Sunday, October 26, 2014

ስም የወጣልኝ ዕለት

(እውነት ቀመስ ልቦለድ)
(ከኤፍሬም እሸቴ/ PDF):- 
ንሿ ቤት በጢስ ታፍናለች። ከመታፈኗ ይልቅ ሙቀቷ ሕይወት ይዘራል። አራት ውጫጭ ልጆች እና ሦስት ወጣቶች እንዲሁም እናታችን ቤቱን ሞልተነዋል። አክስታችን አንዱን ጥግ ይዛ በስንጥር ቢጤ ጥርሷ ውስጥ የቆየ ጎመን ይሁን የገብስ ቆሎ ስባሪ ለማውጣት ትታገላለች። ሁሌም እንደዚያው ናት። ዓመት በዓል ካልመጣ  ሥጋ ስለሌለ ጥርሷ ውስጥ የተሰነቀረው የሥጋ ቁራጭ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበርኩ። ባለፈው ፋሲካ የበላነው ሥጋ እስካሁን ለመቆየት ዕድል እንዴት ያገኛል። አሁን ነሐሴ ነው። ለመስከረም 10 ቀን ፈሪ።
ልቋ የአጎቴ ልጅ ብርቱካን ወደ እኔ እያየች “አቡሽ ዘንድሮም ት/ቤት አይገባም እንዴ?” አለች ባለፈው ዓመት ገና በ6 ዓመቴ አንደኛ ክፍል ካልገባ ብላ ስትከራከር የነበረችውን እያስታወሰች። አንዱ ጥግ በተቀመጠበት ቁጭ ብሎ የሚያንጎላጀው ካሳሁን ነቃ ሲል አየዋለሁ። እናቴ ህም ብላ መልስ ሳትሰጥ ዝም አለች። ወንድሞቼ ድብርታቸውን የሚያባርር አጀንዳ እንዳገኙ ሁሉ ጉንጫቸው ውስጥ ሳቅ ደብቀው ወሬው ወዴት እንደሚያድግ አድፍጠው ይጠባበቃሉ። ወሬው እንዲቀጥል የሚፈልጉት ከቤተሰቡ መካከል የት/ቤት ስም የሌለኝ እኔ ብቻ ስለሆንኩ ነው። ከነርሱ ጋር እኩል አለመሆኔን ለማሳየት፣ ምሳ ላይ እንጀራ ተሻምቼ ስበላ ከሚደርስብኝ ኩርኩም በላይ ከትሪው የሚያባርሩኝ ከአቡሽ ውጪ ሌላ ስም እንደሌለኝ እያነሱ ስለሚያበሽቁኝ ነው።
ሚያንጎላጅበት የነቃው ካሳሁን “ስም ሳይኖረው እንዴት አንደኛ ክፍል ይገባል” አለና ነገሩን ለኮሰ። እንቅልፋም ነው ካሳሁን። ማታ ገና ራት ሳይበላ በተቀመጠበት ማንቀላፋት ጀምሯል። ሳይመሽ ማንቀላፋት ስለሚጀምር ማታ ማታ አብዛኛውን ጊዜ እራቱን ሳይበላ ነው የሚተኘው። ጠዋት ደግሞ ለማኝ እንትን ሳይል እሱንና አያታችንን የሚቀድማቸው የለም። ገና ሲፈጥረው ሽማግሌነት በውስጡ የተቋጠረበት ልጅ ይመስላል።
ዲያ ዛሬ ለምን ስም አይወጣለትም?” አለ ከወንድሞቼም በዕድሜ ከፍ የሚለው የአጎታችን ልጅ። ብርቱካን ደስ አላት። ሐሳቡን ግን በይፋ መደገፍ አልፈለገችም። ቀና ብላ የእናቴን ገጽ ታነብባለች። ጀማው በሙሉ ስም እንዲወጣልኝ በመፈለግ መንፈስ ላይ መሆኑን ያስተዋለችው እናቴ “ወይ እናንተ፤ ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ ለልጄ እኔ ስም ሳላወጣ እናንተ ስም ልታወጡለት ነው?” አለች። ነገሩን ግን እንዳልጠላችው ያስታውቅባታል።
