Thursday, July 24, 2014

ያኛውን አልኩህ እንጂ …

 (ኤፍሬም እሸቴ):- ይህም ጽሑፍ እንዲሁ ከተጻፈ አንድ ወር ገደማ አለፈው። የጡመራ መድረክ ላይ ሳይወጣ ቆይቶ ዛሬ በል በል ሲለኝ  ከቀረ የዘገየ ይሻላል ብዬ አመጣኹት። አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።
+++
 ሰዉ ስብሰባ ይወዳል። አጀንዳ ይዞም አጀንዳ ሳይዝም ይሰበሰባል። “ስብሰባ አልወድም” የሚለው ሰውዬም ራሱ በየቀኑ ሲሰበሰብ እንደሚውል አያውቀውም እንጂ ተሰብሳቢ ነው። ቡና ላይ፣ ድራፍት ዙሪያ፣ በቢራ ጠርሙስ ድርድሮሽ … ይበሰባል። ቄሱም ሐጂውም ተሰብሳቢ ነው። ምእመኑም ካድሬውም … እንደየፊናው። ለውጡ አጀንዳ ተይዞ እና አጀንዳው በዘፈቀደ እየተነሣ እየተጣለ ያለ ስብሰባ ነው እንጂ ቅሉ።
ስብሰባ አንድ
ሞቅ ያለ ወሬ መካከል አንዱ ሐሳቡን እንዲህ አቀረበ። “ሰሞኑን አንዲት ነፍሰጡር ሴት እንድትገደል ሱዳኖች እንደወሰኑ ሰምታችኋል? አባቷ ሱዳናዊ ይሁን እንጂ እናቷ እኮ ኢትዮጵያዊት ናት። ሱዳኖች ኢትዮጵያ ላይ ባላቸው ጥላቻ መሆን አለበት እንዲህ የጨከኑባት። ክርስቲያን መሆኗን እያወቁ ካልሰለምሽ በሚል ሰበብ ሊገድሏት ነው። ዝም ማለት የለብንም። ይህቺን ሴት ከሞት ማትረፍ አለብን። መንግሥት በጉዳዩ እጁን እንዲያስገባ መጠየቅ አለብን።”

