Saturday, October 19, 2013

ያማርኛ ስልት

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ “መዝገበ ፊደል፤ የግእዝና ያማርኛ ቋንቋ መክፈቻ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ስለ አማርኛ ቋንቋ የሚከተለውን ብለው ነበር።

ያማርኛ ስልት እንደ ሕዝቡ አራት ክፍል ነው። አንደኛው የቤተ ክህነት፣ ኹለተኛው የቤተ መንግሥት፤ ሦስተኛው የነጋዴ፤ አራተኛው የባላገር። የቤተ ክህነት ዐማርኛ በሰዋስው ተመሥርቶ ባገባብ የታነጠ፣ በትርጓሜ የተቀረጠ፤ በግእዝ አባ የተጌጠ ነው። ከግእዝ በቀር ሌላ ባዕድ ቋንቋ አይገባበትም። የቤተ መንግሥት ዐማርኛ የግእዝ ትምርት ስላለበትና ሠራተኞቹ የካህናት ወገን ስለ ኾኑ እጅግ ስብቅል ነው፤ ቃላትን ኹሉ ‘እግዜር’ እንደ ማለት በማሳጠርና በማሳመር በማከናወን ይነገራል።
… የነጋዶችና የቀራጮች የመዝገብ ጣፎች ዐማርኛ ግን እንደ ንፍሮና እንደ ልመና እኽል ቅይጥ ውጥንቅጥ ነው። ሥራቸውና መሣሪያቸው ከውጭ አገር ጋራ ስለ ኾነ በሸቀጡና በንግዱ ዕቃ መጠን በየጊዜው ሌላ ባዕድ ቋንቋ እየጨመረ፤ ሳይቸግረውም እየተበደረ ያነኑም እያዘናጎለ ብርዑን ‘ብዕር’ እያለ በድብልቅልቅነት ሲጣፍና ሲነገር ይኖራል። . . . የባላገሮች ዐማርኛ ሥረ ወጥ ነው። ጥፈትና ትምርት ስላጣ መታደስ መለወጥ መሰብቀል፣ መሻሻል የለውም። በዚያው በዱሮው በጥንተ ተፈጥሮው ይነገራል።
(አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ “መዝገበ ፊደል፤ የግእዝና ያማርኛ ቋንቋ መክፈቻ”፣ 2ኛ መጣፍ፤ 1953 ዓ.ም ድጋሚ የታተመ። ገጽ 15። መጽሐፉ መጀመሪያ የታተመው በ1926 ዓ.ም ነው።)


አዪዪዪ አለቃ፤ የዘንድሮን የዘመኑን ባዩ። ጋዜጣው እንዴት እንደሚጥፍ፣ የሬዲዮ ተናጋሪው እንዴት ባለ ዐማርኛ እንደሚናገር፣ ፊደላቱ እንዴት እንደሚንገላቱ።

2 comments:

Anonymous said...

deank nwe

ግእዝ በመሥመር-ላይ said...

አትቆፍረው የለኽ፤ አንተ ዐይናማ! አሳፈርከኝ'ኮ። እኔ'ንኳ ቤተ ክህነት ቀመስ ነኝ ብየ ዐስብ ነበርኍ፤ ባለፈው ግን እንደ ነጋዴው አንዱን ቃል አዘናጉየዋለኍ። ይኸውም ብርዑን ብዕር ብየ ጥፌው ቍጭ።

ለነገሩ ዐውቄ ነው ያጠፋኹት። "ብርዔን አነሣኍ" ለማለት ዐሰብኹና የዛሬ አንባቢ ግራ የሚጋባ ቢመስለኝ "ብዕሬን አነሣኍ" አልኍ። ከዚያው ቀጥሎ ቃሉን ሳይዘረዝር ስጠቀመው ግን እንዳጀማመሬ "ብዕር" በማለት ፈንታ "ብርዕ" ብየ ትክክሉን ጣፍኹት። ክህነት ቀመሱ ጣቴ ራሱን በራሱ አቃንቶ መኾኑ ነው።

ይኹን እንጂ ጉዳዩ ጥቂት አመራመረኝ። እንዲኽም አልኍ፦ "የምጥፈው ዐማርኛ፤ ዐማርኛው የግእዙን ብርዕ 'ብዕር' ብሎ ከወረሰው፤ አይኾንም ብለን የምንታገል ለምንድር ነው? 'ሰብአ ቤት'ን 'ቤተ ሰብ' አይደል የምንል?" ከዚኽም ጋር ኮሌጅ ሳለኍ ከሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ጋራ የተሟገትኹትን አስታወስኍ። አንድ ተማሪ "ክብር"ን ሲያነብ "ብ"ን በፍቅደት ያነባል። ርሳቸው "ክብር" ፍጹም ሳድስ ስለኾነ ይጠቀልላል ብለው አርሞ እንዲያነብ ያደርጉታል። እኔ ታዲያ እጄን ብድግ። "የተነበበው'ኮ ዐማርኛ ነው። ባማርኛ ክብር የሚወጣው 'ከበረ' ከሚለው ጠብቆ ከሚነበብ ግሥ ስለኾነ፤ 'ክብር' ተብሎ 'ብ'ን በማጥበቅ ባይነበብ እንኳ 'ብ'ን በፍቅደት ማንበብ የሚገባ ይመስለኛል" አልኍ። ሙግቱ ቀጠለ። እንዴት እንደቋጨነው ግን ትዝ አይለኝም...

አኹን ግን መለስ አልኹና ደግሞ፦ "በዚኽ ዐይነት አካኼድ እንደሻን እንደተመቸን የምንቀጥል ከኾነ'ኮ ባንዳንድ አሥራወ ቃላት አማካይነት ልናያቸው የሚችሉ ክሥተቶች፤ አሥራወ ቃላቱን በማዛባት ምክንያት ይሰወሩብን ይኾናል" አልኍ። ይኸን በተመለከተ ደግሞ ከዚኽ ቀደም እዚኹ እመርበብቱ ላይ አንድ "ዲባቶ" (ዶክቶር) ተነሥቶ እግዜርን አብሔር እንበል ብሎ ዐሳብ በማቅረቡ የገጠምኹት ሙግት ትዝ አለኝ።
http://ethiomedia.com/absolute/on_the_dibato.pdf