ኮ አውጪለታ” አለ ለእኔ ከሌሎቹ በተለየ የሚቆረቆረው አንዱ ወንድሜ። ከቤተሰቡ የመጨረሻ ከመሆን ያዳነችኝ ባለቀ ሰዓት የተወለደችው ታናሽ እህቴ ናት። እንዲያም ሆኖ እንደ ውራ ልጅ የኩርኩም እና የስድብ መዓት የሚወርደው በእኔ ላይ ነው። እህቴ አንድም ሴት ናት አንድም ገና ሕጻን ናትና ለመበሻሸቅ አልደረሰችም። በዚያ ላይ ስም የለኝም። እንደማንኛውም የሰፈራችን ውሪ አቡሽ ነኝ። እኛ ሰፈር ውስጥ መንገድ ዳር ቆማችሁ “አቡ…….ሽ” ብላችሁ ብትጣሩ ከ10 ያላነሱ አቡሾች ብይ ከሚጫወቱበት ወይም የጨርቅ ኳስ ከሚያባርሩበት እየሮጡ ከች ይላሉ። “የእትዬ እንትናን አቡሽ ነው” ካላላችሁ መለየት አትችሉም። እንደ ማዕድን ከመሬት ተቆፍረን የወጣን የምንመስል አፈር የለበስን አቧራ የለበስን ብዙ አቡሾች በሰፈሩ ነበርን።
ውቄ እንጂ ለልጄ ወርቅ የሆነ ስም አዘጋጅቼለታለሁ”  አለች እናቴ እስካሁን ለምን ስም እንዳላወጣችልኝ ውስጧን እንደበላት እንዳያስታውቅባት እየተጠነቀቀች። እኔ ግን አውቄባታለሁ። በትንሽ ልቤ ቂም እንደቋጠርኩባት ግን አላወቀችም። ይህንን ስትል ቤቱ በአንድ እግሩ ቆመ። ልጆቹ ሁሉ አውካኩ። እኛ ቤት ብዙ ልጅ እንዳለ የሚያስታውቀው በየቀኑ እንጀራ መጋገሩ እና ሁሉም አብሮ ሲስቅ ጣራው የሚነቀል መምሰሉ ነው። አንድ ሰበካ ነን እኮ። ብዛታችን።
ን ያስቃችኋል?” አለች እናቴ እሷም ፈገግታዋን ሳትደብቅ። ሁሉም በአንድ ላይ “ንገሪን ንገሪን” አሉ። እኔ ግን የሚወራው ሁሉ ስለእኔ እንዳልሆነ ሁሉ ዝም ብዬ እቁለጨለጫለሁ። እህቴ ነገሩ ምን እንደሆነ አታውቅም ግን ታጨበጭባለች። በኩርኩም ብላት ደስ ባለኝ። ቆይ እናቴ ዞር ስትል አገኛት የለ? ኩርኩም አቅምሻት ላ’ጥ እላለሁ። ስታለቅስ እንጂ ለምን እንዳለቀሰች ለመናገር ገና አፏን አልፈታችም። ታላላቆቼ ሲያናድዱኝ ትንሽ ንዴቴን የሚያስታግሰው እሷን ማንም ያላየው ኩሩኩም በማቅመስ ነው። ያኔ ትልቅ የሆንኩ ይመስለኛል።
ክስቴ፤ ንገሪን እንጂ” አለ ዝም ማለቷን ያየው አንዱ ያጎቴ ልጅ። “ምን ያስቸኩልሃል?” አለች ፈገግታ ፊቷ ላይ እየተሯሯጠ። ሁሉም ጆሮ ብቻ ሆኖ ይጠብቃታል።
ርጫ እሰጣችኋለሁ፤ ትመርጣላችሁ። ለልጄ ሁለት ወርቅ ስም አዘጋጅቼለታለሁ” አለች። ከዚያ ሳቅ። ሳቁ ሁሉም። “አንድ ስም የለው ሁለት ስም?” አሉ እያሾፉ።
“እኮ ዝም በሉ። ምን ያስቃችኋል?” አለች እኔን በፍቅር በሚመስል የማጽናኛ ዓይን እያየችኝ።
“አንደኛው ምርጫ ግርማ ነው። ሁለተኛው ምርጫ ብርሃኑ፤ ምረጡ” አለች። ሁሉም አንድ ላይ ሲስቁ ቤቱ በሳቅ ታፈነ። አንድ አመድ የመሰለን ልጅ ግርማም ብርሃኑም ብለው ለማሰብ አልመጣላቸው አለ። ምኔ ግርማ አለው? ምኔስ ብርሃን አለው? እውነታቸውን ነው።

