውን ትውፊታዊ ሐቲት ከማንሣት እንጀምር።

ጌታ በቅንዓተ አይሁድ ከተሰቀለ በኋላ፣ ታሪኩ እንደሚያትተው፣ የሰቀሉት ሰዎች ባለ ገቢረ ተአምሩን መስቀል ማጥፋት ፈለጉ። ምክንያት? መስቀሉ ተአምራት በመሥራቱ። ስለዚህም እንዲቀበርና የከተማው ቆሻሻ ሁሉ እንዲጣልበት ወሰኑ። ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ ቆየ። ንግሥት ዕሌኒ (የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት) አስቆፍራ ብታስወጣው አንድ መስቀል ብቻ ሳይሆን ሦስት መስቀል ተገኘ። ሁለቱ ከጌታ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች፣ አንዱ የጌታ። ታሪኩ እንደሚነግረን የጌታን መስቀል ከወንበዴዎቹ ለመለየት መስቀሎቹን ፈተኗቸው። “ተአምራት የሚያደርገው ያ ትክክለኛው መስቀል ነው” አሉ። ሙት ላይ ቢያስቀምጡት ሙት አሥነሣ፣ አንካሳ ተረተረ (ፈወሰ)፣ ዕውር አበራ ሌላም ሌላም ተአምራት ሠራ። ሌሎቹ ሁለቱ ግን ምንም ሳይሠሩ ቀሩ። ስለዚህም መስቀሉ ልዩ መሆኑን፣ ጌታ የተሰቀለበት መሆኑን አወቁ። “ለመስቀልከ ንሰግድ ኦ ሊቅነ።”

በሌላ ታሪክ ዲሜጥሮስ የተባለው የግብጽ አባት ድንግላዊ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ቤተሰቦቹ በግድ ካጋቡት ሚስት ጋር በአንድ ቤት ይኖር ነበር። ቢጋቡም ሁለቱም ራሳቸውን እንደጠበቁ በድንግልና ለመኖር የወሰኑ ሰዎች ነበሩ። የረዥሙን ታሪክ በአጭሩ ስናደርገው፦ ይህ አባት ጵጵስና እንዲሾም ይመረጣል። ይሁን እንጂ ጳጳስ ለመሆን ያላገባ ድንግላዊ መሆን ሲገባው ዲሜጥሮስ ግን “ባለትዳር መሆኑ” ብዙዎችን ፈተነ። ይህን የሚያውቅ እግዚአብሔርም ያገባ መስሎ በድንግልና የሚኖረው ዲሜጥሮስ ራሱን እንዲገልጥ አዘዘው። ስለዚህም ሕዝብ በተሰበሰበበት እርሱም የተዳረችለት ሴትም በልብሳቸው እሳት ይዘው በሕዝቡ መካከል ዞሩ። በኋላ እሳቱን ቢዘረግፉት እሳቱ ልብሳቸውን፣ የልብሳቸውን ሰናፊል ሳያቃጥል ቀረ። ንፁሐን መሆናቸውም በዚህ ተመሰከረ። በእሳቱ የተፈተነ ታሪካቸው ምስክርነት አገኘ - ይላል ታሪካቸው።

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ፦ በዘመናችን መስቀል ከሰማይ ከወረደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንን አረጋግጣ ለአማኞቿ የምታሳውቅበት መንገድ ምንድነው? ለሕዝብ ለማሳየት ቀጠሮ የተያዘው “አዎ መስቀሉ ከሰማይ የወረደ ነው፤ ተአምር ነው፣ ስለዚህም እግዚአብሔር በዚህ መልክ እየተናገረን ነው” ለማለት ነው? እንዲህ ያለውን ማስረገጫ የመስጠት ሃይማኖታዊ ኃላፊነቱ የማን ነው? በርግጥስ ይህ አካል በትክክሉ ተናግሯል?

“እንደ ጥንቱ ከሙታን ላይ ቢያስቀምጡት ሙት የሚያሥነሣ፣ ከዕውራን ላይ ቢያኖሩት ዕውር የሚያበራ፣ ሽባ የሚያረታ፣ ተአምራት የሚያሳይ መሆኑ ሳይፈተን … ዘመኑ እንደሚፈቅደውም እንፈትነው የሚል ጠያቂ ቢገኝ የዘመኑ ዕውቀት ባስገኛቸው ጥበቦች ታይቶ በርግጥም የሰው እጅ ያልነካው፣ አማናዊ ተአምር፣ ሰማያዊ መስቀል መሆኑ ሳይታወቅና ሳይረጋገጥ በደምሳሳው ለዕይታ የሚቀርብ ነው ማለት ነው?” ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ከአርባ  ዓመት በፊት  በግብጽ ካይሮ በዘይቱን ማርያም ቤተ ክርስቲያን  እመቤታችን ቅ/ድንግል ማርያም ተገልጣ በጉልላቱ ላይ ስትመላለስ ታይታለች፡፡ ምንም እንኳን መገለጧ ሰው ሁሉ የሚመለከተው የአደባባይ ተአምር ቢሆንም ሲኖዶሱ ልዑካንን ወደ ቦታው ልኮ ሊቃነ ጳጳሳት አይተው እውነተኛነቱን እስኪያረጋግጡ ጊዜ ተወስዷል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ (የወቅቱ የግብጽ ፓት) የእመቤታችንን መገለጥ ይፋ ያደረጉት ከዚያ በኋላ መሆኑ ይነገራል፡፡

