Saturday, May 17, 2014

ብሶት የወለደን፣ ብሶት የምንወልድ

“የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ 
እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም።” (መጽሐፈ ምሳሌ 21፥13)
(ኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- እኛ እንዲህ ያለን ሕዝቦች ነን። “ብሶት የወለደው” የሚያስተዳድረን፣ ብሶት አርግዘን ብሶት የምንወልድ፣ በብሶት አገር የምንኖር ሕዝቦች። ብሶት የወለደን፤ አባት እናታችን ብሶቶች የሆኑ ሕዝቦች። ሰው ወላጁን መቀየር እንደማይቻለው፣ የብሶት ልጅ ብሶት እንጂ የብሶት ልጅ ደስታና ርካታ እንደማይሆነው ሁሉ እኛ ብሶቶችም ብሶትን አምጠን ብሶት እንወልዳለን። ብሶቶቻችን ከምሬትና መከፋት ጋር ይጋቡና እልቂት እና ውድመትን ያፈራሉ። ከብሶት አዙሪት ያልወጣ አገርና ሕዝብ ፍጻሜው ሳይታለም የተፈታ ነው።

ግንቦት 1983 ዓ፣ም ሐዋሳ ከተማ በእግሬ እየተጓዝኩ፣ ከአንድ ሱቅ በትልቁ በተለቀቀ ሬዲዮ የሰማኹት የዚያ ተጋዳላይ ድምጽ እና ያቺ ብሶት የምትለው ቃል አሁን ድረስ በኅሊናዬ አለች። በረኸኞቹ ሬዲዮ ጣቢያውን ሲቆጣጠሩ ያንን መልእክት ለማሰማት ቀድመው የተዘጋጁበት ይሁን አይሁን ባላውቅም፣ በቃላት ምርጫ ደረጃ “ብሶት”ን መጠቀማቸው በብዙው ገላጭ ነበር። ነፍጥ አንግበው ትግል የገጠሙት ብሶት ፈንቅሏቸው እንደሆነ ለማጠየቅ፣ ሌላ ምንም አማራጭ እንዳልነበራቸው ለማስረገጥ የሚችል ጥሩ ቃል ነው።
ብሶት፦ ባሰ ከሚል ግስ የሚመዘዝ መቀየምን፣ መበሳጨትን፣ ማዘንን፣ መከፋትን የሚያመለክት ነገር ነው። ተራ መከፋት ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለ ቅሬታ ነው። ሰዎች የሚፈልጉትን ባለማግኘታቸው የሚፈጠር ቅሬታ። የሚፈልጉትን ባለማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን የሚገባቸውን፣ የራሳቸው የሆነውን ባለማግኘታቸው፣ ከዚያም አልፎ ሊደርስባቸው የማይገባ ነገር ሲደርስባቸው የሚፈጠር ጠንካራ ስሜት ነው።
እንዲህ ያለው ከፍ ያለ ብሶት በቀላሉ የሚፈጠር ተርታ ቅሬታ አይደለም። በተግባር የደረሰም ይሁን በታሪክ እየተነገረ አሁን እንደተፈጠረ ተደርጎም ቢቆጠር “ብሶት” ሆድ አንጀትን አላውሶ ሞትን የሚያስመርጥ፣ ብረት የሚያስነሣ፣ ከአገር የሚያስሸፍት፣ ከዘመድ ባዳ ከአገር ምድረ በዳ የሚያሰኝ “ሮሮ” ነው። ያውም የጽኑዕ በደል ውጤት። መጽሐፉ እንዳለው ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ የሚያጽናናቸውም አልነበረም በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።” (መጽሐፈ መክብብ 41)
ብሶት ላይ አምጸው የተነሡ ሰዎች ራሳቸውም በእነርሱ ላይ ይፈጸም የነበረውን በደል ለመድገም የሚችሉበት ዕድል እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን የአገራችን ታሪክ ጥሩ እማኝ ነው። በበደል ውስጥ ያለፉ ሰዎች የሚቃወሙት በጠቅላላው በደልን ሁሉ ነው ወይንስ እነርሱ ላይ የሚደርሰውን በደል ነው? “እኔን ምንም አይንካኝ ሌላው እንደፈቀደው” ነው ወይንስ “በእኔ ላይ እንዲደርስ የማልፈልገውን በማንም ላይ እንዲደርስ አልፈልግም” ከሚል ሐሳብ?
የራሳቸው ወገን ሲነካ ተቆጭተው የተነሡ ሰዎች፣ ያው በደል በሌላው ወገን ላይ ሲደርስ የማይቆረቁራቸው ከሆነ፤ በራሳቸው እምነት ላይ የተፈጠረው አደጋ በሌላው እምነት ላይ ሲጋረጥ የማይከነክናቸው ሰዎች በትክክል በደል እና ብሶት ገብቷቸዋል ማለት ይቻላል?
ትናንት የበደሉን ሰዎች በብረታቸው ይመኩ እንደነበረ እናውቃለን። እንኳን ጥቃቅን የአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ከአፍሪካ ከየትኛውም ጥግ ጦር ቢነሣ ወገቡን ሰብረን እናስቀረዋለን እንደተባለ እናውቃለን። እነዚያው የተናቁት የአገር ውስጦቹ ወንበሩን እንደገለበጡም እናውቃለን።

