Saturday, November 1, 2014

"ዘረኝነት፣ ጎጠኝነት በኢትዮጵያችን ላይ የተመዘዘ ሌላኛው የጥፋት ሰይፍ"

(በዲ/ን ተረፈ ወርቁ/ Read in PDF)
ኤፍሬም እሸቴ የተባሉ ጦማሪ ከሰሞኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ምድር ኦሮሞ እየተጋዘና ሰብአዊ መብቱ ክፉኛ እየተገፈፈ ያለ ሕዝብ መሆኑን የሚያረዳውን የድርጅቱን አሳዛኝ መግለጫ አስከትሎ ‹‹አይቴ ብሔሩ ለኦሮሞ?!›› (‹‹የኦሮሞ አገሩ እንግዲህ ወደየት ነው!››) የሚል ጽሑፍ አስነብበውናል፡፡ ይህን የጦማሪ ኤፍሬምን ጽሑፍ ያነበብኩት በኢትዮጵያ ምድር በዘረኞችና በጎጠኞች ክፉ ልብ ውስጥ የተመዘዘው የጥፋት፣ የቂም በቀል ሰይፍ የተነሣ እናት አገር ኢትዮጵያ የተጋረጠባት ሕመሟና ስቃይዋ፣ ሰቆቃዋና መከራዋ ውስጥ ድረስ ዘልቆ እየተሰማኝ ነው፡፡

