Friday, November 28, 2014

"ድልድዮቻችንን አናቃጥል"

(ከኤፍሬም እሸቴ/ PDF)
ፈረንጆች አንድ አባባል አላቸው። “ድልድይ ማቃጠል” የሚባል። አንዱ ከሌላው ጋር ሲነጋገር “ለምንድነው ድልድይህን የምታቃጥለው?” ሊለው ይችላል። ወይም ሌላው “ድልድዬን ማቃጠል አልፈልግም” ይላል። ትርጓሜው አንዴ ያለፍክበትን ድልድይ ካቃጠልክ ወደዚያ ቦታ አትመለስም ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት በሰላም፣ በፍቅር፣ ያልምንም ቁርሾ ቢለቅ ድልድዩን አላቃጠለም፤ እንዳይሆኑ ሆኖ ቢለያይ ግን “ድልድዩን አቃጠለ” ይባላል። “እንጀራ ገመዱን በጠሰ” እንዲል ሐበሻ።

የዚህ አባባል መነሻው ጦርነት እንደሆነ ያገላበጥኩት መዝገበ ቃላት ይናገራል። በጦርነት ወቅት እያስገመገመ ከሚመጣ ጠላት ፊት ለማምለጥ የሚያፈገፍግ ጦር፣ ጠላት እንዳይደርስበት የሚያደርገው አንዱ ነገር የመጣበትን ደህና መንገድ እንዳይሆኑ አድርጎ ማበላሸት፣ በተለይም ድልድዮችን ማፈራረስ ነው። በአገራችን የተለያዩ ጦርነቶችም የምናውቀው ሐቅ ነው። እነሆ ይኸው እውነታ አባባል ሆኖ በፈረንጅኛው አፍ “ድልድይ ማቃጠል” የሚባል አባባል የተለመደ ሆኗል። በርግጥ ብዙ ድልድይ ለሌለበት አገር “ድልድይ ማቃጠል” አባባል ባይሆን አይገርምም።
የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች፣ ምናልባትም ብዙ ታዋቂ የዓለም ከተሞች ከውኃና ከባሕር ተጠግተው የሚሠሩ በመሆናቸው ድልድይ በብዛት አላቸው። እጅግ በጣም የምወዳት የጀርመኗ ዋና ከተማ በርሊን ከ900 በላይ ድልድዮች ያሏት ውኃ በውኃ የሆነች ውብ ከተማ ናት። ድልድዮቹ ብቻ በዓይነት በዓይነት ተከፋፍለው የቱሪስት “መስሕብ” ሆነው ይታያሉ።
በውኃዋ ብዛት የምታስደስተኝ የሰሜን ምዕራብ አሜሪካዋ ሲያትልም ባሕር ላይ ከሚንሳፈፉት (floating bridges) ድልድዮቿ ጀምሮ ብዙ ረዣዥም ድልድዮች ያሏት ከተማ ናት። በድልድዮቿ ላይ እየነዱ የምትጠልቅ ፀሐይ መመልከት ወይም የከተማውን ማዕከል መብራት አሻግሮ ማየት ደስታን ይሰጣል። ወደ ካሊፎርኒያ የሄደ ሰው ደግሞ ሳንፍራንሲስኮን ሲጎበኝ ድልድዮቹን እያደነቀ፣ በሰው ልጅ ጥበብ እየተገረመ፣ እየተደመመ ይመለሳል። በአየር ላይ የሚቀዝፉ የሚመስሉ ድልድዮችን ይመለከታል፤ ከርዝመታቸው የተንጠለጠሉበት መንገድ እጅግ ያስደንቀዋል።

