Friday, April 24, 2015

ሌላ ሐዘንና ሌላ ለቅሶ ሁሉ ሐዘንም ለቅሶም አልመስል አለ!!!!

ሌላ ሐዘንና ሌላ ለቅሶ ሁሉ ሐዘንም ለቅሶም አልመስል አለ። ሌላ ሳቅ፣ ሌላ ጨዋታም አልጥም አለ። ሌላ ንግግር ሌላ ውይይትም ከልብ ጠብ አልል አለ። ከመቅረት መዘግየት ይሻላልና ዘግይተንም ማስታወስ ከቻልን አንድ ነገር ነው። እነሆ።
1. ታላቁ አባት ንቡረ ዕድ ክፍለ ዮሐንስ መኮንን በዚህ ሳምንት አርፈው (ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም.) ምንም እንዳልሆነ ሁሉ በጥቂት ዘገባ ብቻ አለፍነው። ቤተ ክርስቲያንን በብዙ ጥብዓት ያገለገሉ የወንጌል ገበሬ የቅኔ አባት ነበሩ።ማኅበረ ቅዱሳን ስለ ቅኔ ያዘጋጀውን ቆየት ያለ ቪዲዮ (ከዩቲዩብም ከሌላም) ፈልጋችሁ ብታገኙና ብትመለከቱት ምን ዓይነት ሰው እንደነበሩ ብልጭ ያደርግላችኋል። ወይም ከታች ከኅዳጉ ላይ አስቀምጬላችኋለሁ።
2. ይህ ሳምንት አርመናውያን ክርስቲያኖች በኦቶማን ቱርኮች የጅምላ ጭፍጨፋ የተደረገባቸው 100ኛ ዓመት የሚታሰብበት ነው። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኦርቶዶክሳውያን አርመኖች ልክ እንደዛሬው እንደ አይሲስ ባለ ጭካኔ የሰለሙትን አስልሞ፣ የቀሩትን ገድሎ፣ የቀሩትን ከአገራቸው አፈናቅሎ አባሮ ግዛታቸውን የወረሰበት 100ኛ ዓመት ነው። አይሁዶች በናዚ ጀርመኖች ከመጨፍጨፋቸው ቀድሞ የተፈጸመው ትልቁ ጭፍጨፋ ይህ ነው። አሜሪካና አንዳንድ አገሮች (ቱርኮችን ላለማሳዘን) ዛሬም "ጄኖሳይድ ነው" ለማለት አፍረው ተቀምጠዋል።

Wednesday, April 22, 2015

ከሰማዕታቱ ስንቶቹ ታወቁ ስንቶቹ ቀሩ?

ኢትዮጵያውያን ሰማዕታተ ሊቢያ በቁጥር 30 ቢሆኑም ገና ሁሉንም ለይተን አላወቅናቸውም። ለመሆኑስ ይህንን ሥራ በየግላችን ለመሥራት መሞከራችን እንደተጠበቀ ሆኖ የነዚህን ዜጎች ማንነት አጣርቶ ለቤተሰቦቻቸው የማሳወቁ ኃላፊነት የማን ነው?
1ኛ. በጎ ኅሊና ያለን ሰዎች በሙሉ እያንዳንዳችን የወገኖቻችንን ማንነት በመለየቱ በኩል ኃላፊነት አለብን፤
2. ሰማዕት የሆኑት በስደተኝነታቸው ወይም በቆዳ ቀለማቸው ወይም በዜግነታቸው ሳይሆን በሃይማኖታቸው ምክንያት እንደመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት አለባት፤

የሰማዕትነትን ጽዋ ከጠጡት ክርስቲያኖች መካከል አንዱ ሙስሊም፣ ስሙም ጀማል ራህማን ነው?

