Saturday, May 10, 2014

አርበኝነት እና አርበኞች

(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- “ኲሉ ጻድቅ በጊዜ ርቱዕ” እንዲሉ የአገራችን ሊቃውንት “በደግ ጊዜ ሁሉ ጻድቅ ነው”። በሰላም ጊዜ ሁሉ ጀግና ነው። በደግ ዘመን ሁሉ ሃይማኖተኛ ነው። በጥጋብ ዘመን ሁሉ ቸር ነው። በደስታ ዘመን ሁሉ ወዳጅ ነው። በጤና ዘመን ሁሉ ጓደኛ ነው። ጊዜ ሲገለበጥስ? ስለ እምነቱ ሰው መከራ በሚቀበልበት ዘመን ሰማዕት ለመሆን የሚፈቅደው ጥቂት ነው። በጦርነት ወቅት ጀግናው ትንሽ ነው። በረሀብ ዘመን አዛኝ ሰው ጥቂት ነው። በሐዘን ጊዜ ወዳጅ ማግኘት ከባድ ነው። ጤና ሲርቅ እና በሽታ ሲመጣ የሚደግፍና ቀና የሚያደርግ ማግኘት ከባድ ነው። ማዕበሉ ይዞህ ሲነጉድ እጁን የሚያቀብልህ ከየት ታገኛለህ?

