Saturday, March 15, 2014

ተግሳጽ እና ጅራፍ

(READ IN PDF):- ጌታም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። ቤተ መቅደሱ በንግድ ደምቆ ነበር። “ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ትሰመይ” ብሎ ጅራፉን አነሣ። የሸቃጮቹን ገንዘብ በተነ፣ ገበታቸውን ገለበጠ። ያጎሯቸውን እንስሳት አስወጣ። ቅዱስ ዳዊት “የቤትህ ቅናት በላኝች” እንዳለው ሆነ።

በየዓመቱ የዐቢይ ጾም/ ሑዳዴ ሦስተኛ ሳምንት ከፍ ተብሎ የተጠቀሰው ታሪክ የሚታወስበት ሲሆንም ቅዱስ ያሬድ በሠራለት መዝሙር ስያሜም “ምኩራብ” እየተባለ ይጠራል። በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ስለ ክርስቶስ ተግሳጽ እና ኋላም ጅራፍ ገምዶ ከቤተ መቅደሱ ነጋዴዎችን ማስወጣቱ የሚተረክበት በዓል ነው።

ቅዱስ መጽሐፍ ደጋግሞ እንደሚያስተምረን ክርስቶስ የፍቅር አስተማሪ ነው።  “ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት” እንዲሁም “ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ” (ማቴዎስ 5፥39 እና 5፥41) በሚለው የትዕግስት እና የይቅርታ ትምህርት ይታወቃል። ቀኝ ጉንጭህን ሲመታህ ግራህን አዙርለት ቢልም ከሕግ የወጡትን ደግሞ በትምህርቱ “እናንተ ግብዞች … በውጭ አምረው የሚታዩ … በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።” (ማቴዎስ 23፥27) እያለ ይገስጻቸዋል። ቃለ ትምህርቱን አልሰማ፣ ቃለ ተግሳጹንም አልቀበል ብለው በመቅደሱ ገበያ ያደሩትን ደግሞ ጅራፉን ገምዶ እየገረፈ አስወጥቷቸዋል።

ይህ ታሪክ በየዓመቱ በታላቅ ክብር ይነገራል፤ ይተረካል፤ ይሰበካል። የሚገርመው ግን መገሰጽ ያለባቸው፣ ጅራፍ የሚያስፈልጋቸው ዋና ነጋዴዎች ሳይቀሩ ታሪኩን አሳምረው ይተርኩታል። ሰሚውም የዚያን ዘመኑን የመቅደስ ሸቃጭ ነጋዴ እየረገመ፣ የዚህን ዘመኑን እያየ እንዳላየ እየሰማ እንዳልሰማ ሆኖ ያሳልፋል። ይህንን አላዋቂነትም ከጥበብ ይቆጥረዋል።

ጅራፍ ኋላ ቢመጣ ትምህርቱ ቢቀድም ተገቢ ነው። በትምህርት ያልተገራ ልብ በጅራፍና በአለንጋ ይገራል ማለት ከባድ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “መቶ ግርፋት በሰነፍ ጠልቆ ከሚገባ ይልቅ ተግሣጽ በአስተዋይ ሰው ጠልቆ ወደ ልቡ ይገባል” ብሏል (መጽሐፈ ምሳሌ 17፥10)። ለጠቢብ ሰው አካላዊ ጉዳት ሳይሆን የምክር ክብደት የበለጠ ዋጋ አለው። ሰውን በኃይል ከማስገበር የበለጠ በጥበብ ማንበርከክ ረዥም ዘመን የሚዘልቅ ውጤት ያመጣል።

ክርስቶስ በቃሉ ተግሳጽ ብቻ ሳይወሰን ጅራፍ ማንሣቱ በተለይ በሃይማኖት ውስጥ ነን ለሚሉ ነገር ግን እጅግ የሚያከብሩት የሃይማኖትም ሆነ የአገር ሥፍራ መሸቀጫ ሲሆን ጅራፍ ማንሣትን ለሚኮንኑ ጥሩ አስተማሪ ነው። ለኢትዮጵያውያን አገራችን መቅደሳችን ናት። አያት ቅድመ አያቶቻችን ደማቸውን ስላፈሰሱላት ብቻ ሳይሆን ቀደምት የሃይማኖት መሪዎቻችን በጸሎታቸውና በተጋድሏቸው ስለባረኳትም ጭምር “ቅድስቲቱ አገራችን” እያልን እንጠራታለን። “እቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ /ወሃይማኖታ/ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ፤ አቤቱ ሕዝቧንና ሠራዊቷን/ ሃይማኖቷን” ጠብቅልን እያልን እንጸልያላታለን።

