Sunday, November 2, 2014

“ዚአከ ለዚአየ”፤ የጉርሻ አመጣጥ ... The Origin of Gursha

(ከኤፍሬም እሸቴ/ Read in PDF)
Gursha by Alex Tefera
ከዕለታት በአንድ ቀን እግዚሐርን የማይፈራ ሰውን የማያፍር ንጉሥ በአገራችን ነገሰ አሉ። ያም ክፉ ንጉሥ ሕዝቡን ከዋለበት አላስውል፣ ካደረበት አላሳድር ብሎ ሰላም ነሣው። በሕዝቡ መከራና ሥቃይም እጅግ ይደሰት ነበር። እንደርሱ በሰው ለቅሶ ወደሚደሰቱ ሳዲስት የሮማ ሄሮድሶች እየተጻጻፈ አዳዲስ ነገር እየተማረ በክፋቱ ላይ ክፋት ጨመርን ልማድ አደረገ። ለሄሮድስ በጻፈው አንድ ደብዳቤው እንዲህ አለ፦
የተከበርክ ታላቁ ሄሬድስ ሆይ፤
ለጤናህ ከነሰፊው ግዛትህ እንደምን አለህ? እኔ ይኸው ከምድረ አዜብ እስከ ባሕር ማዶ፣ ተራራውንና ሜዳውን ቆላውንና ደጋውን እንዲሁም ወይና ደጋውን እንደ ገል ቀጥቅጬ እንደ ሰም አቅልጬ እየገዛኹት ነው። ሙቀት አስቸገረን ሲሉ ብርድ አገር፣ ብርዱ በረታብን ሲሉ ቆላ እያሰደድኩ እነሆ በደስታ እኖራለሁ። በዋዕይ አንድም በቅዛቃዜ አሳራቸውን አበላቸዋለሁ። እንደ አባቶቼ ዘመን ጦሬን እፈትንበት ዘንድ፣ ጋሻዬ ተሰቅሎ የትኋን ማዕከል እንዳይሆን ብዬ የጦር ያለህ ብል የሚገጥመኝ ባጣ ሕዝቡን ራሴው ገጥሜዋለሁ።

እነሆ አንተም ሰዎችን ከአንበሳ እያታገልክ በአደባባይ ቁጭ ብለህ እንደምትመለከት ከእናንተው አገር የመጣ ሮማዊ ነግሮኛል። ሕዝቡን ሁሉ ክትት አድርጎ የሚይዝ ትልቅ ቤት መሥራትህንም ነገረኝ። እንዴት አድርገህ ብትሠራው ነው መኳንንቱንም መሳፍንቱንም ከነ ኩታራው ሕዝብ አንዱ በአንዱ ላይ ሳይራኮት የሚያመስቀምጥ ቦታ ማደራጀት የቻልከው? ይኼን ብልሃት ለእኔም ብታስታውቀኝ ባለ ውለታህ ነኝ። ባይሆን ከሰው የምታታግለው አንበሳም ሆነ ነብር፤ አውራሪስም ሆነ ጎሽ፤ የምታጌጥበት ወርቅም ሆነ ብሩር እሰድልሃለሁ። ብቻ ብልሃቱን ንገረኝ። እኔም በበኩሌ የፈጠርኩትን አንድ የጨዋታ ብልሃት እነግርሃለሁ።
ጨዋታው የራበው ሰው ምግብ አቅርበህለት ነገር ግን እንዳይበላ የማድረግ ጨዋታ ነው። ይኸው ለረዥም ጊዜ ጨዋታውን የተጫወቱት አንዳቸውም አልተረፉም። ምግቡን እያዩት በረሃብ አልቀዋል። እንዲያውም የዚህ ጨዋታ አንዱ በቅርቡ አለና ምን እንደሚመስል እዚህ ያለው የአገርህ ሰው ተመልክቶ መጥቶ እንዴት እንደሆነ ይነግርሃል። እስከዚያው ሰላም ሁን።
ወሰን-ከወሰን-ያለውን-አማስን
ንጉሠ ነገሥት ዘምድረ አዜብ

