Friday, December 19, 2014

“ህልም እንደሆነ አይታሰርም”

(ጦማሪ አቤል ዋበላ/ Read in PDF)
‹‹ስሜ አቤል ዋበላ ነው፡፡ አዲሱ አመት ሲጠባ በአዲስ መንፈስ አዲስ ህልም ለአገሬ ማለም የነበረኝንም ማጠናከር እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያችን የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የሀብት፣ የትምህርት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ሌሎችም ልዩነቶች አብሮነታችንን የማያደናቅፉባት ከነልዩነታችን በጋራ ለታላቅነት የምንጠቀምባት ለሁላችንም ዕኩል ዕድል እና ተጠቃሚነት የሚቀርብባት ሁላችንም እንደየ ችሎታችን ለጋራ ደህንነታችን ነፃነታችን እና ብልፅግናችን የምንሰራባት ብቻ ሳይሆን በጋራ ስኬታማ የምንሆንባት እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕኩል የሚያፈቅራት ኢትዮጵያ እንድትሆን እመኛለው፡፡ ይህ የእኔ ኢትዮጵያዊ ሕልም ነው፡፡››

Friday, December 5, 2014

“ፌስቡክ እና ስደት፦ የሰው ልክ አያውቅም … ቢሆንም"

(ከኤፍሬም እሸቴ/ Read in PDF)
እንደ ስደት ክፉ ነገር የለም። የታወቀ ነገር ነው። ቢሆንም ለአጽንዖተ ነገር እንድገመው። የተሰደደ ሰው ማንነቱ ምንነቱ በቅጡ አይታወቅም። ስደት ከሰው ያሳንሳል። አንገት ያስደፋል። ከስደትም ስደት አለው በርግጥ። በአውሮፕላን ከአገራቸው ወጥተው ሕግ ያለበት አገር (ሰው በሌለበት አገር) የሚኖሩ አሉ። ሰው የሌለበት ማለቴ ወዳጅ ዘመድ ለማለት ነው። “ከዘመድ ባዳ፣ ከአገር ምድረ በዳ” እንዲል። ደግሞ በእግራቸው አገር ቆርጠው፣ ባሕር ተሻግረው፤ በምድር ከሚሽከረከረው፣ በባሕር ከሚንከላወሰው አውሬ ጋር ታግለው፤ ከሰው አውሬዎችም ጋር ታግለው እያለፉ ስደት የሚገቡም አሉ። በባሌም ይውጡ በቦሌ፣ ስደት ያው ስደት ነው። የሰው ልክ አያውቅም።

Friday, November 28, 2014

"ድልድዮቻችንን አናቃጥል"

(ከኤፍሬም እሸቴ/ PDF)
ፈረንጆች አንድ አባባል አላቸው። “ድልድይ ማቃጠል” የሚባል። አንዱ ከሌላው ጋር ሲነጋገር “ለምንድነው ድልድይህን የምታቃጥለው?” ሊለው ይችላል። ወይም ሌላው “ድልድዬን ማቃጠል አልፈልግም” ይላል። ትርጓሜው አንዴ ያለፍክበትን ድልድይ ካቃጠልክ ወደዚያ ቦታ አትመለስም ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት በሰላም፣ በፍቅር፣ ያልምንም ቁርሾ ቢለቅ ድልድዩን አላቃጠለም፤ እንዳይሆኑ ሆኖ ቢለያይ ግን “ድልድዩን አቃጠለ” ይባላል። “እንጀራ ገመዱን በጠሰ” እንዲል ሐበሻ።

Thursday, November 27, 2014

Thanksgiving የምሥጋና በዓል፣ በዓለ አኮቴት

 (ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ TO READ IN PDF)
ዛሬ “Thanksgiving” ላይ ቆሜ ስለዚህ በዓል ለብዙ ጊዜ ልጽፈበት እየፎከርኩ አለማድረጌን እየወቀስኩ ጥቂትም ቢሆን ልልበት ወሰንኩ። ምናልባት የፈረንጅ በዓል ስለሆነና ገና ስላልተዋሐደኝ ባዕድ ሆኖብኝ ይሆን እንጃ በተከታታይ ሦስት ዓመታት ብዕሬን አንስቼ ሳልፈጽመው ቀርቻለኹ። ዘንድሮስ አይሆንም ብያለኹ። በተለይ ለረዥም ዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን በሐላፊነት ሲመሩ የነበሩትና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ “እኛ ልመና እንጂ ምስጋና አናውቅም፤ ማመስገን ያስፈልገናል” ይሉት የነበረው አባባላቸው የበለጠ አበረታቶኝ የግል ሐሳቤን ለመጠቆም ደፈርኩ።