የቀደሙት አባቶችና እናቶች እንዲህ ብለው ለጸለዩላት አገር መከበር፣ ደማቸውን ከማፍሰስ እና አጥንታቸውን ከመከስከስ ወደ ኋላ አላሉም። በተግሳጽ የሞከሩት ጠላት ምክራቸውንና ተግሳጻቸውን ባይሰማ ጅራፋቸውን አንስተው ገርፈው አባርረውታል። ክርስቶስ ጌታችን መቅደሱን ከሸቃጮች በጅራፉ እንዳጸዳ እነርሱም ታቦታቸውን ይዘው ዘምተው፣ በጸሎታቸው አምላካቸውን ተማጽነው፣ በጦራቸው ጠላታቸውን ወግተው፣ ድንበራቸውን በአጥንታቸው አጥረው አገር አቆይተዋል።

ተግሳጽ ብቻ ለሚገባው ተግሳጽ ብቻ፣ ጅራፍ ለሚያሻው ደግሞ ጅራፍም ተግሳጽ ነው። እንደዚያ ያደረጉና በጸሎታቸው የተራዱ ብዙዎች ነበሩ። ደግሞ ግንባራቸውን ለጥይት፣ ደረታቸውን ለጦር ሰጥተው ገስጸው የሚያንቀጠቅጡ፣ ተዋግተው የሚያዋጉም ያስፈልጉ ኖሯል። ተግሳጽ ብቻ ቢሆን ኖሮ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከአንዱ ገዳም ገብተው በዓታቸውን ዘግተው በተሸሸጉ ነበር። ለዚህም ሰማዕትነትን በክብር ተቀብለዋል። “እንኳን ሕዝቡ ምድሪቱ እንኳን ለጠላት እንዳትገዛ” አውግዘው በክብር አርፈዋል።

ተግሳጽ ከመንፈስ እና ከዕውቀት ልዕልና ጋር የሚገኝ ነው። ዕውቀት በየትምህርት ማዕዱ ይገበያል። የመንፈስ ልዕልና ግን በቀላሉ አይገኝም። የተማረ ሁሉ የመንፈስ ልዕልና የለውም። ከፊደል ገበታ ሳይውሉ በምግባራቸው ግን ከስብዕና ማማ ላይ የቆሙ ብዙዎችን እናስታውሳለን። አንድ ምሳሌ እናንሣ። ባርነት የአገሪቱ ሕግ በነበረባት የ18/19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አሜሪካ በተፈጥሮ የመንፈስ ብርታቷ የተመሰገነች አንዲት “ባሪያ” ተገኘች። ይህች ሴት ባርነትን ተጸይፋ፣ ራሷን ነጻ ለማውጣት ከተሰደደች በኋላ በድብቅ እየተመላለሰች ብዙ ባሮችን ነጻነት ወዳለባቸው፣  ሥርዓተ ባርነት ወደፈረሰባቸው  የአሜሪካ ግዛቶች ታመላልስ ነበር።

ባሮችን ነጻ የማውጣቱን ይህንን ተግባር “Underground Railroad” ይሉት ነበር። ሐሪየት ቱብማን (1820-1913) የተባለችው ይህች ሴት፣ በተፈጥሮ ብሩኅ አዕምሮና አስተሳሰብ የነበራት፣ ሌሎችንም ለመምራት የመንፈስ ልዕልና የተጎናጸፈች ሴት ነበረች። እንዲህ አለች “በሺህ የሚቆጠሩ ባሮችን ነጻ አውጥቻለኹ። በባርነት ቀንበር ሥር የሚኖሩ መሆናቸውን የተረዱ ቢሆኑ ኖሮ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ባሮችንም ነጻ ማውጣት እችል ነበር።” ነገር ግን ቀድመው ራሳቸውን ነጻ ለማድረግ የተዘጋጁ አልነበሩምና ወይም ነጻ ለመውጣት ፈቃድ የላቸውምና ነጻ የሚያወጣቸውም ቢገኝ ለመቀበል ስለተጨገሩ የርሷን ርዳታ ሳይቀበሉ ቀርተዋል። ነጻነት ከውጪ አይገኝም፤ ከውስጥ የሚፈልቅ ነው። ያልፈለግነውን አናገኘውም።

