Sunday, April 6, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን በፓርቲ ፖለቲካ የማይጠረጠርባቸው ምክንያቶች

 የግል ምልከታ
(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF)
ይህ ጽሑፍ የእኔን የግል ምልከታና አስተያየት ብቻ የሚመለከት እንጂ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰውን ማኅበርም ሆነ ከእርሱ ጋር የአገልግሎት ግንኙነት ያላቸውን ተቋማት የማይመለከት መሆኑን አበክሬ በመግለጽ ልጀምር።
አንድ ብሒል አለ። ውሸትን ደጋግመው ቢናገሩት እንደ እውነት የሚቀበለው ሰው መፍጠር ይቻላል። ስለዚህም ሐሰተኞች ሐሰታቸውን ሳያሰልሱ በተናገሩት መጠን፦ አንደኛ ራሳቸውንም በሐሰታቸው እውነትነት ያሳምናሉ፤ ብሎም ሌሎችን ማሳመን ይችላሉ። ደጋግሞ የመናገር ጥቅሙ ይኼው ነው።

አንዳንድ እውነት የያዙ ሰዎች ደግሞ “እውነት እስከያዝን ድረስ ደጋግሞ መናገር ለምን ይገባል?” ብለው ያቀርባሉ። እውነት አላቸው። ፀሐይ ሲወጣ ጨለማ መሸሹ፣ ሻማ ሲለኮስ ብርሃን መፈንጠቁ ላይቀር “ጨለማን ማውገዝ ምን ጥቅም አለው?” ይላሉ። ይህም እውነት ነው። “ጨለማን ደጋግሞ ከማውገዝ አንድ ሻማ ማብራት” እንደተባለው። ነገር ግን ሐሰት ተደጋግማ በመነገሯ ተከታይ መፍጠር እስከቻለች ድረስ እውነትን ደጋግሞ በመናገር የሚመጣ ምን ችግር አለ? ሻማውንም እየለኮሱ እውነቱንም ደጋግሞ መናገሩስ? ስለዚህ በእውነት ተደጋግሞ መነገር፣ በሻማ መለኮስም አምናለኹ። ደጊመ ቃል እንዲሉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት።
እንኳን አገር ቤት ያለው አንባቢ ይቅርና እኛ ከአገራችን በብዙ ሺህ ማይሎች ርቀን የምንገኘው ሳንቀር በየዕለቱ የምንኮመኩመው አዲሱ ትኩስ ዜና የማኅበረ ቅዱሳን እና “የተጠመደለት ወጥመድ” ጉዳይ ነው። በማኅበራዊ ድረ ገጾች እና በጡመራ መድረኮች፣ እንዲህ በሕትመት ውጤቶች በሰፊው ሽፋን ያገኘ ጉዳይ ሆኗል። ብዙ ኢትዮጵያውያን (እምነት ሳይለይ) ይህንን ጣልቃ ገብነት በጽኑዕ እየተቃወሙት እያወገዙት ነው። “ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪ የሚባል ከሆነ እኔም አክራሪነትን እወደዋለኹ” የሚሉ ሐሳቦች በብዛት ተጽፈው ተመልክቻለኹ።
“የአክራሪነቱ ነገር”፣ ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ በፓርላማ ተናግረውት በነበረ ጊዜ፣ እኔን ጨምሮ ብዙ ፀሐፍት አስተያየታቸውን የሰጡበት ከመሆኑ አንጻር ወደዚያ መመለስ አይገባ ይሆናል። ማኅበሩ ከፓርቲ ፖለቲካ ጋር ግንኙነት እንዳለው በመንግሥት ሰዎች እና በደጋፊዎቻቸው የሚነሣውን ሐሳብ በተመለከተ ግን የግል አስተያየቴን ላሰፍር እወዳለኹ።
ማኅበሩ ፖለቲካ ውስጥ አለበት? ለመሆኑ ፖለቲካ ውስጥ መግባት/ አለመግባት ምንድነው? ማንኛውም ሰው የተባለ ፍጡር ፖለቲካዊ አመለካከት አለው። ፖለቲካ አልወድም የሚሉ ሰዎች ራሳቸው እንኳን ፖለቲካዊ አቋም አላቸው። ልዩነቱ እያወቁ ማወቅ እና ሳያውቁ መኖር ናቸው። የተለያዩ ሐሳቦች እስካሉ ድረስ፣ አስተዳደሮች፣ ገዢዎችና ተገዢዎች እስካለን ድረስ ፖለቲካዊ አመለካከቶች መኖራቸው ግድ ይመስለኛል። “ፖለቲካ እና ኮረንቲ በሩቅ” የሚለው ሰው ራሱ በኮረንቲ ከመጠቀም፣ ሕይወቱ በፖለቲካ ተጽዕኖ ሥር መውደቁ እስካለ ድረስ ፖለቲካ የማይነካው ኢትዮጵያዊ አይኖርም።
ይኼ በፖለቲካ ምሁራን ሳይሆን እኔን በመሳሰሉ ለፖለቲካው ዕውቀት ተርታ በሆንን ሰዎች ቋንቋ “ፖለቲካ ውስጥ መግባት ወይም አለመግባት” የምንለው የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ማለታችን እንደሆነ ይሰማኛል። ፖለቲከኞች የምንላቸው እንደዚያ ያሉ ሰዎችን ነውና። ማኅበረ ቅዱሳን “ፖለቲካ ውስጥ ገባ/ አልገባም” የሚለውንም የምፈታው በዚሁ አንድምታውና አገባቡ ብቻ ነው።