 አሁን የጠቀስኳቸው ብዙዎቹ ድልድዮች አሁን ጃፓኖቹ አባይ ሸለቆ ውስጥ እንደሰሩት፣ ሸዋን ከጎጃም እንደሚያገናኘው ያለ ድልድይ ማለት ነው። እንግዲህ “ድልድይን ማቃጠል” የሚለው ብሒል ዋጋ የሚኖረው እዚያ ላይ ነው። እንዲህ የደም ሥር የሆነ መገናኛ መበጠስ ማለት ነው ብሒሉ።
ጥበበኛ አገር ድልድይ ይሠራል። ድልድዩንም ይጠብቃል። ዞሮ መገናኛው ነውና። ሰው ከሰው ጋር ያለው ግንኙነትም በድልድይ ይመሰላል። የግንኙነቱ መቋረጥ ደግሞ እንደ ድልድዩ መፍረስ፣ ወይም መቃጠል ሊወሰድ ይችላል። ሰው ከሰው ጋር ሲኖር አለመግባባትና መለያየት ሊገጥም ይችላል። ነገር ግን የከፋ ነገረ ካልመጣ በስተቀር “ድልድይን ማቃጠል” እጅግ በጣም ሞኝነት ነው።
በተለይ በአንድ አገር የሚኖሩ ሰዎች፣ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የተለያየ ቀለም፣ የተለያየ እምነት ያላቸው ሰዎች በተቻለ መጠን ድልድዮቻቸው እንዳይቃጠሉ በብዙው ሊጨነቁና ሊጠበቡ ይገባቸዋል። በሥጋ ዝምድና፣ በአገር ልጅነት፣ ክፉና ደጉን አብረው በማሳለፍ የኖሩ ሰዎች ለሚያልፍ ጊዜ ክፉና ደግ ተነጋግረው ድልድዮቻቸውን ካፈረሱ ነገ መመለሻው ይጨንቃል።
ኢትዮጵያና ኤርትራን አስባለሁ። መለያየት ያባት ነው። ትዳርም ይፈታል፤ አገርም ይከፈላል፤ ንብረትም ይከፋፈላል። ነገር ግን ነገ እንመለስብህ ቢሉት የሚጨንቀው መለያየቱና መፋታቱ ሲመጣ ድልድዮቹን እንዳይመልሱን አድርገን አቃጥለናቸው ከሆነ ነው።
የ30 ዓመት የርስበርስ ጦርነት ሳያንሰን፣ ሰላም ወረደ በተባለበት ዘመን የማይረባ ጦርነት ገጥመን በ30 ዓመቱ ጦርነት ያላለቀ ሕዝብ ቁጥር በጥቂት ወራት ውጊያ እምሽክ አስደረግን። ሰዎችን ከየአገሮቻችን አባረርን። ድንበሮቻችንን በጦር ዘጋን። የዓይናችንን ቀለም እየለካን ግፍ ተዋዋልን። ተቀያየምን። የበደል ቁርሾ አስቀመጥን። ድልድዩን ካቃጠልን በኋላ ዛሬ መንገድ አጣን - እንገናኝበት ብንል ከየት ይመጣል?
በሰሜን አንድ ድልድይ አቃጥለን ስናበቃ አሁን ደግሞ በመሐል አገር፣ በደቡቡ፣ በምዕራቡ፣ ሌሎች ድልድዮቻችንን ለማቃጠል እሳት ማንደድ ይዘናል። አማራው ከኦሮሞው፣ ኦሮሞው ከትግሬው፣ አማራው ከኑዌሩ፣ ከቤንሻንጉሉ፣ ኦሮሞዉ ከሶማሌው፣ ወላይታው ከሲዳማው ያለውን ድልድይ እንዲያቃጥል እሳት እናነዳለን። ተመልሶ እንዳይገናኝ። ይቅርብን ይቅርብን ብሎ እርቅ እንዳያወርድ፣ ድልድዩን እናሰብረዋለን። እሳት እናቀብለዋለን።
  ጥሩ የአገራችን አባባል አለ። “ጉድጓድ ስትቆፍር አርቀህ አትቆፍር፤ ማን እንደሚገባበት አይታወቅምና” የምትል። በድልድዩ እንተካው። “ድልድይ ስታቃጥል ብዙ አስብበት፤ አንተው ኋላ ልትሻገረው ብትፈልግ አታገኘውምና”።

 ዛሬ ብዙ የድልድይ ተንከባካቢዎች ያስፈልጉናል። የሰው ለሰው ድልድዮቻችን ተጠቃለው እንዳይፈርሱ የሚጠብቁ ባለ ድልድዮች። ምሁራን፣ የሃይማኖት አስተማሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የነገ ተስፋ በሩቅ የሚታያቸው ታዳጊዎች … ድልድዮቻችን እንዳይፈርሱ ካልጠበቁ ምን ተስፋ ይኖር ይሆን። ድልድይ በማፍረሱ ረገድ ግንባር ቀደሙ ምሁሩና የሃይማኖት መሪው ከሆነ ሌላው ዕውቀት ያልዘለቀው ጨዋው እና ምዕመኑ ምን ተስፋ ያደርጋል? ድልድዮቹን የምንፈልጋቸው እኛስ ከዚህ በላይ እንድትለያዩን አንፈቅድም የምንልበት አንደበት ካላወጣን ከእኛ በላይ ተጎጂ ማን ይኖራል?
በርግጥ ሊቃውንት እንደሚሉት “ኢየሐድጋ ለሀገር ዘእንበለ አሐዱ ሔር፤ አገርን ያለ አንድ ቸር (ጠባቂ) አይተዋትም”ና ታዳጊ ሰማዕት ጠባቂ መልአክ ይልክልናል። ድልድዮቻችንን ከመፍረስ ታድጎ ለረዥም ዘመን በሕብረት የኖረ አገር እንደድሮው በአንድነቱ እንዲኖር። እስከዛው ግን ድልድይ አፍራሾች፣ ድልድይ አቃጣዮች አንሁን።


6 comments:

Kinfe Michael said...

Great comment, as usual. I like your articles because they always sound, look and smell Ethiopian. Thanks.

Anonymous said...

የሰው ለሰው ድልድዮቻችን ተጠቃለው እንዳይፈርሱ የሚጠብቁ ባለ ድልድዮች። ምሁራን፣ የሃይማኖት አስተማሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የነገ ተስፋ በሩቅ የሚታያቸው ታዳጊዎች … ድልድዮቻችን እንዳይፈርሱ ካልጠበቁ ምን ተስፋ ይኖር ይሆን።ይህን ተስፋ ለማየት አልታደልን ምን መሠለህ ታሪክ የሚያው ትውልድ እንዳይኖር ታሪክ አስተማሪው የውሸት አባት ነው የውሸት አባት ደግሞ የሚወልደውም ውሸታም ስለሆነ ምን ታረገዋለህ በትውልዱ አላዝንም የሚያየውን ስለሆነ ምን ብትነግረው ስለማይሰማህ አትድከም ሠላላ ድልድይ እያለቀሠ ነው የተለያየው ማስታወሱ አስፈላጊ አይመስለኝም ምንም ፋይዳ ስለሊለው ስለዚህ ለሁሉም የሰማይ አምላክ ይድረስልን ፡፡

Anonymous said...

what a great looking. God bless you.

asmamaw tesfaye said...

great view.thank you. God be with our beloved country Ethiopia.

Anonymous said...

Great view, and good initiation on a work that requires great deal of attention i.e BRIDGE Building!

I hope to see more of these and views your followers on this.

Anonymous said...

በአንድነታችን ያጽናን . እናመሰግናለን መልካም ሀሳብ ነው።

Blog Archive