ሞቅ አለ ወጉ። ሁሉም በስሜት የየራሱን ሐሳብ ሰጠ። “የሚመለከታቸውን አካላት” በማሳተፍ አሳታፊ የሆነ ሰላማዊ ጥያቄ ለማቅረብ፣ የሱዳን ኤምባሲን ለማነጋገር፣ ጉዳዩ የሚያገባቸውን ሁሉ ለማስተባበር እጅግ ሐሳብ እየተሰጠ ስብሰባው ሞቅ ደመቅ ብሎ ቀጠለ። ስብሰባው ሲጀመር ያልነበሩ ሰዎችም እየተደበሉ ጉባኤተኛው ሰፋ። ይህች ስለ እምነቷ ሰማዕት ለመሆን ስለተፈረደባት ሴት እንባ ቀረሽ ንግግሮች ተደረጉ።
በማጠቃለያው አካባቢ አንድ ሰው ሐሳብ ለመስጠት ጉሮሮውን ጠራረገ። “ይህ ስብሰባ መቸም እጅግ በጣም ደስ የሚል መነሣሣት የታየበት ነው። ለወገኖቻችን ያለንን መቆርቆር ፍንትው አድርጎ አሳያል። በዚሁ እግረመንገዳችንን በእንትን ክፍለ ሀገር በእንትን አውራጃ የምትገኘውን የእንትን ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ታውቁታላችሁ። ቤተ ክርስቲያኗ ልትፈርስ ነው። አይፍረስብን ያሉ ካህናትና ምዕመናን ታስረዋል። ለምን አቤቱታቸውን አናሰማላቸውም?” ብሎ ከመናገሩ ቤቱ በጸጥታ ድባብ ተዋጠ። የሚናገር ጠፋ። አንዱ ጣልቃ ገብቶ “ውይይታችን ሱዳን ስላለች ወገናችን እንጂ ስለዚህ ነው ማን አለህ? ያኛውን አልንህ እንጂ ይኼኛውን ተባልክ?” ብሎ እስኪቆጣ ድረስ።
ስለ ሱዳን ወገናችን ችግር የተቆረቆረው አጠገቡ ስላለው ወገኑ ሲነሣ ለመስማት ሳይፈልግ ቀረ። ከዚያ ሌላ ቀጠሮ እንደደረሰባቸው የተናገሩ ብዙ ተሰብሳቢዎች ብድግ ውልቅ፤ ብድግ ውልቅ ማለት ጀመሩ። የዚህኛው አጀንዳ በመነሣቱ የዚያኛውም ውሳኔ ፈረሰ። ብት …… ን።
ስብሰባ ሁለት
እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ላይ የምታደርሰው ግፍና በደል እጅግ ስለበዛ ድምጻችንን ለማሰማት … በሚል የተጠራ ስብሰባ ሞቅ ብሎ እየተካሄደ ነው። አሜሪካ በአረቡ ምድር ላይ ያላት ተጽዕኖ እና አረቦችን፣ ሙስሊሞችን ለማጥፋት ያለመው ግብ ይተነተናል። በሱማሌ ያሉ ወገኖች ስለሚደርስባቸው በደል ይቀርባል። ሁሉም ቁጭትና መጠቃት ፊቱ ላይ ይነበባል። በእነዚህ አገሮች ያሉ ወገኖች መብታቸው መጣሱ ያብከነክነዋል። “ወንድሞቼ አንድ ሐሳብ አለኝ” የሚል ድምጽ ሲሰማ በዚህ ስሜት ለማዳመጥ ዘወር አሉ።
“በወገኖቻችን ፍልስጥኤማውያን ላይ የሚደርሰው በደል እጅግ ይዘገንናል። ድምጻቸው መሰማት አለበት። እዚህ አገራችን ውስጥም እንደምታውቁት ችግር አለብን። ለመነጋገር ብለን ብንሰበሰብ የሰበሰቡን ሰዎች ታሰሩ” ከማለቱ የሞቀው ስሜት በረዶ የፈሰሰበት መሰለ። “መብት፣ ሰብአዊነት፣ ወገኖቻችን” የሚሉት ቃላት ራሳቸው ኩምሽሽ ብለው መቀመጫ ሥር ገቡ። ከዚያማ ቀጠሮ እንደደረሰባቸው የሚናገሩ ብዙ ድምጾች ተሰሙ። እያጉረመረሙ መውጣት ያዙ። “ያኛውን አልነው እንጂ ይኼንን ማን አንሣ አለው” እያሉ። ተበተኑ።
ስብሰባ ሦስት
በቱሪ-ናፋ ቲቪወሬዲዮ ላይ የቀጥታ ስርጭት እየቀረበ ነው። ተከራካሪዎች ቀርበው ሐሳባቸውን ይሰጣሉ። አድማጭ ወተመልካች በስልክ ጥያቄ ያቀርባል፤ ይከራከራል። አጀንዳው ቬኔዙዌላ ስላለው አገር ወዳድ መንግሥት፣ በመንግሥቱ ላይ ስላለው የምዕራባውያን ተጽዕኖ፣ ስለ መሬት እና ሀብት ክፍፍል ወዘተ ነው። ምሁራኑ የከረባታቸው ጫፍ ተገንጥሎ እስኪበር፣ መነጽራቸው ተስፈንጥሮ እስኪወድቅ፣ መላጣቸው በስሜት ሙቀት አዲስ ፀጉር እስኪያበቅል ይከራከራሉ። የሰው ልጅ መብት መጣስ ምን ያህል ክብረ-ነክ መሆኑን ለማጠየቅ የማይጠቅሱት ፈረንጅ የለም።
“እንትና የተባለው ሊቅ፣ እንትን በተባለው የፍልስፍና ዐምድ በሆነ መጽሐፉ ላይ …”፤
“የአሜሪካው እንትነኛ መሪ የሆኑት እንትና ስለ ግለሰብ መብት በተናገሩበት ንግግራቸው” ….፤
“የመሬት ባለቤትነትን በተመለከተ ….” የጦፈ ውይይት።