ማኅበሩ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ አባላት አሉት። አባላቱ ሰዎች እንደመሆናቸው ፖለቲካዊ አመለካከት አላቸው። ማኅበሩን በአባልነት ለመቀላቀል የሚያበቃቸው ግን ይህ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው አይደለም። የአባላቱ የዓላማ አንድነትና መሠረቱ ማኅበሩ የሚያራምደው ቤተ ክርስቲያናዊ አቋም ብቻ ነው። በሃይማኖትና በአገልግሎት ዓላማ አንድ ናቸው እንጂ በፖለቲካ ርዕዮት የተሰባሰቡ አይደሉም። ሲጀመርስ ስለ ፖለቲካ አመለካከታቸው የት ተጠያይቀው? የት ተገማግመው? የት ተለካክተው? በየትኛው ጊዜ?
ስለዚህም ማኅበሩ አንድ ሃይማኖታዊ አቋም ያራምዳል እንጂ “አንድ ፖለቲካዊ አቋም” የሚባል የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ለምን? ምክንያቱም “ፖለቲካዊ አቋምን ለማራመድ” መጀመሪያ ፖለቲካዊ አቋም መያዝ ያስፈልገዋል። ያንን ለማድረግ ደግሞ አባላቱን በሙሉ በዚህ ፖለቲካዊ አቋም ማሳመን ያስፈልጋል፤ ያንን ማድረግ ደግሞ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ማኅበሩ የያዘውን ሃይማኖታዊ አቋም የሚጻረርና ማንም ሳይነካው እንዲፈርስ የሚያደርገው ድማሚት ነው።
እዚህ ላይ መነሣት ያለበት ቁምነገር፤ የማኅበሩ አባላት በሃይማኖታዊም ሆነ በፖለቲካዊ አስተሳሰባቸው ራሳቸውን የቻሉ (ማለትም ማመዛዘን የሚችሉ) ክርስቲያኖች እንጂ የአንድ ቡድን ጀሌዎች አለመሆናቸውን ነው። ራሱን የቻለ አስተሳሰብ ያለው ማንኛውም ሰው፣ አባል የሚሆንበትን ድርጅት ያያል፤ ይመዝናል፣ ያስባል። እንደማይጠቅመውና እንደማይስማማበት ከተረዳ ይተወዋል። ጀሌ ግን የተነገረውን ተቀብሎ እንደ በቀቀን ያስተጋባል፤ ሳያውቅ አባል ይሆናል፤ በጥቂት ጥቅም ይደለላል፣ የሚኖርለትም-የሚሞትለትም ቋሚ መርሕ አይኖረውም።
ማኅበረ ቅዱሳንን እና አባላቱን በአገራችን ላለፉት 40 ዓመታት በጠነነው የፖለቲካ ድርጅት ጀሌነት መገምገም ትክክል የማይሆነው ለዚህ ነው። አባላቱ አገልጋዮች እንጂ ካድሬዎች አይደሉም። አመራር ላይ የሚቀመጡት ሰዎች በተራቸው ለማገልገል እንጂ ከሌላው አባል የተለየ መርሕ ለማራመድ አይችሉም። እናራምድ ቢሉም አባላቱ ጀሌዎች ስላልሆኑ ሊከተሏቸው የሚችሉበት ምንም መንገድ አይኖርም። የአባላቱ አንድነት በሃይማኖት እና በሃይማኖት ብቻ ነው። በበሰለ ሚዛን የሚለካቸው ቢኖር ኖሮ በዘር፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አቋም፣ በትምህርት ደረጃ፣ በዕውቀት፣ በዕድሜ ወዘተ ወዘተ የተለያዩ እንጂ እንደ ሜዳ አህያ አንድ ወጥ እና ልሙጥ አለመሆናቸውን ይገነዘባል።
ስለዚህ አንድ አባል በግልጽ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብቶ የዜግነት ድርሻውን መወጣት ቢፈልግ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። በማኅበሩ ውስጥ ያለውን የአመራር ኃላፊነት ማስረከብ ይኖርበታል። በዚህ ደረጃ በይፋ ከአመራርነታቸው በሰላም ተሰናብተው ወደፈቀዱት ይፋዊ የፖለቲካ መስመር መጓዝ የቻሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ማኅበሩንም የፖለቲካ ድርጅታቸውንም መምራት የሚችሉበት መንገድ አይኖርም። እነርሱ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለማቸውን በማኅበሩ ላይ ለመጫን ቢፈልጉም እንኳን “የፍላጎት መላተም” ("conflict of interests") ስለሚኖር ሊሳካላቸው አይችልም። የማኅበሩ አባላት በፖለቲካ መሳተፍ የዜግነት መብታቸው ሲሆን በማኅበሩ አገልግሎት መሳተፍ ደግሞ ሃይማኖታዊ የትሩፋት ሥራ እንደመሆኑ ማቻቻል የአባሉ ፈንታ ነው።
