Saturday, May 3, 2014

“ከተራበ ይልቅ ለጠገበ አዝናለሁ”

(ኤፍሬም እሸቴ PDF):- “ችግርን አስችለኝ” ማለት አንድ ጸሎት ነው። “ጥጋብን አስችለኝ” ማለት ደግሞ እንዴት ያለ አዋቂነት ነው። የጠገበ ሰው የሚረገጠውን የማያውቅ ልበ ድፍን ይሆናል። የአንድ ወዳጄ አባት “ከተራበ ይል ለጠገበ አዘንኩ” ይሉ እንደነበር አጫውቶኛልአበው ካልጠገቡ አይዘሉ፤ ካልዘለሉ አይሰበሩ የሚሉት ብሒል አላቸው።

መጥገብ የሆድ መሙላት ብቻ ማን አደረገው። ዓለምን በመዳፍህ ያደረግኻት ሲመስልህ፣ ማን ይነካኛል፣ ማን ይነቀንቀኛል ስትል … ያ ነው ጥጋብ። የመንደር ጎረምሳ፣ ሰው አላስወጣ አላስገባ የሚል፣ ጉልበተኛ ውሻ ይመስል፤ ምን ይባላል እንዲህ ዓይነቱ ሰው? “ጥጋበኛ” ነዋ። እንዲህ ዓይነቱን ሰው በአቦ በላሴም ብሎ፣ አልያም “ውረድ እንውረድ” ተባብሎም መፍትሔ አይጠፋም። ወይም ጥጋበኛው በራሱ ዕድሜና ተሞክሮ ያሰክነዋል።ሥኢልጣንና ጥጋብ ሲዛመዱ፣ ሲዋደዱ ምን ይደረጋል።


ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል። “በድሀ ሕዝብ ላይ የሚገዛ ክፉ መኰንን እንደሚያገሣ አንበሳ፣ እንደ ተራበ ድብ ነው።” (ምሳሌ 28፥15) ጥሎብኝ ከአውሬ ዘር እንደ ድብ የምፈራውም የምጠላውም የለኝም። አንበሳ ቢሆን ዛፍ ላይ ወጥቶ ወይም ወንዝ ገብቶ ይመለጣል። ድብ ግን ብትሮጥ ይሮጣል፣ ውኃ ውስጥ ብትገባ ይዋኛል፤ ዛፍ ላይ ብትንጠለጠል እሱም አንደኛ ነው። ለጉልበት ቢባል ማን ተስተካክሎት? መጽሐፉ ክፉና ዕቡይ መሪዎችን ከድብ ጋር ሲያመሳስላቸው እሱንም እነሱንም በጣም ፈራኋቸው።

የኛ አገር የየዘመኑ መንግሥታት ችግር መሸከም ይችላሉ እንጂ ጥጋብ አይችሉም። ጥቂት ዓመት ቆይተው ጥጋብ ደረታቸውን ያሳብጣቸዋል። ድሃውን ሕዝብ አጥንቱን ይግጡታል። በቀን ቅቤ እንዳያገኝ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በሕልሙም እንኳን ቅቤ እንዳይጠጣ ሕልሙን ይነጥቁታል። ንግግሩን ይፈራሉ። ዝምታውንም ይፈራሉ። ሲስቅ ይናደዳሉ፣ ሲያለቅስ ይበሳጫሉ። የጠገበ ሲመስላቸው በቀረጥ ወገቡን ይሰብሩታል። ተራብኩ ካለ እንዴት በእኛ ዘመን ተራብኩ ትላለህ ብለው ጀርባውን በጅራፋቸው ይገሸልጡታል።

ለአውራጃቸውና ለወንዛቸው ሰው አገሩን ሁሉ አከፋፍለው ሰጥተው መጥገብ ይሳናቸዋል። ከላይ ከላይ እያገሱ በደሃው ጥቂት ሀብት ይቀናሉ። ፀሐይ በእነርሱ ቸርነት የምትወጣ፣ ዝናም በእነርሱ ረድዔት የሚዘንም፣ ወንዞች በእነርሱ ችሎታ የሚፈስሱ፣ ነፋሳት በእነርሱ ጥበብ የሚንቀሳቀሱ ይመስላቸዋል። ጥጋብ ዓይን ያሳውራል። ሀፍረት እና ይሉኝታ ያሳጣል።