በ፲፱፻፷ዎቹ ግራ ዘመም የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ተከትሎ ሲቀነቀን የነበረው ‹‹ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት!›› ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል!›› የሚለው መፈክር በኢትዮጵያ ምድር የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲከፈት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህን ስታሊናዊ መርሕ አንግቦ ለ፲፯ ዓመታት በጽናት የታገለው ኢህአዴግም ከድሉ ማግሥት በኋላ ይኼውን የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጉዳይ ማይሻርና የማይለወጥ የሕግ መንግሥቱ የማዕዘን ራስ ድንጋይ አድርጎ አቁሞታል፣ አጽንቶታልም፡፡ በምንምና በማንም ላይደራደርበትም ተገዝቶበታል፡፡
በእርግጥም ያ ትንታግ፣ ፋኖ ትውልድ ሕዝቦች በቋንቋቸው እንዲማሩ፣ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን በሚገባ እንዲያውቁና በማንነታቸው እንዲኮሩ ለማድረግ የከፈለው መሥዋዕትነት እጅግ ግዙፍ ነው፡፡ ከእነ ስህተቱና ድካሙም ቢሆን ያ ትውልድ የተነሳበትን፣ ያለመውን ርእዩን አሳክቷል ለማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሳይሉ በአንድነት ክቡር ሕይወታቸውን ለወገናቸው ክብር፣ መብትና ፍትሕ ሲሉ መክፈላቸው እሙን ነው፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ገደብ ያጣ የሚመስለው ብሔረተኝነትና ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ያለ ቅጥ እያራገቡት ያለው የዘርኝነት ጦስና አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ አድርገው እያቀረቡት ያለ ትርክት አገሪቱን ለሌላ ውድቀትና የእልቂት መዓት እያዘጋጃት ያለ ይመስላል፡፡ በዚህም በአገሪቱ ባረበበው የዘረኝነት፣ የጎሰኝነት ቀውስ ሰበብ በርካታዎች ብሔራቸው እየተለየ በጠራራ ፀሐይ ከምድራቸው፣ ከቀዬያቸው እንዲነቀሉ፣ እንዲሰደዱ፣ እንዲጋዙ፣ እንዲገደሉ ሆነዋል፡፡
ይኸው የበቀል ሰይፍ ዛሬም ወደ ሰገባው አልተመለሰም፡፡ እናም መፈናቀሉ፣ መጋዙና ግድያው እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህን የዘረኝነትና የጎጠንነትን አብዮት እያነደዱና እያጋገሉ በቅጡ ያልተጻፈና ያልተፈተሸ የፈጠራ ታሪክ ከየስርቻው እያወጡ በጋብቻና በአምቻ፣ በአጥንትና ደም በተሳሰር ሕዝብ መካከል የቂም በቀል ዘር የሚዘሩ፣ የጥፋትና የሞት ነጋሪት የሚጎስሙ ፖለቲከኞችም በእናት ኢትዮጵያ ምድር ሌላ የጥፋት፣ የበቀል ሰይፋቸውን ከሰገባቸው መዘው ሰልፋቸውን እንዳሳመሩ እያየን ነው፡፡
ገዢዎች፣ ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱና መኳንቱ በእርስ በርስ የኃይል ፉክክር፣ በገብር አልገብርም የሀብት መቀራመትና የበላይ የመኾን ሕልም የተፈጠረውን ጦርነትና ወረራ የአንድ ጎሳ/ብሔር ሕዝብ በሌላው ብሔር ላይ ያወጀው የዘር ማጥፋት ዘመቻ አድርጎም እየተነገረ፣ እየተጻፈም ነው፡፡ ግና እነዚህን በታሪካችን የኾኑ ወረራዎችንና ጦርነቶችን የሌላውን ሕዝብ ታሪክ፣ ቋንቋና ማንነት ለማጥፋት አስቦና አልሞ የተደረገ ወረራ አድርጎ በመውሰድ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያቃቅር የበቀል ታሪክን የሚሰብኩ ሰዎች እየለኮሱት ያለው የቂም እሳት ወላፈኑ እነርሱንም ሊፈጃቸው እንደሚችል ቆም ብለው ማሰብ ቢችሉ ደግ ነበር፡፡
መላውን ዓለም ጉድ፣ እ-ግ-ዚ-ኦ! ያሰኘ የሩዋንዳውያንን ያን ዘግናኝና ኢሰብአዊ የኾነ ጎሳን/ብሔርን መሠረት ያደረገ እልቂትና ፍጅት አሳፋሪ ታሪክ ያየና የሰማ ዳግመኛ በጎሳና በብሔር ተቧድኖ እርስ በርስ ለመጠፋፋት፣ ለመበላላት ተነስ፣ ታጠቅ ብሎ ማለት ጤነኝነት አይመስለኝም፡፡ የጎረቤቶቻችን የሶማሊያ፣ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጎሳን ወይም ብሔርን መሠረት ያደረገው የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት፣ እልቂትና ፍጅት የሚነግረን እውነታ ቢኖር ዘረኝነት/ጎሰኝነት ክፉ ነቀርሳ መሆኑን ነው፡፡ 
ከታሪክ መማር ያቃታቸው ይኸው እነዚሁ ታሪክን እንዳሻቸው ይጽፉና ይተነትኑ የጀመሩ የዘመናችን ፖለቲከኞች ግን ዐፄ ምኒልክ በኦሮሚያና በደቡብ ሕዝቦች ላይ አድርሰውታል የሚሉትን ግፍና ጭፍጨፋ እያነሡና እየጣሉ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ/Genocide/Mass Massacre እንደተካኼደበት ዘግናኝ የኾነ ታሪክ ወይም ትራጄዲ እየነገሩን፣ እየተረኩልን ነው፡፡ ለዚህ የታሪክ ቅሌት መታሰቢያም ይሆን ዘንድ ያሉትንም የተቆረጠ ጡት ሀውልት ምስል በአርሲ አኖሌ አቁመዋል፡፡