ንጉሡ እንዳለውም በረሃብና በምግብ የሚያደርገውን ጨዋታ ለሮማው ሰው ለማሳየት ጓጉቶ ጠኔ የመታቸው አራት ሰዎች ወደ አደባባዩ አስከተተ። ሲያዩት የሚያስጎመጅ በወጥ የረሰረሰ ምግብ በአገልግል መካከላቸው አስቀመጠ። ረሃብተኞቹንም ተራርቀው እንዲቀመጡ አዘዘና ረዣዥም ማንኪያ ሰጥቶ እንዲበሉ አዘዛቸው።
ረሀብተኞቹ ምግቡን ሲመለከቱ፣ መዓዛው ከአፍንጫው ሲደርስ አንጀታቸው ተላወሰ። በሚንቀጠቀጥ እጃቸው ያንን ረዥም ታላቅ የብር ማንኪያ አንስተው ከፍርፍሩ እና ከፍትፍቱ ቢያነሱለትም ወደ አፋቸው ማድረስ ሳይቻላቸው ቀረ። ሁሉም እያነሳ አፉ ከማያደርሰው ምግድ አብዛኛው ማንኪያ ከማንኪያ እየተጋጨ መሬት ይወድቅ ያዘ። ንጉሡ በሁኔታው ተደስቶ አንጀቱ እስኪፈርስ ይስቅ ጀመር። ይህንን ጨዋታ በመፍጠሩ በራሱ እየተደሰተ ራሱን ከደመናት በላይ በአክናፈ-ሳዲዝም አስፈነጠረ። የሮማው ገዢ ሄሮድስ ታላቁ ሲሰማ በምድረ አዜብ ንጉሥ ብልሃት እንደሚደነቀ ሲያስብ ልቡ በኩራት ጭላሎ ተራራን ቁልቁል ያየው ጀመር።
በእጃቸው እንዳይበሉ ጠብደል የንጉሥ አጋፋሪዎች በማጅራታቸው ላይ የሚተነፍሱባቸው እነዚያ ረሃብተኞች የምግብ አምሮታቸው ከኅሊናቸው ጓዳ ብልሃት አላፈልቅ ብሎ ማንኪያቸውን ሲጥሉ ሲያነሱ ብዙ ባተቱ። አንዲትም ቅንጣት ምግብ ከማንም ረሃብተኛ አፍ ሳትደርስ ቀረች።
በዚያ መሐል ነገሩ ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን መሆኑን ያዩ አዛውንት ረሃብተኛ ከሌሎቹ እኩል መራኮቱ አንድ የመከራ ዕለት ለመቆየት ካልሆነ በስተቀር ከዚህ ጠኔ ተርፈው ሰው እንደማይሆኑ ሲረዱ ወጣቶቹን ቢያተርፉ ብለው ማንኪያቸውን አስቀምጠው ዘዴ ለመምታት ጀመሩ።
መራኮታቸውን ትተው፣ ማንኪያቸውን ማስቀመጣቸውን ያየው ንጉሥ እንዲሁም ታዳሚው ተመልካች ቀድሞ የሚወድቀው ማን እንደሆነ በመረዳት አውካኩ።  “ሽሜው ሊወድቅ ነው፤ ተስፋ ቆርጦ ተወው ይኼን የመሰለ ምግብ” እያሉ ተዘባበቱ።
ሽማግሌው አረጋዊ ዓይናቸውን ከድነው፣ የጆሯቸውን በር ለውጪው ጫጫታ ዘግተው መላ መላ መላ መላ መላ አሰቡ። “ዓይንህን ክደን፣ ከውጪ የሚመጣውን ጫጫታ ግታ፣ ወደ ውስጥህ አስብ፣ ያሁኗን ጉርሻና ምግብ ዘልለህ የነገውን አስብ … መፍትሔ ታገኛለህ” የሚል የጥንት አባቶቻቸው ምክር ትዝ አላቸው።
መልካም፤ ይህንን ምግብ መብላት እንችላለን። ነገር ግን ማንኪያው ረዥም ነው። ረሃብተኞች ስለሆንን በችኮላ ስንራኮት ምግቡን ከመድፋት ውጪ ማንኛችንም አልተጠቀምንም። ታዲያ ምን ይሻላል?” ብለው ጥያቄውን ደግመው ደግመው ሲጠይቁ፣ መፍትሔውን ከራሳቸው መራኮት አሻግረው ሲመለከቱ … መፍትሔው ብልጭ አለላቸው።