Monday, November 24, 2014

“የምክር ቃል”፦ የውጪ አገር ነገር

This article was first posted in 2011. Reposted today. Enjoy.
ባለፈው “በኢትዮጵያ አእምሮ” ያለውን “የአሜሪካ ኑሮበተመለከተ አንዳንድ ሐሳቦች ለማካፈል ከሞከርኩ በኋላ ብዙ አበረታች ሐሳቦች እና መልእክቶች ደርሰውኛል። የበለጠ እንድንወያይበት የሚያደርጉ መነሻዎችም አግኝቻለኹ። በተለይም የኒውዮርኩ ወዳጄ ዶ/ር ታዬ ሁሴን ያደረሰኝ “የምክር ቃል” የምትል የቆየች “ምጥን መጽሐፍ” (ትንሽ መጽሐፍ) ርዕሰ ጉዳዩን እንድመለስበት አድርጋኛለች። ይህ መጣጥፍ በዚህቹ መቶ ዓመት ሊሞላት 14 ዓመት በሞላት መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱትን ነጥቦች ለማስታወስ ይሞክራል።

Tuesday, November 18, 2014

አስገድዶ በመድፈር ለተቀጠፈች ነፍስ መልሱ ምንድነው?

(ከኤፍሬም እሸቴ/ Read in PDF)
ይህንን ነገር በተመለከተ እንዲህም እንዲያም ከማለታችን በፊት ነገሩ ምን እንደሆነ የሪፖርተር ጋዜጣን (NOVEMBER 16/2014) ዘገባ በማስቀመጥ እንጀምር። “በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቄራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አየር ጤና አካባቢ አንዲት የአሥረኛ ክፍል ተማሪ በተሳፈረችበት ታክሲ ታፍና ከተወሰደች በኋላ በደረሰባት አስገድዶ መደፈር ጉዳት ሕይወቷ ማለፉን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ነሟቿ ተማሪ ሃና ላላንጎ ጥቅምት 21 ቀን 2007 .. አየር ጤና በተለምዶ ሳሚ ካፌ በሚባለው አካባቢ በአንድ ሚኒባስ ውስጥ ተሳፍራ ወደ ጦር ኃይሎች እየመጣች … የተወሰነ ርቀት ከተጓዘች በኋላ መድረሷን ተናግራ ‹‹ወራጅ አለ›› ስትል፣ በሚኒባሱ ውስጥ የነበሩ አራት ወንዶችና ሾፌሩ ስለት በማውጣት አስፈራርተውያግቷታል። ከዚያም “በሰዋራ ቦታ በታክሲው ውስጥ እንድታመሽ ከተደረገች በኋላ፣ ከተጠርጣሪዎቹ አንደኛው ቤት ወስደው ለአምስት እየተፈራረቁ እንደደፈሯት … አንደኛው ተጠርጣሪ በራሱ ቤት ውስጥ እንድትቆይ በማድረግ ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲደፍራት እንደከረመ ሁለተኛ ተጠርጣሪ ነው የተባለው ግለሰብ ለአምስት ቀናት በተደጋጋሚ ሲደፍራት ከከረመ በኋላ፣ ከቤት አውጥቶ ጭር ባለ ቦታ ጥሏት” ተገኘች፡፡ ነገር ግን “የማሕፀንና የፊንጢጣ ጉዳት አጋጥሟት ስለነበር በተለያዩ ሆስፒታሎች ሕክምና ያደረገች ቢሆንም፣ በደረሰባት ከባድ ጉዳት በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል በመታከም ላይ እያለች ሕይወቷሊያልፍ ችሏል።”
“ሟች በመሀል በአንደኛው ተጠርጣሪ ስልክ ወደ ቅርብ ጓደኛዋ በመደወል ስልኩን በመዝጋቷ ጓደኛዋ የደወለችበትን ስልክ ለቤተሰቦቿ ትሰጣለች፡፡ የሟች ቤተሰቦች የሞባይሉን ቁጥር ለፖሊስ አሳልፈው በመስጠታቸው ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ የክትትል ሥራ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርበው በወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 35 መሠረት የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውም” ተገልጿል፡፡