ኢሕአዴግ አሁን እንዲህ ባለ ጥጋብ ላይ ናት። አሁን ያለነውን ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆቻችንን እንደምትገዛ እርግጠኛ ናት። እንኳን አገር ውስጥ “ጨረቃም ላይ ብትሆን አታመልጠኝም” እንዳለው የፖሊስ አዛዥ በእግራቸው እርግጥ፣ በእጃቸው ጭብጥ አድርገው፤ እንደ ገል ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው መግዛታቸውን የጥበባቸውና የጥጋባቸው ዳርቻ አድርገውታል። ይሉኝታና ሐዘኔታ ተሟጥጦባቸዋል። እንኳን በአካል ያለ አደጋ፣ ገና ሊታሰብ የሚችለውን ማምከን እንደሚችሉ አምነዋል። ፊቱን ያጠቆረባቸውን፣ የዓይኑ ቀለም ያላማራቸውን በሙሉ …. ያስራሉ ይገርፋሉ። አገሪቱን የእነርሱ ብቻ የግል ንብረት እንደሆነች፣ ኢትዮጵያዊነትም በእነርሱ ማሕተም የሚታደል እንደሆነ አስበዋል። “ቆይ እዛች አገር ትገቧታላችሁ” ሲሉ የሰማኋቸው የኤምባሲ ሰዎች ምክንያታቸው ይህችው ጥጋብ አፍ መድረሷ መሆኑን አሁን ተረዳሁላቸው።

ከሰሞኑ ከብዕራቸው ውጪ ምንም ነገር በእጃቸው የሌለ ተስፈኛ ወጣት ጦማርያንን (ዞን 9) እና ሌሎች ጋዜጠኞችን እየሰበሰቡ ሲያስሩ፤ የአዲስ አበባን አዲስ ማስተር ፕላን የተቃወሙ የኦሮሞ ወጣቶችን በየዩኒቨርሲቲዎቻቸው መከራ ሲያበሉ ስመለከት የጥጋብ ማማ ላይ መውጣታቸውን ተገነዘብኩ። ከጥጋብ ተራራ ወዲያ ያለው ገደል ብቻ ነው። ንስሐ የማይገኝለት ውድቀት፣ ስብራት እና ሞት።

መቸም ጋዜጠኝነት “ወንጀል” የሆነበት አገር ነው ኢትዮጵያ። ሐሳብ እንደ ጦር የሚፈራበት። ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ እንዲታሰሩ ትእዛዝ የሰጡት ጥጋበኞች ከዚያ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት እርስ በርሳቸውም ይሁን ከፓርቲያቸው ቱባ ቱባ ሰዎች ጋር መነጋገራቸው አይቀረም። እርስበርሳቸው እንዲህ የተባባሉ አይመስላችሁም? አደንቁርህ እና አደንዝዘህ ለመግዛት በምትፈልግበት አገር በሁለት እግሩ የቆመ፣ በራሱ የሚያስብ፣ የሚያስበውን ደግሞ “ጎመን በጤናን” እያንጎራጎረ ዝም የማይል ወጣት ትንታግ ብዕረኛ ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? ታስረዋለህ!! ደበድበዋለህ፣ ወጣትነቱን እንዲጠላ፣ አገሩን እንዲጠየፍ፣ አዕምሮውን በመስኮት ወርወሮ በሆዱ እንዲያስብ ታደርገዋለህ። ሌላው፣ ሁለት ጠጉር ያበቀበለው ያለፈ ሥርዓት ናፋቂ ትምክህተኛ፣ ፀረ ሰላም  ቢቃወመ ግዴለም፣ በኛው ዘመን የሽንት ጨርቃቸውን የጣሉ ልጆች፣ የኑ ውኃ እየጠጡ፣ የኑ ስብከት እየሰሙ አድገው እንዴት እንዲህ ያለ ሐሳብ ሊያስቡ ቻሉ? እንዴትስ ያሰቡትን አደባባይ አውጥተው ለመተንፈስ በቁ። ስለዚህ መቀጣጫ ልናደርጋቸው ይገባል!!!! እሰር፣ ግረፍ፣ የታሰሩበትን ምክንያት ደግሞ ጽፈህ አዘጋጅ፤ ፈርጆቹ ሲንጫጩ ሰጣቸው፣ ‘አሸባሪዎች ናቸው’ በላቸው