ከዚሁ የጎሰኝነት ጉዳይ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ አንድ ወዳጄ የገረኝን ገጠመኝ ላነሳ ወደድኹ፡፡ ከሰሞኑን ኢህአዴግ የሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃና ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን፣ መምህራንና ሠራተኞችን በሰበሰበበት የውይይት መድረክ ይኸው ዐፄ ምኒልክ በኦሮሚያና በደቡብ ሕዝቦች ያደረሱት ግፍ ሲገለጽ፣ ሲተነተን ነበር፡፡ በአንፃሩም ደግሞ የውይይቱ መሪዎችና ካድሬዎች ኢህአዴግ በጭቆና ቀምበር ሥር ሲማቅቁ ለነበሩ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ብሔርና ብሔረሰቦች እኩልነትን፣ ፍትሕንና ዲሞክራሲን ማስፈኑን አብዝተው ሲተርኩ፣ ለውለታውም በካድሬዎችና በእበላ ባዮቹ አፍ ሲወደስ፣ ሲቀደስ ነበር የሰነበተው፡፡
ታዲያ በዚህ የዐፄ ምኒልክና የነገሥታቱ ግፍና ጭቆና ተጋኖ ሲነገር በነበረበት መድረክ የኾነውን አንድ አስገራሚ ገጠመኙን በሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት አስተማሪ የሆነ ወዳጄ እንዲህ አጫውቶኝ ነበር፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ዐፄ ምኒልክ በኦሮሚያ ስላደረሱት ግፍ ሲዘረዘር፣ ታሪካቸው ሲረገም፣ ስማቸውም ጥላሸት ሲቀባና ሲወቀሱ የሰሙ፣ በት/ቤቱ ውስጥ በፅዳት ሥራ ተቀጥረው እያገለገሉ ያሉ የስብሰባው ተሳታፊ አንድ እናት ድንገት ብድግ ብለው ኀዘን፣ ቁጣና እልክ በተጫነው ድምፅ፡-፡
እንዴ እናንተ ሰዎች ምንድን ነው የምትሉን፣ እንዴት ዓይነት ታሪክ ነው የምትነግሩን?! እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ትውልዴ ደግሞ ኦሮሞ ነው፡፡ ከአማራውም፣ ከጉራጌውም፣ ከትግሬውም ተጋብቻለኹ፤ ተዋልጃለኹም፡፡ በደስታና በኀዘን፣ በዕድርና በዕቁብ፣ በማኅበርና በሰንበቴ ዘርም ቋንቋም ሳንል ተዋደንና ተከባብረን እስከ አሁን ኑረናል፡፡
ዛሬ ታዲያ እርስ በርሳችን እንድንጠላላ፣ እንድንተላለቅ ነው እንዴ የምትፈልጉት፡፡ ዛሬ እንዲህ በክፉ ስማቸውን የምታነሷቸው ነገሥታቶቻችን እኮ ለዚህች አገር ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው በነጻነቷ የታፈረችና የተከበረች፣ እኔ፣ እናንተ፣ ልጆቻችን ጭምር የሚኖሩባትን አገር እኮ ያስረከቡን ናቸው…፡፡
እኚህ እናት ሳግና ዕንባ እየተናነቃቸው፣ የእናት ምድራቸው ኢትዮጵያና የሕዝቦቿ የነገ ዕጣ ፈንታ እያሳሰባቸው፣ ‹‹እረ እንደው በኢትዮጵያ አምላክ ይሁንባችኹ! እንዲህ ዓይነቱን ጠብን፣ ጥላቻንና ቂም በቀልን የሚዘራ ስብከታችሁን ተዉት፣ እንደው በምታምኑት፡፡›› በማለት ተናግረው ቁጭ አሉ፡፡
እንደእኚህ እናት ዓይነቶች ከቂም ይልቅ ቅርታን የሚሰብኩ፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን የሚዘሩ ሰዎች ልብም ጆሮም ተነፍጓቸው፣ በገዛ አገራቸው ስደተኛና መፃተኛ ሆነው በኀዘንን በቁጭት ውስጣቸው እየነደደና እየተንገበገበ ግራ ተጋብተው፣ ተስፋ ቆርጠው ተቀምጠዋል፡፡ እናም ዘመነኞቹ ያለ ምንም ከልካይና ሃይ ባይ የትናንትናዎቹን ነገሥታትንና ገዢዎችን ታሪካቸውን እየበረዙ፣ እየከለሱና እያራከሱ በኢትዮጵያ ምድር የሞት፣ የጥፋት፣ የእልቂት ነጋሪት በነጋ ጠባ እየጎሰሙብን፣ እያስጎሰሙብን ነው፡፡
ፊደልን ቆጥረናል ተምረናል የሚሉ ምሁራኖቻችንም ከእውነት ጋር ለመቆም፣ ለመወገን በሕዝቦች መካከል መቃቃርን፣ ጥላቻን፣ ቂምን የሚፈጥር የበቀል ታሪክ በይቅርታ፣ በምሕረት ይዘጋ ዘንድ አስታራቂ፣ መካከለኛ መሆን አቅቷቸው፤ እንደውም ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የዚሁ ክፉ የበቀል ታሪክ ትርክት ሰለባና የጥፋት፣ የእልቂት ነጋሪት ጎሳሚ መሆናቸውን በአደባባይ ጭምር እየታዘብን ነው፡፡
የፍቅርና የሰላም መልእክተኞች ናቸው የተባሉ የሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎችም የሚገሠጸውን ገሥጸው፣ የሚመከረውን መክረው፣ ገዢዎችንና ፖለቲከኞቻችንን ከክፉ መንገዳቸው መልሰው፣ ቂም በቀልን በይቅርታ ሽረው ሰላምንና ዕርቅን ለማውረድ ቀርቶ እነርሱም ራሳቸው በዘር፣ በጎሳና በቋንቋ ተለያይተውና ተከፋፍለው፣ እርስ በርሳቸው ተቧድነው፣ እንዳይሰማሙና እንዳይስማሙ ሆነው ተኳርፈው ማዶ ለማዶ ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ እናስ ለዚህ ለኢትዮጵያ ከተደገሰውና ከተመዘዘው የዘረኝነት የጥፋትና የእልቂት ሰይፍና የቂም በቀል የታሪክ አዙሪት የሚታደጋት ማን ጀግና ይሆን?!