ማኅበሩ በፖለቲካ ውስጥ ገብቷል የሚለው (በተለይ በቤተ ክህነቱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች) ከ1980ዎቹ ጀምሮ ሲያዜሙት የነበረ የሰለቸ ዜማ ነው። የሚነቅፉት ግን ማኅበሩ “ኢሕአዴግን አይደግፍም” ብለው ስላሰቡ እንጂ “ተቃዋሚ ነው ብለው ስላመኑ” ብቻ አይደለም። ለነገሩ እነዚህ መንግሥትን በዱላነት ለመጠቀም የሚፈልጉ፣ በመንፈሳዊም በዓለማዊም ሚዛን ቢመዘኑ ውኃ የማያነሱ ደመናዎች “ፖለቲካ” የሚሉት አጎብዳጅነትን ነው። መንግሥት እነሱን ይጠቀማል። እነሱም በአቅማቸው በመንግሥት ይጠቀማሉ።
ታዲያ ማኅበሩ የትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት እንደማይደግፍ ነገሩን ሥራዬ ብሎ ለሚከታተል ለማንኛውም ሰው ግልጽ ሆኖ ሳለ በዚህ ጉዳይ መወንጀሉ ለምን አስፈለገ? ክርስቶስ አምላካችን ራሱ “ግብር አትክፈሉ ይላል? ለቄሳር አትገዙ ብሏል፤ ንጉሣችን ሳይሆን ንጉሥ ነኝ ብሏል” የሚል ፖለቲካዊ ክስ እንደቀረበበት ሃይማኖትን ብለው የሃይማኖት አገልግሎት ላይ የተሠማሩ ሰዎች በየዘመኑ የሚከሰሱበት ጉዳይ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልገናል።
ቅዱስ ሉቃስ “ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም፦ እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር” ሲል እንደጻፈው (ሉቃስ 23፥2)። በሌላው ዓለም ያለውን እንኳን ትተን በአገራችን ያለውን ብናስታውስ፣ ነገር ሰሪዎች በየዘመኑ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችንን ከነገሥታቱ ጋር በማጋጨት በአደባባይ እስከመገረፍ ያደረሱበት ጊዜ፣ በግዞት በእስር እንዲማቅቁ ያደረጉበት ወቅት እንዳለ ታሪክ ያስተምረናል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን እና የደብረ ሊባኖስ እጬጌ ጻድቁ አባ ፊሊጶስን ለአብነት ብናንሣ አባ ጊዮርጊስ እንደተጋዘ፣ አባ ፊሊጶስ በአደባባይ ራቁቱን እንደተገረፈ እናነባለን።
ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ላይ ያለ ማኅበር ትናንት እንደፈላ እንደ ክረምት አግቢ ሊታይ አይችልም። መንግሥት ይኼ ሁሉ ሐቲት አይጠፋውም። ማኅበሩ ተቃዋሚም ደጋፊም እንዳይደለ መግለጹ እስካሁን ጉንጭ አልፋ ከመሆን አልዘለለም። መደገፍ የማይችል አካል፣ ባይቃወምም እንኳን ገለልተኛ መሆኑ ለአደጋ ያጋልጠናል በሚል “ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው” የዶሮ ፍልስፍና የተቃኘ ነው።
ከዚህም ባሻገር አባላቱ ከአንድ ዘርና ቋንቋ፣ ባህልና ፖለቲካዊ አቋም የመጡ አለመሆናቸው፤ ይልቁንም ሕብረ ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው እንቅልፍ የሚነሣቸው አካላት መኖራቸው ግልጽ ነው። “አዳሜ በየቅርጫትህ ግባ” ሲባል አንድ ቅርጫት ውስጥ የማይጨመሩ፣ ከሌላውም ቅርጫት ካለው ጋር ዝምድናና ፍቅር ያላቸው፤ ከቅርጫታቸው ውጪ የሚያስቡ ሰዎች ያሉበት ማኅበር መሆኑ የሚያስፈራቸው አሉ።
በውጪ አገር ባሉ የተለያዩ የመንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ሲጠረጠር እንደኖረ እነርሱም በፈንታቸው “ማኅበረ ቅዱሳን የኢሕአዴግ ደጋፊ መሆን አለበት” ሲሉ ኖረዋል። ለምን እንዲህ አላችሁ ሲባሉ ምክንያቱም “ይህንን የሚያህል ትልቅ ተቋም እንዴት ነጻና ፍፁም ሃይማኖታዊ ብቻ ሊሆን ይችላል? ጠርጥር ጠርጥር” የሚል ጥርጣሬ ያቀርባሉ።
ማኅበሩ አብሯቸው ጀብ ጀብ ላለማለቱ ምክንያቱ ዓላማውና ተፈጥሮው መሆኑን ለመቀበል የአገር ውስጡም የዳያስጶራውም ቡድን፣ እነዚያም እነዚያም ይኸው እንደተቸገሩ አሉ። እነዚያ “የዚያ ደጋፊ ነው” እንዳሉት፣ እነዚያም “የዚያ ደጋፊ ነው” እንዳሉት። ማኅበሩ ደግሞ “አነ ዘክርስቶስ፣ አነ ዘቤተ ክርስቲያን፤ እኔ የክርስቶስ ነኝ፣ እኔ የቤተ ክርስቲያን ነኝ” እንዳለ አለ። መጨረሻውን ደግሞ ዕድሜ ይስጠን እንጂ፣ እናየዋለን።
     