ሶማሌላንድ "somalilandpress" ፕሬስ የተባለ አንድ ድረ ገጽ በሊቢያ የሰማዕትነትን ጽዋ ከጠጡት ክርስቲያኖች መካከል አንዱ ሙስሊም መሆኑን፣ ስሙም ጀማል ራህማን እንደሚባል ከአል ሸባብ ምንጭ አገኘኹ ብሎ ዘግቧል። ክርስቲያን ጓደኞቹን ከአይሲስ ለማስጣል በፈቃደኝነት ተይዞ እንደተገደለ የጠቀሰው ድረ ገጹ "ክርስትናን ጠቀብሎ" እንደነበርም ጠቁሟል። "በሞኝነት ጓደኞቹን አስጥላለሁ ብሎ ራሱም ተገደለ" ያለው ድረ ገጹ ያስነበበውን ጽሑፍ ከዚህ በታች ተመልከቱት። ወንድማዊነት፣ ጓደኝነት፣ ኢትዮጵያዊነት ያስተሳሰራቸው ወገኖቻችን እንደተዋደዱ ወደ መቃብር ሊወርዱ እንደሚችሉ ባንጠራጠርም የዚህን ዜና ምንነት የሚያረጋግጡ ሌሎች ምንጮች ቢገኙ ግሩም ነበር። ይህ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ማን ነው? እንዴት ይህንን ያህል ታላቅ ውሳኔ ሊወስን ቻለ? ብዙ ጥያቄዎች ይነሣሉ።
http://www.somalilandpress.com/ethiopia-muslim-martyr-among-those-killed-by-isis/#.VTdV2APm4qE.twitter

http://goo.gl/Ghm5dU

Monday, April 20, 2015

“የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን [ምርጥ] ዘር ነው” (ጠርጠሉስ)

ጠርጠሉስ የተባለውና በ2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (160 AD - 220 AD) የነበረው ታላቅ ፀሐፊና የክርስትና ጠበቃ ስለ ሰማዕታት ደም በተናገረበት ሥፍራ ያስቀመጠው ነው። ተርቱሊያን/ Tertullian ወይም በእኛ አጠራር ጠርጠሉስ የሚባለው ሊቅ ከመጀመሪያዎቹ የክርስትና አባቶች ጋር የሚቆጠር እንዲያውም የላቲኖች (በላቲን የምትናገረው፣ የምትጽፈው) ቤተ ክርስቲያን ወይም የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን አባት ተብሎ መጠራት እንዳለበት ብዙዎች የሚስማሙበት ሊቅ ነበር። በእኛ በኦርቶዶክሳውያንም ሆነ በካቶሊኮቹ ዘንድ ብዙም ስሙ ሲጠቀስ የማይሰማው ከጻፋቸው ጽሑፎች መካከል ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት የወጡ ስላሉበት ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ሊቅ በዚህ ሥፍራ መጥቀስ የፈለግኹት አገሩና ምንጩ የሰሜን አፍሪካ (የዛሬዋ ቱኒዚያ) አካል በሆነችው በካርቴጅ የተገኘ በመሆኑ ጭምር ነው።
እናም ይህ አፍሪካዊ ሊቅ እንዲህ አለ፦ “ …. የበለጠ በገደላችሁን መጠን የበለጠ እንኖራለን (አለን)። የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን [ምርጥ] ዘር ነው። … ጭካኔያችሁ የሚያሳየው እኛን ከምትከሱበት ወንጀል ነጻ መሆናችንን ነው። … እናም ዓላማችሁን ከንቱ ታደርጋላችሁ። ምክንያቱም ስንገደል/ ስንሞት የሚመለከቱ ሰዎች ለምን እንደምንገደል ይገረማሉ። እንደ ወንጀለኛ እና እንደ ተናቀ ሰው ሳይሆን እናንተ እንደምታከብሯቸው ሰዎች በክብር እንሞታለንና። [ስንገደል/ ስንሞት የሚመለከቱ ሰዎች] እውነቱን ሲረዱ ደግሞ እኛን ይመስሉናል/ ከእኛ ጋር አንድ ይሆናሉ (ይቀላቀሉናል)።”

አሰቃቂ ፎቶዎችን መጠቀም ተገቢ አይደለም

ሃያ ስምንቱ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታተ ሊቢያ (የሊቢያ ሰማዕታት) ላይ የተፈጸመው ድርጊት በቪዲዮ ተቀርጾ ከተለቀቀ በኋላ ብዙ ኢትዮጵያውያን ፎቶዎቻቸውን በመጠቀም ላይ ነን። አንዳንዶቻችን ግን ለማየት እጅግ በጣም የሚዘገንን ፎቶዎችን ለጥፈናል።
በቤተ ክርስቲያናችንም እንደሚደረገው እና በቅርቡም ግብጻውያን (በፍጥነት) አድርገውት እንደተመለከትነው የሰማዕታቱን በደም የተነከረ ሰውነት ከማሳየት ብንታቀብ ጥሩ ነው። ለዚህም ሲባል ተስማሚ የሆነ ሥዕል (Icon) በማዘጋጀት ያንን መጠቀም ይገባናል። ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ የሥዕል ሙያ ያላችሁ ወገኖች ለዚሁ ታሪክ ተስማሚ የሆነ ሥዕል (በየሰማዕታቱ ታሪክ ላይ የሚታየውን አብነት በማድረግ) ታዘጋጁ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ።
ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች፣ ሥዕሎቹን ሊመለከቱ ስለሚችሉ ሕጻናት፣ እርጉዞች እና ሌሎች ወገኖች ሲባል እንዲሁም የሃይማኖታችንን ትውፊት ተመርኩዘን ሥዕል አዘጋጅተን በመጠቀሙ እንተካው።
የሰማዕታቱ ረድዔት አይለየን፣ አሜን 