Saturday, November 8, 2014

ጓደኛ ለማድረግ የማይመቹኝ የፌስቡክ ስሞች

ደግነቱ 5000 ሊሞላኝ ነው እንጂ ባይሞላኝም እንኳን የጓደኝነት ጥያቄያቸውን ለመቀበል ገና ስማቸውን ሳይ የሚከለክለኝ (የሚዘጋኝ አላልኩም) ሰዎች አሉ። ሰው ሰው የማይሸቱ ስሞች፣ ዐ.ነገር የሆኑ ስሞች እና ከሃይማኖት ጋር ተገናኝተው የሚያስፈራሩ የሚመስሉ ስሞች፣ ስማቸው ራሱ ጾታዊ ግንኙነትን የሚያበረታታ የሚመስሉ ስሞች ወዘተ ሲመጡ ያለምንም ጥርጥር አልቀበላቸውም። ከዚህ በታች ያሉት ምሳሌዎች ከዋነኞቹ ትንሽ ለወጥ ተደርገው የቀረቡ ናቸው። እነሆ፦
“ራእዩን እናስቀጥላለን”፤
“ወያኔ ይውደም”፤
“እንትና ስዊት”
“ምናምን ላቭ”
“እንትና የድንግል ማርያም ልጅ”
“እግዚአብሔር ያውቃል”
“አላህ ወኪል”
“የማርያም ልጅ”
“የማርያም ወዳጅ” ወዘተ ወዘተ …

Friday, November 7, 2014

ዩኒት ሊደር፣ ስም ጠሪ እና የክፍል አለቆች

(ከኤፍሬም እሸቴ/ Read in PDF)
በግርፊያ ተቀምሞ፣ በቁንጥጫ ወይም “እጅ-በጉልበት-ሥር-በማሾለክ-ለረዥም-ጊዜ-መቀመጥ” ወይም “በእንብርክክ በመሰለፍ” የሚሰጥ የዕውቀት ዘር ማለት የትምህርት ትርጉም ይመስለኝ ነበር ልጅ ሆኜ። መምህር ማለት ደግሞ ክፍል ውስጥ ስም የሚጠራ እና ልጆችን በተለያየ መልኩ የሚገርፍ ትልቅ ሰውዬ። የክፍል አለቃ ማለት ደግሞ በዕድሜው ወይም በቁመቱ ወይም በሁለቱም  ከመካከላችን ዘለግ ያለ እና የመጨረሻው ወንበር ላይ የሚቀመጥ ጠና ያለ ተማሪ።
ስም ጠሪውን፣ ሌሎቹን መምህራን እና አለቃችንን በመግረፍ ዘርፍ የሚያሰማራቸው ዋናው ሰው ደግሞ ዩኒት ሊደር ይባላል። ትምህርት ቤትና ቅጣት የጀመርነው ገና ሀ ብለን ከቤት ስንወጣ የኔታ ጋር ነው። እንደው ዕድሌ ሆኖ የኔታ አልገረፉኝም። ምናልባት አላጠፋሁ ይሆናል። ምናልባት ፊደሎቹ ቶሎ ገብተውኝ ወይም ከመቅጠኔ የተነሣ ለአቅመ ዕይታ አልበቃሁምም ይሆናል። ከፊደል ቆጠራ ጀምሬ እነ አቡጊዳ እስክደርስ ግን የኔታ አውቀውኛል። የኔታ ውዳሴ ማርያም ደጋሚ፣ ዳዊት ደጋሚ ናቸው። በዕድሜዬ በሙሉ ስሜን ሲጠሩ የሰማኋች አንዲት ቀን ናት እርሷንም ቢሆን ኤፍሬምሳይሆን “የፍሬም” ነው ያሉኝ። የሆነው ሆኖ የኔታ አልገረፉኝም። ግን ሲጋረፉ አይቻለሁ። አቤት አለንጋቸው…..

“አለማወቅ ደጉ”

አለማወቅ፣ አለመጠየቅአያኮራም። አካባቢን ለማወቅ አለመፈለግ፣ ነገሮችን ሁሉ፣ በዙሪያችን የሚከናወኑትን ነገሮች ለመገንዘብ ፍላጎት ማጣት አያኮራም። ጭራሽ ስለ አገር አለማወቅና አለመጨነቅ፣ አለመጠየቅና አለመረዳት እንዴት ሊያኮራ ይችላል

እንግሊዛዊው ገጣሚና የሥነ ጽሑፍ መርማሪ ቶማስ ግሬይ (Thomas Gray) የሚታወቅባት አንዲት የግጥሙ ቅንጣቢ ለእኛም ትሠራለች።
"where ignorance is bliss,
'tis folly to be wise." ብሏል።