ይቆየን - ያቆየን 

 ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።

25 comments:

Anonymous said...

ከዚህም ባሻገር አባላቱ ከአንድ ዘርና ቋንቋ፣ ባህልና ፖለቲካዊ አቋም የመጡ አለመሆናቸው፤ ይልቁንም ሕብረ ብሔረሰባዊና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው እንቅልፍ የሚነሣቸው አካላት መኖራቸው ግልጽ ነው። በትክክል ይህ ነው ምክንያቱ እንጂ መንግሥትም ቢሆን ማህበሩ የትኛውንም ፖለቲካ እንደማይደግፍ አሳምሮ ያውቀዋል ዲያቆን እድሜውን ይስጥህ፡፡

Birhan Bihil said...

ሊበሉት የፈለጉትን አሞራ ጅግራ ነው ይሉታል፡፡ አሉ ሊቃውንቱ፡፡

በየዘመናቱ ....ጠላቶች የተለያየ ምክንያት ይደረድሩ ነበር የዘመኑ ምክንያት ደግሞ... አክራሪ፣ ፖለቲከኛ፣ ገለመሌ ገለመሌ.... ይበሉ እሳት ሲጭሯት ትቀጣጠላለች እንጂ አትጠፋም...
ማኀበረ ቅዱሳን ማለት በሺዎች የሚቶጠሩ በአገልግሎት ላይ የተሰማሩት የሚታዩት አባላት ብቻ ሳይሆኑ የማይታዩ የእግዚአብሔር ልጆች የቤተክርስቲያን ወዳጀች እንዲሁም የሀገር ፍቅር እና ክብር የሚያንገበግባቸው በማንነታቸው የሚኮሩ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ....መሆኑን ማን በነገራቸው...

ማኅበሩ እንደ ተቋም ፖሎቲካዊ ተልዕኮ ያራምዳል ነው እየተባለ ያለው! ማንም ሰው በግሉ የፈለገውን መደገፍና መቃወም ይችላል! ይህ ብቻም ኣይደለም የቤተ ክርስትያኒቱ የበላይ ኣካላት ትእዛዝና መመርያ ኣይቀበልም! ይህን የሚመሰክሩት የቤተ ክርስትያኒቱ የበላይ ኣካላት ናቸው! ስለዚህ ማኅበሩ እየተባለ ያለው ፖሎቲከኛ ነው ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስትያን ኣካል አይደለም ነው! ዳንኤል ክብረት እንደ ተናገረው ሌላ ስዉር ኣመራር ኣለ! ያ ስውር ኣመራር የፖሎቲካ ኃይል ነው ነው!

semenawi said...

Thank You Dn. Ephrem, Mk do not make happy both the government and those corrupted church officials. That is why all this trouble happens. But the fact is all the members of MK are devoted to their God and real church rules. So please let us do our work and our God be with us.

semagnasfaw said...