እውን ግን አማራ ለኦሮሞ ጠላቱ ነበርን፣ ኦሮሞውስ ለአማራው ሕዝብ ደመኛው ነው እንዴ?! አማራው ከኦሮሞው፣ ኦሮሞው ከአማራው ጋር አልተጋባም፣ አልተዋለደም እንዴ?! እነዚህ ሕዝቦች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ጋር በአንድነት ኾነው በአንድ ዓውደ ግንባር ለአንዲት ኢትዮጵያ ነጻነት ደማቸውን በአንድነት አላፈሰሱም፣ አጥንታቸውንስ አልከሰከሱምን እንዴ?! የኦሮሞ ምድር ያፈራቸው ጀግኖች የእነ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ኮ/ል አብዲሳ አጋ፣ ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ የተዋደቁት፣ የሞቱት፣ ደማቸውን እንደ ውኃ ያፈሰሱት ለማን ነበር?! ለኢትዮጵያ አልነበረም እንዴ? በዓድዋ ግንባር የወደቁ ኦሮሞ ጀግኖችና ፈረሰኞችስ ክቡር መሥዋዕትነትስ ለማን ነበር?! ታሪክ ይመስክራ!!
በአገር ፍቅር ስሜት የነደዱ የኦሮሞ ልጆች በድል በደመቁበት የኦሎምፒክ መድረክ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ ሲውለበለብና ሰማዩን ሲያደምቀው ከአበበ በቂላ፣ ከደራርቱ፣ ከቀነኒሳ፣ ከወርቅነሽ ጋር በኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ስሜት፣ ኩራትና ፍቅር ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት አብረው በደስታ አላነቡም እንዴ?! በሲቃ፣ በደስታ ተውጠው የእናት ምድራቸውን መሬት አልሳሙም እንዴ?!
እናም እባካችሁ እናንተ በቂም በቀል ታሪክ አእምሮአችሁ የተያዘ፣ ሕሊናችሁ በዘረኝነትና በጎሰኝነት መንፈስ የታወከ ቆም ብላችሁ የዚህን ሕዝብ አንድነቱን፣ ፍቅሩን፣ አኩሪ ታሪኩንና ባህሉን አስቡ፡፡ ዛሬ ምኒልክ የኦሮሞ ጠላቱና ጨፍጫፊው ነው፣ ዐፄ ዮሐንስ እንግሊዞችን መርተው ዐፄ ቴዎድሮስን ያስገደሉ ‹‹ባንዳ›› ናቸው…ወዘተ በሚል የየነገዳችንን ጀግና ለይተን፣ በጎሳ ተቧድነን ሙግት የገጠምን፣ የትናንትና የታሪክ ሐቅን በዛሬው ነባራዊ እውነታ ለመዳኘት የታሪክ ፍርድ ወንበር ላይ የተሰየምን ሁሉ እስቲ አንድ ጊዜ ቆም ብለን እናሰብ፣ ራሳችንንም እንጠይቅ፡፡
እነዚህ ዛሬ ስማቸው በክፉ የሚነሳ፣ አስቂኝ በሆነ መልኩና ታሪካዊ ትንታኔ የሕዝቦችና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና መብት ጠላቶች እንደነበሩ ተደርገው ስማቸው እየተብጠለጠለ ያሉ ነገሥታቶቻችን ለአንድ ኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር አልተሰዉም እንዴ! እኔ ትግሬ ነኝ የጎንደር መቃጠልና መውደም ምን አገባኝ ብለው ነበር እንዴ ዐፄ ዮሐንስ፣ በመተማ ግንባር እንደ ተራ ወታደር አንገታቸውን ለሰይፍ የሰጡት ለመሆኑ ለማን ነው፣ ለኢትዮጵያችን ነጻነት፣ ክብርና አንድነት አይደለም እንዴ?!
ዐፄ ቴዎድሮስ በመቅደላላ አፋፍ ላይ ሕይወታቸውን የሠዉት ለማን ነበር?! እነ ንጉሥ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ቀፎ እንደተነካ ንብ ዘር፣ ቋንቋ፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል ሆ ብሎ በአንድነት ወደ ዓድዋ ግንባር የዘመተው፣ የከተተው ሕዝብ ያ ዓለምን ያስደነቀው ጀግንነቱና መሥዋዕትነቱ ክብሩና ኩራቱ ለማን ነበር!
ታሪክ እንደሚመሰክረው ይህ ሕዝብ/ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ክብር፣ ነጻነትና ብሔራዊ ኩራት፣ ለወገናቸው ፍቅርና ክብር ሲሉ በአንድነትና በፍቅር ድርና ማግ ሆነው በደማቸውና በአጥንታቸው ጽኑ ቃል ኪዳን ይህችን በነጻነቷ የታፈረችና ተከበረች ውብ አገርን በክብር አስረክበውናል፡፡
ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግሬው፣ አፋሩ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ሐረሪው፣ ሶማሊው…ወዘተ በኢትዮጵያ ምድር ክፉውንም ደጉንም አሳልፎ የኖሩ ባለ ታላቅ ታሪክ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይህ በደም የተሳሰረ ሕዝብ የአንዱ ሕዝብ አኩሪ ታሪክ የራሱ ሕዝብ ኩራት፣ አንዱ ሕዝብ ውርደት የራሱ ሕዝብ ውርደት አድርጎ በመቁጠር የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ እናም ገዢዎችና ፖለቲከኞች ሆይ እባካችሁ የሌለ ታሪክ እየጻፋችሁና እያጻፋችሁ፣ ቂም በቀልን እየሰበካችሁ በሰላም የሚኖረውን ሕዝብ ክፉ አውሬ አታድርጉት፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!