ማርክ ትዌይን እንዲህ አለ፦ “In the beginning of a change, the patriot is a scarce man, and brave, and hated and scorned. When his cause succeeds, the timid join him, for then it costs nothing to be a patriot” (Mark Twain) አፍታትቼ ስተረጉመው “በለውጥና በነውጥ ወቅት፣ አርበኛ ውድ ነው። አርበኛ ጀግና ነው። ግን ማንም አይወደውም። ሁሉም ፊቱን የሚቋጥርበት ሰው ነው። አርበኛው ያነገበው ዓላማ ሲሳካ ግን የጠሉት ሁሉ ይከቡታል፤ ከዚያ ወዲያማ አርበኛ መሆን ዋጋ ስለማያስከፍል ሁሉ አርበኛ ይወዳል፤ አርበኛ ይሆናል” እንደማለት ነው።
 አርበኝነት ጀግንነት ነውና አርበኞች በቀላሉ አይገኙም። ግንባራቸውን ለጥይት፣ ደረታቸውን ለጦር፣ ጀርባቸውን ለግርፋት ያዘጋጁ ሰዎች አርበኞች ናቸው። ነገር ግን እነርሱ በጥይት አረር ለሚመቱት፣ እነርሱ በጦር ለሚወጉትና ለሚገረፉት ሐሳባቸው ብቻ የሚያስፈራቸው ብዙዎች ናቸው። አርበኝነት በሐሳብ ደረጃ ቢወደድም በየዘመኑ የነበሩ አርበኞች ግን ይወደዱ ነበረ ማለት አይቻልም። አርበኛው የሚወደደው እርሱ የቆመለትና የሞተለት ዓላም ሲሳካ ብቻ ነው። ያን ጊዜ በከንፈር መጠጣ፣ በዘፈን ድርደራ፣ በመቃብር ሙሾ የሚያመሰግነው አያጣም። በቁሙ የገፋው ሲሞት ያነሣዋል።
አጼ ቴዎድሮስ እጅግ የተደነቀ ንጉሥ ነው። (ነገሥታት አጼ ዮሐንስ፣ ምኒልክ ወይም ኃ/ሥላሴ አንቱ ናቸው። ለምን ቴዎድሮስን ብቻ “አንተ” እንደምንል አላውቅም። ምናልባት ሞገደኛ ስለሆነ ይሆን ወይስ “የኮሶ ሻጭ ልጅ” የሚለውን ተቀብለነው? ለነገሩ እንኳንስ ቴዎድሮስን እግዜርንም አንተ ስለምንለው በፍቅር ትርጉሙ ወስጄዋለሁ።)
“መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፣
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ” እንበለው እንጂ መጀመሪያውኑ ብቻውን እንዲሞት ፈርደንበት ነበር። እንግሊዞቹን መርተን መቅደላ ተራራ ግርጌ ያደረስናቸው እኛው ነን። አገር ምድሩን ገዝተን (ዝ ይጠብቃል) ሰው እንዳይከተለው ያደረግን እኛው ነን። ሲሞት በዘፈን ያሞገስነውም እኛው ነን። “ወንድ ማን እንደ በላይ” እንበል እንጂ በላይ ዘለቀ መሐል ከተማ ሲሰቀል ማንም አልታደገውም።  
“ተሰቀለ ሲሉኝ ዝናሩ ነው ብዬ፣
ተሰቀለ ሲሉኝ ጠመንጃው ነው ብዬ፣
ለካስ በላይ ኖሯል ትልቁ ሰውዬ” ብለን አለቀስን። አበቃ። አምስት ዓመት በዱር በገደሉ የተንከራተቱ አርበኞች አገራቸውን ነጻ አወጡ። እሰየው። ባንዶቹም ይጸየፉት የነበረውን አርበኝነት አሞገሱ።
“ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፤
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ብለን አዜምን። አርበኞቹ ከነጻነት ማዕዱ ተገለሉ፣ የአብዮት ሰማይ እስኪደፋባቸው ድረስ ባንዳዎቹ ተሞገሱ። ድሮስ አርበኝነትን ማን ይጠላል፤ አርበኛን እንጂ። አርበኝነትን እያሞገስን፣ አርበኛውን እያገለልን፣ ለነጻነት የደማውን ትተን ስለ ነጻነት እንዘምራለን።
አርበኝነት የሚጠይቀው ውድ ዋጋ ሕይወትን መገበር ከሆነ ከጥንት እስከዛሬ ይህንን የፈጸሙ አሉ። ይብዛም ይነስም በአምስት ዓመቱ የጠላት ወረራ ወቅት የተዋደቁት ብቻ በጅምላ ስም “አርበኞች” ይባሉ እንጂ አርበኝነትና አርበኞች እንደየዘመኑና በየዘመኑ አሉ። የኢትዮጵያ ድንበር የታጠረው በአርበኛ አጥንት ነው። አገሪቱ “ዳሩ እሳት መሐሉ ገነት” ሆና ከኖረች እሳቱ በበላቸው ሰዎች ደምና አጥንት እንጂ በሌላ በምን ይሆናል።