ከተቀመጡበት ዘልለው ተነሡ። ቦረቁ። ወጠምሻ አጋፋሪዎች አንገታቸውን ይዘው ሊደፍቋቸው ሲሉ ንጉሡ “ተዉት፤ እኮ የት ይደርሳል?” የሚል የጥቅሻ ምልክት አሳያቸው። አረጋዊው በደስታ ዘልለው ሲያበቁ በታላቅ ድምጽ “ዚአከ ለዚአየ፤ ዚአየ ለዚአከ፤ የአንተን ለእኔ፣ የእኔን ለአንተ” እያሉ ጮኸው ተናገሩ።
ማንኪያቸውን አንስተው በረዥሙ ከፍትፍቱ ከጎመዱለት በኋላ በአሻጋሪያቸው ላለው ሰው ዘርግተው አጎረሱት። እርሱም እንደዚያም ከፍትፍቱ ጠቅሶ አሻግሮ በማንኪያው አጎረሳቸው። ከዚያ በኋላማ ማን ይቻላቸው። መራኮቱን ተዉት። ማንኪያ ለማንኪያ ማንጓጓት ቀረ። እርስበርሳቸው በጥላቻ መገፋፋታቸውን አቆሙ። የአንዱ መኖር ለሌላኛው መጥገብ ዋስትና መሆኑን ተረዱ። እነርሱ እንዲጠግቡ ሌላውም መጉረስ እንዳለበት ተረዳቸው። እነርሱ ተርበው ሌላው እንደማይጠግበው ሁሉ እነርሱ ጠግበው ከማዷቸው ያለው ሰው ሊራብ እንደማይችል ሲረዱ ሌላውን ለማጉረስ ይጣደፉ ያዙ። “በሞቴ በሞቴ በሳንቃው ደረቴ እያሉ በረሃብ አጥንቱ ወጥቶ ሳንቃ የመሰለ ደረታቸውን በእጃቸው ይመቱ ያዙ።
ረሀብተኞቹ አንዱ ለአንዱ እያጎረሱ ረሃባቸውን አስታገሱ። ንጉሡ የሚሆነውን ነገር እያየ ማመን አቃተው። ጠኔ የመታቸው ሰዎች ዓይኑ እያየ ከምግቡ ሲረሰርሱ ተመለከተ። አንድም የሮማውን ንጉሥ ለማስደነቅ ያሰበው ሐሳብ መክሸፉ እያናደደው፣ አንድም የዚያ ዕንቆቅልሽ ጨዋታ መልስ ማግኘቱ እያስደነቀው ከዙፋኑ ላይ ተስፈንጥ ተነሥቶ ወጣ።
ሕዝቡ ደግሞ እያጨበጨበ የረሃብተኞቹን አበላል አዳነቀ። ሁሉም ወደየቤቱ ሲገባ ቀን ያየውን ለመድገም አሰበ። ረዥም የብር ማንኪያ ቢያጣ አንዱ ለአንዱ በእጁ ማብላት ጀመረ።
እነሆ ጉርሻ በዚያው ተጀመረ። ዚአከ ለዚአየ፣ ዚአየ ለዚአከ … ጉርሻ……..!!!!!
+++

(ማስታወሻ፦ The Origin of Gursha (ይህንን ልቦለድ ሐቲት እንደታሪካዊ ማስረጃ የሚጠቅሰው ቢገኝ ከደሙ ንፁህ ነኝ።)

2 comments:

Teddy Ayele said...

Awesome...as usual....

ብቻውን ለመብላት የሞከረ ብቻውን ይሞታል...ዓይነት ነገር

አንድም የአበው ምክር የሕይወት መሰረት ነው፤

አንድም እኚያ ብልህ የሆኑ አባት የመጣላቸውን እንዳገኙ አለመመገባቸው ማሰላሰላቸው የጾም ምሳሌ ነው!ጾም ወደ ፍቅር ያደርሳል...ፍቅርም ወደ ጉርሻ!! ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጽነ እንዲል

አንድም ጉርሻ ፍቅር ነው...አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ይባባሉበታልና፤

አንድም አምባገነኖችና ፍርድ አጉዳዮችን ቢተባበሩባቸው
የመከራ ቀንበር በማናችንም ላይ ሊጭኑ አይቻላቸውም...ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ነውና...፤

Daniel Hailemeskel said...

አባባ ቃለ ሕይወት ያሰማልነኝ፡፡

Blog Archive