አንተ የዚህ ድርሰት ጸሐፊ እድሜና ጤና ይስጥህ!
የምንኖርት ጊዜ የዉሸት ዘመን /በተለይም በሀገራችን/፣ይህም አይገርመንም
ትንቢት አለ እኮ ምን አሱ ብቻ. ክህደቱስ፣የመነዋወጥ ጊዜ ይሏል ይህ ነወ፡፡
የእምነታች ሀላፊዎች፣የነፍሳችን ተጠያቂ ባለደራ አረኞች ተመረጠዉ ካዱ ማለት ነዉ;
ትንቢቱ ነዋ፡፡ ሆዳቸዉ አምላካቸዉ ሆነ ማለት ነዉ;አምላካቸዉን ለስንት ብር ሸጡት;
እግዚያሄርን ያገለገሉ መስለዉ ሆዳቸዉን የሚያገለገሉ፣የናታቸዉ እናታችንን ጡት እየጠቡ ሳይርባቸዉ
ጡት የሚነክሱ ምን ይባላሉ እናታቸዉን የሚያገለግሉ ደጋግ ወንድሞቻቸዉን ማሳደድ ምን ይባላል; እናትና አባትህን አክብር ያለ፣ሀይልን በክንዱ ያደረ፣በልባቸ አሳ የሚኮሩ ትእቢተኞችን የሚበታትን፤ባለጠጎችን ባዶ እጃቸዉን የሚሰድ፤የተራቡትን የሚመግብ እዉተኛ ዳኛ አለን ይፈርዳል፤ ይህም እዉነት ነዉ አይዞን ዎንድሞቸ ፡፡እናታችንማ ስትነከስ እየጮኸች ስቃዋን እያሰማች ነዉ ደጋግ ለጆቿም ወደ አዉነተኛዉ ዳኛ እያመለከቱ ፍርድን መጠበቅ፤ዳኛዉ የማያንቀላፋ እረኛዋ ነዉና ተኩላወችን/አዳኝ አዉሬዎችን/ አሳዳጆቿን ያሳድድላታል፡፡ እኛም በአሳዳጆቿ ሳንደናገጥ ከእቅፏ ሳንወጣ
አይዞሽ እማዬ እያልን መጽናት ግድ ይለናል፡፡ የጸና ይድናል አይደል ያለዉ; እዉነተኛዉ ዳኛ!!!
አባታችን ከማመን ከመታመን አይለየን
አሜን

አይይይ said...

ዘመናዊ ትምህርት መጀመርን ተከትሎ ጥቂት የጰነጠጡና ሁለት ምዕራፍ አንብበው መፈላሰፍ የጀመሩ ተማሪዎች የሚፈጥሩትን ውዥንብር ለመከላከል የተጀመረ መሰባሰብ ማኅበረ ቅዱሳንን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሃይማኖቶችም አቻ ተመሳሳይ/ተገዳዳሪ ማኅበራትን ስለፈጠረለት መንግስት በነዚያ ስብስቦች ፉክክር እንከዛሬ ደስተኛ ነበር። ከዚያ ውስጥ ግን መጅሊሳችንን እኛው እንምራ የሚል "የድምጻችን ይሰማን" እንቅስቃሴ ሲፈጥር መንግስት ኮሚቴዎቹን በማሰር የወጣቶቹን ጥያቄ የሚያበርደው ቢመስለውም አልተሳካም። ሁለት ተፎካካሪ ልጆች ኖረውህ አንዱን ቀጥቶት ማልቀሱን ካላቆመ ሌላኛውንም ይሄው ይህንንም ቀጣሁት ብሎ ዝም ለማሰኘት እንደሚሞክር ምስኪን አባት ኢህአዲግ ማኅበረ ቅዱሳንንም መግረፍ የፈለገች ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ ያን መከረኛ ዶክመንተሪ ቆብ አልብሳ የሾመቻቸውን መነኮሳትና ቁማሩ ያልገባቸውን የሌሎች ሃይማኖቶች መምህራን ምስክርነት እንደምታገኝ ግልጽ ነው። MK እንኳን ሲኖዶሳችንን ልቀቁልን ሊል ይቅርና ከራሱ አባላትም ውስጥ "በሚያስተዛዝብ የታሪክ ግምገማ “የቅንጅት ደጋፊዎች” የተባሉ አንዳንድ አገልጋዮች በውሃ ቀጠነ ፊት ተነሡ" ተብሎ ታምቷል። ይሄን አጋጣሚ የተቃዋሚ ፖለቲካ ደጋፊ እንዳልሆነ ከመናዘዝ ይልቅ ቤተክርስቲያኔን ስጡኝ፣ ላዘምናት፣ መዋቅሯን በሙስና ከላሸቁ ጎጠኞች ይልቅ የዓለምን Social Dynamism በተረዱ ለዘመኑ በሚመጥኑ ሰዎች እንድትመራ ላድርጋት እናቴን መልሱልኝ የርሷ በላቀ የሞራል ልዕናና ላይ መቀመጥ ለአጠቃላይ Social Justice ከፍተኛ ግብዓት ይሆናል ወደሚል እምቢ አብሬ አለቅሳለሁ ወደ ሚል እልህ መቀየር ያለብት ይመስለኛል።ኢህአዲግ በሃይማኖት ዙሪያ የተሰባሰበውን ሳይውቅ በስህተት እያወቀ በድፍረት ፖለቲካ ሃጢአት የሚመስለውን ካምፕ አፍርሳ ራሷም በነጋታው መፍረስ የምትፈልግ ገገማ አትመስለኝም።

