Friday, December 5, 2014

“ፌስቡክ እና ስደት፦ የሰው ልክ አያውቅም … ቢሆንም"

(ከኤፍሬም እሸቴ/ Read in PDF)
እንደ ስደት ክፉ ነገር የለም። የታወቀ ነገር ነው። ቢሆንም ለአጽንዖተ ነገር እንድገመው። የተሰደደ ሰው ማንነቱ ምንነቱ በቅጡ አይታወቅም። ስደት ከሰው ያሳንሳል። አንገት ያስደፋል። ከስደትም ስደት አለው በርግጥ። በአውሮፕላን ከአገራቸው ወጥተው ሕግ ያለበት አገር (ሰው በሌለበት አገር) የሚኖሩ አሉ። ሰው የሌለበት ማለቴ ወዳጅ ዘመድ ለማለት ነው። “ከዘመድ ባዳ፣ ከአገር ምድረ በዳ” እንዲል። ደግሞ በእግራቸው አገር ቆርጠው፣ ባሕር ተሻግረው፤ በምድር ከሚሽከረከረው፣ በባሕር ከሚንከላወሰው አውሬ ጋር ታግለው፤ ከሰው አውሬዎችም ጋር ታግለው እያለፉ ስደት የሚገቡም አሉ። በባሌም ይውጡ በቦሌ፣ ስደት ያው ስደት ነው። የሰው ልክ አያውቅም።

የኒውዮርክን ታክሲዎች ከሚያሽከረክሩት ሺህ ምንተ ሺህ የውጪ አገር ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በየአገሮቻቸው አንቱ የተባለ ሙያ የነበራቸው ሰዎች ናቸው። ደታክሲ መንዳት (አውሮፕላንም ሆነ ታንክ እንደመንዳት ሁሉ) የብዙዎች ሙያ ነው። በገቢ ደረጃም ቢሆን ቢሮ ውለው ከሚመጡ ከብዙዎች የሚበልጥ ገቢ የሚገኝበት።) ኢንጂነሮች፤ ዶክተሮች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ በሥልጣን ደረጃም ካየናቸው ደግሞ ሚኒስትሮች፣ የጦር መሪዎች፣ የተከበሩ የአገር ሽማግሌዎች ወዘተ ወዘተ ታክሲ ሲያሽከረክሩ ይውላሉ። ታክሲው ውስጥ የሚገባው የሚወጣው ሰው ማንነታቸውን ምንነታቸውን አያውቅም። እንደማንኛው ተርታ ሰው ናቸው ለእሱ። ስደት ነዋ።
ስደት የሰው ልክ አያውቅም ስንል የአገሩ ሰው ስደተኛውን ስለማያውቀው ብቻ አይደለም። የተሰዳጁ ሰው የአገር ሰዎችም ያገራቸውን ሰው ልክ በቅጡ አይገነዘቡትም። ስደተኛ ሁሉ በአገሩ የነበረውን ማንነት እና ምንነት ያላገናዘበ አገር ስለሚሰደድ የደረጃ መፋለስ ይገጥማል። ትልቅ ባለሙያ የነበረው ሰው ገና 12ኛ ክፍል ካላጠናቀቀ የአገሩ ሰው ጋር ታክሲ መንዳት ላይ ሊገናኙ ይችላሉ። ሁለቱም ተመሳሳይ በአፓርትመንት ይኖራሉ። ሁለቱም እኩል ታክስ ይከፍላሉ። አገር ቤት የነበረው የክብር እና የመከባበር ድንበሩ በታክሲ ገቢ ይለካና ትከሻ ማሳየት ይመጣል። ስደት የሰው ልክ አያውቅም።
ሶሻል ሚዲያም ስደት ማለት ነው። የሰው ልክ አያውቅም። ማንበብና መጻፍ የሚችል ማንኛውም ሰው ከፍቶ የሚገባበት፣ ምንም ዓይነት የትምህርት ማስረጃ የማይጠየቅበት፣ ሰው ማንነቱን እንዲገልጽ የማይገደድበት፣ ሰው ለሚናገረው ነገር ምንም ዓይነት ተግሳጽ የማያገኝበት “ልዩ አገር” ስለሆነ በርግጥም “የሰው ልክ አያውቅም። ፌስቡክ የሰው ልክ አያውቅም።
ይሁን እንጂ ብለን እንቀጥል። ይሁን እንጂ በመላው ዓለም እንደ ጨው ዘር የተበተነ አዳሜ፣ የተበተነች ሔዋኔ ዘረ-ኢትዮጵያ የስደትን ቀንበር ሰብረው፣ በቀለማቸው እና በመጤነታቸው የሚመጣባቸውን ጫና አሸንፈው አንቱ የተባሉ ሰዎች ሆነዋል። የተከበረ ሙያ አበጅተው፣ የተከበረ ቤተሰብ መሥርተው ለየሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጠቃሚ ዜጎች ሆነው፣ በሰው አገር የወለዷቸውንም ልጆቹ የየአገሮቹ ምርጥ ዜጎች አድርገው ይኖራሉ። ኢትዮጵያዊ በሰው አገር ወድቆ አይወድቅም። ጥርሱን ነክሶ ሰው ይሆናል።
ፌስቡክም ከነኮተቱ፣ የሰው ልክ የማያውቁ ስም የለሽ ተሳዳቢዎችን የተሸከመ መሆኑ ቢታወቅም፣ ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮች የሚተኮሱበት ትልቅ የማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ አውድ ነው። አንድ ሰው ፌስቡካዊ በመሆኑ ከሚጎዳው ይልቅ፣ ሁነኛ ሰው ከሆነ፣ የሚጠቅመውና የሚጠቀመው ይበልጣል። “እንትና ስዊት” ወይም “እንትና አንበሳው” ብለው ስዊትነታቸውን ለማስቀመስ ወይም አንበሳነታቸውን የሰው በጎ ስም ሰብረው ለማስመስከር የሚመጡት ከሚመስሉት በስተቀር፣ በዚህ መገናኛ ዝግ በሆነበት ሁናቴ ፌስቡክ ባለውለታው የማይሆንለት ሰው አይገኝም።
ይሁን እንጂ (ሌላ ይሁን እንጂ) ፌስቡክ የሚሰጠውን ጥቅም ለማግኘት እና ክብረ-ነክ በሆኑ ሰዎች የሚመጣ ጉዳትን ለመቀነስ ጥንቃቄዎች ማድረግ  ይገባል።
1ኛ ጥንቃቄ፦ ጓደኛ የምናደርጋቸውን ሰዎች ማወቅ፣ ማንታቸውን ማወቅ፣ ማንነታቸው የሚታወቁ ሰዎች ሌሎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሁለት ጊዜ ማሰብ ይጠይቃቸዋል። ስለዚህ በማይታወቅ ስም፣ በሐሰት ስም ወይም ማንነታቸውን ደብቀው ከሚመጡ ሰዎች ራስን መጠበቅ።
2ኛ ጥንቃቄ፦ የፌስቡክ ግድግዳችንን ማንም እንደፈለገ የሚጽፍበት፣ የፈቀደውን የሚለጥፍበት እንዳይሆን መጠበቅ። እንዴት? Settings ውስጥ በመግባት “Timeline and Tagging Settings” ደረጃ በደረጃ ያለውን ነገር በማንበብ አጥሩን ማጠባበቅ ይቻላል።
3ኛ ጥንቃቄ፦ የፌስቡክ አባል የምንሆንበትን ምክንያት ጠንቅቆ ማወቅ እና በዚያው መሠረት መንቀሳቀስ። በግሌ የፌስቡክ አባል የሆንኩት ትልቅ የመረጃ መለዋወጫ አውድ በመሆኑ፣ የግል “ሆቢዎቼን” (ለምሳሌ ፎቶ ማንሣት) በፈቀድኩት መጠን ለመፈጸም ዕድል ስለሚሰጠኝ፤ በሥነ ጽሑፍ ሙያዬ የአቅሜን በጎ ነገር ለማበርከት ወዘተ ነው። በወዳጅነት የማውቃቸው ሰዎች በነዚሁ ጉዳዮች ዙሪያ ትምህርት የሚሰጡኝ ሰዎች እንዲሆኑ እጠነቀቃለሁ። እናንተስ?
4ኛ ጥንቃቄ፦ እጅግ ግላዊ በሆኑ ጉዳዮች፣ ስብዕናችንን ሊያጎድፉ በሚችሉ ጉዳዮች አለመጠመድ። ከዚህ ቀደም ተከስተው እንደሰማነው ከሆነ ጾታዊ በሆኑ ጉዳዮች በሚደረጉ ያልተገቡ ግንኙነቶች የወደዱ መስለው በሚያገኙት ምሥጢር የብዙ እህቶቻችንን ሕይወት የሚያበላሹ ሰዎች መኖራቸውን ተረድተናል። በተለይ እህቶች ከእንዲህ ዓይነቱ ነገር ራሳችሁን ለመጠበቅ አትቦዝኑ።

