Friday, November 7, 2014

ዩኒት ሊደር፣ ስም ጠሪ እና የክፍል አለቆች

(ከኤፍሬም እሸቴ/ Read in PDF)
በግርፊያ ተቀምሞ፣ በቁንጥጫ ወይም “እጅ-በጉልበት-ሥር-በማሾለክ-ለረዥም-ጊዜ-መቀመጥ” ወይም “በእንብርክክ በመሰለፍ” የሚሰጥ የዕውቀት ዘር ማለት የትምህርት ትርጉም ይመስለኝ ነበር ልጅ ሆኜ። መምህር ማለት ደግሞ ክፍል ውስጥ ስም የሚጠራ እና ልጆችን በተለያየ መልኩ የሚገርፍ ትልቅ ሰውዬ። የክፍል አለቃ ማለት ደግሞ በዕድሜው ወይም በቁመቱ ወይም በሁለቱም  ከመካከላችን ዘለግ ያለ እና የመጨረሻው ወንበር ላይ የሚቀመጥ ጠና ያለ ተማሪ።
ስም ጠሪውን፣ ሌሎቹን መምህራን እና አለቃችንን በመግረፍ ዘርፍ የሚያሰማራቸው ዋናው ሰው ደግሞ ዩኒት ሊደር ይባላል። ትምህርት ቤትና ቅጣት የጀመርነው ገና ሀ ብለን ከቤት ስንወጣ የኔታ ጋር ነው። እንደው ዕድሌ ሆኖ የኔታ አልገረፉኝም። ምናልባት አላጠፋሁ ይሆናል። ምናልባት ፊደሎቹ ቶሎ ገብተውኝ ወይም ከመቅጠኔ የተነሣ ለአቅመ ዕይታ አልበቃሁምም ይሆናል። ከፊደል ቆጠራ ጀምሬ እነ አቡጊዳ እስክደርስ ግን የኔታ አውቀውኛል። የኔታ ውዳሴ ማርያም ደጋሚ፣ ዳዊት ደጋሚ ናቸው። በዕድሜዬ በሙሉ ስሜን ሲጠሩ የሰማኋች አንዲት ቀን ናት እርሷንም ቢሆን ኤፍሬምሳይሆን “የፍሬም” ነው ያሉኝ። የሆነው ሆኖ የኔታ አልገረፉኝም። ግን ሲጋረፉ አይቻለሁ። አቤት አለንጋቸው…..

