Thursday, July 24, 2014

ያኛውን አልኩህ እንጂ …

 (ኤፍሬም እሸቴ):- ይህም ጽሑፍ እንዲሁ ከተጻፈ አንድ ወር ገደማ አለፈው። የጡመራ መድረክ ላይ ሳይወጣ ቆይቶ ዛሬ በል በል ሲለኝ  ከቀረ የዘገየ ይሻላል ብዬ አመጣኹት። አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።
+++
 ሰዉ ስብሰባ ይወዳል። አጀንዳ ይዞም አጀንዳ ሳይዝም ይሰበሰባል። “ስብሰባ አልወድም” የሚለው ሰውዬም ራሱ በየቀኑ ሲሰበሰብ እንደሚውል አያውቀውም እንጂ ተሰብሳቢ ነው። ቡና ላይ፣ ድራፍት ዙሪያ፣ በቢራ ጠርሙስ ድርድሮሽ … ይበሰባል። ቄሱም ሐጂውም ተሰብሳቢ ነው። ምእመኑም ካድሬውም … እንደየፊናው። ለውጡ አጀንዳ ተይዞ እና አጀንዳው በዘፈቀደ እየተነሣ እየተጣለ ያለ ስብሰባ ነው እንጂ ቅሉ።
ስብሰባ አንድ
ሞቅ ያለ ወሬ መካከል አንዱ ሐሳቡን እንዲህ አቀረበ። “ሰሞኑን አንዲት ነፍሰጡር ሴት እንድትገደል ሱዳኖች እንደወሰኑ ሰምታችኋል? አባቷ ሱዳናዊ ይሁን እንጂ እናቷ እኮ ኢትዮጵያዊት ናት። ሱዳኖች ኢትዮጵያ ላይ ባላቸው ጥላቻ መሆን አለበት እንዲህ የጨከኑባት። ክርስቲያን መሆኗን እያወቁ ካልሰለምሽ በሚል ሰበብ ሊገድሏት ነው። ዝም ማለት የለብንም። ይህቺን ሴት ከሞት ማትረፍ አለብን። መንግሥት በጉዳዩ እጁን እንዲያስገባ መጠየቅ አለብን።”

Wednesday, July 23, 2014

አገራቸው ለናፈቃቸው ሁሉ፤

በዓመት በዓመት አንድ ሰሞን፣ አለው የአገር ናፍቆቴ ጫፍ የሚደርስበት። በየቀኑስ መቼ ጠፍቶ ለነገሩማ። ግን የዚያ ሳምንት ይለያል። ልክ እንደ መንግሥት የሰኔ ወር በጀት መዝጊያ የኔም ናፍቆቶች በጀት መዝጊያ አላቸው መሰለኝ። ያጣድፉኛል። ምንም ባረገው አይለቀኝም። ውስጤን በሰው አምሳል ብስለው፣ ዓይኖቹ ሲያለቅሱ አየው ነበር። ውስጥ ሲያለቅስ በደንብ ይሰማል ለካስ።
ከአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ - ለራሴ እንድትሆን በተቀጠቀጠች ግጥም እንዲህ እላለኹ፦
 “ተደርጎ ያውቃል ወይ እንዲህ ያል  ሥርዓት፣
ልቤ ከአገር ቤት እግሬ ከስደት።”

Tuesday, July 22, 2014

የመረረውን እውነት በቅጡ ማቅረብ

ችግራችንን በትክክል መግለጽ እንልመድ!!!!
እንዲያው ይኼ የአገራችን ፖለቲ………ካ!!!! የምሬት ንግግር። በጣም በብዙ ሐበሻ አፍ የማትጠፋ ምሬት። ልክ ጥፋቱ የሆነች ፖለቲካ የምትባል የኮምፒውተር ቫይረስ የመሰለች በሽታ አገራችንን ያበላሸችው ይመስል። ከዚያ ለጥቆ ደግሞ ሌላ ምሬት። እንዲያው እነዚህ የአገራችን ፖለቲከኞች!!!! ውይ ውይ ውይ!! ልክ ስምና አቋም እንደሌላቸው ሁሉ በደምሳሳው ሁሉንም ደፍጥጠን በጅምላ እንሰድባቸዋልን። ሦስተኛ ምሬት ደግሞ አለች። “ለምን አንደማመጥም፣ ልዩነታችንን ተቀብለን አንድ በሚያደርገን ላይ አንሠራም፣ ልዩነት ውበት ነው” ምናምን ምናምን።

Friday, July 11, 2014

ስም-ደበቅነት እና ስመ-ደበቆች

(ኤፍሬም እሸቴ/ READ IN PDF)
(ይህ ጽሑፍ ከተጻፈ አንድ ወር አለፈው። የጡመራ መድረክ ላይ ሳይወጣ በመዘግየቱ እንጂ።  ከቀረ የዘገየ ይሻላል ይባል የለ? እነሆ። ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።)
+++++++
ደበቅ፦ (ደበቀ) ከሚለው ግስ የወጣ ነው። ከትርጉሞቹ አንዱ “ራሱን፣ ሰውነቱን የደበቀ” ማለት ነው። ስውር ቦታ ለማለትም “ደበቅ” ማለት እንደሚቻል አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ያትታሉ (ገጽ.333)። በጀግንነት፣ በደግ ሥራ የሚታወቅ ሰው “ስመ-ጥር” እንደሚባለው፤ እንዲሁም የመጠሪያ ስም ለማለት “ስመ ተጸውዖ” እንደምንለው ሁሉ ስማቸውን ደብቀው፣ ያለ ስማቸው ሌላ ስም አውጥተው የሚጽፉ ሰዎችን (anonymous and anonymity) “ስመ-ደበቅ፤ ስመ ደበቆች” ብንላቸውስ? ስለዚህ ስመ-ደበቅ “ስሙን ደብቆ የሚንቀሳቀስ ሰውን” እንደሚወክል ተስማምተን ወደ ጽሑፋችን እንግባ።

Thursday, July 10, 2014

“ፖለቲካ ውስጥ አትግባ” የምትባል ፖለቲካ!!!!!!!

አዲሱ የእኛ አገር ፖለቲካ ሰውን “ኧረ ፖለቲካ ውስጥ አትግባ” የምትባል ፖለቲካ ናት። እንዲህ ለሚሉ ሰዎች ትክክለኛውን ምላሽ ለማግኘት ብዙ ጊዜ ቆዝሜያለኹ። አሁን እንኳን በዚህች መሸዋወድ የለም። በነገራችን ላይ፤ ፖለቲካ ውስጥ እንዳትገባ የሚነግሩህ ማንነትህን በሚመጥን መልክ ነው።
1. ሃይማኖተኛ ከመሰልካቸው፣ ለዚያ የሚስማማ ጥቅስ እና አባባል አዘጋጅተዋል።
2. “ምሁር ነገር” ከመሰልካቸው ምሁርነት ከአገራችን ፖለቲካ በላይ በመሆኑ ራስህን በዚያ ውስጥ እንዳታቆሽሽ ያስጠነቅቁሃል።
3. ንግድ ላይ ካለህ በፖለቲካ መነካካት ሊያመጣ የሚችለውን መአት ያመለክቱሃል።
4. ዳያስጶራ ብትሆን አገር ቤት ያሉ ዘመዶችህ ላይ ሊመጣ ያለውን ችግር ያመለክቱሃል፤ ራስህም ብትሆን እዚያችን አገር ድርሽ እንደማትል ያስጠነቅቁሃል።