አካባቢያችን ሰዎች ከግርማና ከብርሃኑ ውጪ ስም አያውቁም? በሰፈሩ ካለው ሰው ግማሹ ግርማ፣ ግማሹ ብርሃኑ ነው። ሕጻናቱ አብዛኛው አቡሽና ማሙሽ ናቸው። “እነዚህ ሰዎች ያማቸዋል እንዴ?” አልኩኝ ለራሴ። “ትልቁን ግርማ ትንሹን አቡሽ፤ ትልቁን ብርሃኑ ትንሹን ማሙሽ? ምን ዓይነቶች ናቸው ባካችሁ?” ስል አጉተመተምኩ።
ገሩን ሁሉ ዝም ብላ ስታዳምጥ የነበረችው አክስቴ “ቢ’ራኑ ጄዻ፤ ቢራኑ ሐተኡ” አለች። አማርኛ መስማት እንጂ መናገር ይቸግራታል:፡ ለገበያ መጥታ እኛ ጋር አድራ ነው እንጂ ኑሮዋስ ገጠር ነው። “ብርሃኑ በሉት፤ ብርሃኑ ጥሩ ስም ነው” ማለቷ ነው። ጎረምሶቹ የበለጠ አሽካኩ። ብርሃኑ ሳይሆን ቢራኑ ስላለችኝ ሊያበሽቁኝ። ቀን ቢሆን ድንጋይ ወርውሬባቸው እሮጥ ነበር። አሁን ግን የት ይኬዳል። እናቴን የበለጠ ተናደድኩባት። ተስፈንጥሬ ጓዳ ገባሁ። የበለጠ ሳቁ በእኔ መናደድ። ትንሿ እህቴ እየሳቀች ታጨበጭባለች። በኩርኩም ባልኳት።
“ምን ታስካካላችሁ?” አለች እናቴ ቆጣ ብላ። “ትመርጣላችሁ አትመርጡም?”
ንሽ ጋብ አሉ። ሳቃጨውን በየጉንጫቸው እንደቋጠሩ ያስታውቃል። “ትመርጣላችሁ አትመርጡም?” አለቻቸው ኮስተር ብላ። ያን ጊዜ ብርቱካን ተናገረች “ሁለቱም ጥሩ ስም ነው። ግን የዘመኑ ስም አይደለም። እስካሁን ስም ሳይወጣለት ቆይቶ ቢያንስ የዘመኑ ስም ይውጣለትና ይካስ እንጂ” አለች ለእኔ ያዘነች መስላ።
“የዘመኑ ስም? ምንድነው ደግሞ የዘመኑ ስም?” እናቴ ናት። ለማጣጣል አፏን ሸርመም አድርጋ። ጎረምሶቹ በብርቱካን ሐሳብ ተስማምተዋል። እውነቷን ነው እያሉ አገዟት። እኔም ነገሩ አልከፋኝ። የጓዳው በር ላይ ቆሜ አዳምጣለሁ።
“እኮ ማን ይባል እስቲ የኛ ዘመነኛ” አለች እናቴ ሐሳቡን መስማት እንደፈለገች እንዳይታወቅባት ያጣጣለች መስላ። ብርቱካን ትንሽ እንደማሰብ አደረገችና …. እ እ እ እ … “ኤፍሬም ይባል” አለች ጥርስ ብቻ ሆና። ጎረምሶቹ ጸጥ አሉ። ስሙ አስደነገጣቸው ልበል? አፈር የመሰለ፣ አንድ ቀጫጫ ልጅ በሰፈሩ የሌለ ዘመነኛ ስም ሲሸከም ጓደኞቻቸው እንዳይስቁባቸው ሳይሰጉ አልቀሩም። ምናልባትም ቅናት ይሆናል። እኔም ራሴ ድንግጥ ብያለሁ። የምን ስም ነው? እያልኩ። በሰፈራችን በዚህ ስም የሚጠራ ሰው የለም።
ርቱካን ከየት እንደሰማችው እንጃ። ምናልባት ከሬዲዮ ይሆናል። ወይም ከምትማርበት የፊንላንድ ሚሽን ት/ቤት ይሆናል። ወይም በዚህ በፍልሰታው ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ላይ ድንገት ሰምታው ይሆናል። ይህንን ሁሉ የተመራመርኩት ካደግሁ በኋላ የስሜ ነገር ከንክኖኝ በራሴ ስመራመር ነው።
ሽኑ ሰባኪ ወይም የአጥቢያችን የቅ/ገብርኤል ካህናት ከኦሪት ዘፍጥረት እየጠቀሱ እንዲህ ሲሉ ሰምታ ይሆን? ብቻ ከየት እንዳመጣችው እንጃ።  ....  
ዮሴፍ ሁለት ልጆች ተወለዱለት። አንደኛውን ምናሴ ሁለተኛውንም ስም ኤፍሬም ብሎ ጠራው፥ እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ ሲል። ለዮሴፍም በግብፅ ምድር ምናሴና ኤፍሬም ተወለዱለት የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት የወለደቻቸው ናቸው። ከዚህም ነገር በኋላ እንዲህ ሆነ እነሆ አባትህ ያዕቆብ ታምሞአል ብለው ለዮሴፍ ነገሩት። እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በያዕቆብ ግራ፥ ምናሴንም በግራው በያዕቆብ ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው። የዮሴፍ አባት ያዕቆብም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኵር ነበርና። ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው። ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በታላቅየው በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው። ያዕቆብም በዚያን ቀን እንዲህ ብሎ ባረካቸው። በእናንተ እስራኤል እንዲህ ብሎ ይባርካል። እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርግህ። ኤፍሬምንም ከምናሴ ፊት አደረገው። ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ።