የየኔታ አለንጋ ከርዝመቱ አጠቋቆሩ። ግርማ ሞገሱ ራሱ “ባይገርፉበት ያስፈራሩበት” የሚባል ዓይነት ነው። አንደኛዋ ደግሞ ጠየም ያለች፣ ቀጠን ያለች አለንጋ ናት። ተማሪዎች የምንገረፈው በሷ ነው። በጥቁሩ የተገረፈ አንድም ተማሪ አላየሁም። ምናልባት ሁላችንም ለአቅመ-ጥቁሩ አልደረሰንም መሰል። አለንጋዬን አላባክንም ያሉ ይመስላል የኔታ። እንኳን በጥቁሩ በጠይሟ እንኳን ሾርርርርርርር ብለን ነበር የምንታዘዛቸው። ሰጥ ለጥ ብለን።
እንደማስታውሰው አንደኛ ክፍል ስገባ የፊደል ዘር ልቅም አድርጌ አውቅ ነበር። እንደነ እንትና “ዮሐንስ” ለማለት “ዩሐንስ” ወይም “ዪሐንስ” እያልኩ አልጽፍም ነበር። ዛሬ ዛሬ “ው እና ዉ” የማይለይ ትልልቅ ሰው ሳይ “ኤዲያ፤ የኔታ አልባ ሁላ” እላለሁ በሆዴ። ያቺን ጠይም አለንጋ የሚያዝለት ሰው ቢኖር ጥሩ ነበር።
ዜሮ ክፍል ለመግባት መስከረም ላይ የሰፈር ውጫጭ ተሰብስበን ት/ቤት ሄድን። ሀ-ሁ ካለ ማንም ልጅ ዜሮ ክፍል መግባት ይችላል። ከዚያ በሳምንቱ የተወሰንነውን ወደ አንደኛ ክፍል ማሸጋገር ፈለጉ መሰል አስተማሪያችን ፈተነችን። ንግሥት የመሰለች ሴት። ጥቁር ሻርፕ ጣል ያረገች። ለቅሶ ኖሮባት ይሆናል። ያ ዘመን መቸም ሞት በየመንገዱ የሚንሸራሸርበት ነበር።
ያቺ ንግሥት የመሰለች መምህርት የጠየቀችኝን አልረሳውም። የ “ጨ” ዘሮችን። እኔ ሌላ ፈተና መስሎኝ እንጂ … ይቺማ …. ዕድሜ ለየኔታ። እኔ ጨ-ን አልፌ፣ ፐ-ን አልፌ “መልዕክተ ዮሐንስ ሐዋርያ ወልደ ዘብድዮስ ቀዳማዊ” የምል ሰውዬ መሆኔን አላወቀች። …. ሁሉንም መለስኩላት። ራሴን በእጆቿ ዳሰስ አርጋ ማለፌን ነገረችኝ።
ንግሥት የመሰለችው አስተማሪያችን፣ ደብተራችን ሽፋን ላይ ያሉትን የነገሥታቱን ቤተሰቦች ፎቶ ትመስላለች። ትምህርት መጀመርን ሳስብ ያቺ መምህርት እና ብሩህ ፈገግታዋ ነው የሚታሰበኝ። በኋላ የመጡትን ጭራቅ ጭራቅ አስተማሪዎች፣ ዩኒት ሊደሮች እና አለቆች ባስብ ኖሮ የልጅነት ትዝታዬ ሁሉ ይበላሽ ነበር።
ሁለተኛ ክፍል ላይ ቲቸር ክፍሌ አሉ። እጅግ ደግ፣ እጅግ ሩኅሩኅ መምህር። አስተማሪነታቸው ሳይሆን አባትነታቸው ነው የሚታየኝ። ለዚያ ሁሉ ውጫጭ እኩል ፍቅር እኩል ዕውቀት የሚመግቡ ደግ ሰው። እንደርሳቸው አረጋዊ የሆኑት መምህር መርዕድም እንደዚያው ደግ ሰው ናቸው።
ሦስተኛ ክፍል ላይ የገጠመችን ክፉ አስተማሪ መፈጠራችንን እንስክንጠላ ድረስ ስታንገበግበን የምንጽናናው በነቲቸር ክፍሌ ደግነት ነበር። ቅጣቱ ሲበረታብን ወደ ሁለተኛ ክፍል ደብል መትተን መመለስ አምሮን ነበር። ደብል የሚመታው ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይደለም እንጂ። ያቺ አስተማሪ “እጅን በእግር ሥር አሾልኮ ለረዥም ጊዜ በመቆየት” ቅጣት የተካነች ነበረች። ከማዕከላዊ እስር ቤት በዕድገት ወይም በብቃት ማነስ የተባረረች የደርግ ገራፊ ሳትሆን አትቀርም። ደግነቱ አራተኛ ክፍል ስገባ ተገላገልኳት።
ከዚያ በኋላ የነበሩት የትምህርት ዓመታት ሰላም ነበሩ። ኳስ መጫወት፣ መማር፣ መጫወት ነው። ዩኒት ሊደሩም ቢሆን እኛን እስከ መቅጣት የሚያደርስ ነገር አልገጠመውም። ስድስተኛ ክፍልን ስናልፍ ነው የሦስተኛ ክፍሏን አስተማሪ ራእይ የሚያስፈጽሙ ሰዎች የመጡብን። በተለይ ዩኒት ሊደሩ አይረሳኝም።