ታዲያ እነዚያው የተናቁት በፈንታቸው ሌላውን “ከፍ ብለን አንገትህን ዝቅ ብለን ባትህን እንቆርጣለን፤ ገና ምኑን ዓይተህ ለልጅ ልጅ እንገዛሃለን፣ አርቀን ስለቀበርንህ በየት ልትወጣ” ሲሉ መስማት ጥላቸው ከበደልና ከግፍ ጋር ሳይሆን ከአንድ በዳይ ጋር ብቻ መሆኑን አያስረግጥም? “እኔን እንዳትነካኝ፣ እኔ ግን ሌላውን እንደፈለግሁ ላድርገው” የሚል የደካማ ፍልስፍና? ጥያቄው “በደል አይኑር” ሳይሆን “በዳዩ እኔ ልሁን”፤ “ረሃብ አይኑር” ሳይሆን “እኔ ብቻ ልጥገብ”፣ “ድህነት አይኑር” ሳይሆን “እኔ ብቻ ሀብታም ልሁን”፣ “ብሶት አይኑር” ሳይሆን “ብሶተኛው እኔ አልሁን” የሚል ግላዊና ቡድናዊ ጉዳይ ይሆናል።
በደል ለመፈጸም አቅምም ፈቃድም ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ለኅሊናቸው አስገዝተው “የሠራኹት ስሕተት ነው” ለማለት እጅግ ከባድ የኅሊና ልዕልናን ይጠይቃቸዋል። የጠገበ ሰው የተራበ ሊኖር ይችላል ብሎ እንዲያስብ፣ የብሶተኛውን ዕንባ ሲያይ በርግጥም ተበድሎ ሊሆን ይችላል እንዲል፣ ከሚያውቃቸው በዳዮች ይልቅ ለማያውቃቸው ብሶተኞች ጥብቅና እንዲቆም ከፍ ያለ ዕውቀት ይፈልጋል። በርግጥም የወደፊቱን በጥንቃቄ ለመገመት መሞከርንና ውጤቱን ከወዲሁ ለማመዛዘን መፍቀድን ይጠይቃል።
ብሶት መፍትሔ የሚያገኘው ለትክክለኛው ብሶት ትክክለኛውን መፍትሔ በማስቀመጥ ብቻ ነው። ጊዜያዊ ማዳፈን እና ማድበስበስ በጭራሽ መፍትሔ አይሆንም። የሚያለቅሱ ሰዎችን ለምን አለቀሳችሁ፣ ለምን አነባችሁ በሚል ማስፈራሪያ ዕንባቸውን ወደ ውስጣቸው እንዲውጡ ማድረግ ይቻል ካልሆነ በስተቀር ሳጋቸውንና ብሶታቸውን ማጥፋት አይቻልም። የሁል ጊዜውም ተረት “ውሻህን ለመቅጣት በር አትዝጋ” ነው። መውጫ ቀዳዳ ተውለት። መውጫ፣ መተንፈሻ ሲያጣ ወደራስህ እንዳይመለስ። አገር ለማስተዳደር፣ ሰዎችን ለመምራት፣ ውሻን ከመግራት ያነሰ አካሄድ መሔድ ውጤቱን አስከፊ ያደርገዋል። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ካልሆነ በስተቀር የታወቀ የተረዳ ነገር ነው።
እንኳን በአገር ደረጃ በግለሰብ እና በቤተሰብ ደረጃ እንኳን ብሶት ማዳመጥ እና ትክክለኛ መፍትሔ መስጠት አዋቂነት እንጂ ተሸናፊነት አይደለም። ባል ወይም ሚስት ችግር አለብኝ፣ ደስተኛ አይደለሁም እያሉ አንድኛው ወገን ለመስማት ፈቃደኛ ካልሆነ ያ ትዳር ሰላም እንደማይኖረው ግልጽ ነው። አንድ መሥሪያ ቤት የሠራተኞቹን ብሶት ሰምቶ ትክክለኛ መፍትሔ ካልሰጠ ቢያንስ ውጤታማነቱ ላይ ጉዳት እንደሚያስከትልበት ይታወቃል። አገርም እንደዚያው ነው። የዜጎችን ብሶት የማይሰማ መንግሥት ምን እስከ አፍንጫው ቢታጠቅ መንበርከኩ አይቀርም። ሮሮን በኃይል ማዳፈን አይቻልም።
የሰው ብሶት በአንደበቱ ባይነገር ፊቱ፣ ኑሮው፣ ሕይወቱ ይናገራል። በዝምታ ይጮኻል። በዝምታ ያለቅሳል። በዝምታ አቤ…..ት ይላል። የጥንት ገዢዎች “እረኛ ምን አለ? አዝማሪ ምን አለ?” የሚሉት የሕዝቡን የዝምታ ጩኸት ለማዳመጥ ነው። ትዕግስተኛው ኢዮብ “የዝምታ ድምጽ ሰማሁ” ያለው አለነገር አልነበረም (መጽሐፈ ኢዮብ 4፥16) ። ለካስ ዝምታም ድምጽ አለው!!! ጋቢውን አፉ ላይ ጣል አድርጎ የሚሰማህ ባለዝምታ ሰው በርግጥ እየጮኸብህ መሆን አለመሆኑን ጠይቅ። የሰማህ ሁሉ አያዳምጥህም። ያጨበጨበልህ ሁሉ አይደግፍህም። የታዘዘልህ ሁሉ አይስማማልህም። ቀን ነው የሚጠብቅልህ።
ስለዚህ የዝምታ ጩኸቶችን ስማ። ያለ ዕንባ የሚያለቅሱ ዓይኖችን ተመልከት። ባይቃወሙህም የማይደግፉህን ሰዎች ሐሳብ አዳምጥ። ለምን ተዘረፍኩ ብለህ ዛሬ መዝረፍህ፣ ለምን ተገፋሁ ብለህ ዛሬ ገፊ መሆንህ፣ ለምን ተገደልኩ ብለህ ዛሬ ገዳይ መሆንህ፣ ለምን ተራብኩ ብለህ ዛሬ አለመጥገብህ ከታሪክ አለመማርህን እንጂ ጉብዝናህን አያመለክትም። ብሶቶችን አብርድ፣ ግፍ በደሉን ተው። አንተን የወለደ ብሶት ሌሎችን መውለዱን ግን በፍጹም አትጠራጠር።  
ይቆየን - ያቆየን 

 ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።

5 comments:

Anonymous said...

አንተን የወለደ ብሶት ሌሎችን መውለዱን ግን በፍጹም አትጠራጠር።

Anonymous said...

አንተን የወለደ ብሶት ሌሎችን መውለዱን ግን በፍጹም አትጠራጠር።

Anonymous said...

DEACON EPHREM;
CONTINUE TO MOTIVATE PEOPLE ABOUT THEIR COUNTRY AND RELIGIOUS ISSUES

Anonymous said...

“ውሻህን ለመቅጣት በር አትዝጋ” ነው። መውጫ ቀዳዳ ተውለት። መውጫ፣ መተንፈሻ ሲያጣ ወደራስህ እንዳይመለስ። አገር ለማስተዳደር፣ ሰዎችን ለመምራት፣ ውሻን ከመግራት ያነሰ አካሄድ መሔድ ውጤቱን አስከፊ ያደርገዋል። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ካልሆነ በስተቀር የታወቀ የተረዳ ነገር ነው።

Anonymous said...

“ውሻህን ለመቅጣት በር አትዝጋ” ነው። መውጫ ቀዳዳ ተውለት። መውጫ፣ መተንፈሻ ሲያጣ ወደራስህ እንዳይመለስ። አገር ለማስተዳደር፣ ሰዎችን ለመምራት፣ ውሻን ከመግራት ያነሰ አካሄድ መሔድ ውጤቱን አስከፊ ያደርገዋል። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ካልሆነ በስተቀር የታወቀ የተረዳ ነገር ነው።17