Anonymous said...

እነኤፍሬም እሸቴ የሚዘሉዋቸው የማኅበረቅዱሳን ድክመቶች!!
1. እኛና እነሱ ዘይቤን መከተል!!
ቤተክህነት የሚለው ቃል በተለምዶ የሃይማኖቱን አስተዳደራዊ መዋቅር ይመለከታል፡፡መዋቅሩ የወረዳ፣የሀገረስብከት እና የጠቅላይ ቤተክህነት በሚል ይገለጻል፡፡ማኅበረቅዱሳን በጠቅላይ ቤተክህነት ስር ነው፡፡ስለዚህ ራሱም አንድ የቤተክህነት ክፍል ነው፡፡ስኬቱም ድክመቱም የቤተክህነቱ ስኬትና ውድቀት ነው፡፡ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንዳልሆነ ተደርጎ “እኛ” እና “እነሱ” አይነት ንግግሮችን እንሰማለን፣እናነባለን፣እንመለከታለን፡፡ስህተት ነው እላለሁ፡፡
2. የሚዲያ አጠቃቀም!!
መደበኛው የማኅበሩ ሚዲያ በቤተክርስቲያን ስላሉ ጠቅላላ ወቅታዊ ሁኔታዎች ከመዘገብ ይልቅ የማኅበሩን እንቅስቃሴ ብቻ ወደማስተዋወቅ ያደላል፡፡ስለሆነም ቤተክርስቲያኗ እንደተቋምና በአጥቢያ ደረጃ የምታደርጋቸው የልማትም ሆነ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡ እንዲያውቃው አይሰራም፡፡ይሄ ደግሞ ማኅበሩ ብቻውን ቤተክርስቲያኗን እንደተሸከመ ማስመሰል ነው፡፡የሰሞኑ ማኅበራዊ ሚዲያዎች “ማኅበረቅዱሳን ባይኖር ኖሮ ኦርቶዶክስ አልቆላት ነበር” የሚል ትምክህታዊ አስተያየትም ይሄው ሚዛናዊ ያልሆነ ሚዲያ የፈጠረው ነው፡፡እውነት ለመናገር ሚዲያው ከቤተክርስቲያን አገልጋይነት ወደ ማኅበር አገልጋይነት እየወረደ ነው፡፡ማኅበሩም ቀስ በቀስ ከአገልጋይነት ወደ ተገልጋይነት እየገሰገሰ ነው፡፡በተለይ በተለይ ያለፈው ወር የሐመር መጽሄት እትም ያስተዛዝባል፡፡ማኅበሩ ኢመደበኛ ሚዲያ አይጠቀምም ለማለትም የነደጀሰላም እና የነዕንቑ መጽሄት አቋም ያስቸግረኛል፡፡
3. ከበላይ አካላት አለመናበብ!!
ማኅበሩ ከተሃድሶዎች ጋር ባለው ግብግብ ችግር የለብኝም፡፡ነገር ግን የቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎችን፣ያልተወገዙ ሰባክያንና ዘማርያንን የሚያይበት መንገድ ከማእከላዊው የቤተክህነት አስተዳደር ጋር የተናበበ አይደለም፡፡ይልቁንስ ብዙ ጊዜ ተጻራሪ ሆኖ ነው የማየው፡፡ሶስት የሲኖዶስ ተወካይ ጳጳሳት ሐዋሳ ላይ እርቅ እያስፈጸሙ የማኅበሩ ድረገጽ “የወጡ ሰዎች እንዴት ነው የሚመለሱት” የሚል ሰዎቹ በውግዘት ባልተለዩበት እንደተለዩ የሚያስመስል ጽሁፍ ምንጩ አለመናበብ ነው፡፡ማእከላዊነትን አለመጠበቅ ነው፡፡
4. አባቶችን አለማስተዋወቅ!!
ጳጳሳት ካልሞቱ በቀር ስብከታቸውንም ሆነ ህይወታቸውን እንድናውቀው አይደረግም፡፡እንዲያውም ከአቡነ ጎርጎርዮስ በኋላ ጳጳስ ያልተሾመ እስኪመስለን ድረስ ስለ ሌሎቹ አይተረክም፡፡ለዚያ ይመስለኛል ትውልዱ ማንነትን እስከማጣት በሚያደርስ የዕጓለማውታነት ስሜት በግብጽ ኮፕት ቸርች ፍቅር እንዲወድቅ እየሆነ ያለው፡፡አባቶች ለአመታት በየሚዲያው በመሰረተ ቢስ ውንጀላ መዘባበቻ ሲሆኑ እያየ ማኅበሩ በመደበኛ ሚዲያው ድርጊቱን ሲኮንን አለመታየቱም ለስድቦቹ ድጋፍ የመስጠት ያህል ነው የሚሰማኝ፡፡የሚለካው ባደረገው ብቻ ሳይሆን ማድረግ እየተገባው ባላደረገውም ነውና፡፡