Sunday, November 2, 2014

“ዚአከ ለዚአየ”፤ የጉርሻ አመጣጥ ... The Origin of Gursha

(ከኤፍሬም እሸቴ/ Read in PDF)
Gursha by Alex Tefera
ከዕለታት በአንድ ቀን እግዚሐርን የማይፈራ ሰውን የማያፍር ንጉሥ በአገራችን ነገሰ አሉ። ያም ክፉ ንጉሥ ሕዝቡን ከዋለበት አላስውል፣ ካደረበት አላሳድር ብሎ ሰላም ነሣው። በሕዝቡ መከራና ሥቃይም እጅግ ይደሰት ነበር። እንደርሱ በሰው ለቅሶ ወደሚደሰቱ ሳዲስት የሮማ ሄሮድሶች እየተጻጻፈ አዳዲስ ነገር እየተማረ በክፋቱ ላይ ክፋት ጨመርን ልማድ አደረገ። ለሄሮድስ በጻፈው አንድ ደብዳቤው እንዲህ አለ፦
የተከበርክ ታላቁ ሄሬድስ ሆይ፤
ለጤናህ ከነሰፊው ግዛትህ እንደምን አለህ? እኔ ይኸው ከምድረ አዜብ እስከ ባሕር ማዶ፣ ተራራውንና ሜዳውን ቆላውንና ደጋውን እንዲሁም ወይና ደጋውን እንደ ገል ቀጥቅጬ እንደ ሰም አቅልጬ እየገዛኹት ነው። ሙቀት አስቸገረን ሲሉ ብርድ አገር፣ ብርዱ በረታብን ሲሉ ቆላ እያሰደድኩ እነሆ በደስታ እኖራለሁ። በዋዕይ አንድም በቅዛቃዜ አሳራቸውን አበላቸዋለሁ። እንደ አባቶቼ ዘመን ጦሬን እፈትንበት ዘንድ፣ ጋሻዬ ተሰቅሎ የትኋን ማዕከል እንዳይሆን ብዬ የጦር ያለህ ብል የሚገጥመኝ ባጣ ሕዝቡን ራሴው ገጥሜዋለሁ።

Saturday, November 1, 2014

የጠፋችው ሦስተኛዋ ፎቶ

የጠፋችው ሦስተኛዋ ፎቶ እነሆ ተገኝታለች። የፎቶዋ ባለቤትነት የሮይተርስ መሆኑን ቢቢሲ ጽፏል። በመጀመሪያ የትኛዋን ፎቶ ማለቴ እንደሆነ ለገባችሁ፣ ከዚያም በላይ ፎቶዋን ጎልጉላችሁ/ ጎጉላችሁ (ጉግል እንዲል) ፈልጋችሁ ላገኛችሁ ሁለት ወዳጆቼ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ። አንድ ነገር ላስታውሳችሁ፤ ግርምቴን። ፕሬዚዳንት ኬኔዲ ዳላስ ቴክሳስ ውስጥ በተገደሉበት ጊዜ (November 22, 1963 ማለትም በእኛ አቆጣጠር ኅዳር 12/1956 ዓ.ም) መንገድ ዳር ከነበሩና በፎቶ ቀራጺዎች እና አንሺዎች “ሌንስ ውስጥ” ከገቡ ሰዎች መካከል ሁለቱን ጋዜጠኞች ፈልገው ሲያናግሩ ተመልክቼ ነበር። እኛም እንዲህ ያለው ወግ አንድ ቀን ይደርሰን ይሆናል። ፎቶ አንሱ። አስቀምጡ። ታሪክ የሚመዘገበው እንዲህ ነው። “ለፎቶ ዋጋ ሥጡ” እንበል እንዴ?
(Source BBC, EthiopiaTesfaye)

"የጠፋችብኝ ሦስተኛዋ ፎቶ"


1997 ዓ.ም (2005) ትዝ ሲለኝ፣ አገር በየቀኑ ለቅሶና ኃዘን ላይ የተቀመጠበት ያ ሰሙን ሲታወሰኝ፣ በየቀኑ ከቤተሰቤና ከወዳጆቼ ጋር ተሰብስበን ያፈሰስነውን የጸጥታ ዕንባ ሳስታውስ በኅሊናዬ የሚመጡት በየሰዓቱ የምናየው ደም (አሰቃቂና ዘግናኝ ፎቶ) ብቻ ሳይሆን በወገኖቼ ዓይኖች ላይ ያየኋቸው ጥርት ያሉ ዕንባዎችም ናቸው። 
በተለይ በተለይ እስካሁንም የማልረሳቸው ሦስት ፎቶዎች አሉኝ። ሁለቱን ዛሬም ድረስ ይዣቸዋለሁ። ሦስተኛዋ ናት የጠፋችኝ። የጠፋችብኝ ፎቶ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ በጥይት ለቆሰሉ ሰዎች ርዳታ የምትሰጥ የአንዲት ባለ ሹሩባ ነርስ ፎቶ ነው። ያቺ ልጅ ከለበሰችው ነጭ ጎዋን እና ከዕለት የነርስነት ተግባሯ በላይ የሚፈስሰው ዕንባዋ አይረሳኝም። እያለቀሰች የወገኖቿን ቁስል የምታክም ልጅ። ሁለቱን ፎቶዎች ደግሞ እነሆ ከዚህ ለጥፌያቸዋለሁ። የ1997 ዓ.ም ምልክቶች የሆኑ ፎቶዎች። 

Blog Archive