Friday, July 11, 2014

ስም-ደበቅነት እና ስመ-ደበቆች

(ኤፍሬም እሸቴ/ READ IN PDF)
(ይህ ጽሑፍ ከተጻፈ አንድ ወር አለፈው። የጡመራ መድረክ ላይ ሳይወጣ በመዘግየቱ እንጂ።  ከቀረ የዘገየ ይሻላል ይባል የለ? እነሆ። ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።)
+++++++
ደበቅ፦ (ደበቀ) ከሚለው ግስ የወጣ ነው። ከትርጉሞቹ አንዱ “ራሱን፣ ሰውነቱን የደበቀ” ማለት ነው። ስውር ቦታ ለማለትም “ደበቅ” ማለት እንደሚቻል አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ያትታሉ (ገጽ.333)። በጀግንነት፣ በደግ ሥራ የሚታወቅ ሰው “ስመ-ጥር” እንደሚባለው፤ እንዲሁም የመጠሪያ ስም ለማለት “ስመ ተጸውዖ” እንደምንለው ሁሉ ስማቸውን ደብቀው፣ ያለ ስማቸው ሌላ ስም አውጥተው የሚጽፉ ሰዎችን (anonymous and anonymity) “ስመ-ደበቅ፤ ስመ ደበቆች” ብንላቸውስ? ስለዚህ ስመ-ደበቅ “ስሙን ደብቆ የሚንቀሳቀስ ሰውን” እንደሚወክል ተስማምተን ወደ ጽሑፋችን እንግባ።