ከአርበኝነት ሁሉ ዳሩ እሳት በተባለው የጦርነት አውድማ የሚውሉትን እንጂ መሐሉ ገነት በተባለው ሥፍራ የሚኖሩትን የየዘመናችንን አርበኞች ማስተዋል ችለን ይሆን? የሚከፍሉትን ዋጋስ ማን ይረዳላቸው? የአርበኛ ኑሮና ሕይወት ምኑ ይማርካል? ሕይወትን ለአደጋ ማጋለጥ፣ ከራስ አልፎ የራስ ወገንን ኑሮ ማናጋት። አምስት ዓመት በዱር በገል ከመዋጋት ከጣሊያኑ ጋር ወግኖ መኖር አለ አይደል? ዛሬስ ቢሆን ብረት ያነገበውን ተቃውሞ በማዕከላዊ እስር ቤት ከመንገላታት ገዳዩን ጻድቅ፣ ሌባውን ለጋስ፣ ቀጣፊ ውሸታሙን እውነተኛ አድርጎ በመናገር መኖር ይቻል የለ?
አርበኝነት ደስ ይላል። የአርበኛ ዕጣ ፈንታ ግን ያስፈራል። ባንዳነት ያሳፍራል ባንዳ መሆን እና የባንዳ ኑሮ ግን ያስጎመጃል። ባንዳው ራሱ ቢጠየቅ ባንዳነትን ያወግዛል። ባንዳ ለምን እንደሆነ ቢጠየቅን ግን ምክንያት አያጣለትም። “ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው” ከማለት ይልቅ “የንጉሡ ልብስ ያምራል” የሚለው ቢጠየቅ ውሸታምነትን ይኮንናል። ለመዋሸቱ ለራሱ ውሸት ግን ምክንያት አያጣለትም።
ታዲያ አርበኞችን ማን ይወዳል? መከራን ማን ይናፍቃል። በአርበኝነት ጀምረው በባንድነት የሚጨርሱ ሰዎችን ታሪክ ልብ ብለን ካስተዋልን ምክንያቱን እንረዳዋለን። ስለ መብት መከበር ይጮኹ የነበሩ ተገልብጠው ለመብት መከበር የሚጮኹትን የሚያስሩ ሲሆኑ አይተናል። ስለ ነጻነት በመጻፍ ጀምረው አሁን ነጻነትን የሚገፍፉትን ሰዎች የሚያሞካሹ ሰዎች እናውቃለን። እነዚህም ቢሆኑ ግን አርበኝነትን አይጠሉም አርበኛ ግን አይወዱም። በአርበኛው ውስጥ የራሳቸውን ባንዳነት ያያሉና።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኛ መሆን ወይም ከመንግሥት ተቃራኒ የሆነ ፖለቲካ የሚያራምድ ሰው መሆን አርበኝነት ይጠይቃል። መዘዙን እያየነው ነውና። ጋዜጠኛም ሆነ ፖለቲከኛ ባትሆን ነጻ ሰው መሆንም አርበኝነት ነው። ኅሊናን ዳኛ አድርጎ መኖር፤ ክፋትን መጥላት፣ ከመልካም ጋር መተባበር፣ ለደሃው ማዘን፣ አገርን መውደድ፣ ያልሰሩበትን ገንዘብ አለመፈለግ፣ ዘረኝነትን መጠየፍ አርበኝነት ነው። ባንዳነት በየዘመኑ አለ ካልን በዚህ ዘመን ያለው ባንድነት ከሚሞተው ሰው ይልቅ ለገዳዩ ማዘን፣ የአገዳደሉን ትክክለኛነት ለማሳመን ደፋ ቀና ማለት ነው። ገዳይማ ከሞተው ሰው ሕይወት ይልቅ ለመግደል ስለጠፋው ጥይት መቆርቆሩ የታወቀ ነው።
  በዚህ ዘመን ከአስኮ እስከ አሶሳ፣ ከደብረ ዘይት እስከ ሐሮማያ ድምጻቸውን የሚያሰሙ ልጆች አርበኝነት ያስገርመኛል። አንዲት ወረቀት በጻፉ እጃቸው በካቴና የሚታሰሩት ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የሚከፍሉት ዋጋ ልቤን ይገዛዋል። ብረት ካነገበው ደፋር ነኝ ባይ ይልቅ በፈገግታ አንገታቸውን ደፍተው በየፍርድ ቤቱ የሚቆሙት ሰዎች ጀግንነት ያስደንቀኛል። ሁለት ጸጉር አብቅሎ ገራፊዎችን ከሚያሰማራው ሽማግሌ ይልቅ ግርፋቱን ለሚታገሱት ወጣቶች ክብር አለኝ። በብዙ ወንጀል ከተበላሸ አረጋዊነት ይልቅ በንጽሕና የተጌጠ ወጣትነት ይማርከኛል። "ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቈጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ 'ባለ አእምሮ ነው' ይባላል።" (መጽሐፈ ምሳሌ 17፥28) እንዲል እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ ከሚሆኑ “አዋቂዎች” ይልቅ “ጆሮ ያለው ይስማ” እያሉ በበረሃ የሚጮሁ ሰዎች ያስደንቁኛል።
ይቆየን - ያቆየን 

 ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።

6 comments:

Anonymous said...

Yes..we want others to die for us. The utmost we might do is praising the Patriots while we are eating their fruits.

Anonymous said...

ኤፍሬም
ለጽሑፍህ አስተያየት ለመስጠት ያክል 9ኙ ጦማርያንና ጋዜጠኞ አስመልክተህ አርበኞች ናቸው ስትል ግርምት ፈጠረብኝ፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በሰብአዊ መብት ስም ከተጀቦኑ የውጭ ድርጅቶች ጋር በገንዘብና በሓሳብ ተስማምተው ሕዝቡን ለአመጽ ለማነሳሳት የሀገራችንን ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሥርዓትን በቀለም አብዮት ለመቦጫጨቅ ታጥቀው የተነሱ ድርጅቶች አንደ ፌስ ቡክ ያሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም ጥቂት የዲያስፖራ ጽንፈኞች ሁኔታውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመዘወር ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ ሕዝቡን ለማደናገርና ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት፡፡
የግብጽና የተላላኪው የኤርትራ መንግሥት ፍላጎት ሀገራችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ቋሚ ሽብር መፍጠር መሆኑ ቢታወቅም፣ አርቲክል 19 (ኢንፎርሜሽን የልማት ፖሊሲዎችና ክንዋኔዎቻቸው ገቢራዊ ይሆኑ ዘንድ ሚዲያና ዘመቻዎቹ በአብዝሃነትና በልዩነት አንዲሠሩ ለማረጋገጥ ይሠራል) ቢልም ሃቁ ግን ይህ አይደለም፡፡ ድርጅቱ በየቦታው የቀለም አብዮት በማስነሳት የእነ ዲታው ጆርጅ ሶሮስን የኒዮ ሊበራሊዝም ህልዩት ለማስፈጸም እንዲሁም አንድን ሀገር ለማጥቃት ሲል ለከፈለው ሁሉ የሚሰራ፣ ሴራ የሚጎነጉን ብሎም በተለያዩ ሀገራት ውስጥ ተላላኪዎችን በመፍጠር የቀለም አብዮት አየቀመረ በዴሞክራሲያዊ መንግሥት የተመረጠን መንግሥት ለመገልበጥ የተፈጠረ አክራሪ ኒዮ ሊበራል ኃይል መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በአጭሩ በበላበት የሚጨህ ውሻ ነው ልንለው እንችላለን፡፡
አርቲክል 19 በዩክሬይን የቀለም አብዮት የማቀጣጠል ተግባር ውስጥ ተዋናይ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ግን የቀለም አብዩት ሞዴል ዩክሬይን ውስጥ ገቢራዊ ሳይሆንና የተፈለገውን ለውጥ እንዳላመጣ ምናልባትም አክራሪ ኒዮ ሊበራሎች ትምህርት ያገኙበት ይመስለኛል፡፡ ዩክሬይን የቀለም አብዩት ሞዴል መሞቱን ለዓለም አሳይታለች፡፡
አርቲክል 19 እና መሰል አክራሪ ኒዮ ሊበራሎች እንደሚሉት ሀገራችን ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ስለሌለ ይሆን ጦማሪዎቹና የግል ጋዜጠኞቹ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት? በአገራችን ከ36 በላይ መጽሔቶችና ጋዜጦች ለሕትመን የሚበቁበት፣ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች የባጥ የቆጡን የሚለፍፉባቸው መጽሐፎች ያለ ከልካይ እየታተሙ ለሕዝብ የሚሠራጩበት፣ በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች በሰላማዊ ሠልፍ የፈለጉትን የሚናገሩበት ምህዳር መኖሩ የአደባባይ ምስጢር ስለሆነ ነው፡፡ አሁን አንተ የምትጽፋቸው ጽሑፎች ሁሉ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት እንደሚወጣው ማለት ነው፡፡ የፋክቱ ጽንፈኛው ተመስገን ከሀገሪቱ ሕግ ጋር የሚቃረኑ አመጽ ቀስቃሽ ጽሑፎች