እኛም በፈንታችን በባዕድ ከመገዛት ብንተርፍም በራሳችን-ባዕዳን ግን ለብዙ ዘመናት ተቀጥቅጠናል። ጋናዊው ደራሲ አርማህ ድኅረ ቅኝ ግዛት አፍሪካን ስለተቀራመቱት ጥቁር አምባገነኖች፣ ሲናገር “በጥቁር ቆዳ የመጡ ቅኝ ገዢ ነጮች/ "white man in black skin (?)” እንዳለው በሐበሻ ቆዳ በመጡ ገዢዎች መገዛት እጣ ፈንታችን ሆኗል። መገስጽ (የሚገስጽ አዋቂ ሰው) የሚያስፈልገን ለዚህ ነው።

ተግሳጽ የዕውቀት እና የመንፈስ ልዕልናን ይጠይቃል ብለናል። ጅራፍ ማንሣት ደግሞ ድፍረትና ወኔን ይሻል። የዕውቀትና የመንፈስ ልዕልና የሌለው ለመገሰጽ እንደማይበቃው ሁሉ ልቡን በጀግንነት ጥቡዕ ያላደረገውም ጅራፍ ካለበት ሊደርስ አይችልም። የዕውቀት ልዕልና አዋቂዎችን፣ አስተማሪዎችን፣ ሊቃውንትን፣ አገር ያፈራቸውን ባለ ሁለት ጸጉር … ቢናገሩ የሚሰሙ ሰዎችን ሁሉ ይመለከታል። ጅራፍ ማንሣት ደግሞ እንደ መቅደስ የሚያከብረው ሕይወቱ፣ ክብሩ፣ ማንነቱ፣ እኔነቱ፣ ታሪኩ፣ ባህሉ የተደፈረበትን ሰው ሁሉ ይመለከታል።

መገስጽ - አዋቂ - ሰው ቢናገር የማይሰማበት ዘመን አለ። አገር ጆሮዋን የምትደፍንበት ዘመን። አፍ እንጂ ጆሮ የማይኖርበት ዘመን። በድፍረት መናገር ብቻ ዕውቀት የሚሆንበት፣ ዝምታ ከድንቁርና የሚቆጠርበት ዘመን አለ። አዋቂዎች “ብንናገርስ ማን ይሰማናል?” የሚሉበት ዘመን። ለነቢዩ ሕዝቅኤል እንደተባለው “የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ” (3፡27) የሚባልበት ጊዜ አለ። እንደ እቴጌ ጣይቱ ተናግሬ የምሰማበት ዘመን አልፏል፤ አሁንም ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልህ ትሰማኛለህ ብዬ ሳይሆን “እግዚአብሔር ይወደዋል ብዬ ነው” የሚባልበት ጊዜም አለ። ተግሳጽ የማይሰሙ መቅደስ አርካሾች ሲበረቱ ምን አማራጭ አለ? ጅራፍ ማንሣት እንጂ።


ይቆየን፣ ያቆየን 


This article is published on Addis Guday Magazine. 

4 comments:

Anonymous said...

Welcome, Deacon Ephrem. It is good to read your articles again.

Anonymous said...

መገስጽ - አዋቂ - ሰው ቢናገር የማይሰማበት ዘመን አለ። አገር ጆሮዋን የምትደፍንበት ዘመን። አፍ እንጂ ጆሮ የማይኖርበት ዘመን። በድፍረት መናገር ብቻ ዕውቀት የሚሆንበት፣ ዝምታ ከድንቁርና የሚቆጠርበት ዘመን አለ። አዋቂዎች “ብንናገርስ ማን ይሰማናል?” የሚሉበት ዘመን። ለነቢዩ ሕዝቅኤል እንደተባለው “የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ” (3፡27) የሚባልበት ጊዜ አለ። እንደ እቴጌ ጣይቱ ተናግሬ የምሰማበት ዘመን አልፏል፤ አሁንም ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልህ ትሰማኛለህ ብዬ ሳይሆን “እግዚአብሔር ይወደዋል ብዬ ነው” የሚባልበት ጊዜም አለ። ተግሳጽ የማይሰሙ መቅደስ አርካሾች ሲበረቱ ምን አማራጭ አለ? ጅራፍ ማንሣት እንጂ።
You and yor freins are just like that

Anonymous said...

yehulet alem sew!

Anonymous said...

thanks for your brave articel but you didnt make clear what you really want to say?

"Wendime anten yemegeses alama yelengim gen hasabih gen gira yemiyasgeba new" malet kristnan bemenem yihun bemin "jiraf" mansat atstemrim.