Saturday, May 17, 2014

ብሶት የወለደን፣ ብሶት የምንወልድ

“የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ 
እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም።” (መጽሐፈ ምሳሌ 21፥13)
(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- እኛ እንዲህ ያለን ሕዝቦች ነን። “ብሶት የወለደው” የሚያስተዳድረን፣ ብሶት አርግዘን ብሶት የምንወልድ፣ በብሶት አገር የምንኖር ሕዝቦች። ብሶት የወለደን፤ አባት እናታችን ብሶቶች የሆኑ ሕዝቦች። ሰው ወላጁን መቀየር እንደማይቻለው፣ የብሶት ልጅ ብሶት እንጂ የብሶት ልጅ ደስታና ርካታ እንደማይሆነው ሁሉ እኛ ብሶቶችም ብሶትን አምጠን ብሶት እንወልዳለን። ብሶቶቻችን ከምሬትና መከፋት ጋር ይጋቡና እልቂት እና ውድመትን ያፈራሉ። ከብሶት አዙሪት ያልወጣ አገርና ሕዝብ ፍጻሜው ሳይታለም የተፈታ ነው።

Saturday, May 10, 2014

አርበኝነት እና አርበኞች

(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- “ኲሉ ጻድቅ በጊዜ ርቱዕ” እንዲሉ የአገራችን ሊቃውንት “በደግ ጊዜ ሁሉ ጻድቅ ነው”። በሰላም ጊዜ ሁሉ ጀግና ነው። በደግ ዘመን ሁሉ ሃይማኖተኛ ነው። በጥጋብ ዘመን ሁሉ ቸር ነው። በደስታ ዘመን ሁሉ ወዳጅ ነው። በጤና ዘመን ሁሉ ጓደኛ ነው። ጊዜ ሲገለበጥስ? ስለ እምነቱ ሰው መከራ በሚቀበልበት ዘመን ሰማዕት ለመሆን የሚፈቅደው ጥቂት ነው። በጦርነት ወቅት ጀግናው ትንሽ ነው። በረሀብ ዘመን አዛኝ ሰው ጥቂት ነው። በሐዘን ጊዜ ወዳጅ ማግኘት ከባድ ነው። ጤና ሲርቅ እና በሽታ ሲመጣ የሚደግፍና ቀና የሚያደርግ ማግኘት ከባድ ነው። ማዕበሉ ይዞህ ሲነጉድ እጁን የሚያቀብልህ ከየት ታገኛለህ?

Wednesday, May 7, 2014

ጉዱ ካሳ እና “ሰበነክ-ሊቃውንት”(ኤፍሬም እሸቴ/adebabay.com/ PDF)፦ እንግሊዛዊ ሆኖ “ሼኪስፒርን የማያውቅ፣ ሥራዎቹንም ያላነበበ፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሀዲስ ዓለማየሁን የማያውቅ ‘ፍቅር እስከ መቃብርን’ም ያላነበበ” ቢኖር እጅግ የሚደንቅ ይሆናል። እንዲያውም ጥያቄው ‘ስንት ጊዜ አነበብከው?’ እንጂ ‘አንብበኸዋል እንዴ?’ አይሆንም የሚል ግምት ነበረኝ። ከዕለታት በአንዱ ቀን በድሮ የትምህርት ቤት መጽሐፎቻችን ውስጥ ስላሉ ታሪካዊ ጽሑፎች ስናወጋ በመካከሉ አብዲሳ አጋን አስታወስን። “ስንተኛ ክፍል መጽሐፍ ውስጥ ነበር ጃል?” እያልን ስንጠያየቅ አጠገባችን የነበረ አዕምሮው ብሩህ የሆነ ልጅ እግር የዩኒቨርሲቲ መምህር “ማነው አብዲሳ አጋ?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። በመጀመሪያ እንደ ቀልድም ወሰድነው። ቀጥሎ እንደ መገረምም አደረገን። ከዚያ በኋላ ግን በርግጥ ሐሳብ ውስጥ ከተተን። “እንዴት ነው ነገሩ?” አሰኘን። በዚያ ሁሉ ብሩህ አዕምሮው ውስጥ አብዲሳ አጋን ሳያውቅ ያለፈበት አጋጣሚ ወይ ከእርሱ ስንፍና ነው ወይንስ ከመማሪያ መጽሐፉ ውስጥ አልነበረም? እየተባባልን መልካም ወግ ፈጠርን።

Saturday, May 3, 2014

“ከተራበ ይልቅ ለጠገበ አዝናለሁ”

(ኤፍሬም እሸቴ PDF):- “ችግርን አስችለኝ” ማለት አንድ ጸሎት ነው። “ጥጋብን አስችለኝ” ማለት ደግሞ እንዴት ያለ አዋቂነት ነው። የጠገበ ሰው የሚረገጠውን የማያውቅ ልበ ድፍን ይሆናል። የአንድ ወዳጄ አባት “ከተራበ ይል ለጠገበ አዘንኩ” ይሉ እንደነበር አጫውቶኛልአበው ካልጠገቡ አይዘሉ፤ ካልዘለሉ አይሰበሩ የሚሉት ብሒል አላቸው።

መጥገብ የሆድ መሙላት ብቻ ማን አደረገው። ዓለምን በመዳፍህ ያደረግኻት ሲመስልህ፣ ማን ይነካኛል፣ ማን ይነቀንቀኛል ስትል … ያ ነው ጥጋብ። የመንደር ጎረምሳ፣ ሰው አላስወጣ አላስገባ የሚል፣ ጉልበተኛ ውሻ ይመስል፤ ምን ይባላል እንዲህ ዓይነቱ ሰው? “ጥጋበኛ” ነዋ። እንዲህ ዓይነቱን ሰው በአቦ በላሴም ብሎ፣ አልያም “ውረድ እንውረድ” ተባብሎም መፍትሔ አይጠፋም። ወይም ጥጋበኛው በራሱ ዕድሜና ተሞክሮ ያሰክነዋል።ሥኢልጣንና ጥጋብ ሲዛመዱ፣ ሲዋደዱ ምን ይደረጋል።