በልጅነት አዕምሮዬ ከርዝመቱ የተነሣ ደመና እንዳይገጨው ዝቅ ብሎ የሚሄድ ሰው ይመስለኝ ነበር። ለካስ ቁመቱ ሳይሆን ዱላው ነው እንደዚያ እንዳስበው ያደረገኝ። አንድ ቀን፣ አዲስ አበባ ታክሲ ስጠብቅ …. አጭር ሰውዬ አጠገቤ ቆሟል። ድንገት ዞር ስል የማውቀው ፊት። ያ አንድ ብሎክ ሙሉ በጉልበታችን በእንብርክክ የሚያስኬደን ዩኒት ሊደር። ያለ ማጋነን መሐል አናቱን ቁልቁል አየዋለሁ። ለካስ አጭር ኖሯል። ጭካኔው ግን እንደ መናገሻ ተራራ እንድናገዝፈው አድርጎናል ማለት ነው። “የሚያድግ ልጅ አይጥላህ” አለ ያገሬ ሰው።
አንድ ትዝታ ልንገራችሁ። የክፍለ ጊዜው መምህር በቀረበት በአንዱ ቀን ክፍሉን በጩኸት እያናወጥነው ነው። ዩኒት ሊደሩ እንደድመት የእግሩ ዳና ሳይሰማ ሹክክ ብሎ ሲገባ እኛ አገሩን አንድደነዋል። ምንም አላለም። ሁል ጊዜ የማይለየውን የሜታ ገበሬዎች የሚይዙት ዓይነት ዱላ እንደያዘ ከክፍል እንድንወጣ አዘዘን። ወጥተን ሲሚንቶው ላይ ተሰለፍን። አንበረከከን። ከዚያ በኋላ ያንን ሕንጻ በእንብርክካችን ያስዞረን ገባ። በእርግጠኝነት አሁን ብንሄድ የልብሳችን ቅዳጅ ወይም ያኔ የተፋቀች ቆዳችን ዘር እዚያ ድንጋይ ላይ በአርኪዎሎጂም ቢሆን ብትፈለግ ትገኛለች። በእውነቱ “ቶርች” ነበረ ማለት ይቻላል።  
የክፍል አለቃስ ቢሆን መቼ ይቻላል? የክፍል አለቃ እንደ አጨካከኑ ሲያድግ ክፉ የቀበሌ ሊቀመንበር የመሆን ተስፋው ከፍ ያለ ነው። በዚያች አቅሙ ጉቦ ይለምዳል። ስምህን በአቦ ሰጡኝ ጽፎ እንዳያስገርፍህ ለራስህ የማትበላትን ደስታ ከረሜላ ለአለቃ መገበር አለብህ። በተለይ ሴቶቹ ልጆች ፍርሃታቸው። ለራሳችን ጠጠር ከረሜላ እየበላን ለአለቃ ደስታ ከረሜላችንን እንገብራለን። ሙስና በተግባር ማለት ናት። አሁንም እኮ ያው ነው። ካደግን በኋላ። ሰዎቹ ደስታችንን እየነጠቁ በጠጠር ቀርተን የለም እንዴ?
የክፍል ስም ጠሪው መምህር በቀን አንድ ጊዜ ስም ይጠራል። ከዚያም በአምባሳደሩ በአለቃው በኩል ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ የረበሹ ልጆችን የመግረፍ መብቱና ሥልጣኑ የሱ ነው።
እገሌ እገሌ …. አቤት፣
እገሌ እገሌ .….. አቤት፤
ከዚያ አንድ ልጅ ስሙ ተጠራ። ተማሪዎቹ የሚያውቁት ስም አልሆነም። አንድ ላይ ሳቁ። መምህሩ ቀና ሲል ጸጥ ይላል ክፍሉ። አጠገቡ የተቀመጠው ተማሪ “ይኼንን ስም ብለህ አቤት ከምትል ዝም ብትልና ቀሪ ብትባል አይሻልህም?” ከዚያ …. ሌላ የታፈነ ሳቅ። በዚያች ዕድሜያችን ሌላውን ሰው ማሳቀቅና መርጠን መናቅ በደንብ ተክነናል። ከየት ነው ያመጣነው ግን?
ስም ተጠርቶ ሲያልቅ የረበሹ ልጆችን ስም ይቀበልና በየስማችን እየጠራ ያስወጣናል። “ዘርጋ” ይላል ኮስተር ባለ ድምጽ። አንድ ጊዜ የግራህን አንድ ጊዜ የቀኝህን ትዘረጋለህ። መግረፊያው ከመዳፋችን ሲሳሳም የሚፈጥረው ድምጽ ሌላ ክፍል በደንብ ይሰማል? በምን አወቅሁ? ሌላ ጊዜ እዛኛው ክፍል ሲገረፉ እንሰማ የለ?
አዳሜ እንዲህ እያለ ነው ተምሮ ለቁምነገር በቃ የሚባለው፤ ከበቃ። እቤታችን ስንገባ ያለውን የወንድሞቻችንን እርግጫ፣ የእህቶቻችንን ኩርኩም ወይም እናቶቻችን የሚያጥኑንን በርበሬ እና የአባቶቻችን ከመሬት የሚደባልቅ ቁጣ ሳይጨምር በዚህ መልክ በግርፍ እና በትምህርት በልጽገን “ሳይማር ያስተማረንን ወገናችንን” ለማገልገል፤ እና እናት አገራችንን ለመርዳት የተማሩ ሰዎች ተብለን አደባባይ እንወጣለን። የተማሩ ሰዎች ከሚለው ጋር የተገረፉ ሰዎች የሚለው ለምን እንደሚረሳ እንጃ።
+++