“ፌስቡክ” እና “ስደት”፦ የሰው ልክ አያውቅም … ቢሆንም ስደቱም አልቀረንም፤ ፌስቡኩንም አልተውንም። ታዲያ እንዴት እንዴት እናርጋቸው ይሆን? እስቲ ይህችን አጭር ጸሑፍ አንብቡና አስተያየታችሁን ስጡ። እነሆ ወደ "አደባባይ" ግቡ።

5 comments:

Anonymous said...

senay wuitu ehune.

Anonymous said...

I LIKE THIS. Thanks a lot

Andy said...

thank you very very muchh..

ZELALEM KEBEDE said...

EWNET NEW EFRI ENE ERASU FACEBOOKEN ZEGICHEWALEW GIN KEAMET BEWALA SASIBEW YEMAGEGNEW TIKIM YIBELT NEBER ENA YANIN MULU FILEN ATIFICHEW NEBER AHUN GIN ADIS KEFICHE YEMAWKACHEWIN BICHA NEW ADD YEMADERGACHEW ENA EWNETIHIN NEW SIDETINA FACEBOOK YESEW LIK AYAWKUM.

Anonymous said...

ጦማሪው ወንድሜ አሁን አሁን ሁሉንም ሠው ፊስ ቡክ አበላሸው ጥሩውንም መጥፎውንም በቀላሉ ማግኘት መቻሉ ይመስለኛል ፡፡ ግን ግን መለኪያዎችና ሚዛኖቻችንን አስተካክለን ከተነሳን ማወቂያው መንገዱ ሠው ገና አንደበቱን ሲከፍት ነው ስለዚህ የፌስ ቡክ ወዳጅነት የሚመስለኝ ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥñልኝ የንደሚለው ይመስለኛል