Saturday, November 8, 2014

ጓደኛ ለማድረግ የማይመቹኝ የፌስቡክ ስሞች

ደግነቱ 5000 ሊሞላኝ ነው እንጂ ባይሞላኝም እንኳን የጓደኝነት ጥያቄያቸውን ለመቀበል ገና ስማቸውን ሳይ የሚከለክለኝ (የሚዘጋኝ አላልኩም) ሰዎች አሉ። ሰው ሰው የማይሸቱ ስሞች፣ ዐ.ነገር የሆኑ ስሞች እና ከሃይማኖት ጋር ተገናኝተው የሚያስፈራሩ የሚመስሉ ስሞች፣ ስማቸው ራሱ ጾታዊ ግንኙነትን የሚያበረታታ የሚመስሉ ስሞች ወዘተ ሲመጡ ያለምንም ጥርጥር አልቀበላቸውም። ከዚህ በታች ያሉት ምሳሌዎች ከዋነኞቹ ትንሽ ለወጥ ተደርገው የቀረቡ ናቸው። እነሆ፦
“ራእዩን እናስቀጥላለን”፤
“ወያኔ ይውደም”፤
“እንትና ስዊት”
“ምናምን ላቭ”
“እንትና የድንግል ማርያም ልጅ”
“እግዚአብሔር ያውቃል”
“አላህ ወኪል”
“የማርያም ልጅ”
“የማርያም ወዳጅ” ወዘተ ወዘተ …

ታዲያ ይህንን የመሰለ ስም ምን ሆነህ ነው አልፈልግም የምትለው የሚል ጠያቂ አይጠፋም። ምክንያቴን ላስረዳ። ፌስቡክ ኢሜይል አይደለም። መልእክቱን ነው እንጂ ከሌላው ምን ግድ አለኝ የሚባል አይደለም። “ሶሻል ሚዲያ” ከኢሜይል የሚለይበት ትልቁ ቁምነገሩ “ሶሻል” ስለሆነ ነው። ከሰዎች ጋር መተዋወቅ፣ በአካለ-ኢንተርኔት ወዳጅ  መሆን፣ መገናኘት መገባበዝ (ሻይ ቡና የለውም እንጂ) ስለሚቻልበት ከኢሜይል ይለያል። ሐሳብ ስትለዋወጥ ትከራከራለህ፣ ትግባባለህ ወይም ትጣላለህ ትተራረማለህ።
እንደዚህ ለማድረግ የማይመቹኝ ስሞች አሉ። ራሱን “የማርያም ልጅ” ወይም “የማርያም ወዳጅ” ብሎ ከመጣ ሰው ጋር መከራከር ይከብደኛል። “እግዚአብሔር ያውቃል” የሚል ስም ያለውን “አሜን” ከማለት ውጪ ቢያጠፋም ለመገሰጽ አይመቸኝም። ምናለበት ትንሽ ለወጥ ያለ ስም ቢፈልጉ? የክርስትና ስማቸውንም ቢሆን ይጠቀሙ። ከመንግሥት ጋር ለመጣላት አንጨነቅም እንጂ ከእግዜር የሚያጣላ ስም ከያዙት ጋር በሩቁ ይሻላል።
ብዙ ጊዜ እንደማስታውሰው ስማቸውን በትክክል ያልገለጹ ሰዎችን ጓደኛ ለማድረግ አልፈልግም ነበር። ይህንን መመሪያዬን ያበላሹ አንዳንድ ሰዎች አሉ። በሐሳቡ ሁሌም የሚያበሳጨኝ “Beyo Te ወይም በአሁን ስሙ Isho Birhan” እና ጽሑፎቹን አሳድጄ የማነባቸው ወዳጄን “Jr Dee/ ጁኒየር ዲ”ን በምሳሌነት ላንሳቸው።
ሌላው ስማቸው የሚከብደኝ ሰዎች ራሳቸውን “ስዊት” እና “ላቭ” የሚሉ ሰዎች ናቸው። ዝርዝሩ ይቅርብኝ። ቁምነገር ያላቸው ሰዎች አይመስሉኝም። በርግጥ ጭፍን ሐሳብ ይመስላል። የሚሰማኝ ግን እንደዚያ ነው።

ሌሎች ደግሞ አሉ። “ራስ” እንትና፣ “ልጅ” እንትና እያሉ ነገሥታት በሌሉበት ዘመን ራሳቸውን “የልጅነት” እና “የራስነት” ሥልጣን የሰጡትንም ቢሆን ስቆ ማለፍ እንጂ ምን ይባላል። “ልጅ” ማለት በዕድሜ የመጣ መስሏቸው ራሳቸውን ወጣት ለማድረግ በመሞከር ያሉ ሰዎች ግን አልመሰሉኝም። “ራስ” መቸም የተከበረ ታላቅ ሥልጣን ነበር። ልጅ ኢያሱን ራስ ዳርጌን፣ ራስ ጎበና ዳጬን ያስታውሷል።

5 comments:

Anonymous said...

leza new yaltekebelkegn

Anonymous said...

you are right

Anonymous said...

Agree

Anonymous said...

እስማማለሁ!

Asmeret Tesfa selassie said...

እስማማለሁ!!!!!!!!!!!!!!!!

Blog Archive