ስም ደብቆ መጻፍ በአገራችን የቆየ ልማድ ነው። በአገራችን ከምናውቃቸው ብዙዎቹ የግዕዝ መጻሕፍት መካከል እጅግ ጥቂቶቹ ካልሆኑ በስተቀር አብዛኞቹ የደራሲዎቻቸው ስም በግልጽ እና በይፋ አልተጠቀሰባቸውም። የብዙዎቹም በገደምዳሜ ከተጠቀሱ ማስረጃዎች የሚገኙ/የተገኙ ካልሆኑ በስተቀር ደራስያኑ ይሁነኝ ብለው ማንነታቸውን እና ምንነታቸውን አይገልጹም።
አንዳንዶቹ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እጅግ ብርቅ ድንቅ የሆኑ ሥራዎቻቸውን “የእኔ ነው” ከማለት ይልቅ በእስክንድርያ ወይም በታናሽ እስያ፣ በሮም ወይም በግሪክ ያሉ ሊቃውንት እንደ ጻፏቸው አድርገው እንደሚያስተዋውቁ የግእዝ ሊቃውንት ይናገራሉ። አባቶቻችን ያንን ያደረጉት አንድም ስለ ትህትና አንድም ተቀባይነቱን ከፍ ለማድረግ እንደሚሆን መላምቶች አሉ። አንድም ደግሞ የደራሲዎቹን ዳራ ተከትለን ፈልገን ስላላገኘናቸው፣ የጻፉትን ማንበብ እንጂ ለፀሐፊዎቹ ቁብ የማይሰጠን ማኅበረሰብ ስለሆንም ይሆናል።
የጥንቱን ዘመን ትተን ወደዚህኛው ወደ ቴክኖሎጂው ዘመን ስንመጣም በስመ-ደበቅ መጻፍ የተለመደ ክስተት ነው። ከኢንተርኔት መወለድ በኋላ ማንም ሰው የፈለገውን ሐሳብ በነጻና በደበቅ (በድብቅ) ማስተላለፍ የሚችልበት ዕድል እጅግ የሰፋ በመሆኑ እገሌ-ባይ ፀሐፊ የሌላቸው እጅግ በጣም ብዙ ግልብ የሆኑም ሆኑ ጠንከር-ከበድ-ጥንቅቅ ያሉ ውኃ የሚያነሡ ሥራዎች እየተሰራጩ ነው።
በጾታቸው ምክንያት ማንነታቸውን ገልጸው በጽሑፍ አደባባይ ለመቆም በማይቻልባቸው ባህሎች ውስጥ ያደጉ አንስት፣ ጨቋኝ መንግሥቶቻቸውን የሚፈሩ ዜጎች ባሉባቸው አገራት፣ ፈጣን ተጽዕኖ ባይኖርባቸውም ውሎ አድሮ ጉዳት ሊያመጣብን ይችላል የሚሉትን ሐሳብ የሚያራምዱ ሰዎች በስመ-ደበቅ የልብ-የልባቸውን ይጽፋሉ፣ ይጦምራሉ፣ ያሠራጫሉ። (ብልግና፣ ስድብ እና እዚህ ግባ የማይባል ተርታ ነገር የሚጽፉትን ሰዎች ባንረሣቸውም ለጊዜው ግን እንተዋቸው። ለምን ቢባል፦ እንስሳዊ ጠባያቸውን የሚገልጡበት ሥፍራ ሲሹ ኢንተርኔት የገጠማቸው ስለሆኑ ከቁምነገር ሊገቡ ስለማይገባቸው።)
 በኢትዮጵያውን ፀሐፊዎች ዙሪያ በወፈር በረር የሚደረግ ዳሰሳ ቢኖር አብዛኞቹ ፀሐፊዎቻችን በትክክለኛ ስማቸው የማይጽፉ ስመ-ደበቆች መሆናቸውን ልንረዳ እንችላለን። በጣት የሚቆጠሩት ብቻ በስማቸው አደባባይ ሲቆሙ ይታያል። ከእነርሱም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ፀሐፍት በሚያነሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች ለስላሳነት ወይም “ጠላት የማይገዛ”፣ ከሰው ዓይን የማያስገባ መሆኑን በመተማመናቸው ስማቸውን ለመግለጽ እንዳላስፈራቸው መገመት ይቻላል።
በታወቀና በተረዳ ሚዛን ከተመለከትነው ኮስተር ባሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉ ሰዎች ማንነታቸውን ገልጸው ከሚያደርጉት ይልቅ በስመ-ደበቅ መጻፋቸው ከብዙ ኩርኩም ያድናቸዋል። ቢያንስ ቢያንስ ማንነታቸውን ለማወቅ ለሚፈልገው ሰው በቀላሉ እጁ አይገቡለትም። በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት የሚሠሩ ከሆነ ቢያንስ ሐሳብን በማካፈል ደረጃ ለሌላው ሊጠቅም የሚችል ብዙ በጎ ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ።
በአገራችን ያለውን ሁኔታ ከተመለከትን የግንባር ሥጋ ሆኖ ሐሳብን ከመግለጽ በስመ-ደበቅነት ተሸሽጎ መንቀሳቀስ እንደሚያዋጣ የጎሉ ማስረጃዎች  ማቅረብ ይቻላል። የዚህ “የስመ-ደበቅነት” ዕድል ተጠቃሚ መሆን የማይቻላቸው ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን መከራ ለተመለከተ፣ በቅርቡም በኃላፊነትና እና በሕጋዊነት ሚዛን የወጣነት በጎ ሐሳባቸውን ለማካፈል ደፋ ቀና ይሉ የነበሩት የዞን-ዘጠኝ ጦማርያን ላይ የደረሰውን አፈሳ እና እስር እንዲሁም ማንገላታት ለሚከታተል ዜጋ “የእንትናን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” ማለቱ አያስፈርድበትም።
ይሁን እንጂ ስመ-ደበቆች በድብቅ በሚጽፉት ጽሑፍ የብዙዎችን አዕምሮ ማሰልጠን ቢችሉም አነሣሣቸውና አከሳሰማቸው እንደዚያው በድብቅ ይሆናል። ከጽሑፎቻቸው ጀርባ ያለውን ተፈጥሯዊ ሰው አለማወቅና ያነሣቸው ሐሳቦች በማንነቱ አለመደገፋቸውም ሐሳቦቹን ባለቤት አልባ እና ምናባዊ ያደርጋቸዋል። ሐሳቦች ከባለቤቶቻቸው ጋር ተዋሕደው መታሰባቸው ሁልጊዜም ያለ ነው።   