Anonymous said...

የኤፍሬም እሸቴ እርቃን ክሶች በቤተክህነት ላይ!!

1. ቤተክህነቱን የፖለቲከኞች ስብስብ ማስመሰል!!
ቤተክህነቱ እንደተቋም ያውም ሰፊ የአማኝ ቁጥርን እንደሚወከል የሃይማኖት ተቋም ከመንግስት ጋር የሚያገናኙ ብዙ ጉዳዮች እንደሚኖሩት ግልጽ ነው፡፡ግድም ነው፡፡ለእኔ ችግር የሚሆነው ቤተክህነቱ ይፋ በሆነ መንገድ የፓርቲን አቋም በተቋም ደረጃ የሚያራምዱና የቆሙለትን መንፈሳዊ ዓላማ ለፖለቲካ የዳረጉ አመራሮች ካሉ ነው፡፡እሱን አላየሁም፡፡እርግጥ ነው ብዙ ጓደኞቼ አስተዳደሩን በፖለቲከኝነት ሲከሱ እሰማለሁ፡፡ግን ከመስማት ባለፈ ያቀረቡት ማስረጃ ስለሌለ እንደመላ ምት ነው የማየው፡፡ምናልባት ይሄ ድምዳሜ መንግስታዊና ፓርቲያዊ እንቅስቃሴዎች ካለመለየት የመጣ እንዳይሆንም ስጋት አለኝ፡፡የትግራይ ተወላጅ ካህናትን ሁሉ ህወሀት ለማለት የማይመለሱት እነ ተመስገን ደሳለኝ የሚነዙት ፕሮፖጋንዳ ወስዶን እንዳይሆንም እፈራለሁ፡፡ለማንኛውም አስተያየቱን ማኅበረቅዱሳን የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲካ አራማጅ ነው በሚል እንደሚሰነዘረው አስተያየት ነው የማየው፡፡ሁለቱም ክስ ናቸው፡፡እዚህ ላይ ኤፍሬም እሸቴ የማኅበሩን አባላት ግላዊ አመለካከት ከአገልግሎታቸው ጋር እንደማይገናኝ ለማሳመን በሄደበት መንገድ ልክ ሳይሄድ ዘሎ ቤተክህነቱን የመንግስት መጠቀሚያ አስመስሎ መጻፉ ያሳዝናል፡፡ የማከብረውን ዳንኤል ክብረት ጨምሮ ብዙ ጊዜ ነባር አባላቱ ስማኅበረቅዱሳን ሲነሳ ነገሩን እንደመደብ ትግል ወስደው ማኅበሩን ለመከላለክል ብቻ ሲጽፉ ስለምታዘብ አይገርመኝም፡፡
2. መንግስት ላደረገብን እንጅ ላደረገልን እውቅና አለመስጠት!!
ይህ መንግስት በተለይ በሽግግሩ ወቅት እና በ19997ዓ.ም ሃይማኖቱን የውስን ብሄሮች አስመስሎ ያቀረበው ዲስኩር ያደረሰው ጉዳት የሚያሳምም ቢሆንም ዛሬ ያን ፕሮፖጋንዳ ጋብ አድርጎ መሬት ወርቅ በሆነባት አዲስ አበባ ላይ ሌሎች እንኳን ለመስሪያ ለመቀበሪያ በተቸገሩበት ጊዜ የያዝናቸውን ሰፋፊ ይዞታዎች እውቅና በመስጠት መጠነሰፊ ግንባታዎችን እንድናካሂድ ከመፍቀዱም በላይ ከተወረሱ ንብረቶች ውስጥ ቅድስት ስላሴ ኮሌጅን ጨምሮ ታላላቅ ህንጻዎችን መመለሱ በበጎ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡በገጠር በተለይ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የመሬት ምሪት ሲካሄድ ገዳማትና አድባራት እንዲመሩ ተደርጓል፡፡ታዲያ ቤተክርስቲያኗም ሀገራዊ በሆነ ጉዳይ ሁሉ ከመንገስት ጎን ለመቆም እንደማታንገራገር መታወቅ አለበት፡፡ቤተክህነት ቃል የገባቸውን የ22 ሚሊዮን የቦንድ ግዥ ለመፈጸም አልዋለችም አላደረችም፡፡ስለዚህ ስንናገር ስላደረግነውና ስለተደረገብን ብቻ ሳይሆን ስለተደረገልን ጭምር ካልሆነ “ኢትኩን ስምዐ በሐሰት” የሚለውን ህገኦሪት ጣስን ማለት ነው፡፡በዚህ ላይ ጳጳሳቱ በሃይማኖታቸው በደል የደረሰ ሲመስላቸው በጅማውና በአርሲው ጭፍጨፋ ወቅት እንዳደረጉት ቀጥታ ለጠ/ሚ/ሩ ደብዳቤ ከመጻፍ ጀምሮ “አታስቆጡን” እስከሚል ተግሳጽ-አዘል ዘለፋ በይፋ እንደሚሰነዘሩ መረሳት ለበትም፡፡ ከዚህ ውጭ አባቶቻችን እንደ አቡነ ሺኖዳ በመንግስት ስላልታሰሩ አባት አይደሉም ማለት ጦር አውርድ ባይ መሆን ነው፡፡ሙዋርትና መከራ መጥራት ነው፡፡ወዳለፍነው አስቀያሚ ዘመን መመለስ ነው፡፡እሱ አይሆንም፡፡በቃን፡፡የመጣውን ሁሉ በራሱ ቡድናዊ ሚዛን እየለካ ይሄ ለቤ/ክ ይበጃል ይሄ አይበጅም እያለ እድሜ ልክ አባቶቹን እየከሰሰ አያቶቹን የሚያወድስ ናፋቂ ትውልድ ከመፍጠር ዛሬን ከአባቶቹ ጋር ተስማምቶ ተቋሙን አክብሮ የሚያስከብር ትውልድ በማፍራት ላይ እንስራ፡፡በድሮው ቅኝት እንሂድ ካላችሁ ግን መንገዱን እናከብደዋለን፡፡ትናንት ዛሬ አይደለም፡፡ዳግም አባቶቻችን በልጆቻቸው እያዘኑ ወደ መቃብር እንዲወርዱ መፍቀድ ከባድ ይሆንብናል፡፡ ለምን ከመንግስት ጋር ዋልክ እያልን ውሎአቸውን ከማስተንተን ይልቅ በቅንነት እናግዛቸው፡፡