ይስተናገዳሉ፡፡ በአንድ ወቅት “ኢህአፓዎች አስቸገሩን፡፡ ምን እናድርግ? ተብለው በመንግሥቱ ኃ/ማርያም ምክር ተጠይቀው፣ “እኛን ምን አድርጉ ትሉናላችሁ መሣሪያው ያለው አናንተ ጋር አይደለም እንዴ?” በሚል “በለው” በሚል ሰቅጣጭ ምላሽ የሰጡት መስፍን ወልደ ማርያም እንኳን ሳይቀሩ፤ አሁን በስተርጅና የሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል ከሚጽፏቸው አናቁሬ ጽሑፎች ባሻገር የተለያዩ ነውጥን ያነገቡ መጽሐፎችን በገሃድ እየቸበቸቡ ያሉባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡
የኛ ፕሬስ ዓይነት ጋዜጦች፣ አፍሮ ታይመሶች የሚስተናገዱባት አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ እናም እንዲህ ዓይነቶቹ ከሀገራችን ሕጎች ጋር የሚቃረኑ ተግባራት በሚዲያ ስም በሚፈጽሙባት ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ፤ ጦማሪዎቹና የግል ጋዜጠኞቹ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ለእስር ተዳርገዋል የሚለው መራር ቀልድ የሚያስቅ አይደለም - የሚያሳዝንና የሚያስተዛዝብ እንጂ፡፡ ደግሞስ ለምን ተግባራቸውን በሕቡዕ መከወን ፈለጉ? ለምን በጨለማ ውስጥ መሸሸግን ፈለጉ? ለምንስ ብርሃንን ለማየት ፈሩ? ምክንያቱም ተጠርጣሪዎቹ “የጨለማው ዘማሪዎች” በታሠሩበት ማግስት የሰማሁትንና ግለሰቦቹ በሕቡእ በመደራጀት ሀገራችን ውስጥ የቀለም አብዮትን ያለ ቦታው ለመፍጠር ከሚታትረው አርቲክል 19 እና መሰሎቹ ጋር የሓሳብ ጋብቻ ፈጥረዋል፤ ከኤርትራና ከግብጽ መንግሥታትም ገንዘብ ተቀብለዋል፡፡ ለነገሩ ተግባራቸው ሕገ ወጥ ፣ ሕዝብና ሀገርን የሚጎዳ በተለይም የግብጽ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነው የኤርትራን መንግሥት ፀረ ኢትዮጵየ የትርምስ አጀንዳን የያዘ መሆኑን ስለሚያውቁ ድርጊታቸውን ከብርሃን ሰውረው እንደ ጅብ በጨለማ መከወናቸው አሳምረው ስለሚያውቁት መደበቃቸው አይገርምም፡፡
አሳፋሪው ነገር ትናንት “አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ እናደርጋታለን” ያለውን የሻዕቢያ ሕልም ለማሳካትና የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት ቁጭት የሆነውን የ”አይቻልምን” መንፈስ የሰበረውን የታላቁን የሕዳሴ ግድብ በሁከት እንዲቋረጥ ባንዳ ሆኖ መሰለፍ ነው፡፡ ማንኛውም ዜጋ በእነርሱ ቦታ ሆኖ ማፈሩ አይቀርም፡፡ ባንዳነት ሀገራችን ውስጥ “ወንዜነት” የሌለው ሀገርን አሳልፎ የመስጠት አሳፋሪ እሳቤ ነውና፡፡
እርግጥም ለገንዘብ ሲባል አዲስ አበባን የዩክሬይኗ ኪዮቭ ለማድረግ ከእነ አርቲክል 19፣ ከኤርትራና ከግብጽ ጋር ሀገርን ሸጦ መሞዳሞድ ታሪክ ይቅር የማይለው ሐጢያት ነው፡፡ ማንኛውም ዜጋ በቀለም አብዮት እስካሁን ድረስ ፍዳዋን እያየች ያለችውን ዩክሬይንን ዕጣ ፈንታ የሀገራችን ሕዝብ እንደገጥመው የሚሻ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ያቺ ሀገር በቀለም አብዮት ቋያ እሳት ዛሬም ድረስ እየተለበለበት ስትሆን ወላፈኑን ደግሞ እንደ አርቲክል 19 ያሉ አክሪሪ ኒዮ ሉበራሎች በርቀት እየሞቁት ስለሆነ ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ግን የእነዚህን የጽንፈኛ ኒዮ ሊበራሎችንና የኢትዮጵያ ጠላቶችን እኩይ ምክባር ለሽራፊ ሳንቲም ሲል አንግቦ የሐዝቡን ሰላም ለመሸጥ የሚቋምጥ ወገን ሕሊናው የታወረ ባንዳ ነው፡፡ እናም ዜጋውን ለገንዘብ ሲል ለሕልፈት ለመዳረግ ጨለማ ውስጥ ሆኖ በአደባባይ የሚቆምር ኢትዮጵያዊ እርሱ የመጽሐፍ ቅዱስን የነብር ዥንጉርጉርነት የማይቀየርበትን ተምሳሌትነት የሻረ ነውና ከእኛ እንደ አንዱ ሊሆን አይችልም፡፡