ሐሳቦችን ለሚጠሉ ሰዎች በግልጽ ከሚጻፉ ጽሑፎች ይልቅ በድብቅ የሚጻፉ ጽሑፎችን ማፈን እንደማይቀል ቢታሰብም እኔ-ባይ ፀሐፊ ያላቸው ጽሑፎች በደበቅ ከሚጻፉት የበለጠ ክብደት አላቸው ብዬ አስባለሁ። የሚከፈልባቸውም ዋጋ የዚያኑ ያህል ከባድ ይሆናል። የዞን-9 ወጣቶች በድብቅ ነገር ግን በተናጠል ሊያደርጉት የሚችሉትን ሐሳብ በግልጽና በአንድነት ማድረጋቸው የበለጠ ድምጽና ተሰሚነት ፈጥሮላቸዋል። ብዙ ጦማርያን ቢኖሩም የእነርሱ የጋራ ድምጽ ልዕልና ኖሮት ከፍ ብሎ ሊታይ ችሏል። የከፈሉት ዋጋ የተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ዳርቻ አመላካች ነው።
አሁን የሚቀጥለው ወሳኝ ጥያቄ “በነዚህ ወጣቶች እና በሌሎች ጋዜጠኞች ላይ የደረሰው ችግር ሌሎችን ተስፋ አስቆርጦ አንገትን ወደመቅበር መውሰድ አለበት ወይስ እንደ እነርሱ ማንነትን ይዞ በጽሑፍ አደባባይ መገኘት ይሻል?” የሚለው ነው። የማያወላዳ እና ቁርጥ መልስ መስጠት ባይቻልም ወጣቶቹ የጀመሩትን ሕጋዊ እና ዜጋዊ ሐሳብን በነጻና በግልጽ የማቅረብ ልምድ መቀጠል ለአገርና ለሕዝብ የሚተርፍ ዋጋ ያስገኛል። አዲስ ነገር መፍጠር አዳጋች ቢሆን እንኳን መጋረጃውን ገልጦ እኔም አለሁ ማለት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።
በርግጥ ከወጣቶቹ እስር በኋላ የሚታየው ድባብ በፍርሃትና መከራን በመሰቀቅ መደበቅን ሳይሆን ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ ሐሳብን መግለጽን ነው። በተለይም የወጣቶቹ እንቅስቃሴ ትክክለኛነት እና ያነሷቸው ሐሳቦች ሕገ መንግሥታዊነት እንኳን የመንግሥትን እርምጃ ለማይደግፉ የመንግሥት ወገን ነን ለሚሉትም የብረት ቆሎ መሆኑ እየታየ ነው።
ቅዱስ መጽሐፍ በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ” እንዳለው እውነተኛ ተስፋ እና ለአገር የሚበጅ በጎ ነገር የሚገኘው በጨለማው የሚነገረው ነገር ሁሉ በቀን በብርሃን ሲነሣ፣ በየጓዳው የምንንሾካሾከው ነገር ሁሉ በሰገነት/ በአደባባይ ለውይይት ሲበቃ ብቻ ነው። ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን እና የአደባባይ ምሁራን ዋናው ተግባራቸው ይኸው ነው። ጠመንጃ ከያዘ ሰው በላይ የሚፈሩትና የሚከበሩትም ለዚሁ ነው። ጨለማ ያለበሰውን የሰው ልጅ አስተሳሰብ በእውቀት ብርሃን ስለሚገልጡ፣ በጓዳ የተሸፈነውን ሕመምና በሽታ በአደባባይ ለመፍትሔ ስለሚያቀርቡ ነው።
ከዚህ አንጻር በስመ-ደበቅነት ከሚዘራ አንድ ሺህ ኩንታል ዘር ይልቅ፣ በይፋ እና በአደባባይ ለሚዘራው አንድ ኪሎ የበለጠ ዋጋ መስጠት ይገባናል። በርግጥ እያሉ እንደሌሉ አንገትን ደፍቶ መኖርን የሚያበረታታ ባህል ውስጥ እንደመኖራችን በግልጽ የሚደረግን በነጻ የመኖር ልማድ ከግብዝነት ልንቆጥረው እንችላለን። ባለችው በዚያች የጨለማ ኑሮ ለተጽናና ሰው ከራሱ ባርነት ነጻ ሊያወጣው የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል ማግኘት አይቻልም። ኅሊናው በባርነት ላለ ሰው ሥጋው ነጻ ቢወጣም የኑሮው ትርጉሙ አንድ መሆኑ የታወቀ ነው።
የብዙው ዜጋ ትልቅ ኃላፊነት ራሳቸውን የግንባር ሥጋ አድርገው አደባባይ ለቆሙ ሰዎች አለኝታ መሆን ነው። የታሠሩትን በመጠየቅ፣ ለዚሁ አገራዊ ዓላማ የተጎዱትን በግልም በሕብረትም በመድረስ፣ ጠያቂ የሌላቸውን ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት በዚህና በዚህ መሰሉ ተግባር ዓላማቸው እንዳይጠፋ ማድረግ ይቻለናል። በቁርጥ ሐሳብ ከልባችን ልናስብበት ይገባል።       
ይቆየን - ያቆየን

ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ ነው።


 

1 comment:

atnatiwos the " gascha" said...

where has Adebabay been for months ? Has it been hiding in "Debeq?".....
I like the article"anonymous" and "anonymity." It is true that most of Ethiopian writers never mention their names on their own books and they would prefer to stay anonymous. That has to be changed now, keeping in mined copy right.