Anonymous said...

አዎ ማህበረ ቅዱሳን የክርስቶስ እና የቤተክርስቲያን እንጂ የተቃዋሚም የገዢው ፓርቲም ተላላኪ አይደለም ::

Teferi said...

ሰሚ ኖረም አልኖረም እውነት ብለሃል ዲ/ን ኤፍሬም

Anonymous said...

Girum ababale neeww! Never gen. Beand-ande belogoch yemitayu negeroch beteley degemo. Yemahiberu wana kehonu. Mahiberun liayasamaw yichelale!!! Bezih guday late enemies seat neberegne....bezu yetsafu negeroch seleneberu(D.Ephrem. yemilew yegebah yemeslegnal)

Anonymous said...

Great Point Dear Efrem. Please explain things as such. I agree 100% on the points stated and ready to die for my church.

Tile As said...

egziabher yisth yihn ewnet eko enersum yawkutal gn menager silemayidefiru new engi

Fantish said...

Kale Hiwot Yasemalen. Leb yalew leb yebel.

Anonymous said...

ኤፍሬም እሸቴ ራስህ ቅልጥ ያልክ ተቃዋሚ ነህ፡፡ ስለ ራስህ ብትጽፍ ይሻልህ ነበር፡፡ ስለ ማህበረ ቅዱሳን ከምትናገር፡፡ ማህበሩ እኮ የናንተ ስብስብ ነው፡፡ therefore ማቅ = ተቃዋሚ ቡድን፡፡

Anonymous said...

kale hiwot yasemalen bertuuuuu

Berhan Teklu said...

ፅሁፍህ በጣም በሳል በመሆኑ ምንም አይወጣለትም። አኔ ማለት የምፈልገው ግን አግዚአብሄር አምላክ በቸርነቱ ሃይማኖታችንን በመጠበቅ ላይ የሚገኙትን ወገኖች ሁሉ አንዲጠብቃቸውና አኛም በምንቸለው ሁሉ ማገዝ ከያንዳንዱ ሀገር ወዳድ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኘ የሚጠበቅ ክርስትያናዊ ግዴታ መሆኑን ነው።