Sunday, October 26, 2014

ስም የወጣልኝ ዕለት

(እውነት ቀመስ ልቦለድ)
(ከኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- 
ንሿ ቤት በጢስ ታፍናለች። ከመታፈኗ ይልቅ ሙቀቷ ሕይወት ይዘራል። አራት ውጫጭ ልጆች እና ሦስት ወጣቶች እንዲሁም እናታችን ቤቱን ሞልተነዋል። አክስታችን አንዱን ጥግ ይዛ በስንጥር ቢጤ ጥርሷ ውስጥ የቆየ ጎመን ይሁን የገብስ ቆሎ ስባሪ ለማውጣት ትታገላለች። ሁሌም እንደዚያው ናት። ዓመት በዓል ካልመጣ  ሥጋ ስለሌለ ጥርሷ ውስጥ የተሰነቀረው የሥጋ ቁራጭ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበርኩ። ባለፈው ፋሲካ የበላነው ሥጋ እስካሁን ለመቆየት ዕድል እንዴት ያገኛል። አሁን ነሐሴ ነው። ለመስከረም 10 ቀን ፈሪ።
ልቋ የአጎቴ ልጅ ብርቱካን ወደ እኔ እያየች “አቡሽ ዘንድሮም ት/ቤት አይገባም እንዴ?” አለች ባለፈው ዓመት ገና በ6 ዓመቴ አንደኛ ክፍል ካልገባ ብላ ስትከራከር የነበረችውን እያስታወሰች። አንዱ ጥግ በተቀመጠበት ቁጭ ብሎ የሚያንጎላጀው ካሳሁን ነቃ ሲል አየዋለሁ። እናቴ ህም ብላ መልስ ሳትሰጥ ዝም አለች። ወንድሞቼ ድብርታቸውን የሚያባርር አጀንዳ እንዳገኙ ሁሉ ጉንጫቸው ውስጥ ሳቅ ደብቀው ወሬው ወዴት እንደሚያድግ አድፍጠው ይጠባበቃሉ። ወሬው እንዲቀጥል የሚፈልጉት ከቤተሰቡ መካከል የት/ቤት ስም የሌለኝ እኔ ብቻ ስለሆንኩ ነው። ከነርሱ ጋር እኩል አለመሆኔን ለማሳየት፣ ምሳ ላይ እንጀራ ተሻምቼ ስበላ ከሚደርስብኝ ኩርኩም በላይ ከትሪው የሚያባርሩኝ ከአቡሽ ውጪ ሌላ ስም እንደሌለኝ እያነሱ ስለሚያበሽቁኝ ነው።

Saturday, October 25, 2014

በአገር ላይ የሚመጣ አደጋን አቅልሎ የማየት ያልሰለጠነ አስተሳሰብ

ታዳጊ አገሮችን በሙሉ የሚያመሳስላቸው አንድ ግርም የሚለኝ ነገር ከገደል አፋፍ ቆሞ ገደሉን መናቅ፣ ከአደጋ ጫፍ ቆሞ አደጋን ማቃለል፤ ከዚያም ከገደሉ ወድቆ መሰበር፣ በአደጋው ተጠራርጎ መወሰድ። ይህ ሐሳብ በርግጥ ፍንትው ብሎ የታየኝ የማሌዢያ አውሮፕላን በዩክሬይን ሰማይ ላይ በሚሳኤል በጋየበት ጊዜ ነበር። ሁላችሁም እንደምታስታውሱት የሰው አካል ቁርጥራጭ ከሰማይ ይዘንብ እንደነበር እማኞች ሲናገሩ መልክተናል።
ታላላቆቹ የዜና አውታሮች ራሺያ ላይ አተኩረው ነገሩን በዚያ ፈፀሙት አንጂ “አውሮፕላኑ በጦርነት ሰማይ ላይ ለምን ሄደ?” የሚለውን የሚያነሱ ሰዎችም ተደምጠዋል። ብዙ አየር መንገዶች አቅጣጫቸውን ቀይረው በሌላ መስመር መሔድ ከጀመሩ ቆይተው ነበር። የሳንቲም ስባሪ ለማትረፍ አንድም በማሌዢያኛ “አቦ አታካብዱ” ብለው ሳይሆን አይቀርም በዚያ በታዳጊ አገር አስተሳሰብ መንገዳቸው ሳይቀይሩ ቀሩ።