ማሳሰቢያ፦ ለአብነት እንዲሆን ግብጻውያኑ ያዘጋጁትን ሥዕል ተመልከቱ።

Sunday, April 19, 2015

ኢትዮጵያዊ መሆኑን ጠላቶቹ አውቀዋል የራሱ ወገን ግን አላወቀውም

ኢትዮጵያዊ መሆኑን ጠላቶቹ አውቀዋል የራሱ ወገን ግን አላወቀውም። የአሜሪካ መንግሥት አውቆ መግለጫ አውጥቶለታል፣ የራሱ ወገን ግን አላወቀውም። ሚዲያዎች በሙሉ አውቀውት በስሙ ጠርተውታል፤ የራሱ ወገን ግን አላወቀውም። የሊቢያ ምድር እንኳን 40 ቀኑ ተጠምቆ የሥላሴ ልጅነትን ባገኘው፣ የክርስቶስን ሥጋ በበላው፣ ክቡር ደሙንም በጠጣው በዚህ ኢትዮጵያዊ ደም ታጥባ "ፋሲካን ስታደርግ" ኢትዮጵያዊ መሆኑን አውቃለች፣ የራሱ ወገን የራሱ መንግሥት ግን አላወቀውም።

ለሰማዕታቱ አታልቅሱ (ሰማዕታተ ሊቢያ)

“ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።” 
(2ኛ ተሰሎንቄ 1፥ 6-7)
አይሲስ የተባለ ነፍሰ ገዳይ ድርጅት በስደት የሚገኙ 28 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን መግደሉን በፊልም አቀናብሮ አቅርቧል። የዓለም ሚዲያዎች በሙሉ ዛሬ እሑድ ይህንን ዜና ሲያሰራጩ ውለዋል። የተገደሉት ሰዎች “ኢትዮጵያውን መሆናቸውን ገና አላጣራኹም” ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዜና ማሰራጫው ኢቲቪ (ያሁኑ ኢብኮ) በደፈናው ግድያውን ማውገዙን ገልጿል። የሞትነውማ በርግጥም ኢትዮጵያውያን መሆናችንን በሊቢያ ዋና ከተማ የሚገኝ ወንድም (ዘርዓያዕቆብ) በፌስቡክ ገጹ አስነብቦናል። (ሙሉውን ስሙን ከመናገር መከልከሉን መርጫለሁ፤ እርሱማ በሰፊው ነው የጻፈው። እግዚአብሔር ይጠብቀው ባለበት)።

Thursday, April 16, 2015

የደርባን ደቡብ አፍሪካ ጥቃት ነገር

“የውጪ አገር ሰዎች ቅማሎች ናቸው። ወደመጡበት አገር መመለስ አለባቸው።” 
(የዙሉ ንጉሥ) ከዚህ ንግግር በኋላ ነው። ጥቃቶቹ የተጀመሩት። 

ታሪክ፦

በደቡብ አፍሪካዋ የደርባን ከተማ በስደተኛ አፍሪካውያን ላይ የተፈጸመው (እየተፈጸመ ያለው?) ጥቃት እጅግ አስደንጋጭ እና ዘግናኝ ነው። ብዙ አስተያየት ሰጪዎች፦
1. እንዴት አፍሪካውያን ሌሎች አፍሪካውያን ላይ እንዲህ ያለ የጅምላ ጥቃት ይፈጽማሉ?
2. ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካውያን ነጻነት ያንን ሁሉ ዋጋ ከፍላ እንዴት "ወርቅ ላበደረ ጠጠር" አደረጉ?
3. ነጮች ላይ እጃቸውን የማያነሱ ሰዎች ጥቁር ወገኖቻቸው ላይ ይህንን ግፍ እንዴት ይፈጽማሉ?
4. (እንደተለመደው) የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹ እንዲህ በአደባባይ በእሳት ሲጋዩ ለአፉ እንኳን ተቃውሞ አያሰማም ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ፌስቡክ-ለፌስቡክ ሲንከባለሉ ነበር።

Blog Archive