2 comments:

Anonymous said...

I always believe that what was happened in the former history of our country didn't happen in the way the so called illiterate politicians presented . If it was happened on the wrong analysis of the present rulers ,let alone to got victory over Italian aggregation as one nation at the Adwa battle ,the country itself couldn't survive before the war .I raised that battle as an example just to show the smooth relation of Emperor Minilek's leadership and the people of Ethiopia/nations ,nationalities.../ at that particular historic time which laid the foundation of today's strength . It is obvious that in the building history of every country there were many up and downs happened.As one of the ancient country , the same truth was happened and there were some minor damages on the indigenous people due to the newly coming settlers and new infrastructural lay outs . We have a very good example which we can see it today in our country . How is the land garb in Gambela,Northern Gonder etc have been done? How was the flower farm in the Eastern Showa started ? What was happened to the native people while all the Gilgel Gibe and Abby dams being constructed? Do we really have clear idea about the Midrock gold mining company and the people of Shakiso? What is happening now due to the expanding plan of the Addis Abeba city ? As a concerned matured adult most of the present so called politicians both in the country and abroad, don't like to talk based on tangible historic facts rather than aggravating baseless hear-says of extremists and power seekers of the present govt year after years .More than forty years we had killed each other in the name of certain nations for the freedom and now the silent killing is counting for the same cause with no end .This clearly shows that we have no solution for our own problems and can't stop blaming the past . So the solution is some where else and it is only found from the Almighty God who knows our weakness . Let us see ourselves and find out all our weaknesses and forgive ourselves and then stand up to forgive others for the sin which we think they might did on us. Then the impossible will be possible and the God of the universe will give us the leader,wisdom,know how,capital and etc so that we can live accordingly and use the fruit of our country with others .

Anonymous said...

I always believe that what was happened in the former history of our country didn't happen in the way the so called illiterate politicians presented. If it was happened on the wrong analysis of the present rulers,let alone to got victory over Italian aggregation as one nation at the Adwa battle ,the country itself couldn't survive before the war .I raised that battle as an example just to show the smooth relation of Emperor Minilek's leadership and the people of Ethiopia/nations ,nationalities.../ at that particular historic time which laid the foundation of today's strength . It is obvious that in the building history of every country there were many up and downs happened.As one of the ancient country , the same truth was happened and there were some minor damages on the indigenous people due to the newly coming settlers and new infrastructural lay outs . We have a very good example which we can see it today in our country. How is the land garb in Gambela,Northern Gonder etc have been done? How was the flower farm in the Eastern Showa started ? What was happened to the native people while all the Gilgel Gibe and Abby dams being constructed? Do we really have clear idea about the Midrock gold mining company and the people of Shakiso? What is happening now due to the expanding plan of the Addis Abeba city ? As a concerned matured adult most of the present so called politicians both in the country and abroad, don't like to talk based on tangible historic facts rather than aggravating baseless hear-says of extremists and power seekers of the present government year after years .More than forty years we had killed each other in the name of certain nations for the freedom and now the silent killing is counting for the same cause with no end .This clearly shows that we have no solution for our own problems and can't stop blaming the past . So the solution is somewhere else and it is only found from the Almighty God who knows our weakness. Let us see ourselves and find out all our weaknesses and forgive ourselves and then stand up to forgive others for the sin which we think they might did on us. Then the impossible will be possible and the God of the universe will give us the leader, wisdom, know how, capital and etc so that we can live accordingly and use the fruit of our country with others

Blog Archive