ግይቶ ቢወጣልኝም የተለየ ዘመናዊ ስም ስለሆነ በውስጤ ደስ ሳይለኝ አልቀረም። ከመቼው ነግቶ ኳስ ሜዳ ለጓደኞቼ እንደምነግራቸው እያሰብኩ ነበር። ብዙዎቹ ጓደኞቼ ማሙሾች እና  አቡሾች ወይም እነ ጭንቅሎ፣ እነ ዶጮ፣ እነ ቻይና … ሁሉም ቅጽል ስም እንጂ ስም እንዳላቸው እንጃ። ሁላችንም ት/ቤት ስላልገባን ስም ይኑረን አይኑረን ማንም አያውቅም። ወላጆቻችንም እየወለዱ ይቀላቅሉናል እንጂ ስለ ስማችን ማን ሊጨነቅ። የልደት ሰርተፊኬት የለ፣ የሆስፒታል ማስረጃ የለ …. ሁላችንም በየመንደሩ ማርያም ማርያም እየተባለ ከተወለደን በኋላ ከሰፈሩ አዋራ ጋር ተቀላቅለን፣ እዚያው በማሙሽነት እና በአቡሽነት አድገን ወግ የምናገኘው ት/ቤት ልንገባ ስንል ነው። ያኔ ስም ይወጣልናል። አንዳንዱም ወላጆቹ ያወጡለትን ስም አስተማሪው ካልወደደው በራሱ ጊዜ ይቀይረዋል።
ናቴ ከገባችበት የሐሳብ ጉዞ ስትመለስ “እና ይሄ ስም ይሁን ነው የምትሉት?” አለች ኤፍሬም ለማለት ሳትሞክር እንዲያው በደፈናው። ሁሉም በአንድ ድምጽ “አዎ አዎ አዎ” አሉ። የአጎቴ ልጅ ብርቱካን ደስ አላት። እኔም እንኳን ስም ኖረኝ እንጂ ስለትርጉሙ ብዙም አልተጨነኩም። እናቴ “ይሁና” በሚል ዓይነት አንገቷን ቀለስ አደረገች። አክስቴ ብቻ “ኤኙ ጄተኒ?” ትላለች። “ማን አላችሁት?” ማለቷ ነው። እንኳን ያኔ እንደ አዲስ ሰምታው እስከዛሬም ስሜን አስተካክላ ጠርታኝ አታውቅም። አያታችንም ቢሆኑ ኤፍሬም ማለት አይችሉበትም። “ፍሬው” እያሉ ይጠሩኝ ነበር።
ሜ ኤፍሬም እንዲሆን እናቴ መስማማቷ ሲታወቅ ወንድሞቼ እያቀፉ እያሾፉም አስር ጊዜ “ኤፍሬም ኤፍሬም” እያሉ ይስቁ ጀመር። ብዙም አልከፋኝም። እንደማፈርም እንደ መሳቅም እያደረገኝ ማብሸቃቸውን ተቀበልኩ። ስም ወጣልኛ።

 

4 comments:

Anonymous said...

Interesting article God bless you.

mamit said...

AY D.n Ephrem besak gedelkegn eko.Gibts ager west ye aba bishoy gedam yemibal ale Kidus Ephrem soriyawi selam lilew meto wede gedamu west ligeba sil yeyazewn betr kewech mert lay teklot geba siweta gen betru abiba tsedika agegnat ena ezaw titoat hede yelalu yachim betr eskezare zaf huna bekila begedam west alech .ke 14 amet befit new yayewat zafwan begedamu yalu menkosatoch yehinen tarik negrewenal .Antem ye talakun abat sim new yeyazkew Girum sim new.

Abayneh Reda said...

What g great Article, u make me fill like when i was live in ...

Anonymous said...

Dn. Ephrem, while I was reading your article I go so many years back and remember my childhood with my 6 bros and two sis. specially I never forget how my elder bro treat me, for your surprise his name is Birhanu, he used to nag me with every silly thing I did and I replay with the same manner and run to my mother.uffffffffffff u make my day lots of laugh. thank u keep on writing, we're gonna read.