የከተማ ፕላንን መቃወም ከመብት ጥያቄ አንጻር እጅግ በጣም ትንሹ ነው። በቀላል የአስተዳደር ውሳኔ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችል ነው። ግድያ፣ እስርና መከራ ማድረስ አያስፈልገውም። ጥጋበኞች ግን እንደዚያ አያስቡም። እንደመንደር ጎረምሳ “እንዴት ተደፈርን” በሚል መመሪያ ስለሚራመዱ። ደግሞም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው ደሃው ገበሬ ሲፈናቀል መሬቱ ለማን እንደሚሰጥ ሳይታለም የተፈታ ስለሆነ ተቃውሞው ያበሳጫቸዋል።

የናቡቴ ለምለም የወይን መሬት እንዳስጎመዠችው እንደ አክአብ፣ የደሃው ጥቂት ኩርማን መሬት ያሳሳቸው የዘመኑ ሰዎችና ዘመዶቻቸው በወታደር ጥይት የገበሬ ልጅ እየፈጁ ማረጋጋት ይፈልጋሉ። አክአብ ናቡቴን በሐሰተኛ ክስ፣ በሐሰተኛ ፍርድ ፊት አቁሞ ሞት እንዳስፈረደበትና በድንጋይ አስወግሮ እንዳስገደለውና መሬቱን እንደወሰደበት ሁሉ ገበሬውን አስገድዶ፣ ልጆቹን ገርፎ መሬቱን መውሰድ ይቻል ይሆናል። የጥጋብ ጥግ። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ገድለህ ወረስኸውን?’ …  … ‘ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል’ … ”። (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 20፡19)

በወዲህ ጋዜጠኛው፣ ጦማሪውና ተቃዋሚው ይታሠራል። በወዲያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪው፣ ገበሬው እና ሌላው ሕዝብ ይሰቃያል። ሁሉም ጥጋበኞቹን ፈርቶና ሰግቶ የሚኖር እንጂ የሚቃወማቸው አልነበረም። ሁሉም በየቤቱ እየሞተ ነው። ተራ በተራ መሞት። አንድ ላይ ድምጽን ማሰማት እንፈራለን። ለየብቻችን እንሞታለን። መከራው አልቀረልንም። መሞታችን ካልቀረ እየተናገርን እንሙት እንጂ።

በጠገብክ ጊዜ በሰዎች ላይ ያደረግኸውን … ያንኑ እንደምታገኝ አትጠራጠር። አስረህ ገርፈህ ከሆነ፣ ያስሩሃል ይገርፉሃል …. ገድለህ፣ ልጆቻቸውን ወላጅ አልባ አድርገህ ከሆነ፣ ባንተም ቤተሰብ ያቺው ትደርሳለች። የወጣቶቹን ተስፋ ገድለህ፣ ልጅነታቸውን አጨንግፈህ ከሆነ ሌላ አትጠብቅ። ታሪክ የሚነግረን ይኼንኑ ነው። ልበ አምላክ ዳዊት በርግጥ ተናግሮታል “ርኢክዎ ለኃጥእ፤ ዐብየ ወተለዐለ ከመ አርዘ ሊባኖስ፤ ወሶበ እገብእ ኃጣእክዎ። ኃጥእን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። ብመለስ ግን አጣሁት። ፈለግሁት፣ ቦታውንም አላገኘሁም።” (መዝሙር 36፡35)

ከተራበ ለጠገበ አዘንኩ!!! በእውነት።

ይቆየን - ያቆየን 

 ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።

2 comments:

Anonymous said...

They rule by fear. ..but for believers, God gives them the courage to speak the truth. That is the missing element in today's Christianity. Many play with words, but christianity is laying out the fact as crude as it is. Think about Abune Petros . that is the difference between real Christians in the past and many actor christians at present.

Anonymous said...

ዲ/ን ኤፍሬም፡
ስለ ኦሮሚያ ተማሪዎች ጥሩ ያልሆነ ነገር ትፅፋለህ ብዬ ፈርቼ ነበር (እንደሌሎቹ ፀሃፊዎች ማለት ነው)፡፡ ፅሁፍህ ሚዛናዊ ነው… እንደዚሁ ቀጥል