በሌላ ታሪክ፦ ጌታችን በተቀበረ ጊዜ ሥጋው ተጠቅልሎበታል ተብሎ የሚነገርለትና የሰው መልክዕ እና ገጽ በተአምራት የታተመበት ጨርቅ (“Shroud of Turin”) በካቶሊኮች እጅ ይገኛል። ለብዙ ዘመናት ሲያከራክር የነበረ ነገር ነው። ገሚሱ በመካከለኛው ዘመን የተሠራ ማታለያ ነው ሲል ሌላው ደግሞ የጌታ ሥጋ የተታታበት ቅዱስ ጨርቅ ነው ብሎ ሲከራከር ቆይቷል። ከ1960ዎቹ ጀምሮ ብዙ ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት ቡድን ሳይቀር ሳይንሳዊ ምርምር አድርጎበታል። በ2005 ዓ.ም በተደረገ የተራቀቀ ጥናት ጨርቁ በክርስቶስ ዘመን የነበረ መሆኑን ሳይንቲስቶች ማረጋገጣቸውን እማኝ ሆነዋል። ቫቲካን ግን አሁንም “አዎ ትክክለኛ የክርስቶስ መግነዝ ነው” ብላ አልተናገረችም። ጥንቃቄው እንደተጠበቀ ነው።

ከሰማይ ወርዷል የተባለው የእኛ መስቀል በሊቃነ ጳጳሳት መታየቱ መልካም ነው። ውጤቱንና የደረሱበትን ለመስማት በጉጉት እንጠብቃለን፡፡ አሁን እየሰማን ያለነው ግን ከተለያዩ የዜና ምንጮች ብቻ ነው፡፡ በጥንቱ ዘመን ተአምራት መፈጸማቸውን ሕዝቡ ቢያቀርብም በመጨረሻ  ትክክለኛ መሆኑን የማረጋገጥ ድርሻ የቤተ ክርስቲያኒቱ ነበር፡ አሁንም ይኸው መቀጠል አለበት። ቤተ ክርስቲያን የእውነት መዝገብ እንደመሆኗ እንዲህ ላለው ነገር ማረጋገጫ የመስጠት፣ አማናዊውን ከሐሰተኛው ተአምር ለይቶ ሕዝቡን በርቱዕ እውነት የመጠበቅ ኃላፊነት የእርሷ ነው።

ክርስትና በተአምራት የታጀበ ሃይማኖት ነው ሕዝቡ “በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው?” ብሎ እስኪደነቅ ድረስ (ማርቆስ 6፡2) ራሱ ክርስቶስ በማስተማር ዘመኑ ብዙ ገቢረ ተአምራት ያደርግ ነበር። ተአምር በየዘመኑ ይደረጋል። ተአምር በዚህ ዘመን ነበር በዚህ ዘመን ግን አይኖርም ሊባል የሚቻል አይደለም። አበው እንደሚሉት “ሰማይን ያለ ካስማ ምድርን ያለ ማማ ያቆመ አምላክ” ሥራውን መሥራቱን የማያርጥ እንደመሆኑ ተአምራትም በየጊዜውና በየዘመናቱ መታየታቸው ይቀጥላል። ጥያቄው ቅ/ዳዊት እንደሚለው “መኑ ያርእየነ ሠናይቶ?” ነው (መዝሙረ ዳዊት 4፡6)።

ይቆየን - ያቆየን

 


ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ በሚታተመው ‘አዲስ ጉዳይ’ መጽሔት ላይ ሰፕቴምበር 21/2013 (መስከረም 11/2006 ዓ.ም) የወጣ ነው።


A Must listen audio about Meskel. 

(http://www.aleqayalewtamiru.org/files/aat_16_01_95_meskel.mp3

3 comments:

Anonymous said...

+++
እንደ ጥንቱ ከሙታን ላይ ቢያስቀምጡት ሙት የሚያሥነሣ፣ ከዕውራን ላይ ቢያኖሩት ዕውር የሚያበራ፣ ሽባ የሚያረታ፣ ተአምራት የሚያሳይ መሆኑ ሳይፈተን … ዘመኑ እንደሚፈቅደውም እንፈትነው የሚል ጠያቂ ቢገኝ የዘመኑ ዕውቀት ባስገኛቸው ጥበቦች ታይቶ በርግጥም የሰው እጅ ያልነካው፣ አማናዊ ተአምር፣ ሰማያዊ መስቀል መሆኑ ሳይታወቅና ሳይረጋገጥ በደምሳሳው ለዕይታ የሚቀርብ ነው ማለት ነው?” ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

elias kiflemariam said...

በዛው ጋዜጣ ላይ ሳይንሳዊ ምርመራ ማድረግ አይፈቀድም በማለት መልስ የሰጡት አባት ያለሲኖዶሱ ፈቃድ ይህን ማለት ይችላሉን?

elias kiflemariam said...

በዛው ጋዜጣ ላይ ሳይንሳዊ ምርመራ ማድረግ አይፈቀድም በማለት መልስ የሰጡት አባት ያለሲኖዶሱ ፈቃድ ይህን ማለት ይችላሉን?