በመካከሉ ለውይይቱ ድምቀት ሱቱዲዮ ከተጋበዙት ተመልካቾች (“የሕብረተሰብ ክፍል”) መካከል ዕድል የተሰጣቸው አንድ አዛውንት ለመናገር ጉሮሯቸውን ጠራረጉ። “ይህ ያላችሁት ሁሉ እጅግ ልብ የሚመስጥ ነገር ነው። በእኛ አገርም እነዚህን መብቶች ለማስገኘት ከተማሪ እስከ አስተማሪ፣ ከቤት እመቤት እስከ አደባባይ ባለቤት፣ ከወታደር እስከ ለፍቶ አደር ብዙ ነፍስ ተገብሮበታል። አሁንም ግን በአገራችን እነዚህ ያላችኋቸው ፈረንጆች የተናገሩትና እናንተም በስሜት ያወሳችኋቸው መብቶች አልተከበሩም።  ለምሳሌ …” ብለው ሊቀጥሉ ሲሉ ጋዜጠኛው በጎርናና ድምጽ አቋረጣቸው። “ይኼንን ማን አሎት? አጀንዳው ስለዚያ ነው እንጂ ስለዚህ ነው? ለምንድነው አጀንዳ የመጠበቅ ባህላችንን የምትንዱት?”
ጥልቅ ማብራሪያ “በስብሰባ ላይ አጀንዳ ስለመጠበቅ” ቀጠለ። “ተጨማሪ አለኝ” አለ አንድ ሰው። ረዳት-ጋዜጠኛው ነው። (ረዳት ፓይለት እንደሚባለው)። ከዚያም በአገራችን ያለው ሁኔታ ጥያቄ ለማንሣት እንኳን በማያስፈልግ ደረጃ መብቶች የተከበሩበት እንደሆነ፣ ይህንን ፕሮግራም ራሱ ለማቅረብ የተቻለው በዚያ የመብት መከበር መነሾ መሆኑን መጽሔት፣ ጋዜጣ፣ ታላቅ መሪ እየጠቀሰ አብራራ። አንዳንዶች ግን ይሄንን መብት እና አከባበሩን ለማጣጣል የሚሞክሩበት ሁኔታ እንዳለ አስረዳ። “ከአፍታ ቆይታ በኋላ እንመለሳለን” አለና ማስታወቂያ አየሩን ተቆጣጠረው።
ከዚያ ሦስት የብሔረሰብ ዘፈን በተከታታይ ተለቀቀ። በመካከሉ ያንን የመሰለ ውይይት ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ያፈሰሱት ሰው ተገሰፁ። “የውይይታችን አጀንዳ ቬኔዙዌላ ነች። ከአጀንዳ መውጣት ትክክል አይደለም። የስብሰባ ሥርዓት ማወቅ ያስፈልጋል” እየተባለ ትምህርት ተሰጣቸው። የመወያያ ጠረጴዛው ላይ የተቀመጡት ምሁራን አጉረመረሙ። “አስተያየት ሰጪው ምን ነካቸው? እኛ ስለ ቬኔዙዌላዎች አልናቸው እንጂ ስለእኛ ጥያቄ አቅርቡ አልናቸው እንዴ?”
ውይይቱ ካቆመበት ቀጠለ። ስሜቶችና ሙቀቶች ተቀዛቀዙ። መላጣዎች ያፈልቁ የነበረውን ትኩስ ላብ ቀጥ አደረጉ። ከረባቶች ተስተካከሉ። አንገቶች ዝቅ አሉ። ይኼኛውን ትቶ ያኛውን፣ የቅርቡን ትቶ የሩቁን፣ የቤተሰብን ትቶ የጎረቤትን ማንሣቱ አሳፈራቸው። በሌላ ቀጠሮ፣ በብዙ ዘፈኖች እና በጋዜጠኛው ሰፊ ዲስኩር የቀረው ሰዓት ተጠናቀቀ። ተበተኑ።
ስብሰባ አራት
ስለ ስብሰባዎች አጀንዳ ከራሴ ጋር ተሰበሰብኩ። አንደኛው እኔ “ለምንድነው ስለራሳችን፣ ስለችግራችን፣ ስለአሁን-ስለዚህ ከማውራት ይልቅ ስለነዛ፣ ስለሩቅ፣ ስለወደፊት ማውራት የቀለለን? ዛሬ-እዚህ-የኛ ጉዳይ ከብዶ ያኛው ምነው ቀለለ?” ይላል።
አንዱ ውስጤ መለሰ፤ “ስማ የኔ ወንድም፤ መፍትሔ የለህ አሁንም ትፈላሰፋለህ? እነሆ ግጥም …” ብሎ እንደ አዝማሪ ወረወረብኝ። ሊያሳፍረኝ። አንገቴን ሊያስደፋኝ። ግን እውነት አለው።
“የነገር ፀጉር መሰንጠቅ የነገር ዝተት ዘትቶ፤
የነገር ዘባተሎ መቅደድ የነገር ዘባተሎ ሰፍቶ፤
የነገር ብልት ማወራረድ የነገር ጭቅና አውጥቶ፤
ጠቢብና ሊቅ መሆንህ በዚህ ከሆነ የሚለካ፤
ያልተዘራውን መኸር አጭደህ ያልተፈጨውን ዱቄት አቡካ።”
የመጀመሪያው እኔ በበኩሉ “ስለነዚያ ሰዎች አውራኝ አልኩት እንጂ ስለእኔ አልኩት እንዴ?” እያለ ተነሣ። ስለ ስብሰባዎች የነበረኝ ስብሰባም በዚሁ ተበተነ። “ወይ ጉድ፤ ስለዚያ ሲሉት አይ ስለዚህ የሚል ወቃሽ መብዛቱ“ እያልኩ። ዋጋ ስላማያስከፍለው፣ ስለማያሳስረው፣ ስለማያስገርፈው፣ “እጅህ-ከምን” ስለማያሰኘው ስለ ውጪው፣ ስለሩቁ ማውራት እየተቻለ ስለዚህ-ስለቅርቡ ማውራት፤ ዋጋ ስለሚያስከፍለው፣ ስለሚያስገርፈው መወያየት ምን ያደርጋል? “ጎመን በጤና” እያለ?
ይቆየን - ያቆየን
ማስታወሻ፦ ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ግጥም “ስብሰባ” በሚል ርዕስ ኅዳር 3/93 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ከጻፍኩት የተወሰደ ነው።

ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።


 

5 comments:

Zekios said...
This comment has been removed by a blog administrator.
Zekios said...
This comment has been removed by a blog administrator.
Fisseha Moges said...

You are my hero and my icon!!! Long live long live and long live!!!

Dannyfikir said...

Thank you for your insight. Yes, now we can't talk about Ethiopian current situation. No body, even one who dares to talk on public about us. BTW, if there is such a thing "us" as before.

Anonymous said...

please write some thing as a response to "Minister" Shiferaw on his announcement for Christians not to wear Maeteb.