Anonymous said...

ከዚህ በላይ ያለውን አስተያየት የጻፉትን (ለጽሑፍህ አስተያየት ለመስጠት ያክል 9ኙ ጦማርያንና ጋዜጠኞች ...ብለው የጀመሩትን) “ባንዳ” አእምሮ ማንበብ አማረኝ። እኝህ ሰው እውነታውን ያለመረዳት ችግር እንደሌለባቸው የጽሑፋቸው ፍሰት ራሱ ያሳብቃል። መሠረታዊ ችግራቸው የሚመስለኝ እውነትን መፍራት፣ ወይም እርሳቸውን በብቸኝነት የሚያስጨንቃቸው የዘውግ ወገንተኛነት ነቀርሳ ሰለባ ሆነውም ይሆናል። ይህን ጽሑፍ “ተቀጥረው”ም እየጻፉት ሊሆን ይችላል። በየዋህነት ወይም በሀገር ወዳድነት መንፈስ የተጻፈ ያለመሆኑን ግነ ለመረዳት እርሳቸው የዘረዘሯቸውን እውነታዎች ማንበብ ይበቃል። ግለሰቡ የዘረዘሯቸው የፀሐዩ መንግሥታችን “መልካም ምግባራት” መሬት ላይ የሌሉ የማደናገሪያ ሃሳቦች መሆናቸውን እኝሁ አስተያየት ሰጪ እንደሚያውቁት መገመት አያዳግትም።

በሀገራችን ለዘመናት የዘለቀ የጨቋኝና አምባገነን መንግሥታት (የሁሉም) አንድ አስቂኝ ፎርሙላ አለች- የተወሰነውን የማኅበረሰብ ክፍል የምንገድለው፣ የምናሥረው፣ የምናሰድደው “ለሕዝቡ” ብለን ነው የምትል። እኛ “ሕዝቦቻችሁ” እነዚህን ሕገ ወጥ ተግባራት እንድትፈጽሙ “አልቀጠርናችሁም” እያልን መሆኑን የሚረዳ ህሊና የሌለው መንግሥታችን እና “የሰው ልጆች ሰብአዊ መብት ሊገፈፍ አይገባም” የሚለውን የነጻነት ድምጽ በጥይት ሐረር ጸጥ ለማሰኘት እየሞከረ ካለው መንግሥት ጎን ተሰልፈው በብእራቸው ጫፍ/በኪፖርዳቸው ቁልፍ የነጻነትን ጩኀት ለማፈን የሚሞክሩትን እንደዚህ አስተያየት ሰጭ ያሉ “ምሁራን -ባንዳዎችን” በኤፍሬም ጽሑፍ ላይ እንደተጠቀሰው በየዘመኑ እናገኛቸዋለን። ስለሆነም እርስዎ ከነዚያ አንዱ እንጂ የመጀመሪያም የመጨረሻም ስላልሆኑ አይገርምም። የሚያሳዝነው ግን ይህ የሚፈሩትና ወገኖችዎን በግፍና የመግደልና የማሠር ስልጣን እንዳለው የሚመሰክሩለት ሥርዓት ሲወድቅ (መቼስ ለዘመናት እንደማይቀጥል ልብዎ ያውቀዋል)ተመልሰው ዛሬ ስለነጻነት ስለጻፉና ስላስተማሩ ብቻ የሀገርን ክብር በማያውቁና የታሪክን እውነታ ጨልጠው በካዱ የዘረኞች ስብስብ (በመንግሥት ስም) በጭለማ እሥር ቤት የሚያንገላቷቸውን እነዚያን ወጣት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እና ስለእነርሱ የተቻላቸውን ያህል ለመተንፈስ የሚሞክሩትን እንደ ኤፍሬም ያሉትን “አርበኞች” ሲያሞግሱ እንደሚገኙ አልጠራጠረም። እንኳንስ ነገ ከነገ ወዲያ ዛሬም ቢሆን ነፍስዎ በጸሐፊው የተነሱትን እወነታዎች ለመቀበል እንዲችሉ “ሹክ” እያለችዎት ይመስለኛል። አውቀው ያደርጉታልና ከጥፋት ይመለሱ ማለት የቂል ምክር ይሆናል።

Anonymous said...