(ለዚህች ጽሑፍ መጻፍ ምክንያት የሆነኝ ከአፍሪካ ት/ቤቶች በአንዱ፣ መምህር ተማሪዎቹን ሲገርፍ የሚያሳይ ቪዲዮ ነው። https://www.facebook.com/video.php?v=10154284736835051&fref=nf)

5 comments:

Solomon Z said...

Truly u Remind me my days in Elementary school... Specially the Unit Leader.....Thank you Ephrem

Anonymous said...

1974 ዓ.ም አራተኛ ክፍል እያለሁ እንድ እንግሊዘኛ አስተማሪ ነበረን በጣም ክፉ ነበር የሱ ፔሬድ ሲደርስ ሁሉ ነው በፍርሃት የሚርደው ገና ክፍል ሳይገባ ከደጅ መፅሐፋችሁን አውጡ ብሎ ይጮሃል ከዚያ ከመጀመሪያ ዴስክ አንብብ ተብሎ ይጀመራል አንድ ሁለት ደህና እንደተነበበ በመሐል አንዱ ማንበብ የማይችል መንተባተብ ይጀምራል ከዚያ ውጣ ተንበርከክ ይልና ማንበብ የማትችል ሁሉ ና ውጣ ይላል እኔም የእንግሊዝኛ ነገር አይሆንልኝም ነበርና ከክፍሉ ግማሽ በላይ የምንሆነው ወጥተን እንበረከካለን ከዚያም እስክሪፕቶ ጣታችን መሃል እየከተተ ባለ በሌለው ሀይሉ ሲጨመድደን እግሩ ስር ወድቀን እንፈራፈራለን በቅጣት ጊዜው ያልቃል የሚቀጥለው ጊዜም እንዲሁ ነው ማን ጠይቆ !!!

Anonymous said...

Yehimemen kusil Nekakahbign, bihonim gin endayidegem begna yibiqa lemalet yiredalina malefia new, enam muniterachin bedereq limich werwuro kulalite lay yeqededegn eske zare milikitu bedemb ale, enam himemen afign lemanim salinager zim neber yalkut binageris min limeta, bicha bizu new.....

Tsehaye Abrham said...

እስክሪፕቶ ጣታችን መሃል እየከተተ ባለ በሌለው ሀይሉ ሲጨመድደን እግሩ ስር ወድቀን እንፈራፈራለን በቅጣት ጊዜው ያልቃል የሚቀጥለው ጊዜም እንዲሁ ነው ማን ጠይቆ !!

Anonymous said...

የሚገርም ዘመን አሳልፈናል፡፡ ማንበርከክ፣ እጅ በእግር ስር አሾልኮ ጆሮ ማስያዝ እና በዘለንጋ ቂጥ መግረፍ፣ በእጆች መካከል ብዕር (አንዳንዴም እንጨት) በማስገባት ማሳመም፣ እግር ስር መግረፍ፣ መዳፍ እስክደማ መግረፍ፣ …የተለመዱ ነበሩ፡፡ አንድ አስተማሪያችን ደግሞ በጠራራ ፀሃይ እያንበረከከ ትኩር ብለው ፀሃይ እንዲመለከቱ ያደርጋል፡ ዓይን እንዲጠፋ፡፡ ብቻ አልፏል… ቢያለፋንም…

Blog Archive