ለAnonymous May 13, 2014 at 12:54 PM “አለማወቅ ደጉ” አለ የአገሬ ሰው፡፡ በጎ አስተሳሰብ እንዳለህ ከጽሑፍህ መረዳት ችያለው፡፡ ነገር ግን ችግሩ በቂ የሆነ እውቀት የለህም፡፡ በጽሞና ካነበብከው ድንግርታህን ያበራልሃል፡፡ አርቲክል 19 በሌላው ሀገር ውስጥ እንደሚያካሂደው ሁሉ፤ ሀገራችንም ውስጥ በማህበራዊ ሚዲየዎች ህዝቡን በመረጃ ለማደናገር በቅድሚያ ያከናወነው ድርጊት የግል “ጋዜጠኞችን” በተለይም በመንግሥት ላይ ጥላቻ ያላቸውን በማስጠናት ለሥልጠና ወደ ናይሮቢ መጥራት ነበር፡፡ እኔ እንደሰማሁት በአሁኑ ወቅት እውቅና የሌለውና በአስገራሚ ሁኔታ “መንግሥት እውቅና ካልሰጠኝ እንደ ሕጋዊ አካል ራሴን ቆጥሬ ሥራዬን እቀጥላለሁ” በማለት ከወዲሁ ሕገወጥነትን የሚያቀነቅነው፣ የተላከበትን የጉዳይ አስፈጻሚነት ተልዕኮን ለማሳካት ደፋ ቀና የሚለውና ራሱን የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ /ኢጋመ/ እያለ የሚጠራው ስብስብ የቀለም አብዮት አበጣባጭነት ቁርባን ወስዶ ተመልሷል፡፡ ከመሰንበቻው በፖሊስ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት 9 ግለሰቦችም በድብቅ በየሆቴሉ ውስጥ በአርቲክል 19 በድብቅ ሥልጠና ሲሰጣቸው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡
ይህን እውነታ ሚዛን እንዲደፋ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ አንድ የአርቲክል 19 አባል ወደ ሀገራችን በመምጣት እነዚሁን ጦማሪዎችና የግል “ጋዜጠኞች” እንዲሁም እውቅና አልቦውን “ማህበር” ስብስብን “ለማሰልጠን ነው” በሚል ሽፋን የተለያዩ ዶክመንቶችን ይዘው ሲገቡ በፀጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኃላ፣ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አንዲመለሱ የመደረጋቸው ትዕይንት ነው፡፡ የተቋሙ ተመራማሪ መሆናቸውን የሚናገሩት ኬንያዊ ፓትሪክ ሙታይ ምንም እንኳን ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ምክንያት “ለሁለት ቀናት በደብረዘይት ከተማ ይካሄድ ለነበረ ሥልጠና ለመስጠት ነው” በማለት ቢናገሩም፤ ሰውዬው ሆኑ ሥልጠና የሚሰጣቸው አካላት ምንም ዓይነት ፈቃድና ሕጋዊ እውቅና የሌላቸው ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እጅግ አስቂኙ ነገር ሰውዬው “ለሥልጠናው” ይዘውት የመጡት ዶክመንቶች ናቸው፡፡ ከዶክመንቶቹ ውስጥም ሁሉም ማለት ይቻላል ስለ “Safety & Security’’ /ጥንቃቄና ደህንነት/ የሚያትቱ ናቸው፡፡
እርግጥ “የጥንቃቄና ደህንነት ሥልጠና እኛ ሀገር ውስጥ ምን ይሠራል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለምን ቢሉ፤ ሀገራችን ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ያለ በመሆኑ ነው፡፡ እናም ስልጠናው መሰጠት ያለበት አልሸባብ በተቆጣጠራቸው ሰላም አልባ ጥቂት ቦታዎች አሊያም አፍጋኒስታን ወይም ኢራቅ ውስጥ እንጂ እኛ ሀገር ሊሆን አይደለም ጋዜጠኞች ሙትና ቁስለኛ እየሆኑ ካሉባቸው ሀገራት ውስጥ የሚመደቡት ናቸውና፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሀገራት ውስጥ ለሚሰሩ ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች የጥንቃቄ ደህንነት ሥልጠና መስጠቱ አግባብነት አለው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አርቲክል 19 በትክክል ለጋዜጠኞች መብት የቆመ ቢሆን ኖሮ እኛ አገር መሰጠት ያለበት ሥልጠና “Peace Journalism” “የሰላም ጋዜጠኝነት” መሆን በተገባው ነበር፡፡ እናም በሌለ ነባራዊ ሁኔታ የጥንቃቄና ደህንነት ሥልጠናን በግድ ጎትቶ ወደ እኛ አገር ለማምጣት መሞከር “አያ ጅቦ ሳታማሃኝ ብላኝ” ማለት ከመሆን የዘለለ ምንም ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡
ዳሩ ግን በእኔ እምነት አርቲክል 19 ይህን ሥልጠና ለመስጠት የፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ ይኸውም ተቋሙ በተሳሳተ ስልት የቀጠራቸው ተጠርጣሪ ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች እንዲሁም እውቅና አልባው የጽንፈኛ ጋዜጠኞች ስብስብ እንዲያከናውኑ የሰጣቸው ተግባር ሕገ ወጥና ሕዝብን ለብጥብጥ የሚዳርግ መሆኑን ስለሚያውቅ ለእነርሱ ሽፋን ማበጀቱ ነው፡፡ ካለው የቀለም አብዮተኝነት ብሎም በጎዳና ላይ ነውጥ ንፁሃንን አስገዳይነት ልምዱና ተሞክሮው በመነሳት አስቀድሞ የመከላከል ስልት መዘየዱ ነው ሊባልም ይችላል፡፡ ይሁንና የሕግ የበላይነት በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ጋዜጠኛም ይሁን ዜመኛ፣ ተኳሽም ይሁን ቀዳሽ፣ ጦማሪም ይሁን ዘማሪ . . . ሁሉም ዜጋ ህግና ሥርዓትን አክብረው ሊሠሩ የግድ እንደሚላቸው ድርጅቱ ሊያውቅ ይገባል በየትኛውም ሀገር የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሁለት እግሩ ቆሞ እየፈካና እያበበ ሊሄድ የሚችለው የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ ነውና፡፡
እናም ተቋሙ ያሰበው የብጥብጥ ሴራና ኃላ ላይም ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ለማዳን ያለመበት “የጥንቃቅና ደህንነት ሥልጠና” በምድረ በዳ ላይ እንደተዘራ ዘር መቁጠር ይኖርበታል ባይ ነኝ፤ እያንኳኳ ያለው የተሳሳተን በር ነውና፡፡ የተሳሳተ በርን የሚያንኳኳ ማንኛውም ግለሰብ ይሁን ቡድን ደግሞ ዘው ብሎ የሚገባው የሌላ ሰው ቤት በመሆኑ፤ ቢያንስ በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ በሚፈተፍተው ጣልቃ ገብነቱ ሊያፍር ከፍ ሲልም “በኢትዮጵያ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት 9 ጦማሪዎችና የግል ጋዜጠኞች ሃሳባቸውን በነጻነት ስለገለፁ የታሠሩ በመሆናቸው በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን” ከሚለው የቁራ ጩኸቱ ሊታቀብ ይገባል፡፡ ምክንያቱም እንደ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ የሚጮህበት የአክራሪ ኒዮ ሊበራሎች የከሸፈ ስልት “የተበላ እቁብ” መሆኑን ማንኛውም ዜጋ በቀላሉ ይገነዘበዋል፡፡

Anonymous said...

Do not pretend as if you know Geez.
Mehayim

Anonymous said...

We do well only when our neighbors or ordinary people do well. We feel secure, not from firearms or soldiers surrounding us, but from respect or trust we get from ordinary people. No person in authority will be secure until the people feel secure in their country. No matter how rich you are, no matter how armed you are, you cannot send your children to school or playground safely unless you create an environment (country) safe to live in. It may seem that you may skip these dangers temporarily, but this will not last long. Either you personally and or your closest relatives or your kids will pay for it. In simple terms, thinking about your country means working for the bright future of your own kids.
those who benefit from the existing government may want the status quo continue because they have a lot to lose. But, what the ordinary poor people lose from the situation where they are forced to live below human standards, seeing their rights violated daily? The answer is nothing. That is when revolution comes when the majority get pushed to the edge. No one can stop this.you may manipulate few around kebele by providing some benefits, but you don't have the resources to do these for millions. That's why things may only be delayed, but cannot be avoided. So, act before it is too late. Not for others, but for the sake of your kids because they deserve safe and peaceful environment to live.